ወጣት ትንሳኤ ዓለማየሁ ይባላል። ውልደቱ በመዲናችን አዲስ አበባ ነው። ዕድገቱ ደግሞ በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች ሲሆን፤ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን ጄኔሬሽን 2000 በተባለ ትምህርት ቤት ተከታትሏል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ አቡነ ጎርጎርዮስ ተምሯል። በትምህርቱ ጎበዝ ከሚባሉ ተማሪዎች መካከል የነበረው ትንሳኤ፤ በ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ጥሩ ውጤት በማስመዝገብ ለከፍተኛ ትምህርት መቀሌ ዩኒቨርስቲን ተቀላቅሏል።
ከልጅነቱ ጀምሮ ለሕዋ ሳይንስ ልዩ ፍቅር ስለነበረው ለዚህ ይረዳው ዘንድ ለዘርፉ ይቀርባል ያለውን የሜካኒካል ምሕንድስና ትምህርት ክፍል መርጦ በመቀላቀል ትምህርቱን እስከ አምስተኛ ዓመት መጨረሻ ድረስ ተከታትሏል። ለተግባር ልምምድ አዲስ አበባ በነበረበት ወቅት በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል አጋጥሞ በነበረው ጦርነት ምክንያት ወደ መቀሌ ተመልሶ ትምህርቱን ማጠናቀቅ አልቻለም፤ በዚህም የመቀሌ ዩኒቨርስቲ ቆይታው እስከ መጨረሻው አልዘለቀም።
የትምህርት ሚኒስቴር በትግራይ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርታቸው ሲከታተሉ የነበሩ ተማሪዎችን ወደ ተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች በማስቀየር ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ሲያደርግ ወጣት ትንሳኤ ሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ደረሰው። በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ የቀሩ ኮርሶችን፣ በተግባር ልምምድ የሠራቸውን ሥራዎች እና የመመረቂያ ጽሑፍ በማቅረብ ማጠናቀቅ ቻለ። ዩኒቨርሲቲው በወቅቱ ስለእነርሱ መረጃ ስላልነበረው ማስመረቅ እንደማይችል በመግለፅ፤ የሁለተኛ ደረጃ ሰርተፍኬት ብቻ ሰጥቶ ሸኘው።
አሁንም ድረስ የትምህርቱ ጉዳይ በዚሁ መንገድ ዕልባት ሳያገኝ ቢቆይም፤ አሁን ወደ ቀድሞ ሰላም መመለስ በመቻሉ የትምህርቱ ጉዳይ መቋጫ ያገኛል የሚል እምነት እንዳለው ወጣት ትንሳኤ ይናገራል።
በወቅቱ እርሱ በግሉ በውጭ ሀገር ትምህርቱን ለመከታተል የተለያዩ የትምህርት ዕድሎችን ይሞክር ነበር። ሙከራው ተሳክቶለት በውጭ የሚሰጡ ኮርሶችን ለመማር ከሀገር ውጭ በመጓዝ ትምህርቱን ተከታትሏል።
ወጣት ትንሳኤ ከአውሮፓውያኑ 2012 ጀምሮ የኢትዮጵያ የጠፈር ሳይንስ ማኅበረሰብ አባል ሲሆን፤ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ቆይታውም በኢትዮጵያ የጠፈር ሳይንስ ማኅበረሰብ የመቀሌ ቅርንጫፍ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ሆኖ ሠርቷል። በተባበሩት መንግሥታት የሕዋ ሳይንስ ድጋፍ በሚደረግለት ስፔስ ጄኔሬሽን አድቫይዘሪ ካውንስል በተባለው እና ወጣቶችን የማስተሳሰር ሥራ በሚሠራው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ውስጥ ከአውሮፓውያኑ 2013 ዓ/ም ጀምሮ የኢትዮጵያ አስተባባሪ በመሆን ሠርቷል።
ከልጅነት ጊዜው ጀምሮ ለሕዋ ሳይንስ ምርምር እና ለምሕንድስና ሙያ ከፍተኛ ፍላጎት እንደነበረው የሚናገረው ወጣት ትንሳኤ፤ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ከነበረበት ጊዜ አንስቶ የኢትዮጵያ የሕዋ ሳይንስ ማኅበረሰብ አባል በመሆን ከመደበኛ ትምህርቱ በተጓዳኝ በንባብ ያገኘውን የኅዋ ሳይንስ ዕውቀት ለሌሎች ለማካፈል ሥልጠናዎችን ሲሰጥ ቆይቷል።
‹‹መሠረታዊ በሆኑ ነገሮች ላይ ብዙ የሚቀረን ነገር አለ›› ብሎ የሚናገረው ይኸው ወጣት አብዛኛዎቹ ሥራዎቹ በግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራሞች ላይ ያተኮሩ ነበሩ። ወጣት ትንሳኤ፤ በዚህም ምክንያት በአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ በዩኒቨርስቲ ተማሪዎች፣ በአጠቃላይ ሕዝቡ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን በስፋት ይሠራ እንደነበር ተነግሯል።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ጅማሮው አካባቢ ለዘርፉ ፍላጎቱ እየጨመረ እንደመጣ እና የታሪክ መጽሐፍትን፤ የብራና ጽሑፎችን ለመዳሰስ በሚሞክርበት ወቅት ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን ነገር በተወሰነ መልኩ ማየት እንደቻለ እና በባሕርይ ብዙ ያልተዳሰሱ ሐሳቦችን ማየት ስለሚወድ ትኩረቱን እንደሳበው ይናገራል። ነገር ግን በሕዋ ሳይንስ የበለጠ እንዲሳብ ያደረገው የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ በነበረበት ወቅት የፊዚክስ መምህሩ እንደሆኑ ወጣት ትንሳኤ ወደኋላ ተመልሶ ያስታውሳል።
የኢትዮጵያ ስም በታሪክ፣ በሕክምና እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች ሊነሳ ይችላል። በሕዋ ዘርፍ ግን ብቅ ማለት የተጀመረው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነው የሚለው ወጣት ትንሳኤ፤ የብራና መጽሐፍት ላይ የድሮ አባቶች በጊዜው በነበራቸው አረዳድ የሕዋ ሳይንስን የተረዱበት መንገድ ያስደንቀው እንደነበር እንዲሁም እርሱን ከሌሎች በዘርፉ ከተሰማሩ ግለሰቦች ለየት የሚያደርገው በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ የተነሳ ብቻ ሳይሆን የታሪክ ጥናት ወደ እዚህ ዘርፍ ያመጣው እንደሆነ ይገልፃል።
እ.ኤ.አ በ2019 ዓ.ም በአፍሪካ ደረጃ በየዓመቱ የሚዘጋጀውን ሦስተኛውን የአፍሪካ የሕዋ ሳይንስ ዐውደ ጥናት በአዲስ አበባ ከተማ እንዲዘጋጅ እንዳደረገ እና የእርሱን ተስፋ ሰጪ ሥራዎች የተመለከቱ አፍሪካ ኢን ስፔስ የተባለው ተቋም ባካሄደው የ2021 የአፍሪካ ወጣት ምርጥ የሕዋ ሳይንስ ተመራማሪዎች ምርጫ ዕጩ ሆኖ ቀርቦ ከበርካታ የአፍሪካ ሀገራት የተወከሉ ተወዳዳሪዎች በተሳተፉበት ውድድር ወጣት ትንሳኤ ከአፍሪካ 10 ምርጥ የሕዋ ሳይንስ ተመራማሪ ወጣቶች ዝርዝር ውስጥ መካተት ችሏል።
በወቅቱ እውቅናው ከዚህ ቀደም ለተሠሩ ሥራዎች ዋጋ ከመስጠቱ ባሻገር በዓለም አቀፍም ሆነ በሀገር አቀፍ ደረጃ ወደ ፊት ለሚሠራቸው ሥራዎች በር ከፋች በመሆኑ አስተዋፅዖው ትልቅ እንደነበር ይናገራል። በተጨማሪ አንድ ሰው ወደዚህ ዘርፍ ሲመጣ በብዛት በመጀመሪያ የሚጠየቀው በዚህ ዘርፍ ምን ሠርተሃል? ምን አይነት ልምድ አለህ? የሚል ነው። እንዲህ አይነት ዕውቅና ደግሞ የወደፊት እቅዶቹ ለማሳከት በር ከፋች ናቸው ብሎ እንደሚያስብ ወጣት ትንሳኤ ይነገራል።
በቱርክ ሀገር የአቪየሽን ቴክኖሎጂ ሥልጠናን የተከታተለው ትንሳኤ፤ የመቀሌ እና የቤልጅየሙ ቶማስ ሞር ዩኒቨርሲቲዎች በጋራ ባዘጋጁት ሙን ሹት ኢትዮጵያ የተባለ ልዩ የትምህርት መርሐ ግብር ተከታትሎ የድርብ ክብር ዲግሪ አግኝቷል። ለዘርፉ ተመራማሪዎች በሚሰጠው ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድጋፍ መርሐ ግብር እ.ኤ.አ 2021 ዓ.ም አሸናፊ ከሆኑ ከአምስት የሕዋ ሳይንስ ተመራማሪዎች ውስጥ ከአፍሪካ የመጀመሪያው መሆን ችሏል።
ታሪክና ጥንታዊ መጽሐፍትን ማንበብ ያዘወትር እንደነበር የሚነገርለት ወጣት ትንሳኤ፤ ተወልዶ ባደገባት አዲስ አበባ ከተማ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በተከታተለበት የአቡነ ጎርጎሪዮስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የግዕዝ ቋንቋ መማሩ ደግሞ ተጨማሪ ጥንታዊ መጽሐፍትን ለማገላበጥ ዕድል እንደሰጠው እና ከእነዚህ መጽሐፍት ያነበበው ጥንታዊ ታሪክ የሕዋ ሳይንስ ምርምር የበለፀጉ ሀገራት ብቻ ሳይሆን፤ ኢትዮጵያ ውስጥም ጥንታዊ መሠረት እንዳለው እንዲገነዘብ እንዳደረገው፤ ይህም በትምህርት ቤት ከሚያገኘው ዘመናዊ የሳይንስ ትምህርት ጋር ተደምሮ ወደ ሕዋ ሳይንስ ምርምር የበለጠ እንዲሳብ እንዳደረገው ተነግሯል።
ስድስተኛ ክፍል ተማሪ ሆኖ አቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤት ሲገባ፤ ግዕዝ መማር እንደጀመረ እና ትምህርት ቤቱ ውስጥ ስለሚሰጥ በዚያ ምክንያት ያነባቸው የነበሩ መጽሐፍት ከአማርኛ መጽሐፍት በተጨማሪ የግዕዝ እና የብራና መጽሐፍትን የማንበብ አቅምን እንደፈጠረለት ገልፆ፤ ካነበባቸው ጥንታዊ መጽሐፍት ውስጥ በተለይ አንዱ የበለጠ ለዘመናዊው የሕዋ ሳይንስ ቀረቤታ እንደነበረው ወጣት ትንሳኤ ያስታውሳል።
በተለይ አክሲማሮስ የሚባል አንድ መጽሐፍ ነበር የሚለው ትንሳኤ፤ በመሠረቱ መጽሐፉ ስለ ሥነ-ፍጥረት የሚያወራው ነበር። ነገር ግን እዛ ላይ ስለ ሥነ-ፍጥረት ሲያወራ ሕዋው እንዴት እንደተፈጠረ የሚያብራራበት መንገድ ከሳይንሱ ጋር በአገላለፅ ደረጃ ተመሳሳይነት ስለነበረው እና በተወሰነ መጠን ደግሞ እርሱ በሳይንስ ከሚያውቀው ነገር ጋር ለማገናኘት ሲሞክር መመሳሰሎች ስለነበሩት ይህ በእጅጉ ቀልቡን የሳበው ጉዳይ እንደነበር ወጣት ትንሳኤ ተናግሯል።
ትንሳኤ እንደሚለው በኢትዮጵያ የሕዋ ሳይንስን በንድፈ-ሃሳብ ደረጃ የሚረዱ በርካታ ልጆች አሉ። ነገር ግን ከሳይንሱ በስተጀርባ ያለውን እውነታ በተግባር በተደገፈ ትምህርት እንዲረዱ ማድረግ ላይ ብዙ አልተሠራበትም ይላል። ይህንን ለመቅረፍ በቅርብ ከሚገኙ ቁሳቁሶች የትምህርት መርጃ መሣሪያዎችን በመሥራት በተግባር ትምህርቱን እንዲቀስሙ ቢደረግ ውጤታማ ተመራማሪዎችን ማፍራት እንደሚቻል ይገልፃል። የሕዋ ሳይንስ ዕውቀቱን ለሌሎች ለማካፈል ሥልጠናዎችን ይሰጥ በነበረበት ወቅትም ይህንኑ መንገድ ይከተል እንደነበር ይናገራል።
የሕዋ ሳይንስ ከዕለት ተዕለት የሰዎች ሕይወት ጋር የተሳሰረ እንጂ፤ የቅንጦት እና ለበለፀጉ ሀገራት ብቻ የተሰጠ አይደለም የሚለው ወጣት ትንሳኤ፤ የሕዋ ሳይንስም እንደማንኛውም ዕውቀት ሀብት በመሆኑ ኢትዮጵያም ልትጠቀምበት እንደሚገባ ይገልፃል። ለበለፀጉ ሀገራት እንጂ ለእንደኛ አይነት ታዳጊ ሀገራት የሕዋ ምርምር አይሆንም ማለት እንደማይቻል ያስረዳል። ያለ ሕዋ ሳይንስ የግብርና፣ የትምህርት፣ የጤና ዘርፎችን ማዘመን እንደማይቻል ይገልፃል። ስለዚህ እነዚህን ነገሮች ለማዘመን፤ ለዘርፉ ትኩረት መስጠት ለነገ የሚባል እንዳልሆነም ተነግሯል።
ዘንድሮ ባሳለፍነው ሳምንት መጀመሪያ ወደፊት የሕዋ ምርምር ዘርፍ ይመራሉ ብሎ የዓለም የሕዋ ምርምር ፌዴሬሽን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከመረጣቸው አምስት ወጣት ተመራማሪዎች አንዱ እና በታሪክ በ25 ዓመቱ ይህንን ሽልማት ያገኘ በዕድሜ ትንሹ ሰው መሆን የቻለው ወጣት ትንሳኤ፤ ስለዚህ ጉዳይ ሲናገር አራቱ ግለሰቦች እውቅ በሆኑ የሕዋ ተቋማት የሚሠሩ ናቸው። እርሱ ደግሞ ከአፍሪካ ብቸኛ ሆኖ መቅረቡ እንደ ሀገር ለኢትዮጵያ እንደ አህጉርም ደግሞ ለአፍሪካ ፋይዳው ትልቅ እንደሆነ ገልጿል።
የሕዋ ሳይንስ በየትኛውም ዘርፍ ላይ ያለን ሰው የመቀበል አቅም አለው የሚለው ወጣት ትንሳኤ ጋዜጠኛ፣ ሓኪም፣ ወይም መሐንዲስ በሙያው ለዘርፉ ድጋፍ ማድረግ ይችላል። የሕግ ባለሙያዎች እንኳ በሕዋ ሕግ መገልገል ይችላሉ። የአንድ መሥሪያ ቤት ሥራ አስኪያጅ፣ የቢሮ ባለሙያ፣ ጥበቃ፣ የፅዳት ባለሙያ እንደሚፈልገው ሁሉ፤ ሕዋ እንደ ሴክተር ያለ በመሆኑ የሁሉንም ሙያ ባለቤቶች ይፈልጋል የሚለው ተመራማሪው፤ ስለዚህ ወጣቶች በሕዋ ዘርፍ ላይ መሰማራት ቢፈልጉ ያላቸውን ሥራ ሳይለቁ የራሳቸውን አበርክቶ ማኖር ይችላሉ ብሏል።
‹‹እንደ ወጣት ኃላፊነት ሊሰማን ይገባል፤ እኛ የምንሠራው ለእራሳችን ብቻ መሆን የለበትም›› የሚለው ትንሳኤ፤ ቀጣይ ትውልድ የተቃና ሕይወት እንዲኖረው ለማድረግ ጥረት ማድረግ የወጣቶች ኃላፊነት መሆኑን ይናገራል። የነገዋን ኢትዮጵያ ለመገንባት ዛሬ ለመሥራት ወጣቶች በቁርጠኛነት የመንቀሳቀስ ግዴታ እንዳለባቸውም ያመለክታል።
‹‹ዓለም የሕዋ ሳይንስ ባበረከተው ፈጠራ ላይ ጥገኛ ናት።››፤ የገንዘብ መቀበያ ማሽን፣ የሕክምና፣ የስልክ፣ የቴሌቪዥን እና መሰል በዕለት ተዕለት ሕይወታችን የምንጠቀምባቸው ነገሮች የሕዋ ሳይንስ ውጤቶች ናቸው፤ ኢትዮጵያ ይህንን አገልግሎት ሁሉ የምታገኘው በውጭ ምንዛሪ ከሌሎች ሀገራት በክፍያ ነው። እንደ ሀገር የፈጠራው አካል ብትሆን ወጪ ከማስቀረት አልፋ ገቢ የምታገኝበት ዘርፍ መሆን ይችላል፤ ስለዚህ ወደዛ ለመምጣት ኢትዮጵያ እራሷን ማብቃት መቻል እንዳለበት ወጣት ትንሳኤ ተነግሯል።
የሕዋ ሳይንስ ከሁሉም በበለጠ የሚያስፈልገው ለአፍሪካ ነው፤ አፍሪካውያንም በሕዋ ምርምር የላቀ ደረጃ የመድረስ አቅም አላቸው የሚለው ወጣት ትንሳኤ፤ በአሁኑ ወቅት በደቡብ አፍሪካ በሚገኝ ኪውስርየስ በሚባል የሳተላይት መቆጣጠሪያ ተቋም ውስጥ እየሠራ ይገኛል። ይህ ተቋም በዘርፉ በዓለም ላይ አሉ ከሚባሉ ተቋማት መካከል አንዱ እንደሆነ ገልፆ፤ አፍሪካዊ ድርጅት በመሆኑ ለሥራው ፍቃደኛ ሆኖ ስለመቀላቀሉ ተናግሯል። አፍሪካ ውስጥ የእስፔስ ቢዝነስ ማሳደግ ይቻላል የሚለው ወጣት ትንሳኤ፤ ከእርሱ መርሕ አንፃር አሁን ያለበት ተቋም ለአህጉሪቱ የሕዋ ሳይንስ እድገት በሚያበረክተው አስተዋፅዖ የድርሻውን ሚና ለመጫወት ጥረት እንደሚያደርግም ተናግሯል።
ወጣት ትንሳኤ የወደፊት ዕቅዱን እና ምን ማሳካት እንደምፈልግ ሲናገር፤ የሕዋ ሳይንስ ባለሙያ የመሆኑ ሐሳብ ስላለው በተለያየ ዘርፍ ዕውቀት እንዲኖረው ይሻል። ምክንያቱም ዘርፉ በጣም ሰፊ ስለሆነ ጠቅላላ ዕውቀት ይፈልጋል። በዚህ ምክንያት ትምህርቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል እና በዘርፉ ጥሩ ዕውቀት ይዞ ወደ ሕዋ ኢንዱስትሪው ተቀላቅሎ መሥራት እንደምሚፈልግ ገልጿል። አገሩን ኢትዮጵያን በሕዋ ምርምር የሚያስጠራ እና ከዘርፉ ተጠቃሚ የሚያደርገውን ሥራ በተግባር መሥራት እና ማበርከት እንደሚፈልግ ገልፆ፤ በተጨማሪ በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ እንዲሁም በዓለም በብዙ ዘርፎች ላይ የሚሠራ የሮስፔስ ተቋም እንዲኖረው እንደሚፈልግም ተነግሯል። ወጣት ትንሳኤ ለደረሰበት ስኬት ለወላጆቹ እንዲሁም ለሠራባቸው እና ለተማረባቸው ተቋማት ትብብር ከፍ ያለ ምስጋናውን ያቀርባል።
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ሰኔ 16/2015