
ስኬታማ እንደምትሆንና እንደማትሆን የሚጠቁምህ ነው። የነገ ህይወትህ የጀርባ አጥንት ነው። በህይወታቸው ደስተኛና ስኬታማ የሆኑ ሰዎችም በዚህ እሳቤ ይስማማሉ። በርካታ ምርምሮችና የጥናት ውጤቶችም የስኬታማ ሰው ቁልፍ ፀባይ እሱ መሆኑን ይመሰክራሉ-ራስን መግዛት ወይም /self discipline/።
ስኬት ከመቶ ቢታረም ዘጠና ከመቶው ዲስፕሊን ነው። ራስን መግዛት ከትናንሽ ልፋቶች ጀርባ ህልምህን ለማሳካት የሚገፋህ ኃይል ነው። ከዚህ ውጪ የምታልመው ህልም ጭንቅላትህ ውስጥ የቀረ ምስል ብቻ ሆኖ ይቀራል። መሬት ማውረድ አትችልም። ህልምህን መሬት የምታወርደው ዲስፕሊን ካለህ፣ ራስህን ከተቆጣጠርክና ራስህን ከገዛህ ነው።
ልክ ስትነቃቃ ወይም የመስራት ፍላጎት ሲኖርህ የምታደርገው ነገር ትልቅ ለውጥ አይሰጥህም። ስፖርት መስራት ልትጀምር ትችላለህ። ማንበብም እንደዛው። አዲስ ቋንቋ ትለማመዳለህ። ራስህን ማሳደግ ትጀምርና የሆነ ሰዓት ላይ ታቆማለህ። አየህ ዲስፕሊን ያለው ሰው አያቆምም። ምቾት ባይኖረውም የጠበቀውን ትልቅ ለውጥ ቶሎ ባይሰጥህም የዛሬውን ቅፅበታዊ፣ ጊዜያዊ ደስታህን አዘግይተህ ለነገህ ትልቁ እርካታህ ዋጋ የምትከፍልበት መንገድ ነው ዲስፕሊን።
የተሻለ ህይወት አላቸው፣ ትላንትናቸውን ቀይረውታል፣ ከነበሩበት ችግር ወጥተዋል የምትላቸውንና የምታከብራቸውን ሰዎች ሁሉ አስተውል። ውጫዊ ገፅታቸው ላይ ከሚታየው ደስታ፣ ጥንካሬና እርካታ ጀርባ አንድ ተመሳሳይ ነገር አላቸው። ዲስፕሊን! እነዚህ ሰዎች ትልቅ ደረጃን በአንዴ ካልወጣን ብለው ክችች ከማለት ይልቅ ትናንሽ እርምጃዎችን በልካቸው ሰርተው በየቀኑ እነዚህን ደረጃዎች እየወጡ ከግባቸው የደረሱ ናቸው። ወሳኙን ነገር አውቀውታል። ስኬት የአንድ ቀን ተግባር ብቻ እንዳልሆነ ገብቷቸዋል። ራሳቸውን መግዛት ላይ ተክነውበታል። ህልማቸው ጋር ለመድረስ በሃሳብ ከመኳተን ይልቅ ዲስፕሊንን መጓጓዣቸው አድርገውታል።
በርግጥ በቀላሉ በወሰድናቸው እርምጃዎች በምናገኘው ደስታ ልንሳሳት እንችላለን። የምንኖርባት ዓለም ራሱ አንድን ነገር ለማድረግ አቋራጭ መንገዶችን ላሳያችሁ በሚሉ ሰዎች የተሞላች ነች። ቀላል የተባለው ነገር ሲነገድ የሚዋልባት ገበያ ነች ዓለም። ምንም ብታገኘውም ታዲያ ከዚህ ገበያ ቀላሉን አትምረጥ። እውነተኛው ስኬት በአቋራጭ አይገኝም። የራስህ የሆነውን ከፍታ የምታገኘው በዚህ ቀላልን በምትሰብክ ዓለም ላይ አንተ ከባዱንም እንደምትቋቋም ስታሳይ ነው።
ምን ያህል ለአላማህ ፅኑ እንደሆንክ ስታስመሰክር፣ አሻግረህ ማየት ስትለምድ፣ ሲደክምህ፣ ሰውነትህ ለስራ ሳይጋበዝ ሲቀር መተኛት፣ ቲቪ ማየት እያማረህ አንተ ግን ስሜትህን አሸንፈህ ስለ አላማህ አንድ ርቀት ስትጓዝ ያኔ ትክክለኛውን ከፍታ ታየዋለህ። ይህ አይነት ራስን የመግዛት ጥንካሬ የሚከተሉትን አምስት ቅደም ተከተሎችን አትርሳ።
1ኛ. ራስህን በሚገባ አጥና
በየቀኑ የምታደርገውን ነገር አስተውል። ውሎህ ምን ይመስላል? ዓላማህስ ምንድን ነው ? ምን አቀድክ? የእለት ተእለት ተግባርህ ምንድን ነው? ከዓላማህ ጋር አብሮ የሚሄድ አንድ እንኳን ድርጊት በየቀኑ ታደርጋለህ? ሁሌም ቢሆን የቀን ውሎህን ለነገ ስኬትህ መሰረት እንዲሆን አድርገህ ቅረፀው። ከዛሬው ግዜያዊ ምቾትህ ይልቅ የነገው የረጅም ግዜ ድሎትህ ይበልጣል በልና የሩቁን አስቀድመው።
ስታስብ የምትውለው ምንድን ነው? ምክንያቱም አስተሳሰብ ተግባርን ይወስናል። ተግባር ደግሞ መድረሻህን ይወስናል። ግልፅ የሆነው ግብህ ምን እንደሆነ አስብ። እዚያ ላይ ለመድረስ የሚያስፈልግህን ለውጥና ተግባር ለእያንዳንዱ ቀን አከፋፍለው። ስራህን በትንሹ ጀምር። ለዚህ እቅድህ ቆራጥ ሁን። በአጓጊ ነገሮች አትሰናከል። ይሔ ነው ዲስፕሊን ማለት።
ውሎህን ስትመርጥ አስተሳሰብህን ስታቃና ታዲያ አብረው የሚውሉትን ሰዎች አስተውል። ምክንያቱም አንተ ብዙውን ግዜ አብረሃቸው ከምትውላቸው አምስት ሰዎች አማካይ ነህ። ከአምስት ሰነፍ ሰዎች ጋር የምትውል ከሆነ ስደስተኛው ሰነፍ አንተ ነህ። ከአምስት ጎበዝ ሰዎች ጋር ከዋልክ ግን ስድስተኛውም ጎበዝ ሰው አንተ ነህ።
ያንተን ማንነት የዛሬው ውሎህ ይወስነዋል። ከሚያጠነክሩህ፣ ራስህን ለመግዛት ያለህን ተነሳሽነት የሚደግፉ ሰዎች ጋር መዋል አለብህ። ራስን መግዛት ግን ደስታ የሌለውና የተጨቆነ ህይወት መምራት ማለት አይደለም። ብዙ ግዜ ዲስፕሊን ወይም ራስን መግዛት የሚለው ሃሳብ ሲነሳ ብዙዎች ‹‹እኔ እንደዚህ የተጨናነቀ ሕይወት መኖር አልፈልግም›› ይላሉ። ሃሳብንና ስሜትን ከመገደብና ራስን ከማስጨነቅ ጋር ያያይዙታል።
ነገር ግን ራስን መግዛት ማለት ከነገ ህልማችን ጋር አብረው የሚሄዱ ትናንሽ ምርጫዎችን በየቀኑ መምረጥ ነው። አሁን ልደሰት ካልክ ስሜትህ ሊያረኩልህ የሚችሉ በርካታ ነገሮች አሉ። ነገ ልደሰት ካልክ ግን አሁን ዋጋ እንድትከፍል የሚያስገድዱ ብዙ ነገሮች አሉ። ያንን ማመጣጠን ነው እንግዲህ ዲስፕሊን ወይም ራስን መግዛት ማለት። የማትጨነቅበትና ትክክለኛ ነፃነትን የምታገኝበትን ህይወት የምትኖረው በዚህ መንገድ ብቻ ነው። ይህን መንገድ ከተረዳኸው መጨነቅ ሳይሆን በማመስገን ትኖራለህ።
2ኛ.ወስን
የህይወትህን ኃላፊነት በራስህ ላይ ጣል። አንተን በሚመለከቱ እድገቶች ላይ አተኩር። ድክመትህን ለይተህ አውቀህ ያንን ለማስተካከል ወስን። ታዲያ ውሳኔህ ወጥነት ይኑረው። በህይወትህ ሁለት ምርጫዎች አሉህ። አንደኛው በትክክለኛው መንገድ ፀንቶ መሄድ ወይ ደግሞ ተስፋ ቆርጦ መተው ነው። ሁለቱም ከባድ ምርጫዎች ናቸው። በትክክለኛው መንገድ ሄደን ህልማችንን ለማሳካት የምንታመመው እስኪሳካ ነው። በተስፋ መቁረጥና በመቆጨት የምንኖረው ህይወት ግን የዘላለም ህመም ነው፤ ፀፀት ነው።
በዛሬው ሁኔታህ ላይ ተመስርተህ ሳይሆን የነገውን ተስፋህን አይተህ ወስን። አየህ ግዚያዊ ደስታ አይሸውድህም። ነገን አስቀድም ማለት ነው። ሁሌም ዲስፕሊንን እንደመርህ አድርገህ ተቀበለው። ብዙ ሰዎች ለመለወጥ ተአምር ይጠብቃሉ። ይህ ግን የማይሆን ነገር ነው። ተአምር ያለው በየአንዳንዱ ቀንህ ውስጥ ነው። ትክክለኛ ውሳኔ መወሰንህ ውስጥ ነው ተአምር ያለው። ያለበለዚያ ከሰማይ የሚወርድ ከምድር የሚፈልቅ ተአምር የለም።
አንድ ሃውልት ቀራፂ ድንጋዩን ለመቅረፅ በሚጠቀመው ሹል መዶሻ የሚያሳርፈው አንድ ምት ምን አልባት ሊሰራ ላሰበው ሃውልት ምንም ጥቅም የሌለው ሊመስል ይችላል። ነገር ግን እነዚህ ተደጋጋሚ ትናንሽ ምቶች ሃውልቱን ይቀርፁታል። እኛም በየቀኑ የምናሳርፈው የዓላማችን ትናንሽ ምቶች ናቸው ህይወታችንን የሚቀርፁት። ትናንሽ እርምጃዎች ኃይል የሚኖራቸው ያለማቋራጥ በፅናት ስናደርጋቸው ነው። ከግዜ ወደ ግዜ ሲጠራቀሙ ሊሰጡን የሚችሉት ውጤት ተአምር ነው።
ለምሳሌ በቀን ለሰላሳ ደቂቃ ምንሰራው ስፖርት ምን አልባት የሚታይ ለውጥ ላያመጣ ይችላል። ነገር ግን በነዚህ ትናንሽና ተደጋጋሚ እርምጃዎች ውስጥ ቁልፉ ጉዳይ የእኛ ፅናት ነው። ታዲያ ስለምናደርገው ነገር ቀጣይነት ብቻ ሳይሆን ጠቃሚነትም ልናስተውል ይገባል። ገበሬ የሚዘራውን ነገር መርጦ እንደሚዘራ ሁሉ አንተም የምትከተለውን ልማድ በትኩረት መምረጥ አለብህ። እያንዳንዱ እርምጃህ ማቅናት ያለበት ወደ ዓላማህ ብቻ ነው። 3ኛ.ዓላማ ያዝ
የቤተሰብ፣ የህይወት፣ የስራና የሁሉም ዓላማ ሊኖርህ ይገባል። አለበለዚያ ዓላማ ያለው ሰው አገልጋይ ነው የምትሆነው። ገንዘብ፣ መኪና፣ ልብስ ብቻ አይደለም መቅደም ያለበት። እነዚህ የልፋትህ ክፍያዎች፤ የጥረትህ ጭራዎች ናቸው። አንተ በጣም በጣርክ ቁጥር ሲሳካልህ እነዚህ ነገሮች ይከተሉሃል። ፍፁም ደስታ የሚሰጠን፣ መኖራችንን ትርጉም የሚሰጠን፣ ህይወታችንን ሙሉ የሚያደርግልን ዓላማ ያስፈልገናል።
ያንን ምክንያት ፈልጎ የመኖር ዓላማህ ምንድን ነው? ሁሌም ደካማነት ሲሰማን ጥሩ ስንቅ ይሆነናል ዓላማ። ‹‹ዓላማ ከሌለህ ትሞታለህ›› የሚባል አንድ የጥንት አባባል አለ። ሰዎች ማንን ማግኘት እንደሚፈልጉ፣ የት መሄድ እንደሚፈልጉ፣ ማዳበር የሚፈልጉትን ክህሎት ወይም መሆን የሚፈልጉት ነገር ይኖራል። ለማሳካት መሰልቸትን ማሸነፍ ይኖርብሃል። ይሄ የወደፊት እይታችንና እቅዳችን ነው። መሆን እንችላለን ብለን ያመንበትን ነገር ነው። ያለበለዚያ ህይወት ዋጋ አይኖረውም።
ነገር ግን ግልፅ የሆነ እይታ ካለን የሚከፈለውን ዋጋ እንከፍላለን። እንማራለን። ከህሎቱን እናዳብራለን።
ነገን ለመቅረፅ ዋጋ እንከፍላለን። ቁጭ ብለን ልንመኝ እንችላለን። እንዲህ ቢሆን ኖሮ እያልንም ልናስብ እንችላለን። መጀመሪያ ግን የያዝነውን ድንቅ አእምሮ ካላዘዝንበት፣ የሚታዘዘውን ሰውነት በድካም ውስጥ እንኳን ታታሪ እንዲሆን ካላደረግነው በቁጭት መኖራችን አይቀሬ ነው። ሁኔታዎች አንተ ብትደሰትባቸውም ባትደሰትባቸውም መሆን እንዳለባቸው ይሆናሉ። ይህን መቀየር አትችልም። አንተ ግን ራስህን መቀየር ትችላለህ። የተሻለ ሰው ከሆንክና ከሁኔታው በልጠህ ከተገኘህ ሁሌም የተሻለውን ነገር ታገኛለህ። በዙሪያህ ያለውም አብሮ ይለወጣል።
4ኛ.ከትናንሽ ተግባሮች ጀምር
መለወጥ የወሰንክ ግዜ ለራስህ ትናንሽና ቀላል ተግባሮችን መከወን ጀምር። ራስህ ላይ አታክብድበት። ራስህን መግዛት ከፈለክ ከበደኝ ብለህ እንደትተወው በአቅምህ ልክ ፍላጎትህን ከፋፍለው። ትልቅ ቦታ የሚደርስ ነገር የሚጀምረው በትናንሽ ነገር ግን ወጥ በሆኑ እርምጃዎች ነው። የየቀኑ ልማዶችህን ትቀይራለህ። መጥፎ የምትለው ተግባሮችን ሁሉ ቀስ በቀስ በጥሩ ተግባሮች ትተካቸዋለህ። ትጋት ግን የግድ ያስፈልግሃል። ራስህን ስትገዛው ዲስፕሊንድ ስትሆን አይምሮህ በለመደው መንገድ እንዲሰራ እያዘዝከው ስለሆነ እስክትለምደው ግዜ ይወስዳል። ብቻ ግን ቁርጠኛ ሁን።
ምንአልባት ዛሬ አደርጋለሁ ብለህ ያሰብከውን ሳታደርገው ልታድር ትችላለህ። ከዛ እኔ እኮ ድሮም ራስን ለመግዛት አልታደልኩም። ይሄ ነገር መቼ ይሆንልኛል ብለህ ነው ብለህ እርግፍ አድርግህ አትተወው። ለምሳሌ ማጨስ ማቆም አለብኝ ትልና ሁለት ቀን ታግሰህ በሶስተኛው ቀን ስትሸነፍ በጭራሽ ልታሳካው እንደማትችል ታስባለህ። የመጀመሪያው ነገር ይህን በብዙ ዓመት የተገነባ ሱስ በቀናት ውስጥ አሸንፋዋለሁ ብለህ ከባድ ውሳኔ ውስጥ አትግባ። ወስን ግን በቀላሉ መለወጥን አትተጠብቅ። በመጀመሪያ ውስጥህ የሚያስደስተውን መልካም ልማድ ፈልግ። ከዛ መጥፎውን ልማድ በምታከናውንበት ሰዓት እነዚህን መልካም ልማዶች ማድረግ አዘውትር። በዚህ መንገድ ታሳካዋለህ።
አቅማችንን ሁሉ አሟጠን የምንሰጠው አንድ የተፈጠርልነት ነገር ይኖራል። ስትጀምር ታዲያ አንድ ብር ካለህ በዛ ጀምር። ብዙ ነገር ሊጎድልህ ይችላል። በቃ ከነጉድለትህም ጥረትህን ጀምር። ከታመምክ ታማሚ ሆነህ ትጀምራለህ። ሁሉ ነገር ኖሮህ ካላስደሰተህ አመስጋኝ ሆነህ ትጀምራለህ። ብቻ ጀምር። አስበው እስኪ ያልካቸውን መፅሃፍት ብታነብ፣ ያሰብከውን ትምህርት ብትማር ዲስፕሊን፤ ቆራጥነት ቢኖርህ ፐ! ምን ማድረግ ትችላለህ? እነዚህኑ ዛሬውን በትንሹ ጀምራቸው። በትልቅ የሚያልቁ ታሪኮች ተስፋ ይሰጡናል። በመሃል ያሉትን ትግል ግን መረዳት ይገባል። በየቀኑ ወጥ በሆነ መንገድ ዘላቂ ሆነህ ካንተ የሚጠበቀውን ስታደርግ ህይወት ብዙ አስገራሚ ነገሮችን ታሳይሃለች። ያላሰብከው ሲሳይ እጅህ ላይ ይወድቃል።
ቁጭ ብለህ ግን እድሎች አይመጡም። እድሎች ቢመጡም ራሱ አትጠቀምባቸውም። አንዳንድ ሰዎች የአቅማቸው ልክ በሚፈተንበት ከባድ ሁኔታ ውስጥ ይገባሉ። በብዙ ፈተና ያልፋሉ። ላቁመው ልቀጥለው የሚል ፀብ ከራሳቸው ጋር ይገባሉ። ይሰቃያሉ። ነገር ግን ከዚህ ሁሉ ጭንቀት ውስጥ አስደማሚ ለውጥን ይዘው ይወጣሉ። እነዚህ ሰዎች የሰው ልጅ የአቅም ችግር እንደሌለበት ምስክር ናቸው።
5ኛ. በየቀኑ ራስህን አሻሽል
ራስህን ለመግዛት ከፈለክ በየቀኑ ራስህን ማሻሻል ይጠበቅብሃል። ከትላንት የተሻለ ለመሆን ጣር። ለምሳሌ የተሻለ ባለሞያ፣ የተሻለ ተናጋሪ፣ የተሻለ ተግባቢ መሆን ልትፈልግ ትችላለህ። ስትጀምረው፤ ለለውጥህ ስትጓጓ በእያንዳንዱ እርምጃህ የሚያስደስት ነገር ታገኛለህ። ለቀጣዩ እርምጃህ ይጋብዝሃል። ሁሌም የመማርና የመለውጥ ጉጉትህ ይኑርህ። በስራ ቦታህ አለህ ብቻ አትባል። ለውጥ ፈጣሪ ሁን። የሚማር አስተማሪ፣ የሚማር አባት ለምትመራው ቦታ የሚማር መሪ ሁን። የመማርና የመለወጥ ውስጣዊ ፍላጎት ካለህ ራስን መግዛት አይከብድህም። ዲስፕሊን ማምጣት አይከብድህም።
በቀን አስር ገፅ ማንበብ ማለት በወር ሁለት መፅሃፍ ማንበብ ነው። በዓመት ደግሞ ሀያ አራት መፅሃፍቶች ማንበብ ነው። ‹‹ይሄ እውነት ከሆነማ ለማንበብ ቀላል እኮ ነው›› ልትል ትችላለህ። ማወቅ ያለብህ ነገር ግን ለማድረግ ቀላል የሆነው ነገር ላለማድረግም ቀላል ነው። ማድረግ እንዳለብህ ካላደረከው አንተ የውድቀትን ቀመር እየቀመርክ ነው። እናም ዛሬውኑ አንድ ነገር ማድረግ ጀምር። ለዚህም ማድረግ እችላለው በል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 3/2015
judolbet303
judol303