በተባ ብዕሩ ዘመን አይሽሬ የስነ ጽሁፍ ሥራዎችን ለተደራሲን አቅርቧል፡፡ በቀደምት መጽሔቶችና ጋዜጦች ልዩ ልዩ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ወቅታዊ ጉዳዮችን የሚዳስሱ ጽሁፎችን ለአንባቢያን ጀባ ብሏል፡፡ በውጭ አገራት ተምረው ከመጡ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን ከንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ዘንድ ቀርቦ የሥራ መመሪያ ከተቀበለ በኋላ ‹‹የዛሬይቱ ኢትዮጵያ›› ጋዜጣ አዘጋጅ ሆኖ ሥራውን ጀምሯል፡፡ በዚህም ጋዜጣዋን በይዘቷም ሆነ በቅርጿ ከቀደሙት ዕትሞቿ የተለየችና የተሻለች እንድትሆን አድርጓል፡፡ ወደ ምዕራቡ ዓለም ተሻግሮ የቀሰመው እውቀትም የጋዜጣዋን ተነባቢነት ለማሳደግ አግዞታል፡፡
ከዛም በኋላ በንጉሰ ነገሥቱ ባለቤት በእቴጌ መነን አስፋው ስም የተሰየመችውና በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች ትዘጋጅ የነበረችው የ‹‹መነን›› መጽሔት አዘጋጅ ሆኖ ሰርቷል፡፡ አዳዲስ ጋዜጦችና መጽሔቶች እንዲቋቋሙም ከፍተኛ ጥረት አድርጓል፡፡ ‹‹Addis Reporter›› የተባለ መጽሔት ዋና አዘጋጅ ሆኖም ሰርቷል። በመቀጠል ደግሞ ወደ አሁኑ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ተዛውሮ የሥነ-ጽሑፍ ክፍል ዋና አዘጋጅ እና የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ሆኖ ሰርቷል። የእርሱ ዘመን አይሽሬ ጽሁፎች በጋዜጣው ላይ ተከትበው ዛሬም በጉልህ ደምቀው ይታያሉ፡፡
የዘውዳዊ ሥርዓት አክትሞ የደርግ መንግስት ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ ብዙም ሳይቆይ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጁ ረዳት ሆኖ ተመድቧል፡፡ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ደግሞ የድርጅቱ ዋና ስራ አስኪያጅ ሆኖ አገልግሏል፡፡ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ቋሚ ተጠሪ ሆኖ ተሾሞም ሰርቷል፡፡ ይህ ታላቅ የሥነ- ጽሁፍ ሰው ከመፅሄትና ከጋዜጣ ሥራዎቹ ባሻገር በዘመን አይሽሬ የድርሰት ሥራዎቹ ይበልጥ ይታወቃል፡፡
ከድርሰት ሥራዎቹ ውስጥ ደግሞ ከአድማስ ባሻገር፣ ኦሮማይ፣ የቀይ ኮኮብ ጥሪ፣ የህሊና ደውል፣ ደራሲው፣ ሀዲስና የመሳሰሉት በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በእነዚህ የሥነ-ጽሁፍ ሥራዎቹ በጊዜው የነበረውን ማህበራዊና ፖለቲካዊ ሁኔታ በራሱ ገፀ ባህሪ ቀርጾ ለአንባቢያን አቅርቧል፡፡ በገላጭ የድርስት አፃፃፍ ስልቱም የበርካታ አንባቢያንን ቀልብ መሳብ ችሏል፡፡ ለአገራችን ዘመናዊ የልብ ወለድ አፃፃፍ ስልት መሰረት ከጣሉ ደራሲያን ውስጥም አንዱ ነው፡፡
በእውነተኛ የሥነ-ጽሁፍ አፃፃፍ ዘዴውም ይታወቃል። በድርሰቶቹ ውስጥ በገለፃቸው የጊዜው ጉዳዮች ማለትም የባላባት አገዛዝ፣ የተማሪዎች እንቅስቃሴና የሕዝብ መስዋትነት ፍንትው አድርጎ የሚገልጽባቸው የመጀመሪያ የድርሰት ሥራዎቹ በተለይም ‹‹የቀይ ኮከብ ጥሪ›› እና ሃዲስ የተሰኙት ሥራዎቹ ዋጋ አስከፍለውታል፡፡ ለገፀ ባህሪያት የሚሰጠው ስብእናም ፍፁም ከመምሰሉም በላይ ህያው ሆነው ያሳያቸዋል፡፡
አሁን ደግሞ በዚህ ዘመን አይሽሬ የሥነ ጽሁፍ ፈርጥ ሕይወት ዙሪያ የሚያውጠነጥንና እርሱን የሚዘክር ‹‹በዓሉ ግርማ ቤርሙዳ›› የተሰኘ ቲያትር በውድነህ ክፍሌ ደራሲነት፣ በዶክተር ተሻለ አሰፋ አዘጋጅነትና በአንዱአለም ደጀኔ (አባቡ) መሪ ተዋናይነት በቅርቡ በሀገር ፍቅር ቲያትር ለተመልካች ሊቀርብ ነው፡፡በአወዛጋቢ ክስተት በደርግ ዘመን ሕይወቱ እንደተቀጠፈ የሚነገረው ደራሲና ፀሐፊ በዓሉ ግርማ፡፡
የቲያትሩ ደራሲ ፀሐፊ ተውኔት ውድነህ ክፍሌ ለአዲስ ዘመን እንደተናገረው፣ በዓሉ ግርማ በዘመኑ በጋዜጠኝነትም ሆነ በደራሲነት እውነትን በመናገር ረገድ ትልቅ ዋጋ የከፈለ የሥነ-ጽሁፍ ሰው ነው፡፡ ‹‹ነገር ግን እኔን ጨምሮ በዚህ ዘመን ላይ ያለነው የቲያትር ባለሙያዎችና ጋዜጠኞች በዓሉ ግርማ በከፈለው ዋጋ ልክ ስሙን ማንሳት አልቻልንም›› ይላል የቲያትሩ ደራሲ፡፡ በዓሉ በዛ ጊዜ ‹‹የፍፃሜው መጀመሪያ›› የተሰኘ አጭር ልብ ወለድ ጽፎ ነበር፡፡ ይህች ልብ ወለድ በኋላ ላይ በአጭር ልብ ወለድ ስብስብ ላይ ታትማለች፡፡ በዚች አጭር ልብ ወለድ ውስጥ በበዓሉ ግርማ ውስጥ ያሉ ሁለት ማንነቶች ተንጸባርቀዋል፡፡ ለነዚህ ሁለት ማንነቶች በዓሉ ሁለት ስም ሰጥቷቸዋል፡፡
አንደኛው ‹‹ህሊና ይፍረደኝ›› የሚል ገፀ ባህሪው ውስጣዊ ሙግቱ ሲሆን ሁለተኛው ገፀ ባህሪው ደግሞ ‹‹ስንት አየሁ ካለሕይወት›› የሚል ነው፡፡ ልብ ወለዷ በሁለቱ መሀል በአንድ ሰው ውስጥ ያሉ ማንነቶች ሲሟገቱ ታሳያለች፡፡ አንድ ስራን ለመስራት እውነትን ልግለፅ አልግለፅ የሚል ስሜት ያላትም ናት። ያመንኩበትን ላውጣ አላውጣ አይነት ሙግትም ነው በልብ ወለዷ የሚገለጸው፡፡
ይህች አጭር ልብ ወለድ በዓሉ ግርማ ኦሮማይ የተሰኘው የድርሰት ሥራው ከመውጣቱ ሶስት ወር በፊት የተፃፈች ናት፡፡ በዓሉ ኦሮማይን ለንባብ ሲያበቃው ችግር እንደሚገጥመው ያውቅ ነበር፡፡ ለዚህም ማረጋገጫው በዚች አጭር ልብ ወለድ ውስጥ ወደ እውነት መጠጋት አለብኝ፤ ያመንኩትን ፅፌ ማውጣት አለብኝ ብሎ መግለፁ ነው፡፡ በኋም በዚህ ትልቅ ዋጋ ከፍሏል፡፡
በዓሉ ግርማ ከሰራባቸው ከመነን መጽሔት አንስቶ እስከ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ድረስ ያለው እያንዳንዱ ታሪኩ ሲታይ ለነገሮች ተጋፋጭነቱን ያሳያል፡፡ በመነን መጽሔት ሲጽፍ በነበረበት ወቅት የነበረውን መንግስት በመንካቱና እንዳይወጡ የታገዱ ጽሁፎችን በማውጣቱ በተደጋጋሚ ተከሷል፡፡ አብሮ እየኖረ እውነትን መጋፈጥ የሚችል ሰው ነው፡፡ ነገር ግን የበዓሉ ግርማን እውነት በዚህ ዘመን ያሉ የቲያትር ባለሙያዎችና ጋዜጠኞች እስካሁን ሊረዱለት አልቻሉም፡፡
ወድነህ እንደሚናገረው፣ በዓሉ ግርማ የሞቀ ትዳር እያለው በጊዜው ትልቅ ዋጋ የከፈለ ደራሲ ነው፡፡ ይህ የበዓሉ ግርማ ትርጓሜ ደግሞ የትኛውም ዘመን ላይ ሊመጣ ይችላል፡፡ የሥነ ጽሁፍ ስራዎቹ ቢነበቡም የከፈለውን ዋጋ ያህል አልተዘከረም፡፡ እስካሁንም ዝም ተብሎ ቆይቷል፡፡ እንዲያውም ተረስቷል፡፡ ይህን ቲያትር ለመስራት መነሳሳቱ የመጣውም የእርሱን ውለታ ለመክፈል ነው፡፡
የበዓሉ ግርማ ባለቤት ወይዘሮ አልማዝ ሕይወቱ እስካለፈበት ድረስ ሁልጊዜ ማታ ማታ የሚመጣ ይመስላቸው ነበር፡፡ በር በተንኳኳ ቁጥር እድሜ ዘመናቸውን ሙሉ ሲጨነቁ ኖረው ያለፉ ናቸው፡፡ ይህ ቲያትር ቀድሞ ወጥቶ ቢሆን ኖሮ የክብር እንግዳ እርሳቸው በሆኑ ነበር፡፡ ቲያትሩ ለእርሳቸው ትልቅ ትርጉም ይኖረው ነበር፡፡ አሁንም ግን ቲያትሩ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ትልቅ ትርጉም ያለውና በዓሉ ለከፈለው ዋጋ ቢያንስ የህሊና ምላሽ መስጠት የሚያስችል ብሎም ባለእዳ ከመሆን የሚያድን ነው፡፡ ለከፈለው ዋጋ ትልቅ የቲያትር መነሻ ሆኖም ያገለግላል፡፡
የውድነህ ክፍሌ ‹‹በዓሉ ግርማ ቤርሙዳ›› ቲያትር ድርሰት ከተጀመረ ረጅም ጊዜ ሆኖታል፡፡ እንደውም ሥራው የተጀመረው እርሱ አማተር የቲያትር ባለሙያ እያለ ነበር፡፡ በጊዜው ‹‹በዓሉ ግርማ›› የተባለና አርባ አንድ አባላት ያሉት የኪነ ጥበብ ክበብ በ1980ዎቹ መጀመሪያ ላይ የነበረ ሲሆን የክበቡ የበላይ ጠባቂ የበዓሉ ግርማ ባለቤት ወይዘሮ አልማዝ ነበሩ፡፡ የክበቡ መሪ ደግሞ ራሱ ውድነህ ክፍሌ ነበር፡፡ የበዓሉ ግርማ ልጆች መስከረምና ዘላለምም የክበቡ አባላት ነበሩ፡፡ ከዛ ጊዜ ጀምሮ ታዲያ ውድነህ ክፍሌ ከበዓሉ ግርማ ጋር በተያያዘ በውስጡ በርካታ ነገሮች ነበሩ፡፡ በዩኒቨርሲቲ ቆይታውም የእርሱን አጭርና ረጅም ልብ ወለል ሥራዎች የኮርስ ማሟያ ወረቀቶችን ሰርቶባቸዋል፡፡
ሆኖም ይህን ቲያትር የጀመረው በ2013 ዓ.ም ነው። እስከዛሬ ከፃፋቸው የቲያትር ተውኔቶችም ይህ በብዙ ፈትኖታል፡፡ ምክንያቱም ቲያትሩን ለመስራት ስለ በዓሉ የተፃፉ ታሪኮችን ማንበብና ጥናቶችን ማድረግ ነበረበት። በተለይ ከበዓሉ ግርማ ጋር በተያያዘ በርካታ አወዛጋቢ ነገሮች በመኖራቸው በዛ አወዛጋቢ ክስተት መሃል የተነሳውን እውነት ይዞ እስከ መጨረሻው ድረስ ይዞ በየት ቀዳዳ በኩል ሾልኮ መውጣት እንደሚችል እንደ አንድ ፀሐፊ ተውኔት ትልቅ ጥያቄ በውስጡ ነበር፡፡
የትያትር ድርሰቱ ጥንቃቄና ንባብ ስለሚጠይቅ ውድነህ ክፍሌ ድርስቱ እየተፃፈ በድንገት ለተወሰኑ ቀናት በራሱ ችግር ሳይፅፍ ከወጣ ተመልሶ ለመፃፍ ይቸገር ነበር፡፡ ተመልሶ ወደዛ ስሜት ለመግባትም በበዓሉ ግርማ ዙሪያ የተፃፉ የተለያዩ መጽሐፎችን በድጋሚ ለማንበብ ተገዷል፡፡ ረጅም ጊዜ ከፈጁበት ተውኔቶች ውስጥም ይህ ‹‹በዓሉ ግርማ ቤርሙዳ›› የተሰኘው ቲያትር ነው፡፡ ጥናቱን ሳይጨምር የቲያትር ድርሰቱን ለመፃፍ ብቻ ስድስት ወር ፈጅቶበታል፡፡ ከአስራ አንድ በላይ ለሚሆኑ ደራሲያንና ጋዜጠኞችም ድርሰቱን አስነብቧል፡፡
ውድነህ ክፍሌ እንደሚገልጸው፣ በቲያትር ዝግጅት ስራ ዶክተር ተሻለ አሰፋ የተሳተፈ ሲሆን የቲያትር ሥራው በሀገር ፍቅር ቲያትር ታሪክ ከፍተኛ ወጪ የጠየቀና ከተለመደው የቲያትር አፃፃፍ ወጣ ያለ ነው። በዚህም ተዋንያንም ጭምር ትልቅ ዋጋ ከፍለዋል። ተዋንያን ለማግኘት በሚደረገው ፍለጋ በተለይም ‹‹ፊያሜታ ጊላይ›› የተሰኘችውን ገፀ ባህሪ ለማግኘት ትልቅ ውጣ ውረድ ነበር፡፡ ማስታወቂያ ወጥቶ ሃያ አምስት ሰዎች ተመርጠው ውድድር ተደርጎ በመጨረሻ ገፃ ባህሪያዋን ማግኘት ተችሏል፡፡
በዚህ ቲያትር በመሪ ተዋናይነት አንዷለም ደጀኔ /አባቡ/ የሚሳተፍ ሲሆን ዝናቡ ገብረስላሴ፣ሰለሞን ሃጎስና ሌሎችም አስራ አምስት የሚሆኑ ወጣትና አንጋፋ የሀገር ፍቅር ቲያትር ተዋንያን ይሳተፉበታል። በቲያትሩ ከሚሳተፉ ተዋንያን በተጨማሪ በበዓሉ ግርማ መጻሕፍት ውስጥ ያሉ እንደ ፊያሜታ፣ ፀጋዬ ኃይለማሪያም፣ ስእላይ፣ ኮሎኔል ታሪኩና ሌሎችም ገፀ ባህሪያትም ብቅ ብለው እንዲታዩ ይደረጋል፡፡ ስለዚህ ቲያትሩ የእውናዊና ምናባዊ ገፀ ባህሪያት ድምር ውጤት ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ አዘጋጁ ይህን ሊገልፅ የሚችል ዳንስ ይዞ መጥቷ፡፡
የቲያትር ድርሰት ሲታሰብ ተገቢነቱ፣ ማራኪነቱና ግልፅነቱ ወሳኝነት አለው፡፡ ከዚህ አኳያ በዚህ የድርሰት ስራ ከቲያትር አምስቱ አላባውያን ውስጥ ሁለቱ በርዕስነት ጥቅም ላይ እንዲውሉ ተደርገዋል፡፡ አንዱ አላባ ገፀ ባህሪ ሲሆን በበዓሉ ግርማ ተሰይሟል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ መቼት ሲሆን ‹‹ቤርሙዳ›› በተሰኘው በዓሉ ግርማ ነበረበት ተብሎ በሚገመት የማሰቃያ ቦታ ተገልጿል፡፡ በዚህ መሰረት የሁለቱ ጥምረት የቲያትሩ አርስት ሆኗል፡፡
ሰዎች በበዓሉ ግርማ ጉዳይ ልክ እንደ ቤርሙዳ አዙሪት ውስጥ ነው ያሉት፡፡ በዓሉ ግርማ እንደሞተ ቢያወቁም እንዴት ሊገደል እንደቻለና የት እንደተቀበረ ግን አያውቁም፡፡ አቡነ ቴፍሎስን ያክል ትልቅ አባት ተገድለው አስክሬናቸው ከብዙ ዘመናት በኋላ ተገኝቷል። የታላቁ ደራሲ በዓሉ ግርማ አስክሬን ግን ደብዛው ጠፍቷል፡፡ እስካሁንም አልተገኘም፡፡ ስለዚህ በዚህ ቲያትር ማሳየት የተፈለገው በዋናነት የበዓሉ ግርማን ስብእና ከፍ ማድረግ ሳለ ሆኖ ከተለያዩ ጥናቶች በመነሳት የበዓሉ አሟሟት ሁኔታ ወዴት አቅጣጫ እንደሚያመራ ለመጠቆም ነው፡፡
በዓሉ ግርማ በዛ ጊዜ የፈፀመው ተግባር ዛሬ ለደራሲዎችና ጋዜጠኞች ትልቅ ትምህርት ነው፡፡ እንደ ደራሲና ጋዜጠኛ ምንም የሚያስፈራ ነገር እንደሌለና ላመኑበት ነገር ፊት ለፊት መጋፈጥ እንደሚገባቸው፤ የትኛውንም ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ መሆን እንዳለባቸው የእርሱ ታሪክ አስረጂ ነው፡፡ የዛሬ ጋዜጠኞችና ደራሲያንም ይህን እየሰበሩ ለበዓሉ ግርማ ደግሞ ሐውልት እያቆሙ ነው፡፡
በዚሁ የበዓሉ ግርማ ቲያትር አጋጣሚ ትልልቅ ነገሮችም ወደመዘከር ይመጣሉ፡፡ ለዚህና ለመጪው ዘመን ምንጊዜም ለሙያው ታማኝ ሆኖ መከፈል ያለበት ዋጋ መክፈል እንዳለበትም ቲያትሩ ያስተምራል፡፡ ይህም ይበልጥ ሌሎችንም ያፀናል፡፡
‹‹በዓሉ ግርማ ቤርሙዳ›› የተሰኘውና በዓሉ ግርማ በጊዜው ለሙያው የከፈለውን መስዋትነት ለመዘከርና ከአንዳንድ ጥናቶች በመነሳት በጊዜው እንዴት ሕይወቱ ሊቀጠፍና አስክሬኑ ሊጠፋ እንደቻለ መላምት ለማስቀመጥ የተሰራው ይህ ቲያትር በርካታ የጥበብ አፍቃሪያን በተገኙበት የፊታችን እሁድ ሰኔ 18 ቀን 2015 ዓ.ም በሀገር ፍቅር ቲያትር ለተመልካች ክፍት ይሆናል፡፡
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሰኔ 14/2015