ሀገር በመንግሥት ሲተዳደር፤ ሕዝብ ለመንግሥት ግብር እንዲከፍል ይገደዳል:: መንግሥት ከሕዝብ የሰበሰበውን ገንዘብ መልሶ በተለያየ መልኩ ለሕዝብ ያውላል:: በዚህ ሂደት ሀገር ያድጋል፤ የዜግች ሕይወት ይለወጣል:: ሆኖም አንዳንድ ጊዜ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የሕዝብ ገንዘብ ለብክነት ይጋለጣል:: ይህንን ብክነት ለመከላከል እና ለመቀነስ ዋና ኦዲተርን የመሳሰሉ ተቋማት ክትትል እና ቁጥጥር ያደርጋሉ:: ቁጥጥሩ ተጠያቂነትን በማስፈን ብክነትን ቢቻል ለማስቆም ካልሆነም ለመከላከል ጥረት ይደረጋል:: ይህንን ተግባር በግንባር ቀደምትነት በኃላፊነት እየመሩ ከሚገኙ ተቋማት ውስጥ የፌዴራል ዋና ኦዲተር አንዱ ነው::
የፌዴራል ዋና ኦዲተር የመንግሥትና ሕዝብ ሀብት ለታሰበለት ዓላማ መዋሉን ያረጋግጣል፤ የተቋማትን አሠራር ይፈትሻል፤ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦም ግኝቱን ያስረዳል::
ሆኖም ዋናው ኦዲተር ለቁጥጥር በሚያመች መልኩ በትጋት ሥራዎችን ቢያከናውንም፤ የተጠያቂነት ሥርዓትን ከማረጋገጥ አንጻር ክፍተት ስለመኖሩ ቅሬታዎች ይደመጣሉ:: በሌላ በኩል የፌዴራል ዋናው ኦዲተር የተጣለበትን ኃላፊነት ተከትሎ ሥራዎችን ሲያከናውን፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተጠያቂነትን የማረጋገጥ ግዴታ እንዳለበት ይነገራል::
በዋናነት የዋና ኦዲተርን ሥራ በመደገፍ፤ ተጠያቂነትን በማስፈን አስተዳደራዊ እርምጃዎች እንዲወሰዱም ሆነ የሕግ ተጠያቂነት እንዲኖር ሥራዎች ምን ያህል በመከናወን ላይ ናቸው? ለምን ተደጋጋሚ የኦዲት ግኝቶች ያጋጥማሉ? ተደጋጋሚ ትልልቅ ግኝቶች ያለባቸው ተቋማት እነማን ናቸው? ዋና ኦዲተር ተጠያቂነትን ለማስፈን የተሠጠው ሥልጣን ምን ያህል በቂ ነው? የሚሉ እና ሌሎች ተያያዥ ጥያቄዎችን ለፌዴራል ዋና ኦዲተር በማቅረብ ከዋና ኦዲተሯ ወይዘሮ መሠረት ዳምጤ ጋር ቆይታ አድርገናል:: መልካም ንባብ::
አዲስ ዘመን፡– ዋናው ኦዲተር በሕግ የተሰጠው ሥልጣንና ኃላፊነት ምን ይመስላል?
ወይዘሮ መሠረት፡– ዋናው ኦዲተር በሕግ የተሠጠው ሥልጣን እና ኃላፊነት የሚጀምረው ከሕገመንግሥቱ ነው:: አንቀፅ 101 ንዑስ አንቀፅ ሁለት መሠረት እንዲሁም እንደገና ዋናው ኦዲተርን ለማቋቋም በወጣው አዋጅ ቁጥር 982/2008 አንቀጽ 5 ከንዑስ አንቀጽ 1 እስከ 15 የዋናው ኦዲተር ሥልጣን እና ኃላፊነት የሥልጣን ዘመንን ጨምሮ ሁሉም ነገሮች በዝርዝር ተቀምጠዋል:: በተሻሻለው አዋጅ ቁጥር 1146/2011 አንቀጽ 2 መሠረት የፌዴራል ዋናው ኦዲተር የተሰጠው ሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ኦዲት እያደረገ እና እያስደረገ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና ድርጅቶችን የኦዲት ሪፖርት ለምክር ቤቱ ያቀርባል ይላል::
ኦዲት የሚያደርገው በምክር ቤቱ የፀደቀው በጀት ሲሆን፤ ይህንኑ በጀት እየመረመረ ሪፖርት ለፓርላማው የማቅረብ ግዴታ አለበት:: ስለዚህ ኃላፊነታችን የሚነሳው ከሕገመንግሥቱ ነው:: በአጠቃላይ የሥራችን ሒደት ሲታይ እኛ ኦዲቶችን እየሠራን የተገኘውን ውጤት ለፓርላማው እናቀርባለን:: በአጠቃላይ ይገለፅ ከተባለ በዋናነት የእኛ ተግባር እና ሥልጣን መንግሥት የበጀተውን በጀት በትክክለኛ ቦታው ላይ መዋሉን ኦዲት አድርጎ ለፓርላማው ማቅረብ ነው:: ይህንኑ በማከናወን ላይ እንገኛለን::
አዲስ ዘመን፡– የኦዲት አቅማችሁን ከማሳደግ አንጻር ቴክኖሎጂን በመጠቀም ዙሪያ በምን ደረጃ ላይ ነን ትላላችሁ?
ወይዘሮ መሠረት፡– ቴክኖሎጂን ከመጠቀም አንፃር ዋናው ኦዲተር ላይ ያለ የመረጃ (ዳታ) ማዕከል የዓለም አቀፍ መስፈርትን ባሟላ መልኩ የተደራጀ ነው:: ይህ ማዕከል አጠቃላይ የመረጃ ልውውጦችን በተቻለ መጠን ወረቀት አልባ የማድረግ ሃሳብን የያዘ ነው:: ውስጥ ለውስጥ የምንላላክበት ኮርፖሬት የምንለው መረጃ መለዋወጫ አለን:: በኢሜል እና በዌብ ሳይትም የመረጃ ልውውጥ የምናደርግ ሲሆን፤ ለምሳሌ የሰው ሀብትን (ኤች አር ማኔጅመንት) መጥቀስ ይቻላል:: ከሠራተኞች ፈቃድ ጀምሮ የሚሠራው ወረቀት ሳይሆን ወረቀት አልባ በሆነ መልኩ በሲስተም ነው::
የመዝገብ ቤት ማኔጅመንት ሥራ የሚሠራው በተመሳሳይ መልኩ በቴክኖሎጂ ነው:: ኦዲተሮች ራሳቸውን ከጊዜው ጋር የሚያሳድጉበት የኢ-ለርንኒግ ሥርዓት አለን:: በርከት ያሉ ሲስተሞች አሉን:: እነዚህን ወደ ፊትም እናጠናክራቸዋለን:: ሌላም ከኦዲት ተደራጊዎች ጋር የምንገናኝበት ኦዲት ትራኪንግ የምንለው ሲስተም አለ:: እርሱን ጀምረነዋል:: ወደ ፊት አጠናክረን እንቀጥላለን::
ቴክኖሎጂ ላይ ትኩረት በማድረግ 108 ለሚሆኑ የፌዴራል ተቋማት ስልጠና ለመስጠት አቅደናል:: ኦዲቱን ሠርተን ከላክንላቸው በኋላ ያሉትን ለውጦች ለማየት የምንገናኘው በሲስተም ብቻ ነው:: በተጨማሪ ኦዲተሮቻችንን ካሉበት ሆነው የምንከታተልበትም በቴክኖሎጂ የተደገፈ ሲስተም አለን:: በእርሱ ላይም ለኦዲተሮቻችን ሥልጠና ሰጥተናል:: በርከት ያሉ ሲስተሞች አሉ:: ስለዚህ በአጠቃላይ ሥራዎችን በቴክኖሎጂ አስደግፈን ለመሥራት ጥረት በማድረግ ላይ ነን ማለት ይቻላል::
አዲስ ዘመን፡– ኦዲትን ለማከናወን እና ግኝቱን ተከትላችሁ ተቋማትን በተጨባጭ ተጠያቂ ለማድረግ የተሰጣችሁ ሥልጣን ምን ያህል በቂ ነው?
ወይዘሮ መሠረት፡– በዓለም ውስጥ ሦስት ዓይነት ሲስተሞች አሉ:: በዓለም ፓርላሜንታል፣ ፕሬዚደንሺያል እና ሃይብሪድ የተባሉ ሲስተሞች አሉ:: እንደነብራዚል ያሉ ፕሬዚዳንታዊ ሥርዓትን የሚከተሉ ሀገራት የሚመሩት በኮርት ሲስተም ነው:: ኢትዮጵያ ኮርት ሲስተም የምትከተል አይደለችም:: ምክንያቱም ኢትዮጵያ እንደበርካታ ሀገራት በተለይም እንደብዙ አፍሪካውያን እና አውሮፓዎችም ሳይቀሩ የምንከተለው ፓርላሜንታዊ ሥርዓትን ነው:: ስለዚህ የመንግሥት መዋቅራችን የሚፈቀደው ዋናው ኦዲተር ሪፖርትን ለምክር ቤት እንዲያቀርብ ብቻ ነው::
ዋናው ጉዳይ ተጠያቂነትን የማረጋገጥ ሥልጣን ለዋናው ኦዲተር መሠጠት አለመሠጠቱ አይደለም:: መሠረታዊው ጉዳይ ግዴታ ያለበት ሁሉ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ከተወጣ ተጠያቂነትን ማረጋገጥ ይቻላል ብዬ አስባለሁ:: እኛ ሠርተን የኦዲት ግኝቱን የምናቀርብለት አካል፤ በአግባቡ ሥልጣኑን እና ኃላፊነቱን ከተወጣ ተጠያቂነትን ማረጋገጥ ከባድ አይሆንም:: ስለዚህ ሊሰመርበት የሚገባው ዋናው ጉዳይ እኛ ኃላፊነታችንን የምንወጣውን ያህል ሁሉም የተሰጠውን ሥልጣን በኃላፊነት ቢወጣ ተጠያቂነትን በቀላሉ ማረጋገጥ እንደሚቻል ነው::
አዲስ ዘመን፡– የ2014 ዓ.ም የኦዲት ግኝታችሁን በ2015 ዓ.ም ሰኔ 20 አቅርባችኋል:: በአጠቃላይ ግን ግኝታችሁ ምን ይመስላል?
ወይዘሮ መሠረት፡– ከላይ እንደገለፅኩት የእኛ ሥልጣን የሚነሳው ከሕገመንግሥቱ ነው:: ከዚያ በመነሳት ዝርዝር ሥልጣናችን በአዋጃችን ተቀምጧል:: በተጣለብን ግዴታ እና በተሰጠን ሥልጣን መሠረት የፋይናንሻል እና ሕጋዊ ኦዲት እንሠራለን:: የክዋኔ እና የቴክኖሎጂ ኦዲት እናከናውናለን:: እኛ ኦዲት እናደርጋለን:: በተጨማሪ ግን ለሌሎችም ውክልና ሠጥተን ኦዲት እናስደርጋለን:: በዋናነት የምንሠራቸው ሥራዎች እነዚህ ናቸው::
ከዚህ አንፃር በ2014 ዓ.ም በጀት ዓመት ወደ 165 የሚሆኑ የፌዴራል ባለበጀት ተቋማትን ኦዲት ለማድረግ በዕቅድ ይዘናል:: እነዚህ የፋይናንሻል እና ሕጋዊ ኦዲት ላይ በዕቅድ የተያዙ ናቸው:: በተጨማሪ የክዋኔ ኦዲት ደግሞ 23 አዲስ እና ከባለፈው ዓመት የዞረ አንድ ኦዲት አለ::
ሌላው የክትትል ኦዲት ስድስት ይዘናል:: ልዩ ኦዲት በዕቅድ ስምንት የያዝን ሲሆን፤ የፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ጉዳይ ለማረጋገጥ በገንዘብ ሚኒስቴር ከዓለም ባንክ ጋር የገባቸው ስምምነቶች አሉ፤ እነዚህ በድጋፍ እና ድጎማ ዳይሬክቶሬት ውስጥ የሚሠሩ ኦዲቶች ሲሆኑ 265 ተቋማት እና 50 የማረጋገጫ የማጠቃለያ ሥራዎችን ለማከናወን በዕቅድ ይዘናል::
ከዚህ አንፃር አፈፃፀማችን ሲታይ በዕቅድ ከያዝናቸው የፋይናንሻል እና ሕጋዊ ኦዲት ከ165 ተቋማት እና ከ55 ቅርንጫፎች ውስጥ 164 ተቋማት እና 52 ቅርንጫፎች ላይ በመሥራታችን አፈፃፀማችን 99 ነጥብ 4 በመቶ መሆን ችሏል:: አንዱም ቢሆን የጎደለው በፀጥታ ችግር ምክንያት ደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ መድረስ ባለመቻላችን ነው::
የክዋኔ ኦዲት ደግሞ የነበረውን አንዱን ጨምረን ከአዲሶቹ ጋር 24ቱ ላይ ሠርተናል:: የክትትል ኦዲት ለማድረግ የያዝነው ስድስት ተቋማትን ለማድረግ ነበር፤ አሁን ደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ ስምንት ሆነዋል:: በአጠቃላይ ወደ 32 ኦዲቶችን ሠርተናል::
በድጋፍ እና ድጎማ የሚሠሩት ላይ በአጠቃላይ ወደ 390 የሚሆኑ ተቋማትን ሠርተናል:: በተጨማሪ ልዩ ኦዲት ላይ በዕቅድ ስምንት ይዘን የሠራነው ግን በአስራአንድ ተቋማት ላይ ነው:: ይህ ከዕቅዳችን በላይ ነው::
ወደ እያንዳንዱ ግኝት ስንሔድ መጀመሪያ ከካሽ ስንጀምር ነቀፌታ የሌለባቸው የተባሉት በ2013 ዓ.ም 51 ነበሩ፤ አሁን ግን ወደ 73 ደርሰዋል:: ከጥቂት ጉድለቶች በስተቀር አጥጋቢ ሆነው ተገኙ የምንላቸው ባለፈው ዓመት 73 ተቋማት ነበሩ፤ ዘንድሮ 66 ናቸው:: አብዛኞቹ ተቋማት ላይ ኦዲት ስናደርግ ተቀባይነት የሚያሳጣ የሚባሉት ባለፈው ዓመት 39 ነበሩ፤ ዘንድሮ ግን 19 ናቸው::
በመረጃ ላይ በተመሠረተ ኦዲት ተቀባይነት የሚያሳጣ አስተያየት የተሰጣቸው ቢኖሩም፤ አንዳንድ ሀገራዊ የደህንነት ተቋማት ካለባቸው ሀገራዊ ደህንነት ምስጢር ጋር ተያይዞ በኦዲት የማይነሳ ይሆናል:: ይህም ሆኖ የተወሰነው ይታያል፤ ነገር ግን አብዛኛው 75 በመቶ የሚሆነውን አላየነውም:: ስለዚህ ስላላየን ስለሁኔታው መግለፅ አንችልም እንላለን::
በሌላ በኩል አንዳንድ ተቋማት ላይ ደግሞ ተገቢው መረጃ አልቀረበም:: በዚህ ምክንያት ሰነዱን ስላላየነው ምስክርነት ወይም አቋም መውሰድ አንችልም ያልናቸው ወደ ስድስት የሚሆኑ ተቋማት ናቸው::
እያንዳንዱን የጥሬ ገንዘብ ጉድለትን በተመለከተ ደግሞ፤ በ2013 በጀት ዓመት ወደ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር ነበር:: በ2014 በጀት ዓመት ወደ 206 ሺህ ብር ወርዷል:: ይህም ቢሆን ቀላል አይደለም፤ ምክንያቱም ገንዘቡ ከካዝና የጠፋ ነው:: ይህ የግብር ከፋዩ ገንዘብ ነው:: የሀገሪቷ ገንዘብ አንድ ብርም ቢሆን መጥፋት የለበትም:: ይህም የተከሰተው በሁለት ተቋሞች ላይ ነው:: በጥሬ ገንዘብ ሂሳብ ላይ ተገቢው ቁጥጥርና ክትትል የሚደረግ መሆኑን ለማረጋገጥ ኦዲት ሲደረግ በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ብር 172 ሺህ 466 እና በሞያሌ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ብር 1 ሚሊዮን 134 ሺህ 396 በድምሩ ብር 1 ሚሊዮን 306 ሺ 863 የጥሬ ገንዘብ ጉድለት መኖሩን ለማወቅ ተችሏል::
የጥሬ ገንዘብ ጉድለት በአስቸኳይ ተመላሽ መደረግ ያለበት ነው:: ስለዚህ የተሰጣቸውን ኃላፊነት ዘንግተው ገንዘቡን ባጎደሉ ሠራተኞች ላይ አስተዳደራዊም ይሁን ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ እና በጥሬ ገንዘብ አስተዳደር መመሪያው መሠረት ተገቢው ክትትልና ቁጥጥር መደረግ እንዳለበት አሳስበናል::
ሌላ ውዝፍ ተሰብሳቢ ሒሳብን በተመለከተ በ2013 በጀት ዓመት ወደ 13 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ነበር:: 2014 በጀት ወደ 15 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ከፍ ብሏል:: እዚህ ላይ እንዲያውም ወደ ሁለት ቢሊዮን ጭማሪ አለ:: እዚህ ላይ የሚያሳየው ሰዎች ለሥራ የሚሠጣቸው ብር ሥራቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ተመላሽ ማድረግ ያለባቸውን ገንዘብ ተመላሽ እያደረጉ እንዳልሆነ አመላካች ነው:: በመመሪያ ቁጥር 4 2002 ላይ እንዲሁም መመሪያ ቁጥር 3 ላይም እንዴት መመለስ እንዳለበት በዝርዝር ተቀምጧል:: ተመላሽ መደረግ ያለበት ገንዘብ ከሰባት ቀን በላይ መቆየት የለበትም:: ነገር ግን ከአንድ ዓመት እስከ አስር ዓመት አለመመለሱን አግኝተናል::
ይህ ገንዘብ ተመላሽ ባይሆን እንኳ በአብዛኛው ሰነድ ቢቀርብለት ወደ ወጪ የሚቀየር ነው:: ሰነድ ካልቀረበበት የሚቀመጠው ተመላሽ መደረግ ያለበት ገንዘብ ተብሎ ነው:: ወደፊትም ሰነድ ካልቀረበለት ግን የወሰደ ሰው በካሽ በገንዘብ መመለስ አለበት:: ምክንያቱም ገንዘቡ ከካዝና ለተለያዩ ጉዳዮች የወጣ ገንዘብ ነው:: ይህንን የወሰደው አካል ኃላፊነቱን ወስዶ ማወራረድ አለበት:: ነገር ግን አልተወራረደም::
በሌላ በኩል ወደ 464 ሚሊዮን ደግሞ ከማን እንደሚሰበሰብ የማይታወቅ ገንዘብ አለ:: ገንዘብ መሰብሰብ እንዳለበት የሚያዙ የተቀመጡ አዋጅ እና ደንቦች አሉ:: አዋጆቹ አስገዳጅ ናቸው:: ገንዘብ የሚሰበስብ አካል እነዚህን አዋጆች እና ደንቦች መሠረት ባለማድረጉ ወደ 86 ሚሊዮን ብር አልተሰበሰበም:: ይህ በገቢዎች መስሪያ ቤት በ11 ቅርንጫፎች የታየ ነው:: ይህን ገንዘብ እነርሱም ያውቁታል፤ ግኝቱን ያወጣነው በወቅቱ መሰብሰብ ነበረበት ብለን ነው:: ነገር ግን መሰብሰብ ከነበረበት ጊዜ አልፏል:: ይህ ገንዘብ ከአንድ ዓመት እስከ ስድስት ዓመት ያሳለፈ ሲሆን፤ ተሰብስቦ ለልማት መዋል ነበረበት::
አዲስ ዘመን፡– የ2014 ኦዲት ከ2013 ዓ.ም አንፃር ሲታይ በምን ደረጃ ላይ ነው? አነፃፅረው ይግለፁልን::
ወይዘሮ መሠረት፡– ውዝፍ ተሰብሳቢ ሒሳብን በተመለከተ በ2013 በጀት ዓመት ወደ 13 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ነበር:: 2014 በጀት ወደ 15 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ከፍ ብሏል:: በ2014 በገቢዎች ሚኒስቴር የከፍተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ብር 4 ቢሊዮን 835 ሚሊዮን 679ሺህ 269፣ በጉምሩክ ኮሚሽን የቃሊቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ብር 2 ቢሊዮን 542 ሚሊዮን 237ሺህ 409፣ የምዕራብ አዲስ አበባ ገቢዎች ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ብር 1 ቢሊዮን 846 ሚሊዮን 488ሺህ 725፣ ምሥራቅ አዲስ አበባ ገቢዎች ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ብር 973 ሚሊዮን 477 ሺህ 970 እና አዲስ አበባ መካከለኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ብር 968 ሚሊዮን 111 ሺህ 114 ዋና ዋናዎቹ ናቸው::
የሚሰበሰበው ገቢ መንግሥት የሚያከናውናቸውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት አገልግሎቶችን ለማስፋፋት ወሳኝ ነው:: ስለዚህ የገቢ አሰባሰቡ ትኩረት ተሰጥቶት እንዲሠራ ያልተሰበሰበውም ውዝፍ ገቢ መሰብሰብ አለበት የሚል እምነት አለን::
ሌላው ከወጪ ጋር በተያያዘ ነው:: ወጪ የምንላቸው በጣም ብዙ ናቸው:: የተቀመጡ አዋጆች ደንቦች አሉ:: በሕግ መሠረት የማይከፈሉ ወጪዎች አሉ:: እነዚህን ስናይ ሳይሟላ የሚከፈል ወጪ፣ በብልጫ የሚከፈል ወጪ፣ ተገቢው ማስረጃ ሳይያዝ የሚከፈል ወጪ እያልን መከፋፈል እንችላለን:: ደንብና መመሪያን ሳይከተሉ የሚወጣ ወጪም አለ::
እዚህ ላይ በወጪ ለተመዘገቡ ሒሳቦች የተሟላ ማስረጃ መቅረቡን ለማረጋገጥ ኦዲት ሲደረግ፤ በ52 መስሪያ ቤቶች በድምሩ ብር 307 ሚሊዮን 549 ሺህ 308 የተሟላ የወጪ ማስረጃ ሳይቀርብ በወጪ የተመዘገበ መሆኑ በኦዲት ተረጋግጧል:: የተሟሉ ማስረጃዎች ሳያቀርቡ ወጪ ከመዘገቡ መስሪያ ቤቶች መካከል አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ብር 124 ሚሊዮን 402ሺህ 770፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ብር 65 ሚሊዮን 817 ሺህ 679፣ የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ብር 64 ሚሊዮን 512 ሺህ፣ በጉምሩክ ኮሚሽን የሰመራ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ብር 7 ሚሊዮን 918 ሺህ 972፣ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ብር አምስት ሚሊዮን 657 ሺህ 691 እና የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ብር 4 ሚሊዮን 883 ሺህ 589 ዋና ዋናዎቹ ናቸው::
ወጪዎች መከፈል የሚገባቸው የተሟላ ማስረጃ ሲቀርብ ብቻ ነው:: በመሆኑም ማስረጃ ላልቀረበባቸው የወጪ ሂሳቦች የተሟላ ማስረጃ እንዲቀርብና ለወደፊቱም የተሟላ ማስረጃ ሳይቀርብ የወጪ ሂሳብ እንዳይመዘገብ በየጊዜው ተገቢ ቁጥጥር መደረግ አለበት የሚል እምነት አለን::
በሌላ በኩል የግዢ ሕጉንም ከአንድ እስከ ስድስት ያሉትን ነጥቦች ሳይከተሉ የተፈፀሙ ግዢዎችም አሉ:: ይሔ ሲታይ የ2013 ወደ 4 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ነበር:: በዚህ በ2014 ዓ.ም የዕቃና አገልግሎት ግዥ በመንግሥት ደንብና መመሪያ መሠረት የተፈፀመ መሆኑን ለማረጋገጥ ኦዲት ሲደረግ፤ በ82 መስሪያ ቤቶች ብር 592 ሚሊዮን 454 ሺህ 328 የመንግሥትን የግዢ አዋጅ፣ ደንብና መመሪያ ያልተከተለ ግዢ ተፈጽሞ ተገኝቷል::
ካልተከተሏቸው የግዥ አዋጅ ደንብና መመሪያዎች መካከልም ያለጨረታ በቀጥታ ግዥ በመፈጸም ብር 335 ሚሊዮን 770 ሺህ 566፣ መስፈርቱ ሳይሟላ በውስን ጨረታ የተገዛ ብር 41 ሚሊዮን 750 ሺህ 226 ፣ ግልጽ ጨረታ መውጣት ሲገባው በዋጋ ማወዳደሪያ የተፈጸመ ግዥ ብር 112 ሚሊዮን 419 ሺህ 779፣ የዋጋ ማወዳደሪያ ሳይሰበሰብ በቀጥታ የተፈጸመ ግዥ ብር 19 ሚሊዮን 049 ሺህ 484 እና ሌሎች የግዥ ሂደት ያልተከተሉ ብር 83 ሚሊዮን 464 ሺህ 271 እና ብር 1 ሚሊዮን 699ሺህ 565 ከግዥ ኤጀንሲ ፈቃድ ሳይገኝ የተፈጸሙ ግዥዎች መሆናቸውን ለማወቅ ችለናል::
ከግዥ አዋጅ፤ ደንብና መመሪያዎች ውጪ ግዥ ከፈጸሙ መሥሪያ ቤቶች መካከል የጉምሩክ ኮሚሽን ዋናው መሥሪያ ቤት ብር 66 ሚሊዮን 371 ሺህ 195፤ የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ብር 61 ሚሊዮን 225ሺህ 545፣ የሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ብር 53 ሚሊዮን 71 ሺህ 916፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አገልግሎት ብር 45 ሚሊዮን 24 ሺህ 888፣ የአፍሪካ ልህቀት አካዳሚ ብር 36 ሚሊዮን 216 ሺህ 480 እና የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ 29 ሚሊዮን 383 ሺህ 900 ብር ከመመሪያ ውጪ ግዢ ከፈፀሙት መካከል ዋና ዋናዎቹ ናቸው።
ግዥው መንግሥት ባወጣው የግዥ አዋጅ፣ ደንብና መመሪያ መሠረት መፈጸም እንዳለበት ለምክር ቤቱ ሪፖርት ከማቅረብ በተጨማሪ ለየተቋማቱ አሳስበናል:: በአጠቃላይ ሲታይ ግን በ2014 ወደ 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ወርዷል:: በሒደት መሻሻሎች አሉ:: እኛም የምንመክረው እንዲሻሻል እና እንዲያውም የምንፈልገው ወደ ዜሮ እንዲመጣ ነው::
ሠራተኛ ሳይኖር እና ሠራተኞች ከሥራ ከወጡ በኋላ በአግባቡ መረጃ ሳይያዝ 362 ሺህ 662 ብር ተከፍሏል:: ይህ በሁለት መልኩ የተፈፀመ ነው:: አንደኛው ሠራተኛው አለመኖሩን የሥራ ክፍሉ ለፋይናንስ ክፍሉ ባለማሳወቁ ሲሆን፤ ሌላኛው ደሞዝ ቀድሞ በመውጣቱ ሠራተኛው ከሥራ ቢለቅም ቀድሞ ላልሠራበት ደሞዝ ሲከፈለው ነው:: ይህ በ16 መሥሪያ ቤቶች ያጋጠመ ነው::
ከበጀት በላይ የከፈሉትን እንይ ብለን ስንነሳ በቅድሚያ ከበጀት በላይ ስንል ምን ማለት ነው የሚለውን ማየት አለብን:: እዚህ ላይ ሁለት ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ:: አንደኛው በጀት የሚመደበው በዕቅድ መሆን አለበት:: እኛ የምንጠቀመው ፕሮግራሚንግ በጀት ነው:: በአንድ ፕሮግራም ውስጥ ሒሳብ አለ:: በአንዱ ፕሮግራም ውስጥ የተቀመጠ የገንዘብ መጠን ለምሳሌ ለአበል ለብቻው በጀት አለው፤ ለነዳጅም በተመሳሳይ መልኩ ለብቻው በጀት አለው፤ አበል ላይ ኖሮ ነዳጅ ላይ በጀት ቢያልቅ፤ የመሥሪያ ቤቱ የበላይ ኃላፊ አውቆ በጀቱን ማዘዋወር ይቻላል:: ነገር ግን ከአንዱ ፕሮግራም ወደ ሌላ ፕሮግራም፤ ማለትም ከሥልጠና ፕሮግራም ወደ ድጋፍ ፕሮግራም በጀት ማስተላለፍ ከተፈለገ ለገንዘብ ሚኒስቴር አሳውቆ ማዘዋወር ግዴታ ነው::
በሌላ በኩል ምንጩ የማይታወቅ ገቢም ሊኖር ይችላል:: አንዳንዴ ከሌለ ወይም በበጀት ከተያዘ ገንዘብ በላይ መጠቀም ይታያል:: ሲፈተሽ ከሌለ ገንዘብ በላይ መጠቀም መኖሩን ማወቅ ችለናል:: ይህ አብዛኛው የተከሰተው ዩኒቨርሲቲዎች ላይ ነው:: ይህ የሚያሳየው ዩኒቨርሲቲዎች የሚሰበስቡትን ገቢ በትክክል የሚያሳውቁበት ሁኔታ አለመኖሩን ነው:: ቁጥራቸውም ቀላል አይደለም:: ይህ የተከሰተው በ35 ዩኒቨርሲቲዎች ላይ ነው:: ዋና ዋናዎቹ ወላይታ ሶዶ 338 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ብር አለበት:: ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ 266 ነጥብ 7 ሚሊዮን፣ ሚዛን ቴፒ፣ ዲላ እና አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲም በተመሳሳይ መልኩ የማይታወቅ ገንዘብን ከተጠቀሙ ተቋማት መካከል ዋና ዋናዎቹ ናቸው:: እነዚህ ተቋማት የማያሳውቁት ገቢ አላቸው ማለት ነው::
በገቢ አሠራር ማንኛውም ተቋም ገቢውን አሳውቆ ወጪ የሚጠቀም ከሆነ በማሳወቁ የማይታወቅ ገቢ ተጠቅሟል አይባልም:: ተቋሙ ገቢውን ካሳወቀ ደግሞ ለመንግሥትም ክትትል እና ቁጥጥር ለማድረግ ይመቻል:: ስለዚህ እዚህ ላይ ጉድለት እንዳለ ያመለክታል:: ከሌለ ገንዘብ በምንም መልኩ ከበጀት በላይ አይወጣም::
የበጀት አጠቃቀም ሲታይ ደግሞ በ2013 በጀት አመት ከአንድ ቢሊዮን ያነሰ ነበር:: እንዲያውም 645 ሚሊዮን ነበር:: በ2014 በጀት ዓመት ግን 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ደርሷል:: በጀትን አለመጠቀምም ኦዲት የሚደረግ ሲሆን፤ በጀት አልተጠቀሙም የምንለው ከአስር በመቶ በታች ካልተጠቀሙ እንደግኝት አይቀመጥም:: ለምሳሌ ከተያዘው ገንዘብ 60 በመቶውን ተጠቅመው ቀሪ 40 በመቶ ከሆነ እንደግኝት ይጠቀሳል:: ከተደለደለው በጀት ከ10 በመቶ በላይ ያልተጠቀሙት ሲታዩ አምና ብዙዎቹ በጣም ተጠቅመውበት ስለነበር ግኝቱም አነስተኛ ነበር:: አምና 5 ነጥብ 8 ቢሊዮን ነበር:: ዘንድሮ ግን በርከት ያለ ነው:: ወደ 35 ቢሊዮን ብር ደርሷል:: ይሔ ችግሩ የአንድ አካል ብቻ ላይሆን ይችላል:: ተደራራቢ የሀገሪቷ ሁኔታ እና ሌሎችም ምክንያቶች ይኖራሉ:: እኛ ግን የምንመክረው በጀት አቅማችንን አይተን መሆን አለበት የሚል ነው::
ተመላሽ ገንዘብን በተመለከተ አምና 2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ይመለስ ብለን አስተያየት ሠጥተን ነበር:: አንድ ቢሊዮን 29 ሚሊዮን አካባቢ ተመልሷል:: ነገር ግን ይህ እንዳሰብነው አይደለም:: ይህ እንዲፈጸም ሰፊ ክትትል እና ቁጥጥር ስናደርግ ነበር:: ብዙ ይመለሳል ብለን ተስፋ አድርገን እንዳሰብነው አልሆነም:: በ2014 በጀት ዓመት አምስት ቢሊዮን ሲሆን በ2013 በጀት ጋር ተደምሮ ወደ ስድስት ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር መመለስ አለበት ብለን አስተያየት ሰጥተንበታል::
አዲስ ዘመን፡– በየዓመቱ ተደጋጋሚ የኦዲት ግኝቶች አሉ:: ሳይታረሙ በድጋሚ ይገለፃሉ:: ይህ የሚሆነው ለምንድን ነው? የቆዩ የኦዲት ጉድለቶች የማይታረሙት ለምንድን ነው?
ወይዘሮ መሠረት፡– ተመሳሳይ ግኝቶች የሚኖሩት ሁኔታዎች አስገድደዋቸው፣ በአቅም ችግር ምክንያት ወይም ትኩረት ባለመስጠት የሚመጡ ናቸው ተብሎ ይታሰባል:: በዘንድሮ አመት አመራሮች ትኩረት ሲሰጡ በተጨባጭ ለውጥ መጥቷል:: ትልልቅ መሻሻሎች አሉ:: ይህ በአመራሩ ትኩረት የመጣ ነው:: ታቅደው ከተሠሩ እና ትኩረት ተሰጥቶ ከተሔደባቸው ነገሮች በሙሉ መስተካከል የሚችሉ ናቸው:: የማይስተካከል ነገር የለም:: ሁሉም ይስተካከላል:: የአመራር ቁርጠኝነት እና ተጠያቂነቱ ጠንከር ቢል ደግሞ እነዚህ ነገሮች የማይስተካከሉበት ምክንያት የለም::
አዲስ ዘመን፡– አብዛኞቹ ተቋማት ላይ የሚታዩ የኦዲት ግኝቶች ምን ምን ናቸው? ግኝቱ ተቀባይነት የሚያሳጣቸው እነማን ናቸው?
ወይዘሮ መሠረት፡– ሁለት ዓይነት ነው:: አንደኛው እኛ የምናየው የፋይናንሻል እና የኮምፒሊያንት ኦዲት ማንዋል አለ:: የፋይናንሻል ስቴትመንቱ ሂደቱን ተከትለን በተገቢው መልኩ ስለመከናወኑ እናያለን:: ኮምፕሊያንት የሚባሉት ደግሞ በአብዛኛው የሕግ ጥሰቶች ናቸው:: ስለዚህ የምናየው የፋይናንሻል ስቴትመንቱን እና የሕግ ጥሰቶችን ነው:: ለምሳሌ ሕግን ሳይከተሉ ግዢ መፈፀም የመሳሰሉ ከላይ የጠቀስኳቸው የሕግ ጥሰቶች በተቋማት ላይ የሚገኙ የኦዲት ውጤቶች ናቸው:: አብዛኞቹ የኦዲት ግኝቶች የሚገኙት በየትኛዎቹ ተቋሞች ላይ ነው? የሚለውን ለመመለስ ያስቸግራል:: ለምሳሌ ኦዲት ሲደረግ በርካታ ተሰብሳቢ ያለበት ተቋም አለ:: ተቀባይነት የሚያሳጣ አስተያየት ሊሰጥበት አይችልም:: ይህንን መጥቀስ መልሱን የተዛባ ያደርገዋል::
አዲስ ዘመን፡– ከፍተኛ የኦዲት ግኝት የተመዘገበባቸው ተቋማት ላይ ሊወሰድ የሚገባው እርምጃ ምንድን ነው?
ወይዘሮ መሠረት፡– በተደጋጋሚ ክፍተት ያለባቸውን ለፓርላማው ሪፖርት ስናቀርብ ለመንግሥት ወጪ አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሕዝብ እንዲወያይበት (ሂሪንግ እንዲካሔድበት) ሪፖርት የምንልከው እኛ ነን:: በተለይ ተደጋጋሚ ክፍተት ያለባቸውን እየለየን እየሠጠን ነው:: አምና ቡሌሆራ ዩኒቨርሲቲ በተደጋጋሚ ብዙ ግኝት የታየበት ዩኒቨርሲቲ ነው:: እየተጠሩ እየተጠየቁ ነበር:: በተደጋጋሚ ክፍተት የተገኘባቸው ተቋማት አብዛኛዎቹ አመራሮቻቸው ተቀይረዋል:: አሁን ያሉት አዳዲስ አመራሮች ናቸው::
ሰፊ የኦዲት ግኝት ሲያጋጥም ለገንዘብ ሚኒስቴርም ለይተን እናሳውቃለን:: እኛ በሰጠነው አስተያየት በ39 ተቋማት ላይ ለፋይናንስ ኃላፊዎችና ለኃላፊዎች የገንዘብ ቅጣት እና ሌሎች ማስጠንቀቂያዎችን ሰጥቷል:: ገንዘብ ሚኒስቴር ማስጠንቀቂያውን የሰጠው የእኛን አስተያየት መሠረት በማድረግ ነው:: በተጨማሪ አምና ተቀባይነት የሚያሳጣ አስተያየት የሰጠንባቸውን 14 ተቋማት ለመንግሥት ወጪ አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በማሳወቃችን ፤ ማስጠንቀቂያ እና የገንዘብ ቅጣት ተቀጥተዋል:: ይሔ ሆኗል፤ ነገር ግን በቂ ነው ወይ የሚል አስተያየት ከቀረበ ገና የሚቀር ነገር እንዳለ መካድ አይቻልም::
አንዳንዶቹ ተቋማት ደግሞ ኦዲት እየተደረገ እዛው የሚስተካክሉም አሉ:: ግኝቱን ስናሳውቃቸው ወዲያው የሚያስተካክሉ ተቋማት አሉ:: ለምሳሌ የተመላሽ አሰባሰብ ላይ ኢንሳ እንዲሁም ሌሎችን ጨምሮ ወደ አራት ተቋማት መልሱ ያልናቸውን ገንዘብ መልሰዋል:: ይህ ለውጥ ነው:: ሪፖርቱ ከወጣ በኋላ ተመላሽ መሆን አለበት ያልነው ገንዘብ ገቢዎች ላይ ከ13 ሚሊዮን ውስጥ ወደ 900 ሺህ ተመልሷል:: ያንን አይተናል:: ለውጦች አሉ:: ከሪፖርቱ በኋላ በርካታ ተቋማት እየሻሻሉ መሆኑን እና የተገኘውን ለውጥ እየገለፁ ነው:: ነገር ግን ተጠናክሮ መቀጠል አለበት::
አዲስ ዘመን፡– የኦዲት ሪፖርት ሲቀርብ ሁሉም ተቋማት ፓርላማ መገኘት አለባቸው፤ ነገር ግን እየተገኙ አይደለም:: በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
ወይዘሮ መሠረት፡– ይሔን ጥያቄ መመለስ ያለበት ፓርላማው ነው:: የእኛ ኃላፊነት ሪፖርቱን ማቅረብ ብቻ ነው:: ፓርላማው ላይ ዋናው ኦዲተር ሪፖርት ሲያቀርብ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በስተቀር ሁሉም ሚኒስትሮች መገኘት እንዳለባቸው በሕግ ተቀምጧል:: ለእነርሱም ቢኖሩ በቀጥታ ግኝቱን ማዳመጥ ይችላሉ:: የ2014 የኦዲት ግኝትን ስናቀርብ ወደ 10 ሚኒስትሮችን አይቻለሁ:: ነገር ግን ዋናው ጉዳዩ ሁሉም ሚኒስትሮች እና የሥራ ኃላፊዎች እንዲገኙ ፓርላማው ራሱ መከታተል አለበት::
አዲስ ዘመን፡– ኦዲተሮቻችሁ ምን ያህል ከሙስና የፀዱ ናቸው? ሙስናንን ለመከላከል የምትችሉበት ምን ዓይነት መንገድን ቀይሳችኋል?
ወይዘሮ መሠረት፡– የእኛ ኦዲተሮች አብዛኛዎቹ ከሙስና የፀዱ ናቸው:: ለሥራቸው እና ለሞያቸው ታማኝ ናቸው:: ለሕዝብ እና ለመንግሥት ታማኝ ሆነው የሚሠሩ፤ ሥራውን ለገንዘብ ሳይሆን ለሞያቸው ብለው ኃላፊነታቸውን የሚወጡ በጣም በርካታ ኦዲተሮች አሉን:: አንዳንድ ደግሞ ችግር ያለባቸው አይጠፉም:: እንደዚህ በሚሆንበት ጊዜ የራሳችንን ሠራተኞችን መከታተያ መንገድ አለን:: በቅድሚያ ኦዲተሮችን ወደ ሥራ ከመላካችን በፊት መጀመሪያ በደንብ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ እንሠራለን:: በዚህ ዓመትም ይህ ሥራ ተሠርቷል:: ከፀረ ሙስና ኮሚሽን ባለሞያ አምጥተን ሁሉም ሥልጠና እንዲያገኙ አድርገናል::
ኦዲተሮቹ ሳያውቁ እነርሱ ላይ ክትትል የሚያደርግ ባለሞያ እንልካለን:: በ25 ዩኒቨርሲቲዎች እና በአራት ፌዴራል ተቋማት በድብቅ ክትትል አድርገናል፤ በመጨረሻም ሲከታተሉ የነበሩ ግኝታቸውን አውጥተውልናል:: የእነርሱን እና በሌላ በኩልም ያገኘነውን መረጃ አጣምረን ከቀላል እስከ ከባድ እርምጃ ወስደናል:: በዚህ ላይ ምንም ድርድር የለም:: ምክንያቱም ዋናው ኦዲተር ተበላሸ ማለት አስቸጋሪ ነው:: ትልቅ ዕምነት የተጣለበት ተቋም በመሆኑ፤ አደጋው ቀላል አይደለም::
ከላይ እንደጠቀስኩት ግንዛቤ እንፈጥራለን:: ምክንያቱም ከመቅጣት ይልቅ በማስተማር እናምናለን:: በተጨማሪ አንድ ኦዲተር ኦዲት ለማድረግ ሲወጣ የሚፈርማት የሥነምግባር መመሪያ (ኮድ ኦፍ ኤቲክስ) አለ:: ለሞያው ታማኝ ለማድረግ በእኛ በኩልም ኦዲት በሚደረገው ተቋም ውስጥ ቤተሰብ ካለው ኦዲት እንዳይደረግ እናደርጋለን:: እናም ክትትሉ ጠበቅ ያለ ነው::
አዲስ ዘመን፡– በጥቆማ ኦዲት የምታደርጓቸው ተቋማት አሉ?
ወይዘሮ መሠረት፡– አዎ! በጥቆማ ኦዲት እናደርጋለን:: በርካታ በሰነድ ተደግፈው የሚመጡ ጥቆማዎች አሉ:: የበጀት ዓመቱ ከሆነ እዚያው ያሉት ኦዲተሮች እንዲሠሩት እናደርጋለን:: የቆየ ኦዲት ከሆነ ግን ተራ በማስያዝ ልዩ ኦዲት እናደርጋለን::
አዲስ ዘመን፡- የኦዲተሮች ብቃት እና አቅም እንዴት ይገለጻል ?
ወይዘሮ መሠረት፡– ያው የእኛ ኦዲተሮች በሀገሪቱ ያሉ ዩኒቨርሲቲዎች ያፈሯቸው ናቸው:: ነገር ግን የምናስገባቸው ፈትነን ነው:: ለየት የሚያደርገው የራሳችንን ፈተና መፈተንን ጨምሮ ሥልጠና እንሠጣለን:: እያንዳንዱ ምደባ የሚካሔደው በአቅም ነው:: አንድ ሰው አቅም ካለው እና ከቻለ በሚገባው ቦታ ይመደባል:: አቅምን መሠረት አድርገን እናሳድጋለን:: ሆኖም ብዙዎቹ ኦዲተሮቻችን የተሻለ አቅም ያላቸው ናቸው::
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም እጅግ አመሰግናለሁ::
ወይዘሮ መሠረት፡- እኔም አመሰግናለሁ::
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 17 ቀን 2015 ዓ.ም