በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ የሴት ሙዚቀኞች ተሳትፎ፤ ከድምጻዊነት ተሻግሮ፣ በሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋችነት እና በሙዚቃ አቀናባሪነት እንዲያም ሲል፣ በሙዚቃ ቀማሪነት ደረጃ የደረሰች ማግኘት አደጋች ነው።አንዲት ሴት ግን ይህን ሁሉ ተሻግራ ታሪክ ጽፈዋል።እማሆይ ጽጌ ማርያም ገብሩ።እኒህ ሴት በክላሲካል ሙዚቃ ዘርፍ በብቸኛ የሙዚቃ ቀማሪነት እና ፒያኒስትነት ጉልህ ቦታ ይዘዋል።የፒያኖዋ ንግሥት በመባልም ይታወቃሉ። የሙዚቃ ሥራዎቻቸው በኢትዮጵያውያን እና በሌሎችም ዘንድ ተወዳጅ እና ተደማጭ ለመሆን ችሏል።
በድንቅ የፒያኖ የሙዚቃ ሥራዎቻቸው የሚታ ወቁት እኚህ ድንቅ የሙዚቃ አቀናባሪ ከትናንት በስቲያ የማረፋቸው ዜና ተሰምቷል። በዛሬው የባለውለታዎቻችን አምድም የፒያኖዋ እሜት እንዲሁም የፒያኖዋ ንግስት እየተባሉ የሚወደሱትን እማሆይ ፅጌ ማርያም ገብሩን በእንዲህ መልኩ ሊዘክራቸው ወዷል።
እማሆይ ጽጌማርያም በምንኩስና ወደ መንፈሳ ዊው ሕይወት ከመግባታቸው በፊት ቤተሰቦቻቸው የውብዳር የሚል ስም ነበር የሰጧቸው። ታኅሣሥ 4 ቀን 1915 ዓ.ም. አዲስ አበባ የተወለዱት እማሆይ ፅጌ ገና የስድስት ዓመት ሕጻን ሳሉ ከታላቅ እህታቸው ከሥንዱ ገብሩ ጋር ወደ ስዊትዘርላንድ ሔደው “ሞንት ሚራል” በተባለ አካዳሚ ትምህርት ይጀምራሉ።በትምህርት ቤቱ ውስጥ ከቀለም ትምህርቱ በተጓዳኝ ቫየሊን እና ፒያኖ አጥንተዋል።
ወንድማቸው ኮለኔል ዳዊት ገብሩ “ከንቲባ ገብሩ የኢትዮጵያ ባለውለታ” ባሉት መጽሐፋቸው ላይ፤ የእማሆይን የልጅነት ትዝታ ከራሳቸው ከእማሆይ ማስታወሻ ወስደው እንዲህ ሲሉ አስፍረውታል።“በዚያው በሰባት እና በስምንት ዓመት ዕድሜዬ አካባቢ ከሥነ ፍጥረት ጋር ወዳጅነት ነበረኝ።አበቦች ውብ ልዕልቶች፣ ዛፎች… እንደ ዘበኞቻቸው፣ ነፋስ… ወጣት መልዕክተኛ፣ ፀሐይ…ደግሞ የዓለም ሁሉ ንግሥት ሆነው ይታዩኝ ነበር።ያን ጊዜ በአዳሪ ትምህርት ቤቱ ውስጥ በኔ ዕድሜ ልጅ ስላልነበረ አዳሪ ትምህርት ቤት ውስጥ ብቸኝነት የሕጻንነት ጓደኛዬ ኾኖ አብሮኝ አደገ።ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አንድ የኀዘን ስሜት፣ የመንፈስ ዕረፍት እጦት አደረብኝ።
ሙዚቃ እወድ ነበርና ስሰማው የኀዘን ስሜት ያመጣብኝ ነበር።ለገና ሥጦታ ለገና አባት ደብዳቤ ጽፌ፤ ቫየሊን ጠይቄ ሲሰጠኝ ወዲያው አስተማሪ ተመድቦልኝ መማር ጀመርኩ።የአስተዳዳሪው ዘመድ የሆነች ልጅ ፒያኖ ስትጫወት እየተመለከትኩ እኔም እየተፍጨረጨርኩ መምታት እንደቻልኩ የመጀመሪያ ሙዚቃዬን ጀመርኩ።ስሙን ሲጠይቁኝ `The storm` ነው አልኳቸው። “ማዕበል” ለማለት።ቫየሊኑን ተወት አድርጌ ወደ ፒያኖ በማድላት ብዙውን ጊዜ ፒያኖን ነበር የማጠናና የምጫወተው” ይላሉ እማሆይ በማስታወሻቸው፡፡
እማሆይ ጽጌማርያም ምንኩስናን ከመቀበላቸው በፊት ስማቸው የውብዳር ገብሩ ነበር።የውብዳር ገብሩ 11 ዓመት ሲሆናቸው፣ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ። በዚህ ጊዜ ጣሊያን ኢትዮጵያን ወራ ነበር።ከንቲባ ገብሩም መላ ቤተሰባቸውን ይዘው ወደ ጎሬ ለመሠደድ ተገደዱ። የእህቶቻቸው እና የእርሳቸው ትምህርት ተቋርጦ ከደስታ ገብሩ እና ከገነት ገብሩ ጋር በስደት ቆይተዋል። እንደ ወንድማቸው እንደ ዳዊት ገብሩ ገለጻ፤ ከቤተሰቦቻቸው ጋር በእስር ወደ ጣሊያን ተወስደው ነበር። እዚያም በእስር ላይ እንዳሉ ወንድሞቻቸው በጥይት ተደብድበው ስለተገደሉ፤ “ይህ ሁሉ የባሰውን የመንፈስ ጸጥታዬን እያጠፋው ይሔድ ነበር” እንዳሉ ጽፈውላቸዋል።
የሙዚቃ ፍቅራቸው እጅግ ጠሊቅ እንደነበር በግል ማስታወሻቸው በርካታ ቦታዎች ላይ ተጠቅሷል። እማሆይ ጽጌ ማርያም የጽሕፈት መኪና መምታም ተምረው ስለነበረ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለጥቂት ጊዜ በጸሐፊነት ሠርተዋል።ሙዚቃን በከፍተኛ ደረጃ
ለመማር ቁርጥ ውሳኔ ላይ የደረሱት ከዚህ ጊዜ በኋላ ነበር። ይህን ውሳኔያቸውን በማስታወሻቸው እንዲህ ሲሉ አስፍረውታል።“እንደገና አባባን አስቸግሬ፤ ጃንሆይን እንዲለምኑልኝ አስደርጌ ወደ ውጭ ሀገር ሔጄ የሙዚቃ ትምህርቴን እንድቀጥል ተፈቅዶልኝ ወደ ካይሮ ሔድኩኝ። ትካዜ እንደ ጓደኛ አይለየኝም ነበር።ብዙ የፍቅር መጻሕፍትን ስለማነብ ስለ ሰው ልጅ ጥሩ አስተሳሰብ አልነበረኝም። ሰው አታላይ ነው፣ ውሽታም ነው በማለት ሰውን እምብዛም አላምንም ነበር” ይላሉ።
ለከፍተኛ የሙዚቃ ትምህርት ወደ ግብጽ ሔደው “ቬሉኑስ ኮንሰርቫቶሪ ኦፍ ሉቺኒያ” በተባለው የሙዚቃ ትምህርት ቤት አሌክሳንደር ኮንትሮቪች በተባለ ፖላንዳዊ የሙዚቃ መምህር ሥር ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። አሌክሳንደር ኮንትሮቪች በኋላ ላይ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ፤ በዐፄ ኃይለ ሥላሴ ትዕዛዝ የክብር ዘበኛ ሙዚቃን አደራጅቶ፤ በ1948 ዓ.ም የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ኦርኬስትራ ሙዚቀኞች በመምራት ከፍተኛ አስተዋጽዖ የነበረው የሙዚቃ ባለሙያ ነበር። እማሆይ ከትምህርታቸው በኋላ ወደ ሀገራቸው ተመልሰው የሙዚቃ ቅማሬዎቻቸውን ማዘጋጀት ጀመሩ። ወንድማቸው ኮነሬል ዳዊት ገብሩ “በዚህ ጊዜ ውስጥ” በማለት ይናገራሉ።
በዚህ ጊዜ ውስጥ ከዕለታት አንድ ቀን የንጉሣዊ ቤተሰብ የሆኑ አንድ ሰው ለሁለት ዓመት ትምህርት ወደ እንግሊዝ እንድትሔድ የቅድሞሽ ቢከፍሉላትም፣ የይለፍ ወረቀቱን ሁሉ ይዛ ሳለ፣ ‘ከበላይ የመጨረሻ ፈቃድ አልተገኘም’ ተብላ ቀረች። ይህ ልክ በእኔ የደረሰብኝ ዓይነት ነው፤” ይላሉ ኮነሬል ዳዊት ገብሩ በመጽሐፋቸው። “አባቴ በ1922 ዓ.ም ለትምህርት ወደ ጀርመን ሊልኩኝ ቢያስቡም፤ የትምህርት ሚኒስትሩ ሳህሌ ጸዳሉ ተመሳሳይ ዕግድ በማድረግ የትምህርት እድሌን አጨናግፈውብኛል። እኔ ብዙ ስላየሁ ቻልኩት እህቴ ግን አልቻለችውም” በማለት አጋጣሚውን በኀዘን ይገልፁታል።
ከዚህ በኋላ የወጣቷ፣ በሙዚቃ ብዙ የመግፋት ጉጉት የነበራት የየውብዳር ገብሩ የሕይወት መስመር ሌላ አቅጣጫ ያዘ። የዚህ ዕድል መሰናከል ምን እንዳስከተለ የእማሆይ ማስታወሻ እንዲህ ይገልፀዋል። “የመጨረሻ ዕድሌ በመሰበሩ፣ መንፈሴ ተሰባብሮ፣ ሞትን ብቻ ፈለግሁ።ከ15 ቀን በላይ እህል ውሃ ሳልቀምስ ጥቁር ባዶ ቡና ብቻ እየጠጣሁ ስሰነብት፤ ያው የሞት ጥላ በላዬ ላይ ሲያንዣብብ፣ የመጨረሻ ቁርባን እንዲሰጠኝ ጠይቄ አንድ ቄስ እስከነበርኩበት ምስካየ ኀዙናን መድኀኔ ዓለም አጠገብ ከነበረው ሆስፒታል ድረስ መጥተው አቆረቡኝ። የዚህ ዓለም ፍቅር እና የመኖር ፍላጎት ከህሊናዬ ፈጽሞ ተወገደ” ይላሉ፡፡
በቤተሰቦቻቸው ርብርብ ሕይወታቸው ተርፎ ጥቂት የተጽናኑት እማሆይ፤ ቤተሰቦቻቸውን አዘናግተው ወደ ግሼን ደብረከርቤ ተጓዙ። “ለሁለት ዓመታት አንድ ቀን ሳይቋረጥብኝ ሰዓታቱንም፣ ቅዳሴውንም ሥራውንም ከዘለቅሁት በኋላ ቆረጠልኝ። የሁለት ወር ፈቃድ እና ደመወዝ ይዤ ከአንድ ዓመት በፊት ከእናቴ ከወ/ሮ ካሣዬ ጋር ሔጄበት ወደነበረው ወደ ግሼን ማርያም ተጓዝኩ። ወደዚያ ስሔድ ግን ነፋስ መለወጥ አለብኝ ብዬ አባባን እና እናቴን አስፈቅጄ ነው። እነርሱ ምንም አልጠረጠሩም ነበረና ለሽርሽር የምሄድ መስሏቸው ፈቀዱልኝ” በማለት ይናገራሉ። ከዚያም ለግሼኑ አቡነ ሚካኤል መመንኮስ እንደሚፈልጉ ይነግሯቸዋል። “ዘመዶችሽ በኋላ መጥተው ቢያስቸግሩስ?” ቢሏቸው፤ “በነፍሴ የሚያዝባት ሰው ካለ እኔ ሌላ የለም” ስላሉዋቸው ምንኩስናው ተፈቀደላቸው፡፡
ከምንኩስናው በፊት በጸጉር የመላጨቱ ሥነ ሥርዓት ወቅት የተከሰተው ነገር እዚህ ላይ ሳይጠቀስ አይታለፍም። “ከእንክብካቤ እቅፍ ውስጥ ወጥቶ ተሞነጫጭሮ ትከሻዬ ላይ የተዘረገፈውን ፀጉሬን አይተው አቡነ ሚካኤል ‘ይህ ጠጉር ደግሞ መላጨት አለበት’ አሉኝ። ቀጠል አድርጌ ኧረ እርሱስ ግድ የለም አልኳቸውና አባ ደሳለኝ የሚባሉትን የደሴ ግቢ መርቆርዮስ አስተዳዳሪ እንዲላጩኝ ጠየቅኳቸው። አባ ደሳለኝ ሲላጩኝ እጃቸው ለብዙ ጊዜ ሲያርፍ ‘ምን ኾነው ነው?’ ብዬ ዘወር ብዬ ሳያቸው፤ ዕንባ አውጥተው ሲያለቅሱ አየሁና ‘ምነው አባቴ ምን ሆኑ?’ ብላቸው፤ ‘አባቴ እንኳን ሲሞት አላለቀስኩም፣ እንዲያው አዝኜ ነው’ አሉኝ። እኔም ‘ምን ለፀጉሩ ነው ይህንን ያህል የሚያዝኑት’ ብዬ ቀለድኩባቸው።እንኳንስ ፀጉር ሌላም በነበረኝ ለጌታዬ የምሰጠው አልኳቸው፡፡” ይላሉ። በዚህ ዕለት ማግስት የምንኩስና ሥርዓቱ ተፈጸመላቸው። ይህ ሲሆን ዕድሜያቸው 20ዎቹ መጀመሪያ ላይ ነበር፡፡
በወጣትነታቸው በወሰኑት በዚህ የምንኩስና ሕይወት አባታቸው እና እናታቸው ከፍተኛ ኀዘን ላይ ወደቁ። ብዙም አልቆዩ፤ እማሆይ በመነኮሱ በሁለት ዓመታቸው አባታቸው ከንቲባ ገብሩ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። ከዚያ በኋላ እማሆይ ሙሉ ጊዜያቸውን ለሙዚቃ ቅማሬ እና ለመንፈሳዊው ግልጋሎት ብቻ ወሰኑ። የመጀመሪያ ቅማሬያቸውን ለማስቀረጽ ወሰኑ። የዚህ ሙዚቃ የማስቀረጹ ውሳኔ፤ የራሱ የሆነ ምክንያት ነበረው። “ቅማሬዬን በሸክላ ለማስቀረጽ ያነሳሳኝ ዐቢይ ምክንያት ነበር።ጎንደር በነበርኩበት ጊዜ በየቤተክርስቲያኑ የማይጠገበውን ማኅሌት ሰምቼ ስመለስ፤ እደጅ የአገር ቤት ተማሪዎች በየሜዳው ጥቅልል ብለው ተኝተው አያለሁ። ብጠይቅ ሌሊት ቤተክስቲያን ያደሩ ናቸው፣ ጥግና ቤት የሌላቸው። በዚህም ልቤ ተነካ፣ አዘንኩ። እኔ ሀብት የለኝ፤ ያለችኝ ያቺው ሙዚቃዬ። ስለዚህ እስኪ ሙዚቃዬን ላስቀርጽ እና ሽያጩን እነዚህ ልጆች ገብተው በነጻ የሚያድሩበት ቤት ላቋቁም አልኩ። መከረኞቹም አሉ ሸክላውም ተቀረጸ። ነገር ግን ተንኮለኛ አይጠፋምና ለሽያጭ ከመቅረቡ በፊት እንጉሡ ጆሮ ስለ ደረሰ ሐሳቡ መና ቀረ መሞከሬ ግን አልቀረም” ይላሉ፡፡
ይህንን በመሰለ “እርሳቸው ያልተረጋጋ” በሚሉት ሕይወት እስከ 1975 ዓ.ም ከቆዩ በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ሔዱ።እማሆይ በደብረ ገነት ኪዳነ ምሕረት ከሦስት አሥርት ዓመታት በላይ ኖረዋል።ላለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት ስላሉበት ሁኔታ ምንም ዓይነት አዲስ ዜና ተሰምቶ ስለማይታወቅ በሕይወት መኖራቸውን የተጠራጠሩ ብዙዎች ነበሩ።ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን፣ ሥራዎቻቸው የታላቅ ሙዚቀኞችን ቀልብ መሳብ ጀመረ።በወጣትነታቸው ብዙ መሥዋዕትነት የከፈሉለት፣ ማንም ልብ ሳይለው የዘሩት የረቂቅ ሙዚቃ የቅማሬ ዘር፤ ዛሬ ላይ ብዙዎች እርሳቸውን ብለው፣ የእርሳቸውን ሙዚቃ እንዲያጠኑ እያደረገ ነው፡፡
የዓለም ታላላቅ የዜና አውታሮችም ከ እ.ኤ.አ 2013 ዓ.ም ጀምሮ ስለ እማሆይ ሙዚቃዎች አዳዲስ ነገሮችን ማቅረብ ጀምረዋል።በ2013ቱ የኢየሩሳሌም የባህል ክብረ በዓል ከተከናወኑ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ በእማሆይ ሕይወት ታሪክ እና የሙዚቃ ሥራዎች ዙሪያ ያተኮሩ ተግባራት ነበሩ።ባለሁለት ጥራዝ መጻሕፍትን በእማሆይ የሕይወት እና የሙዚቃ ሥራዎች ላይ መታተም ችለዋል።የሙዚቃ ሥራዎቻቸውን በኖታ የያዘ ባለ 146 ገጽ መጽሐፍም ታትሟል።እንደ ናዳቭ ሀርፐር ያሉ የእስራኤል ታላላቅ ሙዚቀኞች ስለ እማሆይ ሥራዎች ጥልቀት ምስክርነት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡
በወጣትነት ዕድሜ የተሠራ የአስተውሎት ሥራ የኋላ ኋላ የራሱ ትንሣኤ ይኖረዋል።የእማሆይ ጽጌ ማርያም ሕይወት በሙዚቃ በብዙ ተፈትነዋል። ከመንፈሳዊ ሕይታቸው ጋር የሚቃረን የሚመስላቸው አንዳንዶች፣ ሙያቸውን እና የሙዚቃ ፍቅራቸውን አጣጥለውባቸዋል። የሕይወታቸውን አቅጣጫ ፍጹም በማይገመት መንገድ እንዲጓዝ ያደረገም ነው። ከሀገራቸው አሰድዶ በሌላ ሀገር ተነጥለው እንዲኖሩ ያደረገ ነው።ግን ከዚህ ሁሉ በኋላ የስማቸውን ትንሣኤ ዕድለኛ ሆነው፣ ከዘጠኝ አሥርት ዓመታት በኋላ በታላቅ ክብር ከብዙዎች ብድራቱን አግኝተውበታል። በቀድሞው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቴአትር ቤት ከንጉሠ ነገሥቱ ብቻ በቀር ማንም በትዕግሥት ሊያዳምጠው ያልቻለው ኮንሠርታቸው፤ ሐምሌ 23 ቀን 2013 ዓ.ም. ሥራዎቻቸውን በሚጫወቱ ወጣቶች አማካኝነት ከ1ሺ 800 በላይ ታዳሚያን በተገኙበት በአድናቆት ተመልካች አግኝቷል።ገና ያልተደመጡት አዳዲሶቹ ስድስት ክላሲካል ቅማሬዎቻቸው ያላቸው መሆኑን ከአዲስ ስታንዳር መፅሔት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ቢቢሲ በዘገባው የእማሆይ ጽጌማርያም ገብሩ ህልፈትን ተከትሎ በያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ውስጥ “ዝክረ እማሆይ ጽጌማርያም ገብሩ” የተሰኘ የመታሰቢያ መረሃ ግብር በቀጣዩ 15 ቀናት ውስጥ እንደሚዘጋጅ መምህር ዕዝራ አባተ መግለጻቸውን አስታውቋል። በዚህ የመታሰቢያ መረሃ ግብር ላይ “በተቻለ መጠን እማሆይን ጽጌማሪያም የሚያስታውስ መሰናዶ በያሬድ ሙዚቃ ትምህር ቤት ይከናወናል” ብለዋል መምህሩ። ይህ መሰናዶ “ወጣቶች እንዲያስታውሷቸው” ያለመ እንደሆነ ዕዝራ ተናግረዋል።
አያይዘው እንደገለጹት የመሰናዶው ዋነኛ ይዘት የእማሆይ ጽጌማርያም ሙዚቃዊ አበርክቶ ይሆናል። በዋነኛነት ትምህርታዊ አበርክቷቸው ላይ የሚያተኩር ይሆናል። በኢትዮጵያ ሙዚቃ ያላቸውን አስተዋጽኦም ይዳስሳል። በዚህ የመታሰቢያ መረሃ ግብር ላይ ሙዚቀኞች እንዲሁም መምህራን ይሳተፉበታል ተብሎ ይጠበቃል።
ብቻቸውን በምንኩስና የኖሩ ጥቁር እና ነጭ ለብሰው ፒያኖ ከጎናቸው አድርገው በሙዚቃ አጨዋወታቸው የኢትዮጵያን የሙዚቃ ስልት ረጅም መንገድ ያስጓዙ፣ ለዓለም እንደ ቤቶቨን ያስተዋወቁ እኚህ እናት የማይደገም አሻራን ያስተላለፉ ድንቅ ሙዚቃ አቀናባሪ ከዚህ ዓለም ድካም ቢያርፉም ጣፋጭ ቃና ያላቸው ለስልላሳ ሙዚቃዎቻቸው ትተውልን አልፈዋል።በመሆኑም በምድር ቆይታቸው ባኖሩዋቸው ረቂቅ የጥበብ ስራዎቻቸው እስከ ወዲያኛው ሲዘከሩ ይኖራሉ።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን መጋቢት 20/2015