የኢትዮጵያ የፋሽን ኢንዱስትሪ ገና ጨቅላ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ:: ከሰው ሀይል ልማት እና ከግብአት አኳያ ዘርፉ ብዙ ርቀት እንዳልተጓዘ ባለሙያዎቹ ይጠቁማሉ:: እንዲያም ሆኖ ግን አሁን ጥሩ ሁኔታ እንዳለም ነው የሚመሰክሩት:: ዘርፉ እውቅና ያተረፉ ባለሙያዎች አሉት:: የተለያዩ የኢንዱስትሪው መድረኮችም እየተካሄዱ ናቸው:: አልባሳትን በተለያየ ዲዛይን አዘጋጅተው የሚያቀርቡ ተበራክተዋል፤ በተለይም በሀገር ባህል አልባሳት ላይ ብዙ እየተሰራ ነው::
እነዚህ ሥራዎች ግን በልምድ በአጫጭር ጊዜ ስልጠናዎች የተገኙ እንጂ በትምህርት የታገዙ አይደሉም:: የፋሽን ባለሙያዎች ወይም ዝንባሌው ያላቸው አካላት ትምህርት ቤቶችን ከፍተው ስልጠናዎችን ሲሰጡ ቆይተዋል:: ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በከፍተኛ ትምህርትና በቴክኒክና ሙያ ትምህርት ተቋማት ጭምር የፋሽን ዲዛይኒንግ የትምህርት ክፍሎች ተከፍተው ትምህርቱ እየተሰጠ ይገኛል:: ትምህርት ከሚሰጡት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መካከልም የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቴክስታይልና የፋሽን ቴክኖሎጂ አንስቲትዩት ይጠቀሳል:: በአንስቲትዩቱ የፋሽን ዲዛይኒንግ ትምህርት ክፍል በ2003 ዓ.ም ከተከፈተበት ጊዜ ጀምሮ ኢንስቲትዩቱ ብዛት ያላቸው የፋሽን ዲዛይኒንግ ባለሙያዎችን አስተምሮ ለኢንዱስትሪው አበርክቷል::
የኢንስቲትዩቱ የፋሽን ዲዛይኒንግ ትምህርት ክፍል መምህር እስጢፋኖስ ምንቸግሮት እንደገለጹት፤ የትምህርት ክፍሉ የፋሽን ዲዛይነሮችን አስተምሮና አብቅቶ ለገበያ በማቅረብ ላይ ይገኛል:: ‹‹በአውሮፓም ሆነ በአሜሪካ በፋሽን ዘርፍ በጣም ትልቅ ደረጃ ላይ ከደረሱ ሰዎች ወይም ሀገራት ልምድ እንደምናየው የፋሽን ኢንዱስትሪው ያደገው ዲዛይነሮቻቸው በሚሰሩት ሥራ ነው›› ሲሉም መምህር እስጢፋኖስ ያስረዳሉ:: እርሳቸው እንዳሉት፤ ከኢንዱስትሪው ቀድሞ የሚፈጠረው ዲዛይነሩ ሲሆን፤ ዲዛይነሩ ተጠቦበት የሚፈጥረው ሥራ ደግሞ የፋሽን ኢንዱስትሪው ጎልቶ እንዲወጣ የሚያደርገው ነው::
በፋሽን ኢንዱስትሪው ኢትዮጵያ ያለችበት ደረጃ ከሌሎች ሀገራት አንጻር ሲታይ ገና ጀማሪ ናት:: ትላልቆቹ ዲዛይነሮች የሚባሉት እንደ ፓራዳይዝ ፋሽን እና ሌሎችም ዲዛይነሮች ወደዚህ ሥራ የገቡት የዛሬ 25 ዓመት እና ከዚያ በፊት ገደማ ነው:: በኢትዮጵያ ደግሞ ዘርፉ መነቃቃት የጀመረው በቅርብ ነው:: ባለሙያው እንደባለሙያ መጠራት የጀመረውም እንዲሁ በቅርብ ጊዜ ነው::
‹‹በተቋሙ የትምህርት ክፍሉ አስፈላጊነቱ በመንግሥት ታምኖበት ሲመሰረት የፋሽን ኢንዱስትሪው ኃላፊነት በመውስድ መሸከም የሚችሉ ባለሙያዎችና ዲዛይነሮች ለዘርፉ ያበረክታል በሚል ነው›› የሚሉት መምህር እስጢፋኖስ፤ እስካሁን ባለው ሁኔታ አብዛኞዎቹ በኢንዱስትሪ ፖርኮች፣ በትላልቅ ኩባንያዎች፣ በቴክኒክና ሙያ ተቋማት እና በተለያዩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚያስተምሩ መምህራን ከዩኒቨርሲቲው የወጡ ባለሙያዎች መሆናቸው ተናግረዋል:: ‹‹የፋሽን ኢንዱስትሪው ዘርፍ በጣም ብዙ የተማረ የሰው ኃይል ይፈልጋል:: የሰው ኃይል ማፍራቱ በአንድ ተቋም የሚሸፈን ሳይሆን፣ በተለያዩ ተቋማት በርካታ ባለሙያዎች ማፍራትን የሚያጠይቅ ነው›› ሲሉም ይገልጻሉ::
በአሁኑ ጊዜ በሙያው ላይ የሚገኙት ከባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የተመረቁ መሆናቸውን ያስታወሱት መምህር እስጢፋኖስ፤ ከማስተማሩ ስራ ወጥተው በፋሽን ኢንዱስትሪው ዘርፍ ተፅእኖ መፍጠር የቻሉና ትልቅ ደረጃ ላይ የደረሱ ባለሙያዎች መኖራቸውንም ይጠቅሳሉ:: እርሳቸው እንዳሉት፤ የትምህርት ፕሮግራሙ ሲከፈት የተቀመጠለትን ዓላማ ያሳኩ ዲዛይነሮች፣ በፋሽን ኢንዱስትሪው ላይ በስም የምንጠራቸው በጣም ታወቂ ፣ የሥራ እድል የፈጠሩና መሽጫ ቦታዎች ያሏቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ መወዳደር የሚችሉ ዲዛይነሮች መፍጠር ተችሏል::
‹‹በዘርፉ ተወዳዳሪ ለመሆንና ትልቅ ደረጃ ለመድረስ ግን ጊዜ ይወስዳል::››ያሉት መምህር እስጢፋኖች፣ አሁን ባለንበት ልምምድ ግን የሚፈለገው ደረጃ እየደረስን ነው ይላሉ:: ለአብነትም እንደነ ቤተልሔም ወንድሙ፣ አስኳል አለሙ፣ አልሳቤት ጥበቡ እና ሌሎችንም በስም ሊጠቀሱ የሚችሉ በሚሰሩት ሥራ ትልቅ እውቅና ትላልቅ ብራንድ ያላቸው ዲዛይነሮች ማፍራት መፍራት መቻሉን አመልክተዋል:: በባህላዊውም ሆነ በዘመናዊው የዲዛይኒንግ ዘርፍ ላይ በደንብ አድርገው እየሰሩ ያሉ የሀገራችን ዲዛይነሮች እየበዙ መምጣታቸውን ጠቅሰው፤ በተመሳሳይ አሁን ላይ ብቅ እያሉ ያሉ አዳዲስ ዲዛይሮች መኖራቸውን ተናግረዋል ::
አብዛኛውን የፋሽን ዘርፉ ሙያ በልምድ እና በሰው ሰው ቅብብል የመጣ መሆኑን ጠቅሰው፣ ሙያውን በእውቀት የታገዝ አድርጎ፣ ሙያው የሚፈልገው ደረጃ አስጠብቆ መሄድ ያስፈልጋል ይላሉ:: ኢንዱስትሪው የሚፈልገው አይነት እውቀትና ክህሎት ያላቸው ባለሙያዎችን በማፍራት ወደ ገበያው በመግባት ተወዳዳሪ መሆን እንደሚገባም ገልጸው፣ የፋሽን ኢንዱስትሪው በዋነኝነት የሚፈልገው ይህንን መሆኑን መምህር እስጢፋኖስ አስታውቀዋል::
ይህ ሲሞላ ቀጥሎ የሚመጡት ጥሬ እቃ የሚያቀርቡ አካላትና ሌሎች የአቅርቦት ሰንሰለቱ ላይ ያሉት በሙሉ ይነቃቃሉ፤ ዘርፉን ሊመራው የሚችል ባለሙያ ከሌለ ግን የሚሰራው ሥራ ሁሉ በልምድ የሚሰራ ይሆናል ማለት ነው ሲሉ ያብራራሉ:: ፋሽን በባህሪው መሠረታዊ ነገር እንዳልሆነ ጠቅሰው፣ ኢንዱስትሪው ደግሞ ከመሠረታዊነት መውጣት እንደሚፈልግ ይናገራሉ:: አሁን ለዘርፉ በጣም መሠረታዊው ነገር ባለሙያው ነው ብለዋል ::
እሳቸው እንዳብራሩት፤ የትምህርት ክፍሉ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን በየዓመቱ ቢያንስ 50 ያህል ተማሪዎች ያስመርቃል:: በዩኒቨርሲቲ የተካሄደ ጥናት እንደሚያሳየው ካሉት ከሰባት ያህል ፕሮግራሞች ከተመረቁ ተማሪዎች ውስጥ የፋሽን ዲዛይኒንግ ዘርፍ ሥራ በመፍጠር ረገድ የተሻለ ነው:: በዘርፉ ከተመረቁት 80 በመቶ ያህሉ ተመራቂዎች ሥራ ፈላጊ ሳይሆኑ ሥራ ፈጣሪ መሆን የቻሉ ናቸው::
‹‹እንደ ሀገር የፋሽን ኢንዱስትሪው ገና ጀማሪና ብዙ ሥራ መስራት የሚጠበቅበት፣ በጣም ብዙ ባለሙያ የሚፈልግ ዘርፍ ነው›› የሚሉት መምህሩ ፤ አሁን ላይ እንደሀገር ያለው አጀማመራችን በጣም ተስፋ ሰጪ ነው ይላሉ:: የፋሽን ኢንዱስትሪው ገበያም ቢሆን በጣም ጥሩ የሚባል ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ነው የተናገሩት:: ህብረተሰቡ ለፋሽን ኢንዱስትሪው ያለው አመለካከት እየተቀየረና መሻሻሎች እያሳየ መሆኑን ገልጸው፣ ምርቶችን ለመጠቀምም ሆነ ዲዛይነሮችን በማበረታተት የሚሰጡ ገንቢ ሀሳቦች በዘርፉ ተሰማርተው ላሉ ባለሙያዎች ብርታት፣ ጠንካሬና አቅም እንደሚሆኑም ተናግረዋል::
‹‹የፋሽን ዘርፉን አሳድጎ በዓለም ላይ ተፅእኖ ፈጣሪ እንዲሆን ለማድረግ ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት›› የሚሉት መምህሩ፤ የዘርፉን ትምህርት እንደሚሰጥ አካል ተማሪዎች ሙያው የሚጠይቀውን ክህሎትና እውቀት ይዘው እንዲወጡ ሙያዊ ሥነ ምግባራቸው ለሥራው የተመቸ እንዲሆን ማድረግ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል:: ለዚህም ትምህርት ክፍሉ በዚያ መንገድ ገበያ ውስጥ ገብተው በደንብ ሊሰራ የሚችል የሰው ኃይል ማፍራት ትልቁ ድርሻውን እየተወጣ እንደሆነም አመልክተዋል::
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 21 ቀን 2015 ዓ.ም