ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪን የሚጠይቁ እንደመሆናቸው በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የራሳቸውን አሉታዊ ተፅእኖ ያሳደራሉ።በኢትዮጵያም ይህን ጫና ለመቀነስ እንደ ሀገር ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት የሚያስችሉ ተኪ ምርቶች ማምረት ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ይገኛል።
ለእዚህም የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ይጠቀሳል።በግሉ ዘርፍ ተሰማርተው ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመተካት የውጭ ምንዛሪ ለማዳን የሚያስችሉ ምርቶችን በሀገር ውስጥ የሚያመርቱ በርካቶች ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ ለልጆች መጫወቻ አሻንጉሊቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት ከውጭ ሀገር በውድ ዋጋ የሚገቡ አሻንጉሊቶች ለመተካት የሚያስችል ሥራ እየሰሩ ከሚገኙት መካከል አንዷ ቃልኪዳን ኢሳያስ ናት።ቃልኪዳን የአሻንጉሊት ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት ትታወቃለች።
ቃልኪዳን እንደምትለው፤ አሻንጉሊት መስራት የጀመረችው ወልዳ አራስ ቤት ሆና ሳለ ልጆቿ በአንድ አሻንጉሊት ሲጣሉ ተመልክታ ነው፤ ሌላ አሻንጉሊት ለመስራት ያደረገችው ተደጋጋሚ ጥረት የዚህ ሙያ ባለቤት አድርጓታል። ‹‹ለልጆቼ መጫወቻ የሚሆኑ አሻንጉሊቶች ለመስራት በማሰብ ነው፤ ወደ እዚህ ሙያ የገባሁት›› የምትለው ቃልኪዳን፤ በወቅቱ ላጋጠማት ችግር መፍትሔ ፈልጋ በሰራችው አሻንጉሊት ወደ አሻንጉሊት ዲዛይኒንግ ሙያ መግባቷን ትናገራለች።ሙያውን እያዳበረች መጥታ ላለፉት አራት ዓመታትም በሙያው ላይ ቆይታለች።
ቃል ኪዳን መጀመሪያ ላይ በሰራችው አሻንጉሊት ልጆቿ ደስተኛ እንዲሆኑ አድርጋለች።ሥራዋን የተመለከተው ባለቤቷም ሆነ በዙሪያዋ ያሉ ሰዎች በሙሉ ስራውን ስለወደዱት ሌሎች ተጨማሪ አሻንጉሊቶች እንድትሰራ ብርታት ሆነዋት በሙያው እንድትቀጥል አድርገዋታል።የመጀመሪያውን አሻንጉሊት ለህጻናት መጠቅለያነት ከሚያገለግለው ጨርቅ መስራቷን የምታስታውሰው ቃልኪዳን፤ በሁለተኛው ሙከራዋ ደግሞ በጣም ቆንጆ አሻንጉሊት በመስራቷ ሌሎች ሰዎች እንድትሰራላቸው ይጠይቋታል፤ ይህም ሙያውን የበለጠ እያዳበረች እንድትመጣና አሁን ያለበት ደረጃ ላይ ማድረስ እንድትችል ረድቷታል።
ቃልኪዳን፤ ከውጪ የሚመጡ አሻንጉሊቶችን በመመልከት ነው የራሷን ዲዛይን መፍጠር የጀመረችው።እነዚህ አሻንጉሊቶች ፈር ከሚባሉ ጨርቆች እና ከፋይበር (ለትራስ ጨርቅ ከሚሆን ጥጥ) የሚሰሩ ናቸው።መጀመሪያ ላይ አሻንጉሊቶቹን ለመሥራትና የሚቆራረጡትን ጨርቆች ለመስፋት መርፌና ክር ነበር የተጠቀመችው፤ ይሄ አሠራር ረጅም ሰዓት የሚወስድና አድካሚ መሆኑን ቃልኪዳን ታስታውሳለች።
አሁን ላይ ሥራዎቿን ለመስራት የሚያስችላትን የልብስ መስፊያ ማሽን በመግዛት በተለያየ መልኩ ዲዛይን የተደረጉ አሻንጉሊቶችን እየሰራች ለገበያ እያቀረበች ትገኛለች።አሻንጉሊቶችን ለመስራት በቅድሚያ በአእምሮዋ የፈጠረችውን ዲዛይን በወረቀት ላይ ከሳለች በኋላ አሻንጉሊቶችን እንደምትሰራ ነው የምትናገረው።
ቃልኪዳን እንደምትለው፤ ከትንሽ ጀምሮ ትላልቅ እስከሚባል ደረጃ ያላቸው አሻንጉሊቶችን ትሰራለች።ሥራውን ስትጀምር አንድ አሻንጉሊት ለመሥራት ሁለት ቀናት ይፈጀባት ነበር።አሁን አንድ አሻንጉሊት በደቂቃዎች መጨረስ ትችላለች፤ በቀን ውስጥ 20 እስከ 30 ያህል አሻንጉሊቶችን እያመረትች ትገኛለች።የአቅም ውስንነት ስላለባት እንጂ በቀን እስከ መቶ ድረስ አሻንጉሊቶችን ማምረት እንደሚቻልም ነው የተናገረችው።
አሻንጉሊቶችን ብቻ አይደለም ቃልኪዳን የምትሰራው፤ ህጻናት ሲጫወቱም ሆነ ሲተኙ ምቾት እንዲሰማቸው የሚያደርጉ ከአንድ ዓመት እስከ 12 ዓመት ድረስ ለሚሆኑ ህጻናት ቢጃማዎችንም ትሰራለች። አሻንጉሊቶቹንና ቢጃማዎቹን ልጆችና ወላጆች በጣም እንደሚወዷቸውም ነው የምትናገረው።
አብዛኛዎቹ አሻንጉሊቶች ከውጭ ሀገር በኮንቴነር ተጭነው ሲጓጓዙ ረጅም ጊዜ እንዲቆዩ ኬሚካሎች እንደሚደረግባቸው የምትገልጸው ቃልኪዳን፤ እነዚህ አሻንጉሊቶች በጭነትና በቆይታ ብዛት መቀዳደድ ሊገጥማቸው እንዲሁም ለአቧራ ሊጋለጡ እንደሚችሉም ትጠቁማለች።እርጥበት ሲነካቸው ቶሎ የማይደርቁና መጥፎ ጠረን የሚያመጡ አሻንጉሊቶች እንዳሉም ትገልጻለች። ‹‹እኔ የማመርታቸው አሻንጉሊቶች ግን ጥራታቸውን የጠበቁና ኤክስፖርት ስታንዳርድ ናቸው›› የምትለው ቃልኪዳን፤ አሻንጉሊቶቹ ከውጪ ሀገር የሚመጡትን አሻንጉሊቶች የሚተኩ እንደሆኑም ነው የምታብራራው።
አሻንጉሊቶቹ የሚሸጡበት ዋጋ ተመጣጣኝ እና ሁሉም ሰው በየአቅሙ ሊገዛቸው የሚችል መሆናቸውን ጠቅሳ፤ ከ150 ብር ጀምሮ እንደሚሸጡም ትናገራለች።ከውጭ የሚገቡ አሻንጉሊቶች በውጭ ምንዛሬ ስለሚገቡ ዋጋቸው ውድ ነው የምትለው ቃልኪዳን፤ ምርቶቿን በሀገር ውስጥ በብዛት በማምረት ከውጪ የሚመጡትን በመተካት የውጭ ምንዛሬ ወጪን ማስቀረት እንደሚቻል ትናገራለች። አሻንጉሊቶችን በብዛት በማምረት ለውጪ ገበያ በተለይ ለአፍሪካ ሀገሮች ለማቅረብ ሃሳቡ እንዳላትም ጠቁማለች።
ከውጭ ሀገር የሚመጣው ትንሹ አሻንጉሊት እኛ የምናመርተው ትልቅ አሻንጉሊት በሚሸጥበት ዋጋ ነው የሚሸጠው የምትለው ቃልኪዳን፤ ከውጭ ሀገር የሚገቡት በሀገር ውስጥ ከሚመረቱት ጋር ሲነጻጸሩ በዋጋ ብቻ ሳይሆን በመጠንም ሆነ በጥራት ከሀገር ውስጦቹ አይወዳደሩም ትላለች፡፡ መጀመሪያ አካባቢ የምትሰራቸውን አሻንጉሊቶች ለመሸጥ የሚረከቧት ሰዎች አጥታ እንደነበር የምታስታወሰው ቃልኪዳን፤ ምርቷን እንዲረከቧት የምትጠይቃቸው ሰዎች በሀገር ውስጥ በእጅ የተሰሩ አሻንጉሊቶች ናቸው ስትላቸው አይቀበሏቸውም ነበር። አሻንጉሊቶቹ ቀስ በቀስ እየተለመዱና የገዥዎችም ፍላጎት እየሆኑ መምጣታቸውንም ገልጻለች።
እሷ እንደምትለው፤ መጀመሪያ ላይ በምታቀርባቸው የአሻንጉሊት ምርቶች ላይ በሀገር ውስጥ በእጅ የተሰራ የሚል መለያ ለጥፋባቸው ስለነበር ብዙ ሰዎች ይህንን መለያ እንድታነሳው ይጠይቋትም ነበር።የተረከቧትም ቢሆኑ መለያውን ከላዩ ላይ ገንጥለው ሲሸጡት ታዝባለች። ‹‹ቤት መጥተው በርካሽ ዋጋ የሚረከቡኝም ሰዎችም የተለጠፈበትን መለያ ቆርጠው ሲሸጡ ደርሼባቸዋለሁ›› የምትለው ቃልኪዳን፤ ለዚህ ሁሉ ምክንያቱ ከውጭ ሀገር በውድ ዋጋ የገባው ነው እያሉ አስመስለው ለመሸጥ ካላቸው ፍላጎት የተነሳ እንደሆነ ትጠቁማለች።
አሁን ላይ በአብዛኛውን ሰው ዘንድ ይህ አይነቱ አመለካከት እየተቀየረ በምትሰራው ሥራ እውቅና እየተሰጣት እንደሆነም ትናገራለች።ሥራዎቿን እያስፋፋች ለስምንት እናቶችና ሴቶች የሥራ እድል በመፍጠርና ሙያውን ለሌሎች ለማስተላለፍም ጥረት እያደረገች ትገኛለች።
እንደ ቃልኪዳን ማብራራያ፤ በቀጣይ የልጆችን ፍላጎት መሠረት በማድረግ ብዙ ነገሮች መስራት ትፈልጋለች።የዲዛይኒንግ ሙያዋን ለማሻሻል የሚያስችላችን የዲዛይኒግ ትምህርት በኦንላይን እየተማረች ነው።በተቻላት መጠን ሥራዎቿን ለማሳደግ ጥረት እያደረገች ነው።‹‹የሚደግፈኝ አካል አለማግኘቴ እንጂ ሥራዬ ለብዙ ሴቶችና እናቶች የሥራ እድል መፍጠር የሚችል ነው››ብላለች።
አሁን ላይ በአዲስ አበባ ከተማ ሁለት የማሳያና የመሸጫ ቦታዎች እንዳሏት ጠቅሳ፤ ከዚህ በተጨማሪም የምትስራቸውን አሻንጉሊቶች እንደ ቴሌግራም፣ ፌስቡክ፣ ኢንስተግራም እና ቲክ ቶክ የመሳሰሉትን የማህበራዊ ሚዲያ ቻናሎች በመጠቀም በኦንላይን እያስተዋወቀች ትገኛለች፡፡
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 19 ቀን 2015 ዓ.ም