ወጣት ባዬ እምቢዓለው ይባላል። ተወልዶ ያደገው በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም ዞን ሞጣ ከተማ ነው። የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በዛው በትውልድ አካባቢው ተከታትሏል፡፡ በትምህርቱ መካከለኛ ከሚባሉ ተማሪዎች የሚመደብ እንደሆነ የሚናገረው ወጣት ባዬ ነገር ግን በወቅቱ በነበረው የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ውጤት ስላልመጣለት በማታ የትምህርት ክፍለ ጊዜ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሶሾሎጂ እና ሶሻል አንትሮፖሎጂ ትምህርቱን ተከታትሎ በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቋል።
በወቅቱ ከመደበኛ ትምህርቱ ጎን ለጎን በዛው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነ ጥበብ እና ዲዛይን ትምህርት ክፍል ተወዳድሮ በመግባት በ2001 ዓ.ም የመጀመሪያ ዲግሪ በቅርፅ ጥበብ ሁለተኛ ዲግሪውን ደግሞ በአርት ቲኦር በ2009 ዓ.ም ተቀብሏል። ወጣት ባዬ በተመሳሳይ ጊዜ በተለያየ የትምህርት አይነት ሁለት ዲግሪ ማግኘት ችሏል።
ወጣት ባዬ ወደኋላ ተመልሶ ዩኒቨርሲቲ ቆይታውን ሲያስታውስ ከተለያየ የሀገሪቱ አካባቢ የመጡ ወጣቶች ያሉበት እንደመሆኑ ትንሿን ኢትዮጵያ ማየት የቻለበት ወቅት እንደነበር ያስታውሳል፡፡ የተለያየ ሃይማኖት፣ ባህል፣ ቋንቋ እና አመለካከት ያለው ሰው በአንድ ላይ ሆኖ የሚኖርበት እና ዓላማውን ለማሳካት ሁሉም የሚጥርበት ቦታ እንደሆነ እና ደስ የሚል ቆይታ ያሳለፈበት እንደነበር ያስረዳል።
የስዕል እና ቅርፃ ቅርፅ ጥበብ ጅማሮው እንዴት እንደነበር ወጣት ባዬ ሲናገር ወደ ልጅነት ጊዜው ተመልሶ ያስታውሳል፤ አጎቱ መጽሐፍ አንባቢ እንደነበሩ እና ታዋቂ የነበሩ ግለሰቦችን ማለትም ካርል ማርክስ፣ ሌኒን እና ሌሎች መሰል የወቅቱ ታወቂ ሰዎች መጽሐፍት፣ ፎቶ እና ስዕል በቤታቸው እንደነበረ እሱም ምስሎቹን ይወዳቸው ስለነበር በተደጋጋሚ በትክክል ኮፒ እያደረገ ይስላቸው እንደነበረ ይገልጻል።
የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ እንደመሆኑ በልጅነቱ እምነቱን የሚገልፁ የማሪያም እና መልዓክትን ስዕሎች በተደጋጋሚ ይሰራ ነበር፡፡ በወቅቱ በትምህርት ጥሩ እንቅስቃሴ ያሳይ ስለነበር ታላቅ ወንድሙ የስዕል ሥራውን እንዲተው እና ትምህርቱ ላይ ብቻ እንዲያተኩር እንዳደረገው እና ለተወሰነ ጊዜ የስዕል ሥራውን አቁሞ እንደነበረ የሚነገረው ወጣት ባዬ የስዕል ፍላጎቱ እና ተስጥኦ በውስጡ ስለነበር የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ሲጀምር የስዕል ሥራውን ዳግም መስራት እንደጀመረ ወጣት ባዬ ይነገራል።
በወቅቱ በትንንሽ ወረቀቶች እና ሸራ ላይ የተለያዩ ስዕሎችን በተለይ መንፈሳዊ ይዘት ያላቸውን ሥራዎች እየሰራ መንገድ ላይ በመሸጥ ገቢ ማግኘት እንደጀመረ ይገልፃል፡፡ በ1995 ዓ.ም ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባው ውጤት ሳይመጣለት ሲቀር ለአንድ ዓመት በትውልድ ስፍራው እንዳሳለፈ እና ይህም ለስዕል ሥራው ሰፊ ጊዜ ለማግኘት መልካም አጋጣሚ እንደፈጠረለት የሚገልፀው ወጣቱ በዛው ዓመት መደበኛ ባልሆነ መንገድ ትምህርቱን ለመከታተል አዲስ አበባ እንደመጣ እና በዛው ወቅትም ቢሆን ከትምህርቱ ጎን ለጎን የስዕል ሥራውን ከመስራት እንዳልተቆጠበ ይነገራል።
በ1998 ዓ.ም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነ ጥበብ እና ዲዛይን ትምህርት ቤት በዘርፉ ፍላጎት ያላቸውን ልጆች ተቀብሎ ለማስተማር በወጣው ማስታወቂያ መሰራት ተመዝግቦ በአምስት ዙር የተሰጠውን የመግቢያ ፈተና በብቃት በማለፍ ትምህርቱን መከታተል እንደቻለ እና ይህም የስዕል እና ቅርፃ ቅርፅ ሥራው በተሻለ እውቀት እና መረዳት መሥራት እንዲችል እንደረዳው ወጣት ባዬ ይገልፃል።
መጀመሪያ አካባቢ የሙያውን ፍላጎት ብቻ ይዞ እንደተነሳ እና ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ተቀላቅሎ ሙያውን መማር መቻሉ የሙያውን ሳይንስ መረዳት እንዲችል መልካም አጋጣሚ እንደፈጠረለት የሚናገረው ወጣት ባዬ ስዕል የገቢ ምንጭ ሆኖ እያገለገለው እንደሆነ እና በአሁኑ ወቅት ቤተሰቡንም የሚያስተዳድረው ከዚሁ ከስነጥበብ ሥራ በሚያገኘው ገቢ እንደሆነ ተነግሯል።
ስነጥበብ የዕለት ተዕለት ሕይወታችን አካል ነው የሚለው ወጣቱ የምንለብሰው ልብስ፣ ቀለም፣ ሁሉ የስነጥበብ አካል ነው። ስነጥበብ አሁን አድጎ በግራፊክስ ዲዛይን እና አርክቴክቸር በመደገፍ ትልቅ የገንዘብ ምንጭ እየሆነ መጥቷል። በሌሎች ሀገራት በሚሊዮን ዶላር ስዕሎች ይሸጣሉ እኛ ሀገርም አሁን አሁን ገበያው እየተነቃቃ መምጣቱንና እስከ አንድ ሚሊዮን ብር ድረስ ስዕሎች ይሸጣሉ የሚለው ወጣት ባዬ በኢትዮጵያ ደረጃም ቢሆን ሕዝቡ ለስዕል ያለው ዝቅ ያለ አመለካከት እየተሻሻለ መምጣቱን ይናገራል፡፡ ለሆቴሎች፣ ለሎጆች፣ ለመኖሪያ ቤት ሰዎች የስነጥበብ ውጤቶችን ይገዛሉ ይህም ከፍተኛ የገቢ ምንጭ ሆኗል ይላል።
ስዕል ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ባሻገር በራሱ ፍልስፍና ሀሳብ እና ስሜትን የመግለጫ መንገድ ነው የሚለው የስነጥበብ ባለሙያው ወጣት ባዬ ሰው ያደገበትን፣ የኖረበትን፣ አስተሳሰቡን፣ ባህሉን በስነጥበብ መግለጽ እንደሚቻል ያብራራል፡፡ ኢትዮጵያ በርካታ የስነጥበብ መገለጫዎች እንዳሏትና የአክሱም ሃውልቶች፤ የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት፤ የፋሲል እና የሀረር የግንብ ጥበቦች ሁሉ የቅርፅ ውጤቶች ሁሉ የሰው ልጅ የተጠበባቸው ውጤቶች መሆናቸውን ይናገራል።
ሰዓሊው እንደሚናገረው በንጉሡ ጊዜ በስዕል እና ቅርፃ ቅርፅ የንጉሳዊ ቤተሰብ በሚገልጽ መልኩ ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ በዘመነ ደርግ ከአብዮቱ ጋር የተያያዙ ስዕሎች ይሰሩ እንደነበር ከዛ በኋላ በነበረው መንግስት የስነጥበብ ዘርፉ ተዳክሞ ቆይቷል፡፡ አሁን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ለቱሪዝም ዘርፉ ትኩረት ተሰጥቶ ፓርኮች፣ መዝናኛ ማዕከላት እየተሰሩ የስዕል ኤግዚቢሽኖች ይዘጋጃሉ፤ ይህ ለኢንዱስትሪው ትርጉሙ ከፍ ያለ ነው።
ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ሁኔታ ምስቅልቅል ቢሆንም ይህንን ችግር ስነጥበብን ተጠቅሞ ማለፍ እንደሚቻል ያምናል፡፡ ኢትዮጵያ በርካታ ባህሎችና የእርስ በእርስ መስተጋብሮች የሚታይባት ሀገር ነች፡፡ ከልዩነት ይልቅ አንድነት፤ ከመለያየት ይልቅ አብሮነት የሚታይባት ድንቅ ሀገር ነች፡፡ ይሄ በአግባቡ በጥበት አልተገለጸም፡፡ አሁን በየማህበራዊ ሚዲያው የሚገለጸው የሚያራርቁና የሚያጣሉ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ይሄ ደግሞ ኢትዮጵያውያንን አይገልጽም፡፡ ኢትዮጵያውያንን የሚገልጸው አብሮነት፤ አንድነት፤ ጀግንነት እና የሀገር ፍቅር ነው፡፡
ስለዚህም እነዚህን ውድ ዕሴቶች በስነጥበቡ አማካኝነት በአግባቡ አዲሱ ትውልድ ጋር መድረስ አለባቸው፡፡ አዲሱ ትውልድ ሲነገረው በነበረው መጥፎ ትርክት ሀገሩን በአግባቡ መረዳት አልቻለም፡፡ ስለዚህም በስነጥበቡ ዘርፍ የተሰማሩ አካላት የኢትዮጵያን ማንነትና ዕሴቶች በአግባቡ ወጣቱ ጋር እንዲደርስ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ከዚሁ ጎን ለጎንም የሀገራችንን መልካም ዕሴቶች እና ውብ የተፈጥሮ ስጦታዎች በጥበብ አማካኝነት ለውጭው ዓለም ማሳየት የስነጥበብ ባለሙያው የሙያ ድርሻ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ተነግሮ የማያልቅ ታሪክ፤ ባህል፤ ወግና ውብ የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት ነች፡፡ የሰው ልጅ መገኛ፤ አመቱን ሙሉ የሚፈሱ ወንዞች ባለቤትና የድንቅ አራዊትና አዕዋፍ መገኛ ሀገር ነች፡፡ ይህ ለስነጥበቡ ትልቅ መነሻ ነው፡፡ እነዚህን ውብ ዕሴቶች በማስተዋወቅ ብቻ ከራስ አልፎ ለሀገር መድህን መሆን ይቻላል፡፡
ሆኖም ባለፉት አመታት ለስነጥበብ ትኩረት በመነፈጉና ወጣቱም ሞራሉ እንዲላሽቅ በመደረጉ ሀገሩን በቅርብ ማየት አልቻለም፡፡ ስለዚህም ወጣቱ አይኑን ከፍቶ የሀገሪቱን ውብ ገጽታ እንዲመለከት፤ እንደ አባቶቹና ቅድመ አያቶቹ በጋራ መኖርን ባህሉ አድርጎ ኢትዮጵያን እንዲያሻግር ለጥበብ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡
ማንም ሰው በተፈጥሮ አንዳች አይነት የጥበብ ተስጥኦ አለው የሚለው ወጣት ባዬ፤ ብዙ ወጣቶች ሰዓሊ የመሆን ፍላጎት እንዳላቸውና ነገር የተመቻቸ ሁኔታ እና በአጋጣሚ ባለማግኘታቸው ተሰጥኦዋቸው ተቀብሮ ይቀራል፡፡
ወጣት ባዬ እንደሚለውም ወደ ሙያው የሚቀላቀሉት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ተስጥኦ ያላቸውን ልጆች ትኩረት ሰጥቶ ሁኔታዎች ቀላል የሚያደርግላቸው የለም፡፡ ይህ በመሆኑ ችሎታ እና ተስጥኦው ያላቸው ልጆች እዛው ተቀብረው ይቀራሉ፡፡ ይህ እንዳይቀጥል የሚመለከተው አካል በትኩረት ቢሰራ መልካም ነው ይላል።
በልጅነት የነበረውን ሁኔታ ወጣት ባዬ ወደኋላ ተመልሶ ሲያስታውስ የአንደኛ ደረጃ ተማሪ በነበረበት ወቅት የስዕል ትምህርት ይሰጥ ነበር፡፡ በየትምህርት ቤቶቹ የስዕል ማዕከላት እና ክበቦች ነበሩ፡፡ እነዚህን በመቀላቀል እና በመጠቀም ተስጥኦውን ማዳበር እንደቻለ እና አሁን ላይ በትምህርት ስርዓቱ ይህ አይነት አሰራር አለመኖሩ ዘርፉን እንደጎዳው ነገር ግን ከልጅነት ጀምሮ በህፃናት ብሎም በወጣቶች ላይ መስራት ከተቻለ እንደ ሀገር ብዙ አፈወርቅ ተክሌዎችን ማፍራት እና የኢትዮጵያን ስነጥበብ ወደፊት ማራመድ እንደሚቻል ያለውን እምነት ይገልጻል።
ስነጥበብ ካደገ የፋሽን ዲዛይኑ ያድጋል፣ አርክቴክቸሩ ወይም የህንፃ ጥበቡ ያድጋል አስተሳሰብ አብሮ ያድጋል፤ ለወጣቱ የሥራ ዕድል ይፈጠራል የሚለው ወጣቱ፤ መዋያቸውን ለራሳቸውም ለሀገራቸውም ጥቅም በማይሰጥ አልባሌ ቦታ ያደረጉ ወጣቶች እና ታዳጊ ልጆች ከጥፋት እንዲድኑ ብሎም አቅማቸውን ማውጣት እንዲችሉ የሚያግዛቸው አካል መኖር እንዳለበትና ወጣት ተኮር የሆኑ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እንደ ሀገር መስፋፋት አለባቸው ይላል።
ዘመኑ ሁሉንም ነገር በቀላሉ በእጃችን ማግኘት የምንችልበት የቴክኖሎጂ ዘመን ነው። ተስጥኦ እና ፍላጎቱ ያላቸው ወጣቶች የግድ ትምህርት ቤት ሄደው መማር ሳይጠበቅባቸው የፈለጉትን የስነጥበብ አይነት ማወቅ እና ማየት ይችላሉ፤ በዚህም ጥበቡን በእርሳቸው መንገድ በመቀየር ተስጥኦቸውን ወደፊት መምጣት እና ማሳደግ እንደሚችሉ ይገልፃል።
አሁን ላይ ለስዕል ሥራው የቦታ ጥበት እንቅፋት እንደሆነበት የሚነገረው ወጣት ባዬ ነገር ግን የተለያዩ አማራጮችን ተጠቅሞ በመሥራት ታዋቂ ሰዓሊ የመሆን ህልሙን መሳካት እንደሚፈልግ እና ሀገሩን በስነጥበቡ ዘርፍ በዓለም አቀፍ መድረክ ማስጠራት እንደሚፈልግ ይናገራል፡፡ ብሎም ዓለም አቀፍ የስዕል ኤግዚቢሽኖች ላይ ተሳትፎ የስዕል ሥራዎቹን ማቅረብ ማሳካት የሚፈልገው ህልሙ እንደሆነ እና ከፈጣሪ ጋር ይሳካል ብሎ እንደሚያምን ተነግሯል።
አሁን ዓለም የውድድር መድረክ ናት፡፡ ዘመኑ የጥሎ ማለፍ ነው፡፡ ወጣቱ ያንን ተረድቶ ለጊዜያዊ ስሜት እራሱን ማስገዛት ሳይጠበቅበት ሀገሩን የሚያውቅ እና የሚጠቅም አንባቢ ትውልድ እንዲሆን እና በስነጥበቡ ብቻ ሳይሆን በሳይንስ፤ በቴክኖሎጂ ላይ በመሥራት ትኩስ ጉልበቱን ተጠቅሞ ሀገሩን ለመቀየር እና ከድህነት ለማላቀቅ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ እንዳለበት ገልጿል።
ሕይወት ፈተናዋ ብዙ ነው የሚለው ወጣት ባዬ ዓላማ እስካላቸው ድረስ ወጣቶች ለዓላማቸው መሳካት መክፈል ያለባቸውን መስዋዕትነት ሁሉ መክፈል ይኖርባቸዋል። የነገው ራዕያቸውን ከግብ ለመድረስ ቀን እና ሌሊት ሳይሉ እና ተስፋ ሳይቆርጡ መትጋት እንደሚገባቸው እና በርካታ መሰናክሎች ቢኖሩም ነገን አሻግሮ መመልከት እንዳለባቸው መልዕክቱን ያስተላልፋል።
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ሰኔ 9/2015