የመጽሐፉ ስም፡- ጠርዝ ላይ
ደራሲ፡- ዶክተር በድሉ ዋቅጅራ
የሕትመት ዘመን፡- መጋቢት 2011 ዓ.ም
የገጽ ብዛት፡- 192
ዋጋ፡- 120 ብር
ይህ መጽሐፍ የዶክተር በድሉ ዋቅጅራ ነው። ከመጽሐፉ በፊት ደራሲውን መጥቀስ ለምን አስፈለገ? ሰው ሥራውን ስለሚመስል። መጽሐፍ ግዑዝ አካል ነው፤ በውስጡ ግን ነፍስ ያላቸው ነገሮች አሉት። እነዚያ ነፍስ ያላቸው ነገሮች የደራሲው ሀሳብ ናቸው። ስለዚህ ያ መጽሐፍ ማለት ደራሲው ማለት ነው። ብዙ ጊዜ የሰዎችን ምንነት ከሥራቸው መለየት አለብን ተብሎ ይነገራል። አያስማማኝም! የአንድ ሰው ሥራ የሚመነጨው ከማንነቱ ነው።
በአጭሩ ምን ለማለት ፈልጌ ነው፤ ዶክተር በድሉ ዋቅጅራ ደፋር ተናጋሪ ነው፤ ልብ ብሎ የሚያስተውል ነው፤ በዚህም ምክንያት ተወዳጅ ደራሲ ነው። በተለይም አሁን አሁን ደግሞ ከመገናኛ ብዙኃን ጋር በሚያደርገው ቃለ መጠይቅና የመድረክ ንግግሮቹ በብዙዎች ዘንድ ተመስጋኝ ሆኗል። ምክንያቱም ያለምንም ማስመሰልና አድርባይነት ስለሚናገር ነው። ወደ መጽሐፉ!
‹‹ጠርዝ ላይ›› የተሰኘው የዶክተር በድሉ ዋቅጅራ መጽሐፍ ዘውግ አንድ ወጥ አይደለም። ምናልባት ጠቅለል አድርገን እናስቀምጠው ከተባለ ትዝብት እና አስተውሎት (ምልከታ) ነው። ምልከታ ሲባል ግን ዝም ብሎ የግል አስተያየት ብቻ አይደለም፤ ከጥናቶችና ከገጠመኞች በመነሳት ነው። ጥናቶችን ዋቢ በማድረግ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ የሚተነትን ነው።
ገጠመኞችንም ይጠቀማል። ዶክተር በድሉ ዋቅጅራ የስነ ጽሑፍ ሰው ስለሆነም ይሆናል ገጠመኞችን በጣፍጭ አተራረክ ይገልጻቸዋል። ሁነቱ የተከሰተበትን አጋጣሚም ይተነትነዋል፤ ያ ማለት የተከሰተበት ምክንያት አስተማሪ ይሆናል ማለት ነው። እንደ ዶክተር በድሉ ዋቅጅራ አይነት ሰው ደግሞ ብዙ ነገር ያስተውላል፤ ምክንያቱም ከላይ እስከታች ያሉ ነገሮችን የማየት ዕድል ስላለው። ወታደር ነበር፣ መምህር ነው፣ የስነ ጽሑፍ ሰው ነው፣ ብዙ አንባቢ ነው፣ ብዙ ጥናትና ምርምሮችን ሰርቷል፤ ተሳትፏል። በእነዚህ ሁሉ የሕይወት አጋጣሚዎች ውስጥ የአገሪቱን ሁኔታ አስተውሏል ማለት ነው።
የመጽሐፉ ይዘት
‹‹ጠርዝ ላይ›› ከሚለው የመጽሐፉ ርዕስ ሥር ንዑሳን ርዕሶች አሉ። ‹‹የትኛዋ ኢትዮጵያ? የትኛው ቋንቋ? ምን አይነት ጋዜጠኝነት? ማህበረሰባዊ የስነምግባር ዝቅጠት›› የ‹‹ጠርዝ ላይ›› ንዑስ ርዕሶች ናቸው። እነዚህ አራት ንዑስ ርዕሶች በአራት ክፍል ይተነተናሉ። አራቱ የመጽሐፉ ንዑስ ርዕሶች ደግሞ በውስጣቸው የየራሳቸው ርዕሶች አሏቸው። እነዚህን ክፍሎች ጥናት እያጣቀሰ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚሆነው ነገር ጋር ያነጻጽራል። በተለይም ‹‹የትኛው ቋንቋ?›› የሚለው ክፍል ከግል አስተያየትና ምልከታ በላይ በጥናቶች የታጨቀ ነው።
‹‹ጠርዝ ላይ›› የሚለው ቃል በራሱ ብዙ ነገር ግልጽ ያደርግልናል፤ እንዲያውም የመጽሐፉን ርዕስና በሥሩ ያሉትን ንዑሳን ርዕሶች ብቻ አይቶ ይዘቱን ለመገመት ቀላል ነው። ምክንያቱም የአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ለማንም ግልጽ ነው። ነገሮች ሁሉ ጽንፍና ጽንፍ ይዘው ጠርዝ ላይ ነው ያሉት። ደራሲው ‹‹ጠርዝ ላይ›› ያላት ኢትዮጵያን መሆኑ ነው።
ኢትዮጵያን በተመለከተ የጋራ የሆነ ነገር እየጠፋ ነው። አንዱ ያለፈውን ሥርዓት ሲኮንን ሌላው ያለፈውን ሥርዓት ያወድሳል፤ የአንዱ ኢትዮጵያ የበለጸገችና ሰላም የሰፈነባት ስትሆን የሌላው ኢትዮጵያ በድህነት የምትማቅቅና ጦርነት የማይለያት ናት፤ የአንዱ ኢትዮጵያ የራሷ ቋንቋ የራሷ ፊደልና የራሷ አኩሪ ባህል ያላት ስትሆን የአንዱ ኢትዮጵያ ደግሞ የገዥ መደብ ባህልና ቋንቋ የተጫነባትና እነዚህም የተጫነባቸው የዚህ ባህልና ቋንቋ ጥላቻ ያለባቸው ናት። እንግዲህ የዚች አገር ባለቤቶች እነዚህ ጠርዝና ጠርዝ ላይ ሆነው የሚተያዩ ህዝቦች ናቸው ማለት ነው። ስለዚህ ደራሲው ይህን ርዕስ መስጠቱ በትክክል ይገልጽለታል።
ደራሲው በጥናትና ምርምር እየታገዘ ሰፊ ትንታኔ ቢሰጥበትም መጽሐፉን እንዲታነቡት እየጋበዝን አራቱንም ክፍሎች በግርድፉ እንያቸው።
1. የትኛዋ ኢትዮጵያ?
በዚህ ክፍል ሥር ‹‹የድሮዋ ኢትዮጵያ፣ የዛሬዋ ኢትዮጵያ እና የነገዋ ኢትዮጵያ›› የሚሉ ርዕሶች አሉ። በተለይ ‹‹የዛሬዋ ኢትዮጵያ›› ሚለው ርዕስ ሰፊ ነው (ሰፊ ሊሆንም ይገባል)።
ስለድሮዋ ኢትዮጵያ ከደራሲው አንድ ነገር ብቻ ልጥቀስና ዝርዝሩን አንብቡት። ኢህአዴግ ‹‹የድሮ ሥርዓት ናፋቂዎች›› የሚል ስድብ ሲለጥፍ ቆይቷል፤ ህዝቡም ኢህአዴግ የድሮ ሥርዓት ጥላቻ እንዳለበት ሲነግረው ቆይቷል። በዚህ ውስጥ ምሁራንም ራሳቸው ክርክር ላይ ናቸው። የድሮዋ ኢትዮጵያ ትሻላለች አትሻልም በሚል። ደራሲው አስታራቂ ሀሳብ ነው ያለው። የድሮዋ ኢትዮጵያ ዜጎች አገራዊ መንፈስ የነበራቸው ናቸው፤ በአገራቸው ይኮራሉ፤ ያ ማለት ግን የድሮዋ ኢትዮጵያ ትክክል ነበረች ማለት እንዳልሆነ ይናገራል። አንድ ገጠመኙን ብቻ ወስደን እንለፈው።
ደራሲው የሦስተኛ ክፍል ተማሪ እያለ የሳይንስ መምህራቸው ቁርሳቸውን ምን እንደበሉ ትጠይቃቸዋለች (የዕለቱ ትምህርት ስለሚያዝዝ)። ተማሪዎችም ተራ በተራ ተናገሩ። ከተማሪዎች መካከል አንዱ ‹‹ቆጮ›› አለ። መምህሯ ፊቷ በእንባ እስከሚታጠብ ሳቀች፤ ተማሪዎችም ሳቁ (ታሪኩን በጣም ነው ያሳጠርኩት)።
በዚህ ውስጥ ደራሲው የነገረን ነገር የድሮዋ ኢትዮጵያ ማለት የሰሜኑ ኢትዮጵያ ቋንቋና ባህል ብቻ የሚከበርበት መሆኑን ነው።
የድሮዋ ኢትዮጵያ ትክክል አይደለችም የሚለው ደራሲው የዛሬዋ ኢትዮጵያ ላይም አይስማማም፤ ለዚህም ኢህአዴግን አምርሮ ይወቅሳል። በነገራችን ላይ ደራሲው ‹‹ኢህአዴግ›› ብሎ አይጠቀምም፤ ‹‹ህወሓት/ኢህአዴግ›› ነው የሚለው። ደራሲው ዶክተር በድሉ ዋቅጅራ በዋልታ ቴሌቪዥን እንግዳ ሆኖ በቀረበበት ጊዜ ከጋዜጠኛው ይህንኑ ጥያቄ ተጠይቆ መልስ ሰጥቷል። በመልሱም አድራጊ ፈጣሪው ህወሓት ስለነበር ‹‹ኢህአዴግ እያሉ መጠቀም ለእኔ ቀልድ ነው›› ብሏል።
ደራሲው የገለጸበትን ከተናገርኩ እኔ ደግሞ ለዚህ ጽሑፍ ‹‹ኢህአዴግ›› እያልኩ ልጠቀም። የአሁኗ የኢህአዴግ ኢትዮጵያ ‹‹ጠርዝ ላይ›› የተባለችዋ ናት። ለዚህ ያበቃት ኢህአዴግ በቋንቋና በጎሳ መከፋፈሉ ነው። እንዲያውም ‹‹ክልል›› የሚለውን ቃል ደራሲው የቋንቋ ጥናቶችንና መዝገበ ቃላትን ጠቅሶ እንዲህ ያብራራዋል። ‹‹ከለለ፣ ጋረደ፣ ማየት ከለከለ›› ማለት ነው። ማብራሪያውን ሲቀጥልም
‹‹የአማራ ክልል›› ከተባለ ለአማራ የተሰጠ፣ ለአማራ የተወሰነ፣ የአማራ ብቻ የሆነና ሌላው የማያገባው ማለት ነው። ‹‹ክፍለ ሀገር›› ከሚለው ቀደም ከነበረው አጠራር ጋር ያነጻጽረዋል። ‹‹ጎጃም ክፍለ ሀገር›› ቢባል በሰዎች ህሊና የሚመጣው ጎጃም የሚባል ክፍል ነው። በሌላ በኩል ጎጃም ማለት አንድ የአገሪቱ ክፍል ማለት እንጂ የእገሌ ማለት አይደለም።
የነገዋ ኢትዮጵያ የእነዚህ ውጤት ነው የምትሆነው። አሁን ላይ ያለው ጠርዝ ላይ የረገጠ አተያይ ካልተቀረፈ አደጋ ላይ ይጥላታል። ይህ እንዳይሆን መንግሥት ከይስሙላ ያለፈ የብሄሮችን መብት ማክበር እንዳለበት ደራሲው ይነግረናል።
2. የትኛው ቋንቋ?
ይህ ክፍል ሰፊ ነው። ምናልባትም ደራሲው የቋንቋ ምሁር ስለሆነ ይመስላል የብዙ አገራት የቋንቋ ፖሊሲ፣ በቋንቋ ላይ የተሰሩ ምርምሮች፣ የቋንቋ ባህሪ በሰፊው ተተንትነውበታል። ከአገራችን ሁኔታ ጋር በማያያዝም ‹‹እንዲህ ቢሆን፣ እንዲህ ቢደረግ›› የሚል የመፍትሔ ሀሳብ ያስቀምጣል። ኢህአዴግ ግልጽ የሆነ የቋንቋ ፖሊሲ አለማውጣቱ ቋንቋዎች እንዳያድጉ ያደርጋል። ከግለሰብ ይልቅ የብሄር መብት ላይ ማተኮሩ ትንሽ ተናጋሪ ያላቸው ቋንቋዎች እንዳያድጉ አድርጓል። ምሳሌ ሲጠቅስም፤ ለምሳሌ የትግራይ ክልል የሥራ ቋንቋ ትግርኛ ነው፤ በክልሉ ውስጥ ያሉ እንደ ኩናምኛ ያሉ ቋንቋዎች ግን ዞንና ወረዳ ላይ እንኳን አይሰራባቸውም።
ወደ ፌዴራሉ ሲመጣም እንደ ኦሮምኛ ያሉ ብዙ ተናጋሪ ያላቸው ቋንቋዎች የፌዴራል የሥራ ቋንቋ ቢሆኑ ምክረ ሀሳብ ያስቀምጣል፤ ለዚህም የተለያዩ አገራትን ተሞክሮ እንደማሳያነት ተጠቅሟል።
3. ምን አይነት ጋዜጠኝነት?
ይህኛው ክፍል በብዛት በትዝብት የተሸፈነ ነው። በመጀመሪያው አካባቢ ያንኑ የተለመደውን ወቀሳ ይነግረናል። የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞች ታማኝነታቸው ለእውነት ሳይሆን ለመንግሥት እንደሆነና ትክክለኛ ዘገባ የሚሰሩት ደግሞ አሸባሪ ተብለው እንደሚታሰሩ ይነግረናል። እዚህ ላይ ግን ደራሲው ልማታዊ ጋዜጠኝነትን የገለጸበት መንገድ ከታዳጊ አገር አውድ አይደለም። ልማታዊ ጋዜጠኝነት የመንግሥት ፕሮፖጋንዳ እንደሆነ ይነግረናል። አተገባበሩ ይሆናል እንጂ ልማታዊ ጋዜጠኝነት ግን በባህሪው የመንግሥትን ፕሮፖጋንዳ ማስተጋባት ማለት አይደለም።
ሌላው ደራሲው አምርሮ የሚተቸው ነገር (ምናልባትም ‹‹ምን አይነት ጋዜጠኝነት›› ያለበት) የአየር ሰዓት ገዝተው የሚሰሩ አርቲስቶችን ነው። እንኳን አሰራሩ የሰውነት እንቅስቃሴያቸው ሳይቀር ከውጭ የተኮረጀ ነው። የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ እና ለህዝብ የሚጠቅም ነገር የለውም።
4. ማህበረሰባዊ የስነምግባር ዝቅጠት
ይህ ክፍል ርዕሱን አይተን እንደምንገምተው አይደለም፤ እርግጥ ነው ርዕሱን ያየ ሁሉ ምን እንደሚገምት አላውቅም። ዳሩ ግን ይህን ርዕስ ስናይ ምን ለማለት እንደፈለገ ቀድመን የምናውቀው ይመስለናል። በአገራችን የሚታዩ ዘግናኝና ነውር ነገሮች በህሊናችን እያሰብን እነርሱን ማለት ፈልጎ ነው ማለታችን አይቀርም።
ትንታኔው ግን ከዚህ በላይ ነው። በመጀመሪያ የስነምግባርን ምንነት በሳይንሳዊና በቋንቋ ብያኔ ይነግረናል፤ ከዚያም ጥናቶችንና ራሱ ደራሲው በዘፈቀዳዊ መጠይቅ ያገኛቸውን የጥናት ውጤቶች ከገጠመኞቹ ጋር ይነግረናል።
አስተያየት
መጽሐፉን ‹‹የወፍ በረር›› ከሚባለውም በላይ በፈጣን ወፍ በረር ነው የዳሰስኩት። መጽሐፉን ማንበብ ከብዙ ጥናቶችና የሌሎች አገራት ተሞክሮዎች ጋር ያስተዋውቃል።
የምሁራን ዝምታ በዚህ መንገድ ሊቀረፍ ይገባል። እንዲህ አይነት ምሁራን ብዙ ያነባሉ፣ ብዙ የሕይወት አጋጣሚና ምልከታ አላቸውና እንዲህ ማህበረሰብን ሊያንጹበት ይገባል!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 26/2011
በዋለልኝ አየለ