
በየሰፈራችን ብዙ ጊዜ ከምንሰማቸው ድምፆች መካከል አንዱ ‹‹ልዌ ልዌ ልዌ…. ወይም ልዋጭ›› የሚል ቃል ነው:: ይህን ቃል የሚጠቀሙ ሰዎች አዳዲስ እቃዎችን በአሮጌ እቃዎች ይለውጣሉ:: ማንም ሰው ቤቱ ውስጥ የማይፈልገውን ዕቃ በልዋጭ ይለውጣል:: በዚሁ ፅሁፍ አላማዬ ስለልዋጭ ለማውራት ሳይሆን ክፉ አስተሳሰብን በመልካም አስተሳሰብ ስለመተካት በምሳሌነት ለመጠቀም ነው::
በሕይወት መኖር ያለሙትን ነገር ከግብ አድርሶ መደሰት እንዲሁም ያፈሩትን አንጡራ ሀብት ለትውልድ ማውረስ የሚቻለው በጎ አስተሳሰብ ሲኖር ነው:: የሰው ልጅ ስኬትና ውድቀት በአብዛኛው የሚወሰነው በአእምሮ ውስጥ ባለው የአስተሳሰብ አይነት ነው:: በጎ አስተሳሰብ ወደ ስኬት ሲያመራ፤ ክፉ አስተሳሰብ ደግሞ ወደ ውድቀት ያመራል::
የአስተሳሰብ መመረዝ ከግለሰብ አልፎ ቤተሰብን፣ ጎረቤትን፣ ማህበረሰብንና ሀገርን ይጎዳል:: የተመረዘ አስተሳሰብ የተመረዘ ድርጊትን ይወልዳል:: ምክንያቱም ድርጊታችን የአስተሳሰባችን ውጤት ነውና:: ብዙ ጊዜ ለሰዎች የሚታየው ክፉ ድርጊት እንጂ የዚህ ክፉ ድርጊት መንስኤው አስተሳሰብ መሆኑ አይደለም::
ሰዎች በክፉ ድርጊታቸው ጠበኛ፣ ተንኮለኛ፣ ውሸታም፣ ሙሰኛ፣ ሰነፍ፣ ቂመኛ፣ በቀለኛ ወይም በተቃራኒው ሰላማዊ፣ እውነተኛ፣ የዋህ፣ ሀቀኛ፣ ጎበዝ፣ ይቅር ባይ ይባላሉ:: አስተሳሰብ ደግሞ ከድርጊት ጀርባ ተሰውሮ ያለ መንስኤ ነው:: ስለዚህ የሰዎችን ክፉ ድርጊት ወይም ፀባይ ለመለወጥ ክፉ አስተሳሰባችንን መለወጥ መሰረታዊ እርምጃ ነው:: ምክንያቱም አስተሳሰብ ሲለወጥ ድርጊትም አብሮ ስለሚለወጥ ነው::
አሮጌ እቃዎችን በአዳዲስ እቃ መለወጥ የሚያውቁ አሮጌ አስተሳሰባቸውን በአዳዲስ አስተሳሰቦች እንዲለውጡ ሲጠየቁ እምብዛም ፍቃደኞች አይደሉም:: እንግዲህ አሮጌ አስተሳሰብን ገበያ አውጥቶ በአዲስ አስተሳሰብ መለወጥ ያልፈለገን ሰው በምንም መልኩ አስተሳሰቡን መለወጥ አይቻልም:: በልዋጭ ገበያ አሮጌ አስተሳሰብን በአዲስ አስተሳሰብ ለመለወጥ የግል ፍቃደኝነትና መነሳሳት አስፈላጊ ነው::
ብዙዎቻችን ‹‹ከማያውቁት መልአክ የሚውቁት ሰይጣን ይሻላል›› የሚለውን አባባል እናውቅ ይሆናል:: በእኔ እሳቤ ግን ይህ አባባል ጥሩ የሚባለውን የማያውቁትን አዲስ መልአክ ከመተዋወቅና ከመልመድ ይልቅ ከለመዱት ክፉ ሰይጣን ጋር ለመኖር መፈለግን ያመለክታል:: አብዛኛውን ጊዜም ሰዎች ከለመዱት አስተሳሰብ ጋር መቆየት ይፈልጋሉ:: አዲሱ ነገር መልካም መሆኑን እያወቁ ክፉ ከሆነው አስተሳሰብ ጋር ታስረው መኖርን ይመርጣሉ:: አዲሱን አስተሳሰብ በመቀበልና በመለማመድ ሂደት ጥቂት ዋጋ በመክፈል ቀሪ ዘመናቸውን የተሻለ ከማድረግ ይልቅ የለመዱትን ክፉ አስተሳሰብ ይዘው አሉታዊ ውጤቶችን ይለማመዳሉ::
አርባ ወይም ሃምሳ አመታትን ከአሉታዊ አስተሳሰብ ጋር ትክክል እንደሆነ በማሰብ ይኖር የነበረን ሰው የተሻለ አስተሳሰብ እንዳለ ቢነገረው መቀበል ይከብደዋል:: የሕይወቱ ማንነት የተገነባው በዚህ መርዛማ አስተሳሰብ ላይ በመሆኑ መሰረቱን ስለመቀየር ሲያስብ ለዘመናት የገነባው ማንነቱ የፈረሰ ይመስለውና ይቃወማል::
ለግማሽ ምዕተ አመት በቀልን የጀግንነት መገለጫ አድርጎ ያስብና ይለማመድ የነበረን አንድ ጎልማሳ ይቅርታ የተሻለ እንደሆነ ቢነገረው እንዴት ይቅርታውን ሊቀበል ይችላል? በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ‹‹ሲሾም ያልበላ….›› የሚለውን አባባል ሲሰማ የኖረው ሰው የመንግስትን ስልጣን ተጠቅሞ ሀብትን መዝረፍ ወይም ጉቦ መቀበል ሌብነት/ሙስና ወይም ‹‹መሾም የሕዝብ አገልጋይነት ነው›› ተብሎ ቢነገረው እንዴት ነገሩን በአወንታዊ መንገድ ያስተናግዳል?
ሰዎች ከለመዱት አስተሳሰብ ጋር ለመኖር የመፈልግ አዝማሚያ ቢኖራቸውም የለውጥ መስኮቶች ይኖራሉ:: ለምሳሌ አዲስ አመት ሲመጣ ሰዎች መለወጥ የሚፈልጉት ነገር አላቸው:: አሮጌው አመት ሲያልፍና አዲሱ አመት ሲቃረብ ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ የማይጠቅማቸውን ነገር በመለወጥ መልካም የሆነውን ነገር ለመያዝና ለማድረግ ያስባሉ:: ይህ ምኞት መልካም ነው:: ለውጥን መመኘት ብቻውን የሚፈለገውን ለውጥ አያስገኝም:: የአስተሳሰብና የፀባይ ለውጥ ለማምጣት ከመሻትና ከፍቃደኝነት ባለፈ እንዴት መለወጥ እንደሚገባና በጎ እርምጃዎችን እንዴት ማስቀጠል እንደምንችል ማወቅ አለብን::
የአስተሳሰብና ፀባይ ለውጥ ሲታሰብ መለወጥ የምንፈልገውን አስተሳሰብ ለይተን ማወቅ ጠቃሚ ነው:: ቤት ውስጥ ያሉንን እቃዎች ሁሉ ለልዋጭ ገበያ እንደማናቀርብ ሁሉ በአእምሯችን ውስጥ ያሉትን አስተሳሰቦች ሁሉ አንለውጥም:: ስለዚህ አሮጌና ጎጂ የሆኑ አስተሳሰቦችን ለይቶ ማወቅ ያስፈልጋል:: እነዚህን ለይተን ስናውቅ በእነሱ ላይ እናነጣጥራለን:: በህብረተሰባችን ውስጥ በስፋት የሚስተዋሉ ክፉና መለወጥ ከሚገባቸው አስተሳሰቦች መካከል ጥቂቶቹ እኔ አልችልም፣ ነገ እሰራዋለሁ፣ የመንግስት ነው፣ ከራስ በላይ፣ የእኔ ወገን ብቻ…..ወዘተ ናቸው::
በተጨማሪም በአሮጌው ወይም ክፉው ፈንታ የሚተካውን አዲሱን ወይም በጎውን አስተሳሰብ ማወቅ ይጠቅማል:: መለወጥ የምንፈልገውን ክፉ አስተሳሰብ ብቻ ሳይሆን በዚያ ክፉ አስተሳሰብ ቦታ መተካት የሚገባውን መልካም አስተሳሰብን ማወቅም ያስፈልጋል:: በልዋጭ ገበያ አሮጌ እቃ ይዘን ስንሄድ በምን እንደምንለውጥ እናስባለን:: በአስተሳሰብ ገበያም ክፉውን አስተሳሰብ መልካም በሆኑ አስተሳሰቦች ለመለወጥ ማመዛዘን አለብን::
ከላይ የተጠቀሱትን ጎጂ አስተሳሰቦች በመልካምና በአወንታዊ አስተሳሰቦች መለወጥ እንችላለን:: ለምሳሌ፡-
- እኔ አልችልም- ፈጣሪ የሰጠኝን እምቅ ችሎታ በመጠቀም የምችለውን ሁሉ አደርጋለሁ::
- ነገ እሰረዋለሁ- ዛሬ መስራት የሚገባኝን ሁሉ መፈፀም አለብኝ፤ ስራ ለነገ አይባልም::
- የመንግስት ነው- የመንግስት የሆነው ነገር የኔ ነው፤ ስለዚህ መንከባከብ አለብኝ::
- ከራስ ባለይ….- በጎ ነገሮችን ለሰዎች ማድረግ ያረካኛል::
- የእኔ ወገን ብቻ- በጎ አስተሳሰብ ያለውና መልካም የሚያደርግ ሁሉ የእኔ ወገን ነው::
በጎ ነገር ማሰብ ብቻ በጎ ሰው አያደርግም:: በጎ አስተሳሰብን ወደ መልካም ስራ መለወጥ አስፈላጊ ነው:: እንደምንችል ማውራት ብቻ ሳይሆን መስራት የምንችለውን ነገር በመስራት ራሳችንን መለወጥና ለሌሎችም ድጋፍ መስጠት ይገባናል:: ጊዜን በአግባቡ መጠቀም ጠቃሚ እንደሆነ ማሰብ ብቻ ሳይሆን ያለንን ጊዜ በአግባቡ በመጠቀም፣ ሰዓት በማክበር ስራዎችን በጊዜው ማከናወን ለውጥ ያመጣል::
የአስተሳሰብና የፀባይ ለውጥ ሂደት መሰናክሎች እንዳሉትም በመገንዘብ ተግዳሮቶቹን ለማሸነፍ መዘጋጀትም አስፈላጊ ነው:: በልዋጭ ገበያ አሮጌ ጫማዎችን በአዲስ ጫማ ለውጠን ይሆናል:: አዲስ ጫማ ስናደርግ ግን እንደአሮጌው አይመቸንም:: እግራችን የለመደውን አሮጌ ጫማ ይፈልጋል:: አዲሱ ጫማ እንዲመቸን ደጋግመን ማድረግ አለብን እንጂ በመጀመሪያዎቹ ቀናት ስላልተመቸን ወደ አሮጌው ጫማ አንመለስም:: የአስተሳሰብና የፀባይ ለውጥም እንደዚሁ ነው::
ከለመድነው አስተሳሰብ ወጣ ብለን በአዲስ መንገድ ለመሄድ ስንፈልግ መሰናክሎች አሉ፤ በውስጣችን ምቾት ማጣት ብቻ ሳይሆን ከቤተሰብ፣ ከጓደኞቻችንና ከስራ ባልደረቦቻችን የሚመጡብን አሉታዊ ግፊቶች ይኖራሉ:: እነዚህን በመቋቋም በአዲሱ አስተሳሰብ ለመዝለቅ ብዙ መስራት አስፈላጊ ነው::
ክፉ አስተሳሰቦቻችን እስካሁን የት እንዳደረሱንና ምን ውጤት እንዳስገኙልን እናውቃለን:: ስለዚህ በነዚህ ክፉ አስተሳሰቦች ቁጥጥር ስር ሆነን መልካም ውጤት መጠበቅ ጤናማነት አይደለም:: አልበርት አንስታይን እንደተናገረው ‹‹አንድን ነገር ደጋግምን በማድረግ የተለየ ውጤት መጠበቅ እብደት ነው››:: እኛ በመርዛማ አስተሳሰብ ተይዘን መልካም ሕይወት፣ ቤተሰብ እንዲሁም ሀገር መገንባትን ማሰብ እብደት ነው::
ስለዚህ አስተሳሰብ ከእኛ ጋር አልተወለደም:: እኛ ስንወለድ ለማሰብ አቅም ይዘን እንጂ የሆነ አስተሳሰብ ይዘን አይደለም:: ሁላችንም አሁን የያዝነውን/አእምሯችን ውስጥ የሞላውን/ አስተሳሰብ ያገኘነው ከአካባቢያችን ነው:: አካባቢ የሚባለው ደግሞ ወላጅ/አሳዳጊ/፣ ጎረቤት፣ ጓደኛ ትምህርት ቤት፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ ሚዲያና የመሳሰሉትን ያጠቃልላል:: እነዚህ ሁሉ የእኛን አስተሳሰብ በመቅረፅ ላይ ተሳትፈዋል፤ አሁንም እየተሳተፉ ናቸው::
የሰው ልጅ ተምሮ መለወጥ የሚችል ፍጡር ነው:: አስተሳሰብ ተፈጥሯዊ ካልሆነ/ከእኛ ጋር ያልተወለደ ከሆነ/ የሚለወጥ ነገር ነው:: ስለዚህ አስተሳሰባችን ጠቃሚ ካልሆነ መለወጥ አለበት:: አስተሳሰባችን የማይጠቅመን ከሆነ ወደ አስተሳሰብ ገበያ ሄደን በጎና የሚጠቅመንን አስተሳሰብ መሸመት እንችላለን:: የበጎ አስተሳሰብ ዋጋው ውድ አይደለም:: የሚያስፈልገው አሮጌውን አስተሳስብ ይዞ በመሄድ በአዲሱና ጠቃሚው አስተሳሰብ ለመለወጥ ፍቃደኛ መሆን ነው::
የሰው ልጅ የአስተሳሰብ ቀረፃ ቀላል የሚሆነው በልጅነት ወይም በታዳጊ ወጣትነት ጊዜ ነው:: ይህ ምቹ ጊዜ አንዴ ካለፈ በኋላ መርዛማ አስተሳሰብ ሕይወታችንን ከገዛ ለመለወጥ አዳጋች ይሆናል:: ተጣሞ ያደገን ዛፍ ማስተካከል ከባድ እንደሚሆነው ሁሉ:: ያለን እድል ከጠማማ ዛፍ ጋር መኖር ወይም ዛፉን ቆርጦ ማስወገድ ነው:: ጠማማን ዛፍ ቆርጦ ማስወገድ ይቻላል:: ነገር ግን ጠማማ አስተሳሰብ ይዞ ያደገውን ሰው መቁረጥ አይቻልም::
በጎልማሶች ላይ የሚሰራው ስራ መርዛማ የሆነውን አስተሳሰባቸውን ወደሌሎች እንዳያስ ተላልፉ መስመራቸውን መዝጋት ወይም መቀነስ ነው:: አስተሳሰባቸውን የሚቀበል፣ የሚፈፅምና የሚተገብር ትውልድ እንዳይኖር የክፉ አስተሳሰባቸው ማራገፊያ ሊሆኑ የሚችሉ ልጆችንና ታዳጊዎችን ከእነርሱ ማራቅ ያስፈልጋል::
በህብረተሰቡ ውስጥ በጎ አስተሳሰብ ያላቸውን ዜጎች ለማፍራትና ለማብዛት እጅግ የሚያዋጣው መንገድ ከስር እየመጡ ያሉትን ልጆችና ወጣቶችን በመልካም አስተሳሰብ ማነፅ ነው:: በመልካም መቅረፅ ላይ ብዙ ጊዜ፣ እውቀትና ሀብትን ማዋል ክፉ በአእምሮ ውስጥ ከሞላ በኋላ ለመለወጥ ብዙ ጥረት ከማድረግ የተሻለ ነው:: ስለዚህ ጎልማሶችን ለመለወጥ ብዙ ጥረት ከማድረግ ገና በመቀረፅ ላይ ባሉት ልጆችና ታዳጊዎች ላይ ብዙ መስራት ለሀገራችን ትልቅ ጥቅም ይኖረዋል:: መልካም የልዋጭ ገበያ!!
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ግንቦት 26/2015