ዘወትር የሚገኙት በሥራ ቦታቸው ነበር። ዛሬ ግን የደረስንበት ሰዓት ይሁን የዝናቡ ሁኔታ ከቤታቸው ከትመዋል። ያሉበትን ቦታ ለመፈለግ ታች ላይ ወረድን። በመጨረሻ ደምቆ ከሚታየው ሰፈር አስኮ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ዘለቅንና የቤተክርስቲያኑ አትክልተኛ መኖሪያ ቤታቸውን ሊጠቁሙን አብረውን ነጎዱ። የእንግዳችን ቤት ለቤተክርስቲያኑ ቅርብ ቢሆንም በቀላሉ የሚገኝ ግን አልነበረም። መንገድ ጠቋሚያችን እንኳን ጠፋባቸው። ድንገት ግን ከመሥሪያ ቦታቸው አንስቶ ወደቤታቸው ያደረሳቸውን ሰው አገኘን። ይህ ሰው የተወሰነ መግቢያውን አሳየን። ጠቋሚያችንም የመንደሩን ሰው ጠይቀው ወደ ቤቱ ተያይዘን አመራን።
የደጁ መግቢያ አይደለም በዊልቸር ለሚንቀሳቀስ አካል ጉዳተኛ ለጤነኛውም ይከብዳል። ድንገት አዳልጦ ከመሬት የሚቀላቅል አይነት ነው። የአካባቢው ጭቃ ከጫማ ላይ በቀላሉ የሚላቀቅ አለመሆኑን ላስተዋለ አካል ጉዳተኞች እንዴት ዊልቸራቸውን አንቀሳቅሰው ቤት እንደሚደርሱ ሲያስብ በእጅጉ ማዘኑ አይቀርም። እኛም ይህን እያብሰለሰልን እንደነገሩ የተሠራው ግቢ ውስጥ ደረስን ዓይናችን ድንገት ከአንድ የተከፈተ ቤት ላይ አረፈ። ቆም ብለን ወደዚያው ስናማትርም የምንፈልጋቸው አዛውንት በቤቱ ውስጥ ቁጭ ብለው ተመለከትናቸው።
በሩን አልፈን ወደውስጥ መዝለቅ ግን አልቻልንም፤ እግራችን ተገታ። በጥበቱ የተነሳ መቆሚያ መቀመጫ የለም። በዚያ ላይ ቤቱ በሚሠሯቸው ዘንቢሎችና ዊልቸር ተሞልቷል። ከእርሳቸው ውጪ ከአንዳችን በስተቀር መግባት ባንችልም ጠባቧን ክፍል አጨናንቀን እንደነገሩ ቁጢጥ ብለን ከአቶ ገብረጻዲቅ በየነ ጋር ወጋችንን ጀመርን።
በዚህች ጠባብ ቤት ዛሬም ፍላጎት ከተፈጥሮ እየተጋጨ፣ ፍጡር በተፈጥሮ እየተፈተነ ውሎ ያድራል። ለመኖርና እስትንፋስን ለማርዘም ምግብ ይሠራበታል። የአካል ጉዳተኝነት ፈተናን ተጋፍጦ ለእለት ጉርስ የሚሆን ገንዘብ ማምጫ ሥራም ይከናወንበታል።ይህ ቢሆንም ትንሽ ቤት ግን በደስታ እንደተሞላች ከአዛውንቱ አቀባበል ተረድተናል። ገጽታቸው እንደ ፀሐይ ያበራል፤ ደስታቸው ሌሎች ላይ ይጋባል።እንግዳ አቀባበላቸውን ስንመለከት ደግሞ ሙሉ አካል ቢኖራቸው ምን ሊያደርጉ ይሆን ያስብላል።
የእኛ አካሂድ እንደተለመደው ‹‹አይዞት›› ብሎ ለማጽናናት ነበር። ታሪካቸውን ለሌሎች አጋርተን እንዲታገዙ ለማድረግ ብናስብም አዛውንቱ የአካል ጉዳተኛ ግን ካሰብነው በተቃራኒ ሆነው አገኘናቸው። አዛውንቱ ሰው የሕይወት መምህር ናቸው፣ ለዓመታትም ለሌሎች ትምህርት ሆነው እንደዘለቁ ከሁኔታቸው ለመረዳት ጊዜ አልፈጀብንም። የእለት ከእለት ኑራቸውም በዚህ የተቃኘ መሆኑን ሥራቸው ይናገራል።
አዛውንቱ አካል ጉዳተኛ ሃሳባችንን ገዝተው በፈገግታቸው አስጥመውን የኋላ ታሪካቸውን ማውጋቱን ቀጠሉ።
ተወዳጁ ልጅነት
አዛውንቱ ገብረጻዲቅ ከላሊበላ ከተማ ትንሽ ራቅ ብላ በምትገኘው አቡነ ዮሴፍ የምትባል ቦታ ነው አብዛኛውን የልጅነት ጊዜያቸውን ያሳለፉት። የዛሬን አያድርገውና በቀዬው ካሉ የሰፈር ልጆች ጋር ቦርቀው ተጫውተዋል። እናት አባታቸው አርሶ አደር በመሆናቸው የሚጎልባቸው ነገር አልነበረም።
ቤተሰቡ በእርሻ ብቻ ሳይሆን በከብት እርባታም ይታወቅ ነበርና በማር በወተት አድገዋል።የየራሴ የሚሏቸው ከብቶችም ስለነበሯቸው ደስተኛና ሥራ ወዳድ ሆነው የልጅነት ጊዜያቸውን አሳልፈዋል። በከብት እረኝነቱ፤ በከብት ርባታው፤ በቤት ውስጥ ደግሞ የጓሮ አትክልትና ፍራፍሬውን መኮትኮቱ ላይም ብርቱ ሆነው የልጅነት ጊዜያቸውን አሳልፈዋል። ከእኩዮቻቸው ጋር መጫወቱ የእርሳቸው የዘወትር የልጅነት ሥራና ትዝታም ሆኖም አልፏል።
የአዛውንቱ የልጅነት ጊዜ ክረምት ብቻ ሳይሆን በጋም በሥራ ነበር ያለፈው።ክረምቱን እስከ ታኅሣሥ በእርሻ ሥራ ተጠምደው ይቆያሉ። እህሉን ከጎተራው አስገብተውም እፎይ ማለትን አያውቁም። በጋው ላይ በተለይም በግቢያቸው ችግኞችን በመትከልና በመንከባከብ ይታወቃሉ። ስለዚህም በመስኖ ተጠቅሞ መሥራት ትናንት የሚያውቁት ነበር። ይህ ደግሞ ከቤተሰባቸው አልፈው ለአካባቢው ሰው እንዲተርፉ አድርጓቸዋል።
ሥራ ወዳዱ አዛውንት በቅጽል ስማቸው ዓባይ እየተባሉ ይጠሩ ነበር። ልጆቻቸውም ዛሬ የሚጠራቸው በዚህ ስም ነው። ይህ ስማቸው ቀድመው ትርጉሙን ባያስቡትም ዛሬ ላይ ሆነው ሲያጤኑት ግን ከሥራቸው ጋር የተሳሰረ እንደሆነ ያስባሉ። ምክንያቱንም ሲያስረዱ ጊዜው 1977ዓ.ም ርሃብ አካባቢያቸው ላይ የገባበት ነበር። ግቢያቸው ሞልቶ ተርፎት እያለ እርሳቸው ግን ይህንን አላይም ብለው በ30 ሳንቲም ጎመን እየገዙ ለመመገብ ላሊበላ ከተማ ገብተዋል። በተቃራኒው የአካባቢው ሰው የእርሳቸውን ግቢ በነፃ ይጎበኛል። ምርቱን እያፈሰም ይጠቀማል። ሲተርቱባቸውም ‹‹ አይ ዓባይ የሰው ሲሳይ›› ይሏቸዋል ነበር።እናም መሥ ራታቸው እንደ ዓባይ ለሌሎችም መትረፍን እንደሚያጎናጽፍ ከዚህ ስማቸው ተረድተዋል።
ከ20 ዓመታቸው በኋላም ቢሆን ይህንኑ ተግባራቸውን አጠናክረው ነው የቀጠሉት። ምክንያቱም ዛሬ አባወራ ለመሆን ታጭተዋል።የሰባት ዓመት ልጅ የሕይወት አጋር ትሆናቸው ዘንድ አደራ ተሰጥቷቸዋል። ስለዚህም የቀደመውን ማንነታቸውን በይበልጥ ማጉላት አለባቸውና ብርቱ ገበሬ መሆናቸውን እያስመሰከሩ ቀጥለዋል። አዲሷን ባለቤታቸውን ለመንከባከብም ብዙ ለፍተዋል።
በሀገሬው ባሕል አሳድጎ ማግባት ብዙ ነገርን ይጠይቃል። በተለይም የትዳር አጋራቸው እንድትወዳቸው ማድረግ ብዙ ድካምን የሚፈልግ ነው። እርሳቸውም ይህንን እውን ለማድረግ የቻሉትን ያህል ደክመዋል። ሆኖም ታግለው የማይጥሉት ነገር ገጠማቸውና የትዳር አጋር እንድትሆናቸው የተሰጠቻቸውን ልጅ ተለዩዋት።የኋላ ኋላ ግን ብርቱ መሆናቸውን የተረዳች ውሃ አጣጭ አግኝተው የልጆች አባት ሆነዋል።
የነሐሴ መባቻው ሕመም
በአካባቢያቸው ወረርሽኝ የተከሰተው በየካቲት ተድረው በመጋቢት ላይ ነበር። በዚህ ወረርሽኝም ብዙዎች ሞተዋል፤ የአካል ጉዳትም አጋጥሟቸዋል። የዚህን ጊዜ የእነገብረጻዲቅ ቤተሰብ ተጨነቀ። ልጆቻቸውን የት እንደሚያደርሷቸው ግራ ገባቸው። ቤተሰቡ ድንገት የመጣለትም ለጊዜው ካሉበት ከተማ ወደ ላሊበላ ከተማ ማሸሽ ነውና ወስነው አደረጉት። እስከ ሐምሌ ድረስም ምንም አልነካቸውም ነበር። ይሁን እንጂ የነሐሴ መባቻ ወረርሽኙ ቦታ ሳይመርጥ ያሉበት ላሊበላ ደርሶ ባይገላቸውም የማይድን ጠባሳን ጥሎባቸው አለፈ። ሁለቱንም እግራቸውን ነጠቃቸው።
በወቅቱ ፈጥነው ወደ ሕክምና መሄድ ቢችሉ ኖሮ የሆነ መፍትሔ ያገኙ ነበር። ግን አልሆነም። የገጠር ሕይወት የሀገር ቤት ኑሮ ቢያግዳቸው ቀናት ተቆጠሩና መጀመሪያ አንድ እግራቸውን ቀጥሎ ደግሞ በሕክምና ሁለተኛ እግራቸውን አጡ። የመጀመሪያ እግራቸው ከጥቅም ውጪ የሆነው ቤተሰብ ይድኑበታል ብሎ ባሰበው ባሕላዊ ሕክምና ምክንያት ነው። ይህም በማር ሸፍነው ይድናል ብለው መጠበቃቸው ነበር።ሆኖም ያሰቡት ቀረና ያላሰቡት ሆነ፤ እግራቸውም እንዲቆረጠ ሆነ። ሁለተኛ እግራቸውንም በሕክምና እንዲያጡ ተገደዱ።
የሕክምናው ፈተና
አዛውንቱ ገብረጻዲቅ ምኒሊክ ሆስፒታል ሲመጡ ብዙ ነገሮች ፈተና ሆነውባቸው ነበር። አንዱ ጊዜው ሲሆን፤ 1983 ዓ.ም የነበረው ጦርነትና የሰዎች አለመረጋጋት ነው። ስለዚህም ሆስፒታል ቢደርሱም በቀላሉ ሐክምና ማግኘት አልቻሉም። በሩ ላይ ተቀምጠው ዕለት በዕለት የሚመለከቷቸው ሐኪሞች ቢኖሩም መፍትሔ ሊሰጧቸው አልቻሉም። በዚህም በከባድ ስቃይ ውስጥ ዓመት ሙሉ አሳለፉ። መላ አካላቸው እየዛለም መጣ።የእግራቸው ጉዳት ከፍቶ ያሰቃያቸው ገባ።
የሁለተኛው እግራቸው ችግር መንስኤ በአውራ ጣታቸው አካባቢ የተፈጠረው እብጠት ነው። ኪንታሮት ይመስላል። እናም እብጠቱ እያደር ወደሌላው የእግር ክፍላቸው በመዛመቱ ቶሎ መፍትሔ ካላገኙ ሊገላቸውም ይችላልም። እርሳቸው ጊዜ ሳይፈጁ ወደ አዲስ አበባ መጡ።ተቀባይ አጡ እንጂ።መፍትሔ የተሰጣቸውም ምኒሊክ ሆስፒታል በር ላይ ደጅ ጠንተው ዓመት ካሳለፉ በኋላ ነው። እርሱም ቢሆን አንድ ሩህሩህ ሐኪም ረድቷቸው ነው። ስሙ ዐቢይ ይባላል።አልጋ ፈልጎ አስያዛቸውና ተንከባከባቸው።
ሐኪሞች የተቻላቸውን ሁሉ እንዲያደርጉላቸው ጥረት ተደረገ። ነገር ግን በጣም የተጎዳ በመሆኑ የሐኪሞቹ ድካም ፍሬ አላገኘም። እንደበፊቱ የሚራመዱበት ተስፋ አልተሰጣቸውም። ቆሞ መሄዱ ይቅርና ኖረው በዊልቸር ይሂዱ ተብለው ተፈረደባቸው። እግራቸው ተቆረጠም።አሁን ጉዟቸው እንደቀደመው በአንድ እግር ሳይሆን በዊልቸር ነው።
የኑሮ ሀሁ
አዛውንቱ ገብረጻዲቅ ከሆስፒታል ከወጡ በኋላ በቀጥታ ወደ ትውልድ ቦታቸው ነበር ያመሩት። እንደልቡ ተንቀሳቅሶ ለማይሠራ ሰው ደግሞ አዲስ አበባ መቀመጥ ከባድ ነው። እናም እንደልብ መውጣትና መግባት አይሆንላቸውምና ቀጥታ መሥራት የሚችሉትን እያደረጉ ለመቆየት ምርጫቸውን ላሊበላ ከተማን አደረጉ። ቤት ተከራይተውም ከልጆቻቸው እናት ጋር መኖር ጀመሩ።ባለቤታቸው ምግብ እየሠራች ትንከባከባቸዋለች። እርሳቸው ደግሞ በቻሉት ልክ የእጅ ጥበባቸውን ተጠቅመው ለቤቱ የገቢ ምንጭ ይፈጥራሉ።
በሰው እጅ መብላትና የሰው እጅን መጠበቅ በፍጹም አይሆንላቸውም። የራሳቸውን ፍሬ ማግኘት ይፈልጋሉ። እናም መጀመሪያ የልብስ ጥልፍ በመሥራት ከዚያም ጎን ለጎን ጭራ ሠርቶ በመሸጥ ይተዳደሩ ጀመር። አለፍ ሲል ደግሞ የተለያዩ ዘንቢልና ማርገብገቢያዎችን መሥራት ቀጠሉ። ደስተኛና ጥሩ የሚባል ኑሮን ይኖራሉ። ይህ ቢሆንም ግን ደስታቸው በዚያ ብቻ እንዳይገደብ ይፈልጋሉና ለቤተሰቡ የተሻለ ኑሮ ቀያቸውን ለቀው ወደ አዲስ አበባ ነጎዱ።
አዛውንቱ በአዲስ አበባ
አዛውንቱ ገብረጻዲቅ አዲስ አበባን ሲመርጡ ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ እንደማይሆንላቸው ቢረዱም በዚህ ልክ ግን እንገላታለሁ ብለው አላሰቡም። መጀመሪያ ቤት ኪራዩ ከዚያም ደግሞ ሥራቸውን የሚረከባቸው ሰው በቀላሉ አላገኙም።እናም ዓመታትን በችግርና በስቃይ አሳልፈዋል።ጐዳና ነው ቤቴ ብለውም ያውቃሉ። ትንሽ ሲነሱ ደግሞ አንዴት አቃቢት ከጎናቸው ካለ ቤት አስጠግተዋቸው ኖረዋል። ዛሬ ደግሞ እኅተ ማርያም በምትባል ግለሰብ የቤት ኪራይ ተከፍሎላቸው ይኖራሉ።
የእጅ ጥበባቸውን በመጠቀም የተለያዩ ሥራዎችን የሚሠሩት እኚህ አዛውንት፤ ትናንት ከቤተሰቡ ጋር ሆነው ይሠሩት የነበረውን ከዓይናቸው መድከም ጋር በተያያዘ ቀንሰው ትኩረታቸውን ዘንቢል ላይ አድርገው ከ20 ዓመት በላይ አሳልፈዋል።ዘንቢሉም ቢሆን የመሥሪያ ግብዓቱ ዋጋ በመጨመሩ አልተውትም እንጂ በብዙ ፈትኗቸዋል።እርግፍ አርገው ያለመተዋቸው ምስጢር በሥራው ልጆቻቸውን አስተምረዋል፤ ባለቤታቸው ምንም እንዳይጎልባቸው አድርገዋል።ዛሬም ቢሆን ምንም እንኳን ልጆቻቸው ቢደርሱም ልጆቹም ‹‹እኛ ጋር ና›› ቢሏቸውም በማንም ላይ ጥገኛ መሆን አይፈልጉምና የምግባቸውን ፤ ቋሚ ንብረት ሊኖረኝ ይገባል ብለው ለሚከፍሉት ኮንደሚኒየም ቁጠባ የሚሸፍኑት በዚህ ሥራቸው ነው።
አዛውንቱ ገብረጻዲቅ፤ ዛሬ የሁለት ልጆች አባት ከመሆን አልፈው አያት ናቸው።በዊልቸር ሊቀመጡ ግድ ቢሆንም ደስታቸው እጥፍ ድርብ እንደሆነ ያምናሉ።እንደልብ እንዲንቀሳቀሱ እግር የሆናቸውን የዊልቸር ደጋፊ ቲሻዬር ኢትዮጵያንም ያመሰግናሉ። አንድ ነገር ቀረኝ የሚሉትና መንግሥትን የሚጠይቁት ‹‹በዚህ አቅሜ ስቆጥብ ቆይቼ ኮንደሚኒየሙን አላገኘሁምና እባካችሁ አግዙኝ›› የሚለውን ብቻ ነው።
የአረጋዊው ምክር
‹‹ሰው ደስታውንም ኑሮውንም በራሱ ይመርጣል፤ ያስተናግዳልም።›› የሚል እምነት ያላቸው አዛውንቱ ገብረጻዲቅ፤ አካሌ ጎደለ እድሜ ተጫጫነኝ ብለው ለልመና ጎዳና አልወጡም፤ በአቅማቸው መጠን ደክመዋል፤ በአካልም ቢሆን ሲያዩዋቸው ሁሉም ሰው የሚሳሳላቸው አይነት ናቸው። ሆኖም ‹‹ልመናን በእጅጉ እጸየፈዋለሁ›› ይላሉ። ከተፈጥሮ ሕግ መሸሽ፣ ከእውነታ ጋር መጣላት፣ የትም አያደርስምና የሆነውን ተቀብሎ በመሥራት ራስን ማስከበር ያስፈልጋል ባይም ናቸው።
‹‹እኔ ጆሮ ከሆንኩ ሌላ ሰው ደግሞ እጅ ይሆናል። ተባብሮ መሥራትን ከዚህ አኳያ ነው የማየው የሚሉት አዛውንቱ፤ ሁሉም ሰው ህሊና አለው። የሚዳኘውም በዚህ ተፈጥሮ ሕግ ብቻ ነው ብለው ኑሮን ይገፋሉ።ሌላ ሰው ቢያይም ባያይም፣ አመስጋኝና ወቃሽ ታዛቢዎች ባይኖሩም፣ ጥሩ ወይም መጥፎ ነገር በስውር ብንሠራም፣ ሕሊናችን በስውር ያያል፤ ይፈርዳልም። ስለዚህም ወጣት ሆነው ጉልበት እያላቸው የማይሠሩ፤ ለመጠጫ የሚለምኑ በቤተክርስቲያን አካባቢ ስመለከት በጣሙን እበሳጫለሁ ይላሉ። የእነርሱን ጉልበትና ወጣትነት ቢሰጠኝ ስንት ቤተሰብ እንደምመራበትም ሳስብ ዝም ብዬ ላያቸው አልፈልግም። ከሰሙኝ በሚል ተጠግቼ እመክራቸዋለሁ ይላሉ።
አይደለም ወጣቱ ሁሉም ሰው ሥራ ከሆነ ልቡ ተረጋግቶ በፍሬው መደሰት እንዳለበት ያምናሉ። እናም ልመናን ሥራ ለሚያደርጉ ሁሉ አንድ ነገር ይናገራሉ። ‹‹ልመና ብዙ ያንገላታል፤ ያዋርዳል፤ ተስፋን ይነጥቃል።ስለዚህም የሥራ ክፉ ልመና ነውና አትከተሉት ይላሉ።የእኔ ብልሀትም ፤የእኔ ጉልበትም እዚህ አላደረሰኝም የፈጣሪ እገዛ እንጂ። በሆነብኝ ነገር ሳልበሳጭ በሆነልኝ ሁልጊዜ እደሰታለሁ። እናንተም ማድረግ ያለባችሁ ይህንኑ ነው ሲሉ ምክራቸው ይሰጣሉ።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሐምሌ 8/2015