
አዲስ አበባ፡- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ለበልግ ወቅት የግብርና ስራዎች የአፈር ማዳበሪያና የምርጥ ዘር ግብዓት ለአርሶ አደሩ ተደራሽ የማድረግ ስራ እየተሰራ ነው ሲል የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ የግብርና ግብዓት ዘርፍ ምክትል ኃላፊ የሆኑት አቶ ግዳልቅ አልቅሚ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በክልሉ በበልግ ወቅት አብዛኛው የእርሻ መሬት በዘር የመሸፈን ስራ ይከናወናል፤ በበልግ የሚዘሩ አዝርቶች ወቅታቸውን ጠብቀው እንዲዘሩ በአሁኑ ጊዜ የአፈር ማዳበሪያና የምርጥ ዘር ግብዓት ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እየተደረገ ነው።
በክልሉ የግብርና ግብዓት እጥረት እንዳይከሰት ከጥቅምት ወር ጀምሮ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ በበልግ ወቅት የሚዘሩ የእርሻ መሬቶችን በዘር ለመሸፈን የአፈር ማዳበሪያና የምርጥ ዘር ግብዓት ተደራሽ የማድረግ ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
የግብርና ስራዎችን ለማሳለጥ ለአርሶ አደሩ የአፈር ማዳበሪያና የምርጥ ዘር ግብዓት ወቅቱን ጠብቆ ማቅረብና ተደራሽ ማድረግ ተገቢ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በ2014/15 የምርት ዘመን በተከሰተ የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት እጥረት ሳቢያ ክልሉ ማምረት የሚገበውን ምርት ማምረት አልቻለም ያሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፤ ባለፈው ዓመት የተከሰተው የአፈር ማዳበሪያ የአቅርቦት ችግር በዘንድሮው የምርት ዘመን እንዳይደገም የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ ብለዋል።
በ2016/17 የምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ችግር እንዳይከሰት 830 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ወደ ክልሉ እንዲገባ ታቅዶ እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ በአንደኛ ዙር ከተገዛው የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ 189 ሺህ 301 ኩንታሉ ወደ ክልሉ ገብቶ ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ተደርጓል፤ ቀሪውን ከወደብ እንዲጓጓዝ የማድረግ ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የአፈር ማደባሪያ ዋጋ እንደ አካባቢው ርቀት እንደሚለያይ ጠቀሰው፤ከሶስት ሺህ 890 እስከ አራት ሺህ 200 ብር ዋጋ ለአርሶ አደሩ እየቀረበ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
በክልሉ የምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ ተደራሽ የማድረግ ስራ እየተሰራ ነው ያሉት የአቶ ግዳልቅ፤ ለ2016/17 የምርት ዘመን 43 ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር ለበልግ እርሻ ተደራሽ ለማድረግ የታቅዶ ሲሆን፤ እስካሁንም 22 ሺህ 90 ኩንታል የበቆሎ፣ የማሽላና የስንዴ ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ ተደራሽ የማድረግ ስራ ተከናውኗል ብለዋል።
በተያዘው የምርት ዘመን የአርሶ አደሩ የአፈር ማዳበሪያ ፍላጎት በተለየ ሁኔታ ጨምሯል፤ የአርሶ አደሩን የአፈር የማዳበሪያ ፍላጎት ለማሟላት የአፈር የማዳበሪያ በፍጥነት የማቅረብ ስራ እየተሰራ ነው ሲሉ አመልክተዋል።
ታደሠ ብናልፈው
አዲስ ዘመን መጋቢት 12 ቀን 2016 ዓ.ም