ወቅቱ የ2015/16 የምርት ዘመን የመኸር እርሻ የሚካሄድበት ነው፡፡ የሰብል አብቃይ ክልሎችና አካባቢዎች አርሶ አደር ደጋግሞ በማረስ ሲያለሰልስ የቆየውን ማሳውን በዘር በመሸፈን ስራ ተጠምዷል፡፡ የደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ክልልም በ2015/16 የምርት ዘመን ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ድህነትን ለመቀነስ እንደሀገር የተጀመረውን ጉዞ ለማሳካት የራሱን ድርሻ ለመወጣት ቀድሞ ዝግጅት በማድረግ ወደ ሥራው ገብቷል፡፡
በክልሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር፤ በበጋ መሥኖ እና በበልግ የልማት ወቅቶች የነበሩ መልካም ተሞክሮዎችን በዚህ የመኸር ግብርና ሥራም በተመሳሳይ ለመፈጸም ከአንድ ወር በፊት አስቀድሞ በዞን፣ በወረዳና በቀበሌ የንቅናቄ ሥራ መሰራቱንም ይጠቅሳሉ፡፡
ከንቅናቄው ዓላማዎች መካከል ግብርናን በማዘመን እየተሰሩ ያሉ ሥራዎችን አጠናክሮ መቀጠል ስለሚቻልበት ሁኔታ፣በዘርፉ የሚስተዋሉ ጉድለቶችን ለይቶ ክፍተቱን መሙላት፣ ጠንካራውን ማስቀጠል እንዲሁም ከግብአት አቅርቦት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል አሰራር መዘርጋት የሚሉት ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡ ንቅናቄው በአርሶአደሩ ላይ መነሳሳት በመፍጠር ውጤት ማስገኘቱንም ነው የገለጹት፡፡
አቶ ኡስማን የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት እጥረት መኖሩንም ይገልፃሉ፡፡ እርሳቸው እንዳሉት፣ ለክልሉ መቅረብ ከሚገባው የአፈር ማዳበሪያ ወደ 340 ሺ ኩንታል የሚሆነው/40 በመቶው/ እየገባ መሆኑንና በመሠረታዊ የገበሬዎች የህብረት ሥራ ማህበራት በኩል በመሰራጨት ላይ ይገኛል፤ ቀሪው ስራም ይቀጥላል፡፡ በአሁኑ ጊዜም የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም ክፍተቱን ለመሙላት ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ ጎን ለጎንም ማዳበሪያው ኖሯቸው ነገር ግን የዘር ጊዜያቸውን ከሚጠብቁ አካባቢዎች ቀድመው ወደ ዘር ለገቡት የሚደርስበት ሁኔታ እየተመቻቸ ይገኛል፡፡ የተፈጥሮ ማዳበሪያም ጥቅም ላይ እንዲውል ጥረት እየተደረገ ነው፡፡
የመኸሩ የግብርና ሥራ ትኩረት ያደረገው በሰብል ልማቱ ላይ ብቻ እንዳልሆነም ጠቅሰው፣ በምርታማነታቸው የሚታወቁና ገበያ ያላቸውን አማራጭ ተክሎችንም የማልማት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አቶ ኡስማን ገልጸዋል፡፡ በዚህ ረገድ በጉራጌ፣ ከምባታ አላባ አካባቢዎች እንቅስቃሴው መጠናከሩን አመልክተዋል፡፡
በአፈር ማዳበሪያ ዙሪያ አጠቃላይ ያለውን ሁኔታ በተመለከተም በግብርና ሚኒስቴር የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ከበደ ላቀው እንዳሉት፤ ለ2015/16 የምርት ዘመን ከተገዛው የአፈር ማዳበሪያ ወደ ስድስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ኩንታል የሚሆነው ሙሉ ለሙሉ ወደ ሀገር ውስጥ ገብቶ ልማቱ ወደሚከናወንባቸው አካባቢዎች እንዲሰራጭ ተደርጓል፡፡ ግዥው ተፈጽሞ በሂደት ላይ ያለው ማዳበሪያም ሙሉ ለሙሉ ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል፡፡
ስርጭቱ ክልሎች ባቀረቡት ጥያቄ በተለያዩ አማራጮች እየተፈጸመ መሆኑን አቶ ከበደ ጠቅሰው፣ መንግሥት ምርታማነትን ለማሳደግ እያከናወነ ላለው የልማት እንቅስቃሴ አስፈላጊ የሆኑ ግብአቶች እንዲቀርቡ ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡ በስርጭቱ በኩልም መሠረታዊ የህብረት ሥራ ማህበራት ለአርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ተደራሽ በማድረግ ረገድ የተቀላጠፈ እንቅስቃሴ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ያሉት አቶ ከበደ፤ በተለይም ማዳበሪያው ለህገወጥ አሰራር እንዳይጋለጥ በማድረግ ረገድ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡
ህገወጥነቱ የመነጨው አላስፈላጊ ጥቅም ከመፈለግ ጋር በተያያዘ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ከበደ፣ ክልሎች በተጠናከረ ክትትልና ቁጥጥር ይህንንም ለማስቀረት ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ህገወጥነትን ለመከላከል በአንዳንድ ክልሎች እርምጃዎች መወሰድ መጀመሩን ጠቅሰው፣ ክልሎች ከሚመለከተው አካል ጋር ተቀናጅተው በመሥራት ህገወጥነትን የመከላከሉን ሥራ ማጠናከር እንዳለባቸውም ተናግረዋል፡፡
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ በሚችለው ሁሉ ቅሬታውን ለመፍታት ጥረት እያደረገ መሆኑን የገለጹት የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተሩ፣ የአፈር ማዳበሪያው ሙሉ ለሙሉ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ከባለድርሻ አካላት ጋር የተናበበ ሥራ እንደሚሰራም ያስታወቁት፡፡
እንደ አቶ ከበደ ገለጸ፤ ከአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ጋር በተያያዘ ግብርና ሚኒስቴር መድረክ በማዘጋጀት ዘርፉን ከሚመሩ ከተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ እንዲሁም ከመሠረታዊ ህብረት ሥራ ማህበራትና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል፤ ውይይቱ ክልሎች የሚሰራጭላቸውን የአፈር ማዳበሪያ ለአልሚው አርሶአደርና አርብቶ አደር በአግባቡ ተደራሽ እንዲያደርጉ ያለመ ነው፡፡ በማዳበሪያ ስርጭት የገጠሙ ችግሮችና በመፍትሄዎቻቸው ላይም ውይይት ተደርጎ ገንቢ የሆነ ሀሳብ ተገኝቷል፡፡
እንደ አቶ ከበደ ማብራሪያ፣ የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦትን ጨምሮ ለ2015/16 የምርት ዘመን እየተደረገ ያለው የግብአት አቅርቦት በምርት ዘመኑ ለማምረት የተያዘውን እቅድ ለማሳካት የሚያስችል ነው፡፡ የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ጉዳይ ሰሞኑን በተካሄደው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይም ተነስቷል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ከምክር ቤቱ አባላት ለቀሩቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ማዳበሪያን አስመልክተው እንዳሉት፤ ሀገራዊ ለውጡ በተጀመረበት ወቅት መንግሥት ለማዳበሪያ ያወጣው ወጪ 450 ሚሊዮን ዶላር አካባቢ ነበር፡፡ አሁን ላይ ደግሞ ወጪው ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር ገደማ ደርሷል።
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ፤ መንግሥት በዚህ ዓመት ለማዳበሪያ ግዥ ለውጭ ምንዛሪ ካቀረበው ሀብትና ካደረገው ድጎማ በተጨማሪ በትራንስፖርት ዘርፍም በተከናወነው ሥራ ከጅቡቲ ወደብ የማንሳት አቅምን ማሳደግ ተችሏል፡፡ በአሁኑ ጊዜም ከወደብ የማንሳቱ ተግባር በሶስት እጥፍ ከፍ ብሏል፡፡ በባቡር ትራንስፖርትም ከወደቡ የማንሳቱ ሥራ እየተሻሻለ ይገኛል፡፡
ግዥን በተመለከተም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምርት ዘመኑ በመጀመሪያው ዙር 12 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ግዥ መፈጸሙን ጠቅሰው፣ በተጨማሪ 800ሺ ኩንታል ተገዝቶ ለትግራይ ክልል መሰራጩትን አመልክተዋል፡፡ በአጠቃላይ አምና ከተረፈው የአፈር ማዳበሪያ ጋር በድምሩ ለምርት ዘመኑ 15 ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ኩንታል ገደማ ማዳበሪያ መኖሩን አመልክተዋል። ግዥ ከተፈጸመው ማዳበሪያ ውስጥም ከዘጠኝ ሚሊዮን ኩንታል በላዩ ወደ ሀገር መግባቱን ጠቁመዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የተፈጥሮ ማዳበሪያም በስፋት ጥቅም ላይ የሚውለበትን መንገድ በማመቻቸት በኩልም ትኩረት መሰጠቱን አስታውቀዋል፡፡ በዚሁ መሠረትም ወደ 178ሚሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ የሚጠጋ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በሀገር ውስጥ ማዘጋጀት መቻሉን ጠቅሰው፣ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት በማዳበሪያ ግብአት በኩል ያለውን ችግር በዚህ መንገድ ለመፍታት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት፤ የማዳበሪያ አቅርቦት አቅምን ለማሳደግና በአሲዳማነት የተጠቃውን ወደ ሰባት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ለማከም እየተሰራ ነው፡፡ አሲዳማ አፈርን ለማከም ቁጥራቸው ወደ አምስት የሚደርስ አነስተኛ አቅም ያላቸው ኖራ የሚያመርቱ ፋብሪካዎች ተቋቁመዋል፡፡ እነዚህ ሁሉ ትኩረቶች ለግብርናው ሥራ አቅም ለመፍጠር ነው፡፡ ሥራዎችን በዚህ ሁኔታ በመቀጠል የተፈጥሮ ማዳበሪያን የማስፋፋቱና አቅርቦትን የማሳደጉ ሥራ ይጠናከራል፡፡ ምርታማነትን ለማሳደግ የሚሰራው ሥራ በግብአት አቅርቦት ብቻ የሚወሰን እንዳልሆነ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የእርሻ መሬት በማስፋት ምርታማነትን ማሳደግ ግዴታ እንደሆነም ነው ያመለከቱት፡፡
እርሳቸው እንዳሉት፤ በአሁኑ ጊዜ በሄክታር 40 ኩንታል ስንዴ ማምረት በቂ አይደለም፤ በሶስት እጥፍና ከዚያም በላይ በማምረት እንደ ሀገር ምርታማነትን ማሳደግ ይጠበቃል፡፡ አሁን ላይ ለምርት ሥራው እየዋለ ያለው 15 ሚሊዮን ሄክታር መሬትም በቂ ተደርጎ መወሰድ የለበትም። ኖራ እንዲያመርቱ በተቋቋሙት ፋብሪካዎች በሚመረተው ኖራ ብቻ መሬቱን ወደ 20 ሚሊዮን ሄክታር ማድረስ ይቻላል፡፡ እንዲህ ያሉ ተግባራትን በማከናወን በሚቀጥሉት የምርት ጊዜያቶች ምርት ማትረፍረፍ እንደሚጠበቅም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ጋር በተያያዘ በዚህ ወቅት ያጋጠመውንም ችግር አንስተዋል። ሀገሮች የተፈጥሮ ማዳበሪያና ስንዴ በአብዛኛው ከዩክሬን እንደሚገዙ ጠቅሰው፤ በዩክሬንና በሩሲያ መካከል በተነሳው ጦርነት ምክንያት በቀላሉ ኤልሲ ከፍቶ ማዳበሪያና ስንዴ መግዛት ለብዙ ሀገሮች ችግር መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡
ችግሩ የነካው ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን ዓለምን መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህን ተከትሎም ሽሚያ የበዛበት ሁኔታ መታየቱን ገልጸዋል፡፡ በዚህ ምክንያትም ኤልሲ ከፍቶ የማዳበሪያ ግዥ ለመፈፀም መዘግየት መፈጠሩና የገበያ ሥርአቱ መናጋቱ በአንድ በኩል፣ በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያ ማዳበሪያ ስለማታመርትና በግዥ መጠቀሟ ውስንነት እንደፈጠረ አስረድተዋል፡፡
ግዥ ለመፈጸም ኤልሲ ቢዘገይም ግዥው መፈጸሙን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የተወሰነ መዘግየት ቢኖርም የቀረው እንደሚደርስ ተስፋ መኖሩንና ጅቡቲ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ፣ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ግብርና ሚኒስቴር ግብአቱ ወደ ሀገር እንዲገባ ቀዳሚ ሥራቸው አድርገው በትኩረት በመሥራት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
መንግሥት እንዲህ ጥረት ቢያደርግም በአሰራር እንቅፋት የሆኑ ጉዳዮችም መኖራቸውንና ችግሩም በአንዳንድ ቦታዎች እየታየ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል፡፡ አንድ መቶ ሺ እና ሃምሣ ሺ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ቀድሞ ካልደረሰን በሚል ስርጭቱን ወይንም እደላውን ለማከናወን ፈቃደኛ ባለመሆን ክምችት ይዘው የተቀመጡ የአንዳንድ አካባቢዎች ወረዳዎችና ቀበሌዎች ስለመኖራቸው መረጃ እንደደረሳቸው ተናግረዋል፡፡ እንዲህ ያለው አካሄድ አግባብ እንዳልሆነም ጠቅሰው፣ የተገኘው ግብአት ጥቅም ላይ እንዲውል ለአርሶአደሩ ከሥር ከሥር ማድረስ፣ ጎን ለጎን የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማዘጋጀትና አሲዳማ አፈርን ማከም እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት ማዳበሪያ አምርቶ እንደያዘ አድርጎ መውሰድም ተገቢነት እንደሌለው የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ገበያው ሲቀርብ ግዥ እንደሚፈጸም፣ እያንዳንዱ አመራር በየደረጃው ተገንዝቦ እንዲሰራም አሳስበዋል፡፡ የማዳበሪያ ፋብሪካ ለማቋቋም ኢትዮጵያ ሁሉንም አይነት ግብአቶች ማቅረብ የምትችልበት እድል መኖሩንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅሰው፣ ኢንቨስትመንቱ ግን ማነቆ እንደሆነ ነው የጠቀሱት፡፡ ‹‹ማዳበሪያ ፋብሪካ የተፈጥሮ ጋዝ ይፈልጋል፡፡
የተፈጥሮ ጋዝ ለማውጣት ደግሞ ሶስትና አራት ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል፡፡ ማዳበሪያ ለማምረት የሚውል ፖታሽም እንዲሁ ማውጣትን ይጠይቃል። ይህም ቢሆን ሰፋ ያለ ኢንቨስትመንት የሚጠይቅ ጉዳይ ነው፡፡ የተፈጥሮ ጋዝ እና ፖታሽ በሚገኝበት ስፍራ ማስተላለፊያ መስመር (ፓይፕ) ለመዘርጋትም ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል፡፡ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብንና ኮይሻን በመገንባት ላይ ለምትገኝ ሀገር ተጨማሪ ቁርጠኝነት ለመውሰድ ያስቸግራል፡፡›› ሲሉ አብራርተዋል፡፡
ይህም ሆኖ መንግሥት ጥረት ከማድረግ አልተቆጠበም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከባለሀብቶች ጋር ለመነጋገር ጥረት ከማድረግ ባለፈ የመግባቢያ ሰነድም ተፈርሞ በተለያየ ምክንያት ሳይሳካለት መቅረቱን ገልጸዋል፡፡ ጥረቱን በማጠናከር የግሉ ዘርፍ እንዲሰማራ፣ ያም ካልሆነ ዋና ዋና የመንግሥት ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ ቀጥሎ የመንግሥት ትኩረት በማዳበሪያ ግብአት ላይ ይሆናል ብለዋል፡፡ ‹‹ዘርፉ ትልቅ ሀብት የሚጠይቅና በቀላሉ ለማሳካት የሚቻል አለመሆኑ ግንዛቤ ሊያዝበት ይገባል›› ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል፡፡
ለምለም ምንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 3 ቀን 2015 ዓ.ም