የተባበሩት መንግሥታት የምግብ ሥርዓት እና ስነ ምግብ ይፋ የተደረገው ድርጅቱ በ2011 ዓ.ም ባካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ። ያ ወቅት ዓለም በምግብ ሥርዓት እና ሥነ ምግብ የተነሳ ወደ ከፋ ችግር እየተንደረደረች ያለችበት ነበር። ይህን አስከፊ ችግር ለመመከትና ከረሃብ ነጻ የሆነ ዓለም ለመፍጠር ዘላቂ የልማት ግቦች ተቀርጸው ሀገራት እየተገበሯቸው ይገኛሉ።
በኢትዮጵያም የምግብ ሥርዓት እና ሥነ-ምግብ ሥራ በአገር አቀፍ ደረጃ ለውጤት እንዲበቃ የተለያዩ ተግባሮች እየተከናወኑ ናቸው። በኢትዮጵያም በ2012 ዓ.ም የኢትዮጵያ የምግብ ሥርዓትና ስነ-ምግብ ትራንስፎርሜሽን መርሀ ግብር ተቀርጾ እየተሰራ ይገኛል። ይህንንም ለማስፈጸም የሚኒስትሮች ስትሪንግ ኮሚቴ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶክተር) መቋቋሙ ይታወሳል። 15 ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን ያቀፈው ይህ ኮሚቴ ከሰሞኑ የመጀመሪያ ጉባኤውን አካሂዷል። ኮሚቴው የኢትዮጵያን የምግብ ሥርዓት እና ስነ-ምግብ ትራንስፎርሜሽን አጀንዳ ዕውን ለማድረግ የሚሰራ ሲሆን፣ ለተግባራዊነቱም ሀገራዊ አቅሞችን በሙሉ አሟጦ መጠቀም እንዳለበት ተመልክቷል።
የጤና ሚኒስቴር እና የግብርና ሚኒስቴር በዋናነት የሚኒስትሮች ስትሪንግ ኮሚቴውን የሚያስተባብሩና የሚመሩ ሲሆን፤ ከ15ቱ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ጋር በመሆን መክረው፣ አቅደውና ተከታትለው፤ የኢትዮጵያን የምግብ ሥርዓት ሂደት፣ የምግብና የተመጣጠነ ምግብ ስትራቴጂ እንዲሁም የሰቆጣ ቃልኪዳንን/ በህጻናት ላይ የሚከሰት መቀንጨርን ለማስቀረት የሚሰራ/ በማስተባበርና በመምራት፣ ፖሊሲዎችን እና ማዕቀፎችን መምራት፣ የክልል መንግሥታትን መደገፍ እንዲሁም አተገባበሩን መከታተልና መገምገም ይጠበቅባቸዋል።
በኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ የተመጣጠነ ምግብ እጥረትን ለመፍታት እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን ለመከላከል ኮሚቴው እንደሚሰራ የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሠ ይገልጻሉ። በኢትዮጵያ የምግብ ስርዓት እና ሥነ ምግብ ትራንስፎርሜሽን ፍኖተ ካርታ በ2012 ዓ.ም ወደ ትግበራ መግባቱን ሚኒስትሯ ጠቅሰው፤ ይህም የኢትዮጵያን የምግብ ርዓት ለመቀየር፣ ምርትና ምርታማነትን ለማሻሻል እንዲሁም ጤናማ ምግቦችን ለማህበረሰቡ ተደራሽ ማድረግን ዓላማ ያደረገ እንደሆነ ተናግረዋል።
ሚኒስትሯ እንዳሉት፤ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ሥራዎች ከሥርዓተ ምግብ ማሻሻል ጋር ተቀናጅተው ተግባራዊ እንዲሆኑ ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መሥራት ይኖርባቸዋል። የሚኒስትሮች ስትሪንግ ኮሚቴው የምግብ ስርዓት እና ሥነ ምግብ ትራንስፎርሜሽን ፍኖተ ካርታን ወደ ትግበራ ከማስገባት ባሻገር የሰቆጣ ስምምነት ቃል ኪዳን እንዲተገበር በማድረግ አጠቃላይ የምግብ ሥርዓትና ሥርዓተ ምግብ ትራንስፎርሜሽን ፍኖተ ካርታን በጋራ በመምራት ይሰራል።
የኢትዮጵያን የምግብ ሥርዓት እና ሥነ ምግብ መጥፎ ገጽታን ለመቀየርና ምርትና ምርታማነትን ከማሻሻል ጀምሮ ጤናማና በንጥረ ነገር የበለጸጉ ምግቦችን ለማህበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ እንዲሁም ጤናማና ምርታማ ማህበረሰብን ለመፍጠር የሚያስችሉ በርካታ ተግባሮች ተከናውነዋል። ‹‹ ኮሚቴውን ወደ ትግበራ ማስገባት ዘርፈ ብዙ ትብብር የሚፈልግ ሥራ ነው›› ያሉት ዶክተር ሊያ፤ የምግብና የስርዓተ ምግብ ችግሮችን ለመፍታት በርካታ ዘርፎች በቅንጅት መሥራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል። ለዚህም ከፌዴራል ጀምሮ እስከ ክልል ድረስ የቅንጅት ሥራ በመሥራት የማስተባበርና የመምራት ሥራው የተጠናከረ መሆን እንዳለበትም ገልጸዋል። ለዚህም የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች አገልግሎትን ጨምሮ 15 ሴክተር መስሪያ ቤቶች ያሉበት ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ሥራ ለመግባት ሰፊ ጥናት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ዘርፈ ብዙ ትብብር የሚጠይቀው የሚኒስትሮች ስትሪንግ ኮሚቴ አስተባባሪ ከምግብ ሥርዓት ትግበራ በተጨማሪ የሥርአተ ምግብና የሰቆጣ ቃልኪዳን ትግበራን የሚከታተልና የሚያስፈጽም እንደሆነም ጠቅሰው፤ ኮሚቴው የተለያዩ ኃላፊነቶችን ይዞ ወደ ትግበራ መግባቱንና ተግባራዊ የሚደረጉ ሥራዎችንም ማጽደቁንም ጠቁመዋል። በቀጣይም ጉዳዩን በበላይነት የሚከታተል ምክር ቤት እንዲቋቋምና ለሚኒስትሮች ምክር ቤት እንዲቀርብም ስምምነት ላይ መደረሱን አመላክተዋል።
በመጀመሪያው የዐቢይ ኮሚቴው ስብሰባ ላይ የተገኙት የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ስር በሰደደ የምግብና ሥነ-ምግብ ዋስትና ችግር ውስጥ እንደምትገኝ ጠቅሰው፤ ይህን መሰረት በማድረግ ኮሚቴው በፍኖተ ካርታው ውስጥ የተመላከቱ ውጤት ቀያሪ ተብለው በተቀመጡ የመፍትሄ አቅጣጫዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሠራ አስታውቀዋል። ለዚህም የተለያዩ ቴክኒካል ኮሚቴዎች መቋቋማቸውን ገልጸው፤ መሰል አደረጃጀት በክልል ደረጃም እንደሚቋቋም ተናግረዋል።
የምግብ ሥርዓት እና ስነ ምግብ ትራንስፎርሜሽን ፍኖተ ካርታው በዓለም አቀፍ ደረጃ ቀርቦ አድናቆት ማግኘቱን ጠቅሰው፣ በፍኖተ ካርታው ችግሮች መለየታቸውንም ነው ሚኒስትሩ የጠቀሱት። ይህን መሰረት በማድረግም የመፍትሄ አቅጣጫዎች እና የትግበራ መርሃ ግብሮች መዘጋጀታቸውንም አመልክተዋል።
‹‹ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን አስከብራ የኖረች ቢሆንም አንገታችንን ቀና አድርገን መሄድ እንዳንችል ከሚያደርጉን ቁልፍ ጉዳዮች መካከል አንዱ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ አለመቻላችን›› ነው ያሉት ዶክተር ግርማ፤ ከዚህ አንጸር ያሉ ውስንነቶችን ከሥር መሰረቱ መቅረፍ የሚያስችል መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት ኢትዮጵያ በ2030 የምግብና የሥነ-ምግብ መዋቅራዊ የሽግግር ሥርዓትን ለማረጋገጥ ፍኖተ ካርታ አዘጋጅታ ወደ ትግበራ መግባቷን አስታውቀዋል። በፍኖተ ካርታው ውስጥ የተመላከቱ ውጤት ቀያሪ መፍትሄዎች በአግባቡ እንዲተገበሩ ኮሚቴው በቁርጠኝነት እንደሚሠራም አረጋግጠዋል።
የምግብ ሥርዓት እና ስነ-ምግብ ትራንስፎርሜሽን ፍኖተ ካርታው በዓለም አቀፍ ደረጃ ቀርቦ አድናቆት ማግኘቱን ዶክተር ግርማ ጠቅሰው፤ በፍኖተ ካርታውም ችግሮች መለየታቸውንና ቁልፍ የተባሉ ችግሮችን መሰረት በማድረግም የመፍተሄ አቅጣጫዎች እና የትግበራ መርሃ ግብሮች ተዘጋጅተው ወደ ትግበራ እንደሚገባ ነው ያስረዱት። ችግሮችን ከመለየትና የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ከማስቀመጥ በተጨማሪ እንዴት ተግባራዊ ሊሆን እንደሚችል ጭምር የክትትልና ድጋፍ ሥርዓት መዘርጋቱንም አስታውቀዋል።
እንደ ግብርና ሚኒስትሩ ማብራሪያ፤ በፌዴራል ደረጃ የጤና ሚኒስቴር እና የግብርና ሚኒስቴርን ጨምሮ 15 አባላት ያሉት የሚኒስትሮች ስትሪንግ ኮሚቴ ሥራውን በበላይነት የሚመራው ቢሆንም፣ ይህን ተግባር የሚደግፉ ቴክኒካል ኮሚቴዎችም ተቋቁመዋል። መሰል አደረጃጀቶች በክልል ደረጃ የሚቋቋሙ ሲሆን፤ ሶስተኛው ደግሞ የልማት አጋሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበት መድረክ እንደሆነ ጠቁመዋል።
በመንግሥት በጀትም ይሁን በልማት አጋሮች ድጋፍ የሚሰሩ ፕሮጀክቶች በመሉ ለዚህ ግብ መሳካት ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸው ያስገነዘቡት ዶክተር ግርማ፤ ይህ ተግባርም እጅግ በጣም ባጠረ ጊዜ እንደሚከናወን ነው ያመለከቱት። ባልተቀናጀ መንገድ እየተከናወኑ ያሉት ተግባሮች እንዲቀናጁ እንደሚደረግ ፣ አሁን ላይ ከተቀመጠው ግብ አንጻር አላማውን ለማሳካት የተመጣጠነ ሥራ እንደሚሰራም ገልጸዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ ይህን ሥራ ለመሥራት የተቋማትን አጥር አልፎ መሄድ ይገባል። ያለምንም ኃላፊነትና ጂኦግራፊያዊ ገደብ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን እምቅ አቅምና የተለያዩ ጸጋዎች ለዚሁ ዓላማ ማዋል ያስፈልጋል፤ ሌሎች ፕሮጀክቶችን በማዘጋጀትም ተጨማሪ ሀብት የማሰባሰብ ሥራዎች ይሰራሉ። ኮሚቴው እንደ አስፈላጊነቱ ባልተወሰነ ጊዜ የሚገናኝበት ሁኔታ እንዳለ ሆኖ በየሶስት ወራት ደግሞ በቋሚነት የሚገናኝበት መድረክ ይኖረዋል።
‹‹የምግብና የሥርዓተ ምግብ ጉዳይ የማምረት ጉዳይ ብቻ አይደለም›› ያሉት ዶክተር ግርማ፤ አምርቶ በአግባቡ የመጠቀም ችግር እንዳለም ገልጸዋል። ያለውን ምግብ ካለው ይዘት አንጻር ያለመጠቀም ችግር መኖሩንም አስታውቀዋል። ለዚህም ማህበረሰቡን በማሳተፍ ጭምር ሁሉን አቀፍና የተቀናጀ ሥራ መሥራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል። ችግሩን ለመፍታት እጅግ በተቀናጀና በተባበረ መንገድ መሥራት የግድ መሆኑን አብይ ኮሚቴው ማስታወቁን ጠቅሰው፣ ለዚህም የግብርና ሚኒስቴርና የጤና ሚኒስቴር ሥራውን በባለቤትነት መምራታቸውን እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
ከሚኒስትሮች ስትሪንግ ኮሚቴ በተጨማሪ ሌሎች ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች በየአካባቢያቸው ያለውን አቅም በመጠቀም ለዚሁ ሥራ የማዋል ትልቅ ፈቃደኝነት እንዳላቸው ማረጋገጥ እንደተቻለም የግብርና ሚኒስትሩ አስታውቀዋል። ይህም ትልቅ አቅም እንደሆነ በመግለጽ በዚህ አይነት መንፈስ መቀጠል ከተቻለ እኤአ በ2030 ኢትዮጵያ ለማሳካት ያስቀመጠችውን የምግብ ዋስትና እና የሥርዓተ ምግብ ዋስትናዋ የተጠበቀ ኢትዮጵያን የመፍጠር ራዕይን እውን ማድረግ እንደሚቻል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
የፍኖተ ካርታውን ዝግጅት በበላይነት የመሩት የስነ ምግብ ባለሙያው ዶክተር ጌታቸው ድሪባ እንዳሉት፤ የዜጎችን የምግብ ፍላጎት ለማሟላት ምርትና ምርታማነትን ከማሻሻል ባሻገር ጤናማ ምግቦች ተደራሽ መሆን ይኖርባቸዋል። የምግብ ሥርዓት ከበርካታ የልማት ዘርፎች ጋር የሚያያዝ ሲሆን፣ የማይነካው አካል የለም፤አካታችና ሁሉን አቀፍ ነው።
የኢትዮጵያ ችግሮች ለበርካታ ዘመናት ሲንከባለሉ የመጡና በእጥፍ እያደጉ ያሉ መሆናቸውን አስታውሰው፣ እንደ ዜጋ፣ እንደ መንግሥትና እንደ ሀገር የገዘፈውን የምግብ ሥርዓት ችግር ልናስተላልፈው አንችልም ሲሉም ዶክተር ጌታቸው አስገንዝበዋል። ስለዚህ የተደራጁት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ስትሪንግ ኮሚቴዎች ተቀናጅተው የኢትዮጵያን ችግር በሙሉነት አንድ ሆነው በጋራ እንደሚመለከቱ ገልጸዋል።
‹‹ድር ቢያብር አንበሳ ያስር›› እንዲሉ ነገሮችን ከራስ ፍላጎትና ከራስ መስሪያ ቤት ውጪ በማሰብ የጋራ ኃላፊነት ወስዶ ችግሩን መላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲያውቀው በማድረግ ለችግሩ የጋራ መፍትሔ በማምጣት ተጠያቂነትን ማስፈን የሁሉም ኃላፊነት ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል። ዶክተር ጌታቸው እንዳሉት፤ መሰረታዊ የኢኮኖሚ አውታሩ መቀየር ይኖርበታል፤ ለዚህም ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ አንዱና ዋነኛው ጉዳይ ይሆናል። በሌላ በኩል የሚመረተውን ምርት በማቀነባበር ለሰው ልጅ አልሚ ምግብ እንዲሆን በሚያመች መንገድ ለህዝብ ማቅረብ የግድ ያስፈልጋል።
በተለይም ህጻናት ከተወለዱ እስከ አራት ዓመት እድሜያቸው ማግኘት ያለባቸው ምግብ በዕድሜ ልክ ሕይወታቸው የወሳኝነት ሚና እንዳለው ዶክተር ጌታቸው አስታውቀዋል፤ ከዚህም አንድ ጊዜ የቀነጨረን ህጻን በአንድ ጊዜ ለማዳን ቀላል እንዳልሆነ መረዳት እንደሚቻል ገልጸዋል። ይህም እጅግ ውስብስብና ከባድ ችግር እንደሆነ ተናግረው፤ ለዚህም ዘላቂና ስርነቀል የምግብ ሥርዓት እና ሥነ ምግብ የማረጋገጥ ሥራ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። ሁልጊዜ ቀጨጨ፤ ተራበ በማለት እርዳታ ፍለጋ መሄድ እንደማያዋጣ በመጥቀስ ይህን ችግር ለመፍታት የበለጸገና የተመጣጠነ ምግብ ለሁሉም ለማዳረስ የተቋቋመው የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ኮሚቴ ትልቅ ኃላፊነት እንዳለበት ነው የተናገሩት።
በኢትዮጵያ የምግብ ሥርዓት እና ሥነ-ምግብ ትራንስፎርሜሽን አጀንዳ ቀረጻ ሂደት ላይ ከ120 በላይ ባለሙያዎችና 40 የሚደርሱ ተቋማት፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የምርምር ተቋማት እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተለያዩ ኤጀንሲዎች ተሳትፈዋል፤ የትራንስፎርሜሽን አጀንዳው ምርትና ምርታማነትን መጨመር፣ የገጠር ኑሮን ማሻሻል፣ የምግብ ዋጋ ንረትን ማረጋጋት እና ጤናማ ምግቦች አመጋገብን ማሻሻል እንዲሁም የተፈጥሮ ሀብቶችን መጠበቅን ዓላማ ያደረገ መሆኑም ተመላክቷል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 19 ቀን 2015 ዓ.ም