ኢትዮጵያ መልክ አላት..ገነትን እንደሚከቡ አራቱ ወንዞች ዘላለማዊ ቁንጅናን የታጠቁ። የኢትዮጵያ መልኮች እግዚአብሔራዊ መልኮች ናቸው..በመስጠት የከበሩ። ስይጥንናን የማያውቁ ብርሃናማ መልኮች። እንዲህ ስታስብ የአያቷ ድምጽ ከውጪ ተሰማት።
‹እግዚኦ..እግዚኦ..
‹ምነው እማማ ተዋቡ? ጋሽ ቢራራ ጠየቁ።
‹ዘይት ዘጠኝ መቶ ብር ገዝቼ መምጣቴ ነው። በዘመኔ እንዲህ ዓይነት የኑሮ ውድነት አላየሁም። ሰው በሰው ተጨካክኖ የለም እንዴ?
‹ስግብግቦች በዙ። ድሀ አስጨንቀው ኪሳቸውን ለማደለብ የሚሮጡ ነጋዴዎች በረከቱ። ምርት ጠፍቶ እኮ አይደለም በአቋራጭ ለመበልጸግ የሚፈልጉ አንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎች የፈጠሩት ነው። የባሰ እንዳይመጣ መጸለይ ነው›።
‹ከዚህ በላይ ምን የባሰ ሊመጣ በሉ? እኔ የማውቃት ኢትዮጵያ እንዲህ አልነበረችም። በነጣ እየሰጠን፣ እየተቀበልን ቀን የወጣን ነበርን። እግዚኦ ነው..እግዚኦ..እግዚኦ።
‹ምርት የሚደብቁ ወንጀለኛ ነጋዴዎችን በመጠቆምና ለሕግ በማቅረብ ሕዝባችንን ከዚህ መከራ መታደግ አለብን። መንግሥት ብዙ ጥረት እያደረገ ነው እኛም እንደ ዜጋ እኚህን ሌቦች በማጋለጥ ከመንግሥት ጎን መቆም አለብን። እነሱ እስካሉ ድረስ ይሄ የኑሮ ውድነት እልባት አይኖረውም።
‹ሰው እንዴት በሰው እንዲህ ይጨክናል? ኢትዮጵያዊነት መልኩን ሲያጣ ያለዛሬ አላየሁም። የእኔ ኢትዮጵያ እንዲህ አልነበረችም..የልጆቼ ኢትዮጵያ እንዲህ መሆኗ ያሳዝናል። መስጠትን የመሰለ በረከት እኮ የለም። ድሀ አስጨንቆ የሚገኝ ትርፍ ርባና የለውም። ይዞ ነው የሚጠፋው። በሉ እስኪ ሰላም ይዋሉ..
እማማ ትዋቡ የገዙትን አምስት ሊትር ዘይት አራት ትናንሽ የሀይላንድ ፕላስቲክ ላይ ቀንሰው…›ነፃነት..አንቺ ነፃነት› ሲሉ ልጃቸውን ተጣሩ።
‹አቤት እማ? አለች ከውጪ ወደ ቤት እየገባች። እማ ነው የምትላቸው..እናትነትን ከአያትነት ጋር በአንድ ቀላቅለው የሰጧት እሳቸው ናቸው። እማ በዚህ ዓለም ያለ ድንቅ ስም ይመስላታል። ከዚህም በላይ ድንቅና ማራኪ ስም ቢኖር በዛ ትጠራቸው ነበር። ግን አላገኘችም። በአያትነት ውስጥ ከእናትነት የገዘፈ ሴትነት ያለ ይመስላታል። በሴትነት ውስጥ ዘመን የዋጀው ዕድሜ ጠገብ ሌላ ሴትነት ያለ ይመስላታል።
እማማ ተዋቡ ዘይት የነካ እጃቸውን ባደፈ ቀሚሳቸው እየጠረጉ ‹በይ አንዱን ለእትዬ በየነች፣ አንዱን ለጋሽ ፍሰሀ፣ የቀሩትን ደግሞ ለላቀችና ለእማሆይ ወይኗ ሰጥተሸ ነይ። እኔ ስካፈልና ሳካፍል ነው ያደኩት። ድሀ በችግር ተቆራምቶ ለብቻ የሚኖሩት ሕይወት በፈጣሪ ዘንድ ያስጠይቃል። ኢትዮጵያዊነት መልኩ ይሄ ነው…ካለ ላይ እየገመሱ ለሌለው መድረስ። በይ እንዳልኩሽ አደራዬን ፈጽመሽ ነይ›።
ነፃነት ዘይቱን በፌስታል አንጠልጥላ ትወጣለች።
ልጃቸው ወጥታም እማማ ተዋቡ ያወራሉ። ቤቱ ውስጥ ብቻቸውን ናቸው ግን ያወራሉ…ከራሳቸው ጋር፣ መልኳ ከጠፋው ኢትዮጵያ ጋር። ‹ሰው ሰው መሽተት አለብን። በኑሯችን፣ በተግባራችን ፈጣሪን ማስደሰት ሰውኛ ግዴታችን ነው። መልካችን የጠፋው፣ ኢትዮጵያዊነታችን ያደፈው ከሰውነት ስለሸሸን ነው። ሰው መሆን አለብን። ድሀን ማስጨነቅ እግዚአብሔርን ማስጨነቅ ነው። ልቦቻችንን ቸርነት፣ ነፍሶቻችንን ርህራሄ ማስተማር አለብን። ስለሌላው አእምሯችን በጎ ነገር እንዲያስብ ልናሰለጥነው ይገባል። እኔነት ኢትዮጵያዊ አይደለም። ፈጣሪ አምላክ ከነዛ ሁሉ ባለጸጋ መካከል ሳትሰስት ያላትን አንድ ሳንቲም የጣለችውን እመበለት ነው ሌማቷን በእንጀራ፣ ገንቦዋን በወይን፣ ቤቷን በበረከት የሞላው። እኛም እንድንባረክ ሰው መሆን አለብን…ሰው።
ነፃነት እናቷ እንዳዘዟት ለአራቱም ጎረቤቶቻቸው ዘይቱን አከፋፈለች። ይሄ ሲሆን ከነዛ ምንም ከሌላቸው ጎረቤቶቿ ብዙ ነገር አስተውላ ነበር። ሳቅ ስሜት ብቻ ይመስላት ነበር ግን ሳቅ ከስሜት ባለፈ ነፍስ እንዳለው ከነዛ ሰዎች አስተዋለች። ሳቅ በድሀ ሲሳቅና በባለጸጋ ሲሳቅ አንድ ዓይነት እንዳይደለ፣ የድሀ ነፍሶች የሚያደምጣቸው ቢያገኙ የሚናገሩት ብዙ የምንምነት ታሪክ እንዳላቸው ይሄን ሁሉ አስተዋለች። ሰው..ሰው የሚሸተው መቼ ነው ለሚለው የምንጊዜም ጥያቄዋ መልስ አገኘች..ለሌላው መኖር ሲችል ሲል። ከእያንዳንዳቸው ድሀ ጎረቤቶቿ ያየችውና የሰማችው የደስታ ልዕልና ነገዋን በመስጠትና ለሌሎች በመኖር አሻግራ እንድታይ አስገደዳት። ለካ ሰው በሰው ይኖራል፣ ለካ ነፍስ በነፍስ ሀሴት ታደርጋለች። ለካ ሀገር ማለት መተቃቀፍ ነው።
በመስጠት የናኘ ደስ ካላት ነፍስ አብራክ ውስጥ የሚነፍስ እግዚአብሔራዊ ንፋስ ሴትነቷን ተዋሃዳት። ከባለጸጎች ልቃ በእግዚአብሔር እንደተወደደችው እንደዛች ድሀ እመበለት ከእያንዳንዳቸው ሳቅ ውስጥ እየነፈሰ ወደ አያቷ የሚበን የብኩርና ወጀብ ታያት። አያቷና እኚህ አራት ጎረቤቶቿ ዛሬ ላይ መልኳ የጠፋው ኢትዮጵያን መሰለቻቸው። ብዙዎቻችን አምጠን ልንወልዳት የምንፈልጋት ኢትዮጵያ እኚህን ነፍሶች ናት። ኢትዮጵያ ማንን ትመስላለች ላላት የምትመልሰው መልስ አላት..አያቷንና እኚህን አራት ጎረቤቶቿን ስትል። መስጠት ሙላትን አይጠይቅም። መስጠት በጎ ህሊናን ብቻ ነው የሚሻው። አያቷ ኖሯት አይደለም የሰጠችው..ኢትዮጵያዊነት ያስተማራት ተካፍሎ የመብላት ባህል እንጂ። እኛም ሁላችንም የኢትዮጵያን መልክ ለመመለስ የራሳችንን መልክ መመለስ አለብን። ዘመናዊነት መስሎን ካጠፋነው እኛነታችን መታረቅ አለብን። ስልጣኔ መስሎን ካሸሸነው ባህልና ሥርዓት መወዳጀት አለብን። አራዳነት መስሎን ከተውነው የራስ እውነት መቅረብ አለብን። ኋላ ቀርነት መስሎን ከሰወርነው በአንድ መዐድ የመቋደስ ጥበብ መቀመጥ አለብን።
ሁሉም ሰው ሌላ ነው። አንዱ በሩን ዘግቶ የድሀውን ጩኸት ችላ ብሎ ዘመናዊነትን ለማምጣት ይታትራል። ሌላው ከኢትዮጵያዊነት ሸሽቶና አፈንግጦ፣ ድሀ እያስራበና እያስጨነቀ በራስ ወዳድነት ኪሱን ለማደለብ ይሯሯጣል። የተቀረው ጊዜና አጋጣሚዎችን እየጠበቀ በሌሎች ሞት፣ በሌሎች ስቃይ ቤቱን ይሠራል። ለራሱ እያሰበ፣ ለራሱ የሚኖርም ሞልቷል። እንደ አያቷ ዓይነት ጥቂት ነፍሶች ደግሞ ከራሳቸውም ከፈጣሪም ሳይሸሹ በምንምነት ውስጥ ታሪክ ይሠራሉ። ኢትዮጵያዊነትን ታቅፈው ለዛኛው ትውልድ ይንገዳገዳሉ።
ከተማው፣ መንገዱ አስገረማት። አገሩ፣ መንደሩ ደነቃት። ሁሉም ከአያቷ እውነት ውጪ ነው። ሁሉም ለራሱ የሚኖር ነው። ኢትዮጵያ ጠፋችባት..። ይሄ ሁሉ ሰው እንደ አያቷ ደግ ልብ ቢኖረው ኖሮ ይሄ ሁሉ ችግረኛ፣ ይሄ ሁሉ ርሀብተኛ ባልኖረ ነበር ስትል አሰበች። በደግነትና በመልካምነት የአያቷን ነፍስ ተጋርታ በቀሪ ዘመኗ ሁሉ የጠፋችውን ኢትዮጵያ ፈልጋ ለማግኘት ለራሷ ቃል ገባች።
ነገ እንደ አያቷ ሴት ከመሆን ውጪ አማራጭ የላትም። ነገ እንደ አያቷ ከማሰብ ውጪ እውቀት አይኖራትም። ነገ እንደ አያቷ በመስጠት ከመሰልጠን ሌላ ስልጣኔ አይኖራትም። ነገ ላይ እውቀትና ጥበቧ ሁሉ ከአያቷ ሀበሻነት ውስጥ የሚቀዳ ይሆናል።
ኢትዮጵያ ናፈቀቻት። ኢትዮጵያን ፈልጋ የምታገኛት በአያቷ ነፍስ ላይ ነው። ወደ ቤቷ ገሰገሰች..
አያቷ ትምህርት ቤቷ ናት..የእውቀት፣ የጥበብ እልፍኟ። አያቷ የስልጣኔ ደብሯ ናት..ሀበሻዊነትን ያጠናችበት።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን መጋቢት 8 ቀን 2015 ዓ.ም