የ2015 ዓ.ም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመውጫ ፈተና ከሐምሌ 3 እስከ 13 2015 ዓ.ም ድረስ ለመስጠት ማቀዱን ትምህርት ሚኒስቴር ማስታወቁ ይታወሳል። በ2015 ዓ.ም የመውጫ ፈተና ለመውሰድ የተመዘገቡ በግልና በመንግስት ተቋማት የሚገኙ እጩ ምሩቃን እና ባለፉት ዓመታት የህግ መውጫ ፈተና ወስደው የማለፊያ ውጤት ያላስመዘገቡ ተማሪዎች በመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች የመፈተኛ ማዕከላት ውስጥ ብቻ ፈተናውን እንደሚወስዱም ነው የተነገረው::
እኛም በፈተናውና አሰጣጥ እንዲሁም ተማሪዎች ተቋማትና ማህበረሰቡ ሊያደርጉ ስለሚገባቸው ዝግጀት በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ጥራትና ብቃት ማሻሻያ ዴስክ ኃላፊ እንዲሁም ተመራማሪና የፖሊሲ አማካሪ ከሆኑት አቶ ሰይድ መሀመድ ጋር ቆይታን አድርገናል:: ትምህርት ሚኒስቴር በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የተማሩና ዘንድሮ የሚመረቁ ተማሪዎችን የመውጪያ ፈተና ሰጥቶ ለማስመረቅ ዝግጅቱን ከጀመረ ቆየት ብሏል፤ በተለይም ባህላዊ ከሆነው የፈተና አሰጣጥ መንገድ ወጣ ብለን በቴክኖሎጂ የታገዝ ዘዴ ለመከተል እየሰራ መሆኑን አቶ ሰይድ ይናገራሉ::
‹‹በኦን ላይን ከመፈተኑ ጋር ተያይዞ እንደ ትምህርት ሚኒስቴር ስራውን ለመስራት የሚያስችል ሶፍት ዌር የማበልጸግ ስራ ይጠይቃል ፤ ይህንን ስራም በሁሉም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ ተደራሽ ሆኖ ልንጠቀምበት የሚያስችለን የበይነ መረብ ዝርጋታ ያስፈልጋል›› ያሉት አቶ ሰይድ በሌላ በኩል በሁሉም ተቋማት ላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለመፈተን በይነ መረብ የተገናኘባቸው ኮምፒውተሮች ስለሚያስፈልጉ ለማሟላት ስራዎች መጀመራቸውን አስረድተዋል::
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስፈላጊ ነገሮችን የማሟላት ስራን እየሰራ ሲሆን በተለይም ከበይነ መረብ ጋር የተገናኙ ምን ያህል ኮምፒውተሮች በየተቋማቱ አሉ የሚለውን ዳሰሳ አድርጎ እስከ አሁን ባለው መረጃ እንደ አገር በሁለም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ 34 ሺ የሚደርሱ ኮምፒውተሮች መኖራቸው ተረጋግጧል:: እንደ አቶ ሰይድ ገለፃ፣ ሶፍትዌር የማበልጸግ ስራው እንደ ትምህርት ሚኒስቴር ባለሙያዎችን ከተለያዩ ተቋማት በማውጣጣት ዝግጅት ተደርጓል:: የተፈታኞች መረጃም በተገቢው ሁኔታ ተሰብስቧል::
በዚህም ትምህርት ሚኒስቴር ለአሰራር በሚመቸው መንገድ በሲስተም ላይ እየተጫነ ይገኛል:: ፈተናውን በኦንላይን ለመስጠት በሚያስችል መልኩ የፈተና ጥያቄ ዝግጅቱም ተጠናቋል:: በኦላይን ፈተና ለመስጠት የሚያስችለው የትኛው የፈተና ዓይነት ነው ? እንዴትስ ነው የሚመረጠው ? ተማሪው እንዴት ገብቶ ይሰራል? እንዴት መመልከት ይችላል? የሚሉና ሌሎች ነገሮችንም ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቷቸው በመሰራት ላይ ናቸው:: ምልባት የሚቀረው ነገር ሲስተሙን ተማሪዎች እንዲለምዱት ለማድረግ የሚሰጠው የሙከራ ፈተና ነው::
የሙከራ ፈተናው ያስፈለገበትን ዋና ምክንያት አቶ ሰይድ ሲያስረዱ፤ ‹‹ተማሪዎች በአካዳሚክ እውቀታቸው በጣም ጎበዝ ሊሆኑ ይችላሉ፤ ነገር ግን ዲጂታል ቴክኖሎጂ ላይ ደግሞ አቅማቸው ውስን ሊሆን ስለሚችል ተማሪዎች ፈተናውን በደንብ ሰርተው ሲስተሙን ግን በአግባቡ መጠቀም ካልቻሉ ሊወድቁ ስለሚችሉና ይህ ደግሞ በተማሪውም እንደ አገርም የታለመለትን ውጤት ማምጣት ስለማያስችል ቴክኖሎጂውን በአግባቡ ሊጠቀሙበት የሚያስችለውን ክህሎት እንዲይዙ የሙከራ ጥያቄዎች ተዘጋጅተዋል›› ይላሉ::
እንደ አቶ ሰይድ ማብራሪያ፣ ሲስተሙ ዝግጅቱን አጠናቋል፣ አሁን ወደ ሙከራ ትግብራ መግባት ትችላላችሁ በሚባልበት ጊዜ የሙከራ ፈተናውን ተማሪዎች እንዲወስዱ ማድረግ ይቻላል:: ተማሪዎች ከምዝገባ ጀምሮ እስከ ፈተና መፈተንና ውጤት ማየት ድረስ በቴክኖሎጂ እንዲታገዙ መደረጉ ፈተናው ከሰው ንክኪ ነጻ፣ በጣም ቀልጣፋና ወጪ ቆጣቢ ያደርገዋል:: በተለይም እንደ አገር የህትመት ወጪ፣ ማጓጓዣ፣ የአራሚ መምህራንን ድካምና የመሳሰሉ ነገሮችን በማስቀረት ጥቅሙ ክፍ ያለ ነው:: ፈተናው በተሰጠ በአንድ ቀን ልዩነት ሁሉም ተማሪ ውጤቱን የሚያውቅበት መንገድ ይኖራል:: ሁሉም ተቋም የራሱን ተመማሪዎች ውጤት የሚያይበት ሁኔታ የሚፈጠር በመሆኑም ጥቅሙ ከፍ ያለ እንደሚሆን አቶ ሰይድ ይናገራሉ::
‹‹አሁን ላይ እንደ መንግስት የግል ከፍተኛ ትምህርፍት ተቋማት ፈተናውን ለመስጠት የሚያስችል መሰረተ ልማት ሊኖራችሁ ይገባል የሚባል እንደ ግዴታ የሚቀመጥ ነገር የለም›› የሚሉት አቶ ሰይድ ተቋማቱ ፍቃድ ሲያገኙ ሊያሟሉት የሚገባቸውን ትንሹን መመሪያ ተግባራዊ ማድረጋቸውን ታሳቢ ያደረገ ነው ይላሉ:: ከዚህ ውጪ ግን መንግስት በኦላይን የሚሰጠውን ፈተና ለመስጠት የሚያስችል መሰረተ ልማት በሚፈለገው ቁጥር ያሟሉ ካሉ ተቀባይነት አላቸው:: የሌላቸው ግን የግድ አሟሉ ተብለው ጫና የሚደረግበት ሁኔታ የለም::
አቅራቢያቸው ባሉ የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ ግብዓቶቹ ስለሚኖሩ ተቋማቱ ተማሪዎቻቸውን ለፈተናው ካዘጋጁ አገልግሎቱንም እዛው ያገኛሉ ማለት ነው:: ‹‹የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማቶቻችንን የፈተና ማዕከል በማድረግ እንጠቀምባቸዋለን::ከዚህ ውጪ ለግል ለመንግስት ብለን የምናደርገው ክፍፍል አይኖረም::በግል የሚማሩ ልጆች ፈተናው ይመለከታቸዋል:: ፈተናውንም በአቅራቢያቸው ባሉ የመንግስት ተቋማት መውሰድ ይችላሉ›› ሲሉም አቶ ሰይድ ተናግረዋል::
አቶ ሰይድ አክለውም ‹‹አሁን ላይ ከተማሪዎቻችን የምንፈልገው ትልቁ ነገር ፈተናውን ለመውሰድ ከፍ ያለ የስነ ልቦና ዝግጅት እንዲያደርጉ ነው:: ፈተናውን መውሰድ እችላለሁ፤ ፈተናውም ቢሆን መያዝ ከሚገባኝ ብቃት በላይ አይጠይቀኝም ፤የሚለውን በራስ መተማመናቸውን ማዳበር የግድ ይላል:: ተቋማትም ተማሪዎቻቸው ይህንን አይነት ስነ ልቦና እንዲያዳብሩ ማድረግ ይኖርባቸዋል::መውጪያ ፈተናውን ገና ሲያስቡት የሚፈሩ፣ አልሰራው ይሆናል የሚል ያልተገባ ነገር ውስጥ የሚገቡ ከሆነ በጣም ከባድ ስለሚሆን ተማሪዎች የስነ ልቦና ዝግጅት ያድርጉ›› በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል::
አቶ ሰይድ እንደሚያስረዱት፣ እንደ አገር በተለይም ቁልፍ የብቃት መለኪያዎች ተብለው በየትምህርት መስኩ ተለይተው የተዘጋጁና ተደራሽ የተደረጉ ሰነዶች አሉ:: ለአብነት በማኔጅመንት አልያም በሲቪል ምህንድስና የሚመረቅ ተማሪ የሚጠበቅበት ብቃት ምንድን ነው? የሚለውን የያዘ ሰነድ ተዘጋጅቷል::ይህ ደግሞ ስርዓተ ትምህርቱ (ካሪኩለሙ) ላይ ካለው ጋር ተመሳሳይ ነው:: በመሆኑም ፈተናው ስታንዳርዱን የሚያማላ ነው:: ተማሪዎች ይንን ተረድተው እኔ በዚህ ፕሮግራም ስመረቅ የሚጠበቅብኝ ብቃት ምንድን ነው? የሚለውን ሊያውቁና ሊረዱ ይገባል:: አንድ ተማሪ ይህንን ካላወቀ ግን የሚፈተነው ጥያቄ እንኳን የትኛውን ብቃቱን እየለካለት ስለመሆኑ አያውቅም ማለት ነው:: በመሆኑም የሚጠበቅበትን ብቃትና እውቀት ማወቅ ይጠይቃል::ይህንን ሲረዳ ክፍተቱንም ያውቀዋልና::
‹‹ሌላው ከተማሪዎች የሚጠበቀው ነገር ለዲጂታል ቴክኖሎጂ ራሳቸውን ቅርብ ማድረግ ነው::እዚህ ላይ ግን ትኩረት ሊደረግበት የሚገባው ጉዳይ ይህ የመውጪያ ፈተና በ2015 ዓም ተመራቂዎች ላይ ተግባራዊ ይሆናል ተብሎ የተነገረው ባለፈው ዓመት ጀምሮ መሆኑን ነው›› የሚሉት አቶ ሰይድ እናም እነዚህን ጊዜያት በአግባቡ የተጠቀሙ ተማሪዎች በእርግጠኝነት በፈተናው ውጤታማ ይሆናሉ የሚል እምነት አላቸው::ተማሪዎች ከዚህ በኋላ ያለውንም ጊዜ ለፈተናው ብቁ የሚያደርጓቸውን ዝግጅቶች ማድረግ እንደሚኖርባቸው አቶ ሰይድ አክለዋል::
የመውጪያ ፈተናው ሲሰጥ ተማሪዎች በየትምህርት ክፍላቸው የወሰዷቸውን ሁሉንም የትምህርት አይነቶች (ኮርሶች) የሚያጠቃልል ነው ወይስ እነዚህ ብቻ ናቸው የብቃት መለኪያው ላይ የሚካተቱ? ለሚለው ጥያቄ አቶ ሰይድ መልስ ሲሰጡ “…..በአንድ የትምህርት ክፍል ውስጥ በርካታ ኮርሶች ይሰጣሉ ፤ ነገር ግን ለመውጪያ ፈተና የሚወሰዱት ሁሉም አይደሉም፤ እዚህ ላይ ግን ሁሉም ኮርሶች የተማሪውን ብቃት የሚያሳዩ አንዱ የአንዱ ደጋፊና አብሮ የሚሄድ መሆኑን ሊዘነጋ አይገባም:: ነገር ግን አሁን እንደ ጅምር ተማሪዎቹን ሁሉንም ኮርሶች እንፈትናችሁ ብሎ ማጨናነቁም ተገቢ ስላልሆነ ዛሬ ላይ በመውጪያ ፈተናው የሚካተቱት ኮርሶች በጣም አስፈላጊና በትክክልም የተማሪውን ብቃት ያሳያሉ ተብለው የታመነባቸው የትምሀርት አይነቶች ናቸው” ብለዋል::
ፈተናውን ለመስጠት የታሰበው በዲጂታል ቴክኖሎጂ ቢሆንም ሰዎች መስራት አለባቸውና የፈተናው ሚስጥራዊነት የተጠበቀ ይሆን ዘንድ ግድ ነው:: ሚስጥራዊ መሆን ያለባቸው ጉዳዮች ምንም ጥያቄ የለውም ሚስጥራዊ ይሆናሉ፤ ሚስጥራዊ መሆን አያስፈልጋቸውም የተባሉ ነገሮችን ደግሞ በተለያዩ መንገዶች እየተገለፁ መሆኑን አቶ ሰይደ ያስረዳሉ:: ለምሳሌ አጠቃላይ ከሚወጡት ጥያቄዎች ውስጥ ምን ያህል በመቶው ከየትኛው ኮርስ የትኛውን ብቃት የሚለኩ የትኛውን የአቀባበል ሁኔታ የሚያሳዩ ናቸው በሚል ደረጃ ብሉ ፕሪንት ላይ መቀመጣቸውን ይጠቅሳሉ::
‹‹ይህንን ያደረግነው ለፈተናው ዝግጅት ማወቅና መረዳት ስለሚያስፈልግ ነው::በሌላ በኩል ደግሞ የፈተናው ዝግጀት እስከ መልስ ማሳወቅ ድረስ ያለው በሚስጥር የሚጠበቅ ይሆናል›› ይላሉ አቶ ሰይድ:: ከፈተናው ሚስጥራዊነት አንጻር ጎን ለጎን የሚቀመጡ ተማሪዎች እንኳን እንዳይኮራረጁ ጥያቄዎቹ ድብልቅልቅ ብለው የሚመጡበት አሰራር ተዘርግቷል::ሌላው ከሚስጥራዊነቱ ጋር ተያይዞ ተፈታኞች ገብተው ሲፈተኑ የራሳቸው ብቻ ታሳቢ አድርገው እንጂ የሌሎችን ሳይነኩ እንዲፈተኑ ስለሚያስፈልግ ሲስተሙ ላይ የራሳቸውን የሚስጢር ቁጥር (ፓስዋርድ) ተጠቅመው ነው ወደ ኮምፒውተሩ የሚገቡት:: ይህንንም የሚስጥር ቁጥር የሚያገኙት ፈተናውን ሊወስዱ ደቂቃዎች ሲቀሩ ብቻ ነው:: ሲስተሙ ቁጥር ብቻ ሳይሆን ፎታቸውንም ይቀበላል::
ተማሪው ፈተናውን ሰርቶ ውጤቱን ሲያስገባ ወዲያው አልያም ከሰዓታት ወይም ከቀናት በኋላ ውጤቱ ይገለጻል:: ይህ አካሄድ ደግሞ ኩረጃን በተሻለ መልኩ ይቀንሳል ተብሎ እምነትም ተጥሎበታል:: ከዚህ ውጪ በየፈተና ክፍሉ ፈታኝ መምህራኖች መንቀሳቀሳቸው እንደተጠበቀ ሆኖ በካሜራ የታገዘ ጥበቃም እንደሚደረግ ነው አቶ ሰይድ የተናገሩት :: ‹‹የመጀመሪያው ሁላችንም ልናምንበት የሚጋበው ጉዳይ ይህንን አገልግሎት የሚሰጥ አካል አገልግሎቱን ለሚሰጥበት ክፍያ ያስፈልገዋል የሚለውን ነው:: ከዚህ አንጻር ትምህርት ሚኒስቴርም ይሁን ሌላ አካል ፈተናውን በሃላፊነት ወስዶ በአስተዳደሩ የአገልግሎት ክፍያ ይጠይቃል:: ፈተናው ክፍያ ካልተፈጸመበት እንደ አገር ብክነት ያስከትላል›› ሲሉም አቶ ሰይድ አብራርተዋል::
እዚህ ላይ አቶ ሰይድ ተሞክራቸውን ሲናገሩም ‹‹የህግ ትምህርት መውጪያ ፈተና ላይ ቀድሞ ፈተናው ሙሉ ወጪ በመንግስት ነበር የሚሸፈነው፤ አንድ ዓመተ ምህረት ላይ ከ 3ሺ በላይ የሚሆኑ ተማሪዎች አሉ ተብሎ ከየተቋማቱ ዝርዝር መጣ፣ ነገር ግን በትክክል ሲፈተሽ ለፈተናው የተቀመጡ ተማሪዎች ቁጥር 1ሺ 118 ብቻ ነበር:: ይህ ፈተና በወረቀትም ስለነበር ከፍተኛ የሆነ ብክነት አስከትሏል:: ኪሳራውን እንደ አገር ስናስበው ደግሞ ብዙ ነው:: ተማሪው ወጪውን ይጋራ ተብሎ ሲመጣ ግን የሚፈተነው ተማሪ ቁጥር ብቻ ነበር እየተመዘገበ ይላክ የነበረው›› ብለዋል:: በመሆኑም ወጪንም ከመቆጠብ አንጻር አገልግሎቱን የሚያገኘው ተማሪ ክፍያ መፈጸሙ ተገቢ ነው ይላሉ::
ክፍያን በተመለከተ መመሪያ መዘጋጀቱን የጠቆሙት አቶ ሰይድ፣ ምናልባትም ሰሞኑን ለምክር ቤት ቀርቦ ከታየ በሀላ ሲጸድቅና ወደ ገንዘብ ሚኒስቴር ሲሄድ ይፍ እንደሚደረግ ገልፀዋል:: በዚህ መሰረትም ተፈታኝ ተማሪዎች ወጪያቸውን እንዲሸፍኑ ይደረጋል::የመንግስት ከፍተኛ ትምህፍርት ተቋማት ላይ በመደበኛው የቀን መርሃ ግብር የሚማሩት ግን የወጪ መጋራት ክፍያቸው ላይ ተደምሮ የሚከፍሉት ይሆናል:: ለጊዜው ግን የሚማሩበት ተቋም የሚከፍል ይሆናል:: ሌሎቹ ግን በሚጸድቀው ተመን መሰረት ላገኙት አገልግሎት የመክፈል ግዴታ አለባቸው:: ለመጀመሪያ ጊዜ ተፈትነው ያልተሳካላቸውና ሁለት ሶሰት ጊዜ ደጋግመው የሚፈተኑ ተማሪዎችን በተመለከተ ወጪውን እየከፈሉ አገልግሎቱን እንደሚያገኙ አቶ ሰይድ አስረድተዋል::
ፈተናው ለመጀመሪያ ጊዜ የሚሰጥ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ አንደ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ምን አይነት ችግሮች ሊያጋጥሙ ይችላሉ? ለሚለው ጉዳይ አቶ ሰይድ በሰጡት ማብራሪያ “ሊገጥሙን የሚችሉ ተግዳሮቶችን እንደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተማሪ እንዲሁም ማህበረሰብ ጉዳዩን በበጎ ጎን ይቀበሉታል የሚል እምነት አለን:: በበጎ የማይቀበሉ ከሆነ ለእኛ ተግዳሮት ነው::ምክንያቱም የትምህርትን ጥራት ለማረጋገጥ ከጀመርናቸው ስራዎች አንዱ የመውጪያ ፈተና በመሆኑ፤ በዚህ መልኩ የማይረዳ ማህበረሰብ ደግሞ ተግዳሮት ይሆናልና ይህንን ማብራራትና ማስረዳት የእኛ የቤት ስራ ነው” ብለዋል::
በሌላ መልኩ እስካሁን ባለው ሂደት ተቋማት ተማሪዎቻቸውን ከብቃት አንጻር በአግባቡ ሳያዘጋጁ ቆይተው ፈትነን ውጤታቸውን እናስተላልፋለን::አሁን ግን ሁለትና ሶስት ምዕራፍ አንብቡና ትፈተናላችሁ ከማለት ያለፈ የተማሪውን ሁለንተናዊ ብቃት የሚመዝን ፈተና መሆኑን ተረድተው ያላዘጋጁ ካሉ ችግር መፍጠሩ አይቀርም ይላሉ አቶ ሰይድ::‹‹ምናልባት ዛሬ ላይ ቆመን ምን ያህል ተማሪ ያልፋል አልያም አያልፍም የሚለውን ምጣኔ መተንበይ ባንችልም በተቻለ መጠን ተቋማት ከመስከረም ጀምሮ ተማሪዎቻቸውን እንዲያዘጋጁ እያደረግን ነው፣ እኛም በተለያየ ጊዜ ለፍተሻ ስንወጣ እያገዝን እየደገፍን ነው፤ ይህንን ድጋፍ ተጠቅመው ተማሪዎቻቸው ላይ የሰሩ ተቋማት አሉ ፤ ያልሰሩ ደግሞ ትንሽ ያዝ ያደርጋቸዋል ማለት ነው::በጠቅላላው እነዚህ ነገሮች በስራችን ላይ ችግር ሊሆኑ ይችላሉ›› በማለት አቶ ሰይድ አብራርተዋል::
የመውጪያ ፈተናውን ለመጀመሪያ ጊዜ ወስደው ያልተሳካላቸው ተማሪዎች ሁለት ሶስት ጊዜ እንዲፈተኑ መመሪያው ይፈቅዳል የሚሉት አቶ ሰይድ፣ ተማሪዎች ፈተናውን ለመፈተን ዝግጁ ነኝ ማለፍ የምችልበት ቁመና ላይ ነኝ ብለው ሲያምኑም መፈተን እንደሚችሉ ይናገራሉ:: በሌላ በኩልም ፈተናውን በመውሰድ ሂደት ላይ በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ነው ለሚባለው እስከ አሁን በዓመት ሁለት ጊዜ ይሰጣል ይላል መመሪያው:: ነገር ግን እንደ ትምህርት ሚኒስቴር በኦላይን ፈተናውን የሚሰጥ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር የሚሰራው የበይነ መረብ ዝርጋታ ውጤታማ የሚሆን ከሆነና በተቋማቱ ሁሉ የበይነ መረብ መቆራረጥ ካለተፈጠረና መብራትም በተመሳሳይ የማይቋረጥ ከሆነ ስድስት ወር መጠበቅ ሳያስፈልግ ተማሪዎች ደጋግመው ፈተናውን እንዲወስዱ ይደረጋል::መመሪያው ግን ሁለት ጊዜ እንደሚያስገድድ አቶ ሰይድ አስቀምጠዋል::
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 21 ቀን 2015 ዓ.ም