የጮቄ ተራራ ከአዲስ አበባ በ338 ኪ.ሜ እርቀት ላይ በአማራ ክልል የምስራቅ ጎጃም ዞን የሚገኝ ሲሆን 53 ሺህ 558 ሄክታር ይሸፍናል። የ23 ትልልቅ ወንዞችና የ273 ምንጮች መነሻ የሆነው ይኸው አካባቢ፤ ከባህር ወለል በላይ ከ2ሺህ 800 እስከ 4ሺህ 100 ሜትር ርዝመት ባላቸው ተራራዎች የተሸፈነ ነው። መልክዓ-ምድራዊ አቀማመጡ 86 በመቶ ተራራማ 1 ነጥብ 5 በመቶ ሸለቋማ 12 ነጥብ 5 በመቶ ሜዳማ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ረፋድ ላይ ሲታይ በተራራውም ሆነ በሜዳው መልክዓ ምድር ላይ የሚርመሰመሱት በጎች በደንብ ላስተዋላቸው ከተፈጥሮው ውበት ጋር ተዳምረው የተለየ የደስታ ስሜት ይፈጥራሉ። በጎች በትክክልም ለአካባቢው የተቸሩ ገፀ በረከቶች እንደሆኑ ከቅርብ ላለ እረኛ ብቻ ሳይሆን፤ ለእንግድነት የሄደንም ሰው የማሳመን እና ቀልብ የመግዛት አቅም አላቸው። ሆኖም ይህ ፀጋ የአካባቢውን አርብቶ አደር ምን ያህል ተጠቃሚ እያደረገ ነው? የሚለው አጠያያቂ ነው።
የደብረ ማርቆስ ግብርና ምርምር ማዕከል በአካባቢው ያለውን አርብቶ እና አርሶ አደር “ከዋሸራ የበግ ፀጋ” ተጠቃሚ እንዲሆን በማገዝ አስተዋኦ ከሚያደርጉ ተቋማት መካከል አንደኛው ነው። ማዕከሉ የካቲት 2011 ዓ.ም የተመሠረተ እና ለጋ ዕድሜ ያለው ሲሆን፤ ከቆላ እስከ ውርጭ ያለን ሥነ-ምህዳር በማካተት የአርሶ አደሩን ሕይወት የማሻሻል ሃላፊነት ተጥሎበታል።
አብዛኛው ደጋማው አካባቢ ዋነኛ መተዳደሪያው የበግና የጋማ ከብት ርባታ፣ የገብስ እና ድንች ልማት ነው። የምርምር ማዕከሉ አርብቶና አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ለማድረግ ገብስ እና በግ ርባታ ላይ በትኩረት በመስራት ላይ ይገኛል። ከእነዚህ ደጋማ አካባቢዎች አንዱ ከሆነው የስናን ወረዳ 16 ቀበሌዎች ውስጥ፤ በሁለቱ ቀበሌዎች ማለትም ዳንጉሌ እና ጠለዛሞ ላይ የዋሸራ በግ ዝርያ የማሻሻል ሥራ እያካሄደ መሆኑን በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የደብረ ማርቆስ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ ያለው ማዘንጊያ ይገልጻሉ።
ከወረዳው ቀበሌዎች ውስጥ እነዚህኞቹ የተመረጡት የአርሶ አደሩን አኗኗር፣ ያለውን የበግ ቁጥር፣ አርብቶ እና አርሶ አደሮች ዝርያውን ለማሻሻል ያላቸውን ፍላጎት፣ በተሻለ መልኩ የዋሸራ በግ ዝርያ መገኘትና የመሳሰሉትን መስፈርቶች በማየት መሆኑን የሚናገሩት የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር፤ በኢትዮጵያ ካሉት 14 የሚደርሱ የበግ ዝርያዎች መካከል የዋሸራ በግ ለዘመናዊ የበግ ዝርያ ማሻሻል ሰፊ ዕድልን የሚሰጥ ሆኖ መገኘቱን ይገልፃሉ።
ከበግ ዝርያዎች መካከል አንዱ የሆነው የዋሸራ በግ በዋናነት በምዕራብ ጎጃም ፣ ምስራቅ ጎጃም፣ አዊ ዞኖችና በመተከል ዞንና በደቡባዊ የጣና ሐይቅ አካባቢዎች በስፋት ተሰራጭቶ እንደሚገኝ ይናገራሉ። የዋሸራ በግ ዝርያ በአማካይ በውልደት ጊዜ 2 ነጥብ 8 ፣ በጡት መንጠፍ ጊዜ 13 ነጥብ 8 እና በስድስት ወር ዕድሜ 17 ነጥብ 87 ኪሎ ግራም የሚመዝን የበግ ዝርያ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህም በኢትዮጵያ ካሉ የበግ ዝርያዎች ጋር ሲነፃፀር ተወዳዳሪ እንዲሁም የተሻለ እንደሆነና ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ የሥጋ ገበያ ከፍተኛ ድርሻ የሚኖረው የበግ ዝርያ እንዳደረገው ያብራራሉ።
አርቢውን በዘላቂነት የኑሮ ሁኔታውን ከማሻሻል ባለፈ ለአካባቢው ብሎም ለሀገር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና ለወጪ ገበያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል የሚሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ይህንንም እውን ለማድረግ የደብረ ማርቆስ ግብርና ምርምር ማዕከል ማኅበረሰብ አቀፍ የዋሸራ በግ ዝርያ ማሻሻል ሥራን በዳንጉሌ እና ጠለዛሞ ቀበሌዎች ከሚመለከታቸው ጋር ሆኖ የአርቢዎች የኅብረት ሥራ ማኅበር በማቋቋም ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ሥራ መግባቱንም ይጠቁማሉ።
ማዕከሉ የማኅበረሰብ አቀፍ የዝርያ ማሻሻል ሥራን በማኅበረሰብ ደረጃ የጀመረው ስልታዊ በሆነ መልኩ ዝርያ ለማሻሻል ነው። የተደራጀና ተከታታይነት ያለው የእንስሳት መለየትና የአፈፃፀም መረጃዎችን ከመመዝገብ በተጨማሪ የዝርያ ማሻሻል መርሃግብሮችን ቀጣይነት ለማረጋገጥ በማኅበረሰብ ደረጃ እየተሠራ መሆኑንም ይገልፃሉ። አቅምን ለመገንባት እና በተሳታፊዎች መካከል ባለቤትነትን በማረጋገጥ ሥራው ዘላቂ እንዲሆን ታስቦ ማዕከሉ ከማህበራት ጋር በመተባበር እየሠራ መሆኑንም ዋና ዳይሬክተሩ ይናገራሉ።
እንደዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ የማኅበረሰብ አቀፍ የዋሸራ በግ ዝርያ ማሻሻል ሥራን ለመጀመር ከአርሶ አደር ጀምሮ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን አስረድቶ ወደ ተግባር ለመግባት እልህ አስጨራሽ ሂደቶች ታልፈዋል። ይሁን እንጂ አርሶ አደሩ ከተረዳ በኋላ ያለው እንቅስቃሴ ተገቢው ድጋፍ እየተደረገለት ከቀጠለ ተስፋ ሰጪ ጅምሮች መታየታቸው እና አካባቢው የዋሸራ በግ ምንጭ የሚሆንበት ዕድል መኖሩን ማረጋገጥ ተችሏል።
ዝርያ ማሻሻል ሥራው የራሱ የሆነ ግብና ዓላማ አስቀምጦ የሚሰራ ነው የሚሉት አቶ ያለው፤ የማኅበረሰብ አቀፍ ዋሸራ በግ ዝርያ ማሻሻል የባለድርሻ አካላትን አስተባብሮ እና ጠንካራ የሆነ የዝርያ ማሻሻል ሥርዓትን በመዘርጋት አርቢውን ማኅበረሰብ ያልተዳቀለ የዋሸራ በግ ዝርያ ምንጭ በማድረግ በዘላቂነት ተጠቃሚ የማድረግ ግብ ተይዞ እየተሠራ መሆኑ ዋነኛው ጉዳይ ነው ይላሉ።
በሳይንሳዊ መንገድ ብቃቱ የተረጋገጠለት ምርጥ የዋሸራ በግ ዝርያን ለክልሉ ብሎም ለዝርያው ፍላጎት ላለው ማንኛውም የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ገበያ የሀገራችንን ሕግና ደንቡን ባከበረ መልኩ ማቅረብ የአካባቢውን ህብረተሰብ የበለጠ ዘላቂ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ አመልክተው፤ የማኅበረሰቡን ፍላጎት መሠረት ያደረገ እና አሳታፊ የሆነ የዋሸራ በግ ዝርያን በማሻሻል የአርቢውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሠራ መሆኑንም አፅንኦት ሰጥተው ጠቅሰዋል።
ከተቋቋሙት የዋሻራ በግ ዝርያ ማሻሻል ኅብረት ሥራ ማኅበራት ውስጥ አንደኛው የተስፋ ለሕይወት የዋሸራ በግ እርባታ እና ማድለብ ኅብረት ሥራ ማኅበር አንዱ ነው። ማኅበሩ በዳንጉሌ ቀበሌ የተቋቋመ የዝርያ ማሻሻል ማኅበር ሲሆን፤ 97 አባላት እና 528 እናት በጎችን የያዘ ነው የሚሉት በደብረማርቆስ ከተማ የዳንጉሌ ወረዳ ክልክል ጎጥ የሚኖሩት እና ማኅበሩን የሚመሩት አርሶ አደር ባለው ወልዴ ናቸው።
የዋሸራ በግ ዝርያን በማሻሻል ለእዚህ ማኅበር የምርምር ማዕከሉ 25 ምርጥ የዋሸራ አውራ በጎች የቀረቡ መሆኑን በማስታወስ፤ አባላትም በ17 ቡድን በማደራጀት ከምርምር ማዕከሉ በተሰጣቸው መመሪያ መሠረት እርባታውን በማስኬድ ላይ እንደሚገኙ ይናገራሉ። ኅብረት ሥራ ማኅበሩ በአዋጁና ደንቡ መሰረት የተቋቋሙና ሕጋዊ ዕውቅና ያለው የሥራ አመራር ኮሚቴ ፣ የቁጥጥር ኮሚቴ ፣ የግዥ ኮሚቴ ፣ የመራጭ ኮሚቴ ፣ የሽያጭ ኮሚቴ በማካተት በመተዳደሪያ ደንብና በውስጠ ደንብ የሚመሩ መሆናቸውን ይናገራሉ።
‹‹ጆሯቸው ላይ መለያ በማንጠልጠል የማኅበረሰብ አቀፍ የዋሸራ በግ ዝርያ ማሻሻል ሥራው የራሱ የሆነ መረጃ ሰብሳቢ ተቀጥሮለት በዝርያ ማሻሻል ተመራማሪው መሪነት የመረጃ ፎርማቶች ተዘጋጅተውለት ዕለት በዕለት መረጃዎች ይሰበሰባሉ።›› የሚሉት አርሶ አደር ባለው፣ የማይመረጡ አውራዎች ከመንጋው እንዲወጡና ለሌላ አገልግሎት እንዲውሉ ማለትም ለሽያጭ ወይም ለእርድ የሚውሉ መሆኑንም ነው የጠቆሙት።
ህብረተሰቡ አንድ አውራ የዋሸራ በግ እስከ 20 ሺህ ብር በመሸጥ ተጠቃሚ መሆኑ መጀመሩን በማመልከት፤ የዋሸራ በጎች ሲደልቡ ጊዜ የማይወስዱ፤ በቶሎ ሥጋ የሚያጠራቅሙ በመሆናቸው ገቢ ለማስገኘት ምርጥ አማራጮች መሆናቸውን ይናገራሉ። የዋሸራ በጎች ዕርድ ላይ ሲቀርቡ ስጋቸው የተነባበረ ሲሆን፤ ሌሎቹ ግን ቀጭን በመሆናቸው እና ሲታዩም ብዙ የማያስደስቱ በመሆኑ ገበያ ሲወጡም አርቢው የተሻለ ተጠቃሚ የሚሆንበት ዕድል እጅግ የጠበበ መሆኑንም ይናገራሉ። አሁን አውራዎች ብቻ ሳይሆኑ እናት በጎችም ዋሸራ እንዲሆኑ
እየተሠራ ሲሆን፤ ከበግ በተጨማሪ የወተት ከብት ላይም ማዕከሉ እንዲደግፈን እየጠየቅን ነው ሲሉ ከማዕከሉ እያገኙ ካለው ጥቅም ባሻገር ተጨማሪ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ይጠይቃሉ። በአብዛኛው የዋሸራ በግ በማስፋት አውራዎችን በመምረጥ ከማዕከሉ ጋር በመተባበር በጎጃም እንዲስፋፋ እየተሠራ ነው የሚሉት አቶ ባለው፤ ግልገሉም ተወልዶ በሶስት ወር ውስጥ ለገበያ መቅረብ መቻሉ ፈጣን የቤተሰብ ችግርን ለመፍታት የሚያስችል በመሆኑ ይህንን ሃሳብ በመንገር በሌሎች አካባቢዎችም እንዲለመድ በመረባረብ ላይ መሆናቸውንም ይናገራሉ።
ሌላኛው የክልክል ጎጥ ነዋሪ አርሶ አደር አቶ ዳምጤ ንጋቴ እንደሚናገሩት፤ የዋሸራ በጎችን ሲጠቀሙ በተወለዱ በሶስት ወር ውስጥ ግልገሎቻቸውን ለገበያ ማቅረብ ችለዋል። ሶስት ሺህ የነበረው በግ አሁን እስከ አምስት ሺህ ብር፤ ቀድሞ ለብዙ ጊዜ ቀልበው አምስት ሺ ይሸጡት የነበረውን በግ የዋሸራ በመሆኑ እና በደንብ ስለሚደልብ እስከ አስራ አምስት ሺህ ብር ለመሸጥ ችለዋል። የዋሸራ እናት በጎች መንታ የሚወልዱበት ሁኔታ መኖሩን በማመልከት፤ በየጊዜው መጠናቸው መጨመሩን እንደሚከታተሉ እና ሌሎችም አካባቢዎች ይህንን አገር በቀል የዋሸራ በግ ቢያረቡ የበለጠ ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉ ተናግረዋል።
ከተስፋ ለሕይወት የዋሸራ በግ እርባታ እና ማድለብ ኅብረት ሥራ ማኅበር በተጨማሪ በጠለዛሞ ቀበሌ የተቋቋመ የዋሸራ በግ ዝርያ ማሻሻል ማኅበር ያለ ሲሆን፤ 116 አባላት እና 628 እናት በጎችን የያዘ ማኅበር ነው። ለዚህ ማኅበር 18 ምርጥ የዋሸራ አውራ በጎች የቀረቡ ሲሆን፤ አባላትም በ18 የጥቂ ቡድን በመደራጀት ከምርምር ማዕከሉ በተሰጣቸው መመሪያ መሠረት እርባታውን በማስኬድ ላይ እንደሚገኙም የማህበሩ አባል አርሶ አደሮች ይገልፃሉ።
ሌላኛው የተስፋ ለሕይወት ማህበር አባል አርሶ አደር በተመሳሳይ መልኩ ማዕከሉ የሰጣቸውን አውራ የዋሸራ በግ ተጠቅመው የራሳቸውን ሴት በጎች በማስጠቃት የዋሸራ ንፁህ ምርጥ ዘር ለማግኘት ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸውንም አመልክተዋል። ይህንን ወደ ሌሎች አካባቢዎች በማስፋት አካባቢው የዋሸራ በግ ምንጭ እንዲሆን በማገዝ የሚጠበቅባቸውን ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውንም ነው የጠቆሙት።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 26 ቀን 2015 ዓ.ም