በኢትዮጵያ ከእንስሳት ልማት ዘርፍ አንዱ በሆነው የዓሣ ሀብት በዓመት ከ90ሺ ቶን በላይ ዓሣ ማምረት እንደሚቻል መረጃዎች ይጠቁማሉ። ከሀይቆች ጣና፣ ዝዋይ፣ አባያ፣ ጫሞ፣ ሀዋሳ፣ ከወንዞች ባሮ፣ ከግድብ ተከዜ በመሳሰሉት የውሃ ሀብቶች ውስጥ ዓሣ ማስገር የሚያስችል እምቅ ሀብት መኖሩን እነዚሁ መረጃዎች ያመለክታሉ።
የዓሣ ልማትን ጨምሮ የእንስሳት ምርትና ምርታማነት በመጨመር የግብርናውን ዘርፍ ከፍ በማድረግ እንደ ሀገር በምግብ ፍጆታ ራስን ለመቻል፣ ሀገራዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ በመንግሥት በኩል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራበት ይገኛል። ጥቅምት ወር 2015 ዓ.ም ላይ በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ይፋ የተደረገውንና ለአራት ዓመታት የሚተገበረውን የሌማት ትሩፋት ለእዚህ በአብነት መጥቀስ ይቻላል።
የእንስሳት ሀብት ልማት በቅንጅት ከተከናወነና በቴክኖሎጂ ከታገዘ አማራጭ የምግብ ግብዓቶችን ማብዛት እንደሚቻል መርሃ ግብሩን በይፋ ያስጀመሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለፃቸው ይታወሳል። በዚህ መርሃ ግብር የእንስሳት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እና ሥርዓተ ምግብን ማሻሻል እንደ ዋነኛ ዓላማ መያዙንም አመላክተዋል።
መርሃ ግብሩ ይፋ ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ ሀገራዊ ንቅናቄ ተፈጥሮ ወደ ሥራ ተገብቷል። መርሃ ግብሩን ስኬታማ ለማድረግም የምርምር ማዕከላት የተሻሻሉ የእንስሳት ዝርያዎችን ተደራሽ በማድረግ ረገድ ከፍ ያለ ሚና ይጠበቅባቸዋል። በዚህ ረገድ የዓሣ ጫጩቶችን በምርምር በማበዛትና ተደራሽ ለማድረግ ሰበታ ዓሣ ምርምር ማዕከል በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት መካከል ነው።
በኢትዮጵያ ስላለው የዓሣ ሀብትና ጥቅም ላይ በማዋል በኩል በተለይም በሰበታ ምርምር ማዕከል እየተከናወነ ስላለው ተግባር ያነጋገርናቸው የምርምር ማዕከሉ ተመራማሪ ዓለማየሁ ውቤ እንደሚሉት፤ በኢትዮጵያ ከ200 አይነት በላይ የዓሣ ዝርያዎች ይገኛሉ። ነገር ግን በዓሣ ዝርያ በግብርናው ዘርፍ ጥቅም ላይ እየዋሉ ያሉት ከአምስት አይነት የዓሣ ዝርያዎች አይበልጡም። በህብረተሰቡ ዘንድም የሚታወቁት እጅግ ጥቂቶቹ ሲሆኑ፣ በስፋት የሚታወቁትም ቆሮሶና አምባዛ የተባሉት ዝርያዎች ናቸው።
በምርምር ማዕከሉ የተለያየ ዝርያ ያላቸውን የዓሣ አይነቶች የማራባት ሥራ ይከናወናል። በምርምር የተራባው ዓሣ እንዲለማ ደግሞ ጫጩት ዓሣዎችን ለአርሶ አደሮችና ጥያቄ ለሚያቀርቡ የተለያዩ አካላት ወይንም አልሚዎች ማዕከሉ ያቀርባል። የሚሰራጩት ጫጩት ዓሣዎች እንደ ኃይል ማመንጫ እና ለተለያየ የግብርና ሥራ በሚውሉ የመስኖ ግድቦች ውስጥ ሊለሙ የሚችሉ ናቸው። ጫጩቶቹም የገበያውን ፍላጎት ማዕከል ያደረጉ ናቸው።
ጫጩት ዓሣዎችን በተጠቀሚው ፍላጎት መሠረት ለማቅረብ በተደረገው ጥረት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የደንበኛ ፍላጎት ማሟላት መቻሉን የጠቆሙት ተመራማሪው፤ በቅርቡም ሐረር አካባቢ ወደ አምስት ሺህ ጫጩቶች መሰራጨታቸውን ነው የገለጹት። ከግብርና ሚኒስቴር በቀረበ ጥያቄ ወደ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያም “ቆሮሶና ካርፕ” የተባለ ዝርያ ያላቸው ወደ አስር ሺ ጫጩት ዓሣዎች መሰራጨታቸውን አመልክተዋል። በተለይ በግብርና ሚኒስቴር በኩል የሚቀርቡ የጫጩት ዓሣ ጥያቄዎች ምላሽ የሚያገኙት በሰበታ ምርምር ማዕከል በኩል እንደሆነም ተመራማሪው ጠቁመዋል። ማዕከሉ የሚቀርቡ ጥያቄዎችን በማሟላትም የመጀመሪያው የመንግሥት ተቋም እንደሆነ ጠቁመዋል።
ዓሣ በወንዞች ብቻ የሚገኝ አለመሆኑን የሚናገሩት ተመራማሪው፣ አንዳንድ ግድቦች የወንዝ ዓሣ ሊኖራቸው እንደሚችል ግን ይገልፃሉ። ነገር ግን የዓሣ ዝርያው ለምግብነት የማይውል ሊሆን እንደሚችልም ይናገራሉ። እንዲህ ያለው ነገር ሲያጋጥም በምርምር ማዕከሉ ተፈልፍለው የወጡ ለምግብነት የሚውሉ የዓሣ ዝርያዎች በግድቡ ውስጥ እንዲረቡ ይደረጋል ይላሉ። የወንዝ ዓሣዎች ደግሞ በአብዛኛው ሥጋ እንደሌላቸውና አጥንት እንደሚበዛባቸው ነው
ያብራሩት። ገበያ ላይ ያላቸው ተፈላጊነትም አነስተኛ እንደሆነም ተናግረው፣ እንደየሁኔታውና አስፈላጊነቱ በምርምር የተፈለፈሉ የዓሣ ዝርያዎች ለግድቦች እንደሚያስፈልጉ አስታውቀዋል። በሀይቅ ላይ የተለየ ሁኔታ መኖሩንም ተመራማሪው ይጠቁማሉ። የመጥመጃ ቦታን ዝግ በማድረግና እንዳይጠመድም ክልከላ ከተደረገ በውስጡ ያሉት ዓሣዎች ራሳቸውን መተካትና መፈልፈል እንደሚችሉም ይገልጸሉ። ኩሬዎችና አዳዲስ ግድቦች ላይ ግን የመጀመሪያ መነሻ ዘር እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፣ ማዕከሉም መነሻ ዘር በማሰራጨት እርባታው እንዲስፋፋ ያደርጋል ይላሉ።
አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በኢትዮጵያ የዓሣ ምርት አቅርቦት አነስተኛ እንደሆነና በዋጋም ውድ መሆኑ ይነገራል። በሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ያለው አስተዋጽኦ ዝቅተኛ መሆኑ እንዲሁ ይነሳል። የዓሣ ዝርያዎችም እየጠፉ እንደሆነም በስፋት ይነገራል። ይህ ለምን ሆነ በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ተመራማሪው በሰጡት ማብራሪያም፤ የዚህ ምክንያቶቹ ብዙ መሆናቸውን ይገልፃሉ። የተጠቃሚዎች ቁጥር መጨመርና ፍላጎትና አቅርቦት አለመመጣጠን አንዱ ምክንያት መሆኑን ያስረዳሉ። ሌላው ደግሞ ሙያዊ ጉዳይ ነው ይላሉ። በዚህ ረገድም ዓሣን ለማጥመድ የሚውል የመረብ አጠቃቀም ለጉዳቱ ምክንያት መሆኑን ይጠቅሳሉ። ማጥመጃ መረብ መምረጥ ካልተቻለ የዓሣ ዝርያን የሚያጠፋ መረብ እንዳለም ጠቁመው፣ ይህንን ማስወገድ እንደሚገባ አስታውቀዋል።
ተመራማሪው እንዳሉት፤ ይሄ የዓሣ ዝርያን በማጥፋት ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላል ተብሎ የሚገመተው የመረብ አይነት ነው በኢትዮጵያ በስፋት ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው። መረቡ በግዥ ከውጭ የሚገባ ሲሆን፣ በዋጋ ርካሽ በመሆኑ ነው አብዛኛው ዓሣ አጥማጅ የሚጠቀመው። መረቡ አንዴ ዓሣዎቹ በሚገኙበት ሀይቅ ወይንም ግድብ ላይ ሲጣል ከጫጩት እስከ ትልቅ ዓሣ ይይዛል። በዚህ ጊዜም ሁሉንም ሳይመርጥ ይገላቸዋል። በዚህ መረብ የማጥመድ ድግግሞሹ ሲኖር ደግሞ ተተኪ ዓሣዎች ይጠፋሉ። መመናመኑ በዚህ መንገድ ይፈጠራል።
ሌላው ለዓሣ ሀብት መመናመን ምክንያት የሆነው በሕገወጥ መንገድና ኃላፊነት በጎደላቸው ዓሣ አጥማጆች በሚደርስ ጉዳት እንደሆነ የጠቆሙት ተመራማሪው፤ እነዚህ አካላት መቼና እንዴት እንደሚያጠምዱ ክትትል ለማድረግ አስቸጋሪ በሆነበት ሰዓት የማጥመዱን ሥራ ስለሚያከናውኑ መከላከል ባለመቻሉ በዓሣ ሀብት ላይ ጉዳት እየደረሰ መሆኑን ይገልጻሉ። እርሳቸው እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ አብዛኞቹ ሀይቆች ማንም ተነስቶ መረቡንና ጀልባውን ይዞ ለመግባት የሚችልባቸው ለሁሉም ክፍት የሆኑ ናቸው። በዚህ ስፍራ የሚካሄደው ዓሣ የማጥመድ ስራም ይሄን ያህል አጥማጅ አለው ወይንም በዚህ መንገድ ዓሣ መጠመድ አለበት የሚል ሳይንስን ተከትሎ የሚከናወን አይደለም።
አንዳንዴ ለዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ሲባል ከአቅም በላይ ጫና የሚፈጠርበት ሁኔታ በስፋት እንደሚስተዋልም ነው ተመራማሪው ያስገነዘቡት። በዚህ መልኩ ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱ ማህበራትም አላስፈላጊ መረቦችን መጠቀም ብቻ ሳይሆን በዓሣዎቹ የመራቢያ ቦታዎችም ላይም ጭምር በማጥመድ ጉዳቱን የሚያባብሱበት ሁኔታ እንዳለም ይናገራሉ። እንዲህ ላለው ችግር በተለይ በስምጥ ሸለቆ አካባቢ ያሉ ሀይቆች ተጋላጭነታቸው ሰፊ መሆኑን ይጠቁማሉ።
የዓሣ ሀብት ልማት በዚህ ዓመት መተግበር በጀመረው የሌማት ቱሩፋት መርሃ ግብር ከእንስሳት ሀብት ልማት አንዱ በመሆኑ ዘርፉን ከተለያየ ጉዳት በመጠበቅ በልማቱ ውስጥ ድርሻ እንዲኖረው ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ በተለይም ማዕከሉ ዓሣዎችን በማራባትና ጫጩቶችንም ከማሰራጨት ባለፈ በዘርፉ የሚስተዋሉ ክፍተቶችንም ከነመፍትሄው በጥናት ለይቶ ለሚመለከተው አካል በማቅረብ ረገድ ያከናወነው ተግባር ይኖር እንደሆን ተመራማሪው ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ ማዕከሉ ዘር ከማውጣትና ከማሰራጨት በተጨማሪ መረጃ በማውጣት ለፖሊሲ አውጭዎች እንዲደርስ ያደርጋል ብለዋል።
ተመራማሪው እንዳሉት፤ ከአንድ ሀይቅ በዓመት ምን ያህል ዓሣ ሊመረት እንደሚችል፣ መሰማራት ያለባቸው ዓሣ አጥማጆችና ለማጥመጃ የሚውል የመረብ ብዛት በምርምር ማዕከሉ ተመራማሪዎች በየጊዜው ተተንትኖ መረጃ ይወጣል። በአሁኑ ጊዜም በኢትዮጵያ በዓመት ወደ 94ሺ ቶን የሚሆን ዓሣ እንደሚመረት መረጃው የተሰጠው ከሰበታ ምርምር ማዕከል ነው። ዓመታዊ ምርቱ ብዙ ቢሆንም የዓሣ ምርት አሁንም ከውጭ በግዥ የሚገባበት ሁኔታ መኖሩን በመጥቀስ ለተመራማሪው ለቀረበላቸው ጥያቄ “ይሄ የዓሣ ሀብት ያለባቸውን አካባቢዎች ጠንቅቆ ካለማወቅ የሚመጣ ችግር ነው” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ ከዓሣ ምርት ጋር በተያያዘ ስምጥ ሸለቆ እና ባህርዳር አካባቢ ያለው ብቻ ነው ትኩረት የሚደረግበት፤ ነገር ግን መሠረተ ልማት ባልተሟላባቸው ከከተማ በርቀት ላይ በሚገኙ የሀገሪቱ ክፍሎች የዓሣ ሀብቱ በስፋት አለ። ለምሳሌ አፋር ክልል ደረቅ የሆነ የአየር ፀባይ ያለው በመሆኑ ለዓሣ ልማት ይሆናል ተብሎ እንደማይታሰብ አንስተው፤ ነገር ግን ከሰባትና ስምንት ያላነሱ ግድቦችና ሀይቆች ያለበት መሆኑን ይጠቁማሉ።
በዚህም በስፋት ዓሣ ማልማትና ማሟላት እንደሚቻል ይገልፃሉ። በዚህም ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠር እንደሚቻል ጠቅሰው፣ በአካባቢው ግን ዓሣ እየለማ አለመሆኑን ይናገራሉ። ማእከሉ የአካባቢውን ተጨባጭ ሁኔታ የያዘ የተሟላ መረጃ አውጥቶ ለሚመለከተው አካል ማቅረቡንም ነው የጠቆሙት። “የአካባቢ ሀብት በጥናት ተለይቶ ዝግጁ ሲሆን ተከታትሎ ወደ ተግባር ማዋል የአስፈጻሚው አካል ድርሻ ሊሆን ይገባል” ያሉት ተመራማሪው፤ የመሰረተ ልማት ተደራሽነት ትኩረት ቢሰጠው ልማቱ ይፋጠናል የሚል እምነት አላቸው። በዓባይ ግድብም አንዴ የዳሰሳ ጥናት በምርምር ማዕከሉ መደረጉን ጠቅሰዋል።
በማዕከሉ እገዛ በአካባቢው ላይ የዓሣ ልማት እንደሚካሄድ ጠቅሰው፣ ስራው ግን በቂ እንዳልሆነ አመልክተዋል። እርሳቸው እንዳሉት፤ የግድቡ አካባቢ ትልቅ መስህብ እንደሚሆን የሚጠበቅ በመሆኑ ወደፊት የዓሣ ጫጩት ማስፈልፈያ፣ የምርምር ማዕከልና መቋቋም እንዳለበት የዘርፉ ተመራማሪዎች እምነት ነው። ለሚከናወነው ልማትም ዩኒቨርሲቲዎችም ተሳታፊ ቢሆኑ ውጤታማ እንደሚሆንም ምክረ ሀሳብ ሰጥተዋል፡
እንደ መውጫ
ኢትዮጵያ በቀንድ ከብትና በተለያየ የእንስሳት ዝርያ ትታወቃለች። ይሁን እንጂ በግብርናው ዘርፍ በስፋት እየተከናወነ ያለው በሰብል ልማት ላይ ነው። የእንስሳት ሀብት ልማቱ ገበያ ተኮር ባለመሆኑ አርሶ አደሩ በመንደሩ እያረባ ያለው ዶሮ፣ በግ፣ ፍየል፣ የቀንድ ከብት እንዲሁም የዓሣ ልማት በአጠቃላይ የእንስሳት እርባታ ከእለት ከፍጆታ ያለፈ አይደለም። ይህ መሆኑም ዘርፉ እንደሀገር በክፍለ ኢኮኖሚው ላይ የሚጠበቀውን ያህል ድርሻ እንዳይኖረው እንዳደረገው በተለያየ ጊዜ በሚካሄዱ መድረኮች ሲገለጽ ይሰማል።
ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን የእንስሳት ልማቱን ለማሳደግና ውጤቶችንም ከፍ ለማድረግ በመንግሥት በኩል ጥረቶች እየተደረጉ መሆናቸው ይታወቃል። በተለይም በዶሮ እርባታና በወተት ልማት በተከናወኑት ተግባራት መልካም የሚባል እንቅስቃሴ ታይቷል። በተለይም እሴት የተጨመረበት የወተት ልማት እየተለመደ መጥቷል። ልማቱ ተጠናክሮ የበለጠ ውጤት እንዲያስገኝ በማድረግ ረገድ አሁንም ሥራዎች ይቀራሉ።
እንደ ሀገር የተያዘው የሌማት ቱሩፋት መርሃ ግብር እንዲሳካ ከምርምር ተቋማት የሚገኙ የምርምር ውጤቶችና ምክረ ሀሳቦች ጠቃሚ እንደሆኑም ከሰበታ ምርምር ማዕከል እንቅስቃሴ መገንዘብ ይቻላል። ሀገሪቱ በርካታ ሀይቆችና ትላልቅ ጅረቶች ያሏት ከመሆኑ በተጨማሪ ለተለያዩ ስራዎች የሚገነቡ ግድቦች ባለቤትም ናት። ይህን መልካም አጋጣሚ ከዓሣ ልማት ጋር በማስተሳሰር መስራት ይገባል። ለእዚህ ደግሞ የሰበታ ዓሣ ምርምር ማእከል ፋይዳ ከፍተኛ ነው።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 12 ቀን 2015 ዓ.ም