የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን እየፈተኑ ካሉ ችግሮች አንዱ የሀገር ውስጥ ተቋራጮች የመወዳደር አቅም ውስንነት ነው፡፡ የሀገር ውስጥ ተቋራጮች የአቅም ውስንነት ፕሮጀክቶች በታሰበላቸው ጊዜ እንዳይጠናቀቁ ከሚያደርጉ ተግዳሮቶች አንዱ ከመሆኑም ባሻገር፣ ሀገሪቱ አላስፈላጊ ወጪ ውስጥ እንድትገባም ምክንያት ሲሆን ይስተዋለል፡፡ ዘርፉን አሁን ካለበት ችግር ለማላቀቅና አቅም ያላቸው ኩባንያዎችን ለመፍጠር የኮርፖሬት ባህል መፍጠር አንዱ አማራጭ እንደሆነ ታምኖበት እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር በቀጣይ ሊያዘጋጀው ላቀደው አዲስ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ፖሊሲ ሰነድ ግብዓት ለማሰባሰብ ከዘርፉና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅርቡ በመከረበት መድረክ ላይ እንደተገለጸው፤ ውጭ ሄዶ ተወዳድሮ መስራት የሚችል እና በሀገር ውስጥ ባሉ ችግሮች ሸብረክ ሳይል መቆየት የሚችል ኩባንያ ለማፍራት በመጀመሪያ በሀገር ውስጥ የኮርፖሬት ባህል/ ኮርፖሬት ካልቸር/ እንዲገነባ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
በመድረኩ ላይ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡት ኢንጂነር መሰረት ለመች እንደሚሉት፤ የሀገር ውስጥ ኩባንያዎች የአቅም ውስንነት ያለባቸው በመሆናቸው አብዛኞቹን ሜጋ ፕሮጀክቶችን ግንባታ እያከናወኑ ያሉት የውጭ ሀገር ኩባንያዎች ናቸው፡፡ የሀገር ውስጥ ኩባንያዎች ራሳቸውን ተወዳዳሪና ብቁ አላደረጉም፡፡ በገንዘብና በሌሎች አቅሞችም ብቁ አይደሉም፡፡
የውጭ ኩባንያዎች አንዱ የአቅም ምንጭ ደግሞ በኮርፖሬት ደረጃ መወዳደራቸው ነው፡፡ የቻይና የኮንስትራክሽን ተቋራጮች በኢትዮጵያ ውስጥ ሜጋ ፕሮጀክቶችን እየገነቡ ያሉት በኮርፖሬት ደረጃ ተወዳድረው በማሸነፍ ነው፡፡ በተለይም እንደ ቻይና ኮሚዩኒኬሽንስ ኮንስትራክሽን ካምፓኒ (CCCC) ያሉ ኮርፖሬቶች ናቸው ፕሮጀክቶችን እየገነቡ ያሉት፡፡
‹‹ተቋራጮች ኮርፖሬት ሲሆኑ ብዙ ጥቅም ያገኛሉ። የፋይናንስ እና የቴክኒክ አቅማቸውን በአንድ ላይ በማድረግ ሜጋ ፕሮጀክቶችን ይይዛሉ፤ ስኬታማ በሆነ መንገድም ገንብተው ያስረክባሉ፤ ተወዳዳሪነታቸው ከፍ ይላል፤ ለተለያዩ ስራዎች የሚያስፈልገውን ነገርም በቀላሉ ያገኛሉ፡፡ ምክንያቱም ኮርፖሬት ሲሆኑ ለሜጋ ፕሮጀክቶች የሚያስፈልጉ መስፈርቶችን በቀላሉ ያሟላሉ›› ሲሉ ኢንጂነር መሰረት ያብራራሉ፡፡
ለዚህም ነው የሀገር ውስጥ ተቋራጮች ወደ ኮርፖሬት እንዲያድጉ ጥረት እየተደረገ ያለው ያሉት ኢንጂነር መሰረት፤ ‹‹የሀገር ውስጥ ኩባንያዎች ወደ ኮርፖሬት አድገው የግንባታ ድርጅቶችን መያዝ ቢችሉ፣ ሀገሪቱ በከፍተኛ ሁኔታ ተጠቃሚ እንደምትሆንም አብራርተዋል፡፡ መንግስት ለውጭ ኩባንያዎች የሚያወጣውን ወጪ ማዳን ይቻላል። በዚህም በሀገሪቱ ውስጥ ካለው የምንዛሬ እጥረት አንጻር በሀገሪቱ ላይ ያለውን ጫና ይቀንሳል›› በማለት ያስረዳሉ፡፡
እንደ ኢንጂነር መሰረት ማብራሪያ፤ ኩባንያ ዎች በኮርፖሬት መደራጀት ቢችሉ የውጭ ምንዛሬ ከማዳን አልፎ ለሀገሪቱ ተጨማሪ ምንዛሬም ያስገኛል። ኩባንያዎቹ በውጭ ሀገራት የኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶችን ተወዳድረው በማሸነፍ ለሀገር የውጭ ምንዛሬ ሊያስገኙ ይችላሉ፡፡ ለዚህም ነው ደረጃ አንድ እና ደረጃ ሁለት የሆኑ ኩባንያዎች በጥምረት እንዲደራጁ ጥረት እየተደረገ ያለው፡፡
አንድ የማድረጉ ስራ በፈቃድ ላይ የተመሰረተ እንደሚሆን ያብራሩት ኢንጂነር መሰረት፤ ለሀገር ካለው ፋይዳ አንጻር በኮርፖሬሽን ለሚደራጁት የተለያዩ ማበረታቻዎች እንደሚቀርቡም ተናግ ረዋል። ‹‹ለኮርፖሬቶቹ እያንዳንዱ ባለድርሻ አካል የተለያዩ ድጋፎች ይሰጣል፡፡ የሁሉም ዘርፍ ተቋማት የቤት ስራውን ወስደው እንዲሰሩ ይደረጋል›› ብለዋል፡፡
አብዛኞቹ ኩባንያዎች በኮርፖሬት ጉዳይ ደስተኛ መሆናቸውን ያብራሩት ኢንጂነር መሰረት፤ ከእያንዳንዱ ባለድርሻ አካል ጋር በመሆን ወደ ኮርፖሬት የማሳደግ ስራ እንደሚሰራም ነው ያመለከቱት፡፡ የኮንስትራክሽን ፖሊሲ ሲዘጋጅም ተቋራጮቹን ወደ ኮርፖሬት የማሳደግ ጉዳይ አንዱ የትኩረት አቅጣጫ እንደሚሆን አመልክተዋል፡፡
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ወንድሙ ሴታ በበኩላቸው፤ ‹‹በዚች ሀገር ውስጥ የኮርፖሬት ባህል እንዲገነባ ማድረግ ያስፈልጋል። የኮርፖሬት ባህል ማለት አምስት ስድስት ኩባንያዎችን መጨፍለቅ አይደለም፤ ብቻውንም ቢሆን በሚገባ የተዋቀረ የኮርፖሬት የአሰራር ሥርዓት ያለው ተቋራጭ እንዲኖር ማድረግ ከተቻለ ጠንካራ ተቋም ማግኘት ተችሏል ማለት ነው ሲሉ ያብራራሉ። የተቋራጮችን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ እኛ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ የአቅም ግንባታ ፕሮጀክት እንቀርጻለን፤ በዚህም መስፈርቶችን በማዘጋጀት ኩባንያዎችን በማብቃት ትልልቅ ኩባንያዎችን እንፈጥራለን›› ብለዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ የኮንስትራክሽን ኢንዱ ስትሪው የተለየ አሰራር ይፈልጋል፤ የቻይና ኩባንያ እዚህ አገር ለመስራት ድንገት አልመጣም፤ የአገሪቱ መንግስት ኩባንያው ወጥቶ ሰርቶ ገንዘብ እንዲያመጣ ይደግፈዋል። ‹‹ከዚህ አንጻር የኛ አገር መንግስት ተቋራጮች ወጥተው እንዲሰሩ ድጋፍ ማድረግ ይኖርበታል። በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ላይ የሚመጣው ተወዳዳሪነት የሚባክነውን ሀብት ከመቀነስ ባሻገር የሚመደበውን ሀብት በውጤታማ መልኩ ስራ ላይ ማዋል የሚቻልበትን ከባቢ ይፈጥራል።››ብለዋል፡፡ ይህን ተወዳዳሪነት ከፈጠርን በኋላ ይህን ለውጥ የሚሸከም አዲስ ስትራቴጂ መንደፍ ያስፈልጋል›› ሲሉም ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል፡፡
የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ አብቦ የነበረባቸውን የቀደሙትን ዓመታትም አስታውሰው፣ ‹‹በዚያን ወቅት ላይ ያንን እድገት የሚጠብቅ ተግባር አልሰራንም፤ ቁጥር አበዛን፤ ተወዳዳሪነት ላይ ግን እዚህ ግባ የሚባል ተቋራጭ ሳናገኝ ቀረን ሲሉ ገልጸዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው እንዳሉትም፤ ከዚህ አንጻር አዲስ ለውጥ መፍጠር ይገባል፤ ያለውን የገበያ እድል ማስፋት፤ አዳዲስ የገበያ እድሎችን መፍጠር ያስፈልጋል። የዛሬ ሰባት ዓመት መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ እንደርሳለን ስንል መንገዱ ኮንስትራክሽን ነው፡፡ ኮንስትራክሽን የሚፈጥረው እሴት፣ ለውጥና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ነው መካከለኛ ገቢ ላይ የሚያደርሰው።
ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን ዘጋን ማለት መንገዱን ዘጋን ማለት ነው። በዚህ ሂደት ውስጥ በየዓመቱ በኮንስትራክሽን ዘርፉ ያለው ኢንቨስትመንት እየጨመረ ነው፤ ከመጨመርም አልፎ ጥሩ ጥሩ ግንባታዎችም አሉ ያሉት ኢንጂነር ወንድሙ፣ ‹‹ሁሉም ሊባሉ በሚችል መልኩ ሜጋ ፕሮጀክቶች ናቸው። የስራ ተቋራጮቻችንን የባለሙያዎቻችንን የአማካሪዎቻችንን ተወዳዳሪነት ካላሳደግን በስተቀር እነዚህ ሜጋ ፕሮጀክቶች መቶ በመቶ ለውጭ ተቋራጮች ሊሰጡ ይችላሉ›› ሲሉ አስገንዝበዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ እዚህ ላይ መገንዘብ ያለብን ሁሉም አገሮች ያደጉበት መንገድ በውጭ ኩባንያዎች ተሳትፎ መሆኑን ነው። የውጭ ኩባንያዎች ተሳትፎ ግን የአጭር ጊዜ መሆን አለበት። በእነሱ ተሳትፎ ፕሮጀክቶች እየተሰሩ ቴክኖሎጂ እየተሸጋገረ እውቀት እየተቀሰመ ከዚያም የአገር ውስጥ ተቋራጭነት አቅም እያደገ መምጣት አለበት። የአገር ውስጥ ተቋራጮች ከውጭዎቹ ጋር ያላቸው ትስስር እንዲጠናከር ማድረግ ላይ መሰራት ይኖርበታል። እስከ አሁን ያንን ጠንክረን አልሰራንበትም ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፣ በዚህ የተነሳም በሚባለው ደረጃ ቱሩፋቱን ማግኘት አልተቻለም ይላሉ፡፡
የኮንስትራክሽን ማኔጅመነት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ታምራት ሙሉ በቅርቡ በአዳማ በተካሄደ የዘርፉ መድረክ ላይ ለሀገር ውስጥ ተቋራጮች ግሎባል ተወዳዳሪነት መሰረት የሚጥሉ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡ እሳቸው እንዳሉት፤ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው የ30 አመት ሮድ ማፕ አለው፤ የአስር አመት እቅድ ወጥቶም እየተሰራም ይገኛል፡፡ በአስር አመቱ እቅድም ካለው የዘርፉ ገበያ የሀገር ውስጥ ተቋራጮች 75 በመቶ እንዲሁም የምስራቅ አፍሪካን/ ሰብ ሪጅን/ 25 በመቶ ድርሻ እንዲይዙ ታቅዶ፤ ይህ ይቻላል ወይ ሲሉ ዋና ዳይሬክተሩ ጠይቀው አዎን ይቻላል፤ የቻይና ተሞክሮ ይህን ያመለክታል ሲሉ ያብራራሉ፡፡
የሀገር ውስጥ ተቋራጮች እንዴት ይበረታቱ፣ እንዴት ተወዳዳሪ እናድርጋቸው ሲሉም ጠይቀው፣ ዓለም የሚጠቀምባቸውን ቴክኖሎጂዎች እንዲ ጠቀሙ ማድረግ ላይ እየተሰራ መሆኑንም ነው ዋና ዳይሬክተሩ ያመለከቱት፡፡ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች እየተሰጡ፣ የሀገር ውስጥ ኩባንያዎችን የሚያበረታታ አዲስ የግዥ መመሪያ እየተዘጋጀ፣ ተኪ ምርቶችን የሚያመርቱን ከማበረታታት አኳያም እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ በሀገሪቱ ቀደም ሲል ተቋራጭ ሌባ ተደርጎ ይቆጠር ነበር፤ አሁን የልማት አጋር ተደርጓል፤ ተቋራጭም አማካሪም የሀገር ሀብት ናቸው፡፡ ይህ ሳይሆን በመቅረቱ የሀገር ሀብቶችን አጥተናል፤ ያን መመለስ አለብን ያሉት አቶ ታምራት፣ የሀገር ውስጥ ተቋራጮች በተዳከሙ ቁጥር በውጭዎቹ ስር እንወድቃለን ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
ተቋራጮች በቀጣይ በቆይታቸው ሳይሆን በብቃታቸው ልክ ብቻ የሚያድጉበት ሁኔታ እንዲኖርም ይሰራል ብለዋል፡፡ የአቅም ግንባታ በመንግስት በኩል እንደሚደረግ ጠቅሰው፣ መንግስት በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ተደጋጋሚ ስልጠናዎችን እንደሚሰጠም ጠቅሰው፣ ተቋራጮችም በተደራጀ አግባብ ሲቀርቡ እንደሚደገፉም አስታውቀዋል፡፡
የባዛልት ኮንስትራክሽን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ብሩክ ነጋሽ እንደሚሉት፤ የተቋራጮች አቅም ማነስ ተቋራጮችንም ሆነ ሀገሪቱን ይጎዳል፡፡ የተቋራጮች ፍላጎትን መሰረት በማድረግ ተቀራራቢ አቅም ያላቸው ኩባንያዎች በአንድ ላይ በመሆን ወደ ኮርፖሬት እንዲያድጉ ቢደረግ የዘርፉን ችግር ለመቅረፍ እገዛ ሊያደርግ ይችላል፡፡
ይሁን እንጂ የኮንስትራክሽን ተቋራጮችን ወደ ኮርፖሬት የማሳደጉ አካሄድ ሌሎች ዘርፎችን ወደ ኮርፖሬት ለማሳደግ ከሚደረገው አካሄድ እና አሰራር የተለየ ሊሆን እንደሚገባም ይጠቁማሉ። ለአብነት ያህል እንደ ባንኮች እና ኢንሹራንሶች ያሉ የፋይናንስ ዘርፎች ተቋማትን ወደ ኮርፖሬት ለማሳደግ ከሚካሄደው የተለየ አካሄድ መከተል ያስፈልጋል፡፡ እንደ ባንኮች እና ኢንሹራንሶች ያሉትን ኩባንያዎች አይነት ኮርፖሬሽንን በመመስረቻ መንገድ ተቋራጮችን ኮርፖሬት ለማድረግ የሚደረገው ጥረት የሚፈለገውን ውጤት ላያፈራ ይችላል ይላሉ፡፡
የኮንስትራክሽን ዘርፍ ከፍተኛ ሀብት ያለበት ነው ይላሉ፡፡ አንዳንዶቹ የኮንስትራክሽን ተቋራጮች ከፍተኛ ሀብት ሲኖራቸው ሌሎቹ ደግሞ ብዙም ሀብት ላይኖራቸው ይችላል፡፡ ብዙ ሀብት ያለው እና ሀብት የሌለው አንድ ላይ ኮርፖሬት ይሁን ሲባል ሀብት ያለው ሊጎዳ ይችላል ሲሉም ያብራራሉ፡፡
እንደ አቶ ብሩክ ማብራሪያ፤ ተቋራጮችን ወደ ኮርፖሬት በማሳደግ ሂደት ውስጥ የኮንስትራክሽን ስራ ከሌሎች ስራዎች ጋር ያለው ልዩነት ከግምት ሊገባ ይገባዋል፡፡ የኮንስትራክሽን ስራ ብዙ ጥረት ይጠይቃል፡፡ ቀንና ሌሊት የሚሰራበት ነው፡፡ ትልቅ መሰጠትን ይጠይቃል፡፡ ሰዎች ተሰጥተው ካልሰሩ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ስኬታማ ላይሆኑ ይችላሉ፡፡
እንደ ፋይናንስ ዘርፍ ስርዓት በመዘርጋት ብቻ የሚመራ አይደለም፡፡ ከስርዓት ባሻገር ብዙ ድካምን ይጠይቃል፡፡ አቀበት ቁልቁለት መውረድና መውጣት፤ አቧራና ጭቃ ውስጥ መሄድን ይፈልጋል። አንዳንዱ ሳይሰራ የቅንጦት ሕይወት የሚኖር የኮንስትራክሽን ኩባንያ ባለቤት አለ፡፡ ሌላኛው ደግሞ ወርዶ ራሱ የሚሰራ የኩባንያ ባለቤት አለ፡፡ ከዛ አንጻር በመሃል መጓተት ሊኖር ይችላል፡፡
አቶ ብሩክ ወደ ኮርፖሬት ሲመጣ የሰዎች መሰጠት ሊቀንስ ይችላል የሚል ስጋት አላቸው። መሰጠት ከቀነሰ ደግሞ ዘርፉን ወደፊት ሊወስድ ይችላል ተብሎ የታሰበው ኮርፖሬት ዘርፉን ጭራሽ ወደኋላ ሊጎትት ይችላል ሲሉ ያመለክታሉ፡፡
ወደ ኮርፖሬት ማደግ በራሱ ስኬታማ ሊያደርግ እንደማይችል የሚያነሱት አቶ ብሩክ፤ ከዚህ ቀደም በክልል እና በፌዴራል ደረጃ ኮርፖሬት የሆኑት ውጤታማ ናቸው ወይ የሚለውን ማየትም ያስፈልጋል ነው የሚሉት፡፡ በፌዴራል እና በክልሎች የተቋቋሙት የኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽኖች ውጤታማ ሊሆኑ አልቻሉም የሚል መከራከሪያም ያቀርባሉ፡፡
የኮንስትራክሽን ኩባንያዎች ችግር ግን የአቅም ማነስ ብቻ እንዳልሆነም አቶ ብሩክ የጠቆሙት። ገበያ አለመኖር፣ የግብዓት አቅርቦት አለመኖር፣ ኤልሲ ማግኘት ከባድ ነው ሲሉ ያብራራሉ፡፡ ከውጭ የሚመጡ ግብዓቶችን ማግኘት ከባድ መሆኑንም ጠቅሰው፣ ከውጭ ሀገራት የሚገቡ የግብዓት ችግሮች መኖራቸውም ኮርፖሬት የሆኑትንም እየፈተኑ መሆናቸውን ይጠቁማሉ፡፡ ከላይ የተጠቀሱ ችግሮች ሳይፈቱ ኮርፖሬቶችን በመፍጠር ብቻ የዘርፉ ችግር ሊፈታ አይችልም ይላሉ፡፡
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ኮርፖሬት የማድረግ ስራ ከመሰራቱ በፊት የስራ ባህልንም መቀየር ያስፈልጋል፡፡ በኢትዮጵያ አብሮ ተደጋግፎ የመስራት ልምድ አነስተኛ ነው፡፡ ተደጋግፎ ከመስራት ይልቅ አንዱ ሌላውን ጠልፎ ለመጣል ጥረት ሲያደርግ ነው የሚታየው፡፡ ይህንን የስራ ባህል በመሰረቱ ለመቀየር የሚያስችሉ ስራዎች ሊሰሩ ይገባል፡፡
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ሰኔ 10/2015