የዛሬው ኑሮዋ ከተማ ላይ ቢያቆማትም የማንነቷ ምንጭ የሚቀደው ከገጠሩ ክፍል ነው፡፡ ትውልድና ዕድገቷ ሰሜን ጎንደር ዞን ጭልጋ ወረዳ ልዩ ስሙ ‹‹ኩሻይና›› ከተባለ ስፍራ ነው፡፡ የአርሶአደር ልጅ ነች። እንደማንኛወም የገጠር ጉብል በአካባቢው ወግና ባህል አድጋለች፡፡
አጸደ ሰማው ለወላጆቿ በወጉ ስትታዘዝ፣ አድጋለች። የገጠር ልጅ ሁሌም የተባለውን ሊሰራ፣ ሊታዘዝ ግድ ነው፡፡ አጸደ ሰማውም ወላጆቿ ለሚሏት ሁሉ ጉልበቷን ሳትሰስት ስታገለግል ቆይታለች፡፡
ልጅነቷ እንደእኩዮቿ ከብት በማገድ ብቻ አላለፈም። ቤተሰቦቿ ባይማሩም ሴት ናት ብለው አልጨከኑባትም፡፡ ዕድሜዋ ሲደርስ ደብተር አስይዘው ትምህርትቤት ላኳት። እሷም ብትሆን አላሳፈረቻቸውም። ዓላማዋን ሳትዘነጋ በርትታ ተማረች፡፡
አጸደ መንገዷን አልሳተችም፡፡ ነገን ከተሻለ ዓለም ለመድረስ ለትምህርቷ ትኩረት ሰጠች፡፡ በዚህ ሁሉ ጥረት ከጎኗ ያልራቁት ወላጆች ያሻትን እየሰጡ፣ የጎደለውን እያሟሉ ከፍላጎቷ አደረሷት፡፡
የአጸደ ሀሳብ በህክምና ሙያ ጠንክራ መዝለቅ ነው፡፡ የእሷ ዓዕምሮ ሁሌም አርቆ ያስባል፡፡ ወገኖቿን በጤናው ዘርፍ ማገዝ፣ መደገፍን ትሻለች፡፡ ይህ ይሆን ዘንድ ወላጆቿ ያቅማቸውን አድርገዋል፡፡ እስካሁን ከትምህርት ሳያግዷት በወጉ ተምራለች፣ በነጻነት ተራምዳለች፡፡ ከእንግዲህ ምኞት ፍላጎቷን መሙላት የእሷ ድርሻ ይሆናል፡፡
ልፋትን በውጤት…
ያሰበችው ከመሆን አልቀረም፡፡ ትምህርቷን አጠናቃ ኮሌጅ ለመግባት ተዘጋጀች፡፡ የመረጠችው የትምህርት ዘርፍ የፋርማሲስት ሙያን ነበር፡፡ ይህን ዓላማ ከግብ ለማድረስ ከትውልድ አገሯ ርቃ ቤኒሻንጉል ክልል ተገኝታለች፡፡
አጸደ የያዘችውን ትምህርት በርትታ ቀጠለች፡፡ የልጅነት ህልሟ ዕውን ሲሆን በሙያዋ መስራትን ትሻለች፡፡ ሳይማሩ ያስተማሯትን ቤተሰቦች መደገፍ፣ ማመስገን የቀን ተሌት ህልሟ ነው፡፡ ተመልሳ አገሯ ስትገባ ለታናናሾቿ ምሳሌ መሆን እንዳለባት ታውቃለች።
ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ሌሎች የአካባቢው ልጆች በእሷ መንገድ ቢያልፉ ደስታዋ ነው፡፡ ሁሌም ለቤተሰቦቿ አክብሮት አላት፡፡ እነሱ እንደቀድሞው ወግ ባህል በሴትነቷ ‹‹ቤት ትዋል፣ ትዳር ትያዝ›› ብለው አላገዷትም፡፡ በማጀት ስራ፣ ልጆች በማሳደግ ግዴታ ስር አልጣሏትም፡፡ ለነጻነቷ ነፃነት ሰጥተው፣ ለህይወት ምርጫዋ አብቅተዋታል፡፡
አጸደ በቤኒሻንጉል ክልል የትምህርት ቆይታዋ ከቤተሰብ ተነጥሎ መኖርን አወቀች፡፡ ይህ ጊዜ ራስን ለመቻል፣ ፈተናዎችን ለመቋቋም ዕድል ሰጣት፡፡ የዩኒቨርሲቲ ትምህርት ብዙ ይፈልጋል፡፡ ለዕለት ወጪ፣ ለኑሮ መደጎሚያ ለፍላጎት መሙያ ገንዘብ ማግኘትን ይሻል፡፡ እሷን ጨምሮ በርካታ ተማሪዎች ድጋፍ የሚያገኙት ከወላጆቻቸው እጅ ነው፡፡
አጸደ ለትምህርት ቆይታዋ ብዙ እንደሚጎድላት ታውቃለች፡፡ እስከዛሬ ፍላጎቷን ለመሙላት ቤተሰቦቿ ሲደግፏት ቆይተዋል፡፡ አንዳዴ ግን እነሱን ብቻ ‹‹አምጡ›› እያሉ ማስቸገሩ ይከብዳታል፡፡ አሳድገው፣ አስተምረው ቁምነገር ካደረሷት ወላጆች ጫንቃ ዛሬም ድረስ ያለመውረዷ ያስጨንቃታል፡፡
ራስን ለመቻል…
አሁን ለቆመችበት መንገድ የወላጆቿ እጆች ሰፊ ነበሩ፡፡ እሷ ስትማር የበታች እህት ወንድሞቿ ተከትለዋታል፡፡ እስካሁን በቤት ሳለች የሚያሻትን በእኩል ተጋርታ ከእነሱ መስላ አድራለች፡፡ አሁን ደግሞ ከቤት ስትርቅ የግል ፍላጎቷ ጨምሯል፡፡ ከታናናሾቿ በበለጠ ገንዘብና ቁስ ያስፈልጋታል፡፡
አጸደ ይህ እውነት ሁሌም እያሳሰባት ትጨነቃለች፡፡ አሁን ከቤት ውጭ ሆና የእህት ወንድሞቿን ኢኮኖሚ መሻማት አትፈልግም፡፡ ይህ ጉዳይ ሁሌም ወደ ዓይምሮዋ ሲደርስ ‹‹አይሆንም፣ አይደረግም›› የሚል ቃልን ሹክ ይላታል፡፡ ይህኔ በይሉኝታ ተከባ በምንይሉኝ ስሜት ስትተክዝ ትውላለች፡፡
እንዲህ ባሰበች ጊዜ ዓይምሮዋ ለውሳኔ ይፈጥናል። እጅ እግሮቿ ለስራ ይሰላሉ፡፡ ‹‹እኔ እኮ! ተማሪ ነኝ›› የሚለውን ሀሳብ ትተውና ራሷን ለጉልበት ስራ ታዘጋጃለች። ከምትማርበት ትርቃለች፡፡ ዝቅ ብላ በየሰው ቤት ልብስ ስታጥብ፣ በጉልበት ስራ ስትውል መፍራት ማፈርን አታውቅም፡፡
እንዲህ ካልደፈረች ከሰው ጫንቃ አትወርድም። እንዲህ ካልወሰነች ማጣት መንጣቷን አትቅርፍም። በስራ ውላ የድካሟን ዋጋ ስትወስድ የወላጆቿን ዕዳ እንደከፈለች ይሰማታል፡፡ የእህት ወንድሞቿን ድርሻ ያለመቁረሷ ይታያታል፡፡ ይህኔ ዓይምሮዋ በእርካታ ይመላል፤ የነገ ዕቅድ ውጥኗን በነፃነት እያነሳች ትጥላለች፡
አጸደ ውስጧ ለሰዎች ያዝናል፡፡ የሌሎች መቸገር ማጣት ያሳስባታል፡፡ የመረጠችው የትምህርት ዘርፍ በአንድም በሌላም ከሰብአዊነት ጥግ የሚያደርሳት ነው። ሙያዋን ተጠቅማ ከምትሰጠው መልካምነት ባለፈ ከእሷ ድጋፍን ከሚሹ ወገኖች ጎን ብትቆም ትወዳለች። ይህን ስታስብ የልቧ ሁሉ ይከወናል፡፡ ያቀደችው የሞላ የወጠነችው የተሳካ ይመስላታል፡፡
የቤኒሻንጉሏ ተማሪ አጸደ ትምህርቷን ባሰበችው ጊዜ አጠናቀቀች፡፡ ወደ ቤተሰቦቿ ስትመለስ የህይወቷን ዕቅዶች የማሳካት መንገዷን ጀምራው ነበር፡፡ አሁን በተመረቀችበት ሙያ አካባቢዋን ማገዝ፣ ቤተሰቦቿን መደገፍ ይኖርባታል።
ውሎ አድሮ የወጣቷ ዕቅድ እንደታሰበው ተሳካ፡፡ ለተመረቀችበት ሙያ የሚመጥን ስራ አ ግኝታ ደ ሞዝ መ ቁጠር ጀመረች። አጸደ ዛሬን ለቆመችበት ማንነት ያበቋትን ወላጆች ውለታ አልዘነጋችም፡፡ የልፋት ዋጋቸውን በስራ መንዝራ በተግባር አስመስክራለች፡፡
አጸደ አሁን በሙያዋ ደሞዝ የሚከፈላት ሰራተኛ ሆናለች፡፡ ይህ ውጤት የእሷ ብቻ ሳይሆን የቤተሰቦቿ ጭምር ሆኗል፡፡ ዛሬ ላይ አንገቷን የሚችል ራስ አላት። እንደ ተማሪነት ዘመኗ ከሰው እጅ አትጠብቅም። እንደትናንት ህይወቷ ‹‹ስጡኝ.ለግሱኝ›› ማለትን አትሞክርም፡፡
አጋጣሚው…
ከቀናት በአንዱ አጸደ አክስቷን ለመጠየቅ ወደ ባህር ዳር ተጓዘች፡፡ ይህ አጋጣሚ ግን ዘመድ በመጠየቅ ብቻ አልተቋጨም፡፡ በአካባቢው መዘዋወሯ ከእሷ ውስጣዊ ማንነት ጋር ለመገናኛት ምክንያትን ፈጠረ።
በዚህ ቀን እግሮቿ ወደ አንድ ስፍራ አደረሷት፡፡ በቦታው በተገኘች ጊዜ የሰማችው እውነት ከተለመደው ወሬና ጨዋታ ተለየባት፡፡ አጸደ አብሯት የኖረው የሰብአዊነት ስሜት ውስጧን ቢፈትነው ጆሮዋን ሰጥታ በትኩረት አዳመጠች፡፡ አዎ! እየሰማች ያለችው ሀቅ ከእሷ ማንነት ጋር በቀጥታ ይዛመዳል፡፡ ‹‹በጦርነት የተጎዱ ወገኖችን መልሶ ማቋቋምና ማገዝ፡፡ ››
ከጥቂት ዓመታት በፊት በአጸደ የትውልድ አካባቢ ጦርነት ሲካሄድ ቆይቷል፡፡ በዚህ ጦርነት በርካታ ወገኖች ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ ቤት ንብረታቸው ወድሞ ለመፈናቀል ተዳርገዋል፡፡ ከነዚህ መሀል በርካቶችን በስራቸው ያስተዳድሩ የነበሩ ባለሀብቶች ጭምር ይገኙበታል፡፡
አጸደ እነዚህን ወገኖች ጨምሮ በርካታ የአካባቢው ነዋሪ በጦርነት ስለመጎዳቱ የዓይን ምስክር ነች። የመለያየት፣ ያለመግባባትን ስር የሰደደ ችግር አሳምራ ታውቃዋለች፡፡ በዚህ መንገድ ባለፈችበት አጋጣሚም ሰው መሆንዋን እስክትጠላው ተሰምቷት ያውቃል፡፡
በጦርነት እሳት የተማገዱ በርካቶች የአሁን ኑሮ የወደፊት ተስፋ ይሉትን እውነት ይነጠቃሉ፡፡ ህልማቸው ይመክናል፣ ዓላማቸው ይነጥፋል፡፡ እነሱን ከወደቁበት አንስቶ በሁለት እግራቸው ለማቆም ደግሞ የሌሎች እጆች እገዛ ሊኖር የግድ ነው፡፡
አጸደ የባህርዳር ቆይታዋ ያገናኛት ከእንዲህ አይነቱ ሀቅ ጋር ነበር፡፡ መገኛውን አዲስ አበባ ያደረገ ‹‹ወገን ለወገን›› በሚል ስያሜ የተደረጃ ማህበር በእንቅስቃሴ ላይ መሆኑን ሰምታለች፡፡ ደጋግማ ሙሉ መረጃውን ጠየቀች። በቂ ምላሽ አላጣችም፡፡ የማህበሩ ዓላማ በችግር ላይ የሚገኙ ወገኖችን ማገዝና ማቋቋም ላይ ያተኩራል፡፡
አጸደ በአካባቢያዋ የጦርነት ሀሩር ያረፈባቸውን ወገኖች አሰበች፡፡ አብዛኞቹ ከቤት ከቀያቸው ተፈናቅለው ከከፋ ችግር ወድቀዋል፡፡ በዕድሜያቸው መማር ያለባቸው ህጻናት፣ በቤታቸው መኖር፣ መከበር የሚገባቸው አረጋውያንና፣ እናቶች ካላሰቡት መንገድ ውለዋል፡ ፡ እሷ በእነሱ ህመም ስትታመም፣ በሀዘናቸው ስታዝን ቆይታለች፡፡
አጸደ በመቋቋም ላይ ስላለው ማህበር መለስ ብላ አሰበች፡፡ ታላቅ ዕቅዱ ዕውን ይሆን ዘንድ ከጎኑ የቆሙት ጊዜ ጉልበት፣ ዕውቀትና ገንዘባቸውን የሚሰጡ በጎ ፈቃደኛ ወገኖች ናቸው፡፡ አጸደ ይህን ባወቀች ጊዜ ራሷን ለሰብአዊ አገልግሎት አሳልፋ ለመስጠት ወሰነች። አብሯት የኖረው ሰው የመርዳት ማንነቷ ተግባር ላይ የሚውልበት ጊዜው አሁን መሆኑን አመነች፡፡
ቆራጥ ውሳኔ…
እንዲህ መሆኑ በገባት ጊዜ ከማንም ሳትመክር በራሷ ውሳኔ አሳለፈች፡፡ ተምራ ከተመረቀች በኋላ በአንድ የግል ድርጅት ተቀጥራ በቂ ደሞዝ እየተከፈላት ነው፡፡ አሁን ከራሷ አልፋ ለሌሎች የምተተርፍበት ጊዜ ላይ ነች፡፡ እንዲያም ቢሆን የእሷ የህይወት ሙላት ብቻ የሌሎችን ጎድሎ እንደማይደፍን ከገባት ቆይቷል። ስራዋን ትታ፣ ቤተሰቦቿን ርቃ የሚጠበቅባትን ግዴታ ልትወጣ ቆርጣለች፡፡
አሁን የአጸደ ውሳኔ በሌሎች ምክር የሚታገዝ፣ የሚደገፍ አልሆነም፡፡ ለሚቀርቧት ሀሳቧን ብታማክር ማንም ‹‹ስራሽን ትተሸ ለበጎፈቃደኝነት ቁሚ›› እንደማይላት ታውቃለች፡፡ ቤተሰቦቿ ከእሷ ብዙ እንደሚሹ አልጠፋትም። አሳድገው፣ አስተምረው ቁምነገር አድርሰዋታል፡፡ ይህ ሁሉ እውነት ግን ከምታስበው ሀያል ጉዳይ በልጦ አልታያትም፡፡
ከጀመረች ጥቂት ጊዚያት በቆጠረችበት ስራ ያስቀመጠችው ብዙ የማይባል ገንዘብ አለ፡፡ ከእንግዲህ ካሰበችው አድርሶ የልቧን ሊሞላላት የሚችለው ቀጭን መስመር እሱ ብቻ ይሆናል፡፡ እቅዷን ለማሳካት የማትሆነው የለም፡፡ ይህን ካደረገች፣ ዓይምሮዋ ያርፋል፣ ውስጠቷ ይሞላል፡፡
አጸደ የልቧን እቅድ ከመከወን አልታቀበችም፡ ፡ እንዳሰበችው ሆኖ አንድ ቀን ስራዋን አቆመች፡፡ ጓዟን ሸክፋ በእጇ ያለውን ገንዘብ ቆጠረች፡፡ ካሰበችው ዓላማ ያደርሳታል፡፡ ቆራጥ ሀሳቧ ከበጎ ፈቃደኛው ልቧ ተጣምሮ ረጅሙን መንገድ ተያያዘችው፡፡ የት እንደምትሄድ አልጠፋትም፡፡ ተጓዥ እግሯ ከአንድ ግቢ አድርሶ አንድ ዓይነት ዓላማ ካላቸው ነፍሶች ጋር አገናኛት፡፡
ህይወት በአዲስ አበባ …
አጸደና አዲስ አበባ ከተገናኙ ጥቂት ጊዚያት ተቆጥረዋል፡፡ በዚህ ስፍራ ምቾትና ለራስ ማደር ይሉት ዓለም የለም፡፡ እሷን ጨምሮ ሌሎች ለማህበሩ ህልውና የሚታገሉ ወገኖች የአቅማቸውን ሁሉ ያደርጋሉ፡፡ እንደ ትናንቱ ለሰሩበት፣ ላገለገሉበት ወር ጠብቆ ደሞዝ መጠየቅ አይታሰብም፡፡ ሁሉም የእጁን እያዋጣ ለዕለት ኑሮው፣ ለወደፊት ዓላማው ይታገላል፡፡
አጸደ ‹‹ወገን ለወገኑ ›› የተባለው ማህበር በእግሩ እስኪቆም የሚጠበቅባትን ታደርጋለች፡፡ በሀሳብ በበጉልበት ታግዛለች፡፡ ወደፊት ለሚኖረው ሰብአዊ እገዛ መለመን፣ መጠየቅ ቢኖርባት ወደኋላ አትልም፡፡ እራሷን ለሰብአዊ አገልግሎቶች አዘጋጅታለችና ስለክብሯ አትጨነቅም፡፡
አንዳንዴ አጸደ ስለቤተሰቦቿ ወሬ ትሰማለች፡፡ ሁሉም ስራዋን ትታ ወንዝ አቋርጣ በሄደችበት ጉዳይ አመኔታ የላቸውም፡፡ ከእነሱ የራቀችው ላልተገባ ዓላማ እንደሆነ ያስባሉ፡፡ እነሱ እንዲህ በማሰባቸው አዝናባቸው አታውቅም፡፡ አንድቀን ርቃ የመጣችበትን ዓላማ ሲረዱ እንደሚደሰቱ እንደሚያመሰግኗት ታውቃለች፡፡
አጸደ ያሰበችውን ለማሳካት ዛሬን በቆመችበት መንገድ ብቻ መቀጠል አትሻም፡፡ ሁኔታዎች ሲመቻቹ ትምህርቷን መቀጠል፣ በሙያዋም ማገልገል ትፈልጋለች፡፡ እንዲህ በሆነ ጊዜ የምታገኘውን ደሞዝ ለሰብአዊ አገልግሎት የማዋል ዓላማዋ እንደተጠበቀ ይቀጥላል፡፡
እንዲህም ይኖራል…
የአጸደ የህይወት መንገድ ከብዙዎቻን ልማዳዊ አቅጣጫ ይለያል፡፡ እሷ ከራስ ጥቅም ይልቅ ለሌሎች የመኖር እውነትን መተግበር ይዛለች፡፡ ይህች ወጣት ህይወትን እየኖረች ያለችው ከራስ ብቻ በመጀመር አልሆነም፡፡ የሌሎች ህመምና ስብራት አስቀድሞ ይሰማታል፡፡ የብዙዎች ለቅሶና ሀዘንም ከልቧ ደርሶ ይፈሳል፡፡
ይህ ስሜት በውስጧ መዝለቁ ማንነቷን ለሌሎች መኖር አሳልፋ እንድትሰጥ አስገድዷል፡፡ ለሰብአዊነት፣ ለበጎነት ዓላማ ማደሯም ከኑሮዋ አንዳች አላጎደለም፡፡ ዛሬም፣ ነገም ስለሰዎች መልካም መሆንን ታስባለች፡፡
እሷ በነዚህ ነፍሶች ፍስሀ ፈጽሞ ኪሳራ አያገኛትም። በየዕለቱ የሚኖራት ትርፍም የመንፈስ እርካታን ያጎናጽፋታል፡፡ ሁሌም የራሷን ዓለም በእፎይታ እንድትገነባና ‹‹ሰው›› ለሚለው ሰብአዊ ፍጡር እንዲህ ሆና እንድትኖር ታድላለችና፡፡
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ሰኔ 17/2015