በ1950ዎቹና በ1960ዎቹ የታተሙ ጋዜጦች የዛሬው ዓምዳችን መዳረሻ ናቸው። ከመራረጥናቸው ዘገባዎች መካከል አብዛኞቹ ልማት ተኮር ናቸው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት በአዲስ አበባ ስለሚያደርገው ስብሰባ፣ የወጣት ገበሬዎች በዓል በመቀሌ፣ ፈረንሳይ ከአዲስ አበባ ወደ ሲዳሞ የሚወስድ ባቡር መስመር ለመዘርጋት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር መፈራረሟን ግማሽ ክፍለ ዘመን መለስ ብለው የሚያስታውሱ ዘገባዎችን እንድታነቡት እነሆ ብለናል።
ከቆቃ አካባቢ ሕፃናት በሞላ ወንዝ ተወስደው ሞቱ
ናዝሬት ፤ (ኢ-ዜ-አ-) በናዝሬት ከተማና አካባ ባለፈው ማክሰኞ የጣለው ኃይለኛ ዝናብ ያስከተለው ጐርፍ በሰውና በእንስሳት ሕይወት ላይ ጉዳት አደረሰ።
ከሌሊቱ ፲፩ ሰዓት ጀምሮ እስከ ንጋቱ ፩ ሰዓት ተኩል ድረስ በጣለው ኃይለኛ ዝናም በሎሜ ወረዳ ግዛት በቆቃ አካባቢ የሚገኘው ወንዝ ሞልቶ ፪ ሕፃናት በወሀው ተወስደው ሞተዋል።
በናዝሬት ከተማም የምንጃር ጐዳና ተብሎ በሚጠራው መንገድ ግራና ቀኝ ለወሀ መውረጃ ተብሎ የተቆፈረው ቦይ ሞልቶ ፮ የቀንድ ከብቶችን ወስዷል።
እንዲሁም በከተማው ውስጥ የሚገኙት አስፋልት መንገዶች ከመጠን በላይ በጐርፍ ወሀ ተሸፍነው ተሽከርካሪዎችንና እግረኞችን ከማስቸገራቸውም በላይ፤ የጐርፉ ወሀ በአንዳንድ ቤቶች ውስጥ በመግባት ቀላል የንብረት ጉዳት ማድረሱን አንድ የአውራጃው ግዛት ፖሊስ ጽ/ቤት ቃል አቀባይ ገልጧል። (ሰኔ 21 ቀን 1964 ዓ.ም ከወጣው አዲስ ዘመን )
የወጣት ገበሬዎች በዓል በመቀሌ
መቀሌ፤ በትግሬ ጠቅላይ ግዛት በመቀሌ ከጥር ፳፬ /፶፭ ዓ ም ከቀኑ ፰ ሰዓት ጀምሮ በዐፄ ዮሐንስ ት/ቤት ቅፅር ግቢ ውስጥ ብዙ ሕዝብ በተሰበሰበበት የወጣቶች ገበሬዎች በዓል ተደርጐ ውሏል።
የበዓሉ ተካፋይ ለመሆን የመጡት እንግዶች እንኳን ደህና መጣችሁ የሚል ንግግር ከአቶ ተክለ አብ ወልዴ ከተሰማ በኋላ፤ ስለወጣቶች ገበሬዎች ሥራ ማስረዳት ለመወዳደር ከአድዋ፤ ከአዲግራት፤ ከውቅሮ፤ ከማይጨው፤ ከኮረም የመጡትና የመቀሌ ተማሪዎች በየተራ እየተነሱ ስለችግኙ አበቃቀልና አተካከል ስለፍግ አጠባበቅ ስለጓሮ አትክልት አተካከል ዘዴና ስለዶሮ ርቢ አያያዝ ለተሰበሰበው ሕዝብ ካስረዱ በኋላ፤ በውድድር አሸናፊ ለሆኑት ፩ኛ/ለማይጨው ወጣቶች ገበሬዎች፤ ፪ኛ/ የኮረም ወጣቶች ገበሬዎች፣ ፫ኛ/ የአድዋ ወጣቶች ገበሬዎች የአሸናፊነት ሽልማት ከጠቅላይ ግዛቱ ት/ቤቶች ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ በአቶ ግሩም ገብሬ እጅ ተሰጥቶ የበዓሉ ፍጻሜ ሆኗል ሲል በጠቅላይ ግዛቱ የሚገኘው ወኪላችን ባስተላለፈው ወሬ አመልክቷል። (ጥር 27 ቀን 19 55 ከወጣው አዲስ ዘመን)
ቫልድሃይም ለፀጥታ ምክር ቤት ጉባዔ አዲስ አበባ ይመጣሉ
አዲሱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ኩርት ቫልድሃይም የድርጅቱ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት በሚያደርገው ጉባዔ ላይ የሚገኙ መሆናቸውን የድርጅቱ ቃል አቀባይ አስታወቀ። ቫልድሃይም የደርጅቱ ዋና ጸሐፊ ሆነው ከተመረጡ ወዲህ፤ ውጪ አገር ሲጎበኙ ያሁኑ የመጀመሪያቸው እንደሚሆን ተገልጧል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት አዲስ አበባ ላይ የሚሰበሰበው ከጥር ፲፱ ቀን ጀምሮ እስከ ጥር ፳፮ ቀን /፷፬ ዓ/ም/ ሲሆን፤ በዚሁ ጊዜ በደቡባዊው የአፍሪካ ክፍል ችግሮችና፤ እንዲሁም በቅኝ ግዛት ጉዳይ እንደሚነጋገር ታውቋል። እንዲሁም ምክር ቤቱ በአዲስ አበባ እንደሚሰበሰብ ከድርጅቱ ዋና መሥሪያ ቤት ትናንት ለመጀመሪያ ጊዜ በኦፊሴል አዲስ አበባ ለሚገኘው ለአፍሪካ ኤኮኖሚክስ ኮሚሽን ጽ/ቤት መልዕክት ተላልፏል።
አሥራ አምስት አገሮች በአባልነት የሚገኙበት የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት በኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባ የሚያደርገው ስብሰባ እ/ኤ/አ/ ከ፲፱፻፶፪ ወዲህ ምክር ቤቱ ከኒውየርክ ውጪ ሲሰበሰብ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ነው። ምክር ቤቱ እ/ኤ/አ/ በ፲፱፻፶፪ ዓ/ም / በፈረንሳይ ዋና ከተማ ፓሪስ ላይ ስብሰባ ማድረጉ ይታወሳል። ምክር ቤቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ ምድር ላይ የሚሰበሰበው በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ጠያቂነት ነው።
አዲስ አበባ ላይ በሚደረገው የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤቱ ጉባዔ ላይ ብዙ የውጪ ሊቃውንት በውይይቱ ተካፋዮች እንደሚሆኑ ሲገልጥ፤ የ፲፭ ቱ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት አባል አገሮችም በድርጅቱ ዘንድ የሚገኙትን ዋና ዋና መልእክተኞቻቸውን እንደሚልኩ አስታውቀዋል።
የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት በአዲስ አበባ የሚያደርገው የጉባዔ ጊዜ፤ በሮዴሺያና በእንግሊዝ መካከል የተደረገው ስምምነት ተቀባይነት እንዳይኖረው የሚቀርብለትን ሀሳብ እንደሚመለከት ተገልጧል።
ሆኖም እንግሊዝ ሀሳቡን ባለፈው ወር በፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ጉባዔ ላይ ድምፅን በድምፅ በማገድ ሥልጣኗ በመጠቀም መጣሏ ይታወሳል። (ጥር 10 ቀን 19 64 ዓ.ም ከወጣው አዲስ ዘመን)
የምድር ባቡር መስመር ለመዘርጋት የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ
ከአዲስ አበባ እስከ ጅቡቲ ካለው የኢትዮጵያና የፈረንሳይ የምድር ባቡር መስመር አንስቶ ወደ ሲዳሞ የሚወስድ የምድር ባቡር መስመር ለመዘርጊያ የሚሆን የገንዘብ ብድር ስምምነት ኢትዮጵያና ፈረንሳይ ፓሪስ ላይ የተፈራረሙ መሆናቸውን የደረሰን ወሬ አመልክቷል።
ይህን የአምሳ አምስት ሚሊዮን ፍራንክ ብድር ስምምነት ፓሪስ ላይ የተፈራረሙት በኢትዮጵያ መንግሥት በኢትዮጵያ በኩል ክቡር አቶ ማሞ ታደሰ በጠቅላይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ሲሆኑ በፈረንሳይ መንግሥት በኩል ደግሞ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ የተራድኦ አሰጣጥ ም/ሚኒስትር ሙሴ ሚሼል ሐቢብ ደ. ሎንክ ናቸው። ይህን አዲስ የምድር ባቡር መስመር ለመዘርጋት አስፈላጊውን መሣሪያ እንዲያቀርቡ የሚመደቡት የፈረንሳይ ኩባንያዎች መሆናቸውን ወሬው በድጋሚ አስታውቋል። (ሰኔ 21 ቀን 19 64 ዓ.ም ከወጣው አዲስ ዘመን)
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን መጋቢት 26/2015