በሰሜን ኢትዮጵያ ከሁለት ዓመታት በላይ ሲካሄድ የቆየው ጦርንት በሰላም ስምምነት ከተቋጨ ወራቶች ተቀጥረዋል:: በእነዚህ ጊዜያትም የፌዴራል መንግሥቱም ሆነ ሕወሓት በሰነዱ ላይ የተስማሟቸውን አንኳር ጉዳዮች ለመፈፀም የበኩላቸውን ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል:: ከእነዚህም የቀድሞ ታዋጊዎችን ትጥቅ በማስፈታት ወደ ሰላማዊ ሕይወታቸው የመመለሱ ተግባር ቀዳሚው ነው::
ይህንን በተጨባጭ መሬት ላይ ለማውረድ ያስችል ዘንዳም መንግሥት ብሔራዊ የተሐድሶ ኮሚሽን አቋቁሞ ወደ ሥራ ገብቷል:: አዲስ ዘመን ጋዜጣ ተቋሙ እስካሁን እያደረጋቸው ባሉ እንቅስቃሴዎች እና በሌሎች አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የኮሚሽኑን ኮሚሽነር አምባሳደር ተሾመ ቶጋን አነጋግሯል:: እንደሚከተለው አቅርቧል::
አዲስ ዘመን፡- ብሔራዊ የተሐድሶ ኮሚሽንን ማቋቋም ያስፈለገበት ምክንያት ምንድን ነው፤ ተልዕኮዎቹስ ምን ምን ናቸው?
አምባሳደር ተሾመ፡- እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕወሓት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በአገሪቱ ዘላቂ ሰላም ማምጣት የሚያስችል የሰላም ስምምነት ተፈራርመዋል። ስምምነቱ ብዙ ነገሮችን ያካተተ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ የቀድሞ የሕወሓት ታዋጊዎችን ትጥቅ የማስፈታት፤ ወደ አንድ ማዕከል ማሰባሰብ እና ስልጠና በመስጠት ወደ ነበሩበት ኅብረተሰብ እንዲቀላቀሉ ማድረግ አንዱ ነው:: ይህ የሚደረገው እነዚህ ዜጎች ሰላማዊ፣ ጤናማና ምርታማ ሕይወት እንዲመሩ ለማድረግ ነው::
እንደሚታወቀው ትጥቅ የማስፈታቱ ሥራ ከዚህ ቀደም ሁለት ጊዜ ተሠርቷል፤ የሰሞኑ ደግሞ ሦስተኛው ዙር ነው:: ይህ ሥራ የተለያዩ ተቋማት የሚሳተፉበት ቢሆንም በአግባቡ የሚመራው አንድ ተቋም ያስፈልገዋል ተብሎ ስለታመነ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ መሠረት ብሔራዊ የተሐድሶ ኮሚሽን ተቋቁሟል::
ኮሚሽኑ ሦስት የተለያዩ ተልዕኮዎች አሉት፤ አንደኛው አስቀድሜ እንዳልኩት የቀድሞ ተዋጊዎችን ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉና እንዲቋቋሙ ማድረግ ነው:: የቀድሞ ታዋጊዎች የሰላም፤ የዴሞክራሲና የልማት ኃይል እንዲሆኑ ለማድረግ የሚያስችል ሥርዓት የማበጀት ሥራ ኮሚሽኑ ኃላፊነት ተሰጥቶታል:: ለዚህም ከሁሉ በፊት ትጥቅ የማስፈታቱ ሥራ በተከታታይነት የሚሠራ ሲሆን፣ ጎን ለጎንም ታዋጊዎችን ወደ አንድ ማዕከል የማስገባቱ ሥራ የሚከናወን ይሆናል::
በነገራችን ላይ የእኛም ሆነ መሰል ተቋማት የተቋቋሙት ጊዜያዊ ችግር ለመፍታት እንጂ ዘላቂ አይደሉም፤ ሥራቸውን ሲጨርሱ ይፈርሳሉ፤ ለእኛም ቢሆን የሁለት ዓመት ዕድሜ ነው የተሰጠን:: ኮሚሽኑ ምንም እንኳን አሁን የተቋቋመበት ምክንያት መንግሥት ከሕወሓት ጋር የደረሰውን ስምምነት ተከትሎ ቢሆንም የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚያደርገው ውይይት በአገሪቱ ሌሎችም አካባቢዎች ትጥቅ የሚፈቱ ወይም የፈቱ የቀድሞ ሰራዊት አባላት ስለሚኖሩ ይሄ ተልዕኮ ብሔራዊ እንዲሆን ተደርጓል::
ይህ ማለት ትግራይ፣ አማራ፣ አፋር፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ደቡብ ብሔረሰቦች ክልል እንዲሁም ጋምቤላ አካባቢ ያሉ የቀድሞ ተዋጊዎች አሉ:: ስለዚህ ይሄ ሥራ ከተሠራ አይቀር በአንድ አካባቢ ብቻ ላይ የታጠረ ሳይሆን ብሔራዊ እናደርገው የሚል ስምምነት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ተደርሷል:: በመሆኑም የኮሚሽኑ ተልዕኮ ብሔራዊ ሆኖ የሚሸፍናቸው ሁሉንም ክልሎች ነው::
በዋናነት እንድንሠራ የሚፈለገው የቀድሞ ተዋጊዎች ወደ ሰላማዊነት እንዲመለሱ የማድረግ ሥራ ነው:: ይህንን ለማድረግ የመጀመሪያው ሥራ መሆን ያለበት ትጥቅ የማስፈታት ጉዳይ ነው:: በጦርነቱ የተሳተፉ ስለሆኑ መጀመሪያ ትጥቃቸውን መፍታት ይጠበቅባቸዋል፤ ይህ የፕሪቶሪያው ስምምነት አካል ነው:: ይህ ሥራ በእኛ ሳይሆን በመከላከያ በጥሩ ሁኔታ እየተሠራ ነው:: በተጨማሪም ይሄን ሥራ የሚከታተል የአፍሪካ ህብረት የክትትልና የቁጥጥር ቡድን አለ፤ ይህ ቡድን ነው በአካባቢው ይህንን ሥራ እየሠራ ያለው::
በቅርቡ መቀሌ ሄጄ በነበረበት ወቅትም ይህንን ቡድን የሚመራ ጀኔራል አግኝቼ እንደተወያየነው ሥራው በጥሩ ሁኔታ እየተሠራ መሆኑን፤ በተሠራው ሥራ ደስተኞች እንደሆኑ፤ እስካሁን ድረስ ትልቅ እንቅፋት እንዳልገጠማቸው ገልፀውልኛል:: በቀጣይ የቀድሞ ታዋጊዎችን ወደ አንድ ማዕከል ካስገባን በኋላ ስልጠና እንሰጣቸዋለን::
እነዚህ የቀድሞ ተዋጊዎች ከኅብረተሰቡ ጋር ተቀላቅለው ሰላማዊ ሕይወት እንዲኖሩ ለማድረግ መንግሥት በኮሚሽኑ በኩል ድጋፍ የማሰባሰብ ሥራ እየሠራ ነው:: ወደፊትም ቢሆን ምንም ዓይነት የፖለቲካ ልዩነት ቢኖር እንዲሁም ሌሎች ችግሮች ቢከሰቱ ችግሮቻችን በሰለጠነና በሰላማዊ መንገድ፤ በውይይት የሚፈታበትን አግባብ እንዲከተሉ የሚያደርግ ስልጠና እንሰጣለን:: ለዚህ የሚሆን ልምድ እያሰባሰብን ነው:: ጥያቄውን በጥቅሉ ለመመለስ የተቋቋምንበት ዓላማ የሰላም ስምምነቱ አካል ስለሆነ ነው::
አዲስ ዘመን፡- የመቀሌ ጉዟችሁ ምን ይመስል ነበር?
አምባሳደር ተሾመ፡- መቀሌ የሄድንበት ዋና አላማ የጀመርነውን የኮሚሽኑን ሥራ በተመለከተና በአጠቃላይ ትጥቅ ማስፈታትና መልሶ የማቋቋም ሥራ ለመሥራት ነው:: ምክንያቱም እዚያ ከሌላው አካባቢ ላቅ ባለ ሁኔታ የቀድሞ ታዋጊዎች በመኖራቸው ብዙ የሚጠበቅ ነገር በመኖሩ ነው:: የሄድነውም ሁለት አጀንዳዎችን ይዘን ነው፤ አንዱ ስለትጥቅ ማስፈታት የሌሎች አገራት ተሞክሮ ምን እንደሚመስል በማሳየት በእኛም አገር ዘላቂ ሰላም የሚኖረውን ጠቀሜታ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ነው:: ሁለተኛው ተቋሙ የሚሠራቸውን ሥራ ግልፅ ለማድረግ ነው:: በመድረኩ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የፌዴራልም ሆነ የክልል አካላት እንዲሳተፉ አድርገናል:: ከሕዝቡ ከተነሱት ጉዳዮች መካከል በዋናነት ተዋጊዎችን ቶሎ ትጥቅ በማስፈታት ወደ ማህበረሰቡ የመቀላቀል ጥያቄ ነው::
ይህንን ለማድረግ አስቀድሜ እንዳልኩት የአቅም ውስንነት እንደሚኖር ይጠበቃል:: ሆኖም የመቀሌ ቆይታችን በጥቅሉ የተወሰኑ ነገሮች አሳክቷል ብዬ አስባለሁ:: አንደኛ ከሰላም ስምምነቱ በኋላ ብሔራዊ የሆነ መድረክ የተዘጋጀው ለመጀመሪያ ጊዜ ነው:: ይህም እንደዚህ ዓይነት ፕሮግራሞች መቀሌ ማካሄድ የሚያስችል ሁኔታ እንዳለ መልዕክት ያስተላልፋል::
ሁለተኛ ከሁለት መቶ ሰው በላይ እዚያ ድረስ በመሄድ መድረኩን በተሳካ ሁኔታ ማካሄዳችን የሰላም ስምምነቱ እየተፈፀመ ስለመሆኑ ማሳያ ነው:: ይህ ማለት ደግሞ በኢትዮጵያ መንግሥትና በሕወሓት መካከል ያለው መተማመን እየጎለበተ መምጣቱን ያመላክታል::
ከሁሉ በላይ ለቀድሞ ታዋጊዎች የሚተላለፈው መልዕክት ነው፤ ይህም ትጥቃቸውን ቢፈቱም የእነሱ ጉዳይ አብቅቷል ማለት አይደለም፤ በቀጣይ ወደ ሰላማዊ ሕይወት መመለስ የሚያስችል ሁኔታ መንግሥት በቁርጠኝነት የሚያመቻች እንደሆነ ነግረናቸዋል:: በአጠቃላይ ከእቅዳችን አኳያ የተሳካ መድረክ ነበር ማለት ይቻላል::
አዲስ ዘመን፡- የቀድሞ ታዋጊዎችን ትጥቅ የማስፈታቱ ሂደት ምን ያህል ውጤታማ ነው? በተለይ ከተቀመጠለት ጊዜ አንጻር?
አምባሳደር ተሾመ፡- አስቀድሜ እንደገለፅኩት ይህንን ሥራ የሚያከናውነው መከላከያ ነው፤ ይህንን ሥራ እንዲከታተል ኃላፊነት የተሰጠው የአፍሪካ ህብረት ቡድን አለ፤ ከሁለቱም ባገኘነው መረጃ የከባድ መሣሪያዎች ትጥቅ የማስፈታቱ ሥራ በተሳካ ሁኔታ ተከናውኗል:: ይህ ሥራ ከተከናወነ በኋላ መሣሪያዎቹን የአገር መከላከያ ሚኒስቴር ተረክቧል:: በተጨማሪም በግለሰብ ደረጃ ያሉ ትጥቆችን የማስፈታት ሥራ ተጀምሯል፤ እናም ይሄም ሥራ በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ነው ማለት ይቻላል::
የሰላም ስምምነቱ ይሄ ብቻ ሳይሆን ሌሎች አብሮ መሄድ ያለባቸው በርካታ ነገሮች የያዘ ነው:: ሁሉም ባስቀመጥነው የጊዜ ገደብ እየሄደ ነው የሚል እምነት የለንም፤ ለዚህ ብዙ ምክንያቶች አሉ፤ ሰሞኑን የተቋቋመው የትግራይ ጊዜያዊ መንግሥት እንኳን በተባለው ጊዜ አይደለም የተከናወነው፤ ምክንያቱም ሰፊ ውይይት የሚፈልግ በመሆኑ ነው:: ደግሞም ብዙ ክርክሮች ነበሩ፤ እናም ያንን ሁሉ አልፎ የጋራ መግባባት ላይ በመደረሱ የሽግግር መንግሥት ለማቋቋም ብዙ ጊዜ ወስዷል:: ይሄ የማይጠበቅ ነገር አይደለም:: እንደምታውቂው ጉዳዩም ቀላል ነገር አይደለም:: ስለዚህ በተባለው ጊዜ ሰሌዳ እንዳሰብነው ወይም እንደፈለግነው ላይሄድ የሚችልበት ሁኔታ አለ::
ለምሳሌ ሰራዊቱን ትጥቅ ካስፈታን በኋላ ወደአንድ ማዕከል የማሰባሰቡ ሥራ እዚያ ካለው አስተዳደር ጋር በጋራ መስራት መቻል አለብን:: ሰራዊቱን ሲመሩ የነበሩ ሰዎች አሉ፤ ደግሞም እንደ ተቋም ተደራጅተው ነው የሠሩት:: ስለዚህ ሠራዊቱን ወደአንድ ማዕከል የማሰባሰቡ ሥራ እዚያ ካለው አካልና ከፌዴራል ተቋማት ጋር በተለይ ደግሞ ከአገር መከላከያ ሰራዊት ጋር ሊሠራ የሚገባው ጉዳይ ነው:: በዚህ ሂደት ውስጥ በሚፈለገው ፍጥነት ለመሄድ የማያስችሉ ሁኔታዎች ሊያጋጥሙ ይችላሉ::
በመሠረቱ ሌሎች በርካታ አገራትም በተመሳሳይ ሂደት ያለፉ፤ እያለፉም ያሉ አሉ:: ደቡብ ሱዳንን በአብነት ብንወስድ በጣም ረጅም ጊዜ ነው፤ የእኛ ምንአልባት በወራት ውስጥ ያለ ነገር በመሆኑ በጣም ዘገየ ተብሎ ባይወሰድ ጥሩ ነው ብዬ አስባለሁ:: ምክንያቱም ተግዳሮቶቹ ቀላል አይደሉም፤ ስለዚህ ያንን ተግዳሮት ለማለፍ ጊዜ ወስዶ መወያየትና ወደ አንድ የጋራ አመለካከትና አስተሳሰብ ማምጣት ያስፈልጋል::
ለማንኛውም ግን ትጥቅ የማስፈታቱ ሂደት በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ነው ማለት የተሻለ ነው፤ ከዚያ ቀጥሎ ወደ አንድ ማዕከል የማሰባሰቡ ሥራ ይቀጥላል:: አሁንም በተወሰኑ ካምፖች ላይ የገቡ አሉ፤ መቀሌ የሄድን ጊዜ የእኛ ቡድን አይቷቸው አነጋግሯቸው መጥቷል:: አሁን ከተቋቋመው የሽግግር መንግሥት ጋር በመሆን የቀረውን ሰራዊት ትጥቅ በማስፈታትና ወደ ማዕከል ለማምጣት በጋራ እንሠራለን::
አዲስ ዘመን፡-በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ የመገንባት፤ ተሳትፎ የነበራቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች የልማትና የዴሞክራሲ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ምን እየተሠራ እንደሆነ ቢያብራሩልን?
አምባሳደር ተሾመ፡– በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎች ወደሰላማዊ ሕይወት እንዲገቡ ከማድረግ አኳያ ኮሚሽኑ ብቻውን ሊሠራው አይችልም:: የሌሎች የክልልና የፌዴራል ተቋማት ጨምሮ የብዙ አካላትን ተሳትፎ የሚጠይቅ ነው። የብዙ አገሮች የቀድሞ ተዋጊዎችን ትጥቅ ማስፈታትና ወደአንድ ማዕከል ማስገባት ሆነ የመልሶ ማቋቋም ሥራዎችን በስኬት የመወጣት ተሞክሮ የብዙ አካላትን ድጋፍ ጠይቋል::
በርግጥ ሥራው የሚመራው በመንግሥት ነው፤ ምንም ጥያቄ የለውም:: ልክ ሌሎች ፖሊሲዎችን እንደሚያስፈፅመው መንግሥት ባለቤት ሆኖ ይመራል፤ ለዚህ ነው ብሔራዊ የተሐድሶ ኮሚሽን የተቋቋመው::
የእኛ ሚና ማስተባበር ነው፤ በራሳችን የምንሥራቸውም ሥራዎች አሉ፤ እንደተቋም ግን ከብዙ አካላት ጋር ነው የምንሠራው:: መንግሥት የመሪነት ሚና እየተጫወተ የግሉ ዘርፍ ሊሳተፍ ይገባል:: ምክንያቱም ሁላችንም የጦርነቱ ተጎጂዎች ነን፤ የሰላሙም ተጠቃሚዎች ነን:: በተጨማሪም ሲቪል ማህበራት መሳተፍ መቻል አለባቸው::
ተሳትፎ በተለያየ መንገድ ሊገለፅ ይችላል፤ አብዛኞቹ የመልሶ ማቋቋም ሥራዎች በመንግሥት አቅም ብቻ የሚሠሩ አይደለም:: አሁን ያለንበትን ሁኔታም የሚታወቅ ነው:: ስለዚህ ብዙ የመልሶ ማቋቋም ሥራዎች በልማት አጋሮች ድጋፍ የሚከናወኑ ናቸው:: የእኛም ተሞክሮ የሚሳየው ይህንኑ ነው፤ የውጭ ድጋፍ ሲባል የቴክኒካል ድጋፍ ሊሆን ይችላል:: ለምሳሌ ወደማዕከል የማስገባቱን ፕሮግራም እየሠራን ያለነው ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጋር በመሆን ነው:: የራሳችን ቡድን አለን፤ በሌላ በኩል የዓለም አቀፍ ተሞክሮ ስለሚያስፈልገን ከተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም ጋር በመሆን ነው የሠራነው:: ስለዚህ የቴክኒክ ድጋፍ ያስፈልጋል::
ከሁሉ በላይ ለማቋቋም የሚያስፈልገው ገንዘብ በጣም ከፍተኛ ነው:: ደግሞ ከጦርነት ውስጥ ገና እየወጣ በመሆኑ ያንን ማሳካት የሚያስችል አቅም መፍጠር ያሻል:: ስለዚህ ልክ እንደማንኛውም ልማት ይሄም ፕሮግራም እንዲሳካ ከተፈለገ የውጭ የልማት አጋሮች ለጋሽ ድርጅቶች፣ የግሉ ዘርፍ፣ የሲቪል ማህበራት ተሳትፎ ያስፈልጋል::
ከሁሉ በላይ ይሄ ሥራ የቀድሞ ተዋጊዎችን ዝም ብሎ ከማህበረሰቡ ጋር መቀላቀል ብቻ ሳይሆን ማህበረሰቡም ከዚያ ፕሮግራም እንዲጠቀምና ማህበረሰብን መሠረት ያደረገ መልሶ ማቋቋም እንዲሆን ይደገፋል:: ስለዚህ ኮሚሽኑ ስልጠና በሚሰጥበት ጊዜ ሠላም ሚኒስቴር፤ ሥራና ክህሎት ሚኒስቴር እና ጤና ሚኒስቴር ከመሳሰሉ የፌዴራል ተቋማትና ከክልል ቢሮዎች ጋር እብሮ ይሠራል::
በነገራችን ላይ እነዚህ ተቋማት የብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽን ምክር ቤት አባላት ናቸው:: ስለዚህ ሌሎች አካላት የሚሳተፉበት የቅንጅት አሠራር አለ:: ሁሉም አካላት የድርሻቸውን እንዲወጡ ማድረግ ከተቻለ የተሳካ የመልሶ ማቋቋም ሥራ እንሠራለን ብለን እናስባለን::
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ ጋር ተያይዞ በጦርነቱ አካላቸውን ላጡ ዜጎች የታሰበ ነገር አለ?
አምባሳደር ተሾመ፡- አዎ፤ ይህ ሲባል ግን በትግራይ ብቻ ላሉ ሳይሆን በሁሉም አካባቢ ላሉ ማለት ነው:: ሰሞኑን አማራና አፋር አካባቢም ለመሄድ ፍላጎት አለን፤ ከክልሎቹ ጋር እየተነጋገርን ነው:: እንግዲህ አሁን ካለን መረጃ ትግራይ አካባቢ በጦርነቱ ያልተሳተፈ አካል የለም፤ ምክንያቱም የነበረውን ቅስቀሳ ሁላችንም እናውቃለን፤ የትግራይን ሁኔታ ለየት የሚያደርገውም ይህ ነው:: ስለዚህ በዚያ ጦርነት የደረሰባቸውና ልዩ እንክብካቤ የሚፈልጉ የኅብረተሰብ ክፍሎች አሉ::
ሴቶችና ላለፉት ሁለት ዓመታት ከትምህርት ገበታቸው ተነስተው ያለዕድሜያቸው መሣሪያ ይዘው እንዲታገሉ የተደረጉ ሕፃናት አሉ፤ እነዚህን ከቤተሰብ ጋር ማገናኘትና ወደ ትምህርት እንዲመለሱ ማድረግ ይገባል:: በዚያ ስብሰባ ላይ የአካል ጉዳተኞች ተወካዮችም ያነሱት ጥያቄ ይህንን ነው:: በቀጣይ እያንዳንዱ አካል ጉዳተኛ ምንዓይነት ድጋፍ ያስፈልጋዋል የሚል መረጃ ለማሰባሰብ ዝግጅት እያደረግን ነው:: ያ መረጃ በርካታ ጉዳዮችን የያዘ ሲሆን ለምንሠራውም ሥራ ወሳኝ ድርሻ አለው:: የአካል ጉዳተኛው የጉዳቱ መጠን ተለይቶ እንደየሁኔታው ጊዜያዊና ዘላቂ ድጋፍ የሚደረግ ይሆናል:: ይህንን ለማድረግ ከፍተኛ የሆነ ሀብትና የሰው ኃይል፤ የኅብረተሰቡን ተሳትፎ፤ የአጋሮችን ድጋፍ ይፈልጋል::
አዲስ ዘመን፡- በክልሉ የሽግግር መንግሥት እንዲመሠረት መደረጉና የሕወሓት ከሽብርተኝነት መዝገብ መሰረዙ ለሰላም ስምምነቱ በአግባቡ መተግበር ያለው ፋይዳ ምንድን ነው ይላሉ?
አምባሳደር ተሾመ፡- የሰላም ስምምነቱ ለትግራይም፤ ሆነ ለመላው አገሪቱ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ምንም ጥያቄ የለውም:: ከሁለት ዓመት በላይ በጦርነት አሳልፈናል፤ ብዙ ጉዳት ደርሷል:: በክልሉ ብቻ ሳይሆን በአጎራባች ክልሎችና በአገር ደረጃ ትልቅ ተፅዕኖ ፈጥሯል:: አሁን በመልሶ ግንባታ በመንግሥት አቅም የሚሠሩ በጣም ሰፊ ሥራ እየሠራን ነው::
የውጭ ድጋፍ ለማግኘትም በብሔራዊ ደረጃ እየተሠራ ያለ ሥራ አለ:: ይሄ የሆነው ዞሮ ዞሮ የሰላም ስምምነቱ ስለተፈረመ ነው:: ስምምነቱ ባይፈረም ኖሮ ወደመልሶ ግንባታና ኢኮኖሚያችን እንዲያገግም የማድረግ ሥራ ላይ ትኩረት ልናደርግ አንችልም:: ከሁሉ በላይ የተኩስ አቁም ስምምነቱ በራሱ ለዘላቂ ሰላም መምጣት ትልቅ ፋይዳ አለው::
በሌላ በኩል ሕወሓት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ስምምነቱን የፈረመ አንድ አካል መሆኑ ይታወቃል:: ከዚህ ባሻገር እኛ በትግራይ ለሚደረገው ማንኛውም ዓይነት የሰላም ስምምነት ሥራ አጋር ያስፈልገናል፤ ከዚያ አኳያ ነው የሽግግር መንግሥቱ መመስረት ትርጉም ያለው የሚሆነው:: ፖሊስ ፀጥታን፤ መከላከያ የአገር ድንበር ሊያስከብር ይችላል፤ ሆኖም በተጨባጭ የመልሶ ግንባታ፣ የመልሶ ማቋቋም ሥራ የሚሰጡ አገልግሎቶችን የፌዴራል መንግሥቱ ከዚህ እየተንደረደረ ሄዶ ሊሠራ አይችልም::
ስለዚህ በክልሉ አንድ ጊዜያዊ አስተዳደር ሊኖር ያስፈልጋል:: እናም አሁን ከተመሠረተው የሽግግር መንግሥቱ፤ የፌዴራል መንግሥትና ሌሎች አካላት የሚሠሩት ሥራ መንግሥታዊ አገልግሎትን ከመስጠት አኳያ ሕወሓት የዚህ አካል መሆኑ የራሱ ትልቅ ፋይዳ አለው::
ከዚህም ባሻገር የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር መቋቋም ለኮሚሽኑ የሥራ ስኬት ትልቅ አጋዥ ኃይል ይሆናል ተብሎ ይታመናል:: ለምሳሌ የቀድሞ ታዋጊዎችን ትጥቅ የማስፈታቱም ወደ አንድ ማዕከል የማስገባቱ ሥራ ብቻችንን ልንሠራው አንችልም፤ ካምፕ መምረጥ ያስፈልጋል፤ ጥበቃ ያስፈልጋልና ሌሎችም ሥራዎች መሥራት ይጠበቅ ነበር:: ለዚህ ደግሞ እዚያ አካባቢ አስተዳደር ሊኖር ግድ ይላል:: ያለእሱ ብቻችንን እዚያ መሥራት የምንችለው ነገር አይኖርም::
ደህንነትን በሚመለከት የፌዴራልም የፀጥታ ተቋማትም በየአካባቢው ሊያቋቁም አይችልም:: ስለዚህ የጊዜያዊ አስተዳደር መኖር ለእኛ ሥራ በጣም ጠቃሚ ነው:: ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤትም ለማቋቋም እያሰብን ነው:: እያንዳንዱ የቀድሞ ተዋጊ ጋር ደርሰን መረጃ ሰብስበን በቀጣይ ወደ የማህበረሰቡ ጋር ለመውረድ የግድ የክልሉን አስተዳደር ድጋፍ ያስፈልጋል::
ከዚህ አንፃር ከእኛ የሚጠበቀው ለሥራው የሚያስፈልገው ፕሮግራም በጋራ ሆንን እናስፈፅማለን:: ልክ የፌዴራል መንግሥት ተሳትፎ እንደሚያደርግ ሁሉ የክልሉም አስተዳደር ወሳኝ ሚና መጫወት ይጠበቅበታል:: ለምሳሌ አርሶአደሩ ወደእርሻው እንዲመለስ ከተፈለገ የግድ እዚያ አካባቢ የክልሉ ግብርና ቢሮ ሰዎች ጋር አብሮ መሥራት ያፈልጋል፤ የጤና ክብካቤ የሚያስፈልገው ሰው ካለ እኛ የጤና ባለሙያዎች የሉንም፤ ግን የጤና ባለሙያዎች ከጤና ሚኒስትር እንዲሁም ከክልሉ ጤና ቢሮ ጋር በመሆን መሥራት ይገባናል::
ለዚህ ብቻ ሳይሆን የሰላም ስምምነቱን በመፈፀም፤ ክልሉ ወደ ሰላማዊ ሁኔታ እንዲመለስ፤ እንደሌሎች ክልሎች መደበኛ ወደሆነ ሥራ ለመግባት የሚያስችል ሁኔታ ውስጥ ለመግባት የሽግግር መንግሥት ወሳኝ ነው:: ያለሱ የሰላም ስምምነቱ ለመተግበርም ሆነ ሰላማዊና ወደ መደበኛ ሁኔታ ማስገባት አይቻልም::
እርግጥ አሁንም ቢሆን የሰላም ስምምነቱ በአግባቡ እንዳይተገበር የፖለቲካ ስጋት፤ የተፈለገው ገንዘብ ላይገኝ ይችላል የሚሉ ስጋቶች አሉብን:: ከዚያ ውጪ ግን በክልሉ ተንቀሳቅሰን ለመሥራት ብዙ ስጋት የለብንም:: ዋናው ኅብረተሰቡም፤ የቀድሞ ተዋጊዎችም፤ ጊዜያዊ አስተዳደሩም የፌዴራል መንግሥቱም የሚፈልገው ጉዳይ ስለሆነ ብዙ ስጋት የሚሆኑ ነገሮች ይኖራሉ ተብሎ አይታሰብም::
በዋናነት የሚያስፈልገው በጣም ከፍተኛ ሀብት መገኘቱ ላይ ነው:: ሀብቱ ካልተገኘ ምንአማራጭ መከተል አለብን? የሚለው ነው የሚያሳስበው:: ግን አስቀድሜ እንዳልኩት ስጋቱን ብቻ ተንትነን አልተውንም፤ ስጋቱ እንዲቀረፍ ምን መሥራት አለብን? የሚል ትንተና ሠርተናል:: ደግሞም ብዙ ልምድ እንደሚያሳየው ሁሉም የሚመለከተው አካል የሚሠራ ከሆነ ስጋቶቹን ማስወገድ ይቻላል የሚል እምነት አለ::
የሕወሓት ከሽብርተኝነት መዝገብ መሰረዙም ለዚህ ሥራ በጣም አስፈላጊ ነው:: ምክንያቱም መንግሥት እያቋቋምን ነው ያለነው:: ከዚህ በፊት የሰላም ስምምነቱን ተደራድሮ ለመፈረም ጥረት ሲደረግ የነበረው ከሕወሓት ጋር ነው:: በመሠረቱ ድርድር የሚደረገው ከጠላት ወይም ከአሸባሪ ጋር እንጂ ከወዳጅ ጋር አይደለም:: ይህ በዓለም ደረጃም የታወቀ ነገር ነው:: ያ አካል ችግሩን በኃይል ለመፍታት ሲሞክር፤ ከሰላማዊና ሕጋዊ መንገድ ውጪ ፍላጎቱን በኃይል ለማስፈፀም ስለፈለገ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ብሎ ፈርጆታል::
አሁን የሰላም ስምምነት ከተደረሰ በተለይም በሰላማዊ መንገድ ችግሩን ለመፍታት ስምምነት ከገባ በኋላ ‹‹አሸባሪ›› እያልን ልንጠራው አንችልም:: ያኔ ያስገደደ ሁኔታ ነበር፤ አሁን ደግሞ ስለተቀየር ከአሸባሪነት መዝገብ ማንሳት ተገቢ ነው:: በአጠቃላይ የሰላም ስምምነቱን በተጨባጭ ተግባራዊ ለማድረግና በትግራይ በቀጣይ ለምንሠራቸው ሥራዎች እንደዚሁም በሌሎች አካባቢዎችም ለምንሠራቸው ሥራዎች ይህንን ማድረጉ በጣም ተገቢ ነው::
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ የሽግግር መንግሥት በቀጣይ ምን መሥራት ይጠበቅበታል ይላሉ?
አምባሳደር ተሾመ፡- የሽግግር መንግሥቱ የመጀመሪያ ሥራ መሆን አለበት ብዬ የማስበው በክልሉ የሚሰጡ መንግሥታዊ አገልግሎት ለሕዝቡ መስጠት ነው:: ከፌዴራል የፀጥታ አስከባሪዎች ጋር በመሆን የክልሉን ፀጥታና ሰላም ሁኔታ ማስከበር ያስፈልጋል:: በጣም የተጎዳ አካባቢ ከመሆኑም ጋር ተያይዞ መልሶ ግንባታና ልማት ላይ መሳተፍ አለበት:: እንደተባለው የሽግግር ጊዜው ለስድስት ወር ነው የታሰበው:: በዚህ መካከል የክልሉ ምርጫ የሚካሄድበት ሁኔታ አብሮ መሠራት መቻል አለበት::
እነዚህ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳይ ሥራዎች አሁን የምናስበውን የቀሩ የሰላም ስምምነቶችን የማስፈፀም፤ በክልሉ ለመሥራት የምናስበው የመልሶ ግንባታ ሥራ እንዲሳካ ከእኛ ጋር አጋር መሆን ይጠበቅበታል:: ስለዚህ የሚጠበቀው በመጀመሪያ ክልሉን በጊዜያዊነት ማስተዳደር፤ በዋናነትም ለሕዝቡ የሚያስፈልገውን አገልግሎት መስጠት ነው::
ለዚህም ሲቪል ሰርቪሱ ወደ ሥራ እንዲመለስ፤ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተቋማትን ወደሥራ ማስገባት፤ በተለይ በየካምፑ ያሉ ትምህርት ያቋረጡ ሕፃናትን ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ማድረግ ይጠበቅበታል:: በመሠረቱ የክልሉ ኢኮኖሚ ተጎድቷል፤ ስለዚህ በአገር ደረጃ በሚደረገው ጥረት ላይ የክልሉ አስተዳደር ድጋፍ ወሳኝነት አለው::
የክልሉን ፀጥታ ለማስጠበቅ በክልሉ ፖሊስ የሚሠራ እንዳለ ሆኖ ከዚያ በላይ የሚጠይቁ ጉዳዮች ካሉ የፌዴራል መንግሥቱ የሕግና ፀጥታ አካል ጋር አብሮ መስራት ያስፈልጋል:: ከሁሉ በላይ የሽግግር መንግሥቱ ጊዜያዊ ሥራ የሚሠራ እንደመሆኑ ቋሚ ሥራ ለመስራት ምርጫ ተደርጎ በክልሉ ምክር ቤት መኖር አለበት:: በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት መኖር መቻል አለበት:: ይህም የፌዴራል መንግሥት ከምርጫ ቦርድ ጋር በመሆን ያስፈፅማል ብለን እንጠብቃለን::
አዲስ ዘመን፡- የሽግግር ፍትህን ተግባራዊ የማድረጉ ሂደት በምን መልኩ ሊቀጥል ይገባል ይላሉ?
አምሳደር ተሾመ፡– እንግዲህ በዚህ ጦርነት ብዙ የደረሰ ጉዳት እንዳለ ይታወቃል:: ከዚህ አኳያም ብዙ ሰዎች ‹‹ፍትህ መምጣት አለበት›› ብለው ጥያቄ ያነሳሉ፤ በእኔ እምነትም ጥያቄው ትክክል ነው፤ ምክንያቱም ያለ ፍትሕ ሰላም ልናሰፍን አንችልም:: ደግሞም በስምምነቱ ውስጥ አንድ አካል ሆኖ የገባው ጉዳይ የሽግግር ፍትሕ ጉዳይ ነው:: ይህንን ሥራ የፍትሕ ሚኒስቴር በኃላፊነት እየሠራ ነው:: የመጀመሪያ ሥራ መሆን ያለበት የሽግግር ፍትሕ ፖሊስ መንደፍ ነው በሚል ሰሞኑን የፍትህ ሚኒስቴር ያዘጋጀውን ረቂቅ ሰነድ ላይ ሰፊ ምክክር እየተደረገ ነው:: በዚህም ግብዓት እየተሰበሰበ ነው::
አሁን ላይ በፖሊሲው ይዘት ላይ መናገር ባልችልም በሁሉም ላይ የሚተገበር ነው የሚሆነው:: ስለዚህ የቀድሞ ታዋጊዎችም ሆኑ ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ለተጠያቂነት ዝግጁ መሆን አለባቸው:: በዚህ ልዩነት መፍጠር የለብንም ብዬ አምናለሁ:: በመጀመሪያ ግን ፖሊሲው በምክር ቤት ማፅደቅ ቀዳሚ ሥራ ይሆናል ብዬ አምናለሁ::
በመሠረቱ የሽግግር ፍትህን የምናስፈፅመው ለራሳችን ብለን ነው፤ የውጭ አካላት ስለጠየቁን ሳይሆን ለአገራችንና ለሕዝባችን የሚበጅ በመሆኑ ነው:: በሽግግር ፍትሕ የተጎዳ ይካሳል፤ ይቅርታ ይወርዳል:: ደግሞም በዚህ ጦርነት እርስበርሳችን ብዙ ተቆሳስለናል፤ በመሆኑም ፈውስ ያስፈልገናል:: ፈውስ የሚመጣው ደግሞ ፍትሕ ሲሰፍን ነው፤ ፍትሕ የሚመጣው ግን ሰዎችን በማሰር ብቻ አይደለም፤ ጥፋቱን አምኖ የተቀበለ፤ ይቅርታ የጠየቀ፤ በሕግ መሠረት ይቅርታ የሚደረግለት ሊኖር ይችላል:: ይህንን ለማድረግ ደግሞ የወንጀሉ ሁኔታ ይወስነዋል:: በአጠቃላይ በሽግግር ፖሊሲ ማዕቀፍ የሚታይ ነው የሚሆነው::
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ማብራሪያ በዝግጅት ክፍሉ ሥም ከልብ አመሰግናለሁ::
አምባሳደር ተሾመ፡- እኔም አመሰግናለሁ::
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 25 ቀን 2015 ዓ.ም