‹‹በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ተነሳሽነት በኢትዮጵያ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ለአራት ተከታታይ አመታት የተተገበረው አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከኢትዮጵያውያን ለኢትዮጵያውያን የተበረከተ ትልቅ መርሃ ግብር ነው:: መርሃ ግብሩ በርካታ ችግሮችን ለመፍታት ታቅዶ የተጀመረ ነው››ሲሉ የአረንጓዴ አሻራ የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢና የዘርፉ ተመራማሪ ዶክተር አደፍርስ ወርቁ ይናገራሉ::
የአረንጓዷ አሻራ መርሃግብር በኢትዮጵያ ውስጥ ያጋጠመውን ከፍተኛ የተፈጥሮ ሀብት መመናመን ችግር በከፍተኛ ደረጃ ይፈታል በሚል እሳቤ የተጀመረ መሆኑንም ነው የገለጹት:: የተፈጥሮ ሀብት መመናመን እየተባባሰ መምጣቱንና ይህም የሥርአተ ምህዳር አገልግሎቶች መጥፋትና መናጋት፣ የምርትና ምርታማነት መቀነስን እያስከተለ መምጣቱንም ዶክተር አደፍርስ ይጠቁማሉ:: ዘርፉ ለዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር ሚናው የጎላ ቢሆንም የተከሰተው ጉዳት የሥራ ዕድልንም በማሳጣት ተጽእኖ ማሳደሩን አመልክተዋል::
እነዚህን ክፍተቶች ማዕከል አድርጎ የተተገበረው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የደረቁ ጅረቶችንና መጠናቸው የቀነሰ የውሃ ሀብቶችን ለመታደግ፣ የአፈር እንክብካቤ ለማድረግ፣ በምግብ እህል ራስን ለመቻል፣ ሰዎች ከአካባቢያቸው ሳይፈናቀሉ የግብርና ልማታቸውን እንዲያሳድጉ በማስቻል ረገድ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን በማስገኘት ከፍ ያለ አስተዋጽኦ ማድረጉን አብራርተዋል::
በዚህ መልኩ ትልቅ ሆኖ የተካሄደው መርሃግብር ትልቅ ሆኖ መፈጸሙን በመጥቀስ፤ በሃገር መሪዎች የተመራ መሆኑም ለስኬቱ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል:: መርሃ ግብሩ ከመተግበሩ በፊት ቀደም ባሉት አመታት በአረንጓዴ ልማት ይከናወኑ ከነበሩት ተግባሮች ጋር ሲነጻፀር የተሻለ ሆኖ እንዳገኙትም ገልጸዋል:: በአራት አመታት ጊዜ ውስጥ 20 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ 25 ቢሊዮን መፈፀም ትልቅ ስኬት ተደርጎ እንደሚወሰድም አመልክተዋል::
ዶክተር አደፍርስ እንዳሉት፤ በዚህ ልማት ሥራ ውስጥ መልካም የሚባሉ በርካታ ተሞክሮዎች ተገኝተዋል:: ከነዚህ ውስጥም የፍራፍሬ ዛፎች መጠን በአርሶ አደሩ መሬት ላይ መጨመር በአብነት ይጠቀሳል:: ከዚህ ቀደም በማንጎ፣በአቦቮካዶ፣ በፓፓያና ሌሎችም የፍራፍሬ ልማቶች የማይታወቁ አካባቢዎች ተሳታፊ እንዲሆኑ መርሃግብሩ አስተዋጽኦ አደርጓል:: የፍራፍሬ ምርት ለውጭ ገበያ ማቅረብ የጀመሩ አካባቢዎች መኖራቸውንም ጠቅሰው፣ እነዚህም የስኬቱ ማሳያ ተደርገው እንደሚወሰዱም አመልክተዋል:: ፍራፍሬው ለመድረስ በሂደት ላይ የሆነባቸው አካባቢዎችም ተስፋ እንዳላቸውና ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት ጥቂት አመታት በፍራፍሬ ምርት ራስዋን የምትችልበት እድል ይፈጠራል የሚል እምነት እንዳላቸውም ገልጸዋል::
ዶክተር አደፍርስ ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ያለው የደን ሽፋን በቂ ነው የሚባል አይደለም ሲሉም ይናገራሉ:: ለዚህም በማሳያነት ያቀረቡት ኢትዮጵያ ውስጥ በቂ ደን ባለመኖሩ የደን ውጤቶች በሀገሪቱ በበቂ ሁኔታ እየተመረተ አለመሆኑን ነው:: በዚህ የተነሳም የደን ውጤቶች ከፍተኛ ወጭ ተደርጎ በግዥ ከውጭ እንዲገቡ ይደረጋል ይላሉ:: የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር መጠናከር እንዲህ ያለውን ችግር እንደሚፈታም ዶክተር አደፍርስ ይጠቁማሉ:: እስካሁንም በመርሃግብሩ በተከናወነው ተግባር ለኢንዱስትሪ ግብአትና ለማገዶ የሚሆኑ ደኖችን በአርሶ አደሩ አቅራቢያ መፍጠር እየተቻለ መሆኑንም አመልክተዋል::
ለማገዶና ለሌሎች የተለያዩ አገልግሎቶች ጥቅም ላይ የሚውለው የማገዶ እንጨትን በቀላሉ በአካባቢው እንዲገኙ በማድረግ በተለይም ማገዶ በመልቀም ጊዜና ጉልበታቸው የሚባክን ሴቶችን ድካም ለመቀነስ መልካም አጋጣሚ እየተጠፈረ መሆኑን ጠቅሰው፣ ማህበረሰቡ የማገዶ ፍጆታውን በአካባቢው ለማሟላት ጥረት እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል:: ይህም ማገዶ ፍለጋ በሚል እንደ ባሌ፣ ጭሊሞ፣ ቦንጋ በመሳሰሉት ትላልቅ የተፈጥሮ ደኖች ውስጥ በመግባት ይደርስ የነበረውን ከፍተኛ ጭፍጨፋ እንዲቀንስ በማድረግ አስተዋጽኦ አድርጓል ሲሉ ያብራራሉ::
በዚህ የዛፍ ችግኝ ተከላ ሀገር በቀል ዝርያዎችን በስፋት መትከል እየተለመደ መምጣቱንም ጠቅሰው፣ በመርሃግብሩ ከዚህ በፊት ባልተለመደ መልኩ በሰብል ልማት ብቻ የሚተገበረው በበልግ የማልማት ሥራ በዛፍ ችግኝ ተከላም መጀመሩን ዶክተር አደፍርስ አስታውቀዋል:: በበልግ የደን ልማት ወይንም የዛፍ ችግኝ ተከላና የፍራፍሬ ልማት መጀመሩን አመልክተዋል:: እንደ ዶክተር አደፍርስ ማብራሪያ ፤መርሃግብሩ የዛፍ ችግኞችን በመትከል ላይ ብቻ ያተኮረ አይደለም፤ የተከናወኑ ሥራዎች በመረጃ እንዲጠናከሩ እንዲሁም ለዜጎች የሥራ እድል እንዲፈጠርላቸው ማድረግም ተችሏል:: በዚሁ መሠረትም ተከላ የተከናወነባቸው አካባቢዎች ካርታ እንዲኖራቸው ተደርጓል::
በሥራ ዕድሉ ወጣቶችና ሴቶች ተጠቃሚ ሆነዋል:: በተፈጠረው ግንዛቤም በአካባቢ ጥበቃ ላይ ንቁ ተሳታፊ የሆነ ማህበረሰብ መፍጠር እየተቻለ ነው:: እነዚህ በአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር የተገኙ መልካም ውጤቶች ናቸው:: ሀገራዊ ንቅናቄው ጥቅሞችን በማስገኘቱም ክልሎች የዛፍ ችግኝ ተከላውን አጀንዳቸው አድርገው ይዘውታል፤ የመርሃግብሩን አፈጻፀም ለከፍተኛ ስኬት ያደረሱትም በእዚህ መልኩ በመስራታቸው ነው:: ቁጥሩ 20 ሚሊየን የሚደርስ ህብረተሰብ ተሳትፎም የታየበትም ጠቀሜታ ታይቶ ነው::በሁለተኛው ምዕራፍ፣ ከ2015 እስከ 2018 በጀት አመት ‹‹አረንጓዴ አሻራችን ለዘላቂ ልማታችን›› በሚል መሪቃል በሚተገበረው የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ለተከላ ከሚዘጋጁት ችግኞች ውስጥ እስከ 70 በመቶ የሚሆኑት የፍራፍሬ ዛፎች እንደሆኑም ዶክተር አደፍርስ ገልጸዋል::
እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ መርሃግብሩ እንደሀገር በምግብ እህል ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት ለማጠናከር የጥምር ደን እርሻን ማዕከል በማድረግ በተለይም ለምግብነት የሚውሉ የፍራፍሬ የዛፍ ችግኞችን በብዛት በገበሬው ማሣ ላይ እንዲተከሉ ይደረጋል:: መርሃግብሩ በዚህ መልኩ ተጠናክሮ ከቀጠለ ከተወሰኑ አመታት በኃላ የኢትዮጵያ ገበሬ እንደሚኖርበት ሥርአተ ምህዳር ፍራፍሬን ከጓሮው የሚጠቀምበት እድል ይፈጠራል:: ከራሱ ፍጆታም አልፎ ለገበያ በማዋል ኢኮኖሚውን ለማሳደግ ይችላል:: ለተከላ የሚዘጋጁት የፍራፍሬ የዛፍ ችግኞች ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው፣ የሀገሪቱን የአየር ሁኔታም ታሳቢ ያደረጉ ይሆናሉ:: በሁለተኛው ምእራፍ ጥራትን መሠረት ያደረገ የዛፍ ችግኝ ተከላ እንደሚከናወንም ዶክተር አደፍርስ ገልጸዋል::
ኢትዮጵያ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ አራት አመታት የተገበረችውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር አፈፃፀም እንዲሁም በሁለተኛው ዙር ደግሞ ‹‹አረንጓዴ አሻራችን ለዘላቂ ልማታችን›› በሚል መሪ ቃል ለመተግበር ያደረገችውን ዝግጅት አስመልከቶ ባለፈው ሳምንት የዘርፉን ምሁራንና ባለድርሻ አካላት ያሳተፈ የምክክር የጋራ መድረክ መካሄዱ ይታወሳል:: ከተሳታፊ አጋር ድርጅቶችም የጀርመን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ (ጂ አይ ዜድ) አንዱ ነበር::
ድርጅቱን በመወከል በምክክር መድረኩ ላይ የተገኙት በጂ አይ ዜድ የፕሮግራም ኮፖናንት ማኔጀር አቶ መላኩ ታደሰ፤ ጂ አይ ዜድ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር እየሰራ እንደሚገኝ ይናገራሉ:: በዋናነትም ድርጅቱ በስልጠናና በክትትል የአቅም ግንባታ ድጋፍ እንደሚያደርግም ይገልጻሉ:: እሳቸው እንዳሉት፤ በአቅም ግንባታ ድጋፉ አርሶ አደሩን፣ የልማት ሰራተኞችን፣ የግብርና ባለሙያዎችን አቅም ይገነባል:: ሁሉም እንደየሙያ ድርሻቸው ሥራቸውን እንዲወጡ የሚያስችል ስልጠና ይሰጣል:: ክትትልም ያደርጋል:: ለፖሊሲ የሚረዱ ሀሳቦችን በማመንጨትም እገዛ ያደርጋል::
ጂ አይ ዜድ በዚህ መንገድ ኢትዮጵያ ውስጥ ሲሰራ ወደ 60 አመት ማስቆጠሩንና ሥራውንም ሲጀምር የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎችን፣ በተለይ በሥነ ህይወታዊና በአካላዊ ሥራዎች ላይ ትኩረት በማድረግ አካባቢዎቹ እንዲያገግሙ የማድረግ ተግባር እንደሆነ አቶ መላኩ አመልክተዋል:: በሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ የኢኮኖሚ ጠቀሜታን ማሳደግ በሚለው ላይ እንደሚያተኩር ጠቁመዋል:: እርሳቸው እንዳሉት፤ አካባቢው አንዴ ካገገመ በኃላ ምርት የሚሰጥ በመሆኑ ምርታማነቱ በምን አይነት ሁኔታ መሆን እንዳለበት አርሶ አደሩ ከልማቱ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆን ማስቻል ላይ ይሰራል:: የግብርና ሥራ ‹‹አርሶ አደሩ እያለማም እየበላም የሚካሄድ መሆን አለበት›› የሚል እሳቤ በተደጋጋሚ ከዘርፉ ምሁራን እንደሚነሳ ጠቅሰው፣ ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት መደረጉን አመልክተዋል::
ሁለተኛው ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብርን ለመደገፍ በጀርመን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ በኩል ስላለው ዝግጁነትም እንደገለጹት፤ በአረንጓዴ አሻራ ላይ ምርጥ ተሞክሮ ተገኝቷል፤ ይህን ተሞክሮ በመቀመር የማስፋት ሥራ በዋናነት ትኩረት የሚሰጠው ተግባር ይሆናል::ድርጅቱ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ከመንግሥት ጋር በቅርበት እያከናወነ ያለውን ሥራ ለማጠናከር ከአረንጓዴ አሻራ ጋር የሚሄድ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ እንደሚገኝም አቶ መላኩ ጠቁመዋል:: ማዕቀፉ በርካታ አርሶ አደሮችን የሚያሳትፍና ሰፊ የሥራ ዕድልም የሚፈጥር እንደሆነም ጠቁመው፣ ሰፋፊ የሆኑ ቦታዎችንም በልማት ለመሸፈን መታቀዱን ይገልጻሉ:: በደን መሬትን በስፋት ማልማትም ራሱን የቻለ ተግባር ተደርጎ እንደሚከናወን ይናገራሉ::
በኢትዮጵያ ለአራት ተከታታይ አመታት ከተተገበረው የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር የተገኙ መልካም ተሞክሮዎች፣ የታዩ ክፍተቶችና ተግዳሮቶች ተቀምረው አዲስ ዘላቂ የመሬት አያያዝ ፕሮግራም መንደፍም የማዕቀፉ አንዱ አካል መሆኑን ነው አቶ መላኩ የጠቆሙት:: በጂ አይ ዜድ ሊከናወን የታቀደው የዛፍ ችግኞች የተተከሉባቸው የለሙ አካባቢዎች በሰው ሰራሽና በተለያየ አደጋ ለጉዳት እንዳይጋለጡ ወይንም እንዳይደናቀፉ፣ ከአቅም በላይ በሆነ ነገርም ለአደጋ ሲጋለጡ ወይንም ችግር ሲፈጠር ከተለያዩ አካላት ድጋፍ አሰባስቦ ለድጋፍ እንዲውል የማድረግ እንደሆነ አስረድተዋል:: በጂ አይ ዜድ በኩል የእርዳታ መዋዕለነዋዮች መኖራቸውን አመልክተዋል::
በተለይም በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ጦርነት ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመርዳት ከዚህ የእርዳታ መዋዕለነዋይ ከፍተኛ ገንዘብ ድጋፍ መደረጉን ጠቅሰው፣ በተደረገው የገንዘብ ድጋፍም በ20 ወረዳዎች የሚገኙ 40ሺ የሚሆኑ አባወራዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቁመዋል:: ድጋፉ አርሶ አደሮች ለግብርና ሥራቸው የሚያግዝ የእርሻ መሣሪያና ለገቢ ማስገኛ የሚሆኑ የቤት እንስሳት ገዝቶ በመስጠት፣ በተፈጥሮ ሀብቱ ላይም እንክብካቢ እንዲያደርጉ፣ ምርጥ ዘርም አግኝተው እንዲያመርቱ የሚያስችላቸው ነው ብለዋል::
ዓለምአቀፉ ማህበረሰብ ኢትዮጵያ ለተከታታይ አመታት ስላከናወነችው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ያለውን አመለካከት እንዲሁም በድርጅታቸው በኩል እየተደረገ ስላለው ድጋፍ ሲያስረዱ ‹‹አጋር ወይም ድጋፍ የሚያደርጉ አካላት ሁልጊዜ የሚያዩት ያለውን ተነሳሽነት፣ የሀገሪቱ መንግስት ይደግፈዋል ወይ? የሚሰሩት ሥራዎች ከሀገራዊና ዓለምአቀፋዊ ስምምነቶች ጋር የሚሄዱ ናቸው ወይ የሚሉትን ለማረጋገጥ ባለሙያ በመላክ ያስጠናል›› ይላሉ:: ከዚህ ሁሉ ሂደት በኋላ የሚቀርቡትን የድጋፍ ጥያቄዎች እንደሚቀበሉ ይገልጻሉ::
ኢትዮጵያ የተገበረችው አረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ለሌሎችም አስተማሪና በአርአያነት የሚጠቀስ ነው ያሉት አቶ መላኩ፣ ኬንያና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የኢትዮጵያን አርአያ ለመከተል ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ይጠቅሳሉ:: ሌሎችም የአፍሪካ ሀገራት ይህንኑ ለማድረግ ጥረት እያደረጉ እንደሆነ ገልጸዋል:: አቶ መላኩ ‹‹እንዲህ ያሉ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ ጅማሮ ያለው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው::
ኢትዮጵያ በዚህ ትታወቃለች:: አፈር፣ ውሃ በማቀብ፣በተራሮች ላይ እርከኖችን በመሥራት ሰፊ ልምድ አላት:: ወደ ሀገሪቱ በመምጣት ልምድና ተሞክሮ የወሰዱ ሀገራትም ብዙ ናቸው›› በማለት ይናገራሉ:: ሀገሪቱ በዚህ ሥራዋም ከዓለም ባንክ ድጋፎችን እንድታገኝ አስችሏታል ብለዋል:: ኢትዮጵያ በተፋሰስ ልማት ለምታከናውነው ሥራ የጀርመን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲም ሆነ ሌሎችም ዓለምአቀፍ ድርጅቶችና ሀገሮች ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኙም አስታውቀዋል::
አረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ገና ከአሁኑ ብዙ ቱሩፋትን እያስገኘ እንደሆነ ከባለሙያዎቹ ገለፃ መገንዘብ ይቻላል:: ስራውን በጥራት መሥራትና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማሳደግ ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት ይጠበቃል:: ይህ ደግሞ የአንድ አካል ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን፣ የደን ባለሙያውን፣ መርሃግብሩን በመቀበል የችግኝ ተከላውን በዘመቻ እያከናወነ ያሉትን አካላትና የአርሶ አደሩን ርብርብ ይጠይቃል::
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 21 ቀን 2015 ዓ.ም