የኢትዮጵያ ሥነጽሑፍ የደለበ ታሪክ ባለቤት ነው። ይህንንም በርካቶች፣ ከውስጥም ከውጭም ተደጋጋሚ ጊዜያት ለአደባባይ ያበቁት ጉዳይ ነው።
የኢትዮጵያ ሥነጽሑፍ የቱንም ያህል የደለበ ታሪክ ይኑረው እንጂ እንደ ትልቅ ታሪክ ባለቤትነቱ የዓለም የሥነጽሑፍ አደባባይ ላይ ሲንጎማለል ታይቶ አይታወቅም (ምናልባትም፣ ይህ የ’ሱ ድክመት ባይሆንም)።
እርግጥ ነው፣ አፍሪካ ውስጥ በራስ (አፍሪካዊ) ቋንቋ ልቦለድ የጻፈች አገር ኢትዮጵያ ነች (አፈወርቅ ገ/ኢየሱስ “ጦቢያ”)። ይሁን እንጂ ይህንን የሚያክል የፈር ቀዳጅነት ታሪካዊ ድርሻ ይዛ በዛ ልክ እየተነገረላት አይደለም። ለዚህ ደግሞ እንደ ምክንያት የሚነሳው የቋንቋ ጉዳይ ነው – የመጻፊያ ቋንቋ ጉዳይ።
ስለ ባለ 90 ገጹ “ጦቢያ” እ.አ.አ ጥር 1 ቀን 1907 በሮማ ከተማ ለህትመት የበቃ “ልብወለድ ታሪክ” ሲነሳ አለም አቀፍ ገበያ ላይ በድረ-ገጽ ለሽያጭ የቀረበ (አሁንም ከመቶ አመት በኋላ) 4.35 ዶላር እየተሸጠ የሚገኝ ነው። በኢትዮጵያ የሥነጽሑፍ ታሪክ የመጀመሪያ ልብወለድ መጽሐፍ መሆኑ የሚነገርለት ይህ መጽሐፍ በወቅቱ ተነስቶ የነበረውን የአረማውያንንና የክርስቲያኖችን ጦርነት ይተርካል። ደራሲው በመጽሐፉ ውስጥ ስለተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች ማለትም ስለደግነትና ክፋት፣ ስለሃይማኖትና ፍቅር በሰፊው ያትታሉ። መጽሐፉ በተለይ የፍቅርን ሀያልነት ለማሳየትና የሃይማኖት ልዩነት ስላልበገረው ታላቅ ፍቅር በሰፊው ይተርካል። በተጨማሪም ደራሲው በጽሐፉ ውስጥ ሊያስተላልፉ የሞከሩት መልዕክት የሰው ልጅ በባዕድ አምልኮ ተሸብቦ ከመኖር ይልቅ ፈተናና ችግር ቢገጥሙት እንኳን ለእነዚህ ሳይበገር በአንድ አምላክ አምኖ ከጸና ድል ሊያደርግ እንደሚችል ነው።
የአፍሪካ ሥነጽሑፍ ጉዳይ ሲነሳ ምንጊዜም ሳይነሳ የማይታለፈው አቢይ ጉዳይ የመጻፊያ ቋንቋ ጉዳይ ነው። ይህ ደግሞ ዝም ብሎ ሳይሆን ከጀርባው የሰማይ ስባሪ የሚያክል ፖለቲካዊ ጉዳይና ከመጠን ያለፈና ተገቢነት የሌለው ግፊት ስላለበት ነው።
እንደሚታወቀው አብዛኛውን የአፍሪካ ምድር ነጭ ተቆጣጥሮት ነበር የቆየው። በነጭ ቁጥጥር ስር መዋል ደግሞ አፍሪካዊ ማንነትን እስከ ማሳጣት ድረስ የዘለቀ የከፋ ተፅእኖን አድርሶ የነበረ ሲሆን፤ አንዱም የራስ ባልሆነ ቋንቋ መጠቀም ነበር። በእርግጥ አሁንም አብዛኞቹ ከዛ አልወጡም። አፍሪካ ራሷም “እንግሊዝኛ ተናጋሪ” (anglophone) እና “ፈረንሳይኛ ተናጋሪ” (francophone – ብኒን፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ቡሩንዲ፣ ካሜሩን፣ ማእከላዊ አፍሪካን ሪፐብሊክ፣ ቻድ፣ ኮሞሮስ፣ ኮንጎ (DRC)፣ ኮንጎ፣ ኮት ዲቭዋር፣ ጅቡቲ፣ ጋቦን፣ ጊኒ፣ ማዳጋስካር፣ ማሊ፣ ኒጀር፣ ርዋንዳ፣ ሴኔጋል፣ ሲሼልስ (the Seychelles)፣ እና ቶጎ አሁንም አፊሴላዊ ቋንቋቸው (official language) ፈረንሳይኛ ነው) ተብላ ለሁለት ተከፍላ ነው የምትታወቀው። የሚገርመው ኢትዮጵያም ምንም በማይመለከታት ጉዳይ እንግሊዝኛ “ተናጋሪ” አገራት ምድብ ውስጥ መሆኗ ነው። እንግሊዝኛውም ሆነ ፈረንሳይኛው ምንጫቸው አፍሪካዊ ሳይሆኑ የቅኝ ግዛት ጦስ ጎትቶ ወደ አፍሪካ ያስገባቸው ናቸው። በመሆኑም የአፍሪካ ሥነጽሑፍ መለኪያም እራሳቸውን አለም አቀፍ ቋንቋ (global language) ብለው በሚጠሩት እንግሊዝኛ (በይበልጥ) እና ፈረንሳይኛ ቋንቋዎች ሆኑና አረፉት። ከእነዚህ ወጥቶ በራሱ ቋንቋ የፃፈ፣ እሱ ከሚዛን ውጪ ይሆናል ማለት ነው።
ከዚህ አኳያ የሚበረታታው፣ የሚደገፈውም ሆነ የሚደነቀው በእንግሊዝኛ የጻፈ፣ በእንግሊዝኛ የተጻፈ እና በእንግሊዝኛ ተናጋሪዎች ዘንድ መነበብ የቻለ ሆነ። በዚህ መስፈርት መሰረት የኢትዮጵያ ሥነጽሑፍ የጋን ውስጥ መብራት ሆኖ “ቀረ”። አህጉር አቀፍ የሥነጽሑፍ ጉባኤያት ሲካሄዱ እንኳ ኢትዮጵያን ማሳተፍ እየቀረ ሄደ። “ምክንያት?” ሲባሉ መልሱ “በእንግሊዝኛ ስለማትጽፍ” ነበር።
ጉዳዩን አበጥረው የሚያውቁት ደራሲና ሀያሲ አስፋው ዳምጤ በአንድ ረዘም ባለ ንግግራቸው (የማህበራዊ ጥናት መድረክ (FSS) አሳትሞታል) በአንድ ወቅት ኢትዮጵያ በእንግሊዝኛ ባለመፃፏ ምክንያት ብቻ በአፍሪካ ደረጃ በተካሄደ አመታዊ የሥነጽሑፍ ጉባኤ ላይ ሳትጋበዝ (ሳትሳተፍ) ቀርታለች።
እዚህ ላይ የዚህ ጽሑፍ አላማ ደራሲያን በእንግሊዝኛ መጻፍ አለባቸው የሚል አቋም ማራመድ አይደለም። የዚህ ጸሐፊ እምነት ማንኛውም ደራሲ በሚችለው፣ ይበልጥም አጣርቶ በሚያውቀው ቋንቋ ቢጽፍ ይመረጣል የሚል ነው። ወይም፣ በፈለገው ቋንቋ የመጻፍ መብቱ የተጠበቀ መሆን አለበት የሚል ነው። እንደ አገርም እንደዛው። የዚህ ጽሑፍ “ዴስቲኒ”ን ይዞ ወደ’ዚህ ገጽ ሲመጣ አላማው በእንግሊዝኛ እንዲጻፍ የሚፈልጉ ወገኖችን ጥያቄ የመመለስ ክፍተቶችን ሊሞላ ይችላልና እሰየው ለማለት ነው።
ክርክሩ ቀላል አልነበረም። አይደለምም። “እነ ወሌ ሶይንካ፣ ቹና አቼቤ፣ የደቡብ አፍሪካ ፀረ-አፓርታይድ ጸሐፍት ወዘተ (እነ Ngũgĩ wa Thiong’o, Steve Biko, Ama Ata Aidoo, Nadine Gordimer, Buchi Emecheta, Okot p’Bitek ጨምሮ ማለታችን ነው) ሊታወቁ የቻሉት በእንግሊዝኛ ስለ ጻፉ ነው” የሚል ወገን የመኖሩን ያህል፤ “እነ ፑሽኪን (እነ Ivan Turgenev, Fyodor Dostoevsky, Leo Tolstoy, and Anton Chekhov . . . ጨምሮ) በእንግሊዝኛ ጽፈው ነው ወይ የታወቁት? የጀርመኑ ጎተ (Johann Wolfgang von Goethe)ስ ቢሆን?” በማለት እየጠየቀ የሚከራከረው ወገንም ብዙ ነው። ከእነዚህ ሁሉ እሰጥ አገባዎች የምንረዳው አንድ መሰረታዊ ጉዳይ ቢኖር የመጻፊያ ቋንቋ ምን ያህል እያወዛገበ እንደ ሆነ ብቻ ሳይሆን፣ በማንኛውም ቋንቋ ይጻፍ ዋና ይዘቱ (ስራው) መሆኑን ነው።
እዚህ ላይ በእንግሊዝኛ መጻፍን በተመለከተ አንድ ሌላ አተያይ መኖሩንም መጥቀስ ተገቢ ይሆናል።
ጉዳዩን በገራገርነትና ቅንነት የሚመለከቱት አንዳንድ አጥኚዎች የትም ይሁኑ የትም የደራሲያን የመጻፊያ ቋንቋቸው እንግሊዝኛ ቢሆን ይመረጣል። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ለሰፊው አለም ተደራሽ ከመሆናቸውም በላይ ለዓለም ሥነጽሑፍ (World Literature) እድገት አስተዋፅኦ ማድረግ መቻላቸው ነው። (ይህ አተያይ የሚንፀባረቀው በዓለም ሥነጽሑፍ ተመራማሪዎች ዘንድ እንጂ ከ“ፖለቲካል (ኢን)ኮሬክትነስ” ጋር የሚገናኝ አይደለም።)
ወደ ራሳችን ስንመለስና በእንግሊዝኛ መጻፍ / አለመጻፍን በተመለከተ ያለውን የኋላ ታሪክ ስንመለከት በርካታ ጥናቶችን የምናገኝ ሲሆን፣ አንዱም የአቶ መላክነህ መንግሥቱን (አሁን ፒኤችዲ) Map of African Literature (ጃን. 2005) ነው።
መላክነህ በዚሁ መጽሐፋቸው፣ ገጽ 151 ላይ “IV. Ethiopian Literature in English” በሚል ንኡስ ርእስ ስር እንዳብራሩት በአማርኛም፣ በእንግሊዝኛም (በሁለቱም ቋንቋዎች) በመጻፍ አንቱ የተባሉ ኢትዮጵያዊያን በቁጥር በጣም ጥቂት ናቸው።
እንደ መላክነህም ሆነ ከዛ በፊትም ሆነ በኋላ በተደረጉ መሰል ጥናቶች ተደጋግሞ እንደተገለፀው በሁለቱም ቋንቋዎች (አማርኛ እና እንግሊዝኛ) ተሳክቶላቸው ዘመን ተሻጋሪ ስራዎችን የሰሩት በሶስት ቋንቋ (አማርኛ፣ ጉራጊኛ እና እንግሊዝኛ) የሚጽፉ ሁለገብ ደራሲ፣ ተርጓሚና ሃያሲ የክብር ዶክተር ሳህለሥላሴ ብርሀነማርያም፤ ከአጻጻፍ ዘይቤ እና ቋንቋ ተመራማሪነቱ ባሻገር ለአገራችን ሥነጽሑፍ አዲስ መንገድ ፈጣሪ መሆኑም በሚገባ የተረጋገጠለት ዳኛቸው ወርቁ፤ በዘመኑ የሙሉ ጊዜ ስራውን ድርሰት ያደረገ ብቸኛው የኢትዮጵያ ደራሲ አቤ ጉበኛ ሲሆኑ፤ እነዚህ ሶስቱ ብቻም ናቸው በአፍሪካ እውቅና አግኝተው “African Writers Series” (AWS) ዝርዝር ውስጥ ስማቸው ሰፍሮ የሚገኙት። ይህ ማለት ግን ስማቸው አይስፈር እንጂ ሌሎች የሉም ማለት አይደለም። አሉ። (እዚህ ላይ፣ “የመጻፊያ ቋንቋ[ዬ] አማርኛ ቢሆንም / ቀዳሚ ተግባሬና ግዴታዬ ሥራዬን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ማቅረብ ነው።” ያሉትን ጋሽ መንግሥቱ ለማንም ማስታወስ ይገባል። ሌሎችም በእንግሊዝኛ የመጻፍ ከፍተኛ አቅም ያላቸው፤ የጻፉም፤ ያልጻፉም መኖራቸውንም መገንዘብ አስፈላጊ ነው።)
ወደ የአሁን ዘመን ስራ፣ ወደ Destiny (2023) አሰፋ መኮንን (ፒኤችዲ) ስንመጣ ደራሲውን የምናገኘው በሁለት ቋንቋዎች በመጻፍ በኩል ኢትዮጵያዊያን ደራሲያን ከተሳካላቸው መካከል ሆኖ ነው።
ከኋላ ታሪኩም ሆነ በቅርብም ሆነ በሩቅ ከሚያውቁት መረዳት እንደተቻለው ዶ/ር አሰፋ ለረጅም አመታት ከኪነጥበብ (ድራማ፣ ፊልም፣ አማተርነት . . .) ጋር ቆይታ ያላቸው ሰው ናቸው። የተለያዩ ስራዎች (የታተሙም፣ ያልታተሙም) አሏቸው። ስክሪፕት መጻፍ ላይ ተግተው ሲሰሩ የቆዩ ሰው ሲሆኑ “የማቀይደርቅ እምባን” የመሰለ ግሩም ረጅም ልቦለድ ደራሲም ናቸው። በመሆኑም ወደ ፊት በሚደረጉ የባለሙያዎች ጥናቶችና ምዳቤዎች ደራሲ አሰፋን የሆነ ቦታ እንደምናገኛቸው መጠራጠር አይቻልም። ወደ “Destiny” (እጣ ፈንታ?) እንመለስ።
Destiny ራሱን ያቆመበት መሰረት፡-
“At the time, legal ways are closed tightly, The illegal ways will be opened widely”
(በወቅቱ፣ ሕጋዊ መንገዶች በጥብቅ ተዘግተዋል፤ [በተቃራኒው] ሕገወጥ መንገዶች በሰፊው ይከፈታሉ)
የሚል ቆምጨጭ ያለና ቆንጣጭ ሀሳብ ላይ ነው። ምንም እንኳን፣ በዚህ በሰለጠነውና በ21ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ ይህንን አይነት ነገር መስማትም ሆነ ማንበብ ውስጥን ቢነካም አሰፋ ግን በዚህ ሀሳብ ላይ ተንጠልጥሎ 254 ገፆችን ተጉዞ የሚለውን ሁሉ ብሏልና ሊደነቅ ይገባዋል። የአገራችንን ፖለቲካ፣ ስርአተ አስተዳደር፣ የአመራር ሁኔታ … አሳይቶበታልና “ዴስቲኒ” የተሳካለት ብቻ ሳይሆን አሁናዊ ማንነታችንን፤ በተለይም፣ የደለበውን ቢሮክራሲ በፍቅር እያዋዛ፤ በቤተሰብ ሁኔታ እየለወሰ፣ የፋብሪካና ድርጅቶችን ገመና እየገላለጠ… አሳይቶበታል።
ምንም እንኳን የዚህ ጽሑፍ ዐቢይ አላማ ክፍተትን መሙላት ላይ ያተኮረ እንጂ “Destiny”ን በሂሳዊ ብልሀት መፈተሽ አይደለምና ያንን ለሌላ ጊዜ አቆይተን አሁንም ስለ ደራሲው ጥቂት እንበል።
ደራሲ ዶ/ር አሰፋ መኮንን በዚህ ስራው እጅጉን እንደ ለፋበት ያስታውቃል። በባእድ ቋንቋ አይደለም ረዥም ልቦለድ፣ ደብዳቤ መፃፍ እንኳ ምን ያህል ክብደት እንዳለው፤ ምን ያህል የማሰቢያ ጊዜን እንደሚፈልግ . . . ይታወቃልና ለልፋቱ ዋጋ አለመስጠት እንጂ መስጡቱ የሚገርም አይሆንም። ምናልባት በአሁኑ ሰአት የዩኒቨርሲቲ መምህር መሆኑ ልፋቱን አቅሎለት ካልሆነ በስተቀር ይዞልን የመጣው አዲስ ስራ ለሥነጽሑፍ ቤተሰቦች ብቻ ሳይሆን ለማንኛውም አንባቢ ተመስገን የሚያሰኝ ነው።
ሌላው ደራሲውን ይበል የሚያሰኘው ሰው አማኝነቱና “እባካችሁ” ብሎ ለአስተያየት በሩን መክፈቱ ሲሆን፤ የዚህ መገለጫው ደግሞ የተለያዩ ባለሙያዎች (ምሁራን)ያዩለት፣ ይመዝኑለት፣ አስተያየታቸውን ይሰነዝሩለት፣ ከስህተት ይታደጉት፣ የበለጠ ተነባቢ ያደርጉለት ዘንድ . . . ወዘተ ስራውን መስጠቱ ነው። አዎ፣ እነሱም አላሳፈሩትም፤ በጠየቃቸው መሰረት አድርገውለታል፤ ለዚህም ውለታቸውን በ“ምስጋና” (Acknowledgments) ስር አስፍሮት ለአንባቢ አስተላልፎት ለማየት በቅተናል። ይህ ለማንም ጸሐፊ ነኝ ለሚል ሁሉ የሚመከር፣ ከህትመት በኋላም ለመጽሐፉ አንባቢያን ክብር የመስጠት የትጉሀን ተግባር ነውና ሊለመድ እንደሚገባ ሳናሳስብ ማለፍ ከባድ ይሆናል። (ምናልባት በዚህ መዘራረፍ አይን ባወጣበት በዚህ ዘመንና አለም . . . የሚል ተቃውሞ ካለ፣ ያ የህሊናና ሥነምግባር፤ ከፍ ካለም የሕግ ጉዳይ ነውና እሱን እዚህ ለማስተናገድ ጊዜም ቦታም የለም።)
በመጨረሻም፣ ለአገራችን (በተራዛሚውም ለዓለም) ሥነጽሑፍ፣ ለአንባቢያንና ለሥነጽሑሁፍ ባለሙያዎች አንድ እርምጃ ወደ ፊት የሆነውን፣ ኢትዮጵያዊያን ደራሲያን በእንግሊዝኛ አይጽፉም (ወይም “አቁመዋል”) የሚለውን ክፍተት ይሞላል ተብሎ የሚጠበቀውን … “Destiny”ን እዚህ ያነሳነው ከመጻፊያ ቋንቋ አኳያ፣ በአህጉርና ዓለም አቀፍ ደረጃ የነበረውን አጠቃላይ ሁኔታ ያስታውሰን፤ አንዳንድ ጉዳዮችንም አንስተን እንድንወያይ መነሻ ይሆነን ዘንድ በማሰብ እንጂ ሌሎች ቴክኒካዊ ጉዳዮች (ሥነጽሑፋዊ ጣጣዎች) ውስጥ ገብተን ስለ ስራው አስተያየት ለመስጠት እንዳልሆነ ቀደም ሲል ጠቆም ለማድረግ ተሞክሯል። ይህ ወደ ፊት የመሆኑ ጉዳይ እንዳለ ሆኖ እስከዛው ግን የዘርፉ ምሁራን “Destiny”ን መርምረው የራሳቸውን ሙያዊ አስተያየት ይሰጣሉ ብለን እንጠብቃለን። የወደፊት የሥነጽሑፍ (በተለይም የውጭ ሥነጽሑፍ) ተመራቂዎች ለመመረቂያ ስራቸው የሚሆን ትልቅ ግብአት አግኝተዋል ብለን እናስባለንና በእነሱም ጥናቶች በኩል ስለዚህ ረዥም ልቦለድ ብዙ እንሰማለን፣ እናነባለንም፤ ስለ ተነጋገርንበት “የመፃፊያ ቋንቋ”ም አንዳች ነገር ጠብ ይላል ብለን እንጠብቃለን።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ግንቦት 24/2015