ባትመጪም ቅጠሪኝ

ቀጠሮ ማክበር አይሆንላትም። ማንም የሚቀድማት ሴት ናት። ኖራ ኖራ ሰዓት የሚያጥራት ለቀጠሮ ነው። አልመሽ ያላት ቀን፣ በእርዝመቱ ሁሌም የምትረግመው እሁድ እንኳን ቀጠሮ ያላት ቀን አይበቃትም። ቀጠሮ ያላት ቀን ማንም የሚቀድማት ሴት ናት። ቀጥራና ተቀጥራ የቀደመችው ሰው የለም። የቀጠራትም ሆነ የቀጠረችው ሰው እሷን ለመጠበቅ የፈረደበት ነው።

ሴትን ልጅ በተመለከተ ሁሉም ወንዶች አንድ ዓይነት ናቸው ትላለች። በእሷ መዘግየት ውስጥ የተከፉና የሚያጉረመርሙ ብዙ የወንድ ፊቶችን ተመልክታለች። ሙሴ ግን ያን ሁሉ ባህሪዋን የታገሰ ልዩ ወንድ ሆኖ አገኘችው። እንደሌሎቹ ወንዶች ነው ስትል ከራሷ ጋር ተወራርዳ ነበር። ወንድን ልጅ በተመለከተ አስባ የተሳሳተችው፣ አምና ልክ ያልሆነችው በሙሴ በኩል ነው። አባቷ ልክ ነበር ‹አንድ ቀን እንደ እኔ ያለ ወንድ ወደ ሕይወትሽ ይመጣል ብሏት ነበር። የአባቷ ዓይነት ወንድ ስትጠብቅ ብዙ ጊዜያቶች ያለፉ ቢሆንም በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ሆና እንዳባቷ ያልሆነን ወንድ እንደአባቷ ያለ አድርጋ ለመሥራት በተዘጋጀችበት ማግስት ነው ሙሴ የአባቷን ነፍስ ተጋርቶ ያገኘችው።

ብዙ ፈትናዋለች..ከመዘግየት እስከመቅረት ድረስ። እመጣለሁ ብላው ብዙ ቀን ቀርታ ታውቃለች። በእሷ መቅረት ውስጥ ባገኛት ሌላ ቀን በፈገግታ ነበር የሚቀበላት። ስለትናንት አይጠይቃትም…ለምን ዝም አለኝ ስትል ሀሳብ ላይ ትወድቃለች። ‹ትናንት ሳልመጣ ቀረሁ አይደል? ትለዋለች የሚለውን ለመስማት። ሁሌም ግን አንድ ዓይነት መልስ ነው የሚመልሳላት። ‹አልተመቸሽም መሰለኝ..› እንዲህ። ቀርታ አይደለም ዘግይታ ደርሳ ፊታቸው የተቀየመ ብዙ ወንዶች በታሪኳ ላይ ተመዝግበዋል። አንዳቸውም እንደሙሴ ባለ በብዙ መረዳት፣ መረዳት ባይሆን እንኳን በመተው ውስጥ ጎብኝተዋት አያውቁም።

በቃ አይሞላላትም። ጊዜ የሚያጥራት፣ ቀን የሚመሽባት ቀጠሮ ያላት ቀን ነው። እንደሌሎቹ ሴቶች የቱን ልልበስ፣ በየቱ ላጊጥ አትልም፣ እንደሌሎቹ ሴቶች ብዙ በመኳኳልና ብዙ በመጋጌጥ ጊዜዋ የሚያልፍ ሴት አይደለችም..በቃ ዝም ብሎ ይመሽባታል።

አንድ ቀን እንደልማዷ ሁለት ሰዓት ዘግይታ ደረሰች። የሙሴ ፊት አልተቀየረም። እንደእስከዛሬው ዓይኖቹን መምጫዋ ላይ ደፍቶ ሲጠብቃት ነበር። ሲያያት እንደምሥራቅ አድማስ ነው..ደመና ፊቱ በብርሃን ይጥለቀለቃል። ሲያያት ፊቱን ሳይዝ ፊቷ ቆሞ አያውቅም።

ድንገት ደርሳ.. ‹ከዚህ በኋላ እንዲህ አላስጠብቅህም። ለእስካሁኑም ይቅርታ እጠይቅሀለሁ› አለችው።

‹ከዚህ በኋላ አላረፍድም በጊዜ እደርሳለሁ› እያለችው እንደነበር ነው የተረዳው።

ቀጠለች..‹አንተ በየትኛዋም ሴት ልብ ውስጥ ያለህ የምትታለም ህልም ነህ። ትዕግስትህ ሊሠራኝ፣ መልካምነትህ ሊያንጸኝ አልቻለም› እና ከእንግዲህ አትጠብቀኝ..አልመጣም› ብላው ከአጠገቡ ሸሸች።

‹አልገባኝም..› ጠየቃት።

‹ቀጥረሀት ቶሎ የምትመጣ ሴት ታስፈልግሀለች› አለችው።

‹ምን እንደሚያስደስተኝ የማውቅ ወንድ ነኝ። ምርጫዬ ቀጥሬያት ብዙ የምታስጠብቀኝ ሴት እንደሆነች ከእኔ በበለጠ አንቺ ታውቂያለሽ። አንቺ እንዴትም የማላገኘው የደስታዬ ምኩራብ ነሽ። እንዳንቺ ዘግይታ መምጫዋን ናፍቄ ቆሜ የምጠብቃትን ሴት ነው የምፈልገው። ደስታዬ ያለው በመዘግየትሽ ውስጥ እንደሆነ ባለማወቅሽ አዝናለሁ። እንዲያውም ንገረኝ ካልሽ ቶሎ የመጣሽ ቀን ነው የምቀየምሽ። አንቺ ትናንትና ያለምኳት ዛሬም የማልማት ነገም ህልሜ የሆነች ሴት ነሽ።

ልትሄድ ያለችውን ቆመች። ወደኋላዋ ዞራ አስተዋለችው። ምን እያሰበች ነበር? ምን እያሰበች እንደነበር አታስታውስም። ብቻ ስለዚህ አጠገቧ ስለቆመው ወንድና የትኛውንም ወንድ ስለማትመስለው ነፍሱ እንደሆነ ታምናለች። አንድ ነገር ማድረጓን ታስታውሳለች..ተንጠራርታ ጉንጩን መሳሟን እና ለዘላለም የቀረበ በመሰላት የጊዜ ርዝማኔ ሁለመናውን ማስተዋሏን። ያን ቀን ከኦሪቷ ሄዋን ቀጥሎ መልካም ወንድ የታደለች ሁለተኛዋ ሴት እንደሆነች ራሷን አመነች። በብዙ መጥተው በሄዱ የወንድ ኮቴዎች ላይ ተረማምዶ ወደእሷ የመጣ፣ በብዙ መጠበቅ ውስጥ ከነጉድለቷ ሊያፈቅራት የታደለችው እንደሆነ አምና ተቀበለች። ያን ቀን ሌላም ነገር አሰበች። ከዚህ በኋላ ባለው ሴትነቷ ሳይጠብቃት ልትጠብቀው። ከቻለች ቀድማው እስኪመጣ ልትጠብቀው ካልቻለች ዘግይታ ላታስጠብቅ ከራሷ ጋር ተማከረች።

ያን ቀን ከብዙ ወንዶች የሸሸገችውን እውነት ሰጠችው..‹አንተ እንደአባቴ ተመኝቼ ያልጨረስኩት፣ ናፍቄ ያላበቃሁት ሰው ነህ። የእውነት የማምነው አባቴን ብቻ ነበር..እንዳባቴ ሆነህ ተገኘህ። የነፍሴ ጣይ በአንተ ሰማይ በእኔ ምሥራቅ ላይ ወጥታለች። ከእንግዲህ ለብቻዬ የማበራው ብርሃን፣ ለብቻህ የምትሞቀው ጣይ የለህም። የተጋራነው ሰማይና ምሥራቅ በአብሮነት የወረስናቸው ስለሆኑ› ስትል እንደካህን ቡራኬ ነፍስ ድረስ በሚሰማ ኩርኳሬ ቃሏን ሰጠችው።

ሲያደምጣት..ያለኮሽታ ነው። ሰው ሰውን በዛ ወደር የሌለው ጽሟኔ ሲያደምጥ እሱን ነው የምታውቀው። ሳትጨርስ ተናግሮ አያውቅም። ብትጨርስ እንኳን ሌላ የምትናገረው ካለ ሲል ይጠብቃታል። ጥበቧ አስደነቀው። እሱነቱን ከእሷነቷ ጋር ያዋሀደችበት የቃል ብርታት፣ የቅኔ ሰም በዝምታ ለጎመው። መቼም እንዳይለያዩ፣ መቼም እንዳይሰለቻቹ አድርጋ በአንድ መርፌ ከአንድ ክር ጋር አያይዛ ጣፈችው። ከብዙ ዝምታ በኋላ ተናገረ ‹በጋራ ሰማይና ምሥራቅ ላይ የብቻ ጀምበር የለችም። የምናበራው ከነፍስሽ ወደነፍሴ፣ ከነፍሴ ወደነፍስሽ የተላለፈውን ብራቅ ነው።

በሚቀጥለው ቀን ቀጠሯቸው ከእሱ ቀድማ የቀጠሯቸው ቦታ የተገኘችው እሷ ሆነች። ደወለችለት። ‹መጥቻለሁ› አለችው። አላመነም። አለማመን ብቻ አይደለም ከፋው። ደስታው ባለመምጣቷ ውስጥ ነው። እሷን ቆሞ እንደመጠበቅ በዓለም ደስታ የለውም። እየቀለደች እንደሆነ አላጣውም። በአመት አንድ ጊዜ የሚመጣ እንዲህ ዓይነት ቀልድ አላት። ‹እየቀለድሽ ነው አይደል? አላት።

‹እየቀለድኩ አይደለም። በአንተ ሰማይ ላይ እንደማበራ ረሳክ እንዴ? ጠየቀችው።

እውነቷን መሰለው..እውነቷንም አልመሰለውም። ‹እስኪ በለጠ ይሙት በይ? አለ።

‹በለጠ ይሙት› አለችው። እውነቷን ነው ሲል አመነ። በአባቷ ቀልድ አታውቅም። አንዳንድ ጊዜ እንዲህ ባለማመን ውስጥ ሲቆም በአባቷ ነው የሚያስምላት። በለጠ ይሙት ካለችው እውነት ብቻ አይደለችም እውነትም እምነትም ናት። ከልክነት ገዝፋ በፍጹምና ያገኛታል።

እስኪመጣ ጠበቀችው። እስኪመጣ ዝም ብላ አልቆመችም። ስለእሱ እያሰበች፣ ወደመምጫው በመማተር በናፈቀና በጓጓ ሴትነት ነበር። እስከዛሬ እሱ እንጂ እሷ በዚህ መባረክ ውስጥ እንዳልነበረች ስትረዳ ያልኖረችው ሕይወት እንዳለ ደረሰችበት። በመጠበቋ ውስጥ ማንንም ጠብቃና ማንንም አስጠብቃ ያልደረሰችበትን የሴትነት ከፍታ ተዋሃደች። የሚወዱትን ቆሞ እንደመጠበቅ ደስታ እንደሌለ የገባትን ያክል ምንም አልገባሽ አላት። ባለፈውም ሆነ በሚመጣው እሷነቷ ውስጥ ፈልጋ ካላገኘችው፣ ተንጠራርታ ከማትደርስበት ፍቅር ከሚሉት ረመጥ እውነቷ ጋር ተገናኘች።

ወደ እሷ እየመጣ ስታየው ለመጀመሪያ ጊዜ ፍቅርን በተመለከተ ልክ የሆነች መሰላት። እስከዛሬ በራቋት ወንዶች መሄድ ውስጥ የእነሱ ድንቁርና ብቻ ሳይሆን የእሷም አለመረዳት እንዳለ ደረሰችበት። ሳም አደረገችው ከንፈሩን። ይሄን ድፍረት ከየት እንዳመጣችው አታውቅም። እስከዛሬ እሱ ነበር የሚስማት።

‹የነፍሴ ጣይ በአንተ ሰማይ ላይ ስትበራ አየኋት። ያኔ እንደሳራ በየትኛዋም ሴት ነፍስ ላይ ያልታየ ሳቅ ስቄያለሁ። ነፍስን የእኔ ከሚሉት ሰው ነፍስ ጋር መደባለቅ ያስፈራል። ከሆነ በኋላ ግን እግዜር ለሰው ልጅ በጎልጎታ የራስቅል የመስቀሉ ምስጢርና ዓለምም ይሄን ሁሉ ዘመን ኖራ ካልደረሰችበት እየሱሳዊ እውነት ጋር መጋፈጥ ነው። ዓለም ከተለማመደችው እና የሰው ልጅ ከደጋገመው የፍቅር ቃል ሌላ ፊደል ባገኝ እኔ የአንተ እንደሆንኩ በዛ ቃልና ፊደል እነግርህ ነበር። እመነኝ እኔ እኔ ያንተ ነኝ..

‹የእኔ መሆንሽን አሁን ነው እንዴ የም ታውቂው?

‹በለጠ ይሙት! እስካሁን የአንተ አልነበርኩም›። አለችው።

ከንግግሯ በፊት በለጠ የሚለው የአባቷ ስም ስላለ ቃሏን ለማመን ሌላ ጥያቄ መጠየቅ አላስፈለገውም። ለመጀመሪያ ጊዜ ተቀየማት። ላለማኩረፍ ብዙ ታግሎ ነበር አልቻለም።

‹ስፈትንህ ነበር። ራሴን ዝም ብዬ ልሰጥህ ስላልፈለኩ በመቅረት፣ ሰዓት በማርፈድ፣ የማትረባ በመምሰል ስፈትንህ ነበር። አሁን ግን ከአቅሜ በላይ ልክ የሆነ ሰው ሆነሀል።

መጨረሻ ላይ ምን እንዳለች አልሰማትም። ትቷት ሄደ።

እሱን አለመከተል አትችልም። ዛሬ ብቻ አይደለም መቼም የምትከተለው ወንድ ነው። ድምጽዋን ከፍ አድርጋ ‹አንተ ሴቶች ሁሉ የሚከተሉት ወንድ ነህ› አለችው።

ቅያሜው ድራሽ አባቱ ጠፋ..እግሮቹ ግን ከመሄድ አልቦዘኑም።

‹ሰማዬ ነህ..ደምቄ ያበራሁብህ። ከእኔ ውጪ ለብቻህ መድመቅ እንደማትችል ረሳህ እንዴ?

ስትለው..ቆመ።

ከኋላው ሄዳ አቀፈችው..

ወዴት ሊሄድ ነበር? እሷ የሌለችበት ሀሳብ፣ እሷ የሌለችበት መንገድ፣ የሌለችበት ነገ..እንደሌለ እኮ ያውቃል።

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን ሐምሌ 21/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *