ሕይወት ፈርጀ ብዙ ናት። ማንኛውም ሰው እዚህ ምድር ላይ ሲኖር አነሰም በዛ የሚኖርለት ዓላማና ምክንያት ይኖረዋል። ዓላማውን ለማሳካትም በሕይወት መንገድ ውስጥ መውጣት መውረድ፤ ማግኘት ማጣት፤ አባጣ ጎርባጣ የሆኑ መንገዶችን ሁሉ ማለፍ የግድ ይለዋል። ወጣ ገባ በሆነ የሕይወት ጉዞ ተግቶ ማለፍ የሚችል ብርቱ የልቡን መሻት ሞልቶ የሚኖርለትን ዓላማ ማጣጣም ይችላል።
የዕለቱ እንግዳችንም በሕይወት መንገድ ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፈው የልባቸውን መሻት ለማሳካት በብዙ ታግለው ውጤታማ መሆን ችለዋል። እንግዳችን አቶ ቀልቤሳ ቀቀባ የኬኬጊቲ /KKGT/ ኢምፖርት ኤክስፖርት መስራችና ባለቤት ናቸው። ድርጅቱ በዋናነት የግብርና ግብዓቶችን በተለይም ኬሚካሎችን ከውጭ አገር በማስመጣት ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ያደርጋል፤ በተመሳሳይ ቡናን ጨምሮ የተለያዩ ጥራጥሬዎችንና የቅባት እህሎችን ኤክስፖርት ያደርጋል። ድርጅቱ ወደፊት በተለያዩ ዘርፎች የመሰማራት ሰፊ ራዕይን ሰንቆ የሚንቀሳቀስ ሲሆን፣ ለግብርናው ዘርፍ ግን ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ብዙ የመስራትና ዘርፉን የማዘመን ዕቅድ አለው።
ከልጅነት እስከ ዕውቀት በንግድ ሥራ ተሰማርተው የተለያዩ የንግድ ሥራዎችን ሰርተው ማለፍ የቻሉት አቶ ቀልቤሳ፤ ብዙ ገንዘብ መቁጠር የልጅነት ምኞታቸው ነበር። ለዚህ ምኞታቸው ታዲያ ልጅ እያሉ ጀምሮ በርካታ የሙዝ ቅጠሎችን በጥንቃቄ ቆራርጠው በማሰር ‹‹ብር ነው›› በማለት እየቆጠሩ ይጫወቱ እንደነበር አጫውተውናል።
በንግድ ሥራ ብዙ ገንዘብ ማግኘት እንደሚቻል ገና በልጅነት ዕድሜያቸው የተገነዘቡት አቶ ቀልቤሳ፤ የሁልጊዜ ምኞታቸው የነበረውን የንግድ ሥራ ማሳካት ችለዋል። በኦሮሚያ ክልል ወለጋ ሆሮጉድሩ ወረዳ ደዱ ከተማ ተወልደው ያደጉት አቶ ቀልቤሳ፤ የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በደዱ ከተማ ተከታትለዋል። ከመደበኛ ትምህርታቸው ጎን ለጎንም ከትንሽ እስከ ትልቅ የተባሉ በርካታ የንግድ ሥራዎችን በዚች ከተማ ሠርተዋል። ከንግድ ሥራዎቹ መካከልም ዛሬ ለደረሱበት ደረጃ መሰረት ጥሎላቸው እንዳለፈ የሚናገሩለት የልብስ ስፌት ሥራ አንዱ ነው።
የልብስ ስፌትን ከአጎታቸው የተማሩት አቶ ቀልቤሳ፤ በልምድ ብቻ ባገኙት የልብስ ስፌት ዕውቀት ከውስጥ በመነጨ ፍላጎትና በብርቱ ትጋት ሌት ተቀን ሳይሉ ሰርተዋል። ረዘም ላለ ጊዜ በብዙ ትጋት ልብስ ይሰፉ እንደነበርም አጫውተውናል። የሰፏቸውን አልባሳትም ለገበያ በማቅረብ ጠርቀም ያለ ገንዘብ ማግኘት ሲችሉ ነጋዴ የመሆን የልጅነት ህልማቸውን ዕውን ለማድረግ በአካባቢያቸው የሸቀጥ ሱቅ ከፈቱ።
አሁንም ድረስ ለሥራ ከፍተኛ ተነሳሽነት ያላቸው አቶ ቀልቤሳ፤ በአፍላ የወጣትነት ዕድሜያቸው የጀመሩት አንድ ሥራ ሌላ ተጨማሪ ሥራ እየወለደ በአሁኑ ወቅት አስመጪና ላኪ ደረጃ ላይ አድርሷቸዋል። በሸቀጥ ሱቅ የጀመረው የንግድ ሥራቸው አድጎ በወረዳቸው ሱፐርማርኬት መክፈትና ቀጥለውም በአካባቢያቸው ለሚገኙ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የጽህፈት መሣሪያዎችን ማቅረብ የቻሉት አቶ ቀልቤሳ፤ የንግድ ሥራን ከውስጥ በመነጨ ፍላጎትና ተነሳሽነት በመሥራታቸው ውጤታማ መሆን እንደቻሉም ይናገራሉ።
በተለያዩ ጨረታዎች በመወዳደርና ወዲህ ወዲያ በመሯሯጥ የጽህፈት መሣሪያዎችን ማቅረብ ዋነኛ ሥራቸው ያደረጉት አቶ ቀልቤሳ፤ ሥራቸውን ለማስፋት ከዛሬ 15 ዓመት በፊት ነው ወደ አዲስ አበባ ያቀኑት። የጽሕፈት መሣሪያዎችን ገዝተው ለመላክ አዲስ አበባ ውስጥ ረዘም ያለ ቆይታ ማድረግ የግድ ይላቸው ነበርና ሥራቸውን ለማሳለጥ እንዲያስችላቸው ንግድ ፈቃድ አውጥተው ቢሮ ተከራይተው ሥራውን ተዘዋውረው መሥራት ቀጠሉ። ሥራው እየሰፋ ሲመጣም ለሶስት ሰዎች የሥራ ዕድል በመፍጠር እንዲሁም ሥራውን ለሌሎች በማስተማር ብዙዎችን ወደ ዘርፉ በመሳብ የጽሕፈት መሣሪያ አስመጪ እስከመሆን ደርሰዋል።
ማንኛውንም ሥራ በብርቱ ጥረትና ልፋት መሥራት ከተቻለ ውጤታማ መሆን ይቻላል ብለው የሚያምኑት አቶ ቀልቤሳ፤ አስመጪነት ደረጃ የደረሱት ሠርቶ ለመለወጥ ካላቸው ከፍተኛ ፍላጎትና ብርቱ ጥረት እንደሆነ ይገልጻሉ።
አቶ ቀልቤሳ ብዙ ባይገፉበትም በትራንስፖርት ዘርፍ ጭምር ተሰማርተው ሰርተዋል። ‹‹ሰው የአፉን ፍሬ ይበላል›› እንዲል ታላቁ መጽሐፍ፣ ሥራ ሳይመርጡ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ መሥራት በመቻላቸው የልባቸው መሻት የነበረውን ብዙ ብር መቁጠር በአስመጪና ላኪነት የንግድ ሥራቸው ማሳካት መቻላቸውን ይገልጻሉ። ዛሬ ላይ ለሚገኙበት ማማ ለመድረሳቸው በርካታ ውጣ ውረዶችን ማሳለፋቸውና ብዙ ጥረት ማድረጋቸው መሆኑን ነው የሚናገሩት።
ለሥራ ከፍተኛ ፍላጎትና ተነሳሽነት ያላቸው አቶ ቀልቤሳ፤ ከእርሳቸው ተነሳሽነት በተጨማሪ ዛሬ ለደረሱበት ደረጃ እንዲደርሱ የግብርና ሚኒስቴር ሚና እንዳለውም ይጠቅሳሉ። የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ከየክልሉ አንድ አንድ ባለሃብት የግብርና ግብዓቶችን እንዲያቀርብ ባደረገው ጥሪ መሰረት እርሳቸውም ወረዳቸውን ወክለው ተወዳደሩ። ውድድሩን በማሸነፍ ዘርፉን የተቀላቀሉት አቶ ቀልቤሳ፤ አካባቢያቸውን ወክለው የግብርና ግብዓት አገልግሎት ማዕከልን በመገንባት ወደ ሥራው ለመግባት ጊዜ አላጠፉም። በወቅቱ የአግሮ ኬሚካል አስመጪነት ፈቃድ በማውጣት የተለያዩ የጸረ አረም ምርቶችን ለማስመጣት ተዘጋጁ። ከዝግጅቱ አንዱ የሚስመጧቸውን የምርት አይነቶች በንግድ ስም ማስመዝገብ ቀዳሚው ነበርና ሕጉን ተከትለው በማስመዝገብ ምርቶቹን አንድ በአንድ ማስመጣት ጀመሩ።
የውጭ ገበያውን ዳሰሳ በማድረግና ተፈላጊ የሆኑ ጸረ አረሞች የትኞቹ እንደሆኑ በመለየት ለመጀመሪያ ጊዜ ‹‹ግላይን›› የተባለ ጅምላ ጨራሽ አረምን የሚያጠፋ መድሃኒት ማስመዝገብ ችለዋል። የመጀመሪያ የሆነውን ምርት ካስመዘገቡ በኋላም ሌላውን በማስከተል 32 የሚደርሱ የተለያዩ አግሮ ኬሚካሎችን ማለትም ጸረ ነፍሳትን፣ ጸረ አረም፣ ጸረ ሻጋታና ሌሎችንም ከውጭ አገር ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ዝግጅት አድርገዋል። ለዚህም የምርምር ሥራውን ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ ሠርተዋል። ከ32ቱ የግብርና ኬሚካሎች 16 የሚደርሱ ምርቶችን በላብራቶሪ በመለየት አስመዝግበው ወደ ሥራ የገቡ ሲሆን፤ ባለፈው ሳምንት በተጀመረው የ2016 በጀት ዓመትም ተጨማሪ ሶስት አይነት ምርቶችን በማስመዝገብ በድምሩ 19 አይነት የግብርና ኬሚካሎችን ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ለአርሶ አደሩ እያቀረቡ ይገኛሉ።
በKKGT አስመጪነትና የንግድ ስያሜ ከተመዘገቡት 19 የግብርና ኬሚካሎች ውስጥ ዘንድሮ 14 የሚደርሱትን የግብርና ኬሚካሎች ወደ አገር ውስጥ በማስገባት ለገበያ ማቅረብ እንደቻሉ የጠቀሱት አቶ ቀልቤሳ፤ ለገበያ ካቀረቧቸው የግብርና ኬሚካሎች መካከልም ጅምላ ጨራሽ የሆኑ ጸረ ነፍሳት፣ ጸረ አረም፣ ጸረ ፈንገስ ወይም ሻጋታ፣ ጸረ ተባይና ሌሎችም እንደሚገኙበትና ምርቶቹም በስፋት ከቻይና እንዲሁም ከህንድ እንደሚመጡ ተናግረዋል። የግብርና ኬሚካሎቹ ለሁሉም አይነት ሰብሎች እንዲሁም አትክልትና ፍራፍሬዎች የሚያገለግሉ ናቸው።
የተለያዩ የግብርና ኬሚካሎች ስለመኖራቸው የጠቀሱት አቶ ቀልቤሳ፤ መሬቱ ሳይጎዳ አረሙን ብቻ መርጦ የሚጨርስ ጅምላ ጨራሽ ኬሚካል ስለመኖሩ ይናገራሉ፤ ይህም አረሞቹን ጨርሶ መሬቱን ለእርሻ ዝግጁ ለማድረግ እንደሚያስችል፣ ለአረም ሥራ የሚያስፈልገውን የሰው ኃይል ብዛት እንደሚቀንስ ይናገራሉ። አረሙን መርጦ የሚያጠፋው ኬሚካል በተለይ ቅጠለ ሰፋፊ አረሞችን መርጦ እንደሚያጠፋ ለጤፍ፣ ለስንዴና ለሌሎች የሰብል አይነቶች እንደሚያገለግል ነው ያስረዱት።
አቶ ቀልቤሳ የግብርና ኬሚካሎቹን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ለማድረግ በግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የተቋቋሙ የግብርና ግብዓት አገልግሎት ማዕከላትን ይጠቀማሉ፤ እነዚህ ማዕከላትም በሀገሪቱ በሁሉም ክልሎች የሚገኙ ሲሆን፤ በኦሮሚያ ክልል ብቻ 105 አካባቢዎች፣ በአማራ ክልል 87 ቦታዎች ላይ ይገኛሉ፤ በደቡብ ክልልም እንዲሁ 57 ቦታዎች ላይ ማዕከላቱ ይገኛሉ። ይሁንና በሶስቱም ክልሎች የአቅርቦት ችግር ስለመኖሩም አመልክተዋል። ያም ቢሆን በእነዚሁ ማዕከላት አማካኝነት አርሶ አደሩ የግብርና ኬሚካሎቹን እንዲያገኝ ኬኬጌቲ /KKGT/ ኢምፖርት ኤክስፖርት ጋራ እየሠሩ መሆናቸውን ይገልጻሉ።
በሶስቱ ክልሎች የሚገኙ የግብርና ግብዓት አገልግሎት ማዕከላት በኦሮሚያ መሪ ገነማ፣ በአማራ ፈለገ ግዮን፣ በደቡብ ጊቤ የግብርና ግብዓት አቅራቢ በሚል ስያሜ በአክሲዮን የተደራጁ ናቸው። በኦሮሚያ ለተደራጀው መሪ ገነማ የግብርና ግብዓት አቅራቢ አክሲዮን ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ቀልቤሳ፤ በአማራና በደቡብ ክልል ከተቋቋሙት ማህበራት ጋር ጠንካራ ግንኙነት እንዳላቸው ይገልጻሉ፤ እርስ በእርስ ትስስር በመፍጠር KKGT ኢምፖርት ኤክስፖርት የሚያስመጣቸውን የግብርና ኬሚካሎች ለሶስቱም ክልሎች ተደራሽ እያደረገ ነው። በመሆኑም አርሶ አደሩ ከእነዚሁ ማዕከላት ግብዓቶቹን በተመጣጣኝ ዋጋ እያገኘ መሆኑን ተናግረዋል።
ለግብርናው ዘርፍ አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶች ለአርሶ አደሩ በወቅቱና በሚፈለገው መጠን ተደራሽ መሆን እንዳለባቸው የሚያምኑት አቶ ቀልቤሳ፤ በሀገር ውስጥ መመረት የሚችሉትን በሀገር ውስጥ ለማምረት የሚደረጉ ጥረቶች ስለመኖራቸው ነው የገለጹት፤ ይህም በድርጅታቸው የረጅም ጊዜ ዕቅድ ውስጥ ተካትቶ ጥናት እየተደረገበት መሆኑን ተናግረዋል። በኢትዮጵያ የግብርና ኬሚካል አምራች ፋብሪካ ብቸኛው አዳሚ ቱሉ መሆኑንም ጠቁመው፤ የኢትዮጵያ ባለሃብቶች በግብርናው ዘርፍ በስፋት ገብተው መሳተፍ እንዳለባቸውም አመላክተዋል።
የግብርና ኬሚካሎችና ሌሎች ከውጭ ሀገር ወደ ሀገር ውስጥ ለሚስገቧቸው ምርቶች የውጭ ምንዛሪ ማነቆ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ቀልቤሳ፤ ይህን ችግር መፍታት እንዲያስችላቸው ቡና፣ የተለያዩ ጥራጥሬዎችና የቅባት እህሎችን ለውጭ ገበያ መላክን አማራጭ ማድረጋቸውን ይናገራሉ። በአሁኑ ወቅትም ሌሎች የተለያዩ የግብርና ምርቶችን ወደ ውጭ ገበያ ልከው የሚያገኙትን የውጭ ምንዛሪ ወደ ሀገር ውስጥ ለሚያስመጧቸው የግብርና ኬሚካሎች ለመጠቀም ዝግጅታቸውን አጠናቅቀዋል። ያም ቢሆን በተጓዳኝ ግብዓቶቹን በሀገር ውስጥ ለማምረት ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ እንደሆነም አቶ ቀልቤሳ ይጠቁማሉ።
በንግድ ሥራ ተሰማርቶ ገንዘብ መቁጠር የልጅነት ህልማቸው ሆኖ ያደጉት አቶ ቀልቤሳ፤ ህልማቸውን መኖር ችለዋል። በቀጣይም ያቀዷቸውን ሰፋፊ ሥራዎች ለመከወን ሙሉ አቅማቸውን ተጠቅመው እየታተሩ ይገኛሉ። ብቻቸውን የጀመሩት የንግድ ሥራም ለሁለት፣ ለሶስት እያለ በአሁኑ ወቅት 25 ለሚደርሱ ዜጎች በቋሚነት የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል። በተጨማሪም በኮንትራት የሚያሠሯቸው በርካታ ዜጎች እንዳሉም ተናግረዋል። በዱከም ከተማ በ2016 ዓ.ም የሚጀምሩት ኢንቨስትመንት በቀጣይም ሰፊ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ይጠቁማሉ። ኢንቨስትመንቱ ወደፊት የሚለይ ቢሆንም፣ ለጊዜው በኤሌክትሪክ ዘርፍ የዳታ ኬብል ለማምረት ዝግጅታቸውን አጠናቅቀዋል። በግንባታ ወቅት ከሚፈጥሩት የሥራ ዕድል በተጨማሪ ግንባታው ተጠናቅቆ ወደ ሥራ ሲገባ 250 ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር የሚችል መሆኑን አጫውተውናል።
ማህበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ረገድ ከትውልድ ስፍራቸው ጀምሮ በሥራ አካባቢያቸው የተለያዩ ድጋፎችን ያደርጋሉ። በተለይም በትውልድ አካባቢያቸው ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰባቸው ጭምር አርሶ አደሩ ማግኘት የሚገባውን የግብርና ግብዓት እንዲያገኝ ብዙ ዋጋ እየከፈሉ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ቀልቤሳ፤ ተደጋጋሚ ዝርፊያ እንደደረሰባቸውም ነው የጠቀሱት። ይሁንና ይህን ተቋቁመው የአርሶ አደሩ መሬት ጾም እንዳያድርና ማምረት እንዲችሉ ከችግሮች ጋር ተጋፍጠው ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ይገኛሉ።
በግብርናው ዘርፍ በርካታ ሥራዎችን የመሥራት ፍላጎት እንዳላቸው ጠቁመው፣ በተለይም የእርሻ መሣሪያዎችን በማምረት ግብርናውን የማዘመን ራዕይ እንዳላቸው ተናግረዋል። በግብርናው ዘርፍ መሰማራት ሕዝብን ማገልገል መሆኑን ጠቅሰው፣ ከልብ በመነጨ ፍላጎት ደስ እያላቸው ሊሰሩት እንደሚችሉም ተናግረዋል። ሌሎች ባለሃብቶችም ወደ ዘርፉ እንዲገቡም ይመክራሉ። መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል ማድረግ ከቻለ ግብርናውን ማዘመን እንደሚቻልም አመላክተዋል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 8/2015