
ባንኮች ውድቀት እየገጠማቸው ባለበት ጊዜ የአሜሪካ ማዕከላዊ ባንክ በድጋሚ የወለድ ምጣኔን ጨምሯል። ይህንን እርምጃ መውሰድ የፋይናንስ አለመረጋጋትን ይፈጥራል ከሚለው ስጋት በተቃራኒ ባንኩ እዚህ ውሳኔ ላይ መድረሱ ታውቋል። ማዕከላዊ ባንኩ የባንክ ሥርዓቱ ጠንካራና ችግርን መቋቋም የሚችል ነው የሚል ምክንያት በማስቀመጥ የወለድ ምጣኔውን በ0 ነጥብ 25 በመቶ ከፍ አድርጓል።
ባንኮች እያጋጠማቸው ባለው ኪሳራ ምክንያት በመጪዎቹ ወራት የኢኮኖሚ ዕድገቱን ሊጎዳው እንደሚችልም አስቀምጧል። ማዕከላዊ ባንኩ ዋጋን ለማረጋጋት የብድር ክፍያን እያሳደገ ነው። ሆኖም ከባለፈው ዓመት ወዲህ እየተደረገ ያለው ቀጥተኛ የወለድ ምጣኔ ጭማሪ የባንክ ሥርዓቱ ላይ ጫና አሳድሯል። በዚህም ሳቢያ ሲልከን ቫሊ እና ሲግኒቸር የተባሉ የአሜሪካ ባንኮች ከፍተኛ የወለድ ምጣኔ ባስከተለው ችግር ምክንያት በዚህ ወር ኪሳራ አጋጥሟቸዋል።
የወለድ ምጣኔ መጨመሩ በባንኮች ያሏቸው ቦንዶች ዋጋ እንዲወርድ ሊያደረግ ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል። ባንኮች ከፍተኛ መጠን ያለው ቦንድ ስለሚይዙ ከፍ ያለ ኪሳራ ላይ የመውደቅ እድል አላቸው። ባንኮች የያያዟቸውን ቦንዶች ለመሸጥ እስካልተገደዱ ድረስ የቦንድ ዋጋ መውረድ በራሱ ችግር አይደለም።
የወለድ ምጣኔ መጨመሩ በሰፊው የፋይናንስ እንቅስቃሴ ላይ አለመረጋጋትን አያመጣም ብለው የሚያስቡ የበርካታ ሀገራት መሪዎች አሉ። እንደነሱ እምነት ጭማሪው የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር የሚደረገው ጥረት ላይም ተጽዕኖ የለውም። ባለፈው ሳምንት የአውሮፓ ማዕከላዊ ባንክ የወለድ ምጣኔውን በ0 ነጥብ 5 በመቶ ጨምሯል።
የእንግሊዝ ባንክም የዋጋ ግሽበቱ ከባለፈው ወር በ10 ነጥብ 4 በመቶ ባልተጠበቀ ሀኔታ መጨመሩ በተሰማ ማግስት የወለድ ምጣኔ ላይ የሚደረግ ጭማሪን ይፋ ያደርጋል። የአሜሪካ መጠባበቂያ ጽሕፈት ቤት ሊቀ መንበር ጄሮሜ ፖል መሥሪያ ቤታቸው የዋጋ ንረትን መዋጋት ላይ እንደሚያተኩር ገልጸዋል። ሲልከን ቫሊ ያጋጠመወን ችግር ጠንካራ በሆነ የባንክ ሥርዓት ውስጥ የተከሰተ ልዩ ሁኔታ ሲሉ ገልጸውታል።
ሆኖም አሁን ባንኮች ላይ ያጋጠመው ችግር ግን የኢኮኖሚውን እድገት እንደሚጎትት ገልጸዋል። ችግሩ የሚያስከትለው ተጽዕኖ ሙሉ መልክ ግን እስካሁን ግልጽ አለመሆኑን የቢቢሲ ዘገባ አስታውቋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 15/2015