ወፈፌው ይልቃል አዲሴ ዛሬም በሠፈራችን ተከስቷል፡፡ ሁልጊዜም እንደሚያደርገው ዛሬም ሁሉም የሰፈራችን ሰዎች ወደ ዋርካው ስር እስኪሰበሰቡ ድረስ …“በአህያ ታረሰ በበግ ተበራዬ ፤
ክፉ አይናገርም ፖሊስ ጣቢን ያዬ፡፡”
እያለ የተለመደ ዲስኩሩን በጩኸት ይናገር ነበር፡፡ የሰፈራችን ሰዎች ወደ ዋርካው ተሰባስበው ቦታ ቦታቸውን መያዛቸውን ከተመለከተ በኋላ፤ ይልቃል አዲሴ ራሱን ለንግግር እያዘጋጀ “እህ.. እህ…” ብሎ ጉሮሮውን ጠራርጎ ንግግሩን ሊጀምር ሲል ለሰፈራችን አዲስ የሆኑት የቅኔ መምህር የንታ (የኔታ) “ወፈፌው ይልቃል አዲሴ ግን ማን ነው?” ሲሉ ታዳሚውን በመጠየቅ የይልቃልን ንግግር አቋረጡት ፡፡
ሳይጠየቅ ሁሌም የሚመልሰው አብሿሙ ክንፈ ጉደታ “እርስዎ ለሰፈሩ አዲስ ስለሆኑ ይልቃልን አያውቁትም፡፡ ቢያውቁትም ቶሎ ማንነቱ አይረዱትም፡፡ የሆነው ሆኖ ስለይልቃል የተወሰነ ነገር ልንገርዎት፡፡
ወፈፌው ይልቃል አዲሴ እንደዛሬው ከተማሩት ተርታ ሳይመደብ እና ሁሉም የሰፈራችን ሰዎች ወፈፌው ይልቃል አዲሴ ማን እንደሆነ በቅጡ ስላልተረዱት እንደ እብድ ይቆጥሩት ነበር፡፡ እንደ እድር ጡርምባ ሁልጊዜም ጠዋት የሰፈራችን ሰዎች በጩኸቱ የሚቀሰቅሰው ወፈፌው ይልቃል አዲሴ ነበር፡፡ ያኔ እውቅና ሳያገኝ በጠዋቱ የጀመረውን ጩኸቱን የሚያቆመው ሲተኛ ብቻ ነበር፡፡ ከጩኸቱ ብዛት ‹ልቡ ፈንድቶ አለመሞቱ› እያለ ሁሉም የሰፋራችን ሰው በሀዘን ከንፈሩን ይመጥለት፤ ደረቱንም ይደቃለት ነበር፡፡
በታሪክ እና ፖለቲካ የታጀሉትን የወፈፌው ይልቃል አዲሴ ንግግር የሚያደምጠው የሰፈራችን ሰው እጅግ ጥቂት ነበር፡፡ በአብዛኛው የሰፈራችን ነዋሪዎች ግን ንግግሮቹን እንዲሁ የወፈፌ ንግግር አድርጎ ይቆጥራቸው ነበር፡፡ የሰፈራችን መሪዎች እና ተፎካካሪ ቡድኖች የይልቃል አዲሴን ነቆራ ስለሚጠሉ ይልቃል አዲሴን በፊታቸው ካዩ እንዳይሰድባቸው በማሰብ ፊታቸውን አዙረው መሄድን ይመርጣሉ፡፡
አንድ ቀን የእድራችን ሊቀመንበር የሆነውን አቶ መሃመድ ይልማ የሰፈራችን ሰላም እና እድገት በማስመልከት እንዲሁም የእድራችንን ወርሃዊ ስብሰባ ለማካሄድ በማሰብ ሰፈራችን መካከል ባለው ትልቅ ዋርካ ስር ሕዝቡን ሰበሰበ፡፡ ተሰብሳቢዎችም ከዋርካው ስር ለዘመናት ከማይጠፉት ድንጋዮች ላይ አቧራቸውን በቅጠል እያራገፉትና ተቀመጡ፡፡ ይልቃል አዲሴም ስብሰባውን ለመታደም ዋርካው ስር ተገኘ፡፡
ይልቃል አዲሴ መሐመድ ይልማን ፊት ለፊት አገኘው፡፡ መሐመድ ይልማ ፊቱን አዙሮ ማምለጥ የማይችልበት ቦታ ተገኝቷል፡፡ የእድሩን ወርሃዊ ስብሰባ አቋርጦ አይሄድ ነገር ጭንቅ ሆነበት፡፡ ይልቃል አዲሴን ስድብ እና ነቆራ እያዳመጠ አይቀመጥ ነገር ችግር ነው። ሕዝብን ሰብስቦ ምንም ሳይሉ መበተን ችግር ስለሆነበት እየተሸማቀቀም ቢሆን ስብሰባውን አስጀመረ፡፡ የፈሩት ይደርሳል፤ የጠሉት ይወርሳል ማለት ይሄ አይደል፡፡
እንደተለመደው አቶ መሀመድ በሕዝብ ጆሮ በተሰለቹ የፖለቲካ ቃላት በመጠቀም ‘ጎሳችን በቋንቋው እንዲማር፣ እንዲዳኝ’ ብሎ ሲጀምር ይልቃል አዲሴ በጩኸት ንግግሩን አቋረጠው፡፡ ሁሉም የእድሩ አባላት ፊታቸውን ወደ ይልቃል አዲሴ አዞሩ፡፡
ይልቃልም ንግግሩን እንዲህ ብሎ ጀመረ ‹ብልህን ሰው ለማሞኘት መሞከር ትርፉ ትዝብት ነው፡፡ ዛሬም እንደዚህ ቀደሙ በፖለቲካ ቋንቋዎች ሸውደኸን ልትሄድ ነው፡፡ አልፈቅድልህም! መሸዋወዱን ተወውና የእድሩ እና የሰፈራችን ፍላጎት ምንድን ነው? ብለህ ጠይቅ፡፡› ብሎ ንግግሩን ቀጠለ… ‹ ከዚያም ይልቃል አዲሴ የሰፈራችን ሰዎች ብቻ ሳይሆን ሊቀመንበሩም ሊገነዘባቸው በማይችሉ የፖለቲካዊ ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፍልስፍና ቃላትን እየመዠረጠ፤ አንድ ጊዜ በግዕዝ፤ ሌላ ጊዜ በፈረንጅ አፍ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ የአማርኛ ቋንቋን በመጠቀም በፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ትንታኔዎችን ሰጠ፡፡ የሰፈራችንን ሊቀመንበር በጥያቄ አፋጠጠው፡፡ ይሁን እንጂ የሰፈራችን ሊቀመንበር የወፈፌውን ንግግር አንዱንም ሳይረዳው ኖሮ ‘መጽሐፉም ዝም’፤ ቄሱም ዝም’ እንደሚባለው ሆነ፡፡
ወፈፌው ይልቃል አዲሴ ሊቀ መንበሩን በክርክር መርታቱን ከተመለከተ ወዲህ ዋርካው ስር መጮህ ሲጅምር የሰፈራችን ሰዎችም የወፈፌው ንግግሮች እና ዲስኩሮች እንዳያመልጧቸው በማሰብ ከህጻን እስከ አዋቂ ወደ ዋርካው ይሰበሰባሉ፡፡ ምንም አይነት አስቸኳይ ነገር ቢያጋጥማቸው እንኳን ከስራቸው በላይ ንግግሮችን እና ዲስኩሮችን ለማዳመጥን ቅድሚያ ይሰጣሉ፡፡ ንግግሮቹንም ቃል በቃል እየፈቱ በየራሳቸው ይተነትኑታል፡፡” ብሎ ለፍሬው ምላሽ ከሰጠ በኋላ ወደ መቀመጫው ተመለሰ፡፡
አብሿሙ ክንፈ ጉደታ ንግግሩን መጨረሱን የተመለከተው ወፈፌው ይልቃል አዲሴ “ሰለቀደመ ማንነቴ ማተኮሩን ትተን ወደዛሬው አጀንዳችን እንመለስ” ንግግሩን ከአቋረጠበት ጀመረ፡፡
“በአህያ ታረሰ በበግ ተበራዬ ፤
ክፉ አይናገርም ፖሊስ ጣቢን ያዬ፡፡
እንዴት ጎበዝ ሰፈራችን እና እድራችን ተፈጥሮ በወለደው ድርቅ አይሆኑ ሆነው ተጎሳቅለው፤ በዓለም ሕዝብም መዘባበቻ ሆነው፤ የሰፈራችን እና የእድራችን ስም ሆነው እያለ ከእንደዚያ አይነት ድርቅ ለመዳን እና ምርታማነትን ለመጨመር ችግኝ ተክሎ ችግርን መንቀል ፖለቲካ ያደረገው ማን ነው? በእርግጥ በፖለቲካ መሪዎች ፊታውራሪነት ዘመቻው መከናወኑ የፖለቲካ አንድምታ ያለው ሊመስለን ይችላል፡፡ ግን ፖለቲካዊ አንድምታ መስጠቱ ተገቢነቱ አይታየኝም፡፡
ድሬዳዋ በተደጋጋሚ በጎርፍ በመጥለቅለቋ በደግነት የሚታወቁት ነዋሪዎች እጃቸውን እርዱኝ ብለው ሲዘረጉ እያየን፣ የአርባ ምንጭ ዙሪያ ገበሬዎች የአባያ ሀይቅ በደለል መሞላቱን ተከተሎ በየአመቱ ማሳቸውን በመብላቱ ሀገር ቀላቢ አርሶ አደሮች ባዶ እጃቸውን ሲቀሩ እየተመለከትን፣ በጋምቤላ ክልል በየአመቱ በ11 ወረዳዎች ላይ በመያጋጥም የጎርፍ መጥለቅለቅ ሳቢያ የሚጎሳቆለው ሕዝብ ምን ያህል እንደሆነ እየታወቀ ችግኝ ተከላን ፖለቲካዊ አንድምታ መስጠቱ ተገቢ አይመስለኝም፡፡
እንደዚህ የመሰሉ ፕሮጀክቶችን የፖለቲካ ትርጓሜ እንድንሰጥ ያደረገን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሰፈራችን የሚስተዋለው አለመደማመጣችን ይመስለኛል። መደማመጥ በነጋዴው እና በሸማቹ፣ መደማማጥ በፖለቲከኞች፣ በሚዲያዎች፣ በሀገር ውስጥና በውጭ በሚኖሩ የእድራችን እና የሰፈራችን ሰዎች፣ በተለያዩ ሃይማኖት ተከታዮች እና ጎሳዎች መካከል እንደ ሰማይ እየራቀን መምጣቱን እየተመለከትን ነው፡፡ እነኚህ አካላት መደማማጥ ተሳናቸው ማለት ደግሞ የእድራችንን እና ሰፈራችንን የወደፊት እጣ ፋንታ ለመተንበይ የግድ ነብይ መሆንን አያሻም፡፡ በሀገሪቱ በተለያዩ ጊዜያት እና አካባቢዎች የሚስተዋሉ የሰላም መደፍረስ፣ የሰዎች መሞት እና መፈናቀል ለዚህ ዋነኛ ማሳያዎች ናቸው፡፡
ጎበዝ ለምን መደማመጥ ተሳነን? መደማመጥ እኮ የችግሮች ሁሉ መፍቻ ቁልፍ ነው፡፡ መደማማጥ የትእቢተኞችን የጥፋት ድግስ የሚያሽር አይነተኛ መድኃኒት ነው፡፡ መደማመጥ የሌለበት ፖለቲካዊ፣ ልዩነት አደገኛ ነው፡፡ ዓይንን ጨፍኖ ገደልን ለመሻገር እንደመሞከር ነው፡፡ መደማመጥ የሌለበት ፖለቲካ ዓይንን ጨፍኖ መስታወት እንደመመለከትም ነው፡፡ ስለሆነም ለእድራችን እና ለሰፈራችን ህልውና ሲባል ሁሉም የእድራችን እና የሰፈራችን ሰዎች ልዩነታቸውን አቻችለው በመደማመጥ ችግኝ በመትከል ችግርን መንቀል አይነት ፕሮጀክቶችን ተባብረው እና ተረባርበው ሊያከናውኑ ይገባል ባይ ነኝ፡፡
እንደኔ እንደኔ ሁሉን ነገር ከፖለቲካ ጋር ማገናኘት እና ፖለቲካዊ ትንታኔ መስጠት ጤንነት አይመስለኝም፡፡ ምናልባትም በርካታ እድሎች ሊያመልጡን ይችላሉ፡፡ ይህን ስል አንድ በደርግ ዘመነ መንግሥት የተከሰተ ገጠመኝ ልንገራችሁ፡፡
በደርግ ዘመነ መንግሥት ለብሔራዊ ውትድርና በሚል ከትምህርት ቤቶች ወጣቶች ይታፈሱ ነበር፡፡ በተለይ የመንግሥት ባለሥልጣናት ለምንም ይሁን ለምን ትምህርት ቤት አካባቢ ከታዩ ለብሔራዊ ግዳጅ ተማሪዎችን ለማፈስ መጥተዋል በሚል ሁሉም ተማሪዎች ከትምህርት ቤቶች ይቀሩ ነበር፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን የመንግሥት ካድሬዎች ከውጭ ሀገር የተገኘ የትምህርት እድልን ለተማሪዎች አወዳድሮ ለመስጠት በማሰብ እና በመማር ማስተማር ሥራው ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ወደ አንድ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ያቀናሉ፡፡ ይህን ተከትሎ ለብሔራዊ ውትድርና ልንታፈስ ነው በሚል ሁሉም ተማሪ በአጥር እየዘለለ እግሬ አውጭኝ አለ፡፡
በዚህ ወቅት ብቻውን ትምህርት ቤት የቀረው ከትምህርት ቤት ወደ ቤቱ በወላጆቹ እርዳታ የሚንቀሳቀሰው አካል ጉዳተኛው ፈለቀ ብቻ ነበር። የመንግሥት ካድሬዎች በትምህርት ቤቱ ዙሪያ መታየታቸውን ተከትሎ ለአንድ ሳምንት ያህል ሁሉም ተማሪዎች ከትምህርት ቤት ጠፉ፡፡ በመጨረሻም በመከራ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤታቸው እንዲመለሱ ተደረገ፡፡
በዚህ ወቅት አንድ መምህር አካል ጉዳተኛውን ፈለቀን ‘ሌሎች ተማሪዎች ለብሔራዊ ውትድርና እንታፈሳለን ብለው ስጋት ቢያድርባቸው ከትምህርት ቤት ቀሩ፡፡ አንተ ደግሞ ከትምህርት ቤት የቀረኸው ምን ይሁን ብለህ ነው?’ ሲል ጠየቀው፡፡ አካል ጉዳተኛው ፈለቀም ‘ጤፍ ሊጭን የመጣ መኪና ጤፍ ሲያጣ ገብስ መጫኑ ይቀራል?’ ብሎ ጥያቄውን በጥያቄ መለሰለት ይባላል፡፡
የሆነው ሆኖ የመንግሥት ካድሬዎን ተመልክተው የካድሬዎችን መምጣት የተዛባ ትርጉም ሰጥተው ከትምህርት ቤታቸው የቀሩት ተማሪዎች መሙላት የነበረባቸውን ፎርም ሳይሞሉ ጊዜው በማለፉ የውጭ የትምህርት እድሉን እንዲያጡ አደረጋቸው፡፡
በነገራችን ላይ ለነገሮች የተዛባ ትርጉም መስጠት መትረፍ ከነበረብን አደጋ ማምለጥ እንዳንችልም ያደርጋል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ አንድ በጦርነት ያገጠመ ገጠመኝን ልንገራችሁ፡፡ ወታደሩ ስልታዊ ማፈግፍግ በሚያደርግበት ጊዜ ጦሩ ወደ ኋላ የሚያፈገፍገው ሆነ ብሎ የአካባቢው ሰው እንዲወጋ ነው የሚል ወሬ በማኅበረሰቡ አካባቢ በስፋት ይናፈስ ነበር፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ አንድ ቀን ወታደሩ ቆረጣ ለማድረግ ስልታዊ ማፈግፈግ ያደርጋል፡፡ ይህን ተከትሎ ጦሩ የሚያፈግፍገው ሆነ ብሎ ነው በሚል ወጣቶች መንገዱን በድንጋይ ጥርቅም አድርገው ዘጉት፡፡
ወታደሩ እና የአካባቢው ወጣቶች መንገዱን ክፈት አይከፈትም በሚል ግጭት ውስጥ ገቡ፡፡ ሰዓታትም ነጎዱ። የወታደር ኦፕሬሽን የሚመራው በሰዓት ነው፡፡ ወታደሩ ኦፕሬሽን በሚደረግበት ቦታ ሳይገኝ ቀረ፡፡ ኦፕሬሽኑም ሳይሳካ ቀረ፡፡ የጠላት ኃይልም በተዛባ መረጃ ወጣቱ የፈጠረውን እክል እንደ ጥሩ አጋጣሚ ተጠቀመበት። ጠላትም በርካታ ጥፋቶችን በሀገር እና በሕዝብ ላይ አደረሰ፡፡ ይህ የሆነው ለአንድ ነገር በምንሰጠው የተዛባ ግንዛቤ ነው፡፡
ስለዚህ ሁሉን ነገር ከአንድ ነገር ብቻ ማያያዝ እና አንድ ትርጓሜ መስጠት ትክክል አይደለም፡፡ ልጆቹ ከትምህርት ቤታቸው መቅረታቸው የትምህርት እድሉን እንዲያጡ አደርጓቸዋል፡፡ ወጣቶች ያወቁ መስሏቸው ወታደርን በማስተጓጎላቸው ሕዝብን ለችግር ዳርገዋል፡፡
በተደጋጋሚ በድርቅ እና በጎርፍ የምትጠቃ ሀገርን ይዞ ችግኝ መትከልን የተለየ ትርጉም መስጠቱ ትክክል አይደለም፡፡
በነገራችን ላይ የማይፈጥሩ ጭንቅላቶች የሰውን ሥራ ማናናቃቸው የማይቀር ነው፡፡ ሁሉንም ነገር ከራሳቸው እይታ አንጻር ብቻ ይገመግሙታል፡፡ እዚህ ለመድረስ ስንት እና ስንት የሰው ኃይል እና ገንዘብ እንደፈሰሰበት አይረዱትም፡፡ ለተቀማጭ ሰማይ ቅርቡ ነው እንደሚባለው ማለት ነው፡፡
የችግኝ ተከላውን ፖለቲካዊ መልክ የሰጡትን ጊዜ ወስደን ጠለቅ ብለን ብንመለከታቸው የሰነፎች እና መስራት የማይችሉ፤ ከማውራት ውጭ ለማኅበረሰቡ ኑሮ መሻሻል አንድ ስንዝር ድጋፍ ማድረግ የማይችሉ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡
በአጼ ምኒልክ ዘመነ መንግስት ያጋጠመውን ክፉ ቀን ተከትሎ በአጭር ጊዜ ሀገሪቱ ራሷ አምርታ ራሷን በምርት እንድትችል ለማድረግ ንጉሱ በግንባር ቀደምትነት ዶማ ይዘው መቆፈር ጀመሩ፡፡ የንጉሠ ነገሥቱን ድርጊት የተመለከቱ ንጉሶች እና ራሶችም በሚያስተዳድሯቸው ክፍለ ሀገራት ዶማ ይዘው እየቆፈሩ ለደጃዝማቾቻቸው እና ለፊታውራሪዎቻቸው አሳዩ፡፡ ይህን ዘመቻ ሕዝቡም ተቀላቀለው፡፡ በዚህም ክፉ ቀን ሊያደረስው ከሚችለው ጉዳት ኢትዮጵያን ጠበቁ፡፡
ከዚያም ባለፈ ለክፉ ቀን ምክንያት የሆኑትን ጣሊያኖችን መከቱ፡፡ የጥቁር ሕዝቦች ኩራት እና መመኪያም እስከመሆን ደረሱ፡፡ እናም አሁንም ደግሜ እላችኋለሁ
በአህያ ታረሰ በበግ ተበራየ ፤
ክፉ አይናገርም ፖሊስ ጣቢን ያየ፡፡ …በድርቅ እና በጎርፍ ስንት እና ስንት ሕዝቦቿን፣ ከብቶቿን፣ ንብረቶቿን እና ስሟን ያጣች ሀገር፣ ዛፍ መትከሏ ፖለተካ የሚሆነው እምኑ ላይ ነው?
በእርግጥ በዘመቻው የበርካታ ክልሎች መሪዎች በችግኝ ተከላው ወቅት የተለያዩ ፖለቲካዊ አዘል መልዕክት አስተላልፈው ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ማለት ግን ችግኝ ተከላው ለፖለቲካዊ ፍጆታ ነው የዋለው ሊያስብለው አይችልም፡፡
አሸብር ኃይሉ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 13/2015