ቁጭ ብያለሁ እየጻፍኩና እያነበብኩ። አያቴ እንደወትሮዋ ለምስራቅ በር ደረቷን ሰጥታ ውጭ አጎዛዋ ላይ ተሰይማለች። አያቴ ውጭ ናት ማለት ፊቷ ላይ ስጥ አለ ማለት ነው..እና ደግሞ ረጅም ሸምበቆ። ከዚህ አለፍ ካለ መቁጠሪያ ብትይዝ ነው። ቀን ሙሉ አልጋዋ ላይ ውላ ጀምበር ወደ ምዕራብ ስታሽቆለቁል አጎዛዋን ይዛ ወደ ደጅ ትወጣለች። የዛን የበግ ይሁን የፍየል የማላውቀውን ገጣባ አጎዛ ከበሩ ደጃፍ በግራ በኩል ካለው ከፍታ ላይ ታደላድልና ትቀመጣለች። ከዛም ዛሬም ድረስ ወዳልደረስኩበት የሀሳብ ባህር ውስጥ ትዘፈቃለች። ስታስብ በጽሞናና ድምጽ አውጥታ ነው። የማይሰሙ ድምጾችን ለራሷ እያወጣች በለሆሳስ ስታጉረመርም ሰምቻት አውቃለሁ። ከሀሳቧ መልስ ማረፊያዋ ብዙ ነው..ከማረፊያዎቿ አንዱ እኔ ነኝ።
‹ፍሰሀ..አንተ ፍሰሀ? ትለኛለች ከሄደችበት የሀሳብ አርምሞ ነፍስ ዘርታ።
‹አቤት! እላለሁ መጽሀፌ ላይ እንዳቀረቀርኩ።
‹ና እስኪ ጀርባዬን እከክልኝ..ማከኪያዬን አጣኋት› ትለኛለች ረጅሙን ሸምበቆ መሬት ላይ እያንደፋደፈች።
የማነበውን መጽሀፍ የቆምኩበት እንዲታወሰኝ ገጹን አጥፌ ወደ ውጭ እወጣለሁ። ‹የቱ ጋ ነው? እላታለሁ የበላትን ቦታ ፍለጋ ጀርባዋን በእጄ እየዳበስኩና በጥፍሬ እየቧጠጥኩ።
‹ዝቅ..ዝ..ዝቅ..ትትትንሽ ከፍ..እ..እእሱጋ› ትለኛለች ጀርባዋን ወዲያና ወዲህ እያስደነሰች..በፍለጋ እያገዘችኝ። አካታለሁ እንደ ጃርት እሾህ በሰላ ጥፍሬ። ሳካት ፊቷ ላይ የእፎይታ መንፈስ አያለሁ። ሳካት ፊቷ ላይ የህመም ስሜት አስተውላለሁ። ከብዙ ማከክ በኋላ ‹ኧረ ቀስ አሳመምከኝ› ትለኛለች ጀርባዋን ከጥፍሬ እያሸሸች። እሷን እያከኩ እኔ አስባለሁ..ከነፍስ መደሰቻዎች አንዱ የበላን ቦታ ፈልጎ ማግኘት ከዛም ማከክ ነው እላለሁ። እንደዛ ባይሆን ያን ሁሉ ደስታ በአያቴ ፊት ላይ አላየውም ነበር። ማከክ ነፍስን መኮርኮር ይመስለኛል..ልብን በሀሴት ማጥመቅ። ማከክ የነፍስን ራቁት ማልበስ ነው እላለሁ። የልብን ባዶነት መሙላት። አንዳንድ ጊዜ ግን ግራ ይገባኛል..የሌሎችን ባላውቅም እኔ ግን አንዳንድ ጊዜ የበላኝን ቦታ ፈልጌ አጥቼው አውቃለሁ። ሆነ የሰውነቴ ክፍል ላይ በልቶኝ ማከክ አሰኝቶኝ የበላኝ ቦታ ግን ይጠፋብኛል። በልጅነቴ ያን ቦታ ፈልጌ ለማግኘት ብዙ ጊዜ ለፍቻለሁ..እሱን ያገኘሁ እየመሰለኝ ያልበላኝን ብዙ ቦታ አክኬ አውቃለሁ።
በዚህ ሀሳብ ውስጥ ሆኜ ለካ ሳላውቀው በኃይል አክኬአት ነበር..በሰላ ጥፍሬ አዛውንት ገላዋን ቧጥጨው ነበር። ጀርባዋን ከጥፍሬ መንጭቃ እያላቀቀች ‹እከከኝ አልኩ እንጂ አቁስለኝ መች አልኩህ? ለራሱ ገላዬ ሳስቷል ያንተ ጥፍር ተጨምሮበት› ስትል ተማረረችብኝ።
ደሞ በሌላ ቀን አጠገቧ ተቀምጫለሁ..የጀመርኩትን የዶክተር አለማየሁ ዋሴን ‹እመጓ› የተሰኘን መጽሀፍ እያነበብኩ። ‹ቆይ ግን መጣፍ አይሰለችህም? ከጠዋት ጀምረህ እንዳቀረቀርክ ይመሽልሀል› ትለኛለች አዛውንት አይኖቿን ወደ እኔ ወርውራ።
‹አሁን እንኳን እያነበብኩ ነው› እመልስላታለሁ።
‹እሱስ ቢሆን ያደክም የለ?
‹ነፍስ የምትወደውን ስትከውን መታደስ እንጂ ድካም አይጎበኛትም። አእምሮ የሚወደውን ሲያስብና ሲሰራ ይበረታል እንጂ አይዝልም። እያደከሙን ያሉ ነገሮች የማንፈልጋቸው ናቸው። ለመኖር ስንል ሳንፈልግ የተጋፈጥናቸው እነሱ› ስል ላሳምናት እሞክራለሁ።
‹በል እንደዛ ከሆነ ደግ! እኔ እኮ እንዲሁ አቀርቅረህ ሳይህ ቢቸግረኝ ነው። ነገ አማኔል ነው አቅም ባገኝ ቤተክሲያን ስሜ ብመለስ ደስ ይለኛል..አታደርሰኝም?
‹አደርስሻለሁ..
‹ጎሽ ተባረክ! ትለኛለች።
አያቴ ከአማኑኤል ጋር ዘውድና ጎፈር ናት..መዳፍና አይበሉባ። ነፍስ እንደዛ ፈጣሪዋን ስታስብ፣ እንደዛ ለፈጣሪዋ ስትገዛ አያቴን ነው ያየሁት። ሳትጠራው ውላ አታውቅም፡ ጠዋት ከእንቅልፏ ስትነሳ ማታም ወደ መኝታዋ ስትሄድ እያነሳሳችው ነው። የአባት አማኔል የሀገሯ ታቦት ነው..የበቀለችበት፣ የጸደቀችበት፣ የጎመራችበት፣ ሰላሳና ስልሳ መቶም ያፈራችበት የሴትነቷ አልፋና ኦሜጋ።
ውጪ አጎዛዋን ተጋርቼ የባጥ የቆጡን እያወራን ጎን ለጎን ቁጭ ብለናል። እጄን አንገቴ ላይ አሳርፌ እየዳበስኩ ‹ጉሮሮዬን እያመመኝ ነው› እላታለሁ።
‹አ* ላይ ተፍተህ ነው..አ* ማረኝ በል› ትለኛለች።
በዚህ ጊዜ ወዳላባራው ጥያቄዬ እመለሳለሁ። ከዚህ በፊት ይሄን ነገር ብዙ ጊዜ ሰምቼዋለሁ። ለጥያቄዬ መልስ ግን አላገኘሁም። አ* ከአ*..ነት ባለፈ የሆነ ስልጣን የተቸረው መሰለኝ። እውነት ይሁን ውሸት ግን አላውቅም። አያቴ ከዘመናዊው ዓለም ይልቅ ለባህላዊው ዓለም ቅርብ ናት። በዚህና በመሳሰለው እሴቷ ዛሬ ላይ ሳስባቸው የሚያስገርሙኝን ብዙ ነገሮች ነግራኛለች። ለምሳሌ ማታ ቤት አይጠረግም ሲሳይ ይወስዳል። ማታ ጥፍር አይቆረጥም። ማታ ፉጨት አይፏጭም። በማታ መስተዋት አይታይም ብላኛለች።
ጉሮሮዬን እየዳበስኩ ‹አ* ምን ስልጣን ቢኖረው ነው ጉሮሮ የሚያመው? ነው ወይስ እኔ የማላውቀው ስውር ጥበብ አለው? እያልኩ ማሰብ ጀመርኩ። እውነት ለመናገር እንደ እኔ ለአ* እንክብካቤ የሚያደርግ አለ ብዬ አላስብም። ከሀሳቤ መልስ ‹ግን አ* ከጉሮሮ ጋር ምን አገናኝቶት ነው የሚያመው? ስል ጠየኳት።
‹እኔ ምን አውቄ! ግን እንደዛ ይባላል›።
‹እኔ ግን ምንም አልተዋጠልኝም…
‹አንተ እንግዲህ ሰው የነገረህን አትሰማ..በል እንዳሻህ› ስትል ለፍላጎቴ ትተወኛለች።
ደሞ በሌላ ቀን..ኳስ ስጫወት፣ ስዘል ብቻ በሆነ ምክንያት እግሬ ላይ በተፈጠረ ቁስል መራቢያ አካላቴ ጎን ታፋዬ ስር ህመም ይሰማኛል (በአያቴ አጠራር ንፍፊት ይባላል) እሱን ሰበብ አድርጎ እርምጃዬ ይደነቃቀፋል..ጓያ እንዳሽመደመደው አካል እሽመደመዳለሁ።
‹ምን ሆነህ ነው የምታነክሰው? ትለኛለች እዛው በሯ ደጃፍ ላይ አጎዛዋ ላይ ተቀምጣ..ከወትሮው የተለየ አረማመዴን እያጤነች።
የሆንኩትን እነግራታለሁ..ታፋዬ ስር ህመም እንደተፈጠረ።
‹ንፍፊት ነው! ምን አንተ አርፈህ አትቀመጥ..ስትንከወከው፣ ከኩሽናው ጣሪያ ላይ ሳር ምዘዝና በእሳት ለኩስና ሰባት ግዜ እርገጥበት ይተውሀል› ትለኛለች እብለት በሌለው ፍጹም እርግጠኝነት።
እንዳለችኝ አደርጋለሁ..ፈጣሪ ምስክሬ ነው ከዛ በኋላ ህመሙ ይለቀኛል። ግን ከጥያቄ አላመልጥም..የእኔ ህመም ከዛ ሳርና እሳት ጋር ምን አገናኘው ስል ውስጤን እሞግታለሁ። ከሁሉም በኋላ ሕይወት እምነት እንደሆነ ደረስኩበት። ለሚያምን ሁሉ ይቻለዋል አይደል የተባለው? የአያቴ ባህላዊ አተያይ በዘመናዊው ዓለም ተዓማኒነት እንደሌለው ምንም ማረጋገጫ የለኝም። እኛ ኢትዮጵያውያን ብዙ ባህላዊ ልማዶች አሉን። አይናችን ሲርገበገብ፣ መዳፋችንን ሲያሳክከን፣ ውስጥ እግራችንን ሲበላን፣ ምላሳችንን ስንነክስ፣ ስቅ ሲለን በዚህ ሁሉ ውስጥ የምናምነው እምነት አለ።
ኢትዮጵያ ማናት ላለኝ ባላገር ናት ስል እመልስለታለሁ። አዎ ኢትዮጵያ ባላገር ናት። ታሪኳ፣ ባህሏ፣ ስርዓቷ፣ ፖለቲካዋ፣ ኢኮኖሚዋ፣ ማህበራዊ መስተጋብሯ ሁሉ ከገጠር ወደ ከተማ፣ ከባህላዊ ወደ ዘመናዊ የዘመነ ነው። ከተማ ላይ ስለኖርን፣ ህንጻ ስላየን፣ ከመኪና ጋር ስለተጋፋን ዘመናዊ ነን ማለት አይደለም። ዘመናዊነት በታሪክ ምንጣፍ ላይ መራመድ ነው። የኋላን አለመርሳት ነው። ዘመናዊነት እንደ አያቴ ኢትዮጵያን ማፍቀር ነው። አራዳነት እንደ አያቴ በራስ ታሪክ ውስጥ፣ በራስ ባህል ውስጥ፣ በራስ ማንነት ውስጥ በቅሎ መጽደቅ ነው እያልኩ ብዙ አሰብኩ።
አያቴ ትገርመኛለች..ምንም ልሁን..ምንም ሆንኩ ልበላት መፍትሄ አታጣም። ጤናዳሙን፣ ዳማከሴውን፣ በሶብላውን፣ ግራዋውን፣ ግዛዋውን፣ ሬቱን፣ ባህር ዛፉን፣ ስራ ስሩን፣ ጣዝማ ማሩን፣ የቡዳ መድኃኒቱን፣ እምነቱን፣ ጸበሉን፣ ብቻ በአንዱ ፈውስን ታውቅበታለች። እግዜርን ናት..እንደ እግዜር ናት በእምነትና በኢትዮጵያዊነት ሞልታ የምትፈስ።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን መጋቢት 15/2015