አንዳንድ ጊዜ በሰዎች ልቦና ውስጥ ህመም ሰዎችን እንደሚመርጥ ይታሰባል። በተለይም በየዋሁ ማህበረሰብ ዘንድ ህክምና የሚሰጥ ሰው የሚታመም አይመስልም። ምክንያቱም በሽታውን የሚያሸንፈው እርሱ ብቻ ነው ብለው ያምናሉ። በሕክምና ባለሙያዎች ላይ ያላቸው እምነት ከፍ ያለ በመሆኑም የሚሰጧቸውን መድኃኒት ገና ሲወስዱት እንደሚፈወሱ ለአዕምሯቸው ይነግሩታል። ይህ ደግሞ ለአንዳንዱ ወዲያው ይሰራል፤ ለአንዳንዱም ቀስ ብሎ።
ብዙዎች ሐኪምን ልክ ጦርነት ላይ እንደገባ ወታደር ያደርጉታልም። ምክንያታቸው ደግሞ አንድ ነገር ሲሆን፤ እሱም፣ ሁሉንም ሲያክም ምንም ስሜት የሚሰማው ሰው አይደለም ብለው ማመናቸው ነው። እርሱ ሰውን ቀዳዶ የሚሰፋ ጨካኝ ይመስላቸዋል። ሆኖም እንደሚታወቀው ወታደርም ሆነ ሐኪም ስሜት አለው። ወታደር ሀገርን ለማትረፍ፤ ሐኪም ደግሞ ሕመምተኛውን ከበሽታው ለመታደግ ከሚገጥማቸው አካል ጋር ግብግብ ይፈጥራሉ። ከተሳካላቸው ይፈውሳሉ፤ ካልተሳካ ደግሞ እያዘኑ ለሞት አሳልፈው ይሰጡታል።
ሐኪሞች ሁልጊዜ በውል በማይታወቅ በሽታ ከታማሚው እኩል የሚታመሙ ናቸው። እንዴት አድርጌ ይህንን ሰው ልታደገው የሚለው የዘወትር ጭንቀታቸው ነው። በሽታውን ብቻ ሳይሆን የገንዘብ ችግሩንም ለመፍታት በሚችሉት ልክ ይጥራሉ። ነገር ግን በአንድ እጅ ማጨብጨብ አይቻልምና ያሰቡትን ላያሳኩ ይችላሉ። ምክንያቱም ታካሚውም ሆነ በድህነት የሚሰቃየው ሰው ብዙ ነው።
አደባባይ ወጥቶ ለልመና የሚሰማራውንም ቤት ይቁጠረው። ስለዚህም እንደሌላው ሰው ሥራ ሰርተው፣ ወደ ቤታቸው ገብተው በእፎይታ የሚተኙ አይደሉም። ከገቡ በኋላ እንኳን እረፍት አልባ ናቸው። ቀን ላይ ሲያክሙት የቆዩትን ሰው እያሰቡ እንቅልፍ በዓይናቻው ሳይዞር ያድራሉ። ወሬያቸውም ቢሆን ከታካሚያቸው የሚዘል አይደለም። ታዲያ ስሜት ማለት ምንድነው፤ ከዚህ የበለጠ ትርጉምስ ሊሰጠው ይችል ይሆን?
ሐኪሞች የታካሚዎች ሕመምተኛ ናቸው። ማከም ብቻ ሳይሆን በእነርሱ ፈውስ መታከምም ይፈልጋሉ። ግን ይህንን ለማድረግ ብዙ ነገር ይጠይቃል። አንዱ መፍትሄው ራሳቸው እንደሆኑ ማመን ነው። እንዴት ከተባለ መጀመሪያ በሆስፒታል ውስጥ የሚሰጡትን አገልግሎት በቻሉት ልክ መስራት ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ታካሚዎቻቸው ተጨማሪ ህክምና የሚያገኙበትን መስመር መዘርጋት ነው። ለዚህ ደግሞ ሰሞኑን የተሰማው ነገር ይህንን ችግር በብዙ መልኩ ይፈተዋል ተብሎ ይታሰባል።
እንደ ሀገርም ሆነ የህክምና ባለሙያዎችን ሕመም በብዙ መልኩ የሚፈውስ እንደሆነም ተስፋ ተጥሎበታል። ለዜጎችም ቢሆን እፎይታን የሚሰጥ እንደሚሆን ታምኖበታል። ለመሆኑ፣ “ይህ ተስፋ የተጣለበት ነገር ምንድን ነው፤ ማን ነው፤ እንዴትስ ተነሳ፤ አሁን ያለበት ደረጃ ምን ይመስላል?” እና መሰል ጥያቄዎች መነሳታቸው ግድ ነውና ስለጉዳዩ ትንሽ እንበል።
ሆስፒታሉ ሐመር ቴሪሸሪ አክሲዮን ማህበር ይባላል። የህክምና ባለሙያዎች ብቻ ተሰብስበው የመሰረቱት ሲሆን፤ ስያሜውን ያገኘውም ከተለያዩ አቅጣጫዎች በመነሳት እንደሆነ በምስረታው ወቅት ተነስቷል። የመጀመሪያው ከራሳቸው ለሕክምና ከሚጠቀሙበት መሳሪያ የተነሳው ሲሆን፤ “ሐመር” ማለት የህክምና መሳሪያ ነው። በመጠኑ ትንሽ ሲሆን የሚሰራው ሥራ ግን ትልቅ ነው። ማለትም ትልቁን የአዕምሯችንን ክፍልን በአግባቡ እየሰራ ነው አይደለም የሚለውን ያረጋግጣል። አዕምሮ ደግሞ እንደሚታወቀው ሰውነታችንን ሙሉ የሚያዝ ነው። ስለዚህም መሳሪያዋ ትንሽ ብትሆንም ትልቁን የአዕምሮ ክፍል ደህንነቱን ታረጋግጣለች። ሆስፒታሉን ለመመስረት የተሰባሰቡት ሰዎች በቁጥር ትንሽ ቢሆኑም ትልቅ ሕልም እንዳላቸውና በሙያቸው ደግሞ ሀገርንም፤ ዜጋንም መታደግ እንደሚችሉ ያውቃሉና እኛን የሚገልጠን ይህ ነው ሲሉ ስያሜውን እንደሰጡት የማህበሩ ሰብሳቢና መስራች ዶክተር ዳንኤል አዱኛ ይናገራሉ።
ዶክተር ዳንኤል አሁንም ስለ ሆስፒታላቸው “ሐመር” መባል ምክንያት ሌላም ትንታኔ ይሰጣሉ። ይህም ሐመር ማለት የግዕዝ ቃል ሲሆን፤ በአማርኛ “መርከብ” የሚለውን ትርጓሜ ያገኛል። ከዚያም በሌላ በኩል “አሻጋሪ” የሚለውንም ትርጓሜ የሚሰጡት አሉ። እናም መርከብ ከአንዱ ቦታ ወደ አንዱ ደህንነቱ በተጠበቀ መልኩ እንደምታሻግር ሁሉ ሆስፒታሉም ህሙማንን ከነበሩበት ህመም አውጥቶ ወደ ነባር ደስተኛ ሕይወታቸው ይመልሳል በሚል ስያሜውን አግኝቷል። ብዙዎችን በሙያው ማሻገር ላይ ትኩረቱን አድርጎ ስለሚሰራም ከዚህ ጋር እንዲያያዝ ተደርጓል።
ሌላው ዶክተር ዳንኤል ያነሱት ነገር “ሐመር” እንደ ኢትዮጵያ ልዩ የምንሆንበት የማህበረሰብ መጠሪያም መሆኑን ነው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ እነዚህ የማህበረሰብ ክፍሎች ለሰው የሚያደርጉት እንክብካቤ ለየት ያለ ነው። ስለዚህም ሆስፒታሉም ኢትዮጵያን በመወከል ለየት ያለ ተግባር ይሰራል፤ ለዜጎችም ደራሽ ይሆናል ስንል ሐመር ብለነዋል ነው የሚሉት።
ሆስፒታሉ በማህበር እንዲመሰረት የሆነበት ምክንያት ልዩ ነው የሚሉት ሰብሳቢው፤ የመጀመሪያው በየሀኪም ቤቱ መረዳት ያልተቻሉ ህሙማን ጉዳይ ሲሆን፤ በዚህ ችግር ምክንያት ሐኪሞች ከህሙማኑ እኩል ምንም ሊያደርጉላቸው ባለመቻላቸው የተነሳ ሰቀቀን ውስጥ መግባታቸው፤ ሁለተኛው ደግሞ በየሰፈሩ በመኪናና ቁጭ ብለው ወደ ውጪ ሀገር ሄደው ለመታከም ገንዘብ የሚያሰባስቡ ሕሙማን እየሰፉ መምጣታቸው ነው። ስለዚህም መፍትሄውን በራሳቸው ለመስጠት መጀመሪያ ሁለት የሕክምና ባለሙያዎች ምን ማድረግ እንዳለባቸው ተመካከሩ። አንድ ሀሳብ ደግሞ ከሁሉም ልቆ ወጣ። ይህም ተሰባስበን የምናግዝበትን ሆስፒታል እንመስርት የሚል ነበር።
ሀሳቡ ከራሳቸው አልፎ ጓደኞቻቸው ጋር ደረሰ። አንዱ ለአንዱ በመንገርም 17ኛ ሰው ድረስ ዘለቀ። ከዚያም እንሰባሰብና እንምከርበት ተባለ። ሁኔታው ሁሉንም የሚያሳስብ ስለነበር ይሁንታን አገኘ። ሆስፒታል መስርቶ ሕሙማንን ማከም ካልተቻለ እራሳችንንም ከሰዎች ጭንቀት ውስጥ ማውጣት አንችልም ሲሉም የመጀመሪያውን ስብሰባቸውን አደረጉ። በስብሰባቸውም ብዙ ደስ የሚያሰኙና ውጥኑን የሚያጠናክሩ ሀሳቦች ተሰነዘሩ። ሰብሳቢና የቦርድ አመራሮችም ተመረጡ። ሙሉ እውቅና እንዲያገኙ የሚያስችሉ ሥራዎች ተከናወኑና የማህበሩ ምስረታ ይፋ ተደረገ።
እንደ ዶክተር ዳንኤል ማብራሪያ፤ ብዙ ጊዜ በስራ ላይ እያሉ ታካሚዎቻቸው ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ያጋጥማቸዋል። በተደጋጋሚ ውጪ ሄደው ካልታከሙ በስተቀር እንደማይድኑ ይነገሯቸዋልም። ምክንያቱ ደግሞ ሕክምናው በሀገር ውስጥ መሰጠት አለመቻሉ ነው። ለዚህም ሁለት ምክንያት ይነሳል። የመጀመሪያው የሕክምና መሳሪያ ጉዳይ ሲሆን፤ ሁለተኛው በበሽታው ላይ ጥልቅ ምርምር፤ አለያም ስፔሻላይዝ ያደረገ የጤና ባለሙያ አለመኖሩ ነው። እናም ይህ ችግር ሰዎችን ጎዳና ላይ ጭምር ያስወጣቸዋል። ጎዳና ወጥተው ለምነው የህክምና ገንዘቡን የሚያገኙትም ከስንት አንድ ናቸው። ስለዚህም ከመስሪያ ቤት እስከ መኖሪያ አካባቢያቸው ድረስ ያለው የሕሙማን ስቃይ ማህበሩን ለመመስረት አነሳስቷቸዋል።
ዶክተር ዳንኤል መጀመሪያ በመገናኛ ጎዳና ላይ ከአንድ ሥራ ባልደረባቸው ጋር በሚሄዱበት ጊዜ ነበር “እነዚህን ሕሙማን እንዴት ልታደግ?” ሲሉ ሀሳቡ በአዕምሯቸው የመጣው። ከዚያም ሻይ ቡና እያሉ ነገሩን ማጤን ጀመሩ። ቀጥለውም በዘርፉ አንቱታን ላተረፉት የሥራ ባልደረቦቻቸው ጉዳዩን አማከሯቸው። ይህ የሀሳብ ጥንስስም አደገና በብዙ ስራዎች ታጅቦ በ2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር መነሻ ካፒታልና በተከፈለ 34 ሚሊዮን ብር እንዲመሰረት ሆነ ይላሉ።
የሀሳቡ እውን መሆን የሚረጋገጠው ‹‹ማንም ኢትዮጵያዊ ለተሻለ ህክምና ወደ ውጪ ሀገር መሄድ የለበትም›› በሚል የመነሻ ሀሳብ የተመሰረተው ሐመር ተርሸሪ ሆስፒታል ውጥኑ መቋጫ ሊያገኝ እንደሆነ የሚናገሩት ሰብሳቢው፤ በኢትዮጵያ በጤና ባለሙያዎች ስብስብ የተመሰረተ እንደመሆኑ መጠን አክሲዮን ሽያጩ ለሁሉም አካላት እንዲዳረስ ይፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ማህበሩ በርከት ያሉ ሥራዎችና ድጋፍ ያስፈልገዋል ባይ ናቸው። አንዱ ደግሞ የአክሲዮን ሽያጩ ሲሆን፤ የአክሲዮን ሽያጩ በብዙ መልኩ ማህበሩ የሚፈልገውን ነገር ያሳካለታል ብለው ያምናሉ። የመጀመሪያው በገንዘብ መደገፍ የሚቻል ሲሆን፤ ሌላው ደግሞ በየቦታው ያሉ የጤናውን ዘርፍ የሚደግፉ አካላት እንዲሳተፉበት ያደርጋል የሚለው ነው። በተለይም ሙያዊ ግዴታ ያለባቸውና በዜጎች ህመም ራሳቸውን እያሰቃዩ ያሉ የጤና ባለሙያዎች የዚህ ሆስፒታል ባለድርሻ ሲሆኑ፤ ሀገር የጣለችባቸውን ኃላፊነት ከመወጣት አልፈው በህሙማን ስቃይ ዘወትር ከሚታመሙበት ችግራቸው እንዲፈወሱ ይሆናሉ ይላሉ።
ዶክተር መሰለ ተሆነ በዚህ ጉዳይ ላይ ሰፊ ማብራሪያ የሰጡ የማህበሩ አባል ሲሆኑ፤ የሆስፒታሉን ጥቅምና ራዕይ እንዲሁም የወደ ፊት አላማ እንዲህ በማለት ያነሳሉ። ሆስፒታሉ የተመሰረተበት በርከት ያሉ ምክንያቶች አሉት። ራዕዩም ብዙ ነው። ከአነሳሱ ብንጀምር በ2030 ዓ.ም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለህክምና ወደ ውጪ ሀገር መሄድ የለበትም ብሎ የሚሰራ ነው። ይህንን የሚያደርገው ደግሞ ከሀገር ውጪ ሲሰጡ የነበሩ የህክምና አገልግሎቶችን በሀገር ውስጥ በመስጠት ነው። ይህ መደረጉ በርካታ ጠቀሜታዎችን እንደ ሀገር ብሎም እንደ ባለሙያና ህሙማን ይዞ የሚመጣ ነው። አንዱ የሰዎችን የሕክምና ወጪና እንግልት መቀነስ ሲሆን፤ ሌላኛው ደግሞ የሀገሪቱን የውጪ ምንዛሬ ማዳን ነው።
ማህበሩ የያዛቸው አባላት በጤና ባለሙያና ሐኪሞች የታጀበ ሲሆን፤ በእነዚህ ባለሙያዎች ሆስፒታሉ መቋቋሙ እንደ ዜጋ፤ እንደ ሀገርና እንደ አፍሪካ ጭምር ብዙ ጥቅሞችን ያበረክታል። ለአብነት ሁሉም ባለሙያዎች በመሆናቸው በተለያዩ የመንግሥትም ሆነ የግል ሆስፒታሎች ውስጥ መረዳት ያልቻሉትን በራሳቸው ሆስፒታል ውስጥ ተጋግዘው ማዳን እንዲችሉ ያደርጋቸዋል። በተጨማሪም ወደ ውጪ የሚላኩትን ሰዎች በሀገር ውስጥ የሚያክሙበትን እድል እንዲሰጡ ያስችላቸዋል። ሌላኛው ሆስፒታሉ ለሥራ እድል ፈጠራም የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ አለው።
እንደ ዶክተር መሰለ ማብራሪያ፤ ሆስፒታሉ የራሱ ራዕይን የሰነቀ ነው። አንዱ ሰፋ ባሉ የህክምና ዘርፎች ላይ መሰማራት ሲሆን፤ ሰዎች እንደህመማቸው አይነት ባለሙያ አግኝተው እንዲታከሙ እድል የሚፈጥሩበት ነው። ይህንን ሥራውን ደግሞ በስፋት ሊያከናውነው ያሰበው መረጃን መሰረት ያደረገ ህክምና በመስጠት ሲሆን፤ ለዚህ ደግሞ እንደ መንግሥት የተጀመረውን አሰራር እንደሚያግዘው ያምናል። ማለትም መንግሥት የያዘውንና ጤና ሚኒስቴር ያስጀመረውን በመረጃ ተደራሽነት የሕክምና አገልግሎትን መስጠት ላይ በስፋት መስራት ነው። ምክንያቱም መረጃን መሰረት ያደረገ ሕክምና ታካሚውን ከህመሙ ጋር በማገናኘት በኩል ሰፊ ድርሻ አለው። ለሐኪሞችም ቢሆን የተለየ ሙያ ያላቸውን፤ የተለየ በሽታ ለተለየው ባለሙያ ለመስጠትም ያስችላቸዋል። እናም ይህንን አቅጣጫ በመከተል ሕዝብን በህክምናው ዘርፍ ማገልገል የሚለው በዋናነት ይጠቀሳል።
ሌላው ሆስፒታሉ ያለው አላማና ወደ ሥራ ሲገባ ይሰጠዋል ተብሎ የሚጠበቀው አገልግሎት በኢትዮጵያ የሕክምና ቱሪዝምን ማስፋፋት ሲሆን፤ ኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆኑ ዓለም ላይ ያሉ ጭምር ኢትዮጵያ መጥተው የሚታከሙበትን ሥርዓት መዘርጋት ዋነኛ ግቡ ይሆናል የሚለው ነው። እንደውም የሐመር ቴሪሸሪ ሆስፒታል ራዕይ በ2030 ዓ.ም በአይነቱም ሆነ በይዘቱ ከምስራቅ አፍሪካ ቁጥር አንድ ተመራጭ ቴሪሸሪ ሆኖ ማየት እንደሆነም ዶክተር መሰለ ይገልጻሉ።
እንደ ዶክተር መሰለ ሀሳብ፤ ሆስፒታሉ የህክምና የምርምር ማዕከል የመሆን ህልም አለው። በተለይም ቴሪሸሪ የሚለውን ትርጓሜ ሙሉ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራትን በስፋት ያከናውናል። ለአብነትም የህክምና ባለሙያ እጥረትን በስልጠና መሙላትና ጥሩ ስፔሻሊስቶችን ማፍራት ዋነኛ ግቡ ነው።
እንደ ሀገር ከፍተኛ ችግር የሆነውና ሀገር እየተፈተነችበት ያለው ጉዳይ የህክምና መሳሪያ እጦት ነው የሚሉት ዶክተር መለሰ፤ ሆስፒታሉ ይህንን እስከመፍታት ድረስ የሚደርስ ሥራ የመስራት አላማ አለው። ምክንያቱም ብዙ ሀገራት መሳሪያ ቢሰጡም በሀገር ውስጥ የመገጣጠም አለያም ሲበላሹ መልሶ የመስራት እድል ስለሌላቸው ችግሩ ሲገዝፍና አገልግሎት ሳይሰጥ ዓመታትን ሲያስቆጥር ይታያል። በዚያ ላይ ለሕክምና መሳሪያ መግዣ የሚወጣው ወጪ የትየለሌ ነው። ለመጠገኛና ለአንዳንድ ጎደሉ ለሚባሉም የሚወጣው ወጪ ቀላል አይደለም። ስለዚህም ሆስፒታሉ አንዱ ሥራው አድርጎ የሚሰማራበት እንደሚሆንም ተናግረዋል።
እንደ ዶክተር መሰለ ማብራሪያ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ መሰማራታችን የሚሰራው የሕክምና መሳሪያ ታውቆ በቀላሉ ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረግም ይቻላል። በተለይ፣ በቀላሉ መጠገንና በቀላሉ መቀየር እንዲችል እድል ይሰጠናል። ሐኪሙም ቢሆን መሳሪያውን በቀላሉ ሰልጥኖ እንዲጠቀምበት ይሆናል። ቀላል ዘዴዎችን ተጠቅሞ ግልጋሎቶችን ለመስጠትም ያስችላል። ይህ ደግሞ የሀገራችንን የጤና ሥርዓት እና ደረጃ ከፍ ከማድረግ አኳያ የማይተካ ሚና ይኖረዋልም። በእርግጥ ይላሉ ዶክተር መሰለ፣ በእርግጥ ለዚህ ሁሉ ተግባር ብዙ ሥራና ድጋፍ ያስፈልጋል። ለዚህም መፍትሄው ከተለያዩ ባለሙያዎችና ከመንግሥት ጋር አብሮ መስራት ነው። ይህንንም ገና ከጅምሩ እያከናወንነው እንገኛለን ሲሉ አስረድተዋል።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ነሃሴ 6/2015