
‹‹ዛሬ ደግሞ ተጫጭኖኛል፤ እንቅልፍ እንቅልፍ ብሎኛል›› እያሉ እንዲሁ ግዜያቸውን በከንቱ የሚያሳልፉ ብዙዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች በጠዋት መነሳት አይሆንላቸውም፡፡ ማልደው ባለመነሳታቸው ስራቸውን በሰአቱና በአግባቡ አይከውኑም፡፡ ይነጫነጫሉ፡፡ ስልቹ ናቸው። ድብርትም ያጠቃቸዋል፡፡ በህይወቱ ስኬት እንዲመጣ የሚያስብ ሰው ግን እነዚህን ነገሮች ማስወገድ የግድ ይለዋል፡፡ ሰው በእያንዳነዱ ቀን የሚኖረው ብርታት ተጠራቅሞ ነው የሚፈለገውን ነገር ማሳካት የሚቻለው፡፡ ቀንን የሚወስነው ደግሞ የጠዋት ክንውን ነው፡፡
ፈረንጆች ‹‹first impression is last impression›› ይላሉ፡፡ ‹‹ጅማሬህ ፍፃሜህን ይወስነዋል›› እንደማለት ነው፡፡ ለመሆኑ ቀናችን ላይ ባለስልጣን የሆነው የጠዋት ልምዳችን ምን መምሰል አለበት? የተሳካና የሚያስደስት ጠዋት ቢኖረን በቀን ውስጥ ከሚሰሙን መጥፎ ስሜቶች ውስጥ አብዛኛዎቹን የመቀነስ እድል ይኖረናል፡፡
በጠዋት ተነስተን ማንኛውንም ነገር ማከናወን ሞት መስሎ የሚታየን ብዙ ሰዎች ልንኖር እንችላለን። ግን አንድ ሰአት ቀድመን ተነስተን ያለንን አንድ ህይወት ማሳማር መቻል በራሱ ትልቅ ስኬት ነው፡፡ በማለዳ ተነስተን ማድረግ ያለብንና ለህይወታችን እጅግ ጠቃሚ የሆኑ አስር ፀባዮች የሚከተሉት ሲሆኑ ቀጥሎ ከሚዘረዘሩት አስር ፀባዮች ውስጥ ስንቶቹ የእናንተ ፀባይ እንደሆኑ ልትለዩ ትችላላችሁ። የወደዳችሁትን ደግሞ መርጣችሁ ፀባያችሁ ታደርጉታላችሁ።
1ኛ. ቀደም ብሎ መነሳት
ማልዶ መነሳት የብዙ ስኬታማ ሰዎች ፀባይ ነው፡፡ ከሞቀ እንቅልፋችን ለመነሳት ያለውን ትግል ለማሸነፍ አላርማችንን ሞልተን እንተኛለን። ሆኖም አላርሙ በጮኸ ቁጥር ስንቴ ነው ተነስተን አጥፍተን የምንተኛው? የመነሳት ጉጉት እንዲኖርህ የሚያደርግ አላማና አስተሳሰብ ከሌለህ አእምሮህን አሳምኖ መንቃት የማይታሰብ ነው፡፡ ከዚህ በፊት እኮ የምትወደውንና የምታከብረውን ሰው ቀጥረህ በጠዋት ተነስተህ አግኝተኸው ታውቃለህ፡፡ አንዳንዴ ወሳኝ ጉዳይ ሲኖርህም በጠዋት ተነስተህ ታውቃለህ፡፡ ትልቁ ችግር ወጥነት ባለው መልኩ በየቀኑ በጠዋት አትነሳም የሚለው ነው።
ስለዚህ ሁልግዜም አይምሮህን የሚያባንነው ጉዳይ ቢኖር ትነሳለህ ማለት ነው፡፡ ለዛም ነው የሚያባንንና በጠዋት የሚያስነሳ ዓላማ እንዲሁም የአጭርና የረጅም ጊዜ እቅድ የሚያስፈልግህ። ለምሳሌ የሚጮኸውን አላርም በመጠኑ ብታርቀው በጠዋት ለመንቃት በመጠኑ ይረዳሃል። ምክንያቱም አላርሙ ሲጮህ በጠዋት ተነስተህ ለማጥፋት የምታደርገው እንቅስቃሴ ሰውነትህን ስለሚያነቃቃው በዛው እንድትነቃ ሊያደርግህ ይችላል፡፡
2ኛ. ብርሃን ማግኘት
ብርሃን የመነቃቃት ስሜትን ስለሚፈጥር በጠዋት እንደተነሳን መስኮት የመክፈትና ብርሃን ወደመኝታ ቤታችን የማስገባት ልምድ ሊኖርን ይገባል፡፡ ብርሃንን መመልከት ስንል ግን ቀጥታ ፀሃይን ማየት ማለት አይደለም። ነገር ግን መስኮታችንን ከፍተን የምናገኘው ወይ ደግሞ መንገድ ላይ ስንሄድ የምናየውን ብርሃን ማለት ነው።አንዳንድ ጊዜ ቤት ውስጥ ስንውል በቂ ብርሃን ላናገኝ እንችላለን፡፡ ስልክ ወይም ኮምፒዩተር ላይ ግዜያችንን እናጠፋለን፡፡ ቆይተን ከአልጋችን ተነስተን የሚኖረን ስሜት ግን የመደበር ስሜት ነው።
ምንአልባት ግን ከሰአት ያንን በቂ ብርሃን ካገኘን እንነቃለን፡፡ ችግሩ ግን ሰውነታችን ይህን ኡደት ተከትሎ ሲሄድ ማታ በጊዜ ለመተኛት ይቸግረናል፡፡ ምክንያቱም በቂ ብርሃን በሰአቱ ስላላገኘንና ኡደቱን ስላዛባነው የመተኛትና የመንቃት ሰአታችንም አብሮ ይዛባል። ስለዚህ ጠዋት እንደተነሳን በቂ ብርሃን ማግኘት ተአምረኛ የሆነውን ሰውነታችንን የመንቃት ሂደቱን ያስተካክለዋል።አርፈደን ተነስተን የቤትን ብርሃን ዘግተን ከዋልን ግን የድብርት ስሜቶች እኛ ጋር ተሰባስበው መኖር ይጀምራሉ፡፡ ለነገሮች ፍላጎት እንድናጣ፤ አንዳንዴም ህይወት ጣዕም እንዳይሰጠን ያደርገናል፡፡ ተፈጥሮ በፀሃይ በኩል የምትሰጠንን ጥቅም ማባከን የለብንም፡፡ የጠዋት ብርሃን ያስፈልገናል፡፡
3ኛ. ራስን ለማንቃት መሞከር
ሁሉም ሰው ከእንቅልፉ ከነቃ በኋላ ራሱን ለማንቃት የሚያደርገው የተለያዩ ልማዶች ይኖሩታል፡፡ ለምሳሌ ስመጥሩ ባለፀጋ ኤሎን መስክ ‹‹ህይወቴን የቀየረው አንድ ልምድ ቢኖር በጠዋት እየተነሳሁ የምወስደው ቀዝቃዛ ሻወር ነው›› ይለናል። እነ ኦፕራ ዊንፍሬይና ሌሎችም ታላላቅና ዝነኛ መንፈሳዊ ሰዎች ደግሞ ‹‹በጠዋት ተነስቼ በህይወቴ የተደረጉልኝን አምስት ነገሮችን ፅፌ ሳመሰግን ቀኔ እጅጉን ብሩህ ይሆናል›› ይሉናል፡፡
በጠዋት ከተነሳን በኋላ ቀን ላይ እሚሰማን አይነት ንቃት አይኖረንም፡፡ ለጥቂት ጊዜ እንቅልፍ እንቅልፍ ይለናል፡፡ እንደተነሳን ያለውን የእንቅልፍ ስሜት ለማጥፋት የሚረዳን የሰውነት እንቅስቃሴ ነው፡፡ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ስናደርግ የልብ ምታችንና የሰውነት የደም ዝውውራችን ጨምሮ ሰውነታችን ይበልጥ እንዲነቃቃ ያደርገዋል፡፡ ቀዝቃዛ ሻወር መውሰድም ሰውነትን ለማነቃቃት ይረዳል፡፡
4ኛ. በቀን ውስጥ የሚደረጉ ነገሮችን ዝርዝር ማውጣት
በማንኛውም እንቅስቃሴያችን ውስጥ መዳረሻችንን ማወቅ አለብን፡፡ ወዴት እንደሚወስድ የማታውቀው ታክሲ ውስጥ ዘው ብለህ አትገባም፡፡ በቀን ውስጥ የምናደርገውን ማንኛውንም ነገር ጠዋት ማወቅ አለብን፡፡ ይህ ማለት የቀኑን አላማችንን ጠዋት አውቀን መነሳት ማለት ነው፡፡ ይህን ዝርዝር ስናወጣ የቀን መነቃቃት ራሱ ይጨምርልናል፡፡
ታዲያ እነዚህ ዝርዝሮች ላይ የምናስቀምጣቸው ተግባሮች ልምድ ልናደርጋቸው የምንችላቸው መሆን አለባቸው፡፡ ለምሳሌ አንድ ፀሃፊ ተነስቶ ዛሬ ጥሩ ፅሁፍ እጽፋለሁ ካለ ግልፅ አይደለም፡፡ በዚህ ርእሰ ጉዳይ ላይ ሁለት ገፅ እጽፋለሁ ቢል ግን ለመተግበር ቀላል ይሆንለታል፡፡ ልክ እንደዚህ በየትኛው የስራ ዘርፍ ላይ ብትሆን ማድረግ የምትፈልገውን ነገር ለመተግበር በሚመች መልኩ አስቀምጠው። በተለይ ግልፅና አጠር አድርገህ ከፃፍከው ማታ ላይ እንዳሳካኸውና እንዳላሳካኸው ለመመዘን ይረዳሃል፡፡
5ኛ. ከራስ ጋር ንግግርና ምስላዊ እይታ
በጠዋት ተነስተን ለራሳችን የምንነግራቸው ነገሮች ውሏችን ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ አላቸው፡፡ ነጋዴው ዛሬ ሁለት መቶ ብር እሰራለሁ፣ መፅሐፍ አንባቢው ዛሬ ስልሳ ገፅ አነባለሁ ሊል ይችላል። ለራሳችን ደጋግመን የምንነግረው ነገር በውሏችን ውስጥ መከወኑ የማይቀር ነው፡፡ ስለዚህ አወንታዊ የሆኑትንና ዛሬ አደርጋለሁ የሚሉ ማረጋገጫዎችን ለራሳችን እንሰጣለን፡፡
እነዚህን እቅዶች አሉታዊ በሆኑ መንገዶች መግለፅ ግን ተገቢ አይደለም፡፡ ለምሳሌ ‹‹ዛሬ አላረፍድም›› ብንል ሃሳባችን ትክክል ነው፡፡ ነገር ግን አላደርግም ከሚለው ሃሳብ ይልቅ አደርጋለው ወደሚለው ብናመዝን ለአእምሮ ያለው አወንታዊ ጫና ከፍተኛ ይሆናል፡፡ ሌላው ጥሩ ልማድ የሚባለው ደግሞ አደርጋለሁ የምንላቸውን ነገሮች በአእምሯችን መሳል ነው፡፡ እነዚህን ስእሎች በአእምሯችን ውስጥ ስንፈጥር ‹‹visualization›› ይሰኛል፡፡
በርካታ እውቅ ተመራማሪዎች ሊሰሩ ያሰቡትን የፈጠራ ውጤት በጭንቅላታቸው ውስጥ በማመላለስ እያዩት ካሰቡበት ይደርሳሉ፡፡ እኛም ጠዋት ከተነሳን በኋላ የምናደርገውን ነገር ማወቅ ብቻ ሳይሆን በምስል አእምሯችን ውስጥ ማመላለስ አለብን፡፡ ምክንያቱም ምስሎችን አእምሯችን ውስጥ መፍጠር ከቻልን መሬት ላይ ማውረዱ ከባድ አይሆንም፡፡
6ኛ. አመስጋኝ መሆን
ገና እንደተነሳን ‹‹ደሞ ነጋ ወደዛ ስራ፣ ወደዛ አስቀያሚ ትምህርት ልሄድ ነው›› እያልን እያማረርን ከእንቅልፋችን እንነሳ ይሆናል፡፡ እዚህ ጋር ግን አንድ ነገር አስታውሱ! ስራ የሌለው፣ ትንሽ እንኳን ገቢ የሌለው፣ ከሰው የሚጠብቅ፣ ኑሮ የመረረው በሚሊዮኖች የሚቆጠር ሰው ሞልቷል፡፡ በጦርነት፣ በችግርና በድህነት ምክንያት ሳይማር ቤቱ የቀረ በሚሊዮን የሚቀጠር ህዝብ እንዳለም አትዘንጋ፡፡
በመንገድ ስታልፍ እኮ ‹‹ምን አለ እንደዚህ ሰውዬ የምሰራው፤ የምማረው ነገር ብትሰጠኝ›› እያለ ፈጣሪውን የሚጠይቅ ብዙ ሰው ነው፡፡ ቀድሞውኑ ለመንቃት መቻል በራሱ ትልቅ ማመስገኛ ነው። መንቃት ማለት አይንን መግለጥ ብቻ አይደለም። አይናችንን በገለጥንበት ቅፅበት ሰውነታችን እጅግ ብዙ ስራዎችን ያከናውናል፡፡ ይህንን ሁሉ በተሳካ ሁኔታ አልፎ መነሳትን አለማመስገን አይቻልም፡፡ ስለዚህ በተሰጠህና ባለህ ነገር አመስጋኝ ሁን፡፡
7ኛ.ዝምታ
በጠዋት ቀድመን ስንነቃ ከሚን ጫጫው፤ ከሚተራመሰው ዓለም ነፃ የሆነ የራሳችን ጊዜ ይኖረናል። በቀን ውስጥ ልናገኘው የማንችለው የራስ ጊዜ እናገኛለን፡፡ የሰው ልጅ ለማንኛውም ውሳኔ ቅድሚያ ከራሱ ጋር ማውራት አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ ዝም ያለና የተረጋጋ ግዜ ያስፈልጋል። አትርሳ! ህይወት በውሳኔ የተሞላች ነች፡፡ ያንተን ውሳኔ የሚጠብቁ ብዙ ጉዳዮች አሉ፡፡ ስለዚህ ሁሌም ጠዋት ስትነቃ በዝምታ ውስጥ ሆነህ ከዚህ የጫጫታ ዓለም ርቀህ ማሰብ መቻል አለብህ፡፡
8ኛ. የኔ ከምንላቸው ሰዎች ጋር ማውራት
ቢያንስ ለአስር ደቂቃ ከራስህ ጋር ከተነጋገርክ በኋላ ከምትወዳቸው ሰዎች ጋር ደግሞ መገናኘት አለብህ። የሰው ልጅ ብቻውን እንዲኖር አልተፈጠረም፡፡ ለዚህ ነው በሌሎች መፈለግንና መወደድን የምንፈልገው። ታዲያ ይህንን ስሜት ስናገኘው አእምሯችንና ሰውነታችን ይነቃቃል።ደስተኛ ይሆናል፡፡ ጠዋት መጀመሪያ ላይ ለዛ የኔ ለምንለው ሰው ጊዜ መስጠት፣ ፍቅር መለገስ አብሮ ማሳለፍ እንዲሁም የምንወዳቸውን ሰዎች ማቀፍ በራሱ በሰውነታችን ውስጥ ያለውን የሚያነቃቃ ኬሚካል መጠኑ ይጨምራል፡፡ ያለንን እምነትና ግንኙነትንም ያጠናክራል፡፡
9ኛ. አልጋ ማንጠፍ
አልጋ ማንጠፍ በቀላሉ የማይታይ ቀናችን ላይ ትልቅ ተፅእኖ የሚፈጥር ዲስፕሊን ነው። የቀኑ ስኬትህን አንድ ብለህ የምትጀምርበት መነቃቂያህ ነው፡፡ አልጋህን ራስህ ስታነጥፍና ሌላ ሰው ሲያነጥፍልህ የሚሰማህ ስሜት የተለያየ ነው፡፡ በአንተ ምክንያት አንድ የተዝረከረከ ነገር መስተካከሉን ስታይ የስኬታማነት ስሜት ይሰማሃል። ይሄ ስሜት በቀን ውስጥ ልትሰራቸው ላሰብካቸው ሌሎች ተግባሮች በደምብ አድርጎ የሚገፋህ መንደርደሪያ ይሆንሃል፡፡
10ኛ. ማንበብ
ጠዋት ባለን ንቃተ ህሊና ብዙ ነገሮችን ወደአእምሯችን የማስገባት አቅም አለን፡፡ በዚህ ሰአት ቢያንስ አንድ ለስራችንና ለህይወታችን ወይ ደግሞ ለደስታችን፣ ለጤናችንና ለመንፈሳዊ ህይወታችን ጠቃሚ የሆነ አንድ ነገር ብናውቅ ከጊዜ በኋላ ያለን አስተሳሰብና የእውቀት ደረጃ እየተለወጠና እያደገ ይሄዳል፡፡ ጠዋት ተነስተህ የምታነበው ነገር ቶሎ ይገባሃል፡፡ በቋሚነት ሁሌም ካደረከው ደግሞ ይህ ፀባይ ካስተሳሰብህ ጀምሮ እውቀትህንና ገቢህን እስከመጨረሻው ይቀይረዋል፡፡
ከላይ የተዘረዘሩት አስሩ ፀባዮች ፍላጎቱ እስካለን ድረስ በቀላሉ ልንተገብራቸው የምንችላቸው ናቸው፡፡ ምን አልባት ‹‹ይህን ሁሉ ለማድረግ እንዴት ጊዜ ሊበቃን ይችላል›› ትሉ ይሆናል፡፡ ሁለት ሦስቱን ፀባዮች በየቀኑ መርጠው ለጥቂት ደቂቃዎች በመከወን ጀምሩ። ተአምራዊ ለውጥ ያያሉ፡፡ ሰላም!!
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሰኔ 10/2015