ከዚህ ቀደም በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ስር የነበሩትን የምዕራብ ኦሞ፣ የቤንች ሸኮ፣ የከፋ፣ የዳውሮና የሸካ ዞኖች እና የኮንታ ልዩ ወረዳን በአንድነት በመያዝ በኅዳር ወር 2014 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲዊ ሪፐብሊክ 11ኛው ክልላዊ መንግሥት ሆኖ የተዋቀረው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል፤ በተፈጥሮ ሀብት የታደለ ነው።
ክልሉ ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ቀጣና ብቻ ሳይሆን ለሌሎቹ የአገሪቱ አካባቢዎችም የሚበቃ የተትረፈረፈ ሀብት አለው። ዓመታዊ ሰብል፣ ቡናና ቅመማ ቅመም፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ኢንዱስትሪ እና አገልግሎት ዘርፎች በክልሉ በኢንቨስትመንት ለመሰማራት የሚያስችሉ የምጣኔ ሀብት መስኮች ናቸው። በተለይም ክልሉ ያለው የቡና፣ የሻይ ቅጠል፣ የአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የማዕድናት ሀብት አገርን የሚያኮራ፣ ባለሀብቶችን በኢንቨስትመንት ለመሰማራት የሚያነሳሳ እና የሕዝብን የልማት ጥያቄ ለመመለስ ምቹ ሁኔታዎችን የሚፈጥር መልካም አጋጣሚና ፀጋ ነው።
ክልሉ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት የሀገር ኢኮኖሚን በብርቱ የሚደግፉ ምርቶች መገኛ ነው። ከፍተኛ የቡናና የማዕድን ሀብቶችን የያዘው ይህ ክልል፤ ሀብቱ ከክልሉ አልፎ ለአገርም የሚተርፍ ፀጋ ነው። ክልሉ አስደናቂ የሆነ መልከዓ ምድራዊ አቀማመጥ፣ ልምላሜና የተፈጥሮ ሀብት ያለው በመሆኑ የባለሀብቶችን ትኩረት የሚስብ መሆኑ አያጠያይቅም።
የክልሉን ሀብቶች ለመለየት የሚደረጉ ተጨማሪ ጥናቶች እንደተጠበቁ ሆነው፤ እስካሁን በተካሄደው ጥናት 88ሺ 786 ሄክታር ለዓመታዊ ሰብሎች፣ አራት ሺ 875 ሄክታር ለቡናና ቅመማ ቅመም እና 20ሺ 565 ሄክታር ለአትክልትና ፍራፍሬ፤ በአጠቃላይ 134ሺ 126 ሄክታር መሬት ለግብርና ዘርፍ ምቹ እንደሆነ ታውቋል። በአገልግሎትና በኢንዱስትሪ ዘርፎችም ክልሉ የኢንቨስትመንት መዳረሻና አማራጭ መሆን የሚችል አካባቢ ነው።
የክልሉ ማዕድንና ኢነርጂ ልማት ኤጀንሲ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ ክልሉ ወርቅን ጨምሮ የተለያዩ ማዕድናት ባለፀጋ ነው። ከወርቅ ማዕድን በተጨማሪ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚውል የድንጋይ ከሰል በክልሉ በዳውሮ እና በኮንታ አካባቢዎች በስፋት ይገኛል። ለኢንዱስትሪዎች ግብዓት የሚሆን የብረትና የድንጋይ ከሰል ማዕድናትም ሌሎች በክልሉ የሚገኙ ሀብቶች ናቸው። በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ማዕድን ለማዕከላዊ ገበያ ከሚያቀርቡ የሀገሪቱ አካባቢዎች መካከል አንዱ ሆኗል። በክልሉ ገና በጥናት ያልተለዩ ብዙ ሀብቶች አሉ። ኦፓልና ሌሎች ማዕድናትም በክልሉ ይገኛሉ ተብሎ ይገመታል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የተትረፈረፈ የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት ቢሆንም በመሰረተ ልማት አቅርቦት፣ በተለይም በመንገድ ዝርጋታ ረገድ ከፍተኛ ችግሮች ያሉበት ክልል መሆኑን ከክልሉ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። በክልሉ ግንባታቸው ያልተጠናቀቁ እንዲሁም በአፈፃፀም ድክመት ምክንያት ውላቸው እንዲቋረጥ የተደረጉ ፕሮጀክቶች አሉ። መንገዶችን በፍጥነት አጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት በማድረግ ረገድም ከፍተኛ ውስንነቶች አሉ።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመሰረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ፋጂዮ ሳፒ ስለክልሉ የመንገድ መሰረተ ልማት የሥራ እንቅስቃሴ ከ‹‹አዲስ ዘመን›› ጋዜጣ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
የክልሉ የመንገድ ሽፋንና ግንባታ
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በመሰረተ ልማት አቅርቦት ወደኋላ ከቀሩ አካባቢዎች መካከል ይጠቀሳል። በተለይ የመንገድ መሰረተ ልማት ችግሮች በስፋት ይስተዋሉበታል። ለአብነት ያህል ተርጫ አካባቢ የሚከናወኑ ሦስት የመንገድ ፕሮጀክቶች አልተጠናቀቁም። ከሸሽንዳ ወደ ቴፒ እንዲሁም ከቴፒ ወደ ማሻ ጎሬ የሚወስዱት መንገዶችም አፈፃፀማቸው ደካማ ነው። በቤንች ሸኮ እና በከፋ ዞኖች ውስጥ እየተገነቡ ከነበሩ መንገዶች መካከል በአፈፃፀም ድክመት ምክንያት ውላቸው እንዲቋረጥ የተደረጉ ፕሮጀክቶች አሉ። መንገዶችን በፍጥነት አጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ውስንነቶች ይታያሉ።
ይህን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት ግንባታቸው በፌዴራል መንግሥት እየተከናወኑ የሚገኙ የመንገድ ፕሮጀክቶች አሉ። እነዚህ የአስፋልት መንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች ከነጉድለታቸውም ቢሆን በጥሩ አፈፃፀም ላይ ይገኛሉ። ከእነዚህም መካከል በምዕራብ ኦሞ ዞን የሚከናወነው የማጂ መንገድ ግንባታ በተሻለ አፈጻጸም ላይ ይገኛል።
በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች የሰላም መደፍረስ የነበረ ቢሆንም፣ ሕዝቡ ከፍተኛ የመሰረተ ልማት ፍላጎት ያለው በመሆኑ የፀጥታ ችግሮችን እየተከላከለና ተቋራጮችን እየጠበቀ በአካባቢዎቹ የሚከናወኑ የመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታዎች እንዳይቋረጡና ግንባታቸውም በተቻለ መጠን በፍጥነት እንዲከናወን ከፍተኛ እገዛ እያደረገ ይገኛል።
ክልሉ ሰፊ የመንገድ መሰረተ ልማት ችግሮች (በተለይም የመንገዶችና የድልድዮች ችግሮች) እንዳሉ በመገንዘብና ለችግሮቹ ምንጭ የሆኑ የመልካም አስተዳደር ድክመቶችን በመለየት የተጀመሩ ፕሮጀክቶች እንዲጠናቀቁ ጥረት እየተደረገ ነው።
በ‹‹ሁሉን አቀፍ የገጠር መንገድ ተደራሽነት መርሃ ግብር›› (Universal Rural Road Access Program (URRAP)] ተጀምረው የተቋረጡ የመንገድ ፕሮጀክቶችን አቅም በፈቀደ መጠን ግንባታቸውን ለማስቀጠል እየተሰራ ነው። ለአብነት ያህል በዚህ ዓመት የመንገድ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ ነው። ከመንገዶቹ በተጨማሪ የአራት ድልድዮች ግንባታም እየተጠናቀቀ ይገኛል። በክልሉ መንገዶች ባለስልጣን የሚገነቡ ድልድዮችም አሉ። ባለፈው ዓመት አምስት ድልድዮች ግንባታቸው ተጠናቆ ለአገልግሎት በቅተዋል።
የትምህርትና የጤና ዘርፍ መሰረተ ልማት ስራዎች ጥሩ አፈፃፀም ቢኖራቸውም፣ ቀላል የማይባሉ የአፈፃፀም መጓተቶች ይስተዋሉባቸዋል። የግንባታ ግብዓቶች (ሲሚንቶ፣ ብረት…) ዋጋ መናር አንዳንድ የትምህርትና የጤና ዘርፍ መሰረተ ልማት ግንባታዎች እንዲቋረጡ ምክንያት ሆኗል። እነዚህ ችግሮች ቢኖሩም የክልሉን ሕዝብና መንግሥት አቅም በመጠቀም እንዲጠናቀቁ የተደረጉ የትምህርትና የጤና ተቋማት ፕሮጀክቶች አሉ። ከተቋራጮች ጋር በመነጋገር ግንባታቸው የተቋረጡት ፕሮጀክቶች እንዲጠናቀቁ ይደረጋል።
የተቋራጮች አቅም
የመንገድ ግንባታዎችን የሚያከናውኑት አብዛኞቹ ተቋራጮች የውጭ አገራት ድርጅቶች ናቸው። ግንባታዎቹ የጥራት ጉድለቶች ይታዩባቸዋል፤ በሚፈለገው ፍጥነትም አይሰሩም። እንዲህ አድርገው ውላቸው እንዲቋረጥ ይፈልጋሉ፤ውላቸው ሲቋረጥ ግንባታውን ትተው ይሄዳሉ። የግንባታ ውላቸው ከተቋረጠ ፕሮጀክቶች መካከል ብዙዎቹ በውጭ ተቋራጮች የተያዙ ናቸው። የአገር ውስጥ ተቋራጮች የተሻለ አፈፃፀም አላቸው። የአገር ውስጥ ተቋራጮች ችግሮችን ተቋቁመው የመስራት ልምድ አላቸው። ጥሩ አፈፃፀም ያለውና በምዕራብ ኦሞ ዞን፣ ማጂ አካባቢ እየተገነባ የሚገኘው መንገድ በአገር ውስጥ ተቋራጮች የተያዘ ነው። ይህ የሚያመለክተው በግንባታው ዘርፍ ያሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የአገር ውስጥ ተቋራጮችን አቅም ማሳደግ አስፈላጊ እንደሆነ ነው። አቶ ፋጂዮ ‹‹የውጭ ተቋራጮች አፈጻጸማቸው ደካማ ነው። ስለሆነም የአገር ውስጥ ተቋራጮችን አቅም ካላሳደግን የፕሮጀክቶች ግንባታ መጓተት ችግር ተባብሶ መቀጠሉ አይቀርም›› ይላሉ።
የበጀት እጥረት
የበጀት እጥረትም አሳሳቢ ችግር ነው። የሰሜኑ ጦርነት እንዲሁም ሌሎች አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ችግሮች በአገሪቱ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ በማሳደራቸው ለፕሮጀክቶች ግንባታ በቂ ገንዘብ ያለማግኘት ችግር አለ። በክልሉ ለመንገድ የሚመደበው በጀት አነስተኛ ነው። ባለፈው ዓመት ለመንገዶችና ድልድዮች ግንባታ የተመደበው በጀት 53 ሚሊዮን ብር ነበር፤አሁን ባለው አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታ በ53 ሚሊዮን ብር ጥራት ያለው መንገድ መገንባት አይቻልም። ለመንገድ የሚመደበው በጀት አነስተኛ በመሆኑ ያሉንን ትንንሽ ማሽኖችን በመጠገንና በማስተካከል ብዙ የመንገድ ጥገና ሥራዎች እየተሰሩ ናቸው።
የኅብረተሰብ/ባለሀብቶች ተሳትፎ
የመንግሥት አቅም ውስን በመሆኑ፣ ኅብረተሰቡን ማሳተፍ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ የክልሉ ሕዝብ በመሰረተ ልማት ግንባታዎች እንዲሳተፍ እየተደረገ ነው። በዚህም ሕዝቡ ገንዘቡንና ጉልበቱን በመሰረተ ልማት ግንባታና ማስፋፊያ ተግባራት ላይ እያዋለ ይገኛል። ለአብነት ያህል የቤንች ሸኮ ዞን ሕዝብ በራሱ ተነሳሽነት ገንዘቡንና ጉልበቱን አስተባብሮ ሦስት ድልድዮችን ሰርቶ በማስመረቅ ለአገልግሎት አብቅቷል። ይህ ተግባር ኅብረተሰቡ ተነሳሽነት የሚፈጥርለትና የሚያስተባብረው አካል ካገኘ ትልልቅ የልማት ተግባራትን ማከናወን እንደሚችል አሳይቷል።
‹‹አሁን ያለው የመንግሥት ሀብት ውስን ነው፤ የመንግሥትን ሀብት ብቻ ከምንጠብቅ አንዳንድ ሥራዎችን በራሳችን አቅም መስራት እንችላለን›› በሚል እሳቤ መነሻነት፣ ይህ ተሞክሮ ወደ ሌሎች የክልሉ ዞኖች እንዲሰፋና እንዲተገበር እየተደረገ ይገኛል። የከፋ ዞን ሕዝብ ከ35 ሚሊዮን ብር በላይ በማሰባሰብ ያከናወናቸው የመንገድና የድልድይ ስራዎች የዚህ ተሞክሮ ማሳያዎች ናቸው። ሌሎች ክልሎችም ውስን የሆነውን የመንግሥትን በጀት ከመጠበቅ ይልቅ በተቻለ መጠን የሕዝብ ንቅናቄ በመፍጠር አንዳንድ የልማት ፕሮጀክቶችን ግንባታ ቢያከናውኑ የኅብረተሰቡ ተጠቃሚነት ያድጋል።
ክልሉ ለኢንቨስትመንት ከፍተኛ አቅም ያለው በመሆኑ በክልሉ በኢንቨስትመንት ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ባለሀብቶች በክልሉ የመሰረተ ልማት ዘርፎች ግንባታ ላይ የራሳቸውን አስተዋፅዖ እንዲያበረክቱ ይጠበቃል። በዚህ ረገድ አንዳንድ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶቻቸው በሚገኙባቸው አካባቢዎች የሚያከናውኗቸው ተግባራት አሉ። ኅብረተሰቡ በሚሳተፍባቸው የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ላይ የራሳቸውን ተሳትፎ የሚያደርጉ ባለሀብቶችም አሉ።
ክልሉ ካለው አቅም አንፃር ከዚህ የበለጠ ሥራ ስለሚጠበቅ በቀጣይ ይህን አሰራር በተደራጀ መልኩ መምራት ያስፈልጋል። ከወረዳ ጀምሮ እስከ ክልል ድረስ ባለሀብቶችን በማስተባበር በመሰረተ ልማት ግንባታ ተግባራት ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ይደረጋል። በክልሉ በርካታ ባለሀብቶች የቡናና የሰብል ልማትን ጨምሮ በሌሎች ዘርፎችም በኢንቨስትመንት ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ። ባለሀብቶቹ ክልሉን በመንገድ ብቻም ሳይሆን በሌሎችም ዘርፎች ተጠቃሚ ማድረግ ይኖርባቸዋል። በቀጣይ ክልሉ ብዙ ባለሀብቶች በሁሉም ዘርፎች በኢንቨስትመንት ላይ እንዲሰማሩ እና በየቦታው በሚገነቡ የመንገድና ድልድዮች ግንባታ ላይ ከእስካሁኑ የበለጠ ተሳትፎ እንዲያደርጉ የሚያስችሉ አሰራሮችን ያመቻቻል።
የዘርፉ ተስፋዎችና ቀጣይ እቅዶች
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ከፍተኛ የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት የሆነ አካባቢ ነው። ይህ ሀብት በሚገባ ቢታወቅና በመሰረተ ልማት ቢተሳሰር ኢትዮጵያን ሊያሻግር የሚችል አቅም አለው። ቀደም ባሉት ስርዓቶች እንኳን የሀገሪቱ መሪ ይቅርና ሚኒስትሮች አካባቢውን በሚገባ ጎብኝተውት አያውቁም። አሁን ግን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ ከፍተኛ አመራሮች አካባቢውን በመጎብኘት በአካባቢው ያለውን የመሰረተ ልማት ችግር ተመልክተዋል፤የክልሉን አቅም ተገንዝበዋል።
ይህን ተከትሎ በክልሉ የአውሮፕላን ማረፊያን ጨምሮ ሌሎች የመሰረተ ልማት ግንባታዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ። ይህ ደግሞ ለክልሉ የመሰረተ ልማት ግንባታም ሆነ አጠቃላይ ልማት ተስፋ ሰጪ ጅምር ነው። ግንባታቸው የተቋረጡ የመንገድ ፕሮጀክቶችን በዝርዝር ለኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በማሳወቅ የአስተዳደሩ የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ፕሮጀክቶቹን ጎብኝተዋል። በአካባቢው ያለውን ሀብትና አቅም ለይተው ማወቃቸው በቀጣይ የክልሉን የመሰረተ ልማት ችግሮች ለመፍታት ለሚደረገው ጥረት መደላድል ይፈጥራል። አቶ ፋጂዮ ‹‹ከፍተኛ ትኩረት ከሚፈልጉ የክልሉ ችግሮች መካከል አንዱ የመንገድ መሰረተ ልማት አቅርቦት እጥረት በመሆኑ አቅምን አስተባብሮ በመጠቀም የምንችለውን ሁሉ ለማድረግ የሚያስችል የአሰራር አቅጣጫ አዘጋጅተናል›› ብለዋል።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ሰኔ 17/2015