ማስታወቂያ መልክ በመጠየቁና የገቢ ምንጭ በመሆኑ ሴቷም የግድ ተፈጥሮ በቸረቻት ውበት ተጠቅማ የዚህ ፀጋ ተቋዳሽ በመሆኗ ብዙዎች ይስማማሉ።ማስታወቂያ በማስተዋወቅ ሰበብ ሴትነትንና ውበትን እንደ ሸቀጥ ማቅረብ፤ ደግሞ ሲያከራክር ይደመጣል።በመገናኛ ብዙሃን በሚተላለፉ ማስታወቂያዎች ከፊል የሴት እርቃንን፤ ቅርጽና ውበትን ጨምሮ፤ የቤት ውስጥ ሥራ ለሴቷ ብቻ የተሰጠ የሚያስመስሉ ያልተገቡ መልዕክቶች ሲተላለፉ ይስተዋላል።
መልክቶቹ በአገራችን ከማህበራዊ ሚዲያዎች መስፋፋት ጋር ተደማምረው ታዳጊዎችን ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ እንዲያመሩ እያደረጉ ይገኛሉ። በተለይ የነዚሁ ማስታወቂያዎች መልዕክትና ይዘት በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጾታዊ ጥቃቶችን ለማባባስም ኢትዮጵያ በስርዓተ ጾታ ዙሪያ የገባቻቸውን ዓለም አቀፍ ስምምነቶች እየተገበረች ያለችበትንም ሂደት ቀደም ሲል ማህበረሰቡ በተዛባ አስተሳሰብ ምክንያት የወንድ የሴት ብሎ ከፋፍሏቸው ወደ ነበሩ ዘመናት ይመልሳል ተብሎ ያሰጋል።
ባለፈው ሳምንት እንዲህ ዓይነቱን ተግባር በመገናኛ ብዙሃን የሚያስተጋቡ አካላትን የሚከታተልና የሚቆጣጠር አካል ያለ አያስመስልም የሚሉ አስተያየቶችን አስተናግደን ነበር።ለዛሬም የማስታወቂያ ሠራተኞችና አስተላላፊዎች እንዲሁም ተቆጣጣሪና ባለድርሻ አካላትን ያካተተ አስተያየት ይዘን ቀርበናል።
‹‹ማስታወቂያ መልክ ይጠይቃል›› የምትለው የካፌ ኢንዱስትሪ ፈር ቀዳጇ ፀደይ አስራት በ17 ዓመቷ ወደ ፋሽን ኢንዱስትሪ መግባቷን ትናገራለች።ከመድረክ ጀምራ እስከ መገናኛ ብዙሃን በመዝለቅ የልብስ ፋሽኖችንና የተለያዩ ማስታወቂያዎችን ስትሰራ ቆይታለች።‹‹ፋሽን ለመከተል የግድ ፋሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ መሆን የለብኝም››ስትል ፋሽንና ውበትን እንደ ፊቱ የገቢ ምንጭ ባታደርገውም ከራስ ፀጉር እስከ ጥፍር አምሮ መታየት ማንኛዋም ሴት የምትፈልገው እንደመሆኑ እኔም በግሌ እቀጥልበታለሁ እንጂ የፈለገ ቢሆን አልወጣበትም ትላለች። ሥራው ከመልክ በተጨማሪም የተሻለ አስተሳሰብና በራስ መተማመን እንደሚጠይቅም እሷ ባለፈችበት ወቅት ወደ ሥራው የምትገባ ሴት እነዚሁ ጥያቄዎች ትጠየቅ የነበረ መሆኑን በማሳያ ታነሳለች።ቢሆንም አካል የሚገላልጥና ግላዊ ስብናና ክብርን የሚነካ ሴትነትን መጠቀሚያ የሚያደርግ ማስታወቂያ ሴቷ እንድትሰራ ማድረግ አግባብ አለመሆኑን ታወሳለች።
ማስታወቂያ ውበት ይፈልጋል።ውበት ደግሞ በሴት ይገለፃል” የሚሉት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ እታገኝ አሰፋ ሴቶች በውበታቸው በማስታወቂያ በመሳተፍ ሊጠቀሙበት የሚችሉበት እንደሆነ ይጠቅሳሉ። “ማስታወቂያ ሀብት ነው።ትልቅ የገቢ ምንጫችንም ነው። እንደ አገር ሴቶች ከዚህ ተነጥለን ብቻችንን ምንም አናደርግም። ዓለም አቀፍ ተሞክሮ ሁሉንም ያሳያል። በውጭ ማስታወቂያዎችም ቆንጆ ሴቶች ተመርጠው ነው የጽዳትና ውበት መጠበቂያ ግብዓቶችን ሲያስተዋውቁ የምናየው”ይላሉ። ሴቶች በእድገት ጎታችና ሐይማኖታዊና ባህላዊ እንዲሁም የግል ስብእና እና ክብር በሚነኩና በሚሸረሽሩ ማስታወቂያዎች እንዳይሳተፉ ከልብ ከተፈለገ መጀመሪያ አኗኗራችንን ማስተካከል አለብን ይላሉ።ለምን ቢባል ልብስ ማጠብ፤ ልጅ መንከባከብ፤ ማሳከም በደምሳሳው የቤት ውስጥ ሥራ ዛሬም ድረስ በሴቶች እየተሰራ ያለ የእውነታው ነፀብራቅ ከእውነታው የራቀ ማስታወቂያ ተቀባይነት የለውም ባይ ናቸው።በመሆኑም አኗኗራችንን ላይ ሥራ ሳንሰራ ሴት ሁልጊዜ እንዴት ልብስ አጣቢ ብቻ ሆና በማስታወቂያ ትሳላለች የሚለውን ከወሰድን ይቸግራል።መፍትሄው ወንዶች የሴቶችንም ሥራ እየሰሩ፤ ሴቶች የወንዶችንም ሥራ እየሰሩ ልክ እንደ አውራምባ ማህበረሰብ ተሳስበው በሚኖሩበት ላይ ሳያሰልሱ መሥራት የተሻለ እንደሆነና በማስታወቂያ ሥራ እየተሻሻለ የመጣ መሆኑን ማየት እንደሚገባም ይጠቁማሉ።ወንዶች ልብስ እያጠቡ ማስታወቂያ መሰራት መጀመሩን ለአብነት ያነሳሉ።በዚህ መልኩ ሴቶች በማስታወቂያ የሚሳሉበት ሁኔታ ወደፊት ይቀየራል ብለውም ተስፋ ያደርጋሉ።
አቶ ዳንኤል ብርሃኑ ለረጅም ጊዜ በጋዜጠኝነት ሰርቷል። አንዲት እናት ልጇን ስታስከትብ የሚታይበት የኩፍኝ ማስታወቂያው መርፌው ትልቅ በመሆኑ ህፃናት እንዲከተቡ የሚያበረታታ ሆኖ ባለማግኘቱ እንዲለወጥ ለጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በግሉ ደብዳቤ በመጻፉ መርፌውና አስከታቢዋ እንዲለወጡ እስከ ማድረግ በመድረስ በመገናኛ ብዙሃን በሚተላለፉ ማስታወቂያዎች ላይ በትኩረት ይሰራል።የሁለተኛ ዲግሪ መመረቂያ ሥራውን በማስታወቂያ ላይ የሰራ ሲሆን፤ በመገናኛ ብዙሃን በሚተላለፉ ማስታወቂያዎች ዙሪያም መጻፎች ጽፏል።“ማስታወቂያ ሳቢ መሆን አለበት ሳቢ ለማድረግ ከምንጠቀምበት አንዱ ሴቶችን ማሳየት ነው” የሚለው ዳንኤል በማስታወቂያ ሳይንሱ ሰዎች የሚያተኩሩት ቆንጆ መልክና ቅርጽ ባላቸው ሴቶች ሁኔታ ላይ እንጂ በሚተላለፈው ምርትና አገልግሎት ባለመሆኑ ውጤታማ አይደለም ተብሎ እንደሚታመን ያወሳል። ሴቶቹ ላይ በማተኮር እንደማይገነዘቡት የሚያረጋግጡ ጥናቶች እንዳሉም ይጠቁማል። ይሄ እንደ ትምህርት ቤት አስተምረን ፈትነን ለውጡ ይሄን ያህል ነው እንደሚባለው አይደለም። ወጥ ልጇ አብራ እንድትቀምስ የምታደርግ እናት ያለችበትን ማስታወቂያ የምታይ ሴት ልጅ ወጥ መቅመስ የእናትና የሴት ልጅ ሥራ እንደሆነ አድርጋ ነው የምታስበው ተብሎ ይገመታል።ይሄም ታዳጊዎች የመጣውን አስተሳሰብ ዕውነት ነው ብለው እንዲቀበሉ ያደርጋል።
‹‹የስርዓተ ጾታ ጉዳይ ሲነሳ የተለመዱ አስተሳሰቦች፤ የተለመዱ ያለፍንባቸው የኑሮ ዘይቤዎች በማስታወቂያ መደጋገማቸው ደግሞ ያፀናቸዋል፤ እንዲቀጥሉ ያደርጋል›› ይላል።ዳንኤል እንደሚለው ወደፊትም እንለውጠዋለን ብለን የምናስበውን ማህበረሰብ ለመለወጥም ማስታወቂያ ትልቅ ሚና አለው ተብሎ ይታሰባል።ሆኖም ለውጡ እንደ ትምህርት ቤት አስተምረን ፈትነን ለውጡ ይሄን ያህል ነው እንደሚባለው ሳይሆን ረጅም ጊዜ ይፈጃል። ወጥ ልጇ አብራ እንድትቀምስ የምታደርግ እናት ያለችበትን ማስታወቂያ የምታይ ሴት ልጅ ወጥ መቅመስ የእናትና የሴት ልጅ ሥራ እንደሆነ አድርጋ ነው የምታስበው። በመሆኑም ሁሉም ሴት ልጆች የመጣውን አስተሳሰብ ዕውነት ነው ብለው እንዲቀበሉ ያደርጋል።
‹‹የስርዓተ ጾታ ጉዳይ በየትኛውም መመርያዎች ውስጥ በግልጽ አልተቀመጠም›› ይላል። እንደ እሱ የስርዓተ ጾታ እኩልነት ተሳትፎ፤ ተጠቃሚነት፤ እነዚህ ከሰብዓዊ መብት፤ ከባህልና ከልማዶቻችንን ጋር እንዴት ነው የሚታዩት ሲባል የሚያከራክሩ ናቸው። ለምሳሌ አጭር ቀሚስ ምንድነው የቱ ድረስ ሲሆን ነው አጭር የሚሆነው? ራቁትነት የሚፈጠርባቸውና የማይፈጠርባቸው ብለው የሚያስቧቸው አሉ። በከፊል ራቁትነት የሚፈጠርባቸው ተቀባይነት የሚያገኘው እስከምን ድረስ ሲሆን ነው የትስ ቦታ የሚለውም ይታያል። ተገቢ ነው ወይ የሚል ጥያቄም ሲነሳ ይስተዋላል።እነዚህ ሁሉ ማስታወቂያ ሲነሳ አብረው የሚነሱ ናቸው።
‹‹ሴቶች ወደ አመራር እንዲመጡ ብዙ መመቻቸት ያለባቸው ሁኔታዎች አሉ። አንደኛው በዚህ ረገድ እኛ ለእኩል ውክልና የምንሰራበት ሴቷ መምራት ትችላለች ብሎ ማህበረሰቡ ማሰብ ያለበት መሆኑ ነው›› የምትለው በዩኤ ውሜን ሴቶችን ወደ ውሳኔ ሰጭነት የማምጣት ጉዳይ ኃላፊ ደሴት አበበ መገናኛ ብዙሃን ውስጥ ስለሴቶች ያለውን አመለካከት በዋንኛነት የሚቀርጸው ማስታወቂያ እንደሆነም ታሰምርበታለች።ደሴት ምክንያቱን ስትገልጽም አንዲት ሴት ልትመራ ስትሄድ የሚቀበላት ማህበረሰብ ከሌለ በተመደችበት ተቋም መምራት ያቅታታል። ማህበረሰቡ ሴትን መሪ አድርጎ እንዳያይ የሚያደርግ አስተሳሰብ በእምሮው እንዲቀረጽ ከሚያደርጉት ውስጥ አንዱ በመገናኛ ብዙሃን የሚተላለፈው ማስታወቂያ እንደመሆኑ በመገናኛ ብዙሃን ሴቶች የሚሳሉበት በሕይወት ዘመናቸው በሙሉ የሚከተላቸው እንደሆነም ትጠቅሳለች።አሁን ላይ እየተሻሻለ ቢመጣም ሴቶች በማስታወቂያ ውስጥ የሚሳሉት በዳይፐር በወተት፤ በሳሙና፤ በምግብ ቅቤ ሁልጊዜ ከጓዳና ከቤት ውስጥ ሥራዎች ጋር በተያያዘ እንደሆነ ታነሳለች። እንደምትለው ልጅ ማሳደግ የሴት ኃላፊነት ብቻ ተደርጎ ነው የሚሳለው በማስታወቂያ። ወንዶችን ደግሞ መሪ፤ ኃላፊ፤ ውሳኔ ሰጭ፤ ባለገንዘብ አድርጎ መሳል አለ።ይሄ ደግሞ ሴቶች በፖለቲካው ላይ ተፅዕኖ ፈጣሪ አይደሉም፤ በኢኮኖሚው ላይ ተፅዕኖ ፈጣሪ አይደሉም። ቤት ነው እንጂ መሥሪያ ቤት መምራት አይችሉም፤ ቤት ነው እንጂ አገር መምራት አይችሉም የሚለውን አስተሳሰብ በተለይ በህፃናት አእምሮ እያሰረፀ ይሄዳል። አገር ተረካቢ ህፃናት ነገ ስለ ሴቶች የሚያስቡት በማስታወቂያ የሚያዩትንና የሚማሩትን ነው።በመሆኑም ይሄ አመለካከት መቀየር አለበት። ማስታወቂያ የሚሰሩ ሰዎች ሁለቱንም አመጣጥነው ነው መሳል ያለባቸው የሚል ሀሳብ ነው ያለው ዩኤን ውሜን። ከአምስት ዓመት በፊት ከመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ጋር በመተባበር የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎቹን ማሰልጠን ጀምረናልም ትላለች። በሚያሰለጥኗቸው ወቅት የማስታወቂያ ይዘትን ጥራትን የሚወስኑት እነሱ ብቻ ሳይሆኑ ምርታቸው እንዲተዋወቅላቸው የሚፈልጉ ባለሀብቶችም አሉና ስልጠናው ሁሉንም ተደራሽ ማድረግ አለበት የሚል እምነት አላቸው ብላናለች።
ከዩኤን ውሜን ጋር በመቀናጀት በዚሁ ዙርያ በርካታ ሥራዎችን ስትሰራ የቆየችው በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የሴቶች ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ዳይሬክተር ዱረቲ ታደሰ እንደምትለው እሷ እንደምትሰራበት ተቋም በመገናኛ ብዙሃን የሚተላለፉ ማናቸውንም ጉዳዮች የሚቆጣጠርና የሚከታተል ራሱን የቻለ የማስታወቂያ ክትትልና አቅም ግንባታ ዳይሬክቶሬት አለ።ዳይሬክቶሬቱ መገናኛ ብዙሃን ማስታወቂያ ሲሰሩ ስርዓተ ጾታን እንዴት ተረድተው ነው የሚሰሩት የሚል የማስታወቂያ መመሪያ አዘጋጅቷል። ስልጠናዎችንም ይሰጣል። በዳይሬክቶሬቱ ሥር ማስታወቂያ እንዴት ሞኒተር እንደሚደረግ የሚከታተል አካል ያለ ሲሆን እሷ የምትመራው ዳይሬክቶሬትም ሴቶች በማስታወቂያ ውስጥ በሚሳሉበት አግባብ ከማስታወቂያ ክትትልና አቅም ግንባታ ዳይሬክቶሬቱ ጋርም በቅንጅት ይሰራል።በተለይ በማስታወቂያ የሚተላለፉትን በሚቆጣጠርበት ወቅት በእሷ የሚመራው ዳይሬክቶሬትም የራሱ የክትትል አግባብ አለው። በተጨማሪም እንደ ተቋም የቅሬታና የተቃውሞ ማስተናገጃ ስርዓት የዘረጋበት 9192 የተሰኘ ስርዓት በመኖሩ ማንኛውም ሰው በመገናኛ ብዙሃን በሚተላለፉ ፕሮግራሞችና ማስታወቂያዎች ዙሪያ ያለውን ቅሬታ ያቀርባል።
‹‹አንዳንዶቹ ማስታወቂያዎች ሴቶች ከአገራችን ባህል ውጭ በሆነ መልኩ እየተገላለጡ የሚያስተዋውቁባቸው ናቸው።ሴቶች በዚህ ቦታ ላይ ለሚተዋወቀው ዕቃም ሆነ ለማስታወቂያው አስተዋጾ እንዳላቸው ሳይሆን የዕቃው አሻሻጭ ወይም እንደ ዕቃ የሚቆጠሩበት ሁኔታ አለ›› ትላለች። እንዳከለችው ይሄን ችግር ለመፍታት የሚቀርቡ ቅሬታዎችንና በክትትል የተገኙ ችግሮችን መሰረት በማድረግ ማስታወቂያዎች ሞኒተር ይደረጋሉ።የማስታወቂያ ድርጅቶችን አስነጋሪዎችን የማሰልጠንና የማግባባት (የአድቮካሲ ሥራ) ይሰራል።ስልጠናው ምን እንዳገዛቸው መጠይቅ ተበትኖ የዳሰሳ ጥናት ይጠናል።በመጣው ለውጥ ላይም ክትትል ይደረጋል።በዚህ መሰረት የማስተካከያ እርምጃዎች እንዲያደርጉ ደብዳቤ ተጽፎላቸው ትእዛዙንም ተቀብለው ያስተካከሉ አሉ።በመሆኑም ለውጦች አሉ። ከዚህ ቀደም የሳሙና ማስታወቂያ ሲሰሩ የነበሩት ሴቶች ቢሆኑም አሁን እንዲህ ዓይነት ማስታወቂያዎች በወንዶችም እየተዋወቁ መሆኑ ማሳያ ነው።ሆኖም ማስታወቂያ ሥራ ስርዓተ ጾታን ያገናዘበና ጾታዊና ግላዊ ክብርን፤ ባህልን፤ ወግና ሐይማኖትን የጠበቀ እንዲሆን በማድረጉ ረገድ ብዙ ይቀራል።በቀጣይም ብዙ ተተግቶ ሊሰራባቸው የሚገቡ አሉ።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን የማስታወቂያ ክትትልና አቅም ግንባታ ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ፋንታዬ በመገናኛ ብዙሃን ከሚተላለፉ ማስታወቂያዎች ጋር ተያይዞ ባለስልጣኑ የሚሰራበት 759/2004 በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የወጣ የአገር የማስታወቂያ አዋጅ አለ።ይሄን የሚያስፈጽመው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ሲሆን አዋጁ ተፈፃሚ የሚሆነውም በአገር ውስጥ ያሉ ኢንዳስትሪ ላይ ነው። የራሳቸውን ሥራ ስርዓተ ጾታን ያገናዘበ መሆኑን የሚረዱበትና በሴቶች ላይ ሊያደርሱ የሚችሉ አሉታዊ ተፅዕኖን የሚቀንሱበት የማስታወቂያ ካውንስልም ያቋቋሙበት ሁኔታ አለ።በተጨማሪም ስርዓተ ጾታ ተኮር የማስታወቂያ ስርጭት ስታንዳርድ ወጥነት ባለው መልኩ መዘጋጀት ስላለበት ተዘጋጅቷል። የሚመለከታቸው አካላቶች ሀሳብ ሰጥተውበታል። እሱም ዳብሮ ለሚመለከተው አካል ተበትኖ ወደ ተግባር ተገብቷል። ይሄ ከዚህ ቀደም ያሉትን ክፍተት ይደፍናል ከዚህ ጋራም ብዙ ለውጦች አሉ ይላሉ።መልካም ንባብ!
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን መጋቢት 26/2015