ለብዙ ዓመታት ጋዜጦች፣ መጽሔቶች፣ የሬዲዮና ቴሌቪዥን ጣቢያዎች የኢትዮጵያን ፊልም ሲወርዱበት ቆይተዋል፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ መገናኛ ብዙኃኑ የህዝቡን ምሬት ተከትለው ነው፡፡ ሁለትና ሦስት ሆነው ከሚቀመጡበት የካፌ ጠረጴዛ እስከ ትልልቅ መድረኮች ድረስ የኢትዮጵያ ፊልምና ድራማዎች የእርግማን መዓት ሲወርድባቸው ቆይቷል፡፡
ለዚህ የተዳረጉት ደግሞ በይዘታቸው ነው፡፡ ሁሌም ተመሳሳይ ነገር፣ ተመሳሳይ መቼት፣ ተመሳሳይ መልዕክት መሆኑ ነው፡፡ የበሰለ ሀሳብ የሌላቸው፣ ያልተጠኑ፣ የኢትዮጵያን ታሪክ፣ ባህል፣ ወግና እሴት ያልጠበቁ… መሆናቸው ነው ሲያስወቅሳቸው የቆየ፡፡
ሒስ ደግሞ ለኪነ ጥበብ መፈወሻ መሆኑ በባለሙያዎች በተደጋጋሚ ሲነገር የቆየ ነው፡፡ ስለዚህ መገናኛ ብዙኃኑም ሆኑ ግለሰቦች የፊልምና ድራማ ሥራዎችን ሲወቅሱ መቆየታቸው የጥበብ ሰዎች ነገሩን ትኩረት እንዲሰጡት ያደረገ ይመስላል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርካታ ድራማዎችና ፊልሞች በሕዝቡ ዘንድ ተወዳጅነትን እያገኙ ነው፡፡ በማህበራዊ ገጾች ሳይቀር በጉጉት የሚጠበቁ መሆናቸውን ሰዎች ሀሳባቸውን ሲያንጸባርቁ ይታያል፡፡ እነዚህ ድራማዎች የተወደደዱት በሚገባ ተጠንተውና የሚመለከተውን ባለሙያ በማማከር የተሰሩ ስለሆኑ ነው፡፡
መገናኛ ብዙኃን ደግሞ ሕዝቡ ወቀሳ ሲያበዛ ወቀሳውን እንዳስተጋቡ ሁሉ አድናቆት ሲገኝም አድናቆታቸውን ማሰማት ይገባቸዋል፡፡ በዛሬው የኪነ ጥበብ ዓምዳችንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተወዳጅነት ያገኙ ድራማዎችን በጥቂቱ እናስታውሳለን፡፡
በስንቱ
ይህ በኢ ቢ ኤስ ቴሌቪዥን የሚተላለፍ ሲትኮም ድራማ ነው። ድራማው አስቂኝ ነው፤ ምናልባትም አዝግ እና ዋዛ ፈዛዛ የሆነ፣ ለማሳቅ ብቻ ተብሎ የሚደረግ የሚመስለው ይኖር ይሆናል፡፡ ዳሩ ግን ድራማው እያሳሳቀ ጥልቅ ሀሳቦችን የሚያነሳ ነው፡፡ ከሥርዓተ ፆታ፣ ከማህበራዊ ሕይወት፣ በአጠቃላይ በሰው ልጅ ሕይወት ውስጥ ባሉ ነገሮች ላይ ፍልስፍናዊ ሀሳቦችን እያነሳ የሚሞግት ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ከድራማው ላይ እየተቆራረጡ በቀልድ መልክ በማህበራዊ ገጾች የሚዘዋወሩ ቪዲዮች አሉ፡፡ የሚያነሳቸው ጉዳዮች ከማሳቅ ባሻገር ኮርኮር የሚያደርግ መልዕክት ስለሚያስተላልፉ ማለት ነው፡፡
በሕግ አምላክ
ይህኛው ደግሞ በአርትስ ቴሌቪዥን የሚተላለፍ ተከታታይ ድራማ ነው፡፡ ድራማው ጠንካራ ሀሳቦች ላይ የሚያተኩር ነው፡፡ በሕግና ወንጀል ጉዳዮች ላይ ጠንካራ ሀሳቦችን ያነሳል፡፡ በተለይም ሥልጣንን መከታ በማድረግ ከህግ በላይ ለመሆን የሚደረግን ጥረት በድፍረት ይሞግታል፣ ውስልትናቸውን ያሳያል፡፡ የውስብስብ ሴራዎችን ምንነት ያሳያል፡፡ በአጠቃላይ ኪነ ጥበብ ለማህበራዊ ሕይወትና መልካም አስተዳደር መስፈን መሥራት ያለበትን ሥራ ሰርቷል ማለት ይቻላል፡፡
ግራ ቀኝ
ይህ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በቅርቡ የተጀመረ ታሪካዊ ድራማ ነው፡፡ ድራማው ‹‹የሶሻሊስቱ ጠንቋይ›› የተሰኘው የሐማ ቱማ መጽሐፍ ነው፡፡ ሐማ ቱማ የአቶ ኢያሱ አለማየሁ የብዕር ስም ነው። አቶ ኢያሱ አለማየሁ ደግሞ የኢህአፓ መሥራችና ከፍተኛ አመራር የነበሩ ናቸው፡፡ ለዚህም ነው መጽሐፉ (ድራማው) በደርግ ዘመን የነበረውን አምባገነናዊ የፍርድ ቤት አሰራር ያሳያል፡፡ በድራማው ውስጥ ያሉ ተዋናዮች በኢትዮጵያ የትወና ጥበብ ውስጥ አሉ የተባሉ ስለሆኑ ይዘቱ ብቻ ሳይሆን የተዋናዮቹ ብቃት ራሱ ድራማውን ከፍተኛ ውበት ሰጥቶታል፡፡
በመሐል
ይህም በዚያው በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን (መዝናኛ ቻናል) የሚተላለፍ ድራማ ነው፡፡ ይህን ድራማ ለየት የሚያደርገው ተዋናዮች በገሃዱ ዓለም ስማቸው ነው የሚጠሩት፡፡ ሙያቸውም በገሃዱ ዓለም ያለው ሙያቸው ነው፡፡ ለምሳሌ ፀሐየ ዮሐንስ ዘፋኝ ነው፤ በድራማው ውስጥም በዚሁ ሙያ ነው የሚሳተፍ፡፡ ሐረገወን አሰፋ ተዋናይ ናት፤ በዚህ ድራማ ውስጥም ተዋናይ ናት፡፡ ሌሎችም እንደዚሁ፡፡
እቴጌ
ይሄኛውም የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን (መዝናኛ ቻናል) ድራማ ነው፡፡ በነገራችን ላይ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ብዙ ተወዳጅ ፕሮግራሞችን ማሳየት ጀምሯል፡፡ በቅርቡ የተጀመሩ ድራማዎችም ኢቲቪ የብዙዎችን ቤት እንዲቆጣጠር አድርጎታል፡፡
ወደዚህ ድራማ ስንመለስ፤ እቴጌ ትንሽ ወጭበርበር ያለ ቢመስልም በውስጡ ግን የሚተነተኑ ሀሳቦችን የያዘ ነው፡፡ ዘመኑ ያለበትን ነባራዊ ሁኔታ የሚያሳይ ነው፤ አዲስ ሀሳብ ያለው ነው፡፡ ተዋናዮቹ በተለያየ መስክ የተመረቁ ናቸው፤ ያንን የተመረቁበትን መስክ በሥራዎቻቸው ላይ ያንፀባርቃሉ፡፡ ይህ ደግሞ ብዙም ያልተሰራበትና ሊሰራበት የሚገባ ነገር ነው፡፡
እነዚህን አምስት ድራማዎች ያመጣነው ‹‹ለምሳሌ›› ለማለት ያህል ብቻ ነው እንጂ ድራማዎችን ለማብራራት አይደለም፡፡ እያንዳንዱ ድራማ ሰፋ ያለ አስተያየት ይሰጥበት ቢባል ብቻውን ብዙ ሰፋፊ ትንታኔ ይወጣዋል። ምክንያቱም ሀሳብ ላይ ያተኮሩ ናቸው፤ ምሁራን የተሳተፉባቸው ናቸው፡፡ የኢትዮጵያን ታሪክ፣ ፖለቲካ፣ ባህል፣ ወግና እሴቶች የሚዳስሱ ናቸው፡፡ ስለዚህ አንዱ ክፍል እንኳን ብዙ የሚያስወራ ነው፡፡
እነዚህ ድራማዎች ሊመሰገኑ ይገባቸዋል፤ ምክንያቱም በዚህ ዘመን የሰውን ቀልብ መያዝ የቻሉ ናቸው፡፡ በዚህ ዘመን የሰዎችን ቀልብ መያዝ በብዙ ምክንያት ከባድ ነገር ነው፡፡ አንደኛ፤ ዘመኑ እንደ ድሮው ዘመን ሁሉ ነገር ብርቅ የሚሆንበት ነገር አይደለም፡፡ ሁሉም ሰው ሁሉ በእጁ ሁሉ በደጁ ነው፡፡ ብዙ ቀልብን የሚይዙ ነገሮች እጃችን ላይ አሉ፡፡ ከእነዚያ የተሻለ ስናገኝ ነው የምንሄደው፤ ስለዚህ እነዚህ ድራማዎች ያንን አሸንፈው የሰውን ቀልብ ገዝተዋል ማለት ነው፡፡
ሁለተኛ፤ አገራችን ብዙ ውጣ ውረድ ያለባት ናት። በዚህም በዚያም የምንሰማቸው ነገሮች ቀልብን የሚበታትኑ ናቸው፡፡ በዚህ ወከባ ውስጥ የሰውን ቀልብ መያዝ የሚችል ነገር ከተገኘ ያ ነገር በጣም አስፈላጊ ነው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ እሱንም ማሸነፍ ችለዋል፡፡
በዚህ ዘመን በምናባዊ ፈጠራ ማዝናናትም ሆነ ማስተማር መቻል ትልቅ ብቃት ነው፤ ምክንያቱም ነባራዊው ዓለም ከምናባዊ ፈጠራ በላይ ትዕንግርት ሆኗል። በዓለምም ሆነ በአገራችን የሚታዩ ነገሮች አስገራሚ ናቸው፡፡ ከፈጠራ ድራማ በላይ የገሃዱ ዓለም ድራማዎች ዓለምን እየተፈታተኑ ባለበት በምናብ ሥራ ማሸነፍ የዚህ ዘመን ፈተና ነው፡፡
በእርግጥ ምናብ የራሱ ውበት አለው፡፡ ከሀሳቡ ይልቅ ቴክኒካዊ ነገሩ ውበት ይሰጠዋል፡፡ ለዚህም ነው መልዕክት በኪነ ጥበብ ሥራዎች ሲተላለፍ አይረሴ የሚሆነው፡፡
ዘመን የራሱ መልክና ባህሪ አለው፡፡ ስለዚህ ይህ ዘመንም የራሱን መልክ ማስቀመጥ አለበት፡፡ አሁን ላይ የሚሆኑ ነገሮች በኪነ ጥበብ ሥራዎች መንፀባረቅ አለባቸው፡፡ ምክንያቱም የነገ ታሪክ ናቸው፡፡ የድሮ ሥራዎችን የምንወዳቸው ምናልባትም የትውስታ ባህሪ ስላላቸው ነው፡፡ ስለዚህ የዛሬ ሥራዎች ዛሬን በትክክል ወክለው ከሰሩ ነገ ደግሞ ከዛሬው በላይ ይወደዳሉ፤ ዘመን ተሻጋሪ የሚባለውም ለዚህ ነው፡፡
በቅርቡ ደግሞ አንድ ፊልም (ዶቃ) ተወዳጅ ሆኗል፤ ለጊዜው ፊልሙን አላየሁትም፡፡ የኢትዮጵያን ታሪክና ባህል የሚያሳይ ስለሆነ ነው የተወደደው ተብሏል፡፡ ከዚህ በፊትም ካየነው ልምድ አገርኛ ነገሮች ላይ የሚሰሩ የፊልም ሥራዎች ተወዳጅ ሆነዋል፡፡ አገርኛ ፊልም ከተሰራ አገርኛ ይዘት ሲኖረው ነው፤ የውጭ ባህልና ምንነት ለማሳየት ከሆነማ እኮ የውጮችን ፊልም በአገር ውስጥ ቋንቋ መተርጎም ማለት ነው፡፡
ድራማዎችና ፊልሞች የኢትዮጵያን ታሪክና ባህል ሲያሳዩ ይወደዳሉ፡፡ የሚወደዱበት ምክንያት ከወግ አጥባቂነት ወይም የድሮ ነገር ከመውደድ አንፃር አይደለም፡፡ ያልኖርነውን ዘመን በጥበብ ሥራዎች ማየት ስለሚያዝናናም ጭምር ነው፡፡ በተለይም ከታሪካዊ መጽሐፎችና ሰነዶች ላይ የሚሰሩ የጥበብ ሥራዎች ይህን ያሳያሉ። ከማዝናናት ባለፈ ደግሞ ከየት ተነስተን የት እንደደረስን ያሳዩናል፡፡
በእነዚህ በጠቃቀስኳቸው ድራማዎች ውስጥ ሌላው ውበታቸው አተዋወን ነው፡፡ በድራማዎችና ፊልሞች ውስጥ በጣም የተጋነነ (አርቲፊሻል) አተዋወን ይሰለቸኛል፤ የራሴው ችግር መስሎኝ ለሰው አልናገረውም ነበር፡፡ በኋላ ግን ብዙ ተመልካቾችም ሆኑ ባለሙያዎች ሲያወሩበት ሰማሁ፡፡ ከልክ ያለፈ አርቲፊሻል አተዋወን አሰልቺ ነው፡፡
ምንም እንኳን ሥራው የምናብ ፈጠራ መሆኑ ቢታወቅም፣ በገሃዱ ዓለም የማይታይ አይነት ክዋኔ ማሳየት ግን ከሰው ሕይወት ያወጣዋል። ለምሳሌ፤ በጣም የተጋነነ ደስታ (በገሃዱ የማናየው አይነት) በጣም አርቲፊሻል የሆነ አደነጋገጥ ወይም ብስጭት ድራማውን (ፊልሙን) ከሰው ሕይወት ያርቀዋል፡፡
በነባርና አንጋፋ ተዋናዮች ውስጥ የምናየው ግን ድራማ (ፊልም) መሆኑን እስከምንረሳው ድረስ ቀልብን የሚይዝ ነው፡፡ ምናልባትም ድራማ (ፊልም) መሆኑን ሳናውቅ ድንገት ተከፍቶ ብናገኘው ዘጋቢ ፊልም (እውነተኛ) ወይም ዜና ሊመስለን ይችላል፡፡ ምናልባት ተዋናዮቹ ስለሚታወቁ ድራማ (ፊልም) ነው ልንል እንችላለን፡፡
በአጠቃላይ በይዘትም ሆነ በቴክኒካዊ ቅንብር ተወዳጅ የሆኑ የጥበብ ሥራዎች እየታዩ ነው፡፡ ባለፉት ዓመታትም በተከታታይ ድራማ እነ እረኛዬ፣ በሲትኮም እነ ምን ልታዘዝ ተወዳጅ ሆነው እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ ዘመኑ በፈቀደው ቴክኖሎጂ ደግሞ በዩ ቲዩብ የሚታዩ እንደ አስኳላ (በአርትስ ቲቪ መታየት ጀምሯል) የመሳሰሉ ሀሳባዊ ድራማዎች አሉ፡፡ እንደ ተዋናይ ቲቪ ያሉ የዩትዩብ ቻናሎች ከተለመደው የዩትዩብ ስሜታዊ ሥራዎች ወጥተው አገርኛ ወግና ለዛ ያለው የጥበብ ሥራዎችን የሚያሳዩ ናቸው፡፡
የኪነ ጥበብ ሥራዎች ሲንቦጨራረቁ ስንወቅስ እንደነበረው ሁሉ ጥሩ ሆነው ሲገኙም ማድነቅና ማመስገን ይገባል፡፡ አለበለዚያ ከያኒዎቻችን ይህ ሕዝብ ምንም ቢያቀርቡለት አያመሰግንም በሚል ወደ ተስፋ መቁረጥ ነው የሚገቡት፡፡
ከእኛ ምሥጋና በላይ ግን ዘመን ተሻጋሪ ሥራዎች ሰርታችኋልና በእሱ ትኮራላችሁ! ምስጋናም ይገባችኋል!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 6/2015