ኢትዮጵያ ለዘመናት ስታልመውና ስታቅደው የነበረችውን የልማት ግብ ለማሳካት በታላቁ ወንዟ ላይ ግድብ ለመገንባት የመጀመሪያውን መሰረተ ድንጋይ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ጉባ ላይ መሰረተ ድንጋይ ካስቀመጠች እነሆ 12ኛ ዓመቷን ይዛለች፡፡ የግድቡ ግንባታ የብስራት ዜና ከተሰማበት ዕለት ጀምሮ መላው ኢትዮጵያዊ ከዳር ዳር ተንቀሳቅሷል። በተለይም ለኢትዮጵያውያን ደግሞ ባይተዋር ሆኖ የቆየው የዓባይ ውሃን ለአገር እድገት ምሰሶ ለማድረግ መታሰቡ ሲሰማ ሁሉም የድርሻውን ለማበርከት አላመነታም፡፡
ከቅጠል ሻጯ እናት ጀምሮ እስከ ባለሃብቱ ድረስ የልማት ትልሙ እውን እንዲሆን በነቂስ ወጥቶ ድጋፉን አስመስክሯል፡፡ ይህ የዘመናት ቁጭት ሆኖ ህዝቡን አንገት ሲያስደፋ የኖረው ወንዝ ታዲያ ዛሬ ማረፊያውን አግኝቶ እውነተኛውን የልማት ብርሃን ሊያሳየን ከሁላችን ደጅ ቆሟል፡፡ በእነዚህ የልማት ዓመታት ታዲያ በውሃው ከፍተኛ ድርሻ ያላትን ኢትዮጵያ ከዳር ገፍተው ህዝቦቿ በድህነት እየማቀቁ እንዲኖር ለዘመናት ያለማንም ተጋሪ ብቻቸውን ሲጠቀሙ የኖሩት ጎረቤት አገሮች እጃቸውን አጣጥፈው አልተቀመጡም፡፡ ይልቁንም ከዚህ ቀደም ያደርጉት እንደነበረው ሁሉ የቅኝ ገዢዎቻቸው ክንድ ላይ ተንተርሰው አፍራሽ የፖለቲካ አስተሳሰባቸውንም ሆነ ተግባራቸውን ለእድገታቸው ምንጭ በሆነች አገር ላይ ለመወርወር አልቦዘኑም፡፡
ግና ችግር ያጎበጠው የኢትዮጵያ ህዝብ ለየትኛውም ችግር አልተንበረከከም፤ ይልቁንም መንግስትና ህዝቡ እጅና ጓንት ሆነው ጉዳዩን በጥበብ እና በብልሃት ያዙት እንጂ፡፡ በሃሰት የተገነባውን የዓለም ኢ-ፍትሓዊ አስተሳሰብ በትክክለኛ ሳይንስና ዲፕሎማሲ ለማክሸፍ ያደረጉትም ጥረት በብዙ መልኩ ሥኬታማ ሆኖል። እርግጥ አሁንም እነዚህ አገራት ዛሬም ድረስ የግድቡ አይቀሬነትን መቀበል ተስኗቸው የክፋት አጀንዳቸውን ለማስፈፀም ደፋ ቀና ማለታቸውን አላቆሙም፡፡ በተለይም የግድቡ ውሃ ሙሌት በተሳካ ሁኔታ በተከናወነ ቁጥር አፍራሽና ውሃ የማያነሱ አጀንዳዎችን እያነሱ የዓለም ህዝብ ማወዛገባቸውን ቀጥለዋል፡፡ ኢትዮጵያም በእነዚህ ዘመቻዎች ሳትንበረከክ ልማቷን አፋጥና አስቀጥላለች፤ ግድቡም ውሃ ከማቆር አልፎ ብርሃን ማሳየቱን ጀምሯል፡፡
አዲስ ዘመን ጋዜጣም የግድቡ ግንባታ የተጀመረበትን 12ኛ ዓመት ምክንያት በዛጋጀው ልዩ እትም በዚህና በሌሎችም አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑትን ዶክተር ኢንጅነር ጥላሁን ኤርዱኖ ጋር ቃለ-ምልልስ አድርጓል፡፡ እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የዓባይ ግድብ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ሥራ ሲጀምር ለተፋሰሱ አገራት የሚኖረውን አስተዋፅኦ ያብራሩልንና ውይይታችንን እንጀምር ?
ዶክተር ኢንጅነር ጥላሁን፡- የግድቡ መገደብ ከኢትዮጵያ ባሻገር የተፋሰስ አገራቱን በብዙ መልኩ እንደሚጠቅም ይታወቃል:: ኢትዮጵያ ግድቡን ለማልማት ከያዘችው ፕሮግራም ጎን ለጎን በየዓመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዛፎች እየተተከሉ ተፋሰሱን ለማልማት እየተሰራ ያለውም ሥራ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ ነው የሚገኘው:: በዋናነትም በኢትዮጵያ በወንዞች ላይ የሚሰራውን ልማት የሚቃወሙት ሱዳንና ግብፅን በከፍተኛ ደረጃ የሚጠቅም ነው የሚሆነው። ኢትዮጵያ የጀመረቻቸው ተፋሰሱን የማልማት ስራዎች ለሱዳንና ለግብፅ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸውም መሆኑ ደግሞ በሳይንስ በተደረገ ጥናት የተረጋገጠ ነው::
ከዚህ በመለስ እነዚህ የልማት ስራዎች የኢትዮጵያን የአየር ሁኔታ የሚያስተካክል ነው የሚሆነው:: ምክንያቱም ደግሞ በየዓመቱ የሚዘንበው ዝናብ መጠን እንዲጨምር ያደርጋል፤ በዚያው ልክ ምንጮች ይጎለብታሉ፤ የወንዞች የውሃ መጠን ከፍ እንዲል ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል። የውሃው መጠን በደንብ ስለሚጨምር እነሱ ያለበቂ መሰረት የሚናገሩት ችግር ተጨባጭነት እንደሌለው ማሳያ ነው የሚሆነው:: እንዳውም የበለጠ ለዚህ ልማት ተብሎ የሚወጣው ገንዘብና የሚደረገው ጥረት በሙሉ እነሱን የበለጠ ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው::
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ አኳያ እንግዲህ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን በመጠቀም ረገድ የዓለም አቀፍ ህጎች ምንድን ነው የሚሉት ?
ዶክተር ኢንጅነር ጥላሁን፡– ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን በሚመለከት የወጡ ዓለም አቀፍ ህጎች በሙሉ በዋናነት የሚያሰምሩበት ጉዳይ ድንበር የሚሻገሩና አገራትን የሚያስተሳስሩ የውሃ ክፍሎችን በጋራ ማልማት እንደሚያስፈልግ ነው የሚደነግጉት። በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ የልማት ሥራ መስራት እንደሚገባም ያስገነዝባሉ እንጂ ለአንዱ አገር የመጠቀም መብት ሰጥቶ ለሌላው የሚከለክሉበት አንድም ዓለም አቀፍ የህግ አግባብም ሆነ መሰረት የለም። ችግሩ ያለው በብቸኝነት ለዘላለም ሲጠቀሙ የኖሩ ወይም ከዚያ የሚገኘውን ጥቅም ሁሉ ማጋበስ የለመዱ የታችኛው ተፋሰስ አገራት የተለያዩ ምክንያቶችን በየጊዜው በመፍጠር በጋራ ማልማትም አይፈልጉም፤ ሌላው ሲያለማም አይደግፉም፤ ሁልጊዜ እነሱ ብቻ መምራት ነው የሚፈልጉት፤ እነሱ የሚፈልጉት ብቻ መሆን አለበት የሚል ጥያቄ ነው የሚያነሱት:: ይሁን እንጂ የዓለም አቀፍ ህጎች ሁሉም የድርሻውን ያህል በጋራ እየተስማመሙ እንዲያለሙ ነው የሚፈቅደው::
አዲስ ዘመን፡- ወንዙን የሚያዋስኑ 11 ተፋሰስ አገራት ቢኖሩም የዓባይ ግድብን ጉዳይ የኢትዮጵያ፤ የሱዳንና የግብፅ ጉዳይ ብቻ አድርገው የሚያስቡ አካላት አሉ፤ ይህ ከምን የመነጨ ነው ብለው ያምናሉ ?
ዶክተር ኢንጅነር ጥላሁን፡- በመሰረቱ በወንዙ ዙሪያ ያሉት 11 አገራት የላይኛው ተፋሰስ እና የታችኛው የተፋስስ አገራት በመባል በሁለት ይከፈላሉ:: በአብዛኛው የታችኛው ተፋሰስ አገራት የሚባሉት ግብፅና ሱዳን ናቸው፤ ምንአልባት ደቡብ ሱዳንንም ልንጨምር እንችላለን:: ከሁሉ በላይ ግን ሱዳንና ግብፅ ናቸው የግድቡን ልማት በጣም ሲቃወሙና ሲወተውቱ የኖሩት:: በጣም የሚገርመው ግን ምድር ከተፈጠረች ጀምሮ የአባይ ውሃ ከኢትዮጵያ ተነስቶ ወደ ግብፅ ሲፈስ ለብቻቸው ተቆጣጥረውት ሲጠቀሙ ስለኖሩ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረግ ማንኛውም ከውሃ ጋር የተያያዘ ልማት እንደስጋት ነው የሚቆጥሩት:: በተለይም ግብፅ ከአውሮፓና ከአሜሪካ ጋር ባላት ግኑኝነት የተነሳ የላይኛው ተፋሰስ አገራት በጋራ አቋም ሲይዙ ብዙ ጊዜ አይታይም:: አብረው ለመቆም እንቅስቃሴ ቢጀምሩም እምብዛም ሲቀጥሉ አይታዩም ነበር::
እንደማስታውሰው 1993 ዓ.ም ነበር የላይኛው ተፋሰሱ አገራት ለማሰባሰብና ለማወያየት የቀድሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ዘመቻ የጀመሩት:: በዚያን ጊዜ የታየውም በአቋም ሲፈረካከሱ ነው፤ የጋራና የጠነከረ አንድነት የላቸውም:: በወንዙ ተጠቃሚነት ዙሪያ ላይ ያላቸው አቋም በቅኝ ገዢዎቻቸው ልክ የተበታተኑ ሆነው ነው የሚገኙት:: ኢትዮጵያ እንግዲህ እንደሚታወቀው ቅኝ ያልተገዛች ብቸኛ አገር ነች። ከዚያ አንፃር ብቻዋን እንድትቆም የማድረግ፤ ከግብፅና ከሱዳን ጀርባ እንግሊዞች በመኖራቸው ምክንያት፤ ደግሞም ህጉንም ሆነ ደንቡን ያረቀቁት እንዲሁም የፈረሙት እነሱ ስለሆኑ የቅኝ ተገዢዎቻቸውን የቀድሞ ክብር ጠብቆ ለማቆየት በኢትዮጵያ ላይ ጫና የሚያደርጉበት ሁኔታ አለ::
ከዚህ አንፃር እኔ እንዳውም የዓባይ ወንዝን ጉዳይ በሁለት ብቻ ሳይሆን በሶስት ጎራ ነው የማየው። ይኸውም ኢትዮጵያ ብቻዋን፤ ግብፅና ሱዳን በአንድ በኩል፤ በሶስተኛ ደረጃ አንድነት ያጡ እና ጠንካራ አቋም የሌላቸው ሌሎች የተፋሰሱ አገራት ጎራ ተሰልፈው ነው የሚታዩት። እናም ኢትዮጵያ በያዘችው አቋም ጠንክራ መሄድ እንጂ ከእነዚህ አካላት ጋር የሚደረግ ድርድርም አይሰራም፤ አብሮ ማልማትም የሚሆን እንዳልሆነ ባለፉት ዓመታት በተጨባጭ አይተነዋል። በተለይም ግብፅና ሱዳን ‹‹እኛ እንደፈለግነው እኛ እንደምንላችሁ አድርጉ ነው›› የሚሉት። ለምሳሌ ግብፅ ውስጥ ጤናማ አመለካከት ያለው ፖለቲካዊ ስርዓት ቢኖር ኖሮ ‹‹ከኢትዮጵያ ጋር አብረን እንስራ፤ እኛም እናግዝ፤ ወደፊት ስጋትም ቢኖር አብረን ስጋቱን አብረን እንወጣለን፤ እናንተ በምታደርጉት ልማት ድርሻ ይኑረን›› ብለው በጠየቁ ነበር::
ከዚህ አንፃር እንደአገር በተፋሰሱ አገራት ተጠቃሚነት ዙሪያ ሁለት ዓይነት ዘመቻ ኢትዮጵያ ስታደርግ ቆይታለች። አንደኛው ዘመቻ በጣና ላይ ካጋጠመው የእንቦጭ አረም ጋር ተያይዞ ያለውን ችግር ስንናገር እነሱ ይስቁ ነበር። ግን ደግሞ አልተረዱትም እንጂ የሳቁት በራሳቸው ላይ እንጂ በእኛ ላይ አይደለም:: እኛ አነሰም በዛ አረሙን ለማስወገድ ታግለናል፤ በተቻለ መጠንም ከከፍተኛ ስጋትነት ያወረድነው ይመስለኛል። እኔ እንዳውም በወቅቱ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ ፅፌያለሁ:: ማገዝ እንዳለባቸው፤ እዚያ ዳር ቆመው ውሃውን አትንኩብን ከማለት ይልቅ ውሃው እና አካባቢው በተፈጥሮ ሲጎዳ ቆመው ማየት እንደሌለባቸው፤ እንዳውም ማድረግ ያለባቸው ዶላራቸውን ኢትዮጵያን ለማውደም ለሚንቀሳቀሱ ጎሬላቸው ከመመገብ እዚህ መጥተው ዛፍ ቢተክሉ የበለጠ እንደሚጠቅማቸው በግልፅ ፅፌያለሁ፤ ብዙ ተከራክሬያቸዋለሁ:: በዚህ ዙሪያ ‹‹የግብፅና አጋሮቿ ጠላትነት እስከመቼ?›› መፅሓፍም ፅፊያለሁ::
ስለዚህ ኢትዮጵያ በግድቡ ግንባታ ላይ ያላትን በአቋማ ጠንክራ ማስቀጠል ይገባታል፤ ህዝቦቿን አስተባብራ በአንድነቷ እስከቆመች ድረስ አንድ ቀን የእነዚህ አገራት እንቅስቃሴያቸው ትክክል እንዳልሆነ፤ ራሳቸውንም መለስ ብለው የሚያዩበት ሁኔታ መፈጠሩ አይቀርም:: እኔ እንዳውም መፅሓፌ ውስጥ እንደጠቀስኩት ምንአልባት በኛ ዘመን ይህ ነገር እውን ላይሆን ይችላል፤ ግን ደግሞ እነዚህ ሶስቱ አገራት የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በትክክል ስራ ከጀመረ በኋላ ምንም እንደማይጎዳቸው ሲያረጋግጡ የሚፀፀቱ ወይም በሰሩት ስራ የሚያዝኑ ይመስለኛል። ስለዚህ በዚያ ጊዜ ምንአልባት ድንበር አፍርሰን በጋራ የምኖርበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል።
በጥርጣሬ መተያየቱ ተወግዶ በህዝቦች መካከል መፈቃቀር፤ ድንበር አጥፍቶ የጋራ አገር እስከ መመስረት መድረስ ይችላሉ የሚል እምነት ነው ያለኝ:: ምክንያቱም ይህ የውሃ ሃብት የጋራ ነው፤ ህዝቦችን ሊያቀራርብ እንጂ ሊያቃርን አይችልም። ችግሩ ያሉት በጥቂት ባለስልጣናት ዘንድ ነው። ለምሳሌ ብዙ የግብፅ ምሁራን ከኢትዮጵያ ጎን የተሰለፉ አሉ:: እነዚህ ምሁራን የግድቡ መገንባት ግብፅን ሆነ ሱዳንን በምንም መልኩ አይጎዳም ብለው በግልፅ ሲናገሩ ይደመጣሉ:: እንዳውም እኮ ከዚህ በፊት አስዋን ግድብን ሲገድቡ ትልልቅ አሜሪካዊና እንግሊዛዊ የሆኑ ሁለት ምሁራን ‹‹ ትክክል ያልሆነ ግድብ፤ ትክክለኛ ባልሆነ ሥፍራ ›› በማለት ነው የገለፁት። ከዚያ ይልቅም በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገነባ ግድብ ነው ለግብፅ የበለጠ የሚጠቅመው ብለው ነው የተነተኑት::
እነሱ ሁልጊዜ የሚያነሱት ያልተጨበጠ ክርክር ‹‹ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ!›› እንደሚባለው ነው። እነሱ በገዛ አገራቸው ውስጥ ከአባይ አጀንዳ በስተቀር የሚያነሱት ፖለቲካ የላቸውም፤ ኢትዮጵያ ግን በሰላም ግድቧን እያስቀጠለች ትገኛለች:: ስለዚህ የሚያነሱት አጀንዳ ሲያጡ እነዚህ ወታደራዊ መንግስታት ሁልጊዜ ህዝባቸውን የሚመግቡት ‹‹ኢትዮጵያ ውሃ ልታሳጣችሁ ነው፤ እኛ እዚያ ላይ ነው የምንሰራው›› የሚል ሃሳብ በማንሳት የህዝቡን አቅጣጫ ለመቀየር ጥረት ሲያደርጉ ይስተዋላሉ:: ይህም ማለት ህዝባቸው እንዳይሰራ፤ ለዲሞክራሲ፤ ለፍትህ፤ ለእኩልነት የሚያደርገውን ትግል ለማጨናገፍ ሲሉ ሁልጊዜ የአገራቸው ችግር ውሃ ብቻ እንደሆነ እንዲያስብ አድርገውታል::
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ አንፃር ታዲያ ግብፅ ሁልጊዜ የውሃ እጥረት ያጋጥመኛል በማለት የምታነሳው ስጋት ምን ያህል ተጨባጭነት አለው ማለት ይቻላል ?
ዶክተር ኢንጅነር ጥላሁን፡– የትኛውም ሳይንስ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረግ ግድብ ግንባታ በግብፅም ሆነ ሱዳን ላይ የውሃ እጥረት እንደሚያስከትሉ አላረጋገጠም። ከዚያ ይልቅ እንዳውም በየጊዜው የሚፈተኑበትን የጎርፍ አደጋ ይከላከልላቸዋል እንጂ የውሃ ችግር አያመጣም። እውነተኛ ችግራቸው የውሃ እጥረት አይደለም፤ የዓለም አቀፍ ፖለቲካ ድራማ አካል ነው:: ኢትዮጵያ ያለችበት ቀጠና ይህንን ያህል ህዝብና ግዛት ይዛ ገና እንድትወጣ፤ በልማት እንድታድግ አይፈለግም፤ ይልቁንም እየኮረኮሙ፤ እየደኸየችና እየተበጣጠሰች አገር ሆና አንድነቷን አጥታ እንድትቆይ ነው:: በአካባቢው ላይ እንደፈለጉ መፈንጨት ስለሚፈልጉ ከዚያ ጋር የተያያዘ ፖለቲካ ነው እንጂ በምን ተዓምር ነው ኢትዮጵያ ውስጥ ዛፍ መትከል ግብፅንና ሱዳን የሚጎዳው ? ከግድቡ ጋር ተያይዞ እኮ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ዛፎች ተተክለዋል። እነዚህ የተተከሉ ዛፎች በምድር አየር ንብረትና ስነምህዳር ሁኔታ ላይ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳላቸው ይታወቃል::
በተለይ የወንዞች ውሃ መጠን እንዲጨምር በማድረግ ረገድ የላቀ ሚና እንዳለው እሙን ነው። ታዲያ ይህ እየታወቀ እንዴት አድርጎ ነው ግብፅና ሱዳንን ሊጎዳ የሚችለው ? ደግሞም እኮ የአባይን ውሃ ማንም ላቁመው ቢል ሊያቆመው የሚችለው አይደለም:: ይሄ እኮ ቀላል የሂሳብ ስሌት ነው። ይሄ ወንዝ እኮ በግብፅ እና በሱዳን ድርሻ ላይ ምንም ነገር ሳንነካ የተቆፈሩ ጉድጓዶች ከሞሉ በኋላ ውሃ ዝም ብሎ መከመር የማይቻል ነው:: እኛ ውሃ እየገደብን እንኳን ስንት ጊዜ ነው በጎርፍ እየተጥለቀለቁ ያሉት? ስለዚህ እነሱ የውሃ እጥረት ያጋጥመናል የሚሉት ስጋት ውሸትና መሰረት የለሽ ነው::
በአጠቃላይ በዚህ ጉዳይ ላይ ዓለም አቀፍ ፖለቲካው፤ የአገራቱ የውስጥ ችግር ወደ እኛ እያመጡብን ነው እየተቸገርን ያለነው:: በነገራችን ላይ ግብፅ ከፍተኛ የሆነ የከርሰ ምድር ውሃ ካላቸው አገራት ግንባር ቀደም ስትሆን ከዚህ በተጨማሪም በቀይ ባህር እና በሜዲትራኒያን ባህርም የተከበበች ናት::
በሌላ በኩል አባይ ወንዝም ቢሆን የኢትዮጵያ ዝናብም ሆነ ምንጮቹን በምንም ተዓምር ኢትዮጵያውያን ገድበው ሊያቆማቸው አይችሉም። ነገር ግን ይሄ አይነቱ የፖለቲካ አጀንዳቸው ግን ከውሃ እጥረት ጋር የሚያይዙት ነገር ለትዝብት የሚዳርጋቸው ነው የሚመስለኝ:: በመሆኑም እነዚህ አካላት አንድ ጊዜ ቆም ብለው ሊያስቡበት ይገባል። በተለይም ህዝባቸው ‹‹ከዚህ በኋላ ይበቃል!›› ሊላቸው ይገባል። ይሄ ድራማ ከእንግዲህ መቆም አለበት ብሎ መነሳት አለበት::
ኢትዮጵያ ለታችኞቹ አገራት የምትሰጣቸው የህይወት መሰረት የሆነ ውሃ ነው:: ስለዚህ ለኢትዮጵያ መታዘዝ፤ ለኢትዮጵያ ችግር መቆርቆር፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚያጋጥሙ ድርቅን በጋራ ለመከላከል ጥረት ማድረግ ነው የሚገባቸው:: ምክንያቱም ኢትዮጵያ ውስጥ ድርቅ በመጣ ቁጥር ውሃ ሊያንስ ይችላል። በመሆኑም ከዚያ ውጭ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ከንቱ ነው። እስካሁን ባለው ታሪክም አንድም ጊዜ የውሃ እጥረት አጋጥሟቸው አያውቅም፤ የፖለቲካ አጀንዳቸውን እያስፈፀሙ ያሉት:: ከዚህ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያውያን ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ይህንን መከራከር፤ ማስረዳት በእውቀት ላይ የተመሰረተ ግንዛቤ ማስበጥ ይገባቸዋል የሚል እምነት ነው ያለኝ::
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ በያዘችው አቋም መቀጠል አለባት ሲሉ ምን ማለቷ ነው ? ምንስ መስራት ይጠበቅባታል ብለው ያምናሉ ?
ዶክተር ኢንጅነር ጥላሁን፡– አስቀድሜ እንዳልኩት ኢትዮጵያ የግድቡን ግንባታ በማጠናቀቅም ሆነ የመልማት መብት በሚመለከት፤ እንዲሁም በዚህ ጉዳይ የያዘችውን አቋም ላይ ፈፅሞ ልታመነታ አይገባም:: ጠላት የሆኑ አገራት በሙሉ የኢትዮጵያ ወዳጅ መሆን የሚችሉት ግድቡን ጨርሰን ምንም ጉዳት እንዳላመጣባቸው ስናረጋግጥላቸው ብቻ ነው:: አገራችንን ለማሳደግ እና ማልማት ለማምጣት ይህ ግድብ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ሶስት ግድቦች ያስፈልጉናል:: እነዚህን ግድቦች እየሞላን በሄድን ቁጥር በከንቱ ኢትዮጵያን ሲያጠቁ መኖራቸውን፤ የኢትዮጵያን አንድነት ለማፍረስ ሲንቀሳቀሱ መቆየታቸውን እየተገነዘቡ ይመጡ እና ጥሩ ወዳጆቻችን ይሆናሉ ብዬ ነው የማምነው:: ይህን ካረጋገጥን በስተቀር፤ ግድቡን ሞልተን ቶሎ ብለን ወደ ልማት ካልገባን እነሱ ይተኙልናል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው::
መንግስት ይፋ እንዳደረገው ሁላችንም አስተዋፅኦ በማድረግና አሻራችንን በማሳረፍ ቶሎ ጨርሰን ዝም ብለን ቁጭ ብለን ማየት ይገባናል። ደግሞም እነዚህ አገራት ፖለቲካቸው እየተበላሸ ስለመጣ በተቻለ አቅም ሁለቱም አገራት የፖለቲካ ችግራቸውን ወደ ሌላ አቅጣጫ አዙረው ሊሞክሩት የሚችሉት ነገር ስለሚኖር መንግስታችን በደንብ ሊጠነቀቅ ይገባል። በመሆኑም እንደዚህ አይነት ነገሮችን የኢትዮጵያ መንግስት ንቁ ሆኖ፤ በጊዜ ሁኔታውን ገምግሙ ዝግጅት ማድረግ መቻል አለበት:: በመሆኑም በሁሉም ድንበሮቻችንን አካባቢ ጥበቃ ማድረግ ወሳኝ ነው:: በተጨማሪም የውስጥ ችግሮቻችንን በተቻለ ፍጥነት መፍታት ይገባናል::
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ማብራሪያ በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ::
ዶክተር ኢንጅነር ጥላሁን፡- እኔም ሃሳቤን እንድገልፅ እድሉን ስለሰጣችሁኝ ላመሰግን እወዳለሁ።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን መጋቢት 30/2015