ማግኘትና ማጣት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው:: ሁለቱም ተለዋዋጭ በሆነው ዓለም በሰው ልጆች የሕይወት እንቅስቃሴ ይፈራረቃሉ:: ያገኘ ሊያጣ፤ ያጣ ደግሞ ሊያገኝ የሚችልበት በርካታ አጋጣሚዎች ይፈጠራሉ:: ማግኘት የመኖርን ተስፋ ሲያለመልም፤ ማጣት ደግሞ በተቃራኒው ነው ሕይወትን አጨልሞ ፈታኝና ከባድ የኑሮ ሸክምን ያሸክማል:: ያም ቢሆን ታዲያ የሰው ልጆች ማግኘትና ማጣትን አቻችለው እርስ በርሳቸው በመረዳዳትና በመደጋገፍ ስሜት ኑሮን ማጣጣም ይችላሉ:: ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያውያን ጥሩ ምሳሌዎች ናቸው::
የኢትዮጵያውያን መገለጫ የሆነው መረዳዳትና መተጋገዝ ከጥንት ጀምሮ በሰው ልጆች መካከል ሲከወን ቆይቷል:: ያለው የሌለውን በመርዳትና በመደጋገፍ እጅ ለእጅ ተያይዘው በአብሮነት ኑሮን መግፋት የተለመደ ተግባር ነው:: ይህ የኢትዮጵያውያን ብቻ የሚመስለው የመረዳዳትና የመደጋገፍ ባህል ለሌሎች አርአያ ሊሆን የሚችል በጎ እሴት ነው::
የመረዳዳትና የመደጋገፍ ባህል በሰዎች ዘንድ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም አበው ‹‹መስጠት ለራስ ነው፤ መልሶ ይከፍላል›› በማለት በሰዎች መካከል መረዳዳትና መደጋገፍ አስፈላጊ መሆናቸው ሲያስተምሩን ኖረዋል:: የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሉም ባለው አቅም እርስ በእርስ እየተሳሰበ፣ እየተደጋገፈና እየተረዳዳ የመኖር ባሕል ማዳበር የቻለውም ባህልና እሴቱን መነሻ በማድረግ ነው::
በዛሬው የሀገረኛ አምዳችንም በመረዳዳት ውስጥ ያሉ በጎ ተግባሮችን ለማንሳት ወደናል:: መስጠትም ሆነ መቀበል በሰጪውም ሆነ በተቀባዩ ላይ የሚፈጥረውን ስሜትም እናነሳለን:: አስናቀች አለሙ እጅ ካጠራቸውና ደጋፊ የሚፈልጉ በርካቶች መካከል አንዷ ናቸው:: እኚህ ሰው፤ ለመስጠት ባይታደሉም አጋዥ በጎ አድራጊዎች አላጡም:: ዙሪያቸው ጨለማ ሆኖ አይዞሽ ባይ ደጋፊ ባጡ ጊዜ ባዩሽ ኮልፌ በጎ አድራጎት ማህበር አባላት አይዞት አለነዎት በማለት እጃቸውን ዘርግተው እንደተቀበሏቸው ይናገራሉ::
የባዩሽ ኮልፌ በጎ አድራጎት ማህበር አባላት ከእግዚአብሔር ጋር አጋሮቻችን ናቸው የሚሉት ወይዘሮ አስናቀች፤ በየወሩ አስቤዛ እና በበዓላት ደግሞ ለበዓል የሚያስፈልገውን ሁሉ በማቅረብ የሚደፏቸው መሆኑን ናገራሉ:: ‹‹እኔ የሞትኩት ድሮ ነበር፤ ለዚህ መብቃቴ ለመናገር ቃላት ያጥሩኛል›› የሚሉት ወይዘሮ አስናቀች፤ ካለአባት የሚያሳድጉት አካል ጉዳተኛ ልጅ ያላቸው ሲሆን እንደልባቸው ተንቀሳቅሰው ሰርተው ለልጃቸው መትረፍ አቅቷቸው በችግር ላይ ወድቀው እንደነበር ይናገራሉ::
እነዚህ በጎ አድራጎት ማህበር አባላት የሰፈሩ ልጆች በመሆናቸው እሳቸውን በቅርበት የሚያውቁ ቢኖርም እቤት ድረስ በመምጣት ያሉበት ሁኔታ ተመልክተው ልባቸው ተነክቶ ድጋፍ እንዳደረጉላቸው ይገልጻሉ:: እስከዛሬ ድረስ ከሽሮ፣ በርበሬ እስከ ሽንኩርት ድረስ ሁሉም ሳይቀር በየወሩ አስቤዛ በመስጠት ድጋፍ እንደሚያደርጉላቸው ይናገራሉ ‹‹ሥራ መሥራት አልችልም ምክንያቱም ልጄን ትምህርት ቤት የማጓጉዘው፤ አጠገቡ ሆኜ የምንከባከበው እኔው ነኝ፤ ስለዚህ ወር ሲደርስ እነሱን ነው የምጠብቀው›› የሚሉት ወይዘሮዋ፤ እርዳታ መቀበል ከጀመሩ ረጅም ጊዜ እንደሆናቸው ነው ያጫወቱን::
‹‹እኔ ሲሰጠኝ የሚሰማኝ ደስታና ሰላም ነው፤ በጣም ደስ ይለኛል›› የሚሉት ወይዘሮ አስናቀች ፤ ቤተሰብ ሆነውኝ፤ ለልጄ የአባትና የወንድምነት ፍቅር እየሰጡ፤ በዓል በመጣ ቁጥር ሥጋ ሳይቀር ሁሉም አስፈላጊ ነገር በማድረግ ይደግፉናል ይላሉ:: የወር አስቤዛቸውን አንድ ጊዜ ሳይቋረጥ በመደበኛነት እንደሚሰጣቸው ጠቁመው፤ ታዲያ ከዚህ በላይ ምን አይነት ደስታ ሊገኝ ይችላል ብለዋል ::
እዚህ እኛን የሚረዱን ልጆች ገና ተማሪ የሆኑ ወጣቶች ናቸው የሚሉት ወይዘሮዋ፤ ከእነሱ ብዙ ትምህርት ማግኘታቸው ይናገራሉ:: ‹‹እኔም ለሌላው መስጠትን፤ ማካፈልን አብሮ መጠጣትና መብላትን፤ የበረደውን ማልበስ የልቤ ምኞት ነው›› ይላሉ:: ወይዘሮ አስናቀች፤ እነዚህ ልጆች እኛን እንደረዱት ሁሉም ሰው ቢረዳዳ ጥሩ ነው:: መረዳዳት ያለው ለሌላው ካገኘው ላይ ማካፈል ከጥንት ጀምሮ ከአባቶቻችን ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ኢትዮጵያዊ ባህላችን ነውና ሁሉም ሰው ሊያደርገው የሚገባ በጎ ምግባር ነው ሲሉ ይገልጻሉ::
‹‹እኔ አሁን ቢኖረኝ ካለኝ ላይ ለሌላው ባካፍል፤ እነሱ ከሚሰጡኝ ነገር ላይ ባካፍል ደስ ይለኛል›› የሚሉት ወይዘሮ አስናቀች፤ እኔ እየበላሁ ሌላው ሲርበው፤ እኔ ለብሼ ሌላው ሲበርደው መመልከት እረፍት የሚነሳ ነው:: ሁሉም ያለው ቢያካፈል፤ ቢተባበር እጁን ቢዘረጋ፣ መልካም ተግባር ነው:: የኢትዮጵያ ሕዝብ እጁ ሰፊ ነው፤ ደግ ነው፤ ሩህሩህ ለተቸገሩት አዛኝ፣ የወደቁትን የሚያነሳ ነውና ይህንኑ ትብብር አጠናክሮ በማስቀጠል በሚችለው አቅም ሁሉ ለተቸገሩት መድረስ አስፈላጊ ነው ብለዋል::
የባዩሽ ኮልፌ በጎ አድራጎት ማህበር መስራች ወጣት ሄኖክ ፍቃድ በበኩሉ ማህበሩ አሥር የሰፈር ጓደኛሞች ሻይ ቡና ከሚሰጣቸው ገንዘብ ላይ ቀንሰው በማሰበሳብ በዙሪያቸው ለሚገኙ አቅም የሌላቸው ተማሪ ጓደኞቻቸው ለመረዳት ብለው የጀመሩት እንደሆነ ይናገራል:: ከዛሬ 12 ዓመት በፊት ያሰባሰቡትን ብር በአንድ ላይ በማድረግ በአካባቢ ላሉ ታናናሽ ወንድምና እህቶቻቸው ደብተርና እስክብሪቶ የመሳሰሉትን የመማሪያ ቁሳቁሶችን ገዝተው በመስጠት በጎ ምግባራቸውን ‹‹ሀ›› ብለው እንደጀመሩም ያስታወሳል::
ቀስ በቀስ እያሳደጉ የመጡትን በጎ ሥራም በአካባቢያቸው የሚገኙና ብቻቸውን የሚኖሩ እናቶችን ማገዝ ቀጠሉ:: ልጆች የሌላቸው እናቶችን ልብስ እና ገላ በማጠብ፣ ምግብ በማብሰልና የመሳሰሉ በተማሪ አቅም የሚሰሩ ገንዘብ የማይጠይቁ ነገሮች በመስራት ማገዝ መጀመራቸውን የሚናገረው ሄኖክ፤ የእነሱን በጎ ተግባር ያዩ ተማሪዎችም በጎ ሥራቸውን እየተቀላቀሉ መምጣት እንደቻሉ ይናገራል::
ይህ በበጎ ፍቃደኝነት የተመሰረተ ማህበር አሁን ላይ 500 አባላት ያሉት ሲሆን የሚሰጣቸው የድጋፍ ሥራዎች ከፍ እያደረገ መምጣቱን አንስቶ፤ በዚያው ልክ የሚያግዟቸው ቤተሰቦቻቸው እየጨመሩ መምጣታቸውን ይገልጻል::
አሁን ላይ በቋሚነት የወር አስቤዛ እና የህክምና ድጋፍ የሚያደርጉላቸው ከ80 በላይ የሚሆኑ ቤተሰቦች እንዳሉ የሚናገረው ሄኖክ፤ ወርሃዊ አስቤዛ ከመስጠት ባሻገር በበዓላት ወቅት ደግሞ የሚያስፈልጉት ነገሮች በማሟላት አብረዋቸው እንደሚያሳልፉም ያወጋል:: በተጨማሪም 300 ለሚሆኑ ተማሪዎች በቻሉት አቅም የመማሪያ ቁሳቁሶችን በማሟላት፣ ቤተሰቦቻቸውን በመርዳት ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ጠቁሟል::
ሄኖክ ሰው ለመርዳት ምክንያት ስለሆናቸው ጉዳይ ሲናገር አብዛኞቻቸው ጓደኛሞች ተመሳሳይ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ሲሆን ከእነሱ ባስ ባለ ሁኔታ የሚኖሩትን ደብተር እንኳን ሳይኖራቸው ለመማር የሚፈልጉ ሕጻናት ሲመለከቱ ማኪያቶ እና ሻይ መጠጣት ቢቀርብን እና ብናግዛቸው በሚል ሀሳብ እንደተነሳሱ ይናገራል:: ከጨዋታ በዘለለ ቁምነገር ይዘው የበጎ አድራጎት ሥራ መጀመራቸው፤ ‹‹እግዚአብሔር ይመስገን ለካ ሰውን መርዳት የሚፈጥረው ደስታ ማኪያቶ፣ ሻይ በመጠጣት ከምናገኘው ደስታ በላይ ሆነና በዚያው እንድንቀጥል አድርጎናል›› ይላል::
‹‹ሰውን መርዳት የሚሰጠውን ደስታ በቃላት የሚገለጽ አይደለም ፤ በራሴ በሕይወቴ ትህትናን ተምሬበታለሁ፣ ምስጋናን ተምሬበታለሁ፤ ያለሁበት ከማማረር ይልቅ ለምንም ነገር እግዚአብሔር ባደረገልኝ ነገር ሁሉ እንዳመሰግን አድርጎኛል›› የሚለው ሄኖክ፤ ሰውን ማገዝ ያ ሰው ያጣውን ነገር ሙሉ ለሙሉ መሸፈን እንኳን ባይችል የሆነ ነገር መካፈል መቻሉ በራሱ የሚሰጠው የተለየ ስሜት አለ ይላል:: አሁን ከሚሰጠው ደስታ ባሻገርም ነገ በሰማይ ቤት የተሻለ ነገር አለ ብለን እንድናስብ ስለሚያድርግ ትልቅ ዋጋ ያለው መሆኑን እንድናስብ ያደርገናል ብሏል::
‹‹ደስታችን የነሱ ሳቅ ነው፤ በእነሱ ላይ የሚታይ ደስታ በቃላት የማይገለጽ የተለየ ስሜት አለው›› የሚለው ሄኖክ፤ ሰው ለመርዳት በመጀመሪያ የሚያስፈልገው ሰው መሆን እንደሆነ ሁሉ ከዚያ በላይ መልካም ሥራን መስራት የሚችል መልካም ልብ እንዲሚያስፈልግ ይገልጻል::
ከዚህ ባሻገር ያሉት ሌሎች ነገሮች ቀስ እያሉ የሚመጡ መሆናቸውን አንሰቶ፤ አንድ ሰው መሬት ላይ ወድቆ ሲገኝ ምን ሆነህ ነው፤ አይዞህ ብሎ ማንሳት የሚያስችል መልካም ስነልቦና እንደሚያስፈልግ ጠቁሟል:: የሰው ልጅ የወደቀ ሰውን የማንሳት፣ የመርዳትና የመደገፍ ሥራ በመስራት ሰው በመሆን ውስጥ መንገድ የማሻገር መልካም ሥራ መኖር እንዳለበት ያመላክታል::
ብቻቸውን ቀኑንን ሙሉ የሚውሉ ሰዎች ሰው ይፈልጋሉ፤ ሰው ይራባሉ የሚለው ሄኖክ ስለዚህ እነዚህን ቤተሰቦች ‹‹ደህና ዋላችሁ አደራችሁ›› ማለት አብሮ ማሳለፍ መልካምነትን የሚጠይቅ መልካም ሥራ እንደሚያስፈልግ ይናገራል:: ትንሽ ሰዓት ወስዶ አብሮ ማሳለፍ፤ ሕመማቸው፣ ጭንቀታቸውን በመጋራት እንዲሁም ልብሳቸውን ማጠብ፣ ምግብ ማብሰል፣ ገላቸው ማጠብና የመሳሳሉ መልካም ሥራዎች መሥራት የሚጠይቀው ሰው መሆን ብቻ ነው ይላል::
ብዙ ጊዜ አብዛኞቻችን የምናሰበው ሰው ለመርዳት መልካም ሥራ ለመስራት ሀብታም መሆን ወይም ካለን ላይ መስጠት ብቻ ይመስለናል የሚለው ሄኖክ፤ ከሌለን ላይ እራሱ ማድረግ እንደሚቻል ማሰብ እንደሚገባ ይገልጻል:: በተለይ ፍቅር ላይ ትኩረት በመስጠት ብቸኝነት እንዳይሰማቸው ማድረግ፣ ልጆቻቸው እንደሆንን በማስረዳት ፕሮግራም ይዞ ቡና ወይም ሻይ በማፍላት ጊዜን አብረናቸው ማሳለፍ ተመራጭ እንዲሆነ ያስረዳል::
ድጋፍ የሚደረግላቸው ሰዎች ከገንዘብ ከስጦታ በላይ የሚያስደስታቸው ፍቅር እንደሆነ በመግለጽ በተቻለ መጠን ፍቅር በመስጠት የሚፈልጉትን እንኳን ማሟላት ባንችል ከጎናቸው እንደሆንን ሲያውቁ ደስታ ይሰማቸዋልና ይህንን ማድረግ ያስፈልጋል ብሏል::
በተለይም ወጣቶች ገንዘብ ባይኖራቸው ጊዜና ጉልበት ስላለቸው በመዋደድ፣ በመከባበር አብሮ በመኖር መደጋገፍ ይቻላል የሚለው ሄኖክ፤ ከምንም በላይ ደግሞ ፍቅር ያስፈልጋል:: ሰዎችን ለማገዝ መልካም ሥራንም ለመስራት የመጀመሪያ ነገር ፍቅር ሊኖረን ይገባል:: በብሔር፣ በዘርና በሃይማኖት ሳንለያይ ሰው የሆነን ፍጡር ለማገዝ የበኩላችንን ጥረት ማድረግ ይገባል :: ለመልካም ሥራ ረፍዶ አይውቅም ፤ ስለዚህ መልካም ሥራ ዛሬ አሁኑ መጀመር እንችላለን ሲል መልዕክቱን አስተላልፏል ::
‹‹መስጠት ከሁሉም በላይ የሚጠቅመው ራስን ነው›› የምትለው የሥነ ልቦና ባለሙያ ወይዘሮ ራሔል ገብረ መስቀል በበኩሏ፤ መስጠት ጠቀሜታው ለራስ ነው:: የሚሰጥ ሰው የሚያገኘው ደስታ ከሁሉም በላይ ነው::
መስጠት ስላለን ስለተረፈን ብቻ ሳይሆን ሰው በመሆናችን ብቻ ስንሰጥ የምናገኘው ደስታ ላቅ ያለ ነው:: ለአብነት አንድ ልብስ ገዝቼ ሌላውን አውጥቼ ብሰጥ ተመልሶ ይመጣል የሚል አመላካከት አለኝ የሚሉት ወይዘሮ ራሔል፤ መስጠት ለራሳችን ከሚሰጠን ደስታ ባሻገር ስንሰጥ ደግሞ በዚያ ሰው የምናየው ደስታ ደግሞ ተመልሶ እኛኑ ያስደስተናል ይላሉ::
እሳቸው እንደሚሉት፤ መስጠትም ሆነ መቀበል ተፈጥሯዊ ናቸው:: መስጠትም ሆነ መቀበል የሚመጣው በልምምድ ነው:: መስጠትን ከልጅነታችን ካልተማርን አንለምደውም፤ ከልጅነታችን መስጠት መማር አለብን:: ወላጆች ለልጆቻችን መስጠትን ማስተማር አለባቸው:: ስንሰጠን ያ ሰው እንዲያመስግነን አስበን ሳይሆን ለራሳችን ደስታ መሆኑ እየተማርነው ፤ እየተለማመድን ካደግን እንደባህል እንቆጥረዋለን::
ለመስጠት ሰው ከመሆን ውጭ ምንም መስፈርት የለውም የሚሉት ወይዘሮ ራሔል፤ ለመስጠት የሀብት ሆነ የሌላ ነገር መኖር ያስፈልጋል የሚል እምነት የለኝም ነው የሚሉት:: ስላለን አይደለም የምንሰጠው እኛ የሚያስፈልገንን የሌለው ሌላ ሰው እንደሚያስፈልገው ማሰብ እንጂ:: ሁለት ያለው አንዱን ቢያካፍል የሚያገኘው ደስታ ጥልቅ ከመሆኑም በላይ ለተሰጠውም አካል ስጦታው ይጠቅመዋል:: ስለዚህ ይህን መሰል አመለካከትን ማሳደግ ቢችል ጥሩ ነው:: መልካም ሥራ መስራት ይቻላል ሲሉ ይገልጻሉ::
ኢትዮጵያውያን በመረዳዳትና በመደጋገፍ እያከናወኑ ያሉት ተግባር እያደገ መጥቷል:: ድጋፉ ቤተሰብን፣ ዘመድ አዝማድንና ጎረቤትን ከመደገፍ ከፍ ወዳለ ደረጃ እየተሸጋገረ ይገኛል:: እንደ መቄዶኒያ ያሉት ድርጅቶች እያከናወኑ ያሉት ተግባርና ሕዝቡ ለእነዚህ ድርጅቶች እየሰጠ ያለው ድጋፍ፣ በበዓላት ወቅት የተቸገሩ ወገኖችን ለመርዳት እየተደረገ ያለው ርብርብ ይህ መደጋገፉና መረዳዳቱ ከፍ ወዳለ ደረጃ እየተሸጋገረ መምጣቱን ይጠቁማሉ::
ይህ ርብርብ አሁንም መጠናከር ይኖርበታል:: በሀገራችን ካሉት ደጋፍ ፈላጊ ማህበረሰቦች አኳያ ሲታይ ይህ የኢትዮጵያውያን ባህል ይበልጥ እንዲጠናከር መስራት ያስፈልጋል:: ለእዚህ ደግሞ እየተከናወኑ ያሉ የመደጋጋፍና መረዳዳት ተግባሮችን ማሳየት፣ የፍላጎቱን ሰፊነት ማስገነዝብ፣ ኢትዮጵያውያን የመረዳዳት እና መደጋገፍ ባህላቸውን ይበልጥ ማስፋት ላይ መስራት እንዳለባቸው ማስረዳት ያስፈልጋል::
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን መጋቢት 29/2015