በኢትዮጵያ ጥንታዊ ታሪካዊና ባህላዊ ሥርዓት ካላቸው ማህበረሰቦች መካከል የሃድያ ሕዝብ ተጠቃሽ ነው፡፡ ይህ ሕዝብ የራሱ የሆነ ቋንቋ፣ ባህል፣ ታሪክ፣ ሥነ-ጥበብ፣ ወግና፣ የኑሮ ዘይቤ ያለው ሲሆን በተለይም ማህበረሰቡን አስተሳስሮ ለዘመናት ያኖሩ፤ ከትውልድ ትውልድ የተሻገሩ ፤ ለሀገርም አንድነት ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸው በህላዊ ዕሴቶች ባለቤት ነው፡፡ ከእነዚህ ባህላዊ ሥርዓቶች መካከል ‘ጢግ-ጉላ’ የተሰኘው የጥል፣ የበቀልና የፀፀት ስሜትን ወደ ሰላማዊና ጤናማ ግኑኝነት የመመለስ ሥርዓት ዋነኛው ነው፡፡ የዛሬው ሀገርኛ አምዳችችንም በዚህ ሥርዓት ላይ ትኩረቱን ያደረገ ሲሆን የሃድያ ባህላዊ አስተዳደር ሥርዓት ዙሪያ ጥናት ያደረጉ ምሁርንም አነጋግሮ እንደሚከተለው ይዞላችሁ ቀርቧል፡፡
ጥናት አድራጊው ምሁር መምህር ግርማ ሱልዶሎ የሚባሉ የብሔረሰቡ ተወላጅ ሲሆኑ በዞኑ የተለያዩ ትምህርት ቤቶች በመምህርነትና በርዕሰ መምህርነት ለበርካታ ዓመታት አገልግለዋል፡፡ መምህር ግርማ እንደሚሉት፤ ጢግ- ጉላ በሃድያ ሕዝብ ከሚፈፀሙ ባህላዊ አስተዳደር ሥርዓቶች መካከል አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ በተለይም በማህበረሰቡ በግጭት አፈታት ሥርዓት ውስጥ ትልቁን ቦታ ይዞ የሚገኝና ግጭትን በማርገብ፤ ጠብን በማራቅ ጠንካራ ቤተሰባዊ ግኑኝነት እንዲፈጠር በማድረግ ረገድ ትልቅ ድርሻ ያለው ባህላዊ ክዋኔ ነው፡፡
በሀድያ ማህበረሰብ ዛሬም ድረስ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ይህ ‘ጢግ -ጉላ’ የተባለው የእርቅ ሥርዓት በተለይም አንድ ግድያ ከተፈፀመ በኋላ በቂም በቀል ሌላ ደም መፋስስ እንዳይመጣ በማድረግና አካባቢውን በማረጋጋት በኩል አወንታዊ ሚና እየተጫወተ መሆኑን መምህሩ ያስረዳሉ፡፡ ‹‹ጢግ- ጉላ ሰዎች የግድያ ወንጀል ሲፈፅሙ ወደ ፍፁም ይቅርታ የማምጣት ሥርዓት የሚፈፀምበትና ዛሬም ድረስ ለትውልድ እየተላለፈ ያለ አስተዳደራዊ ሥርዓት ነው፡፡ በዚህ አስተዳራዊ ሥርዓት ላይ በባህላዊ አስታዳደር ጉባኤ ከሚታዩ ጉዳዮች መካከል የሚጠቀስ ነው›› ይላሉ፡፡
‘ጢግ-ጉላ’ የበቀል፣ የክፋት፤ የጥፋት፤ የበደል ስሜትን በማንፃት ቤተሰባዊ ሰላም፣ ጤና እና የአባትና የልጅ ፤ የወንድም እና የእህት ግኑኝነት የመፍጠር ሥርዓት መሆኑንም ያስረዳሉ፡፡ ‹‹በቀል ፤ መገዳደል ፤ ማውደም፤ ማግለል የሌለበትና ፈፅሞ በፍቅር ላይ የተመሰረተ፤ ፍፁም ይቅርታን የያዘ የእርቅ፤ የማገናኘት፤ የማስተሳሰር ሥርዓት ነው›› በማለት ይናገራሉ፡፡ በተለይም አንዴ ግድያ ከተፈፀመ በኋላ ያለተጨማሪ ደም መፋስስ ጉዳዩ መቋጫ እንዲያገኝ የሚደረግበት ፍቱን የእርቅ ሂደት መሆኑንም ያመለክታሉ፡፡ ለጠፋ ሕይወት ሌላ ሕይወት ማጥፋት ሳያስከትል ያለበቀል በፍፁም ይቅርታ፤ በልባዊ ፍቅር፤ ቤተሰባዊ ውህደት ፈጥሮ የማስታረቅ ብልሃት ተብሎም በማህበረሰቡ ዘንድ የሚተረጎም መሆኑንም ያብራራሉ፡፡
ይህ ሥርዓት ሲፈፀም ብዙ ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉ መሆኑን የጠቀሱት መምህር ግርማ፤ በዋናነት ሶስት ዘርፎች በተለየ መልኩ የሚታዩ መሆኑን፤ ከእነዚህም መካከል የሽማግሌዎች የአስተዳደር ጉባኤ አንዱ እንደሆነና ከቤተሰብ ጀምሮ እስከ ጎሳና ብሔረሰብ አስታደደር የሚደርስ አምስት መዋቅር ያለው መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ይህ ሥርዓት ሲፈፀም የእነዚህ ዘርፎች መሪዎች በቀጥታ ተሳታፊ በመሆን ወደ እርቅ የሚያመጡበት ሂደት መኖሩን ያነሳሉ፡፡
እንደ እርሳቸው ገለፃ፤ በ’ጢግ-ጉላ’ ሥርዓት የገደለውን ሰው ወደ ይቅርታ ለማምጣት፤ በጥፋቱ እንዲፀፀት እና የሟች ቤተሰብ ፍፁም ይቅርታ እንዲያደርግ፤ ይህንን ሥርዓት ማህበረሰቡ እየፀለየ፣ እየመረቀ ፤ እየባረከ የሚመራ አንጃንቾ ወይም ከሽማግሌዎች መሪ ይሰየማል። ይህ ሰው በጣም በእድሜ የገፋ ሊሆን የሚገባው ሲሆን በማህበረሰቡ ዘንድ መመረቅ፤ መባረክ ይችላል ፤ ፀሎቱ ይሰማል ተብሎ የሚታመን መሆን ይጠበቅበታል፡፡ በተጨማሪም በጣም ከፍተኛውን የዳኝነት ስፍራ የያዘ ‘ሂራጋኖ’ በመባል የሚታወቅ ሰው የመጨረሻውንና ትክክለኛውን ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ ይታመናል፡፡
የሂራጋኖዎች ቁጥር በአጠቃላይ በዞን ደረጃ ከአራት የማይበልጥ መሆኑን መምህር ግርማ አመልክተው፤ ጉዳዩን እንዲያይ የተመረጠው ‘ሂራጋኖ’ የችግሩን ምንጭ ከስር መሰረቱ በማጣራት፤ መርምሮና ተንትኖ ምን መደረግ እንዳለበት የውሳኔ ሃሳብ ለሽማግሌዎቹ የሚሰጥ ቁልፍ ሰው መሆኑንም ያስረዳሉ፡፡ የእነዚህ አካላት ሚና እጅግ ከፍተኛ መሆኑን አንስተው፤ በተለይም የመጨረሻውን ውሳኔ የሚሰጡ በመሆኑ እውነተኛ እና ክልብ የሆነ ይቅርታ እንዲመጣ በማድረገድ ረገድ በህብረተሰቡ ዘንድ ትልቅ አመኔታ የተሰጣቸው መሆኑንም ነው ያስገነዘቡት። ‹‹የሽማግሌ መሪዎቹ በገዳይና በሟች ቤተሰብ መሃል ጣልቃ ይገቡና ከእነሱ ከፍ ያለውን ደግሞ መሪ አድርገው ተሰባስበው የሟች አባት በር ላይ እየሄዱ ደጅ ይጠናሉ፤ እርቅ እንዲመጣ፤ ሰዎች እንዳይተላለቁ የማድረግም ስራ ይሰራሉ›› ሲሉም ጥናት አድራጊው ያብራራሉ፡፡
እንደመምህር ግርማ ማብራሪያ፤ ነፍስ ከጠፋ በኋላ በመጀመሪያ የገዳዩ ቤተሰብ መዋቅር ውስጥ ያሉ ሽማግሌዎች ወደ ሟች ቤተሰብ ሽማግሌዎች ጋር በመሄድ ውይይት ያደርጋሉ፡፡ በመቀጠል ወደ ሟች ቤት ይሄዱና ወደ ክስ እንዳይኬድ በባህላዊ ሥርዓቱ ተፅእኖ ይፈጥራሉ። ሽማግሌዎች ጉዳዩን ይዘው የግድያውን መነሻና መሰረቱን እንዲያጣራና መፍትሔ እንዲሰጥ’ ሂራጋኖ’ ተብሎ የተሰየመው ግለሰብ ጋር ነው የሚሄዱት፡፡ ይህ ሂራጋኖ የተደበቀውን ሚስጥር፣ የወንጀሉን አፈፃፀምና ምክንያት ሁሉ የመርመር ሃላፊነት አለበት፡፡ እነዚህ ሰዎች በተፈጥሮ የተሰወረውን በደል የመምርመርና የመተንበይ ተሰጥኦ ከፈጣሪ የተሰጣቸው ነው ተብለው ይታመናሉ፡፡
በተጨማሪም ‘ሂራጎኖ’ዎቹ ከሕይወት ተሞክራቸው በመነሳት መልካም ነገር እንዲፈጠር ልዩ ጥንቃቄ በተሞላ መልኩ ድምዳሜ የሚሰጡ እና በአካባቢው የተረጋጋ ሁኔታ እንዲፈጠር የሚያደርጉ መሆናቸውን ያስረዳሉ። እነዚህ አካላት ፍቅርን የሚያለመልሙ፤ ዘላቂ የሕይወት ተሃድሶን የሚያመጡ ፤ ከጥፋትና ከመጠፋፋት የራቀና ይቅር ባይነትን ባህል ያደረገ ማህበረሰብን የሚፈጥሩ እንደሆኑ የሚታመን መሆኑን ያመለክታሉ። አመዛዝነው ጥልቀት ያለው ውሳኔ የሚሰጡ ግለሰቦች ሰስለመሆናቸውም ይጠቅሳሉ፡፡
እንደእርሳቸው ማብራሪያ፤ ሽማግሌዎች የራጋኖን ውሳኔን በመያዝ በሟች ቤተሰብ ውስጥ ይሰበሰባሉ፤ በውሳኔውና በቀጣይ ሊሆን በሚገባው ጉዳይ ላይ ይመክራሉ፡፡ በዚያ ጊዜ ግን የገዳይ ቤተሰብ አይገኙም። በመቀጠልም ጉዳዩን ለማቀዝቀዝ በመጀመሪያ ፀሎት ይደረግና ቤት ውስጥ እሳት እንዲነድ በማድረግ የዚያን ቤተሰብ ሴት ልጅ በውሃ ታጠፋዋለች፡፡ ቀጥለው ወንዝ በመሄድ የገዳይ ቤተሰብ ከሽማግሌዎች ጋር በአንድ አካባቢ ይሆናሉ፤ የሟች ቤተሰብ ግን ከእነሱ ሽማግሌዎች ጋር በመሆን ቀድመው መገኘት ይጠበቅባቸዋል፡፡
በእለቱ የገዳይ ቤተሰብ ለዚህ ፕሮግራም የሚውል ጥቁር በግ፤ ነጭ ሻማ ፤ ገንዘብ የማዘጋጀት ሃላፊነት ያለባቸው መሆኑን የሚናገሩት መምህር ግርማ፤ ‹‹ገዳይና የሟች ቤተሰብ ወንዝ ውስጥ ገብተው እርስ በርስ ውሃ በመረጫጨት ይተታጠባሉ፡፡ ከእንግዲህ ነገሩ በዚህ ያብቃ ተብሎ ይመራረቃሉ›› ይላሉ፡፡ መጨረሻም ጥቁር በግ ይታረድና የበጉ አንጀት ሁለቱም እንዲይዙ ተደርጎ በመሃል ላይ ሸክላ ሰሪ የሆኑ ሴቶች ማርና ቅቤ በመያዝ ገብተው አንጀቱን የሚቆርጡበት ሥርዓት የሚከናወን መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ይህም በሁለቱ ወገኖች መካከል የፍቅር ቃልኪዳን እንጂ የመገዳደል ታሪክ አይኖርም የሚል ትርጓሜ ያለው ሲሆን ፤ የዚህ ጥቁር በግ ደም እንደፈሰሰ በደላቸውም እዲሁ ይፈስስ የሚል አመለካከት ያለው እንደሆነ ያብራራሉ፡፡
የገዳይ ቤተሰብ ከወንዙ ታጥበው እንደወጡ አዲስና ነጭ ኩታ (ጋቢ) ለሟች ቤተሰብ የሚያለብሱበት ሥርዓት መኖሩንም መምህር ግርማ ይናገራሉ፡፡ ከዚህም ባሻገር የገዳይ ቤተሰቦች ከነሽማግሌዎቻቸው ጋር በመሆን በቀጥታ ወደ ሟች ቤተሰብ ጋር በመሄድ ትልቅ ነጭ ሰንጋ የሚያርዱ መሆኑን፤ ከዚያ በፊትም ሴቶቹ ጤሪራ (በቂቤ የተዋሃደ የገብስ ቡና) ተዘጋጅቶ ሁለቱን ቤተሰቦች የሚመርቁበት ሥርዓት የሚካሄድ መሆኑንም ይጠቅሳሉ። ሴቶች ደግሞ ሻሜታና ቂቤ አምጥተው በሬው ላይ እንዲቀባ ያቀርባሉ፤ የበሬው ሻኛ ላይ ቂቤ ይደረግና ‹‹የእናንተ ነገር ይቀጥል ፤ ክፉ ነገር እንደዚህ ሻሜታ ይደፋ›› በማለት ተመራርቀው፤ ያንን ሰንጋ አርደው እየበሉ የሚያነጉበት ሂደት መኖሩን ያስገነዝባሉ፡፡
‹‹በዚህ ሥርዓት በጣም አስደናቂው ነገር ገዳይ የሆነው ሰው ከሟች አባት ጋር አንድ ቡሉኮ ለብሰው አብረው ተቃቅፈው ማደራቸው ነው›› የሚሉት ጥናት አድራጊው፤ ከዚያ በኋላ በመሃላቸው የሚኖረው የአባትና የልጅ ግንኙነት መሆኑን ያነሳሉ፡፡ በተጨማሪም በሁለቱ ቤሰቦች መካከል ቃል ኪዳን የሚታሰር መሆኑን ጠቁመው፤ ‹‹ይህም ቃል ኪዳን እርስ በርስ ላለመዋሸት፤ ላለመሰራረቅ፤ በሃሰት ላመስከር ሲሆን የሚኖራቸውም ግኑኝነት የአባትና የልጅ ስለመሆኑ ከፍተኛ ጥንቃቄ ነው የሚያደርጉት›› ይላሉ፡፡
ዝምድናቸው የቱንም ያህል ቢጠናከር ግን በመካከላቸው ጋብቻ ፈፅሞ የተከለከለ መሆኑን ይናራሉ። ከጋብቻ ውጪ ግን ዝምድናቸው እስከለተሞታቸው የሚቀጥል መሆኑን አንስተው፤ ‹‹ የሟችን ቤተሰብ ይጦራል፤ ያርሳል፤ ሴት ልጆቻቸው ደግሞ እንሰት ይፍቃሉ፤ ህፃናት ልጆቻውም የገዳዩን ቤተሰብ ከብት ይጠብቃሉ›› በማለት ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም በዓል ሲኖር የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ በማሟላት እና ስጦታ በመስጠት ግኑኙነታቸው ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም ነው ያብራሩት፡፡
የ’ጢግ-ጉላ’ ሥርዓት አሁንም ድረስ በሃድያ ሕዝብ ከትውልድ ትውልድ የተሻገረ መምጣቱን፤ ይህም ሥርዓት በመኖሩ በቀልና መጠፋፋት እንዳይኖር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ የተፈፀመው እርቅ ዘላለማዊና የማይፈርስ ፤ ሌላ ግድያ የማያስከትል በመሆኑ የህብረተሰቡ መካከል ፍትህና ፍቅር እንዲሰፍን በማድረግ ረገድ እየተጫወተ ያለው ሚና በቀላሉ የሚታይ እንዳልሆነ ያመለክታሉ፡፡
እንደእርሳቸው ማብራሪያ፤ ይህ ሥርዓት በሃድያ ሕዝብ ትውልዱ እየጨመረና እያደገ በመምጣቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ እየተጠናከረ መጥቷል፡፡ ግጭት አሁንም ድረስ ይፈጠራል በሕግ አግባብ ፍርድ ጨርሶ ቢወጣም እንኳን ሌላ በደል ወይም በቀል ይፈፀማል፤ ሌላ ደም ያስከትላል ተብሎ ስለሚፈራ ጉዳዩ በሽማግሌዎች ምርቃት እንዲጠናቀቅ ይደረጋል፡፡ የታሰረውም ሰው ቢሆን ይህንን ሥርዓት ሳይፈፅም ማህበረሰቡን ሊቀላቀል አይችልም፡፡ በመሆኑም የፍትህ ሥርዓቱን የሥራ ጫና በማቃለል ረገድ ያለው ፋይዳ እንዲሆም የሀገር ሰላምን በማጠናከር ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያለው በመሆኑ ተጠናክሮና ተጠብቆ የሚቆይበት ሁኔታ ሊመቻች ይገባል፡፡
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን መጋቢት 22 ቀን 2015 ኣ.ም