በየዓመቱ የሚካሄደው ጉማ የፊልም ሽልማት ከተጀመረ እነሆ ዘንድሮ 9ኛ ዙር ላይ ደርሷል፡፡ ባለፈው አርብ ሰኔ 2 ቀን 2015 ዓ.ም የ9ኛው ዙር የጉማ ፊልም አሸናፊዎች ታውቀዋል፡፡
ጉማ የፊልም ሽልማት የፊልም መነቃቃት ይፈጥራል፤ ፈጥሯልም፡፡ ምንም እንኳን ሽልማቱ በተሰሩ ፊልሞች ላይ ቢሆንም፤ ወደፊት በሚሰሩ ፊልሞች ላይ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል፤ መነቃቃትንም ይፈጥራል፡፡
የፊልም መነቃቃት ይፈጥራል ሲባል፤ ዕጩዎች ከቀረቡበት ጊዜ ጀምሮ ስለፊልም ይወራል፡፡ ስለተዋናዮች ብቃት ይወራል፤ ስለፊልሞች ይዘት ይወራል፡፡ የትኛው ፊልም ይሸለም ይሆን በሚል ፊልሞችን የመዳሰስ ሥራ ይሰራል፡፡ በተለይም በዕጩነት የቀረቡ ፊልሞች ስም ሲዘረዘር፤ ፊልሞችን ያላዩ ሰዎች አፈላልገው እንዲያዩት ያደርጋል፡፡
የተዋናዮች ማንነት ይታወቃል፡፡ በተለይም ወጣት ተዋናዮች ሥራዎቻቸውና ብቃታቸው እንዲታይላቸው ያደርጋል፡፡ ጉማ የፊልም ሽልማት እንቅስቃሴ ከሚጀመርበት ሰሞን ጀምሮ በመገናኛ ብዙኃንም ሆነ በመድረኮች ስለፊልም ይወራል፣ ስለዕጩ ተዋናዎችና ሥራዎቻቸው ይወራል፡፡ በዚህ ሁሉ ውስጥ የፊልም መነቃቃት እየተፈጠረ ነው ማለት ነው፡፡ በአዘቦት ስለፊልም የማይሰሩ መገናኛ ብዙኃን ሁሉ በዚህ ሰሞን ይሰራሉ ማለት ነው፡፡ እግረ መንገድም አንዳንድ ፊልሞች ላይ ዳሰሳዎች ይሰራሉ ማለት ነው፡፡
በሌላ በኩል ጉማ የፊልም ሽልማት የተለያዩ ዘርፎች ስላሉት፤ የተለያዩ የፊልም ሙያዊ መመዘኛዎችን ወደ ፊልሙ ዘርፍ የሚገቡ ሰዎች ይማሩበታል ማለት ነው። ፊልም ሲባል ብዙዎቻችን የምናውቀው ያለቀለትን ሥራ ነው፡፡ ዘርፎቹ ተዘርዝረው ስናየው ግን ከጀርባው ብዙ ቴክኒካል ነገሮች እንዳሉ እናያለን፡፡ ይዘቱን ብቻ ሳይሆን ከማጀቢያ ሙዚቃው ጀምሮ የሜካፕ ባለሙያዎችን ሁሉ ብቃታቸውን እናይበታለን ማለት ነው፡፡
እነዚህን የፊልም ጥበቦች ብዙዎቻችን ልብ ስለማንላቸው በጉማ የፊልም ሽልማት ምክንያት ትኩረት ይሰጣቸዋል ማለት ነው፡፡ እኛም ስለፊልም ያወራነው በዚሁ ሽልማት ምክንያት ነው፡፡
ፊልም በተለያዩ ዘርፎች ቢከፈልም፤ የሰውን ልጅ የአሁኑን የትናንቱንና የነገውን ሁኔታውን የሚያስተላልፍበት መገናኛ መንገድ ነው፡፡ የፊልም ሥራዎቻቸው ባደጉት በትላልቆቹ ዓለም ደግሞ ያሉበትን ሉዓላዊነት ማንፀባረቂያ፣ ያላደጉትን አገራት ማስፈራርያ እና መማረኪያ ንብረታቸው ነው፡፡ ራሱን የቻለ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ነው፡፡
ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ ግን፤ ኢትዮጵያና ፊልም ያላቸው ትውውቅ ከአንድ ክፍለ ዘመን የተሻገረ ቢሆንም የዘመናዊ ፊልም ታሪኳ ግን ከሃያ ዓመታት ያልተሻገረ ነው፡፡
ፊልም እንደ ኢንዱስትሪ መታየት ጀምሮ በብዙ ጎኖች አልፎለት በሲኒማ ቤቶች ደረጃ መታየት የጀመረው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ነው፡፡ እንደ ጉዲፈቻ፣ የበረዶ ዘመን፣ ስላንቺ፣ የወንዶች ጉዳይና የመሳሰሉት ፊልሞች የኢትዮጵያ ዘመናዊ የፊልም ታሪኳ ውስጥ በምሳሌነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
እነዚህን ፊልሞቻችንን ይዘን ጉማ የፊልም ሽልማት ተጀመረ፡፡ ከሃምሳ ምናምን ዓመታት በፊት በሚሼል ፓፓታኪስ የተሠራው እና በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ባለቀለም ፊልም በሆነው ‹‹ጉማ›› ፊልም መጠሪያውን ያደረገው ጉማ የተሰኘው ሽልማት ስለፊልሞች በሰፊው እንዲወራ አስደረገ፡፡
ሽልማቶች ለፊልም ኢንዱስትሪው እያበረከቱት ያለውን አስተዋፅዖ ማንም ወደ ፊልሙ ተጠግቶ የማያውቅ እንግዳ ሰውም ሊያውቀው የሚችለው ጉዳይ ነው፤ ሽልማትና ምሥጋና መነቃቃትን ይፈጥራል፡፡ የተለያዩ ጉዳዮችን የሚዳስሱ ፊልሞችን እየያዘ የሚመጣው ጉማ የፊልም ሽልማትም በየዓመቱ ደመቅ ባለ መልኩ ነው የሚከናወነው፡፡
በነገራችን ላይ ጉማ የፊልም ሽልማት በ2012 ዓ.ም የተከሰተውን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በማድረግ አልተካሄደም ነበር፡፡ በ2013 ዓ.ም ነው እንደገና በደማቁ የተጀመረው፡፡
በኢትዮ ፊልም ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት የሚዘጋጀው ጉማ ፊልም ሽልማት ጥሩ ብቃት ላሳዩ ፊልሞች እና አርቲስቶችን ክብርና እውቅና መስጠት ዓላማው እንዳደረገ አዘጋጆች በተለያየ ጊዜ ተናግረዋል።
ተደጋጋሚ ወቀሳ የሚሰነዘርበት የኢትዮጵያ የፊልም ኢንዱስትሪ እንዲህ አይነት የማነቃቂያ ሽልማቶች ያስፈልጉታል፡፡ የፊልም ኢንዱስትሪውም ወቀሳው ብዙ ስለተደጋገመበት እንጂ በዓለም አቀፍ ደረጃ የታዩ ተወዳጅ ፊልሞችም ተፈጥረዋል፡፡
በተለይም ባለፉት 20 ዓመታት የጎሉ እንቅስቃሴዎች ታይተውበታል። ለምሳሌ፤ በጀርመን ታዋቂ በሆነው ዓለምአቀፍ የፊልም ውድድር በርሊና መድረክ እና በዩናይትድ ስቴትሱ የሰንዳንስ ፊልም ፌስቲቫል ላይ ሽልማትን ያገኘው የኢትዮጵያው «ድፍረት» የተባለው ፊልም ተጠቃሽ ነው።
በፊልም ስራ የከፍተኛ ደረጃ ትምህርቱን በአሜሪካ ያጠናቀቀውና በርካታ ፊልሞችን እንደሰራ የሚነገርለት የጉማ ፊልም ሽልማት ዋና አዘጋጅ አቶ ዮናስ ብርሃነ መዋ፤ የጉማ ፊልም ሽልማት የተጀመረ ዓመት ለዶቼቬሌ እንደተናገረው፤ ዝግጅቱ የፊልም ጥበብንና ጥበበኞችን ለመደገፍ የታሰበ የሽልማት ሥነ ሥርዓት ነበር፡፡ እነሆ አሁን እዚህ ደረጃ ላይ ደርሶ ብዙ መነቃቃትን ፈጠረ፣ ፊልሞችም በጥራት መሰራት ጀመሩ፡፡
በጉማ የፊልም ሽልማት ሥነ ሥርዓት ላይ በተለያዩ ዘርፎች ከሚሰጠው ሽልማት በተጨማሪ ደግሞ፤ ለውድድር የማይቀርብ ዘርፍ አለ፤ ይህ ዘርፍ ‹‹የሕይወት ዘመን ተሸላሚ›› ነው፡፡ የሕይወት ዘመን ተሸላሚ የሚሆነውን ሰው መርጦ ማውጣት ነው።
የመጀመርያው የጉማ ፊልም ሽልማት ላይ የሕይወት ዘመን ተሸላሚ የነበሩት፤ ከአርባ ዓመት በላይ በፊልም ጥበብ ስራ ላይ የቆዩትና የመጀመርያው የኢትዮጵያ ፊልም ዳይሬክተር ሚሼል ፓፓታኪስ ናቸው።
ሚሼል ፓፓታኪስ፤ አባታቸው አዲስ አበባ ውስጥ የፊልም ቤት የከፈቱ የግሪክ ዜጋ ሲሆኑ እናታቸው ደግሞ ኢትዮጵያዊትና ትውልዳቸውም ኢትዮጵያ ውስጥ ነው።
የፊልም ሽልማት ሥነ ሥርዓቱን ጉማ ሲል መጠርያ የሰጠው የሥነ ሥርዓቱ ዋና አዘጋጅ እና የፊልም ስራ ባለሙያው ዮናስ ብርሃነ መዋ በወቅቱ ለዶቼቬለ እንደገለጸው፤ በሚሼል ፓፓታኪስ የተሰራው ጉማ ፊልም፤ ስያሜውን ከአፋን ኦሮሞ ቋንቋ እንደወሰደና፤ ካሳ ማለት እንደሆነ ተናግሯል፡፡
ፊልሙ በኦሮሞ ማህበረሰብ ውስጥ ስላለው የግጭት አፈታት ባህል ላይ የሚያውጠነጥን ዘጋቢ ፊልም ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ፊልሙ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ሙዚየም ወመዘክር ውስጥ ይገኛል፡፡
ጉማ የፊልም ሽልማት ሥነ ሥርዓት አሁን አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት እየታየ ላለው የቪዲዮ ፊልሞች ምርት መሰረት የጣሉትን ሰዎች ያስታወሰ፤ በዳኝነትም ሆነ አንጋፋ የፊልም ተዋናዮችን ታሳቢ ያደረገ መድረክ ነው፡፡
የፊልም ኢንዱስትሪው እንዲያድግና፤ በኢኮኖሚው ውጤታማ እንዲሆን ሁሉም የተቻለውን ጥረት እንዲያደርግ ያነሳሳል፡፡ ሆኖም ግን ከሚመለከታቸው አካላትም ድጋፍ መደረግ አለበት፡፡ ምክንያቱም ፊልሞች የኢትዮጵያን ባህል በማስተዋወቁም ረገድ ሆነ ዓመታዊ ገቢን ከፍ እንዲል በማድረግ ከፍተኛ ሚና ይኖራቸዋል፡፡
በኢትዮጵያ የፊልም ስራ ዕድገት፣ ጥራትና ኢትዮዮጵያዊ ደረጃን የጠበቀ እንዲሆን የፊልም ሰራተኛ ማህበሩ ጥረት እያደረገ መሆኑንም የዘርፉ ሰዎች ሲናገሩ ቆይተዋል፡፡ ስለዚህ እንዲህ አይነት ሽልማቶች፤ መንግሥትንም፣ የፊልም ባለሙያውንም፣ የፊልም ተመልካቹንም መነቃቃት ይፈጥሩለታል ማለት ነው፡፡
የፊልም ተመልካቹ ላይ ግን አንድ ትዝብት እናጋራ። ሁልጊዜ የፊልም ኢንዱስትሪውን መውቀስ ብቻውን ለውጥ አያመጣም፡፡ የኪነ ጥበብ ዘርፍ እና ስፖርት አንፃራዊ ነፃነት ስላለው ይመስላል ሰዳቢው ብዙ ነው፡፡ ከማድነቅ ይልቅ መተቸቱ የሚቀል ይመስላል፡፡ እርግጥ ነው ወቀሳ ስለበዛበት ነው ያላደገ ማለት አይቻልም፤ ቢሆንም ግን ጥሩ የተሰሩ ፊልሞችን ማድነቅና እውቅና መስጠት ደግሞ የበለጠ ያበረታታል። ስለዚህ እንደ ጉማ አይነት የፊልም ሽልማቶች ሲደረጉ ከፊልም ባለሙያው በተጨማሪ ተመልካቹም ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል፡፡
ለምሳሌ፤ በባለፉት ዓመታት ሁሉ የተደረጉ የጉማ ፊልም ሽልማት አስተያየቶችን እናስታውስ፡፡ በመድረኩ በተለያየ ዘርፍ ከተሸለሙ ፊልሞች ይልቅ አጀንዳ ሆኖ የነበረው የሴት አርቲስቶች አለባበስ ነበር። የተሸለሙትን ፊልሞች የይዘትም ሆነ የቴክኒክ ጥራት ከመገምገም ይልቅ የአርቲስቶች አለባበስ የሳምንት አጀንዳ ሆኖ ይቆያል፡፡ እንዲያውም አሸናፊ የሆኑ ፊልሞች እስከሚረሱ ድረስ ዋናው መከራከሪያ አለባበስ ሆኖ ይታያል፡፡ የዕለቱ የመድረክ አለባበስ ለዚያ ቅጽበት እንጂ በተሸለሙበት ፊልም ላይ የሚጨምረውም ሆነ የሚቀንሰው ነገር የለውም፡፡
በአጠቃላይ የአገራችን የፊልም ኢንዱስትሪ የሚያድገው በኪነ ጥበብ ባሙያውም፣ በታዳሚውም በመንግሥትም የጋራ ፍላጎት ነውና ከሁላችንም የሚጠበቀውን እናድርግ! በመጨረሻም በዘንድሮው 9ኛው የጉማ ፊልም ሽልማት የተሸለሙ የፊልም ዘርፎችንና ባለሙያዎችን እናስታውስ፡፡
ምርጥ አጭር ፊልም፡-
የጉድ ሀገር መንገድ /ብስራት ተስፋ
ምርጥ የተማሪ አጭር ፊልም፡- መሐይማን /አማኑኤል ተሾመ
ምርጥ ተከታታይ ኮሜዲ ድራማ ፡- አስኳላ
ምርጥ ውርስ ትርጉም ድራማ፡- አደይ
ምርጥ ዶክመንተሪ፡- ባሌ ብሄራዊ ፓርክ /አዚዝ አህመድ
ምርጥ ውርስ ድራማ ተዋናይት፡- በእምነት ሙሉጌታ / አደይ
ምርጥ ውርስ ድራማ ተዋናይ፡- አለማየሁ ታደሰ / አጋፋሪ
ምርጥ የፊልም ሙዚቃ፡- የሱፍ አበባ
ምርጥ ስኮር፡- ረመጥ / ብሩክ አሰፍ
ምርጥ ሜካፕ፡- ተሚማ ሁላላ / ረመጥ
ምርጥ ፊልም ፅሁፍ፡- ረመጥ / ዳንኤል በየነ
ምርጥ ቅንብር፡- የሱፍ አበባ /እስክንድር ተፈራ
ምርጥ ሲኒማቶግራፊ፡- የሱፍ አበባ / ዋለልኝ አደገ
ምርጥ ተስፋ የተጣለበት ተዋናይነት፡- ክሱት / እየሩሳሌም አሰፍ
ምርጥ ተስፋ የተጣለበት ተዋናይ፡- ፊናፍ / ብሩክ ግርማ
ምርጥ ረዳት ሴት ተዋናይት፡- የማር ውሃ / መስከረም አበራ
ምርጥ ረዳት ተዋናይ፡- ጥላዬ / እንግዳሰው ሀብቴ
ምርጥሴት ተዋናይት፡- ክሱት / ጠረፍ ካሳሁን
ምርጥ ወንድ ተዋናይ፡- ሄኖክ በሪሁን /ረመጥ
ምርጥ ዳይሬክተር፡- ረመጥ/ ዳንኤል በየነ
ምርጥ ፊልም፡- የሱፍ አበባ /ለገሰ ገነቱ
የህይወት ዘመን ተሸላሚ፡- አርቲስት ኪሮስ ኃይለስላሴ
የሔርሜላ አሸናፊ፡- ገነት ከበደ
አርአያ ሰብ ከያኒ፡- አርቲስት መሰረት መብራቴ
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ሰኔ 8/2015