
የሰው ልጅ ሁሉን የሚያደርገው ጊዜን ተጠቅሞ ነው። ዘግይቶም ሆነ ፈጥኖ፤ አርፍዶም ሆነ ቸኩሎ ሁሉን የሚፈፅመው ጊዜን ተንተርሶ ነው። እያንዳንዱ እንቅስቃሴውም በጊዜ መቁጠሪያ የተሰፈረ ነው። እርግጥ የጊዜ አጠቃቀም ከሰው ሰው ቢለያይም ማንም ሰው ከጊዜ ኡደት ውጪ ሊሆን አይችልም። ሁሉም የሚሆነው በጊዜ ነውና!
ጊዜ እንደተጠቀሙበት ነው። ጊዜን በአግባቡ መጠቀም ብዙ ማግኘትና ማትረፍን ያጎናፅፋል። በተቃራኒው ጊዜን ማባከን ብዙ ያከስራል፤ ብዙ ያሳጣል። አንዳንድ ሰው አመቱ ሲያልቅ ይነቃል። ‹‹ወይኔ! ወይኔ! ይህን ዓመት ምንም ሳልጠቀምበት ሌላ አዲስ አመት መጣ›› ይላል። ሌላው ደግሞ ወሩ ሲያልቅ ብንን ይልላል። ‹‹መስከረምን ሳልጠቀም ጥቅምት ገባ›› ይላል። አንዳንዱ ሳምንቱ ሲያልቅ ‹‹ከምኔው እሁድ ደረሰ! እንደው እስከ ሰኞ ድረስ ምን ሠራሁ?›› ይላል።
ንቃ ያለውና የተሻለው ደግሞ ማታ አልጋ ላይ ሊተኛ ሲል ‹ምን ሳደርግ ዋልኩኝ፤ ቀኑ በቃ እንደዚሁ ሲባክን ዋለ›› ይላል። አያችሁ! በሕይወታችን ውስጥ ጊዜው የሚነጉደው ሳንጠቀምበት ነው። የሚቆጨን ግን የሆነ ሰዓት ነው። ከባከነ በኋላ ነው። ከዚህ በኋላ ግን የሚባክን ጊዜ የለም። የምናጠፋው፤ የምናቃጥለው ጊዜ የለም። እንዴት? ካላችሁ መልሱ ይኸው።
እርግጠኛ ነኝ ተጨማሪ ገንዘብ ታገኛለህ። ተጨማሪ ጊዜ ግን የለም። ብትለፋ፤ ብትሮጥ፤ብትሠራ ገንዘቡ ያድጋል። ጊዜህን ግን አትገዛውም። ማንም ጊዜን አይሸጥልህም። እንዲያውም አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ። አንተ መሆን የምትፈልገው ምርጥ ሰው ጊዜውን ያባክናል? እንደዚህ ነው ጊዜውን የሚጠቀመው? በጊዜ እሱም መልሶ ይቀልድብሃል። ካከበርከው ደግሞ መልሶ ያከብርሃል። እያጠናህ ወይም ሥራ እየሠራህ ይሆናል። ስልክህ ከኪስህ አውጥተህ ቀልድ ታያለህ። ወይ ደግሞ ከጓኞችህ ጋር ትቀልዳለህ፤ ትጫወታለህ። ትንሽ ቆይታ ሕይወት ትቀልድብሃለች። ለምን? ሕይወትን ንቀሃታላ። ጊዜህን አላከበርከውም። እሱም መልሶ አያከብርህም።
አንድ ሰው ሁሌ ውሻው ያስቸግረዋል። መኪናውን ይዞ በመጣ ቁጥር እየተከተለው ይጮሃል። የት ድረስ እንደሚከተለው አይታወቅም ተከትሎት ግን ይጮሃል። የሆነ ጊዜ ጎረቤቱ ይመጣና ‹‹እኔ የሚገርመኝ እኮ ሁልጊዜ መኪና በመጣ ቁጥር ይከተላችኋል። እንደው ይይዛቸው ይመስል ዝምብሎ ይከተላል። እንዴት አድርጎ ነው አሁን መኪናውን የሚይዘው። ዝምብሎ እየተከተሉ መጮህ›› አለው። የውሻው ባለቤት ‹‹እኔ መከተሉ አይደለም የሚገርመኝ። መኪናውን ሲይዘው ምን ሊያደርገው እንደሆነ ነው›› ብሎ መለሰለት።
በሕይወት ውስጥ የምናሳድዳቸው፣ የምንሮጥባቸው ነገሮች ሕይወታችን ላይ ምንም አልጨመሩልንም። ምን ጨምረውልናል? ስልካችን ላይ ያለው ፌስቡክ፣ ቲክቶክና ሌሎችም ሕይወታችን ላይ ምን ጨመሩልን? ጓደኞቻችን እንደማንችል ነገሩን እንጂ ምን ጨመሩልን? በዙሪያችን ያሉ ሰዎች ሊወዱን ይችላሉ ነገር ግን እንደማንችል ነው የሚነግሩን። ጊዜያችን እየባከነ ነው። የምንሰማውና የምናየው ነገር ሕይወታችን ላይ የሚጨምርልን አይደለም። ጊዜ ባከነ ማለት እሱ ነው። ሁሉም ነገር እየባከነብን ነው።
ለምን? ለጊዜያችን ክብር አልሰጠነውም። ስለዚህ ቅድሚያ የምትሰጠውን ነገር እወቅ። አንተን የሆነ ከፍታ የሚያወጣህ በቀን ውስጥ ሁለት ወይም አንድ ሥራ ነው። እሱን ሳትጨርስ ሌላውን አትጀምር። አንተን እኮ ወደኋላ ያስቀረህ ዕድልህ አይደለም። ስንፍናህ አይደለም። የጊዜ አጠቃቀምህ ነው። እስቲ ዝም ብለህ አስበው በዋዛ ፈዛዛ የሚባክነውን ጊዜህን። እንዴ! ትልቁን ማንነትህንና ህልምህን የምታሳካው እኮ የሆነ ቀን ከእንቅልፍህ ስትነቃ አይደለም። ከአሁን ጀምሮ ነው። መሆን መጀመር አለብህ።
ጀምስ አለን የተሰኘ ደራሲ ‹‹የምትፈልገውን አታገኝም፤ የሆንከውን ነው›› ይላል። መሆን መጀመር አለብህ። እንዴት አድርጌ ካልከኝ ለሚጠቅምህ ነገር ብቻ ቅድሚያ ስጥ። ለእምነትህ ቅድሚያ ስጥ። ደስታህ የሚወሰነው በፈጣሪህ ባለህ እርግጠኝነት ነው። ለቤተሰቦችህ ቅድሚያ ስጥ። የለፋኸውን የምትበላው ከነእርሱ ጋር ነው። ለሥራህ ቅድሚያ ስጥ። ከፍ የሚያደርግህ እሱ ነው። ለትምህርትህ ቅድሚያ ስጥ። ህልምህን የምታሳካው በሱ ብቻ ነው። በቃ! ነገህን ለሚያሳምርልህ ነገር ቅድሚያ ስጥ!
ከዚያ እኮ ብትዝናናም ያምር ብሃል። ጊዜዬ ባከነ አትልም። አይቆጭህም። ቅድሚያ ከሰጠህ የሚባክን ጊዜ አይኖርህም። አንተ ብትለወጥ ባትለወጥ፤ ወጥረህ ብትሠራ ባትሠራ፤ ገንዘቡን ብታስቀምጥ ብትበትን ጊዜው እንደሆነ መሄዱ አይቀር። ቁጭ ብለህ የሰቀልከውን ቆመህ ማውረድ የሚያቅትህ ቀን ይመጣል። እየቀለድክ ያለፈ ጊዜ የፈሰሰ ውሃ ነው። መቼም አታገኘውም። መቼም አትመልሰውም። ጊዜ ወርቅ ነው። በወርቅ አይቀለድም ወዳጄ!
ሕይወትን እንደሙከራ አስቦ መኖርህን አቁም። ጊዜ የሚባል የፈጣሪ ታናሽ ወንድም አለ። ቆሞ አይጠብቅህም። ‹‹ሺ ዓመት አይኖር! ለምን ረፈድ አድርጌ እንቅልፌን አልተኛም›› ብሎ ውስጥህ ሊነግርህ ይችላል። ሰበበኛውን ድምፅ እንዲህ በለው ‹‹ልክ ነህ ሕይወት ስታበቃ ማንም አይከለክልህም። ሺ ዓመት ትተኛለህ። አሁን የምትኖረው ዕድሜ ግን የተገደበ ነው። ተነስ!›› በለው። ጠንክረህ ሥራ። እንዳይባክን ጊዜህን በአግባቡ ተጠቀም።
ዛሬ የመጨረሻ ቀንህ እንደሆነ አስበህ ጊዜህን በሙሉ አቅምህ ተጠቀምበት። ትናንት ላይመለስ አልፏል። ነገም አስተማማኝ አይደለም። ዛሬ ነው እጅህ ላይ ያለው ወዳጄ! ለዛሬ ታመን። ነገ ያንተ ነው። በቀን ውስጥ ማድረግ ያለብህን ሁሉ የምታደርገው በአንድ ጊዜ ተአምር ለመፍጠር አይደለም። ነገር ግን እንደጨለማ ቀስ እያለ የሚገፈፈውን የስኬት ብርሃን ለመግለጥ ነው። ስለዚህ ጠዋት መነሳት ካለብህ ትነሳለህ። ማንበብ ካለብህ ታነባለህ። ሥራ መግባት ካለብህ መግባት ብቻ ሳይሆን በትጋት ትሠራለህ። መማር ካለብህ ከልብህ ትማራለህ። ወዳጄ! አሁን የለፋኸው አሁኑኑ ሳይሆን እንደባንክ ወለድ ተጠራቅሞ ሲከፈለህ እንኳንም በሙሉ አቅሜ ሠራሁ፣ እንኳንም ጊዜየን ተጠቀምኩበት ትላለህ። አይቆጭህም።
‹‹ሰዎች እየደጋገሙ የትም እንደማትደርስ የሚነግሩህ ከሆነ ድምፃቸው እስከማይሰማበት ርቀት ድረስ በስኬትህ ጥለሃቸው መሄድ አለብህ›› ይለናል ሚሼል ሩዝ የተሰኘ ደራሲ። አየህ ማን እንደሆንክ ስለማይረዱህ ይንቁሃል። ደስ የሚለው ግን ፈጣሪህ የናቁህን አንገት የሚያስደፋ አቅም በውስጥህ አስቀምጧል። ጠንክረህ ብዙ ርቀት ለመጓዝ መነሳት ያለብህ አሁን ነው። ጊዜ የለም ወዳጄ! ፍጠን። የሚባክን ጊዜ የለም።
አንተ እኮ ብዙ ፈተና ያለፍክ ሰው ነህ። አበቃልህ ሲባል ለዛሬ ደርሰሃል። ጠንካራ ነህ። አሁን ያለህበት ላይ ለመቆም አንተን መሆን ይጠይቃል። ያንተን ጥንካሬ ይፈልጋል። እውነት ነው ወደኋላ የሚጎትት መጥፎ ትዝታ ይኖርሃል። እሱን እያሰብክ በመቆጨት የሚባክነውን ጊዜ አስብ። ያንተን ጊዜና ትኩረት የሚፈልጉ ብዙ ጉዳዮች አሉ። እንዴ! ህልምህስ፤ሥራህስ፤ የነገ የፍቅር፣ የትዳርና የቤተሰብ ሕይወትህስ? ከእነርሱ የሚተርፍ ጊዜ ኖሮህ ነው በጭንቀት ቀንህ የሚያልፈው?
እርግጠኛ ነኝ ብዙ ነገር መቀየር፣ ማሳደግ የተሻለ ሕይወት መኖር ትፈልጋለህ። ወደኋላ የሚጎትትህን ትዝታ ማየት እስከማትችልበት ርቀት ድረስ ተጓዝ። አለበለዚያ ከፍ ዝቅ የሚል ስሜት ይጫወትብሃል። የሚወዱህ ሰዎች ገንዘብ ሊሰጡህ ይችላሉ። ሃሳብ ሊቸሩህ ይችላሉ። ያላቸውን ሊያካፍሉህ ይችላሉ። ዕድሜ ግን ሊሰጡህ አይችሉም። ቁርጥህን እውቀው። ሽርፍራፊ ሰከንዶችን እንኳን ሊጨምሩልህ አይችሉም። ‹‹እንዲህ ባደርግ›› አትበል። አድርገው። ዛሬ ተኝተህ ማደርህን እርግጠኛ አይደለህም። ህልምህን ማን ሊኖርልህ ነው። አንተ ራስህን ካልሆንክ ሌላ ማን እንዲሆንልህ ትፈልጋለህ? ህልምህን መኖር አለብህ።
የምትፈልገውን ነገር ስታሳድድ የሚባክን ጊዜ አይኖርም። ቻይናውያን ‹‹ዛፍ ለመትከል የመጀመሪያው ምርጡ ጊዜ ከዛሬ ሃያ ዓመት በፊት ነበር። ሁለተኛው ምርጥ ጊዜ ግን አሁን ነው›› ይላሉ። አየህ የምትፈልገው ጫፍ ላይ ለመድረስና ራስህን ለማሳደግ ሙሉ አቅምህን መጠቀም የነበረብህ ከዚህ በፊት ነበር። አሁንም ብትጀምር ግን ራስህ ላይ አተኩረህ ታላቁ ማንነትህን ለማውጣት ምርጥ ጊዜ አለህ። ስለዚህ ጊዜህን አሁኑኑ ተጠቀምበት።
በሕይወት ውስጥ ሁለት ዓይነት ሸክሞች አሉ። አንደኛው ጠንክሮ የመሥራት ሸክም ነው። ሁለተኛው ደግሞ የፀፀት ሸክም ነው። የመጀመሪያው ሸክም አንድ ኪሎግራም ብቻ ነው የሚመዝነው። ጊዜያዊ ነው ክብደቱ። ታልፈዋለህ። ጠንከረህ ከሠራህ በኋላ ስታልፈው ለዚህችው ነው የለፋሁት ትላለህ። ውጤቱ ያስደስትሃል። የፀፀት ሸክሙን ግን አትችለውም። መቶ ኪሎግራም ነው። ‹‹በቃ! እንዲህ ሳደርግ ጊዜዬ ባከነ ማለት ነው። ዕድሜዬ፤ ቁም ነገር ሳልሠራ ጊዜዬ ሁሉ ጠፋ ማለት ነው›› ትላለህ።
ስለዚህ ወዳጄ! የፀፀት ሸክምን ስለማትችለው መሥራት አለብህ። መጠንከር አለብህ። ሕይወትህ ካለፈ በኋላ ወይም ስታረጅ የሚቆጭህ ካደረከው ይበልጥ ያላደረከው ነው። ‹‹ለምን እንደዚህ አላደረኩም? ለምን ጊዜዬን አልተጠቀምኩም?›› ብለህ መፀፀት የለብህም። ሸክሙን አትችለውም።
አንዳንድ ሰው ደስተኛ በማያደርገው ፍቅር ግንኙነት ውስጥ ገብቶ ጊዜውን ያባክናል። ለምን አታቆምም ሲባል ‹‹እንዴ ቀልድ መሰለህ እንዴ! ከዚያ ሰው ጋር ሁለትና ሦስት አመት ቆይቻለሁ›› ይላል። ‹‹አሁንማ አቃጥሎ ሊደፋኝ ነው›› ትላለች። ‹‹ኧረ አሁን ልታሳብደኝ ነው›› ይላል። ታዲያ አብረሃት የምትቆየሁ ዕድሜ ዘመንህን ሁሉ ልታዝን ነው። ለሁለት አመት ውለታ ብለህ ሃያ ዓመት ልትቃጠል ነው። ጊዜ የሚባክነው ወዴትም የማይወስድህን መንገድ ይዘህ እየተጓዝክ ከሆነ ነው። ሰው ወደምሥራቅ መጓዝ እያለበት እንዴት ወደ ምዕራብ ይጓዛል?
ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን፡-
«የማይድን በሽታ ሳክም፣
የማያድግ ችግኝ ሳርም፣
የሰው ሕይወት ስከረክም፣
እኔ ለእኔ ኖሬ አላውቅም፣ ይሉናል በእሳት ወይ አበባ ግጥማቸው። ለራስህ የማትኖረው ጊዜህን ካልተጠቀምክበት ብቻ ነው። የሰው ህመም ትታመማለህ። የሰው ነገር ያሳስብሃል። መቼ ነው የምታድገው አንተ? መቼ ነው ጊዜህን የምትጠቀመው? ራስህን ለመቀየር መቼ አሰብክ? ገንዘብ ለማስቀመጥ ለመቼ አሰብክ? ጊዜህ እየባከነ ነው። ካልሮጥክ እሱ ቆሞ አይጠብቅህም።
ጊዜህን የምትጠቀመው ለራስህ ስትል ነው። የቤት ሥራህን እየሠራህ ነው። የቤት ሥራህን ቶሎ ከሠራህ ረጅም ጊዜ በደስታ ታሳልፋለህ። ረጅሙን ሳቅ የሚስቀው በመጨረሻ የሚስቅ ሰው ነው ይባላል። አየህ ጊዜህን አሁኑኑ ከተጠቀምክበት ረጅሙን ዘመን ትደሰታለህ። ሰላም!!
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ግንቦት 19/2015