ትዕግስት አልባው መሸተኛ

 ወጣት ምትኩ ይመር በ1985 ዓ.ም ተወልዶ ያደገው በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 07 ነው። ዕድሜው ለትምህርት ሲደርስ በዘርፈሽዋል የመጀመሪያና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገብቶ ከ1ኛ እስከ 4ኛ ክፍል ትምህርቱን ተከታትሏል። በመቀጠል ከ5ኛ እስከ 6ኛ ክፍል በቦሌ አዲስ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትሏል። ከዚህ በላይ በትምህርቱ ገፍቶ ለመቀጠል ግን አልወደደም። ምክንያቱ ደግሞ ወላጆቹ አቅመ ደካማ ስለሆኑ ቤተሰቦቹን ባለው አቅም ሠርቶ ለመደገፍ በመወሰኑ ነው።

ወጣቱ ቤተሰቦቹን ለመርዳት ካለው ጉጉት የተነሳ ትምህርቱን አቋርጦ ሥራ ሳይመርጥ በቀለም ሥራ በረዳትነት ተቀጥሮ ለረጅም ዓመት ሠርቷል። በዚህ ሥራ ላይ ተሠማርቶ በሚያገኘው ገቢ ከራሱ አልፎ ቤተሰቦቹን ይደጉም ነበር። በኋላም የቀለም ሥራው እየተቀዛቀዘ መምጣቱን ተከትሎ የራሱን የሥራ ዕድል ፈጥሮ ድንች ቅቅል በመሸጥ ሥራ ላይ ይሰማራል። በዚህ ሥራ በሚያገኛት ገቢም ያማረውን በልቶና ለብሶ ባያድርም እንደ አቅሙ መኖርን ግን የከለከለው አልነበረም ። ከሥራ መልስ በተለይ ማታ ማታ በሰፈሩ በምትገኝ አንዲት አረቄ ቤት ጎራ እያለ አንድ ሁለት ሳይል ወደ ቤቱ ገብቶ አያውቅም። ሁሌም ቢሆን በመሸታ ቤቷ አንድ ሁለት እያለ ከሰዎች ጋር ሀሳብ ይቀያየራል፣ ይጫወታል፣ ብሶቱን ያወጋል። አንዳንዴም ቁጭ ብሎ እየጠጣ በሀሳብ ጭልጥ ብሎ ይጓዛል፣ ከራሱ ጋር ይመክራል፣ ብሶቱን ያብሰለስላል፣ “የኔ እጣ ፈንታ እንዲህ ሆኖ ቀረ” እያለ በሚመስል አኳኋን አንገቱን ወደ ግራና ቀኝ እያወዛወዘ ከራሱ ጋር ያወራል። ሁሌ ጀንበር ስታዘቀዝቅ ወደ መሸታ ቤቷ እያመራ እንዲህ ጊዜውን አሳልፎ ወደ ቤቱ ይገባል።

ወጣት ምትኩ ከራሱ ጋር እንዲህ እየመከረና ከሰዎች ጋር እየተጫወተ ዘወትር የሚያመሽበት መሸታ ቤት በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 07 ልዩ ቦታው መሳለሚያ ባጃጅ ተራ አካባቢ የሚገኘው መኮንን አረቄ ቤት ሲሆን የአረቄ ቤቱ ታዋቂ ደንበኛም ነው። ሐምሌ 10 ቀን 2014 ዓ.ም ግን ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ወደ መሸታ ቤቱ የገባው በጠዋት ነበር። ሁኔታውም ደስ የማይል እንደውም ነገር የፈለገው ያለ እስኪመስል ድረስ ገና በጠዋት ከላይ ከላይ ያናግረውም ነበር ። ከሰዎች ጋር ከመሳቅና ከመጫወት ይልቅ ነገር ነገር ማለቱን ቀጠለበት። ያስቀዳውን መጠጥ ሳይጨርስ ይወጣል ይገባል። ተቀምጦም በሰከነ መንገድ መጠጡን አይጠጣም፣ ያቁነጠንጠዋል። የሚጠጣውን መጠጥ ያስቀመጠበትን ጠረጴዛ በጡጫ ደጋግሞ ይቀጠቅጠዋል። የገባ የወጣውን ይዘልፋል። ከዚህ አልፎ ተርፎ “ዛሬማ ይሄን ቤት አቃጥለዋለሁ፤ እዚህ ቤት አንድ ሰው አንድ ነገር ሳላደርግ አልወጣም” እያለ ይዝታል። በጥቅሉ በወቅቱ እንደ እብድ ውሻ ወደ መሸታ ቤቱ የገባውን የወጣውን ሰው ሁሉ ሲለክፍ ሲሳደብ አረፈደ።

እንደሚታወቀው ሰው ከሥራ መልስ አንድ ሁለት ብሎ ወደ ቤቱ ስለሚገባ በተለይ ዘወትር ከሥራ ወደ ቤት በመግቢያ ሰዓት መሸታ ቤቷ ትደምቃለች። እንደ ወትሮው ሁሉ ጀንበር እየጠለቀች ስትሄድ አረቄ ቤቷ በደንበኞቿ ተሞላች። የአረቄ ቤቱ አንዱ ደንበኛ የሆኑት አቶ ሞገስ ይገዙም ከሥራ ውለው በግምት ምሽት 12 ሰዓት 30 ደቂቃ አካባቢ ወደ መሸታ ቤቷ ጎራ ብለው አንድ ሁለት እያሉ ነበር። ሌሎችም ደንበኞች አረቄያቸውን እየጠጡ ይሳሳቃሉ፣ ይጫወታሉ። እግር ጥሎት ጎራ ያለም በተመሳሳይ እየጠጣ ከሚያውቀውም ከማያውቀው ሰው ጋር የጋራ በሚያደርገው ጨዋታ ጣልቃ እየገባ ይጫወታል። በጠቅላላ ቤቱ በማይደማመጡ ግን ደግሞ የመሰላቸውን እያወሩ በሚዝናኑ ጠጪዎች ሞቅ ደመቅ ብሎ ነው ያመሸው::

ቀኑን ሙሉ “እዚህ ቤት አንድ ነገር ሳላደርግ አልወጣም” እያለ ሲዝትና ሲሳደብ የነበረው ወጣት ምትኩ ማታም በመሸታ ቤቱ አረቄውን ይዞ ተሰይሟል። ልክ እንደቀኑ ማታም ከሥራ መልስ በመሸታ ቤቱ ራሳቸውን ሊያዝናኑ የታደሙትን ሁሉ መጥፎ ስድቦችን እየተሳደበ ሁሉንም በጅምላ ሲያስቀይም በጨዋታ መሐል ወሬ ማቆርፈዱንና ማወኩን ተያያዘው። አረቄ የምትቀዳው አስተናጋጅ “እባክህ ደንበኞችን አትስደብ” ብላ ብትለምነውም እሷም ከእሱ ስድብ የምታመልጥ አልሆነችም። እየቆየም ተው ሲሉት ብሶበት ከመሳደብ አልፎ ከሰዎች ጋር ለመጣላት ይገለገል ጀመር።

ይሄኔ እየጠጡ ከነበሩት ሰዎች አንዱ አቶ ሞገስ “ለምን አትተውም፣ የምትሰድባቸው ሰዎች ትልቅ ሰዎች አይደሉም ወይ” ብለው ወጣት ምትኩን ይናገሩታል። ወጣቱ በምላሹ “አንተ ምን አገባህ፣ ምን ቤት ነህ” ብሎ ከአቶ ሞገስ ጋር ግብግብ ይያያዛል። ይህኔ አስተናጋጇና ጓደኛዋ መሐላቸው ገብተው አገላግለው ወጣት ምትኩን ይዘውት ከቤት ይወጣሉ። አቶ ሞገስ ግን በሁኔታው ተገርመው መሸታ ቤቱ ውስጥ ተቀምጠው ነበር። ወጣት ምትኩን አስተናጋጇና ጓደኛዋ መውጫ በር ላይ አድርሰውት ተመልሰው ቤት እንደገቡ እግር በእግር ተከታትሏቸው ገብቶ ሁለቱንም መሬት ላይ አሽንቀጥሮ ይጥላቸዋል። እነሱም በወደቁበት ኡ! ኡ! እያሉ የድረሱልኝ ጥሪ አሰሙ። ወጣቱ ግን እነሱን ገፍትሮ ጥሎ ቀጥታ አቶ ሞገስ ወደተቀመጡበት በመሄድ ግብግብ ይያያዛል። ሰዎች ለመገላገል መሐላቸው ሲገቡ ወጣት ምትኩ ድንች የሚልጥበት ቢላዋ ይዞ ስለነበር አንድ ጊዜ አቶ ሞገስን ጀርባቸውን ከኋላ በኩል በስለት ሰንዝሮ ይወጋቸዋል። አንድ ጊዜ እንደወጋቸው ደግሞ ሳይወጋቸው ሰዎች መሐል ላይ ገብተው የያዘውን ቢላዋ ቀምተው ከቤት ያስወጡታል። ወጣቱ ይህንን የወንጀል ድርጊት ከፈጸመ በኋላ ከቦታው ወዲያውኑ ይሰወራል።

በአንጻሩ አቶ ሞገስ በተቀመጡበት ወንበር ላይ ሸርተት ብለው ወደ መሬት ይወድቃሉ። አስተናጋጇና ጓደኛዋ ከወደቁበት ተነስተው አቶ ሞገስን ሲያዩቸው በግራ በኩል ከፍተኛ ደም እየፈሰሳቸው ነበር። እነሱም ወዲያው አፋፍሰው በአቅራቢያው ወደሚገኝ ክሊኒክ ይዘዋቸው ይሄዳሉ። ሆኖም በክሊኒኩ በራፍ እንደደረሱ ምንም አይነት የሕክምና አገልግሎት ሳያገኙ ሕይወታቸው ማለፉን የአረቄ ቤቱ አስተናጋጅ ነፃነት ወንደሰን ለፖሊስ በሰጠችው መረጃ አረጋግጣለች:: ወጣት ምትኩ ገና በጠዋቱ በአረቄ ቤቱ ገብቶ እየረበሻት አላስቀዳት ሲል አብራት እንድታመሽ ለምና አምጥታት ወንጀሉ ሲፈጸም በቦታው የነበረችው ጓደኛዋ ወይዘሮ ጌጤ  አበበ (ከዚህ ቀደም ትዳር ከመያዟ በፊት በአረቄ ቤቱ በአስተናጋጅነት ስትሠራ ነበር) ለፖሊስ በሰጠችው የምስክርነት ቃል ተናግረዋል። ሁለቱም በተመሳሳይ ከላይ በተገለጸው መሠረት ተጠርጣሪው ወንጀሉ በተፈጸመበት ቦታና ዕለት ከጠዋት ጀምሮ ወንጀሉን ፈጽሞ ከመሸታ ቤቱ እስከተሰወረበት ቅጽበት ድረስ ሲያደርገው የነበረውን እያንዳንዱን ነገር እና እንዴት የወንጀል ድርጊቱን እንደፈጸመ ለፖሊስ በሰጡት ቃል አስረድተዋል።

የተጠርጣሪው የእምነት ክህደት ቃል

ከላይ በተጠቀሰው ቀንና ቦታ ከምሽቱ 2 ሰዓት ገደማ መኮንን አረቄ ቤት ወንጀሉ እንደተፈጸመ ተጠርጣሪው ወጣት ምትኩ ገልጾ፤ በወቅቱ ተወልዶ ባደገበት ሰፈር በምትገኝ መኮንን አረቄ ቤት እየጠጣ እንደነበር ይናጋራል። በተመሳሳይ ወንጀሉ በተፈጸመበት ቦታ፣ ቀን እና ሰዓት ሟች በዚሁ አረቄ ቤት እየጠጣ ነበር። የፀቡን መንስኤ ሲያስረዳም አረቄ ቤቱ ውስጥ እየጠጣ እያለ ከአንድ ከሌላ የአረቄ ቤቱ ደንበኛ ጋር ይጨቃጨቃሉ። አስተናጋጆቹ እንዳይጣላ ብለው በጓሮ በር ያስወጡታል። ተመልሶ ወደ አረቄ ቤቱ ሲገባ ለመጣላት ጫፍ ደርሰው ሲጨቃጨቁ የነበረው ግለሰብ ወጥቶ ሄዷል። እሱም ግለሰቡ ወጥቶ እንደሄደ ሲያይ እንደገና አዞ ቁጭ ብሎ መጠጣት ይጀምራል። በዚህ መሐል ሟች አቶ ሞገስ ይገዙ ከመቀመጫው ተነስቶ “ለዚህ ቤት ወንዱ አንተ ብቻነህ እንዴ? በማለት በመጥፎ ቃላት ስድብ መለዋወጣቸውን ወጣቱ ምትኩ ይናገራል።

ይሄኔ ወጣቱ ከመቀመጫው ተነስቶ ከሟች ጋር ግብግብ ይያያዛሉ። ድንች የሚልጥበት ቢላዋ እጁ ላይ ይዞ እንደነበር ጠቁሞ፤ ሰዎች ለመገላገል መሐላቸው ሲገቡ ተንጠራርቶ ሟችን ጀርባውን ከኋላ በኩል አንድ ጊዜ በያዘው ስለት ቢላዋ ሰንዝሮ ይወጋዋል። አንድ ጊዜ እንደወጋው ለማገላገል መሐላቸው የገቡ ሰዎች ቢላዋውን ቀምተው ውጣ ብለው ከቤት ያስወጡታል። በኋላም ሟች እዛው አረቄ ቤቱ ውስጥ እንደወደቀና ሕክምና እንደወሰዱት ሰዎች ይነግሩታል። እሱም ይህንን የወንጀል ድርጊት ከፈፀመ በኋላ ወደ ቤቱ ሳይገባ ከአካባቢው ራቅ ብሎ ሌሊቱን ሙሉ ሲዞር ያድራል። በነገታው ማለትም በ11/11/2014 ዓ.ም ላይ ጠዋት ወደ ቤቱ ሲመለስ ማታ በስለት የወጋው ሰው ሕይወቱ ማለፉን የአካባቢው ነዋሪ የሆነ አንድ ግለሰብ ሹክ ይለዋል። ግለሰቡ መሞቱን ሲሰማ ወደ የረር ፖሊስ ጣቢያ ሂዶ “የሰው ሕይወት አጥፍቻለሁ” ብሎ ለፖሊስ እጁን ይሰጣል።

እጁን ከሰጠ በኋላም ወንጀሉ በተፈጸመበት ሰዓት ለሥራ ይዞት በነበረ በሁለት በኩል ስለታማ እጀታው መልኩ ጥቁር በሆነ ቢላዋ ሟችን ከጀርባ በኩል ወግቶ በመግደሉ ጥፋተኛ እንደሆነና በሠራው ወንጀል እንደተጸጸተ ለፖሊስ የእምነት ክህደት ቃሉን ሰጥቷል። ፖሊስም ተጠርጣሪውን እጁን ከሰጠበት ዕለት ጀምሮ በቁጥጥር ሥር አውሎ፤ የተጠርጣሪውን የእምነት ክህደት ቃል፣ የምስክሮችን የምስክርነት ቃል፣ የሟቾች በስለት ተወግቶ ሕይወቱ ማለፉን የሚያስረዳ የአስከሬን ምርመራ የሕክምና ውጤት፣ የአማሟት ሁኔታ፣ የደረሰበትን ጉዳት … ወዘተ የሚያሳይ ምስሎችና መረጃዎች አደራጅቶ ዐቃቤ ሕግ በተጠርጣሪው ላይ ክስ እንዲመሠረትበት መረጃውን አቅርቧል።

ዐቃቤ ሕግ

በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 540 ሥር በመተላለፍ ተከሳሽ ሰውን ለመግደል አስቦ በቀን 10/11/2014 ዓ.ም በግምት ከምሽቱ 2 ሰዓት ሲሆን በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 07 ክልል ልዩ ቦታው መሳለሚያ ባጃጅ ተራ እየተባለ የሚታወቀው አካባቢ መኮንን አረቄ ቤት ውስጥ ሟች ሞገስ ይገዙን በተፈጠረ ወቅታዊ አለመግባባት ተከሳሽ ሲሳደብና ሲዝት፤ ሟች ተው እንዲህ አትበል ሲለው አንተ ምናገባህ በማለት ግብግብ ሲያያዙ ተከሳሽ በያዘው ቢላዋ በስለት በቀኝ ጀርባው ላይ በመውጋት በጀርባው ላይ በደረሰበት በስለት መወጋት ጉዳት ምክንያት ሕይወቱ እንዲያልፍ አድርጓል። በመሆኑም ተከሳሽ በፈጸመው ተራ የሰው ግድያ ወንጀል ዐቃቤ ሕግ ክስ መሥርቶበታል።

ዐቃቤ ሕግም አምስት የሰው ማስረጃ፤ በፌዴራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የፎረንሲክ ሜዲስንና ቶክሲኮሎጂ ትምህርት ክፍል በቁጥር ጳሀ8/412 በቀን 06/12/2014 ዓ.ም ስር የተሰጠ ሟች በስለት መሣሪያ በጀርባው ላይ በደረሰበት ጉዳት ምክንያት ሕይወቱ ማለፉን የሚገልጽ ደብዳቤ ከነመሸኛው እና ማብራሪያ ትርጉሙ 06 ገጽ ቅጂ፤ ከኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ የፎረንሲክ ምርመራ ዘርፍ በደብዳቤ ቁጥር ፌፎ/ባ-08/246/2015 በቀን 19/11/2014 ዓ.ም የተላከ የፎረንሲክ ምርመራ ውጤት ከነመሸኛው 02 ገጽ ቅጂ፤ የሟቾችን አስከሬን፣ የደረሰበትን ጉዳት፣ የአማሟት ሁኔታ፣ የወንጀል ስፍራውንና ወንጀል የተፈጸመበትን ቢላዋ የሚያሳዩ አጠቃላይ 13 ገላጭ ፎቶግራፎችን፤ በተጨማሪም ተከሳሽ በወ/መ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 27(2) መሠረት ወንጀሉን መፈጸሙን አምኖ የሰጠውን የእምነት ክህደት ቃል በማስረጃነት አያይዞ ለፍርድ ቤት አቅርቧል። ፍርድ ቤቱም ዐቃቤ ሕግ ያቀረበውን የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን መርምሮ በተከሳሽ ላይ የሚከተለውን ውሳኔ ሰጥቷል።

 ውሳኔ

 ታህሳስ 15 ቀን 2015 ዓ.ም የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ 1ኛ ምድብ ችሎት በተከሳሽ ላይ የመጨረሻውን ውሳኔ ለመስጠት በችሎቱ ተሰይሟል። ፍርድ ቤቱም በዚህ ቀን በዋለው ችሎት ክስና ማስረጃውን ከሕግ ጋር አገናዝቦ ተከሳሽ በ13 (አሥራ ሶስት) ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ሲል ውሳኔ አሳልፏል።

ሶሎሞን በየነ

አዲስ ዘመን   ሐምሌ 29/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *