በሀገሪቱ ግንባታ በስፋት ይስተዋላል፤ ከፍተኛ የግንባታ ፍላጎት እንዳለም ይገለጻል። በመንግስት የሚካሄዱ የመሰረተ ልማትና ሌሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶች፣ በግሉ ዘርፍ የሚካሄዱ የመኖሪያ ቤቶችና የሪልስቴት ህንፃዎች፣ ሆቴሎች፣ ኢንዱስትሪዎች፣ ወዘተ. ግንባታዎች ለእዚህ በአብነት ሊጠቀሱ ይችላሉ። በእዚህ ላይ ህዝቡ የሚያካሂዳቸው የመኖሪያ ቤትና የንግድ ተቋማት ግንባታዎች በርካታ አሉ።
ግንባታው በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል። የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ በአስር ዓመቱ የመንግስት እቅድም በመንገድ፣ በባቡር መስመር፣ በመኖሪያ ቤት፣ ወዘተ ሰፋፊ የግንባታ ስራዎች ይካሄዳሉ። በየቦታው የሚካሄዱ ግንባታዎች፣ የሲሚንቶ፣ የብረትና የመሳሰሉት የግንባታ ግብአቶች ፍላጎትና እጥረት የግንባታውን መስፋፋት ከሚጠቁሙት መካከል ሊጠቀሱ ይችላሉ።
የግንባታው ሥራ እያደገና እየጨመረ ሲሄድ ለግንባታው የሚያስፈልጉ ግብአቶችም መጨመር ይኖርባቸዋል፤ ግብአቶቹ ከወቅቱ ጋር በጥራትና በመጠን በጊዜ መቅረብ ይኖርባቸዋል። ይሁንና የግንባታ ግብአት በማቅረብ በኩል ሰፊ ክፍተት እንዳለ ይታወቃል። ይህን ጉዳይ የዘርፉ ተዋንያን ሁሌም ያነሳሉ።
በዚህ ወቅት በኮንስትራክሽን ዘርፉ ቅሬታ እያስነሱ ከሚገኙት መካከል ለግንባታ የሚውሉ ግብአቶች አለመገኘታቸውና በወቅቱ እየቀረቡ አለመሆናቸው ነው። ለግንባታው ዋና አስፈላጊ የሆነው የሲሚንቶ አቅርቦትም እንዲሁ በከፍተኛ ሁኔታ ቅሬታ ሲነሳበት ቆይቷል። በሲሚንቶ አቅርቦት ላይ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር በተለያዩ ጊዜያት መመሪያዎችን ቢያወጣም ችግሩ አሁንም እንደቀጠለ ነው። በግዥ ከውጭ በማስገባት አገልግሎት ላይ የሚውሉ በተለይም እንደ ህንጻ ማጠናቀቂያ ያሉ ግብአቶች በውጭ ምንዛሪ እጥረት እንደ ልብ አለመገኘታቸው፣ ቢገኙም በዋጋም የሚቀመሱ አለመሆናቸው ከግንባታው ጋር የሚጣጣም አቅርቦት እንደሌለ እንደ አንድ ምክንያት ይጠቀሳል።
ከግንባታ ግብአት አቅርቦት ጋር በተያያዘ በከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር አንድ የዳሰሳ ጥናት በቅርቡ ተደርጓል። ጥናቱ የለያቸውን ችግሮች፣በአጭር ጊዜና በረጅም ጊዜ ያመላከታቸውን የመፍትሄ ሀሳቦች ጥናቱን ያካሄዱት በሚኒስቴሩ የግንባታ ግብአት ልማት አቅርቦትና ጥራት ኤክስፐርት ኢንጂነር ዘሪሁን ዘገየን ጠይቀናቸው እንደሚከተለው ማብራሪያ ሰጥተውናል።
ኢንጂነር ዘሪሁን እንደገለጹልን፤ የዳሰሳ ጥናቱ የሲሚንቶ፣ የብረታብረትና የግንባታ የማጠናቀቂያ ግብአቶች አቅርቦትን የሚደግፍ የፖሊሲ ግብአት የሚሆን ምከረሀሳብ ለማቅረብ የተዘጋጀ ነው፤ በ2006 ዓ.ም ስራ ላይ የዋለውን የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ፖሊሲ መከለስ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል። አሁን ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ደግሞ የግንባታው ዘርፍ የግንባታ ግብአት አቅርቦት ማነቆ የሚታይበት ሆኗል። ለችግሩ መከሰት መንስኤዎቹ ምን እንደሆኑ፣ የጥናቱ አስፈላጊነትና መሠረታዊ ዓላማ፣ እንዲሁም ጥናቱ ሊያስገኛቸው የሚችሉ ውጤቶች ምንድናቸው የሚለውን ያካተተ የዳሰሳ ጥናት ነው የተካሄደው።
ለግንባታው የሚያስፈልጉ መሰረታዊ ከሚባሉት መካከል ሲሚንቶ፣ የቤት ክዳን ቆርቆሮን ጨምሮ ብረታብረት እንዲሁም እንደ ሴራሚክ፣ ታይልስ፣ የመፀዳጃ ቤት የግንባታ ማጠናቀቂያና ቀለም ግብአቶች አቅርቦት በግንባታ ኢንዱስትሪው ላይ ሰፊ ክፍተት እየፈጠረ እንደሆነ የጠቆሙት ኢንጂነር ዘሪሁን፤ እነዚህን መሠረት በማድረግም የግንባታ ግብአት ስትራቴጂክ በሚል በሶስት ደረጃ በመክፈል ጥናቱ መሰራቱን ጠቁመዋል። ግብአቶቹ ስትራቴጂክ ተብለው የተያዙበት ዋናው መነሻም የግብአቶቹ ወጭ ከፍተኛ በመሆኑ እንደሆነ አመልክተዋል።
በነዚህ ግብአቶች ላይ የሚስተዋለውን ክፍተት እንዲሁም መንግሥት በነዚህ ላይ ጣልቃ ገብቶ ኢኮኖሚውን እንዴት ሊያስተካክለው ይችላል በሚል ለሚዘጋጀው ፖሊሲ ምክረሀሳብ ለመስጠት የግንባታ ግብአት ጉዳይ በዳሰሳ ጥናቱ በደንብ መታየቱን ገልጸዋል።
እንደ ኢንጂነር ዘሪሁን ማብራሪያ፤ በግንባታ ግብአቶቹ አቅርቦት ላይ እየተስተዋለ ያለው ክፍተት የግንባታ ሥራዎች በወቅቱ እንዳይጠናቀቁ፣ በጥራትም እንዳይሰሩ እያደረገ ይገኛል፤ ይህም በዋናነት ከሚታዩ ችግሮች መካከል ይጠቀሳል። ይህ የአቅርቦት ክፍተት በሥራው ላይ በስፋት ተሰማርቶ የነበረውን የሰው ኃይል ከሥራ ውጭ በማድረግም አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል። በአሁኑ ጊዜም በሺዎች የሚቆጠር የሰው ኃይል ያለሥራ ተቀምጧል፤ ቤተሰቡም ተጎጂ ሆኗል። በዘርፉ ላይ እየተስተዋለ ያለውን ተደራራቢ ችግር እንዲህ በጥናት በመለየት መፍትሄ መስጠት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።
እጥረቱ እንዲከሰት ምክንያት የሆኑትንም ጥናቱ አመላክቷል፤ ለአብነት ካመላከታቸው አንዱ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በአቅማቸው ልክ ማምረት ካለመቻል ጋር የተያያዘው ነው። ለፋብሪካዎቹ የማምረት አቅም መቀነስ አንዱ ለሥራ የሚጠቀሙባቸው ማሽኖች በግዥ ከውጭ የሚገቡ መሆናቸው ናቸው። አሁን ባለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት አዲስ ማሽንም ሆነ የመለዋወጫ እቃ ግዥ ለመፈፀም አያስችላቸውም። ሌላው በፋበሪካዎቹ በኩል የሚነሳው ሥራ ላይ ያሉትን ማሽኖች መጠገን የሚችል ባለሙያ አለመኖርም ነው።
እነዚህ ተግዳሮቶች በፋብሪካዎቹ የማምረት አቅም ላይ አሉታዊ ተጽእኖ አሳድሯል። በ2010 ዓ.ም በዓመት ይመረት የነበረው ሲሚንቶ ስምንት ነጥብ አራት ሚሊዮን ቶን ነበር። ይህ አሀዝ አሁን ላይ ወደ አምስት ነጥብ አምስት ዝቅ ብሏል። ከፍላጎቱ 20 በመቶውን እንኳ ያልሞላ ማለት ነው። ፋብሪካዎቹ እስከ 2013 ዓ.ም ድረስ እያመረቱ የነበሩት ከማምረት አቅማቸው 49 ነጥብ 6 በመቶውን ነበር። በአጠቃላይ ከ50 በመቶ በታች በማምረት ላይ ይገኛሉ። በተመሳሳይ በብረት ምርት ላይም ችግሩ እየታየ ነው።
በነዚህና በሌሎች ምክንያቶች የተነሳ በአሁኑ ጊዜ ለግንባታው ዘርፍ ከሚያስፈልገው ግብአት 85 በመቶ የሚሆነው ከውጭ በግዥ የሚገባ ነው። መንግሥት ይህን ችግር የተለየ ሁኔታ እንዲያመቻች ይጠበቅበታል። ነገር ግን ያጋጠመው የውጭ ምንዛሪ እጥረት እና የገንዘብ የመግዛት አቅም ማነስ የግንባታ ግብአት በአግባቡ ተደራሽ እንዳይሆን አድርጎታል።
ከጥራት አንጻርም እንዲሁ ጥናቱ ክፍተቶችን አመላክቷል። ኢንጂነር ዘሪሁን በዚህ ላይ በሰጡት ማብራሪያ እንዳሉት፤ በተለይ የግንባታ ሥራ ማጠናቀቂያ የሆኑት እንደ ሴራሚክ፣ ታይልስና የመፀዳጃቤት እቃዎች እንዲሁም ቀለምና ለመስኮትና ለተለያየ ጥቅም የሚውሉ የመስታወት ግብአቶች በሀገር ውስጥ በበቂ ሁኔታ ተመርተው ይቀርባሉ። ለእነዚህ አገልግሎቶች የሚውሉ ግብአቶችን 99 በመቶውን በሀገር ውስጥ ምርት መሸፈን ይቻላል። ይሁን እንጂ በጥራት አምርቶ ማቅረብ ላይ ክፍተት እንዳለባቸው በስፋት ይነሳል። በጥራት መጓደል ምክንያትም ወደ ውጭ የማማተር ሁኔታ ተፈጥሯል። ይሄ ደግሞ የሀገር ውስጥ አምራቾች እንዳይበረታቱም ምክንያት እየሆነ ነው።
የኃይል አቅርቦት መቆራረጥም በሀገር ውስጥ አምራቾች ላይ እያሳደረ ያለው ተጽዕኖ ሌላው ተግዳሮት እንደሆነም ኢንጂነር ዘሪሁን ጠቁመዋል። የኃይል መቆራረጡ ፋብሪካዎች በአቅማቸው ልክ እንዳያመርቱ እንዳደረጋቸው ፋብሪካዎቹ በሚገኙባቸው አካባቢዎች ሄዶ በማየት ማረጋገጥ መቻሉንም አመልክተዋል።
በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ያለው ያለመረጋጋትና የፀጥታ ችግርም በተመሳሳይ ለዘርፉ ተግዳሮት መሆኑን ነው ኢንጂነሩ የጠቀሱት። የፀጥታው ችግር በፋብሪካዎች ላስከተለው ችግር አንዱ ማሳያ አርገው የጠቀሱት በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ሳቢያ በትግራይ ክልል የሚገኘው መሰቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ ሥራ እንዲያቆም መገደዱን ነው። ፋብሪካው በሥራ ላይ በነበረበት ወቅት በዓመት ወደ ሁለት ነጥብ ሁለት ሚሊየን ቶን የማምረት አቅም ነበረው።
የዋጋ ንረት ሲከሰት ለመከላከል የፖለቲካ ቁርጠኝነት አለመኖር ሌላው የዘርፉ ችግር መሆኑን ኢንጂነሩ ጠቅሰዋል። በአመራር ኃላፊነት ላይ ያሉት አካላት አስተማሪ እርምጃ በመውሰድ መፍትሄ አለመስጠታቸው ለችግሩ መባባስ አንዱ ምክንያት ተደርጎ ይወሰዳል።
ግብአቱን በግዥ ከውጭ ለማስገባት የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ በሀገር ውስጥም የሚመረተው በጥራት አለመቅረብና የፀጥታ ችግሮች፣ በመካከል ላይ ያለ ደላላ ለጥናቱ መነሻ ሆነው ይቅረቡ እንጂ፣ ችግሩ እየተንከባለለ መጥቶ አሁን ላይ የከፋ ደረጃ ላይ የደረሰ እንደሆነ ይታወቃል።
በተለይ ደግሞ በሀገር ውስጥ አቅም በመፍጠር ላይም የትኩረት ማነስ መኖሩ እንደ አንድ ምክንያት ይነሳል። እንዲህ ያሉ ክፍተቶች በጊዜ በጥናት ተለይተው ለምን መፍትሄ ሳይሰጣቸው ቆየ የሚል ጥያቄ ኢንጂነር ዘሪሁን አንስተንላቸው፤ በ2005 ዓ.ም እና 2007 ዓ.ም ሲሚንቶ በሀገር ውስጥ በበቂ ሁኔታ እየተመረተ እንደነበር ጠቅሰው፣ ከውጭ በግዥ እንዳይገባ እግድ ተጥሎ እንደነበር ገልጸዋል። ከ2005 ዓ.ም በኋላ የግንባታው ዘርፍ በከፍተኛ ሁኔታ መስፋፋትና በተለይም የጋራ መኖሪያ ቤቶች እና የቀላል ባቡር የመሠረተ ልማት ግንባታ የግብአቱን ፍላጎት ከፍ እንዳደረገው ይጠቅሳሉ። ይህም ሆኖ በሀገር ውስጥ ምርት የግንባታ ፍላጎት ይሟላ እንደነበር ገልጸዋል።
በአሁኑ ጊዜ የግንባታ ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መሆኑንና በየዓመቱም ወደ 400ሺ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ለማከናወን እቅድ በመያዙ፣የመስኖ ግድቦች እና ሌሎችም ግንባታዎች በስፋት መኖራቸውን በመጠቆም የሲሚንቶ ግብአት አስፈላጊነት ወሳኝ እንደሆነም ኢንጂነሩ ያመለከቱት። ይህን ፍላጎት ለማሟላትም በሀገር ውስጥ ያለውን ሀብት አሟጦ መጠቀምና በቴክኖሎጂ መታገዝ እንደሚገባም አመልክተዋል።
የዳሰሳ ጥናቱ ያመላከተውን የመፍትሄ ሀሳብ በተመለከተም ኢንጂነር ዘሪሁን እንደጠቆሙት፤ በጥናቱ የአጭርና የረጅም ጊዜ እቅዶች ምን መሆን እንዳለባቸው እንዲሁም ከማን ምን ይጠበቃል፣ ክልሎችና ፌዴራል መንግስት አብረው መስራት ያለባቸው መሆኑ ተመላክቷል። በተለይ ተናብቦ መሥራት ላይ ለአብነትም ማዕድን ሚኒስቴር ለግብአት የሚውሉ ጥሬ እቃዎች የሚገኙባቸውን አካባቢዎች በማመላከትና ለባለሀብቶች መረጃ ምቹ በማድረግ፣ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ስርጭቱ ላይ ዲጂታል የሆነ የአሰራር ሥርአት ዘርግቶ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አስታውቀዋል።
ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርም ለአምራች ኢንዱስትሪዎች ጥሬ እቃ በማቅረብና በክህሎት እንዲበቁ በማድረግ የበኩሉን ድርሻ የሚወጣበት አግባብ መኖሩም በጥናቱ ተመላክቷል። ከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ደግሞ የአሰራር ሥርአቶችንና ደረጃዎችን፣ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን ምቹ ማድረግ፣ ጥናቶችን ማካሄድ አዋጆች ላይ ትኩረቱን እንዲያጠናክር ተጠቁሟል።
ዘርፉ ያስከተለው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመፍታት በአጭርና በረጅም ጊዜ በጥናቱ የተመላከተውንም እንዳስረዱት፤ በአጭር ጊዜ ዘርፉ የውጭ ምንዛሪ ለተወሰነ ጊዜ በልዩ ትኩረት የሚያገኝበትን ሁኔታ በማመቻቸት ሲሚንቶ በተመጣጣነ ዋጋ ከውጭ ገበያ ማግኘት የሚቻልበትን አማራጭ እንዲፈለግ ተጠቁሟል። የብረት ግብአትንም እንዲሁ የብረት ፍላጎትን በ70 በመቶ ሊቀንሱ የሚችሉ ቴክኖሎጂዎችን ለመሥራት እየተደረገ ያለውን ጥረት ተግባራዊ ማድረግ በሚል የተቀመጠ መፍትሄም ተጠቁሟል።
በረጅም ጊዜ ደግሞ በልማት ሥራ ላይ ትኩረት ማድረግ ነው። ለግብአቱ የሚሆኑ ማዕድናት በሚገኙባቸው አካባቢዎች ለማምረትና ለማጓጓዝ የሚመቹ መሠረተ ልማቶችን በማሟላት ዘርፉ ዘላቂ መፍትሄ የሚያገኝበት ሁኔታ እንዲመቻች በጥናቱ ምክረሀሳብ ተቀምጧል።
ጥናቶችን ወደተግባር በመቀየር በኩል ክፍተቶች እንደሚስተዋሉ ከዚህ ቀደም ያሉ ተሞክሮዎችንም ኢንጂነር ዘሪሁን አንስተንላቸው፣ ጥናቱ ላይ አጠቃላይ ግንዛቤ እንዲያዝና ጥናቱም በደንብ እንዲዳብር ዘርፉ ላይ በተለያየ ደረጃ እየሰሩ ካሉ ባለድርሻ አካላት እና አስፈጻሚ ተቋማት ጋር ምክክር መደረጉን ገልጸዋል። በዚህ መልኩ የተከናወነው ተግባር ጥናቱ ተግባራዊ ይሆናል የሚል እምነት እንዳላቸው ምላሽ ሰጥተዋል።
በጉዳዩ ላይ ሀሳባቸውን እንዲሰጡን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰርና የዘርፉ አማካሪ ዶክተር ውብሸት ዠቅአለ የጠየቅናቸው በጥናቱ ላይ መረጃ ባይኖራቸውም ዘርፉ ላይ የሚስተዋለውን ችግር በቅርበት እንደሚያውቁት ይገልፃሉ። አብዛኛው ግብአት ከውጭ በግዥ የሚፈጸም ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ለግዥ የሚሆን የውጭ ምንዛሪ ማግኘትና የግዥ መጓተት በግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ ጫና በመፍጠር መዘግየት እንዲከሰት ምክንያት መሆኑን ጠቅሰዋል። የዘርፉን ችግሮች የሚፈቱ መንገዶች ግን መኖራቸውንና መፍትሄው ላይ ትኩረት አድርጎ መስራቱ የተሻለ እንደሆነም ጠቁመዋል።
እንደ ተባባሪ ፕሮፌሰሩ ማብራሪያ፤ ለግንባታው ሥራ የብረት ግብአትን መቀነስ እንጂ ማስቀረት አይቻልም። ብረት አስፈላጊ ግብአት ነው። ለአብነትም ከዓለም ተሞክሮ የኖርዝ ኮሪያን ተሞክሮ አንስተዋል። ሀገሪቱ በጣም በከፍተኛ ሁኔታ የብረት ግብአት ችግር እንደነበረባት በማውሳት፤ ሀገሪቱ አማራጮችን በመጠቀም የብረት ግብአትን ለመቀነስ ጥረት ማድረጓን ገልጸዋል። እንዲህ ያሉ ተሞክሮዎችን ማየቱ አስፈላጊ እንደሆነ ነው ምክረሀሳብ የሰጡት።
በቅድመ ግንባታ በሚከናወን የዲዛይን ሥራ ላይም ግብአትን ለመቀነስ የሚያስችል አሰራር መጠቀም የሚቻልበት እድል መኖሩንም ዶክተር ውብሸት ገልፀዋል። ለእዚህም ለአዲሱ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ህንፃ ግድግዳ የዋሉትን ግብአቶች ለአብነት ጠቅሰዋል።
የሀገርንም አቅም ያገናዘበ አካሄድ መከተል ዘርፉ ላይ የሚስተዋለውን ጫና ይቀንሳል የሚሉት ተባባሪ ፕሮፌሰሩ፤ የግንባታ ግብአት የግድ ብሎኬት ወይንም ኮንክሪት መሆን አለበት የሚል እምነት እንደሌላቸው ይገልጻሉ።
እርሳቸው እንዳሉት በአፈር ግብአት ከአንድ ወለል በላይ ቤት የገነቡ ሀገራት ተሞክሮ መኖሩንና በኢትዮጵያም ቢሆን በአፈር የተሰሩ ጥሩ ቤቶች መኖራቸውን አመልክተዋል። በብሎኬት ግንባታ ማከናወን በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች አስገዳጅ መሆን እንደሌለበትና እንደየአካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ መፍትሄ መስጠት እንደሚቻል ነው ሀሳብ የሰጡት።
ከሀገር አቅም ጋር አያይዞ መፍትሄ መስጠቱ ከማን ምን ይጠበቃል የሚል ጥያቄም አንስተንላቸው በሰጡት ምላሽ፤ ትልቁ ነገር ግንዛቤ መፍጠርና ይህ ከሆነ በኋላ ደግሞ የአሰራር ሥርአት እንዲኖር ማድረግና እንዲህ ከተሰራ መተግበሩ እንደማያስቸግር ነው ያስረዱት።
‹‹በግንባታ ሥራ ላይ በአስገንቢው በኩል በውበት የተለያየ ምርጫ ወይንም ፍላጎት እንደሚኖር ይገመታል። የግድ በዚህ መንገድ ካልሰራን በሚል ግንባታዎችን በማዘግየት የሀገር ኢኮኖሚ መጉዳት ተገቢ ነው ብዬ አላምንም›› የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ፣ የጭቃ ቤት በብሎኬት ከተሰራ ቤት ያንሳል ያለው ማነው? የሚል የመከራከሪያ ሀሳብ በተለያዩ መድረኮች ላይ ባገኙት አጋጣሚ ማንሳታቸውን ነው የሚናገሩት። ፍላጎትን ወደ መገደብ መሄድ እንደሚገባ አስረድተዋል። ፕሮጀክት ከሚያሟላቸው ስድስት ነጥቦች ውስጥም አንዱ ከአካባቢ ጋር የተጣጣመ መሆንን እንደሆነም ገልጸዋል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 1/2015