አብዛኞቻችን ውበት ምንድነው የሚል ጥያቄ ቢቀርብለን በአፍንጫ ሰልካካነት፣ በፀጉር እርዝመትና ዘንፋላነት፣ በቁመና እና በመሳሳሉት መገለጫዎች የራሳችንን አመለካከትና አተያይ ልናስቀምጥ እንችላለን። ይሁን እንጂ ውበት አንገተ መለሎነት (ረጅምነት) ነው ብንባል “እንዴት ሆኖ?” በማለት በግርምት ልንጠይቅም እንችላለን፡፡ ለዚህም ይመስላል “ውበት እንደተመልካቹ ነው” እየተባለ የሚተረተው፡፡
ዛሬ ላወጋችሁ ያሰበኩት ስለ አንገት ርዝመት ነው፡፡ ‹‹አንገተ ረጅም›› ስንል መቼው ቀድሞ ወደ አእምሮአችን በፍጥነት የሚመጣው ቃል ‹‹ቀጭኔ›› በመባል የምትታወቀው እንሰሳት ትመስለኛለች፡፡ ነገሩ ግን እንዲህ አይደለም፡፡ ከሰው ልጆችም ቁጥራቸው ጥቂት ይሁን እንጂ በተፈጥሮ ረጅም አንገት የተቸራቸው ሰዎች መኖራቸው እንመለከታለን፡፡ በተለይ በተፈጥሮ በተቸሩት ረጅም አንገት ከሌሎች ሰዎች በተለየ መልኩ ማራኪና የሰውን ቀልብ የሚስቡ ቆነጃጅት ሞልተዋል፡፡
ረጅም አንገት ካላቸው የዓለም ሕዝቦች መካካል በማይናማርና በታይላንድ (Myanmar and Thailand) የሚገኙ ፓዳኡግ (Padaung) በመባል የሚታወቁ ጎሳዎች አንገተ ረጅም እንደሆኑ ይነገራል፡፡ ከእነዚህ ጎሳዎች መካካል አንገተ ረጅም ተብላ የተመዘገበችው የአንዲት ሴት የአንገት ርዝመት 40 ሳንቲሜትር (15 inches) መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
ወደ አፍሪካ ስንመጣ በቅርቡ አፍሪካውያን የድንቃ ድንቅ መዝገብ / ‹‹ Book of African Records››/ በመባል የሚታወቀው ድርጅት እንዳሳወቀው እስካሁን ድረስ ባለው ሁኔታ በአንገተ ርዝመት ከአፍሪካ የመጀመሪያዋ ሪከርድ የያዘች ሴት በኢትዮጵያ መገኘቷን አሳውቋል። ከኢትዮጵያ የረጅም አንገት ባለቤት በመሆን እስካሁን ያለውን የአፍሪካን ክብረ ወሰን የያዘችው ኢትዮጵያዊት ሞዴል ሕይወት ባህሩ ትባላለች፡፡
ሞዴል ሕይወት ባህሩ ተወልዳ ያደገችው ምዕራብ ሐረርጌ ገለምሶ በሚባል የምትታወቅ ቦታ ነው። እድሜዋ ለትምህርት ሲደርስም ከእኩያቿ ጋር ወደ ትምህርት ቤት በመግባት የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን እዚያው ገለምሶ ተከታትላለች፡፡
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን እንዳጠናቀቀችም የከፍተኛ ደረጃ ትምህርቷን ለመከታታል ያስችላት ዘንድ ወደ አዲስ አበባ ከተማ የመጣችው ሞዴሊስቷ፣ አዲስ አበባ መምጣቷ ከትምህርቱ ጎን ለጎን የትወና ጥበባትንና የሞዴሊኒግ ትምህርት እንድትማር በር ከፍቶላታል፡፡
በሞዴል ትምህርት ላይ እያለች እስታር ሞዴል ኢን አፍሪካ (star model in Africa) በመባል በሞዴልነት እንደተመረጠች ትናገራለች፡፡ ሞዴል ሕይወት እንደምትለው፤ እስታር ሞዴል ኢን አፍሪካ በመባሏ በፋሽን እና ፎቶ ሞዴልነት ለመስራት እድሉን አግኝታለች፡፡ ይህንን እድልን በመጠቀም በጣሊያን፣ በፈረንሳይና በመሳሳሉ የተለያዩ ዓለም አገራት በመዞር የፋሽንና ፎቶ ሞዴሊንግ ሥራዎችን እየሰራች ትገኛለች።
‹‹እውነት ለመናገር እኔ ሞዴል እሆናለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር ›› የምትለው ሕይወት ሰዎች ሲያይዋት ሞዴሊንግ እንድትሞክር ቢገፋፏትም በትምህርት ላይ ስለነበረች ብዙ ትኩረት አልሰጠችውም ነበር፡፡ ትምህርቷን እንደጨረሰች በሰዎች ግፊት የሞዴሊንግ ሙያው ብትጀምር አሁን ላይ ስኬታማ መሆን እንደቻለች ትናገራለች፡፡
በዚህ መልኩ ‹ሀ› ብላ የጀመረችውን የሞዴሊኒግ ሥራዋን አጧጡፋ በቀጠለችበት ወቅት ከአፍሪካ አንገቷ ረጅም ሴት በመባል የአህጉሪቱን የድንቃ ድንቅ መዝገብ / ‹‹ Book of African Records››/ ላይ በመስፈር ሰርተፊኬት ማግኘቷን ትገልጻለች፡፡ የሞዴል ሕይወት ባህሩ የአንገት ርዝመት ፊት ለፊት 14 ሳንቲ ሜትር ሲሆን ከጎን ደግሞ 18 ሳንቲሜትር ርዝመት አለው፡፡
‹‹በቁመቴ ሁሉም ሰው ስለሚነግረኝ ሞዴል እንደምሆን እንዳሰበው አድርጎኛል፤ ነገር ግን የአንገቴ ርዝመት ግን የተለየ ነው ብዬ በፍጹም አስቤው አላውቅም ነበር›› የምትለው ሞዴሏ፤ በድንገት ጓደኞቿ በአፍሪካ ድንቃ ድንቅ መዝገብ ላይ እንድትመዘገብ እንዳነሳሷት ትገልጻለች፡፡ ‹‹በወቅቱ የአንገቴን ርዝመት በአፍሪካውያን የድንቃ ድንቅ መዝገብ እንዲመዘገብ በፎቶ ግራፍ ስልከው ፎቶዬን ያየው ሰው ማመን አልቻለም ነበር፤ በአካል ሲያየኝ ነው ያረጋገጠው›› ትላላች ሞዴል ሕይወት፡፡
‹‹ቀደም ሲል በኛ አገር እንደዚህ ለየት ያለ ተፈጥሮ ሆነ ችሎታ ያላቸውን ሰዎች መመዝገብ ነገር ብዙ አልተለመደም ነበር›› የምትለው ሕይወት፤ አሁን ላይ የተጀመረው የተለየ ተፈጥሮና ተሰጦ ያላቸው ሰዎች የማድነቁና የማበረታታት ሥራ ጥሩ ጅምር መኖሩን ትናገራለች፡፡
ሞዴሏ እንደምትለው፤ አሁን ላይ በሙያው የተለያዩ የዓለም አገራት በምትጓዝበት ጊዜ ኢትዮጵያ እያስተዋወቀች ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በቱሪዝሙ መስክ ሆነ በሌሎች ዘርፎች በርካታ የሚተዋወቁ ነገሮች ስላሉ ማስተዋወቁ ሥራ ትሰራለች፡፡ አሁን ላይ ደግሞ አንገቷ ረጅም በመባል የአፍሪካ ድንቃድንቅ መዝገብ / ‹‹ Book of African Records››/ ›› ያገኘችውን እውቅና በመጠቀም ከዚህ በበለጠ አገራን ለማስተዋወቅ ትጠቀምበታለች፡፡
‹‹እስካሁን ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ ላይ የምትታወቀው በጦርነትና በረሃብ ነው›› የምትለው ሕይወት፤ በሞዴሊንግ ሙያ ዓለም ላይ በምትዞርበት ጊዜ ያጋጠማት ይሄው እንደነበር ገልጻለች፡፡ ይህንን አመለካከት በመቀየር የአገራችንን ገጽታ በመገንባት ረገድ ተባብረን ከሰራን አገራችንን ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማድረስ እንችላለን ትላለች፡፡
ሞዴሏ እንደምትለው፤ ሴት መሆን በራሱ ፈተና አለው፡፡ ሴቶች ምንም አይነት ችሎታ ቢኖረን ‹አትችይም አታረጊውም› የምንባልበት ሁኔታዎች ይበዛሉ፡፡ ሴቶች ከሁሉ በፊት በራሳቸው ማመን አለባቸው፡፡ በራሳቸው አምነው እችላለሁ ብለው ከተነሱ ምንም ነገር የማድረግ አቅሙ እንዳላቸው መረዳት ይችላሉ፡፡ በተለይ ወጣት ሴቶች እንችላለን የሚለው አቅም ሰንቀው ሊነሱ ይገባል።
ሞዴሏ ‹‹እግዚአብሔር ሲፈጥርን ድንቅ አድርጎ የፈጠረን በመሆኑ በምን ነገር ማፈር የለብንም›› ትላለች። አንዱ ያለው ሌላው፤ ላይኖረው ይችላል፤ ይሄ የኔ ስጦታ ነው ብሎ ተቀብሎ ወደፊት በመውጣት ያለ ነገር ለዓለም ማስተዋወቅ ተገቢ ነው ብሏ እንደምታምንም ትናገራለች፡፡
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ሰኔ 5/2015