በፋሽን ኢንዱስትሪው ተሰማርተው የሚገኙት የዘርፉ ባለሙያዎቹ ዘርፉን ለማሳደግ የራሳቸውን ጥረት እያደረጉ ስለመሆናቸው በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲናገሩ ይሰማል። ተሰጥኦና ችሎታቸውን ተጠቅመው ባደረጉት ጥረት ነጥረው ወደፊት የወጡ የዘርፉ ሙያተኞች ሀገራቸውን በዓለም አቀፍ መድረክ ለማስተዋወቅ ትልቅ እድል እንዳገኙም ይገለጻል።
በፋሽን ኢንዱስትሪው ተሰማርተው ተሰጥኦና ችሎታቸውን ተጠቅመው የሀገራቸውን ቱባ ባህል በዓለም አቀፍ መድረኮች እያስተዋወቁ ያሉ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ጥቂት የሚባል አይደለም። ከእነዚህ መካከል ተሰጥኦውን ተጠቅሞ ሀገሩን በዓለም አቀፍ መድረኮች እያስተዋወቀ የሚገኝ አንድ እንግዳ በዛሬ ፋሽን አምዳችን ይዘን ቀርበናል። እንግዳችን ሰዓሊና የፋሽን ዲዛይነር ኦስማን መሀመድ ይባላል። ሙያውን በውጭ ሀገራት ትምህርት ቤቶች ጭምር ያስተምራል።
ሰዓሊና የፋሽን ዲዛይነሩ አቶ ኦስማን ተወልዶ ያደገው በአዲስ አበባ ከተማ ነው። ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ የልብስ አሠራርና ፈጠራ የታከለባቸው የቆዳ አልባሳት እንዲሁም ጫማዎችን ዲዛይን በማድረግ ይታወቃል። ኦስማን በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ ዓለም አቀፍ የፋሽን መድረኮች ላይ በመሳተፍ ሀገሩን እያስተዋወቀ መሆኑን ይገልጻል።
የዲዛይኒንግ ችሎታ ከልጅነቱ ጀምሮ በውስጡ እንደነበረው የሚያስታውሰው ኦስማን፤ ይህ አቅሙ ፍንትው ብሎ የወጣው ግን ትምህርት ቤት እያለ መሆኑን ይናገራል። ትምህርት ቤት እያለ በቤቱ ውስጥ ያሉ ቁሳቁስን በመጠቀም ለራሱም ሆነ ጓደኞቹ ጫማ በመስራት የፈጠራ ችሎታውን በማሳየት ተፅእኖ ይፈጥር ነበር። በዚህ መልኩ የተጀመረው የዲዛይኒንግ ሥራ ከሰዓሊነት የፈጠራ ጥበብ ጋር ተዋህዶ በየቀኑ አዳዲስ ነገሮች በመፍጠር በጓደኞቹና በመምህራኑ እንዲሁም በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ እንዲታወቅ አድርጎታል። አሁን ለደረሰበት ደረጃ በወቅቱ ያገኝ የነበረው አበረታች ምላሽ ትልቅ የሞራል ስንቅ እንደሆነው ይናገራል።
በዚህ መንገድ የተጀመረው የፈጠራ ጥበብ ዛሬ ላይ አድጎ ፍልስፍና የተሞላባቸው ብዙ እይታ ያረፈባቸው ሥራዎች ለመስራት እንዳስቻለው ዲዛይነር ኦስማን ገልጿል። ‹‹ውጭ ሀገር በሚዘጋጁ መድረኮች ላይ ተሳትፎ ማድረግ የጀመርኩት ትምህርቴን እንደጨረስኩ ነው›› የሚለው ዲዛይነር ኦስማን፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ብዙ የዓለም ሀገራት ላይ በመዞር የልምድ ልውውጦች የማድረግ፣ የውጭ የትምህርት እድል (ከእስኮላር ሽፕ) እንዲሁም በውጭ ሀገር የማስተማር እድል ማግኘቱን ይጠቅሳል፤ እነዚህ አጋጣሚዎች ኢትዮጵያን በፋሽን ኢንዱስትሪው ለማስተዋወቅ እንዳስቻሉት ይገልጻል።
የፋሽን ዲዛይነር ኦስማን፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ እ.ኤ.አ በ2005 እና በ2007 በፈረንሳይ ሀገር በተካሄደው የፋሽን ዲዛይነሮች ውድድር በአሊያንስ ትምህርት ቤት አማካይነት በመሳተፍ በሁለቱም ጊዜያት ሽልማት አግኝቷል። እ.ኤ.አ 2008 በኢትዮጵያ በተካሄደ ዓለም አቀፍ የፋሽን ትርዒት ላይ ተሳትፎ ሥራዎቹን አቅርቧል። በተጨማሪም እ.ኤ.አ 2010 ላይ ጀርመን ሀገር የኢትዮጵያ የፋሽን ህዳሴ (Renaissance fashion show) በሚል የተካሄደው የፋሽን ትርዒት ላይ በመሳተፍ ሥራዎቹን አቅርቦ ሀገሩን ማስተዋወቅ ችሏል።
‹‹ዓለም አቀፍ የፋሽን ውድድር ከተለያዩ የዓለም ሀገራት የተውጣጡ ወጣት ዲዛይነሮች የሚሳተፉበት ነው›› የሚለው ዲዛይነር ኦስማን፤ በውድድር ነጥሮ ለመውጣት ዓለምን የሚያነጋግር ተፅእኖ ፈጣሪ የሆነ፣ ለየት ያለ ፈጠራ የታከለበትና ታሪክ ያለው ፋሽን ይዞ መቅረብ አስፈላጊ እንደሆነ ይናገራል። ‹‹እኔ ደግሞ በተፈጥሮዬ ወጣ ያለ ነገር የማየት ልምድ አለኝ። ስለዚህ የአርት ጥበቡን በመጠቀም በቆዳ ላይ ብዙ ነገር መሥራት እንደሚቻል ማሳየት ችያለሁ›› ይላል።
እንደዲዛይነሩ ገለጻ፤ በፋሽን ኢንዱስትሪው ተፅእኖ ፈጣሪ የሚባለው አንድን ነገር ለመስራት የራሱ የሆነ ታሪክ ሲኖረውና የሚታዩ ነገሮችን ሁሉ ወደ ሃሳብ በመቀየር ውጤት ማምጣት ሲቻል ነው። ከዚህም በተጨማሪ አነጋጋሪ የሆነ ሥራ ሰርቶ ወጣ ብሎ ማየትን፣ ሰፋ አድርጎ ማሰብን እና ድፍረትን የሚጠይቅ ነው ብሏል።
‹‹እጄ ላይ የተሰጠኝ ጥበብ ወይም ሙያ ከራሴ አልፎ ለሁሉም መትረፍ የሚችል፣ ለብዙዎች የገቢ ምንጭ ሊሆን እንደሚችል እያየሁት ነው›› የሚለው ዲዛይነሩ፤ ቤተሰቦቹ በሥራዎቹ በማበረታታት መሞከር ያለበትን ነገር ሁሉ ያለመሰልቸት እስከሚችለው ጥግ ድረስ ትግል አድርጎ እንዲሞክር ትዕግስት እንዲኖረው ነገሮችን በብቃት፣ ትጋትና በጥረት እንዲያልፍ እያደረጉ እንዳሳደጉት ይገልጻል፤ ይህም ወደ ጥበብ ሙያው የበለጠ እንዲገባ ያደረገው መሆኑን ነው ያጫወተን።
የመጀመሪያው የኢትዮጵያ የፋሽን ማህበር መስራች ከሆኑት አንዱ መሆኑን የሚናገረው ዲዛይነር ኦስማን፤ ወጣቱ ተሰጥኦ እያለው የሚያበረታታው አጥቶ ወደኋላ እንዳይመለስ በማሰብ በአዲስ አበባ ካሉ ሌሎች ዲዛይነሮች ጋር በመሆን ሰባት ሆነው ማህበሩን እንደመሰረቱት ይናገራሉ። አሁን ላይ ማህበሩ ከመቶ ያላነሱ አባላት ያሉት ሲሆን ብዙ ሥራዎችን እየሰራ ለፋሽን ኢንዱስትሪው አስተዋፅኦ እያደረገ ይገኛል ይላል። ማህበሩ ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር የተሳሰረ መሆኑን በተለያዩ ነገሮች ላይ ለመሳተፍ ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረ መሆኑን ጠቅሶ፤ ይህም ባለሙያውን ብቻ ሳይሆን ለፋሽን ኢንዱስትሪው እድገት ትልቅ እድል የሚፈጥር መሆኑን አመላክቷል።
ዲዛይነር ኦስማን ‹‹የፋሽን ኢንዱስትሪው እንዲያድግ ከተፈለገ ለሙያው ትኩረት በመስጠት የኛ የሆኑ አልባሳትን፣ ጫማዎች፣ ቦርሳዎችም ሆኑ ሌሎች ነገሮችን ተጠቅመን ልናጌጥና ልናደንቀው ልናበረታታው ይገባል። የፋሽን ሥራዎች ሁልጊዜ ተሰርተው የሚላኩት ውጭ ሀገር ላለው አድናቂው (ለፈላጊው) ነው። እኛ ራሳችን ዲዛይን
ያደረግነውን ለብሰን አንታይም ሲል ይገልጸል። ራሳችን የሰራነውን ለብሰን ስናስተዋውቅ ሰዎች ያደንቁታል፤ ይገዙታል እንዲሁም በመልበስ ይጋሩታል። በእንዲህ መልኩ ካልሄድን ሁልጊዜ የሌላውን እያየን በመጣን ቁጥር የራሳችንን እያጣን እንሄዳለን ነው የሚለው። የራሳችንን ተጠቅመን የመሥራት እድላችንን እያሰፋን ስንሄድ እያደግንና ከፍ እያልን እንመጣለን። የዓለምን እይታ በመሳብ ጭምር ተፈላጊነታችንና ተቀባይነታችን እየጨመረ ይመጣል በማለት አስረድቷል።
ዲዛይነር በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ በሚያቀርባቸው የፋሽን ሥራዎቹ ሀገሩን ወክሎ የሚቀርብ መሆኑን ጠቅሶ፣ ሀገሩን የሚያስተዋውቅ ሰው የመጀመሪያ አምባሳደር ነውና ሥራዎቹ ትኩረት ሊሰጣቸውና ሊበረታቱ እንደሚገባ አስገንዝቧል። እንደ ዲዛይነሩ ገለጻ፤ የፋሽን ኢንዱስትሪውን መንግሥት ቢያበረታታ እድል ቢሰጥ በጣም ሊያድግና ለብዙ ሰዎች የሥራ እድልን መፍጠር የሚችል ዘርፍ ነው። በዓለም ደረጃ ተወዳዳሪ ሆኖ ለሀገር የገቢ ምንጭ ትልቅ ድርሻ ያለው በመሆኑ የሚመለከታቸው አካላት ዘርፉን ሊደግፉ ይገባል በማለት ሃሳቡን አጠቃሏል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 26 ቀን 2015 ዓ.ም