ኢትዮጵያ የበርካታ ባህል፣ ትውፊት፣ እሴትና እምነት መገኛ መሆኗ በተደጋጋሚ ይወሳል። የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ቅርሶች መገኛ፣ የአኩሪ ታሪክ ባለቤትና የሰው ዘር መፍለቂያ መሆኗም ይታወቃል። ይህች ባለብዙ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሀገር ኢትዮጵያ፤ የነዚህ ሁሉ ቋሚ ሃብቶች ባለቤት ብትሆንም ይህን ሀብቷን በተገቢው መንገድ ለተቀረው ዓለም በማስተዋወቅ ጥንታዊና ታሪካዊ ቅርሶቿ በሚፈለገው ልክ እንዲጎበኙ ማድረግ አልተቻለም።
ይህን ክፍተት ለመሙላት በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያና ሀገሪቱን በልዩ ልዩ መንገድ ለዓለም ያስተዋውቃል የተባለለት በኢትዮጵያ ታሪክ፣ ባህል፣ ጥበብ፣ እሴት፣ ፍልስፍና፣ ወግ፣ ሀገር በቀል እውቀት፣ ስነ-ፅሁፍ፣ ኪነ- ጥበብ፣ ማንነትና በመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ አተኩሮ በመላው ዓለም በመንቀሳቀስ የሚሰራ ‹‹ሰገል ዘ ኢትዮጵያ›› የተሰኘ ቦርድ መር ሀገር በቀል ድርጅት ሚያዚያ 28 ቀን 2015 ዓ.ም ተመስርቶ ስራውን ጀምሯል።
ድርጅቱ በርካታ ሊህቃንን በልዩ ልዩ ዘርፎች ያካተተና ኢትዮጵያዊ አውቀቶችን በመላው ዓለም ለሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ለሌሎች የውጪ ሀገር ዜጎች በማቅረብ የኢትዮጵያን ትላልቅ እሴቶች በማስተዋወቅ ተገቢውን ከብርና ሞገስ እንዲያገኙ የማድረግ አላማን ሰንቆ እንደተቋቋመ ተነግሯል።
ድርጅቱ በውጪ ሀገራት ውስጥ የሚገኙ አያሌ ኢትዮጵያውያንንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን እርስ በርሳቸው የበለጠ እንዲተዋወቁ፤ በጋራም ሆነ በተናጠል በሀገራቸው ልዩ ልዩ አመላካች ጥናትና ምርምር ላይ እንዲሳተፉ የማቅረብ ራእይ አንግቦ እንደመጣም ታውቋል። በመላው ዓለም በመዘዋወር ኢትዮጵያን አስተዋውቆ በምትኩ ሀገሪቱ ያሏትን ጥንታዊና ታሪካዊ ቅርሶቿ እንዲጎበኙና እንዲዳሰሱ የማድረግ ውጥን እንዳለውም ተገልጿል።
በዚህ ሀገር በቀል ድርጅት ውስጥ በተለይም በታሪክ፣ ባህል፣ ሃይማኖት፣ ፍልስፍና፣ ጥበብ፣ ስነ-ፈለግ፣ ሀገር በቀል እውቀት፣ ትውልድን በመታደግ፣ በሰብዓዊ ስራና በመሳሰሉት እውቀቶች የበለፀጉ፤ በርካታ ጥናትና ምርምሮችን ያካሄዱ ሊቃውንት የተካተቱ በመሆናቸው በዚህ ረገድ የሚሰራውን ሥራ በማሳደግ ሀገሪቷን በውጪው ዓለም በስፋት ለማስተዋወቅ የሚያስችል እንደሆነም ታምኖበታል።
ሊቀ ትጉኃን መምህር ደረጄ ነጋሽ የሰገል ዘ ኢትዮጵያ ድርጅት መስራችና ዋና የቦርድ ሰብሳቢ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት ኢትዮጵያ የምትታወቅባቸው መልካም ነገሮች ዛሬ ላይ እየጠፉ በመምጣታቸው ታሪኩን የማያውቅ፣ ባህሉን የማያከብር፣ ተሳዳቢና ስደተኛ ትውልድ እየተፈጠረ መጥቷል። ድርጅቱ የተመሰረተበት ዋነኛ ዓላማም የኢትዮጵያን ታሪክ፣ ባህል፣ ቅርስ፣ ፍልስፍና ሀገር በቀል እውቀት፣ ስነ-ፅሁፍና ኪነ-ጥበብ ለአሁኑ ትውልድ ማሳወቅ ነው። በተለይ ይህን ትውልድ የኢትዮጵያን ጥንታዊነት በማሳወቅ መገደብ ያስፈልጋል።
የአሁኑ ትውልድ አሁን አሁን እንደ ቫላንታይን ቀን፣ ዋተር ቀን፣ ከለር ቀንና አህያ ቀንን የመሰሉ መጤ በአላትን እያከበረ ይገኛል። ከዚህ አንፃር ጥንታዊ የኢትዮጵያ የበአል አከባበሮችን የሚያጎሉና አብሮነትን የሚያሳዩ ስራዎችን መስራት ያስፈልጋል። ይህንንም በዓለም ዙሪያ በመዟዟር ለማስተዋወቅ ሰገል ዘ ኢትዮጵያ ይሰራል።
ኢትዮጵያ የምትታወቀው በመጎብኘት ነው። ለአብነትም ንግስተ ሳባ በጥበብ ተሞልታና ሰው ሰራሽ (አርተፊሻል) አበባ ይዛ ጠቢቡ ሰሎሞን ጋር ከሶስት ሺ ዓመት በፊት ሄዳለች። እየሩሳሌም ሲመሰረት ሙሴን ያስተማረውም ኢትዮጵያዊው ዮቶር ነው። ኢትዮጵያውያንም የዮቶሪያውያን ልጆች ናቸው። ስለዚህ እንዲህ አይነቶቹ የኢትዮጵያን ጥንታዊነት የሚያሳዩ ታሪኮችን ይህ ትውልድ እንዲያውቅ ማድረግ ይገባል። በቴክኖሎጂ የጠፋውን ትውልድ ከወዲሁ ማስተካከል ያስፈልጋል። ከዚህ አኳያ ሰገል ዘ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴ በማድረግ በታሪክ ደረጃ ኢትዮጵያ ከፍ እንዳለች፤ ትላንትናም ከፍታ እንደነበራት ትውልዱ ተስፋ እንዳይቆርጥ የማድረግ ስራ መስራት ጀምሯል።
ዋና ቦርድ ሰብሳቢው እንደሚናገሩት፣ ድርጅቱ ይዞት የመጣው ፅንሰ ሀሳብ ግለሰቦች ምን አሉ የሚሉትን ሳይሆን ኢትዮጵያ ምን አለች የሚለውን ነው። ለምሳሌ ኢትዮጵያ የመቶ ዓመት ታሪክ አላት ቢባል እነ ካሲዮፓ ከንግስት ሳባ በፊት ኢትዮጵያን አስራ ዘጠኝ ዓመት የገዙ ናቸው። ይህንንም የዓለም ታሪክ መዝገብ ላይ ሰፍሮ ይገኛል፤ ምስክርነትም ሰጥቶበታል። እነ ፕሉቶና ሆሜርም የመሰከሩላት ሀገር ናት ኢትዮጵያ። ግሪካውያን ሳይቀሩ የኢትዮጵያን ክብር ከፍ አድርገው ህብረ ከዋክብትን በሚያገኙበት ግዜ ሶስቱን የኢትዮጵያ ነገስታትን በህብረ ከዋክብት መዝገብ እንዲመዘገቡ አደርገዋል። ይህንን እውነት ደግሞ መላው ዓለም ያውቀዋል።
ሰዎች ሊያልፉ ይችላሉ። ታሪክና ህብረተሰብ ግን አያልፍም። ኢትዮጵያም የምታልፍ ሀገር ስላልሆነች ይህን የታሪክ ሁነት መናገር ይጠበቃልና ግለሰቦችን ተመክቶ የሚደባበስ ጉዳይ ሳይሆን እውነትን በመግለጥ ስለ ኢትዮጵያ ለመላው ዓለምና ለዚህ ትውልድ ማሳወቅ የድርጅቱ ተቀዳሚ ዓላማ ይሆናል። ኢትዮጵያዊነት ደግሞ የተዳፈነ እሳት እንደመሆኑና በሰው ልብ ውስጥ እፍፍፍ.. ሲሉት እንደ እሳት ስለሚቀጣጠል ይህን እውነት በዓለም ላይ ድርጅቱ ይመሰክራል። ለዚህም በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ ቀን ሲከበር ኢትየጵያውያን ለሀገራቸው ያሳዩት ፍቅር ጥሩ ማሳያ ነው።
የዚህ ድርጅት አባላት በየግላቸው በኢትዮጵያዊነት ላይ ልዩ ልዩ የመገናኛ ብዙሃን አማራጮችን በመጠቀምና በተለያዩ ዓለማት በመዟዟር በርካታ ስራዎችን ሲያከናውኑ ቆይተዋል። በጋራ መቆም ሲቻል ደግሞ ጥንካሬ ስለሚመጣና የተሻለ እውቀት ስለሚኖር ሰገል ዘ ኢትዮጵያ የተሰኘውን ቦርድ መር ሀገር በቀል ድርጅት መመስረት ተችሏል። ስራው ጅምር ቢሆንም ገና ከአሁኑ የተሰሩ ስራዎችን የሰሙ ሁሉ ደስታቸውን እየገለፁ ነው። ባለሃብቶችም ከድርጅቱ ጋር አብረው ለመስራት ፍቃደኝነታቸውን ገልፀዋል። በውጪ ሀገራት ያሉ ኢትዮጵያውያንም በጣም ጓጉተው ‹‹ቅድሚያ ወደ እኛ ሀገር ኑ›› እያሉ ጥሪ እያቀረቡ ይገኛሉ። ከዚህ አንፃር ድርጅቱ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም የሚሳተፉበት ጉዳይ ሆኗል።
በቀጣይም ድርጅቱ በመላው ዓለም እየተንቀሳቀሰ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን በማሳተፍ በተለይ ሚዲያዎችን በመጠቀም ሀሳቡ ለህዝቡ እንዲተዋወቅ ማድረግ ይሆናል። ለዚህም ሀምሌ 9 ቀን 2015 ዓ.ም በስነ- ከዋክብት፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ፣ ሀገር በቀል እውቀት ዙሪያ ልዩ ዝግጅቶችን ያሰናዳል። በዚህም ገቢ ማሰባሰብና የኢትዮጵያ ሀገር በቀል እውቀቶች ምን እንደሚመስሉና በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ለማሳየት ይሞከራል። በሌላ በኩል በዓለም አቀፍ ደረጃ በድረ-ገፅ ተሳትፎ የሚደረግበትና የኢትዮጵያን ሀገር በቀል አውቀት፣ ታሪክና ባህል የሚተዋወቅበት ፕሮግራም ይካሄዳል።
በመቀጠል ደግሞ በመጪው መስከረም ወር 2016 ዓ.ም ጉዞ ወደ ሰሜን አሜሪካ በማድረግ ኢትዮጵያን በልዩ ልዩ መስኩ የማስተዋወቅ ፕሮግራም ይዘጋጃል። ይኸው ኢትዮጵያን ለመላው ዓለም የማስተዋወቅ ስራ በልዩ ልዩ መስኩ ለኢትዮጵያ መልካም ስራን የሰሩና እውቀታቸውን ለሀገር ያበረከቱ ሌሎችንም ሰዎች በመያዝ በተለያዩ የአውሮፓ ሀገራትም ይቀጥላል።
የሰገል ዘ ኢትዮጵያ ምክትል ቦርድ ሰብሳቢ ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ እንደሚናገሩት፣ ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ሶስት ትላልቅ ሃይማኖቶች ነበሯት። ጁዲይዝም፣ ክርስትናና እስልምና። አሁን ደግሞ ክርስትናና እስልምና በጉልህ የሚጠቀሱ እምነቶች አሉ። ኢትዮጵያም የተሰራቸው በነዚህ ሃይማኖቶች ነው። ትውልዱም የተቀረፀው በነዚህ ሃይማኖቶች ነው። ኢትዮጵያም ጠንክራ የኖረችው በነዚህ ሃይማኖቶች ነው። ከሚመጡባት አስቸጋሪ ሁኔታዎች፣ ሀገር ማፍረሶች፣ ውጥረቶች ያለፈችውና የቆመችው እነዚህ ሀይማኖቶች ባስተሳሰሩት ኢትዮጵያዊ ማንነት ነው።
ምንም እንኳን እነዚህ ሃይማኖቶች ከውጪ ሀገራት የመጡ ቢሆኑም ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ ኢትዮጵያዊ ሆነው ነው። የኢትዮጵያን ባህልና ማንነት የያዙ ናቸው። በዓለም ላይ በክርስትናና በእስልምና እምነቶች ውስጥ የማይታዩ በኢትዮጵያ ውስጥ አሉ። ለምሳሌ በክርስትና እምነት ውስጥ ሽብሸባውና ያሬዳዊ ዝማሬው ኢትዮጵያዊ ነው። እንደየአካባው ደግሞ የክርስትናው እምነት መተግበሪያ የሆኑ ባህላዊ ሃይማኖቶች አሉ። እነዚህ ሁሉ ኢትዮጵያዊ ናቸው። በተመሳሳይ እስልምና የወሎን መንዙማ የትኛውም ዓለም ማግኘት አይቻልም። ኢትዮጵያዊ ነው። የባሌውና የአርሲው የድሬ ሼ ሁሴን መንዙማ የትም ዓለም የለም።
ስለዚህ ስለ ኢትዮጵያ ስናወራ ከነዚህ ውጪ መሆን አይቻልም። እነዚህን መያዝ ካልቻልን ኢትዮጵያ ሙሉ ኢትዮጵያ አትሆንም። ኢትዮጵያ ህብረ ብሄራዊ እንደመሆኗ በርካታ ባህልና ቋንቋዎች አሏት። ከዚህ አንፃር እነዚህን የኢትዮጵያ እውነታ ለአሁኑ ትውልድም ሆነ ለተቀረው ዓለም በስፋት ማስተዋወቅ ይገባል። ለዚህ ደግሞ ሰገል ዘ ኢትዮጵያ ይዞት የተነሳው ዓላማም ከዚህ ጋር የሚጣጣም በመሆኑ የሚደገፍና የሚበረታታ ነው።
ምክትል ቦርድ ሰብሳቢው እንደሚሉት፣ አሁን ያለው አገራዊ ሁኔታ አስጋሪ ወደመምሰል ሄዷል። ነገር ግን ከዚህ ችግር ለመውጣት ልናወጋቸው የምንችላቸው በርካታ ታሪኮች አሉን። ለምሳሌ እነዚህ ችግሮች ውስጥ ልንገባ የቻልነው በማንነታችን ላይ በሚገባ ስላልሰራን ነው። ከሶስት ሺ ዘመን በላይ መንግስት መስርታ የኖረችና በሌሎች ያልተገዛች ሀገር ማለት ትልቅ ኩራት ነው። ነገር ግን ይህ በሚገባ አልተነገረም። ይህን ሁሉ ዘመን እንዴት በጋራ ተባብረን ሀገርንና ህዝብን እንዳቆየን በደምብ አልተገለፀም። ስለዚህ እነዚህን ጉዳዮች ተቀራርቦ ማውጋት ያስፈልጋል።
እያንዳንዱ ማህበረሰብና ብሄረሰብ ውስጥ ትልልቅ ታሪኮች አሉ። ትልልቅ ኢትዮጵያዊነት አለ። ኢትዮጵያን ያቆየንባቸው ታሪኮች አሉ። ነገር ግን አልተነገረም። ስለዚህ እነዚህን ሁሉ ታሪኮች በማውጣትና በማሳየት ከሚለያዩ አስተሳሰቦች ይልቅ አንድ የሚያደርጉ፣ የሚያጠነክሩ፣ ህይወትንና ሀገርን የሚቀይሩ፣ ወደተሻለ ምእራፍ የሚያሻግሩ በርካታ ሃሳቦች በመኖራቸው እነሱን እያወጣን ማሳየትና ማስረዳት ይጠበቅብናል።
በትምህርት ስርአት ውስጥ ኢትዮጵያዊነት የሚለው ትምህርት ገብቶ ትውልድ በኢትዮጵያዊ ማንነት እንዲታነፅ ማድረግ ይገባል። ለምሳሌ ሉሲ ወይም ድንቅነሽ እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው የተገኘችው። ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላው ዓለም ትልቅ ታሪክ ነው። ኢትዮጵያ የስንት ዘመን ቀደምት ሀገር መሆኗንም ይጠቁማል። የኢትዮጵያ የጊዮን/ናይል ወንዝ መነሻ ሀገር ናት ማለት ትልቅ ኩራት ነው።
የዜማና የቅኔ ሀገር ናት መባል ትልቅ ታሪክ ነው። የእርሻና የብዙ ታሪኮች ባለቤቶች መሆንም አስደናቂ ነው። ትልልቅ እምነቶች ያሉባት ሀገር ናት መሰኘትም ትልቅ ኢትዮጵያዊነትን የሚያጠናክር ስለሆነ የዛሬ ልጆችን፣ ትውልዱን በትምህርት ስርአት ውስጥ እያበለፀጉ መጓዝ ያስፈልጋል። በኢትዮጵያ አንድነትን እያስተማሩ ማስቀጠል ይገባል።
ለምሳሌ ኢትዮጵያ ማውራት ያለባት ስለ ኢትዮጵያዊነት ሳይሆን ስለ አፍሪካዊነት ነው። ምክንያቱም አፍሪካ የምትባለዋ አህጉርና የአፍሪካ ሀገራት የነፃነት መነሻቸው ኢትዮጵያ በመሆኗ ነው። እያንዳንዱ አፍሪካዊ ሀገር ታሪኩን ሲፅፍ መነሻው ኢትዮጵያ ናት። ወደ ነፃነት ያደረጉት ጉዞም ከኢትዮጵያ ነፃነት አንፃር ነው። ሀገራቱ ኢትዮጵያ እንዴት ነፃ ሆነች? እንዴትስ ህዝቡ ሀገሩን ጠበቀ? እንዴት ለአንድነታቸውና ለነፃነታቸው በጋራ ቆሙ? ብለው ነው የሚነሱት። እነ ጆሞ ኬንያታ፣ ክዋሜ ንኩሩማ፣ ጁሊየስ ኔሬሬ፣ ኬኔት ካውንዳና የነፃነት ትግላቸውን ያቀጣጠሉት ኢትዮጵያን የነፃነት ፋና ወጊ አድርገው በመቁጠር ነው። የዩጋንዳው የወቅቱ ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ በልጅነታቸው የተማሩት እንደ ኢትዮጵያ ለመሆን እንደሆነም በአንድ ወቅት ተናግረዋል።
ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ ማውራት ያለባት ስለ አፍሪካዊነት ነው። ኢትዮጵያ አይደለም ለራሷ ለመላው አፍሪካ የሚተርፍ ያገለገለ የታሪክ ማንነት ያላት ሀገር በመሆኗ ይህን ለአሁኑ ትውልድና ለመላው ዓለም ማስተዋወቅ ያስፈልጋል። ይህንኑ በማስተማር ያሉትን ችግሮችና እንቅፋቶችን ኢትዮጵያ ባላት የማንነት ታሪክ ማስተካከል ይቻላል። ለዚህ ደግሞ ሰገል ዘ ኢትዮጵያ ስራውን ‹‹ሀ›› ብሎ ጀምሯል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሰኔ 22/2015