ዝናብ የጠገበው መንገድ በየቦታው ውሃ አቁሯል። በማይመች የእግረኛ መንገድ የሚጓዝ ሰው በአንዳንድ አካባቢ በአሽከርካሪ የቆሸሸ ውሃ መረጨት ግዴታው ይመስል መላ አካላቱ በውሃ ይርሳል። መኪናው እና እግረኛው ተመሳሳይ ቦታ ላይ ሲገናኙ፤ አሽከርካሪው አቀዝቅዞ ካልነዳ እግረኛው ሮጦ የሚያመልጥበት ዕድሉ ጠባብ ስለሆነ በከተረ ውሃ ሰውነቱ መራሱ አይቀሬ ነው።
ዛሬ ዘውዴ መታፈሪያም አንድ የጠገበ አሽከርካሪ መኪናውን ይዞ ሲጋልብ ከፀጉሩ እስከ እግሩ ውሃውን አልብሶት በብስጭት ወደ ቤቱ ሔዶ፤ በእልህ ሥራ መሔዱን ትቶ ቤቱ ዋለ።
ሲመሻሽ እንደለመደው ማምሻ ግሮሰሪ ትዝ አለው። ቱታ ለብሶ ወደ ግሮሰሪው አመራ። ቀድሞ በመድረሱ ተሰማ መንግስቴ እና ገብረየስ ገብረማርያም በማምሻ ግሮሰሪ አልነበሩም። በስሱ የሚወርደው ዝናብ እና ብርዱ የእነርሱ አለመኖር ታክሎበት ከቤት ባልወጣሁ አለ። ያው መቼም ሱስ ሆኖበት ዝናብና ቅዝቃዜ ሳይበግረው ማምሻ ግሮሰሪ ተገኝቷል። ብዙም ሳይቆዩ ተሰማ እና ገብረየስ ሁለቱም ተከታትለው መጡ።
ከቀን ወደ ቀን ሰውነቱ እየወፈረ በማያቋርጥ ሁኔታ እያማረበት የሚታየው ተሰማ፤ ዘውዴን በቱታ ሲያየው ተገርሞ ‹‹ብለህ ብለህ በቱታ ቢሮ መሄድ ጀመርክ?›› አለው። ‹‹እንግዲህ ምን ይደረግ? አንድ የጠገበ ራቫ መኪና የያዘ አሽከርካሪ ጠዋት ወደ ሥራ ስሔድ በቆሸሸ ውሃ ከፀጉሬ ጀምሮ አጠመቀኝ። ተበሳጭቼ ወደ ቤት ከገባሁ በኋላ ሳስበው 33 ዓመት ሥራ ተመላለስኩ፤ ነገር ግን እንኳን ራቫ መኪና ሳይክልም አልገዛሁ፤ ምን አደከመኝ? ብዬ ቤቴ ተኝቼ ዋልኩኝ። ›› ብሎ በረዥሙ ተነፈሰ።
ገብረየስ ‹‹ፈገግ አለ፤ መኪና ባለመግዛትህ ከመማረር መንገዱ ባለመሠራቱ ብትማረር ይሻልህ ነበር። ነገሩ በዛም ሆነ በዚህ በምንም መልኩ መማረር ምንም ዓይነት ውጤት አያመጣም። ከመማረር ይልቅ መተባበር ይሻላል። በመተባበር መንገዱንም ማስተካከል መኪናውንም መግዛት፤ ሁሉን ማግኘት ይቻላል። ከጋራ ውጤታማነት ይልቅ የራስን ስኬት ብቻ ለማረጋገጥ ለብቻ መሯሯጥ ግን ራቫ ለመግዛት ቢያስችልም እንዳንተ ዓይነት የተማረረ እግረኛ ከመኪና አውርዶ ውሃ ማስረጨት ብቻ ሳይሆን እስከ መጨረሻ አጠፋችኋለሁ ብሎ ሊንጠራራ ይችላል። ›› ብሎ መሳቅ ጀመረ።
ተሰማ የገብረየስ ሳቅ ተጋብቶበት እርሱም በፈገግታ ‹‹ዘላለም ስለተራ ችግር እያወሩ ራስን ከማድከም ይልቅ፤ መመሰጋገን፣ ፍቅር እና አንድነትን መሠረት ብናደርግ፤ ብንተሳሰብ የት በደረስን? ዘፋኙ ሰው ለሰው ቢፋቀር ሁሉም ቢተባበር የት ይደረስ ነበር? እንዳለው መተባበር በሽታ ሆኖብናል። የእኛ ሥራ ሁልጊዜ ሞኝ ሆነን በብልህ ላይ እንደሳቅን ነው። አላዋቂዎች በመሆናችን ጥሩውን ነገር ሳይቀር ከመተቸት ወደ ኋላ ብለን አናውቅም። ሞኝ ሲናገር ብልህ ያዳምጣል ይባላል። እና ግን ማዳመጥ ብሎ ነገር የለንበትም።
ነገሮችን በጥሞና ተከታትሎ በቁም ነገር ላይ ከማዋል እና ሌላው ሲናገር በጥሞና አዳምጦ ነገሮችን በትክክል ከማገናዘብ ይልቅ ወሬ፣ ሃሜት እና መማረር ላይ እናተኩራለን። በተለይ አሁን አሁን እንደውም የእኛ አካባቢ ሰዎች ብልህ ናቸው ለማለት እቸገራለሁ።›› አለው።
ዘውዴ በበኩሉ መረር ብሎ ‹‹ አለመታደል ሆነና የገዛ ሰውነታችንን የራሳችንን አካል የምናስበው ከፋፍለን ነው። ዓይናችንን ወድደን አፍንጫችንን እንጠላለን። ዓይናችን ያለአፍንጫችን መዋብ እንደማይችል እንዘነጋለን። ሁልጊዜም የገዛ አካላችንን፤ የራሳችንን ሰውነት አንዱን ከሌላው መርጠን ለማጥፋት እንጥራለን። ግራ እጃችን ብቻውን ከሚሠራ ይልቅ ከቀኝ እጃችን ጋር በጋራ የሚሠራው የተሻለ ሊሆን እንደሚችል አንገምትም። በደመነፍስ ስለምንመራ ቀኝ እጃችንን ለመቁረጥ አንሳሳም።
የሌሊት እና የቀን ህልማችን እጃችን፣ እግራችን፣ ዓይናችን ወይም አፍንጫችን እና አንድ የሆነውን የአካላችንን ክፍል በማስወገድ፣ በመገንጠል ወይም በማጥፋት ላይ ብቻ ያተኩራል። ሁልጊዜ ለምን በዚህ መልኩ እንደምንሔድ ሳስብ ግራ ይገባኛል። እንኳን እጃችን የእጃችን ትንሿ ጣት ለሰውነታችን አስፈላጊ መሆኗን የምናስብበትን ዋናውን ጭንቅላታችንን ስለማናሰራው አንድ በአንድ አካላችንን እየቆራረጥን እንጥላለን።
በገዛ ሰውነታችን ላይ ስንጨክን ለአፈር የሚበቃ የተሟላ አካል ቀርቶ፤ የጎደለ አካል ማግኘት እስከሚያዳግት ድረስ እንደፍራለን። የአንዱ መኖር ለሌላው ጥንካሬ እና ውበት ስለመሆኑ እንዘነጋለን። በቅንነት መነሳት ብርቃችን ነው። በክፋት ታሽቶ ተቦክቶ ተጋግሮ መሻገትን ልማድ አድርገነዋል። እንደሰማነው ከሆነ ቀደም ሲል እንዲህ ዓይነት ሁኔታ የሚስተዋለው በጥቂት ሰዎች ላይ ለዚያውም ዕድሜያቸው ሲገፋ ነበር አሉ። አሁን አሁን ግን ወጣቱም አዛውንቱም ሁሉም በክፋት በመነሳሳት አንዱ ሌላውን ለማጥፋት ሴራውን ሲጠነስስ ይውላል። አንዱ የሚያድገው በሌላው መኖር ላይ መሆኑ ተረስቶ ሁሉም ትኩረቱ መጠፋፋት እና ማጥፋት ላይ ሆኗል።
እየገነነ ሀገር እያስጨነቀ ያለውን መጠላለፍ ትተን ወደ ተራው ጉዳይ ፊታችንን ስናዞር የምናስተውለው ተመሳሳይ ነገርን ነው። ከዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያችን ስንነሳ ነጋዴው በእውነት ያለሸማች እንደማይኖር አይገነዘብም። በእውነት ሠርቶ ተገቢውን ትርፍ ከማግኘት ይልቅ አጭበርብሮ ጊዜያዊ ገንዘብ ማግኘትን ይመርጣል። ሸማች ላይ የተወሰነ ገንዘብ ጨምሮ በማግስቱ እንዲመለስ ከማድረግ ይልቅ በአንድ ጊዜ ከፍተኛ ትርፍ ለማግኘት በመሞከር ሸማችን ይጎዳል። የገዛ አካሉን ያጎድላል።
አገልጋይም ያለተገልጋይ መኖር እንደማይችል ልብ አይልም። ሩቅ መንገድ አቋርጦ የመጣ ተገልጋይ ለ10 ደቂቃ ሥራ በማግስቱ ወይም ከሦስት ቀን በኋላ እንዲመለስ ያዛል። የምርት አቅራቢው በበኩሉ እንጀራ ላይ ጀሶ፣ በርበሬ ላይ ሸክላ፣ ጎመንዘር ላይ ሰጋቱራ እየቀላቀለ የገዢው ጤና ላይ ጉዳት ያስከትላል።
እያንዳንዱ ሥራችን ገንዘብ ከመውደድ በላይ ሆኖ፤ የገዛ ሰውነታችንን ከመውደድ ይልቅ እየቆራረጥን መጣል ተፀናውቶናል። ለነጋዴው ሸማቹ፤ ለአገልጋዩም ተገልጋዩ የራሱ አካል እንደሆነ ረስቶ ቆርጦ ሲጥለው አይሳሳም። እያንዳንዱን እንቅስቃሴ ካስተዋልን አንዱ ሌላውን የገዛ አካሉን እያስጨነቀ፤ ሁሉም ያለጊዜው ረክሶ እየተጣለ ነው። የዚህ ሁሉ መነሻው አለመተባበር ነው። ›› ብሎ ረዢሙን ንግግሩን አጠናቀቀ።
ገብረየስ በበኩሉ፤ ‹‹ስነልቦናዊ ስምምነት በመግባባት ላይ አንዱ ሌላውን በመረዳት ላይ የተመረኮዘ ነው። እኛ ደግሞ ለመስማማት እና ለመግባባት ዝግጁ አይደለንም። ስነልቦናዊ ስምምነት የለንም። ሳንስማማ እና ሳንግባባ ደግሞ መተባበር ያዳግተናል። ምክንያቱም ሰዎች ነን፤ ላልገባን እና ላልተስማማንበት ጉዳይ አንተባበርም። ጓደኛሞች ሆነን ሳይቀር በራሳችን ውስጥ የምናየው አለመደማመጥ፤ የንግግር እና የመረዳት መዛባት አለ። እርስ በእርሳችን ስንነጋገርም የምንረዳው በተዛባ መልኩ ነው። ለእዚህ መፍትሔው አስቀድሞ በአግባቡ ለመረዳት እየሞከሩ፤ አንዱ ሌላውን በእነርሱ ጫማ ውስጥ ከቶ ቢያዳምጥ፤ ለመረዳት ቢሞክር ይሻላል። ያለበለዚያ ትናንት ላይ ስንፈርድ፤ ሳንረዳው ሳይረዳን፤ ሳያዳምጠን ሳናዳምጠው፤ ሳናርመው ሳያርመን ዛሬም ተመሳሳይ ድርጊት እየፈፀምን ነው።
የዛሬውን ቀን ተባብረን የሁላችንም ማደጊያ መሠረት ማድረግ ሲገባን ለመተባበር ፍቃደኛ አለመሆን፤ የሚተባበርን ሰው ማሸማቀቅ፣ መተባበርን በተዛባ መንገድ በመተርጎም በአንድላይ መቆምን እንደተሳሳተ ድርጊት መቁጠር መለያችን ከሆነ ከራርሟል። ባለፈ ነገር ከመፀፀት ይልቅ አሁን ባለው እና ወደ ፊት መፈፀም ባለበት ተግባር ላይ በማተኮር ለመተባበር ፈቃደኛ ብንሆን በተጠቀምን ነበር። ›› አለ።
ተሰማ ደግሞ፤ ‹‹ዋነኛው ችግር የግንኙነት ሁኔታን በማሻሻል ለመተባበር እና አንድ ለመሆን ሁሉንም ነገር በግልፅ ማሳወቅ ይገባል። ሞኝ ለጠበቃው ምስጢር ይሸሽጋል እንደሚባለው ሞኝ ሆነን ለሚረዳን ሕዝብ ያለብንን ጫና ምስጢር ካደረግንበት፤ ሞኝ ችግሩን ለሚያቀልለት ሰው ስለማይናገር ችግር ላይ እንደሚወድቀው ሁሉ እኛም ትልቅ ውድቀት ሊያጋጥመን እንደሚችል አያጠያይቅም።
ባለመግባባት ውስጥ ያለትብብር በጥቂቶች ብርታት ብቻ ብዙ ዋጋ በመክፈል የተገነባን ቤት ሲገነባ ያልነበረ ያፈርሰዋል። ቀዳዳ ያለምንም ጥርጥር እንደሚያፈሰው ሁሉ፤ ይሔም ግልፅ ነው። የተሠራው ሁሉ እነርሱን የሚጠቅም ቢሆን እንኳ አንዳንድ ሰዎች እነርሱን ለመጉዳት ተብሎ የተሰነዘረ ጥቃት እንደሆነ ያስባሉ። ከማሰብ አልፈው ሙከራው ላይ እርግጠኛ ሆነው ሥጋት እና ብስጭት ውስጥ ይገባሉ። ይሔኔ የደረሰው ይድረስ ብለው በድፍረት ያሰቡትን ይናገራሉ። በተቃራኒው በኩል ያለው ሰውም በእነርሱ ጫማ ውስጥ ሆኖ ለመረዳት ከመሞከር እና የእነርሱ ሃሳብ የተዛባ ዕይታ ውጤት መሆኑን አስረግጦ ከመንገር ይልቅ በተቃራኒው ሃቅ ያለኝ እኔ ነኝ ብሎ ሲደነፋ ነገሩ ከመንተክተክ አልፎ ይገነፍል እና የተጣደበትን ትልቅ ምድጃ ያበላሻል። ›› ብሎ እርሱም በበኩሉ የሚያምንበትን ለማስረዳት ሞከረ።
ገብረየስ ወደ ዘውዴ እያየ፤ ‹‹ እኛ እኮ በልጆቻችን ጉዳይ ላይ ሳይቀር ከመምህር ጋር ለመተባበር እና እንደወላጅ ኃላፊነትን ለመወጣት የምንቸገር ነን። ከወላጅ ጋር መተባበር ሲኖር፤ ልጆች ስኬታማ ይሆናሉ። ሃኪም ከነርስ እና ከታካሚው ጋር ሲተባበር ታማሚ ይድናል። ከዚያ መመሰጋገን ይከተላል። እንዲህ ሲሆን ሕይወት ይቀላል። የእኛ ነገር ግን ተቃራኒ ነው። ዘውዴ እንዳለው ትኩረታችን ከመተባበር ይልቅ መቆራረጥ እና መለያየት፤ አንዱ በሌላው ላይ መነሳት እና አንዱ ሌላውን በማጥፋት ላይ ጊዜያችንን መጨረስ ነው።
ሠርተን ለሀገር ጠብ የሚል ነገር አስቀርተን ሳይሆን እንዲሁ እንደባከንን የድካም ዘመናችን ይደርሳል። 60 እና 70 የተባሉ ዓመታትን አሳልፈን ወደ ማይቀረው ሞት እናመራለን። የብዙ ኢትዮጵያውያን ታሪክ ይህ ብቻ በመሆኑ ሀገራችን አሁንም ያለችው ድሮ ከነበረው በተመሳሳይ ደረጃ ላይ ነው። …›› ብሎ ሊቀጥል ሲል ተሰማ አቋረጠው።
ተሰማ ገብረየስ ላይ እያፈጠጠ ‹‹እኛ መቼ አናዳምጥም፤ አንደማመጥም አልን? ነገር ግን የውስጥም የውጭም ጠላት ተነጋገረን እንድንደማመጥ እና ተግባብተን በትብብር እንድንሠራ በአንድነት ለአንድ ዓላማ እንድንነሳ አልተፈቀደልንም። አንዳንዴ ድህነት መጥፎ ነው። ድሃ ከሆንክ ባትፈልግም ለሌሎች ትገዛለህ። ጊዜው ዘመናዊ ነውና ገዢዎቹ ገዝተንሃል ሳይሉ በድብቅ ይገዙሃል። በተዘዋዋሪ ገንዘብ እየሰጡ በዘዴ ሀገር የማፍረስ ዕቅድ በመያዝ በምስጢር በዚያ ላይ እንድትሠራ ያስገድዱሃል። አማራጭ ስለሌለህ አውቀህ ለራስህ ስትል ወይም ባለማወቅ የእነርሱን ሃሳብ የሚደግፍ ድርጊት ትፈፅማለህ። ይሔኔ ሀገር አደጋ ላይ ትወድቃለች። ስለዚህ መፍትሔው መደጋገፍ ብቻ ነው።›› አለ።
ዘውዴም ተራውን ለመናገር አፉን አዘጋጀና፤ ‹‹ኢትዮጵያ ብዙ ጠላቶች እንዳሏት አያጠያይቅም። አቀማመጧ፣ የሕዝብ ብዛቷ እና ታሪኳ ለብዙ ሀገራት ስጋት ነው። የአፍሪካ አልፋ ተርፋ የዓለም መሪ እንዳትሆን እንደሚሰጉም እናውቃለን። ነገር ግን ችግሩ ይሔንን በተጨባጭ ለመላው ሕዝብ በማሳወቅ ሕዝቡ እርስ በእርሱ ከሚነቋቆር ይልቅ እንዲከባበር፤ እንዲነጋገር እና ተባብሮ ችግሩን እንዲፈታ ማድረግ አለመቻላችን ነው።
ጠላቶቻችንም ለዘመናት በሚያለያዩን ሁኔታዎች ላይ ሲሠሩ ቆይተዋል። እኛም ለእነርሱ ምቹ ሆነን በሚያለያየን ጉዳይ ላይ ጉልበታችንን ጨርሰናል። በትክክልም አሁን ይበቃናል። ችግራችንን አውቀን ግዴታችንን መወጣት ይገባናል። ግዴታችንን የምንወጣው በተናጠል ሳይሆን በጋራ መሆን አለበት። መተባበር ኃይል ነው፤ ሙሉ ኃይላችንን ተባብረን ውጤት በሚያመጣ ጉዳይ ላይ ካተኮርን ለውጥ መምጣቱ አይቀርም። ውሃ የሚያቁረውን መንገድ በመሥራት ብቻ ሳይሆን ሌሎች ብዙ ተዘርዝረው የማያልቁ ከቀላል እስከ ከባድ ችግሮችን ከማቃለል አልፈን ትልልቅ ውጤቶችን በማስመዝገብ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የብዙዎች ተስፋ መሆን እንችላለን። ›› ብሎ ንግግሩን አጠናቀቀ።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 27/2015