‹‹እረኛ ምን አለ?›› የእረኛ ቅኔ

በድሮ ጊዜ ‹‹እረኛ ምን አለ?›› ይባል ነበር አሉ። ይህን የሚለው መንግሥት ነው፡፡ በተለይም በነገሥታቱ ዘመን ልክ ዛሬ ‹‹ዓለም እንዴት አደረች›› ተብሎ የበይነ መረብ መረጃዎችን እንደሚዳሰሰው በጥንቱ ዘመን የመረጃ ምንጭ እረኛ ሳይሆን አይቀርም፡፡ እረኛ ምን አለ? የሚባለው ግን ትኩስ መረጃ ለማግኘት ሳይሆን በሕዝቡ ውስጥ የነበረውን ስሜት ለማወቅ ነው፡፡

እረኛ በተለየ የሚፈለግበት ምክንያት ልጆች ስለሆኑ ነው፡፡ ልጆች ስለሆኑ ክፉ ደጉን ለይተው አያውቁም፤ ቤት ውስጥ ወላጆች በምሥጢር ያወሩትን ነገር በአደባባይ ሊያወጡት ይችላሉ፡፡ ምክንያቱም ያመጣውን ጉዳት አያገናዝቡም፡፡ በድሮው ጊዜ የመገናኛ ብዙኃን አውታሮች ስለሌሉ መንግሥት የሚወቀሰው በእሳት ዳር ጨዋታ ነው፡፡ የመገናኛ ብዙኃን አውታሮች አለመኖር ብቻ ሳይሆን በዘመኑ መንግሥትን በአደባባይ መውቀስም አይቻልም። ሰዎች ቤት ውስጥ ብሶታቸውን ሲያወሩ ልጆች ይሰማሉ፤ ያንን በእረኝነት ወሏቸው በእንጉርጉሮ ይናገሩታል፡፡ እረኛ ምን አለ የሚባለው ለዚህ ነው፡፡

ከዚያ ውጭ ግን እረኞች የውስጥ (የግል ስሜታቸውን)፣ የአካባቢ ችግሮችን፣ የኑሮ ሁኔታዎችን፣ የልጅነት ጨዋታዎችን በእንጉርጉሮ ሀሳባቸውን ይገልጻሉ፡፡ ወቅቱ የክረምት (የእረኝነት) ነውና እስኪ እነዚህን የእረኛ ቃል ግጥሞች እናስታውስ፡፡

ግጥም የብዙ ስሜቶች መግለጫ ነው፤ የደስታም የሀዘንም፡፡ የቃልም ሆነ የጽሑፍ ግጥሞች ለውደሳ እንደሚገጠሙ ሁሉ ለእርግማን እና ውስጣዊ ብሶትን ለመግለጽም ይገጠማሉ፡፡ እንዲህ አይነት ውስጣዊ ስሜቶች በስነ ቃል ግጥም በቀጥታ አይነገሩም፤ የሚነገሩት በዘፈን ውስጥ ነው፡፡ በነገራችን ላይ በንጉሣዊውም ሆነ በወታደራዊው (ደርግ) ሥርዓቶች አንዳንድ ዘፈን በመገናኛ ብዙኃን እንዳይተላለፍ ይታገድ እንደነበር ይነገራል፡፡ የሚታገድበት ምክንያት የሚያስተላልፈው መልዕክት የመንግሥትን ጥፋት የሚገልጽ ሲሆን ነው፡፡ በዘፈኖቹ ውስጥ በቀጥታ የመንግሥትን ስም በመጥራት ሳይሆን ቅኔ ለበስ በማድረግ ነው፤ ያም ሆኖ ግን እንዲህ ማለት ተፈልጎ ነው በሚል ይተረጎምና ይታገዳል፡፡ በእንዲህ አይነት የመንግሥት የጥርጣሬ ክልከላ መንግሥት የባሰ ወቀሳ ውስጥ ይገባል፡፡ ሕዝብ በዘፈኑ ፖለቲካዊ መልዕክት ክርክር ውስጥ ይገባል፡፡ አንዳንዱ ይሄ ነው ትርጉሙ ሲል ሌላው የለም እንዲህ ለማለት ተፈልጎ ነው ይባላል፡፡ በዚህም ምክንያት ዘፋኙ ያላሰበው ትርጉም ሊሰጥበት ይችላል፡፡ ይሄን በመፍራት ሀገርን በተቃራኒ ፆታ (በሴት) በመወከል መዝፈን የተለመደ ነበር፡፡ ይህ በስነ ቃል ብቻ ሳይሆን ለዘፈን ተብሎ በሚገጠሙ ግጥሞች ውስጥም ይገኝ ነበር፡፡

የእረኛ ስነ ቃልም እንደዚሁ ነው፡፡ ሀሳብ የሚገለጸው በሆነ ነገር በመወከል ነው፡፡ የሌላውን ብሶት ለማሰማት ራስን በቦታው በማድረግ ይገለጻል። ጭቆናን ለመግለጽ ነፃነት ናፋቂዎች ራሳቸውን የድርጊቱ ተሳታፊ ያደርጋሉ፡፡ ይህን ብሶታቸውን ለመግለጽ የሚመቻቸው ዘፈን ነው፡፡ በዘፈን ካልሆነ በቀጥታ መናገር አይችሉም፡፡ ለምሳሌ በሰው ቤት ተቀጥራ የምትሰራ ሴት ቀጣሪዎቿን ‹‹እንዲህ በደላችሁኝ!›› አትልም፡፡ ወፍጮ እየፈጨች ግን እንዲህ ብላ ትዘፍናለች፡፡

ወፍጮው ውረድ ውረድ

ቋቱ ሙላ ሙላ

በዋዛ አይገኝም የሰው ቤት እንጀራ

‹‹ቋት›› ማለት የሚፈጨው ዱቄት የሚጠራቀምበት የወፍጮ ክፍል ነው፤ በድሮ ጊዜ የነበረው የድንጋይ ወፍጮ ማለት ነው፡፡ የዚች ብሶተኛ እንጀራ ያለው በሰራችው ሥራ ብዛት ነው። አለበለዚያ ቁጣና ማመናጨቅ ይደርስባታል፡፡ ቋቱ ካልሞላ እንጀራ ላትበላ ትችላለች፡፡ እንደ እናቷ ቤት በፈለገች ጊዜ ‹‹እንጀራ ስጡኝ›› ማለት አትችልም፡፡

በተመሳሳይ በሰው ቤት ተቀጥሮ የሚሰራ እረኛ ብሶቱን የሚገልጸው በከብቶች ስም ነው፡፡ ከጓደኞቹ ጋር የሚነጋገር መስሎ ነው፡፡ እግረ መንገዱንም ነፃ መውጣትን ይሰብካል፡፡ ከድህነት ነፃ መውጣት ማለት ነው፡፡ ከድህነት ነፃ ለመውጣት ደግሞ ጠንክሮ መሥራት ማለት ነው፡፡ ለዚህም ነው እንዲህ እያለ የሚያንጎራጉረው፡፡

ከብቶችን በሏቸው ወደ ጥቁሩ መሬት

የሰው ቤት እንጀራ ይመራል እንደ እሬት

‹‹በሏቸው›› ማለት በዘፈኑ አውድ አሰማሯቸው ማለት እንጂ ደብድቧቸው ማለት አይደለም። ‹‹እሬት›› ማለት በጣም የሚመር መርዛማ ተክል ነው፡፡ እንግዲህ ቀጣሪዎች (ባለሀብቶች) በተቀጣሪዎቻቸው ላይ የሚያደርሱት ግፍ እንጀራን ከእሬት ጋር የሚያወዳድር ነው ማለት ነው። ተቀጣሪ እረኛ የቀጣሪዎቹን የቁጣ ፊት ሲያይ የሚበላው እንጀራ እንደ እሬት ይመረዋል ማለት ነው፡፡ ልጃቸው ግን እንዲህ እየተሳቀቀ አይበላም፤ ልጃቸው የቱንም ያህል ሰነፍ ቢሆን እንደፈለገው ይናገራል፣ ይሞላቀቃል፡፡ ይሄ ተቀጣሪ ግን አመመኝ እንኳን ማለት አይችልም፡፡ ከእንዲህ አይነቱ ግዞት ነፃ ለመውጣት ነው የሚያንጎራጉረው፡፡

እረኞች ብሶታቸውን የሚያቀርቡት በተለያየ ጊዜ ከሚገኙበት የኑሮ ደረጃ ጋር በማዛመድ በእንጉርጉሮ፣ በዘፈን፣ በፉከራና በቀረርቶ ነው። በውስጡ የታመቀውን ብሶትና ወደፊት ይሆናል ብሎ የሚገምተውን ችግር ከአዕምሮው አውጥቶ በመናገሩ ከችግሩ የተላቀቀ እየመሰለው ይረካል፡፡ እረኞች ብዙ ጊዜ ተቀጥረው በሚሰሩበት ቤት የሚደርስባቸውን በደል በእንጉርጉሮ ይገልፃሉ፡፡ እረኞች ከብቶችን ሩቅ ቦታ ይዘው የሚሄዱ ከሆነ በጠዋት ተነስቶ ለእነሱ ምግብ አይሰራላቸውም፡፡ በጠዋት ሳይበሉ ከብቶችን ይዘው ይሄዳሉ፡፡ ምሳ የሚላክላቸው ከራባቸውና ከደከማቸው በኋላ ነው። በዚህ ጊዜ በርሃብ አንጀቱ ቢጠበስ

የሰው ቤት እንጀራ ምን ቢጋገር ብዙ

ይርብ አይገኝም ሳይቅበዘበዙ

እያለ ብሶቱን ይገልጻል። እረኛ በአካባቢው ነዋሪ ዘንድ ዝቅ ያለ ቦታ የሚሰጠው በመሆኑ ለእረኛ ተብሎ ምግብ አይሰራም፡፡ እረኛ ቤት ያፈራውንና የተገኘውን በልቶ ይውላል፡፡ ወጥ ከቤት ውስጥ አልቆ ከሆነ በአዋዜ ወይም በድልህ ተደርጐ በደረቅ እንጀራ ይሰጠዋል፡፡ ይህ አዋዜ መደጋገሙ ያሰለቸው እረኛ የውስጡን እንደሚከተለው በእንጉርጉሮ ቅሬታና ብሶቱን ይገልፃል፡፡

ማታ በጨው በላሁ እንዲያው በደረቁ

ምሳ በጨው በላሁ እንዲያው በደረቁ

የሰው ቤት እንጀራ ይሄ ነበር ጠንቁ

ራቡና ጥሙ በዛብኝ ሁልጊዜ

የሚቀርበው ምግብ ወጥ የለው አዋዜ

እረኞች በተቀጠሩበት ቤት ውስጥ እንደቀጣሪዎች ልጆች እኩል ምግብ አይሰጣቸውም። ለእረኞች ትንሽ ለዚያውም የልጆች ትርፍራፊ ይሰጣቸዋል፡፡ በዚህ ጊዜ የከፋው እረኛ ብሶቱን ይገልፃል፡፡

እህቴ ትፍጭና እናቴ ትጋግረው

ይህን በልቷል ብላ የማትናገረው

አንቺ የሰው እናት ይብላሽ አረመኔ

ትኩሱን ለልጅሽ ያደረውን ለኔ

አንቺ የሰው እናት ጠባይሽ ወለላ

አይቡን ለልጅሽ አጓቱን ለእረኛ

እያለ ያንጎራጉራል። አይብ ቅቤያማው ወተት ሲሆን አጓት ግን ወተቱ ተነጥሮ ከሥር የቀረው ውሃማው ቅራሪ ወተት ነው፡፡ ከሰው ቤት ተቀጥሮ በችግር ምክንያት የሰው አገልጋይ በመሆኑ ያዝናል። እረኛው ቀኑን ሙሉ ከብት ሲያግድ ይውላል፡፡ በተጨማሪም ይጎለጉላል (መጎልጎል ማለት በጤፍ እርሻ ጊዜ ከእርሻው ውስጥ ቅጠላቅጠልና ሌሎች ባዕድ ነገሮችን ለቅሞ ማውጣት ማለት ነው)፣ ያርማል፣ ያጭዳል፣ ያበራያል እንዲሁም ሌሎች የቤት ውስጥ ሥራዎችን ይሰራል፡፡ ይሄን ሁሉ ደክሞም ሰዎቹ የሰራ ስለማይመስላቸው ልፋቱን በሙሉ ገደል ይከቱበታል። በዚህ ጊዜ

ውሃ ወርዶ ወርዶ መቆሚያው ዓባይ

እናት ወልዳ ወልዳ ለሰው አገልጋይ

እውሃ ቢዶሉት አይሟሟም ኩበት

አይመሰገንም የድሃ ጉልበት

በማለት ስነቃሉን ያሰማል። በተጨማሪ በአካባቢው ብዙ መሬት ያለው ነገር ግን ጉልበቱ ከመድከሙ የተነሳ መሬቱን ማረስ ያልቻለ ሰው መሬቱን ማረስ ለሚችል ሰው በመስጠት አዝመራውን እኩል ይካፈላል፡፡ እነዚህን ሰዎች የተመለከተ እረኛ ቢከፋው ጊዜ ጉልበት ካለኝ የእኩል እየሰራሁ፣ እየተዘዋወርኩ እኖራለሁ ለማለት በግጥም መልዕክት እረኞች በከብት ጥበቃ ወቅት እንደሚከተለው በዜማ ይዘፍኑታል፡፡

ሚስትም አላገባ ላሳብም አልቸኩል

የደከመ እያየሁ እገባለሁ የእኩል

እያለ ከዚህ ሁሉ ችግር ዕድሜው ለእርሻ ሲደርስ የእኩል እየሰራ መኖር እንደሚችል ይገልጻል። ግጥሙን በብዛት የሚጠቀሙት በችግር ምክንያት ኑሮ የከበዳቸው፣ ትዳር መያዝ ያልቻሉ ሰዎች ናቸው። እርግጥ ነው የሀብታም ልጅ የሆኑትም ስለማግባት ያንጎራጉራሉ፡፡ ለምሳሌ ቤተሰቦች ‹‹ሲያድግ ነው የሚያገባ›› ሲሉ የሰማ እረኛ ጉርምስና ከተሰማው እንዲህ ይላል፡፡

አፋፍ ለአፋፍ ስሄድ አገኘሁ እንኳይ

ያላደኩ እንደሆን አላገባም ወይ

እንኳይ ማለት የዛፍ አይነት ሲሆን ፍሬው የሚበላ እና በእረኞች የሚወደድ ነው፡፡ ይሄን ዘፈን በቁመታቸው አጭር ሆነው ትልቅነታቸው ያልታወቀላቸው እረኞችም ያንጎራጉሩታል፡፡ ‹‹ከዚህ በላይ የማላድግ (ቁመቴ የማይረዝም) ከሆነ ላላገባ ነው እንዴ?›› ብለው እየጠየቁ ነው፡፡ በነገራችን ላይ እረኞች ብሶታቸውን የሚገልጹት በድህነት የሚደርስባቸውን ብቻ አይደለም፡፡ ምናልባት አሳዛኝ ስለሆነ እና ችግሩም የከፋ ስለሆነ አንጀት ስለሚበላ እሱ ላይ አተኮርን እንጂ በፍቅርም ብሶታቸውን ይገልጻሉ፡፡ ፍቅር ግን እንደ ቅንጦት ስለሚታይ፤ በዚያ ላይ ድሃ እና ሀብታም፣ የተቸገረ እና ያልተቸገረ… ብሎ ስለማይለይ ከመዝናኛነት ያለፈ ብዙም ልብ አይባልም፡፡ ያም ሆኖ ግን የፍቅር ብሶትም በጥበብ ስሜትን መግለጽን ይጠይቃል፡፡ ደግሞስ ፍቅርን ተራ ነገር ያደረገው ማነው? ስለእረኞች የፍቅር ብሶትም ጥቂት እንበላችሁ፡፡

እረኞች የጉርምስና ስሜት ላይ ሲደርሱ ፆታዊ ፍላጎት ይጀምራሉ፡፡ ይሄ ማለት ተቃራኒ ፆታቸውን ለማናገር መፈለግ፣ ፆታዊ መልዕክት ማስተላለፍ ማለት ነው፡፡ ደግነቱ ግን እንደ አዋቂዎች አይደለም። አዋቂዎች በቀጥታ ለወሲባዊ ግንኙነት ሲሆን እረኞች ግን ልጅነትም ስላለ መልዕክቱን ብቻ ነው የሚያስተላልፉ፡፡ ደፍረው አይናገሩም፤ ነውርም ነው፡፡ ባል ያላትን ሴት ቀና ብሎ ማየት ትልቅ ነውር እንደሆነ ያምናሉ፡፡ ለዚህም ነው እንዲህ እያሉ ይጫወታሉ፡፡

አጋሙን ግራሩን የፈጠርከው ጌታ

ሸጋ ሸጋውን ሴት አርገው ጋለሞታ

ጋለሞታ ማለት በድሮው ትርጉሙ አግብታ የፈታች ማለት ነው፡፡ በአዋቂዎች ሲወራ እንደሚሰሙት ደግሞ ጋለሞታዎች ካገኙት ወንድ ጋር ሁሉ ይወሰልታሉ የሚል ሀሜት አለ፡፡ ለዚህ ሀሜት የዳረጋቸው የድርጊቱ ፈፃሚ ሆነው ሳይሆን ሁኔታው ነው፡፡ ሁኔታው ማለት፤ ለምሳሌ ባለትዳሮች ከባላቸው ጋር ስለሆኑ ይፈራሉ (ጠብቆ ይነበባል) ይከበራሉ፤ ይሄን አልፎ የሚሄድ ካለ በዱላ (ሲከፋም በጥይት) ይቀምሳል፡፡ ያላጋቡት ደግሞ ክብረ ንፅህና (ድንግል) ያላቸው ናቸው። ክብረ ንፅህና ደግሞ ስሙ እንደሚያመለክተው የክብር መገለጫ ነው፡፡ እስከ ጋብቻ ድረስ ጠብቃ መቆየት አለባት፡፡ ነውርነቱ ስለሚታወቅ ያላገባችን ሴት ለትዳር ካልሆነ በስተቀር ለውስልትና የሚጠይቅ የለም፡፡ ጋለሞታ የሚባሉት ግን ከሁለቱም ውጭ ናቸው፡፡ ቢያደርጉትም ባያደርጉትም ሁኔታውን መሰረት በማድረግ ይሄው እረኞች ሁሉ ይመኟቸዋል፡፡ ‹‹ሸጋ ሸጋውን ሴት አርገው ጋለሞታ›› ሲሉ እንደፈለገን እንናገር (በአራድኛው አገላለጽ እንልከፋቸው ማለታቸው ነው)፡፡

አንድ እረኛ የእረኝነት ጊዜው የሚያልቅበት የተቀመጠ የዕድሜ ገደብ የለም፡፡ ከእረኝነት የሚወጣው የጉርምስና ዕድሜ ላይ ደርሶ ሲያገባ ነው፡፡ ከማግባቱ በፊት ግን ከእረኝነቱ ወጣ እያለ ወደ ግብርና ሥራው ያመዝናል፡፡ በተለይም በገጠሩ የሀገሪቱ ክፍል ደግሞ ከ18 ዓመት በታች ሆኖም ሊያገባ ይችላል፡፡ እናም ጉርምስና ሲጀማምረው አለማግባቱን መውቀስ ይጀምራል፡፡ ካገባ በኋላ እረኛ አይደለም፡፡ የሚመገበውና የሚተኛበት ሁሉ እንደበፊቱ የተገኘውን አይደለም፡፡ ሲያገባ የራሱ ጎጆ ይሰራል፤ አልጋ ይሰራል፡፡ ከዚያ በፊት ግን የሚተኛው መደብ (የቤቱ ወለል) ላይ ነው፡፡ እናም ባልንጀሮቹ አግብተው እሱ ከቀረ እንዲህ ሲል ብሶቱን ይገልጻል፡፡

አባት አልረገመኝ

እናት አልረገመኝ

የመደብ መኝታ ምነው ደጋገመኝ!

የፍቅር ብሶት በወንዶች ብቻ ሳይሆን በሴቶችም ይገለጻል፤ እንዲያውም የሴቶች ንፁህ ፍቅር ነው። የወንዶች አንዳንዱ ፆታዊ ግንኙነትን መሰረት ያደረገ ነው፤ የሴቶች ግን ፍቅርን ብቻ የሚገልጽ ነው፡፡ ፍቅርና ወሲብ ያላቸውን ግንኙነት ለጊዜው እንተወውና በሴቶች የፍቅር መግለጫ ግጥሞች ውስጥ ግን ‹‹አብረኸኝ ተኛ፣ እንዲህ አድርገኝ….›› የሚሉ መልዕክቶች የሉም፡፡ በወንዶች በኩል ግን በጋዜጣ ለመግለጽ የማይመቹ ቃላትን በመጠቀም እንደወረደ ሁሉ ያንጎራጉራሉ፡፡

አንዲት ኮረዳ ያፈቀረችው ጎረምሳ ካለ እሷም ስሜቷን በእንጉርጉሮ ትገልጻለች፡፡ ከብት ጥበቃም ይሁን ሰብል ጥበቃ አብረው ይሄዳሉ፡፡ የሚሄዱት ተጠራርተው ነው፡፡ ይሄ ምናልባትም ልጅ እያሉ ነው፤ እየጎረመሱ ሲሄዱ እንዳይታወቅባቸው አይጠራሩም፤ ሌላ የመግባቢያ ኮድ ይጠቀማሉ፡፡ ኮድ ስል አንድ የአዋቂዎች የመግባቢያ ዘዴ (ኮድ) ትዝ አለኝ፡፡

አፋፉ ላይ ቆሜ ፉጨቴን ብለቀው

ወጣች ከነ ሊጧ ሳትለቃለቀው

ፉጨቱ የሚግባቡበት ቋንቋ መሆኑ ነው፤ በፉጨቱ ውስጥ ራሱ የሚግባቡበት ሌላ የተለየ ዜማ ይኖራል፡፡ ወደ ሴቶች እንመለስ፡፡

አንዲት ኮረዳ የምትወደውን ልጅ ለማግኘት ሞክራ አልሳካላት ሲል እንዲህ በእንጉርጉሮ ስሜቷን ትገልፃለች።

አፋፉ ላይ ቆሜ ሸግዬ ብልህ

‹‹የለም ቆላ ወርዷል›› አሉኝ እባትህ

‹‹የማናት ምላሳም!›› አሉኝ እናትህ

በላይኛው ገደል ልንኮትኮትልህ

በታችኛውም ልደገምልህ

አጥንቴ በቅርጫት ይለቀምልህ

ደሜ በብርሌ ይንቆርቆርልህ

ሸግዬ ደማሙ እኔ ወዳጅህ!

መጪዎቹ የነሐሴ እና የመስከረም ወራት በተለይም ለልጃገረዶች እና ለጎረምሶች ልዩ የፍቅር ወራት ናቸው፡፡ እነ አሸንዳ፣ አሸንድዬ፣ ሻደይ፣ ሶለል፣ ከሴ አጨዳ፣ እንቁጣጣሽ…. እየመጡ ነው፡፡ በዓላቱ ሲደርሱ በሌሎች የልጃገረዶች የፍቅር መገለጫዎች በሰፊው እንገናኛለን፡፡ ትኩረት ለአገራዊ ጥበባት!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን   ሐምሌ 13/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *