የአይሲቲ ኩባንያዎችንና ምርቶቻቸውን ያስተዋወቀው መድረክ

ኢትዮጵያ በዲጂታል ኢኮኖሚው ዘርፍ የጀመረችውን እንቅስቃሴ ይበልጥ ለማጎልብት የሚያግዙ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሁነቶችን እያስተናገደች ትገኛለች። እየተጠናቀቀ ባለው 2015 ዓመት 17ኛውን ዓለም አቀፍ የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባኤን ጨምሮ በርካታ ዓለም አቀፍ ሁነቶችን ማስተናገዷ ይታወሳል።

በዚህ ወር ዘጠነኛውን የሕንድ-አፍሪካ አይሲቲ ኤክስፖ አስተናግዳለች። ኤክስፖው ወጣቶች ቴክኖሎጂን እንዲማሩና የፈጠራ ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩ ልምድ የሚያገኙበት እንደሆነ እና በዘርፉ የተጀመሩ ሥራዎችን ለማሳደግ ወሳኝነት እንደሚኖረው በጉባኤው ዝግጅት ወቅት አስቀድሞ ተጠቁሟል። የዝግጅት ክፍላችን ያነጋገራቸው የኤክስፖው ተሳታፊዎችም ከኤክስፖው በርካታ ልምድ እንዳገኙበት ገልጸዋል።

በመድረኩ የተሳተፈው የግራንት ቶርንተን የሳይበር ደህንነትና የኢይሲቲ ዓለም አቀፍ አማካሪ ድርጅት (Grant Thronton Cyber security and IT Advi­sory) ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አስተዳዳሪ አቶ ፍጹም ሚሊዮን እንዳሉት፤ ድርጅቱ በዓለም በ140 ሀገራት ላይ እንደሚሰራና በኢትዮጵያም አገልግሎት መስጠት ከጀመረ አሥር ዓመታት አስቆጥሯል። የቢዝነስ ተቋማት ስጋቶችን መቀነስ የሚያስችል ሥራ ይሠራል። የኦዲት፣ የታክስና የማማከር አገልግሎት ይሰጣል። ከኮርፖሬት ፋይናንስ ጀምሮ ያሉ የቢዝነስ ተቋማት እና የውጭ ኢንቨስተሮች ወደ ሀገር ውስጥ ሲገቡ ፈቃድ ከማውጣት ጀምሮ ያሉ ሂደቶችን በሙሉ በተመለከተ የማማከር አገልግሎት ይሰጣል። እነዚህን ሥራዎች የሚያከናውነው ዓለም አቀፍ የአሠራር ሥርዓትን በተከተለ መልኩ ነው።

‹‹ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚታወቁ ተመሳሳይ ድርጅቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ቢሮ ያለው የኛ ድርጅት ነው›› የሚሉት አቶ ፍጹም፤ ሌሎቹ ግን መቀመጫቸውን ሌላ ሀገር አድርገው እንደሚሳተፉ ይናገራሉ። እነርሱ ለመንግሥትም ሆነ መንግሥታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች፣ የግል ድርጅቶች ሆነ ለዓለም አቀፍ ተቋማት አገልግሎት ይሰጣሉ ይላሉ።

አቶ ፍፁም እንደሚሉት፤ ኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ላይ ስትራቴጂ ከማውጣት ጀምሮ የተለያዩ ሶፍትዌሮችንና ሲስተሞችን በተመለከተ አገልግሎት ይሰጣል። ለምሳሌ አንድ የጨርቃጨርቅ ድርጅት አገልግሎቱን ፈልጎ ወደ ድርጅታቸው ቢመጣ ለዚህ ድርጅት አስፈላጊ የሆኑ የኢርቢሲ ሲስተም፣ አካውንቲንግ ሶፍትዌር፣ የሰው ኃይል ሶፍትዌር እና መሰል ሶፍትዌሮችን በተመለከተ የማማከር አገልግሎት በመስጠት ከጅምሩ አንስቶ ተግባራዊ እስኪሆን ድረስ ከተቋሙ ጋር በትብብር ይሰራል።

አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችንና አገልግሎቶችን ለማስተዋወቅ እንዲሚጠቅሙ አቶ ፍጹም ጠቅሰው፣ ድርጅቱ በኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ እና በሳይበር ደህንነት ላይ የሚሰጣቸውን አዳዲስ አገልግሎቶች በመያዝ በኤክስፖው ላይ ማስተዋወቁን አመልክተዋል።

‹‹እንደዚህ አይነት ሲስተሞች ተቀናጅተው ተግባራዊ እስከሚደረጉ ድረስ ብዙ ጊዜን ስለሚፈጁ ድርጅቶች ይህንን ሁሉ ሂደት ካለፉ በኋላ ሲስተሙ ተሰርቶ ካልተሳካላቸው ኪሳራ ውስጥ ይገባሉ።›› ያሉት አቶ ፍጹም፣ ድርጅቱ ይህ እንዳይሆን ሲል ለእነዚህ ድርጅቶች የሚሆነውን አገልግሎት አስቀድሞ ለይቶ እንደሚሰጥ ይገልጻል። በሳይበር ደህንነት በኩል እንዲሁም አንድ ድርጅት የሳይበር ጥቃት እንዳይደርስበት ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን በመለየት፣ ተቋሙ መጠቀም ያለበትን የሳይበር ደህንነት ማስጠበቂያ መንገድ ጭምሮ ለሠራተኞች ስልጠና እስከ መስጠት ድረስ ያሉ ሥራዎችን ያከናውናል ነው የሚሉት። ከዚህ በተጨማሪም ድርጅቱ የሳይበር ጥቃት ቢደርስበት እንደገና ራሱን ተከላክሎ መቀጠል የሚያስችለውን አገልግሎት እንደሚሰጥ ይናገራል።

አቶ ፍጽም እንዳሉት፤ አሁን ላይ ድርጅቱ በህንድ ሀገር እና በደቡብ አፍሪካ ከሚገኘው የድርጅቱ ቢሮዎች ጋር አብሮ እነዚህን አገልግሎቶች ይሰጣል። አገልግሎቱን የሚሰጠው ድርጅታቸውን ለማስፋፋት ለሚፈልጉ ወይም አዲስ ቢዝነስ ለመክፈት ለሚፈልጉ “የአዋጭነት ጥናትና የገበያ ዳሰሳ” ይሠራል።

‹‹በአይሲቲው ዘርፍ ላይ በተለይ የውጭ ዜጎችም ሆኑ ኢንቪስተሮች ወደዚህ ሲመጡ የመረጃ እጥረት አለ›› የሚሉት አቶ ፍጽም፤ መሰል ኤክስፖዎች በብዛት ስለማይዘጋጁና ዘርፉ ግልጽ የሆነ የመገናኛ መድረክ ስለሌለው መረጃ ማግኘት ላይ ችግር እንደሚፈጠር ይናገራሉ።

በኤክስፖው ላይ ህንዶች የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ይዘው መምጣታቸውን በመግለፅም፤ እነርሱን ተረክቦ የሚሸጥ ወይም አጋር ሆኖ የሚሰራላቸው መፈለጋቸውንም ጠቅሰው፣ ለዚህ ደግሞ የህንድ ሀገር ቴክኖሎጂዎችን በተመለከተ ግንዛቤ መፍጠር ቅድሚያ የሚጠይቅ ጉዳይ መሆኑን ይናገራሉ። ኤክስፖው ችግሩን ሊቀርፍ እንደሚችል ነው ያስታወቁት። ኤክስፖው ፈላጊንና ተፈላጊን የሚያገኛኝ መድረክ እንደሆነም ጠቅሰው፤ የእርሳቸው ድርጅትም በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ዘርፍ ላይ መሳተፍ ከሚፈልጉ ኢንቨስተሮች ጋር መገናኘቱን እንደ መልካም አጋጣሚ አንስተውታል። በተለይ ከቴክኖሎጂ ሽግግርና ትውውቅ አንፃር ኤክስፖው ፋይዳው ጉልህ መሆኑን መስክረዋል።

ሌላኛው የኤክስፖው ተሳታፊ የሞቲ ኢንጅነሪንግ ፒኤልሲ (MOTI Enginerhing Plc) ፕሮጀክት ዲቪዥን ማናጀር ወጣት መዝሙረ ዳዊት እንደምትለው፤ ሞቲ ኢንጂነሪንግ ባለፉት 17 ዓመታትና ከዚያ በላይ ከባንኮች፣ ከፋይናንስ ኢንስቲትዩቶች እና የተለያዩ የግልም ሆነ የመንግሥት ተቋማት ጋር ይሠራል። ድርጅቱ ኤቲኤሞችን የሚያስመጣ ሲሆን፤ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩቶችን መሠረተ ልማቶችንና የመረጃ ማዕከላትን ማስገንባት፣ ሰርቨሮች ማስመጣትን የመሳሰሉ ተግባራትም ያከናውናል።

እንደ መዝሙረ ገለጻ፤ ድርጅቱ በአብዛኛው በአጋርነት ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ይሰራል። በዚህ ሂደት ከጊዜ ወደ ጊዜ ቴክኖሎጂ እያደገ በመምጣቱ ምክንያት ራሳቸውን ከቴክኖሎጂው ጋር ለማራመድ የሚያስችሉ ሥራዎች ይተገብራሉ። ከእነርሱ ደንበኞች መካከል ባንኮች ዋነኞቹ መሆናቸውንና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እንደሚፈልጉ ትናገራለች። ተቋማቱ ከዘመኑ ጋር አብረው መሄድ እንዲችሉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች እንደሚያስፈልጓቸው ትጠቅሳለች። ዘመኑ የውድድር ስለሆነ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች በመጠቀምና በፍጥነት ተግባራዊ በማድረግ ለውድድር ራሳቸውን ዝግጁ እያደረጉ እንደሚገኙም ነው የተናገረችው።

ማናጀሯ እንደምትለው፤ ቴክኖሎጂ በየጊዜው እየተለዋወጠና እያደገ ይገኛል። ድርጅቱም አብሮ ከሚሰራቸው አጋሮች ጋር በመሆን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማስመጣት በየጊዜው ራሱን እየለወጠ አቅሙን እያሳደገ ይገኛል። እነርሱ በተሳተፉበት ኤክስፖ ላይ የተገኙት አፍሪካ ውስጥ ያሉ ቴክኖሎጂ አምራቾች ስለሆኑ ኢትዮጵያውያኑ ልምድ ለመለዋወጥና ራሳቸውን ለማስተዋወቅ እድል አግኝተዋል። ልምድ ከመጋራት ባለፈ ምርታቸውን በማስተዋወቅ እንደተሳተፉም ነው የገለጸችው።

በኤክስፖ ላይ ተሳታፊ ከሆኑት ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነው የአሸዋ ቴክኖሎጂ ሶልሽን ኦፕሪሽናል ማናጀር ወጣት ደጀኔ ኃይሉ በበኩሉ፤ ድርጅቱ በ11 ዘርፎች ላይ እንደሚሰራ ይናገራል። በኤክስፖው ላይ እንዲገኝ ያደረገው ዋንኛ ምክንያት በቅርቡ ስማርት ሶፍትዌር ሶልሽን ላይ አዳዲስ ምርቶች ይዞ ብቅ በማለቱ መሆኑን ነው የገለጸው።

ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ 98 በመቶ ያህሉ ኩባንያዎች የማንዋል አሠራር የሚከተሉና ሲስተም የሌላቸው ናቸው ሲል ጥናቶችን ዋቢ በማድረግ የገለጸው ወጣት ደጀኔ፣ ከኩባንያዎቹ 57 በመቶ የሚሆነውን ወጪያቸውን ለማንዋል አሠራር እንደሚያውሉ ይናገራል። በሲስተም ቢሰሩና የተሳለጠ አካሄድ ቢጠቀሙ ይህንን ወጪያቸውን ማስቀረት እንደሚችሉም ጠቁሞ፣ ድርጅቱ ይህንን ሲስተም ሊያሳልጥ የሚችል አገልግሎት ይዞ መምጣቱንም አስታውቋል።

እንደ ወጣት ደጄኔ ማብራሪያ፤ ድርጅቱ ኢንተርፕራይዝ ሪሶርስ ፕላኒንግ (ERP) የሚባል የኢንተርፕራይዞች ሀብት ማስተዳደሪያን የተመለከተ አገልግሎት ይሰጣል። ሲስተሙ አንድ ሰው ሲቀጠር ጀምሮ ያሉ ሂደቶችን /ደመወዝ ፣ፈቃድ እና የመሳሳሉት/ ሁሉ እንዲጨርስ ማድረግ የሚያስችል ነው። ከሠራተኛ ቅጥር አንስቶ ሁሉንም ነገሮች ለመቆጣጠር የሚያስችል ሲስተም መዘርጋትም ያስችላል። የፋይናንስ ሂደቱም ቢሆን እንዲሁ ከመጀመሪያው አንስቶ በሲስተም ለማስኬድ ያስችላል። “የደንበኛ ግንኙነት አስተዳደር (CRA)” የተሰኘው ሌላኛው አገልግሎት ደግሞ ደንበኛ ወደ ቢሮ ሲመጣ ጀምሮ ያገኛቸውን ሠራተኞች ፣የጊዜ ቆይታውን እና ጉዳዩ ምን ደረጃ ላይ እንዳለ ለመቆጣጠር የሚያስችል ነው።

ድርጅቱ ለተቋማት ዌብሳይቶችን የመስራት አገልግሎት እንደሚሰጥም ጠቅሶ፣ የተጠቀሱትን አገልግሎቶች ለሚፈልጉ ተቋማት ደግሞ የኪራይ አገልግሎት የሚሰጥበት ሁኔታ መኖሩንም አመልክቷል። የኪራይ አገልግሎት የሚፈልጉ ተቋማት የሚፈልጉት አይነት አገልግሎት ተሰርቶ ከተሰጣቸው በኋላ በየወሩ፣ በዓመት ወይም በሚፈልጉት አማራጭ ኪራይ የሚሰጣቸው ይሆናል ይላል። ብዙ ተቋማት እነዚህ ሲስተሞች ቢኖሯቸውም በየጊዜው ተከታትለው ወቅታዊ ማድረግ ላይ ክፍተት አለባቸው ሲል የገለጸው ደጀኔ፤ ይህንን አገልግሎት በኪራይ መልኩ ከወሰዱ ግን እየተከታተለ አዳዲስ ነገሮችን በማስገባት ወቅታዊ የሚያደርግ ኃላፊነቱን የሚወጣው ድርጅቱ እንደሆነ ይናገራል።

ኤክስፖውን አስመልክቶ አስተያየቱን የሚሰጠው ወጣት ደጀኔ፤ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ምን ላይ እንደ ደረሱ ለማወቅ እንደሚረዳ ይገልጻል። በተለይ ስለ ቴክኖሎጂ ያለውን እይታ ለማስፋትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመንቀሳቀስ በር ከፋች መሆኑን ጠቅሶ፤ ኤክስፖው ድርጅቱ ገና ብዙ መስራት እንደሚጠበቅበት እንዲገነዘብ እንዳስቻለው አስታውቋል።

የሲ ኤይ ጂ ግሎባል ኮርፖሬሽን ኩባንያ (CIG Global) የሽያጭ ሠራተኛ ወጣት እድላዊት በቀለ በበኩሏ፤ ኩባንያው በአይሲቲ ዘርፍ የአስር ዓመታት ልምድ ያለው እና ስራውንም በሕንድ የጀመረ መሆኑን ትናገራለች። በመካከለኛው ምስራቅ ሲሠራ ቆይቶ አሁን ላይ ወደ አፍሪካ የመጣና በኢትዮጵያ የራሱ መስሪያ ቤት ሊከፍት መሆኑንም ትጠቁማለች። በአፍሪካ ሩዋንዳና ኮንጎ እንዲሁም በአሜሪካ፣ በአርመኒያና በህንድ በመሥራት ረጅም ልምድን ማካበቱንም ትገልፃለች።

እድላዊት እንደምትገልጸው፤ ኩባንያው ከሌሎች ኩባንያዎች የሚለየው ማንኛውም አይነት ቢዝነሶችና ቴክኖሎጂዎች ያለው በመሆኑ ነው። በተለይ በሳይበር ደህንነት ስልጠና ይሰጣል። ኦራክል(Oracle) የተሰኘ ደህንነቱ የተጠበቀ ዳታ ቤዝ ያለው በመሆኑ በመረጃ መንታፊዎች በኢንተርኔት በዳታ አካውንት ወይም በኦንላይን የሚደረጉ የግንኙነት መድረኮች ላይ ስርቆት ሊፈፅምበት ወይም “ሃክ” ሊደረግበት አይችልም።

ኩባንያው ይህንን ችግር መፍታት የሚያስችል ሥራ እንደሚሰራ ጠቅሳ፤ ኢትዮጵያ ገና ወደ ዲጅታል ሲስተም እየገባች ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ የዳታ ቤዝ ችግሮችን ሊፈታ የሚችል መፍትሔ ይዞ መምጣቱን ነው የገለጸችው። በኤክስፖው ላይ ራሱን ለማስተዋወቅና አጋሮችን ለማሰባሰብ የተገኘ መሆኑን ገልጻ፤ በዚህም በርካታ እድሎችን ማግኘቱን ተናግራለች።

ትምህርት ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራው ዲቪሎፐር በኮሬቪር ሶፍትዌር ኢንጀነሪንግ ኩባንያ የሶፍትዌር አልሚዋ/ ዴቨለፐሯ ወጣት ረቂቅ ማህልቅ ፣በበኩሏ የምትሰራበት ኩባንያ ከተቋቋመ አምስት ዓመታት ያህል ማስቆጠሩን ትናገራለች። እሷ እንደምትለው፤ ኩባንያው ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራው ትምህርት ላይ ነው። ለትምህርት ቤቶች የሚሆን የመማር ማስተማር ማስተዳደር ሥርዓት(learning management system) ሶፍትዌር ይሰራል። ሶፍትዌሩ ከምዝገባ ጀምሮ ያለውን ሙሉ ሂደት የሚይዝ ነው። መምህራንና ተማሪዎች መረጃ የሚለዋወጡበት፣ ፈተና እና ውጤት የሚሰጥበት ሲሆን፤ እስከ ሰርተፊኬት መስጠት የሚደርስ አገልግሎት መስጠት የሚያስችልም ነው። ቀደም ሲል ትምህርት ቤቶችን ከወረቀት አሠራር ለማላቀቅና ይህንን ሲስተም እንዲቀበሉ በማድረግ በኩል ተግዳሮቶች እንደነበሩ ረቂቅ አስታውሳ፤ አሁን ላይ ዲጅታላይዘይሽን እየተስፋፋ ሁሉም ነገሮች ወደ ሲስተም እየገቡ በመሆኑ መሻሻሎች እየታዩ መሆናቸውን ትናገራለች።

እዚህ ኤክስፖ ላይ የመጡት የህንድ ኩባንያዎች በትምህርት ፣በአካባቢ ጥበቃ፣ ሀርድዌር እና የመሳሰሉት ላይ የሚሰሩ ናቸው። እኛ ሶፍትዌር ላይ የምንሰራ ከመሆናችን ጋር ተያይዞ የሚያስፈልገንና የማያስፈልገንን ቢዝነስ ለቢዝነስ ልምድ በማካፈል ተሞክሮ መለዋወጥ ያስቻለና አጋሮችን ማግኘት ያስቻለ መሆኑን ገልጻለች። ‹‹ወደፊት አሁን ላይ የተጀመሩትን ሥራዎች በማስቀጠል አዳዲስ ሲስተሞችን ጎን ለጎን እየሰራን እያስተዋወቅን መሄዱን አጠናክረን እናስቀጥላለን›› የምትለው ረቂቅ፤ ኤክስፖው የቴክኖሎጂ ትስስር ከመፍጠሩም ባሻገር የግንኙነት መድረኩን እንደሚያሰፋው ገልጻለች።

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ነሐሴ 30 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You