“ቀጣዩ ትውልድ ሀገሩን በደሙና በላቡ አስጠብቆ ማስቀጠል አለበት”ብርጋዴር ጀነራል ወርቁ ከበደ – የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊ

አዲስ አበባ ፡- ሀገር ሉዓላዊነቷ ተከብሮ የምትቀጥለው ጀግኖች በሚከፍሉት መስዋዕትነት በመሆኑ ቀጣዩ ትውልድ ሀገሩን በደሙና በላቡ አስጠብቆ ማስቀጠል አለበት ሲሉ የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊ ብርጋዴር ጀነራል ወርቁ ከበደ ገለጹ፡፡

የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊ ብርጋዴር ጀነራል ወርቁ ከበደ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ጳጉሜን ሁለት የመስዋዕትነት ቀን ሆኖ መከበሩ ለሀገር ሉዓላዊነትና ዘላቂ ሰላምን ለማስከበር ሲሉ የአካል ብሎም የሕይወት መስዋዕትነት የከፈሉ ጀግኖችን ለመዘከርና አሁን ያሉትንም የጸጥታ አካላት የበለጠ ለማትጋት ትልቅ እገዛ የሚያደርግ ነው፡፡

የመስዋዕትነትን ቀን ስናስብ ማንኛውም ሀገር እና ህዝብ ወዳድ የሆነ ዜጋ የሀገሩን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ለወገኑ እና ለሀገሩ ያለምንም ስስት እስከሕይወት መስዋዕትነት ድረስ ዋጋ የሚከፍሉትን የጸጥታ አካላት ለማሰብ መሆኑን ገልጸው፤ይህም ጊዜን፣ ጉልበትን፣ የማህበራዊ ኑሮን ትተው ለሀገር ቅድሚያ መስጠት፤ በዓላትን ሀገርን በመጠበቅ ግዳጅ ላይ ማሳለፍ፣ የአካል ጉዳትና የሕይወት መስዋትነትን መክፈል ጭምር የሚያካትት ነው ብለዋል፡፡ ይህንን ለመፈጸም እያንዳንዱ ዜጋ የሀገሩን ታሪክ ከማወቅ የሚጀምር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እንደ መከላለከያ ሠራዊት ዘንድሮ የመስዋእትነት ቀን እንዲከበር መደረጉ መስዋእትነት የከፈሉ የሠራዊት አባላትም ብሎም ሌሎችም የጸጥታ አካላት እንዲታሰቡ እና መላው ሠራዊት በህዝብ ዘንድ ያለውን ከበሬታ እንዲረዳ እና የበለጠ እንዲበረታታ እና እንዲነሳሳ ያደርጋል ነው ያሉት፡፡

ቀኑም በመከላከያ ደረጃ እና ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር የሚከበር መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

መስዋእትነት ከኢትዮጵያ ታሪክ ጋር የተቆራኘ መሆኑን አመልክተው፤ ይህም በተለያዩ ጊዜያት በተከፈለ መስዋእትነት ኢትዮጵያ እስከ ዛሬ ድረስ ጸንታ የቆየች ሀገር ናት፡፡ አሁንም ሰላቂ ሰላሟን ለማስጠበቅና ሉዓላዊነቷን አስከብሮ ለማስቀጠል መስዋእትነት እየከፈልን እናቆያታለን ሲሉ ብርጋዴር ጀነራል ወርቁ ተናግረዋል፡፡

ትውልዱ እስከዛሬ ነጻነቷን ጠብቃ የቆየች ብቸኛዋ ሀገር የተረከበው በአባቶቹ በተከፈለ መስዋእትነት መሆኑን ተረድቶ ይህንንም አደራ በመረከብ የሚያስፈልገውን መስዋእትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

ብርጋዴር ጀነራል ወርቁ በጸጥታው ሥራ ላይ የተሰማሩ ኢትዮጵያውያን በሙሉ የከፈሉት መስዋእትነት በህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ከበሬታ እና አድናቆት አግኝቶ ዛሬ የመስዋእትነት ቀን በመከበሩ እንኳን ደስ አላችሁ ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ማህሌት ብዙነህ

አዲስ ዘመን ጳጉሜን 2 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You