‹ትቸር..! አለችው ከክፍል ወጥቶ ወደ ቢሮው ሲሄድ ከኋላው ተከትላ።
ለይኩን ወደ ኋላው ሲዞር ሳራን አጠገቡ አያት። ፊቱ መቆሟ አልገረመውም ሁሌ የሚያስገርመው ወደ እሱ ስትመጣ ብዙ አበሳን ነፍሷ ላይ ተሸክማ መሆኑ ነው። የነፍሷ አበሳ ይገርመዋል..እሱ ፊት እሷና ነፍሷ መከረኛ ናቸው..ለምን የሚለውን ጥያቄ ግን አልደረሰበትም።
‹እሺ ሳራ..ምን ልታዘዝ? ክፍል ውስጥ በምታውቀው ትህትናው አናገራት።
ከምትፈራው ነገሩ አንዱ ትህትናው ነው። በዛ ልክ ትሁትና ለተማሪዎቹ የተገባ መምህር ባይሆን ኖሮ አታፈቅረውም ወይም ደግሞ አትከተለውም ነበር። ሲበዛ መልካም መምህር ነው..ለተማሪዎቹ የሚሆን ብዙ ነገር አለው በዚህም ወደደችው።
መልሷ ሲርቅበት የሆነ ነገር እያሰበች እንደሆነ ገባው። ምን እንደሆነ ግን አያውቅም። ፊቱ ላይ ናት..ረጅም ጸጉሯ በከሰዐት በኋላው ጎረምሳ ንፋስ እየተሰቃየ። ሊስቅና ሊያለቅስ በቃጣው መንታ ፊት።
‹ምነው ዝም አልሽ? ምን ላግዝሽ እያልኩሽ ነበር..› ደግሞ ጠየቃት
‹አ..አይ..ምንም..
‹ታዲያ ምን ሆነሽ ነው?
‹ዛሬ ያስተማርከን ብዙም አልገባኝም ጊዜ ካለህ በድጋሚ እንድታስረዳኝ ብዬ ነው…› ደስ የሚልና የሚያሳዝን የተማጽኖ ድምጽ ከአፏ ወጣ።
ለምን የእሱ ትምህርት እንደማይገባት አያውቅም። ክፍል ውስጥ ያልገባው አለ ብሎ ሲጠይቅ ገብቶናል ከሚሉት ውስጥ አንዷ ናት። እግሩ ከክፍል ሲወጣ ግን እንዲህ እንደአሁኑ ሌላ ናት። እሱም እንደ እሷ ብዙ ያልገባው ነገር ነበር..
‹ቅድም እኮ ስጠይቃችሁ እንደገባሽ ነግረሽኝ ነበር..› አላት የምትለውን ለመስማት እንደ ጉድ ቸኩሎ።
‹አዎ ብዬ ነበር!
‹ታዲያ አሁን ምን ተፈጠረ? በጥያቄ ፊቷ ላይ ተንቀዋለለ። የሆነ ልትነግረው የፈለገችው ነገር እንዳለ አይኖቿ አሳበቁባት። ጥያቄውን ረስቶ በልቡ ውበቷን ማድነቅ ጀመረ። ቆንጆ እንደሆነች ያውቃል። ቆንጆ ብቻ አይደለም የትኛውም ወንድ የሚፈልጋት አይነት ሴትም እንደሆነች ይሄንንም ያውቃል። አይኖቿ በቆመበት ያባብሉት ጀመር።
ወንድ አይደል የሆነ ስሜት ተሰማው…በልቡ እየከጀላት መጣ። ግን የትኛውም ስሜት ለአገር ከገባው የአደራ ቃል አይበልጥበትም። የትኛውም ስሜት እምነቱን እንዲሸረሽርበት አይሻም። በሙያው አገር ሊለውጥ፣ ዜጋ ሊፈጥር ቃል ገብቷል። በተማሪዎቹ የሚወደድ ብቻ ሳይሆን የሚከበርም መምህር ለመሆን ለራሱ ቃል አለው። በቆመበት በተማሪው ላይ ያሳየውን ያልተገባ የስሜት የበላይነት አባረረ።
‹ደሞ….› የሆነ ነገር ልትለው ብላ ዝም አለች። ሀሳቧ ቆመ..ሀሳቧ ብቻ አይደለም ልቧም የቆመ ይመስላታል። ልቧ ብቻ አይደለም መኖር ያቆመችም ይመስላታል። ምን ልትለው ነበር?
‹ደሞ ምን? ከአፏ ላይ ተቀበላት።
ዝም አለችው..አንድ መዐት ዝምታ። በዝምታዋ ውስጥ ግን እሷና እሱ..ነፍሷና ነፍሱ ነበሩ። በዝምታዋ ውስጥ መቼም የማትረሳው ትህትናው..ጥሩነቱ ነበሩ። በዝምታዋ ውስጥ በእሱ ፊት በኩራት የሚያቆማት ድፍረት ብቻ ነው የሌለው።
በዝምታዋ ውስጥ ብዙ አሰበች.. መምህሬ ነው.. እንደ ማፈቅረው ብነግረው እሺ ይለኝ ይሆን? አንድ ተማሪ የሚያስተምራትን ለዛውም ለሴቶች ሁሉ አስፈላጊ የሆነን መልካም መምህር ለፍቅር ብትጠይቅ ምንድነው ችግሩ? ልቧ በዝምታዋ ውስጥ ምንም ችግር የለውም ሲል መልስ ሰጣት። ተደፋፈረች። አይኗን ወዳለበት ወረወረች…የሆነ ነገር ብላለች መሰለኝ መልሷን እየጠበቀ በሚመስል ሁናቴ አገኘችው። ትዕግስቱ ይገርማታል..እንደ እሱ ሴት የሚያደምጥ ወንድ አይታ አታውቅም። ሴትን ልጅ የሚማርክ ብዙ ነገር አለው።
‹ምን እያሰብሽ ነው..? የሆነ ነገር ልትይኝ ነበር..።
በዝምታዋ ውስጥ ድምጹን ሰማችው። ድምጹ ያምራታል። ድምጹ የሰፈራቸውን የተንስኦ ጸሎት ያስታውሳታል። እሱ ሲናገርና አባ ተንስኦ ለጸሎት ሲሉ አንድ ነው። በዝምታ ወስጥ ነፍስ ዘራች..በድምጹ። አይኑ ላይ አይኗን ተክላ..በሰላ ሴትነት ወንድነቱን እየመረመረች፣ ነፍሱ ጥግ ደርሳ እየተመለሰች፣ ባልተመለሱ ብዙ ጥያቄዎች በዚህ ሁሉ ፊቱ ቆመች።
በህይወቱ ሴት አጠገብ ቆሞ ምን መናገር እንዳለበት ጥበብ የከዳው ያኔ ይመስለዋል። ምን ያክል እርግጠኛ እንደሆነ ሳያውቅ ጥያቄዋን ተቀብሎ ሊያስረዳት ወደ ቢሮ ጋበዛት።
በላመ ቀይ ፊት፣ የእሳት አሎሎ በሚመስሉ ብርሀናማ አይኖች ተከተለችው። የእሱን ባታውቅም እሷ ግን ዓለም ላይ ደስተኛዋን ሴት ሆና ነበር። ቢሮ ሲደርሱ የልቧ ድለቃ ይሰማት ነበር።
በዝምታ ወንበር ስቦ ተቀመጠ። በዝምታ አጠገቡ ወዳለው ወንበር አመላከታት። የዛሬውን የትምህርት ርዕስ የያዘውን መጽሀፍ ጠረጴዛው ላይ ዘረጋው…
አጠገቡ ናት..ነክታው። የሆነ እንግዳ ስሜት ከእሱ ወደ እሷ ሲሰርግ ይሰማታል።
‹የቱ ነው ያልገባሽ? ከእንግዳ አለሟ መለሳት።
‹እ…የሚያቃስት አይነት ድምጽ ከአንደበቷ ወጣ።
‹ይሄ አልገባኝም..› ጣቷን ወደ መጽሀፉ ጠቁማ እያሳየችው።
‹ይሄን እኮ ቅድም ጥሩ አድርጌ አስረድቻችሁ ነበር..
‹እኔ ግን አልገባኝም..።
እጇ ከመጽሀፉ ላይ ተንሸራቶ እጁን ነካው..በደንብ ያዘችው።
እያደረገች ያለው ነገር ስላልገባው ዝም አለ።
‹ትቸር..አንተ ውስጥ እንደ ሰለሞን አይነት ኃያል ጥበብ ይታየኛል።
‹ምን አይነት ጥበብ?
‹እንዲህ እንደ አሁኑ አይነት ጥበብ። ከአንተ ወደ እኔ..ከእኔ ወደ አንተ የሚፈስ የሆነ አይነት ጥበብ።
ዝም አላት..እንደ ዛሬ ምንም ነገር ገብቶት አያውቅም።
እጆቿን በዝግታ እያንቀሳቀሰች ዳሰሰችው…ሳያውቀው ከሰማያት ሰማያት ቀላቀለችው። እጆቿ አይታክቱም..እጆቿ ነፍስ አላቸው። ጣቶቿ መለኮታዊ ሀይል ተቀብተው አገኛቸው።
አይኗን ወደ አይኑ ሽቅብ ወረወረች..የሆነ ነገር ልትነግረው መሰለው..ነገረችው
‹አፍቅሬሀለው…በአንተ መከራዬን እያየሁ ነው› እንዲህ አለችው።
እንደዛሬ ደንግጦ አያውቅም። ማድረግ ያለበትን በደንብ ያውቃል። ትውልድ ሊቀርጽ ቃል ያለው መምህር ነው።
‹በጣም አዝናለው ሳራ..እኔ መምህርሽ ነኝ። አንቺን አስተምሬ ለአገርሽና ለቤተሰብሽ እንድትበቂ እንጂ ባልተገባ መንገድ ከአላማሽ ላሰናክልሽ መምህር አልሆንኩም። አንቺ ገና ልጅ ነሽ ወደ ፊት ብዙ ተስፋ ይጠብቅሻል..ትክክል ባልሆነ ነገር ህልምሽን ማጣት የለብሽም። ጥሩና ጎበዝ ተማሪ እንድቶኚ ላግዝሽ ዝግጁ ነኝ።
ቀና ብላ አየችው..ከፍቅሩ በላይ መልካምነቱ ገዛት..ፍቅሩን በመልካምነቱ ቀይራ እንዳላት መምህርና ተማሪ ሆነው ለመኖር ለራሷ ቃል ገባች።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን መጋቢት 29/2015