ኢትዮጵያ የበርካታ ብሔረሰቦችና ቋንቋዎች ባለቤት የመሆኗን ያህል በውስጧ ለዘመናት በጠንካራ ማህበራዊ ትስስር የተጋመደ ሕዝብ ያለባት አገር ነች።ይህ ማህበራዊ ትስስርና ማህበራዊ የአኗኗር ዘይቤ ታዲያ ሕዝቡ ባህሉን፤ ወጉንና ልምዱን ጠብቆ ለማቆየት ካበረከተው ፋይዳ ባሻገር ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በመፍታት ረገድ ወሳኝ ሚና ሲጫወት ቆይቷል።
ማህበራዊ እሴቱን ጠብቀው ካቆዩና አሁንም ድረስ ማህበራዊ አደረጃጀቶችን ለትውልድ ጥቅም ካሻገሩ የኢትዮጵያ ሕዝቦች መካከል የሲዳማ ሕዝብ አንዱ ነው። በዛሬው የሀገርኛ አምዳችንም የዚህን ማህበረሰብ ማህበራዊ አደረጃጀትና ይህንን አደረጃጀት በመጠቀም የሚከናወነው ባህላዊ ቤት አሠራር ሥርዓትና የአኗኗር ዘይቤን ለመዳሰስ እንሞክራለን፡፡
የሲዳማ ብሔረሰብ አቋም እንደማንኛውም ኅብረተሰብ ጠንካራ ማህበራዊ መስተጋብር የሚታይበት ነው።በጣም ቀላል ካልሆነ በስተቀር ማንኛውንም ሥራ በህብረት ይሠራል።ቀላል ሥራ ቢሆን እንኳን ማህበረሰቡ ‹‹ዴ›› እያለ በሚጠራው በደቦ ሥርዓት አማካኝነት ነው የሚሠራው። አቶ ከቤታና ሆጤሶ የተባሉ ጸሐፊ ‹‹የሲዳማ ሕዝብና ባሕሉ›› በሚል ርዕስ 1983 ዓ.ም ላይ ባሳተሙት መጽሐፋቸው ላይ እንደገለፁት፤ ‹‹ዴ›› ማለት በዘመዳሞች ወይም በጓደኛሞች ማለትም በቅርበት ከሚተዋወቁት መካከል በደቦ፤ በፈቃደኝነትና በፍቅር የሚሠራ ሥራ ነው። በ‹‹ዴ›› የሚሠራው ሥራ ዓይነት ቁፋሮ፣ አረማ፣ ዘር መዝራትና አጨዳ የመሳሰሉት ናቸው።ከዚህ ከፍ የሚሉ ድርጅቶች ግን በ‹‹ሴራ›› (በሕግ) የሚቋቋሙ ሲሆን ‹‹ጭናንቾ›› እየተባለ በሚጠራው ጎጥ እና ‹‹ኦላ›› በተባለው የቀበሌ አደረጃጀት የሚደራጁ ናቸው።
ጭናንቾ
በሲዳምኛ ‹‹ሴራ›› ማለት ሕግ ማለት እንደሆነ የሚጠቅሱት ጸሐፊው፤ በአንፃሩ እነዚህ ‹‹ጭናንቾ›› በመጠን ከኦላ ያነሰ ንዑስ ማህበራዊ አደረጃጀት መሆኑን እንዲሁም ‹‹ኦላ›› በስፋቱ ከፍ ያለና የቀበሌን ያህል በቁጥር ከፍ ያለ ሕዝብ ወይም አካባቢን የሚያካትት ማህበራዊ አደረጃጀት መሆኑን ያብራራሉ። ሁለቱም አደረጃጀቶች ግን በኅብረተሰቡ ሕግ መሠረት የተደራጁ ስለሆኑ በአካባቢው የሚገኝ ለአቅመ-አዳም የደረሰ ወንድ ሁሉ በእነዚህ ድርጅቶች በግድ መካፈል የሚኖርበት መሆኑን ያስረዳሉ። ‹‹የጭናንቾ›› ተግባር ቤቶችን (መኖሪያ ቤቶች) መሥራት መሆኑን ገልፀውም፤ ‹‹በዚህ ድርጅት ውስጥ የሚገኝ ማንኛውም አባል ቤቱ ቢበላሽበት ለማሠራት ሙሉ መብት አለው፤ ለዚህ ደግሞ ድርጅቱን የሚመሩ ሁለት ሰዎች ይኖራሉ›› ይላሉ። መሪዎቹም በሲዳምኛ ‹‹ሙርቻ›› የሚባሉ መሆኑን አመልክተው እነርሱም ሙሉ አባላት ባሉበት ዋና እና ረዳት በመሆን በድምፅ ብልጫ የሚመረጡበት ሥርዓት መኖሩን ያብራራሉ።
እንደእርሳቸው ገለጻ፤ ቤት ለመስራት የሚፈልግ ሰው ሄዶ ለ‹‹ሙርቻ›› ዎቹ (ለመሪዎቹ) ይነግራል።እነርሱም ለመላው አባላት ያስታውቃሉ።ሕዝቡም ውጣ በተባለው ቀን ወጥቶ ቤቱን ሠርቶ ለባለቤቱ ያስረክባል።ለሥራ በሚወጡበት ጊዜ በታዘዙበት መሠረት ጥቂት ጠርብና ማገር ይዘው ያመጣሉ። ቤት ለማሠራት ቀደም ብሎ ለጠየቀው ሰው መጀመሪያ ይሠራለታል።ቤቱ ሲሠራ ‹‹ሙርቻ›› በደንብ ይቆጣጠራል።ሥራው ሲበላሽ አፍርሶ እንደገና እንዲሠራ ያደርጋል። የማይታዘዝ ሰው ቢኖር በደንቡ መሠረት ይቀጣል። ቅጣቱም የሚወሰነው በሙርቻና በሽማግሌ ነው። የተወሰነበትን ቅጣት የማይቀበል ሆኖ ቢገኝ ለመላው የድርጅቱ አባላት ፊት ቀርቦ የተጣለበት መቀጫ ትክክል ከሆነ እንዲከፈል ይገደዳል።ይህንን የማይፈፅም ከሆነ ከድርጅቱ እንዲወገድ ይሆናል። ማንም ሰው ከድርጅቱ ወደተወገደው ሰው ቤት አይገባም፤ ከማንም ጋር ቡና ሊጠጣ አይችልም።ቢታመም እንኳን የሚጠይቀው ሰው የለም።ቢቸገር የሚደርስለት ሰው አይኖርም፣ ከእቤት እሳት ቢጠፋ ከአካባቢው እሳት ሊወስድ አይችልም።ክብሪት በሌለበት ዘመን ከጎረቤት እሳት ማጣት ምንኛ ከባድ እንደሆነ ለመገመት አያዳግትም።
ሌላው ይቅርና የተጣለበትን መቀጫ ሳይከፍል ይህ ድርጅት (ጭናንቾ ወይም ኦላ) በድሎኛል ብሎ በሌላ ድርጅት ውስጥ ሄዶ እንዲገባ የማይፈቀድለት መሆኑን ጸሐፊው ይገልፃሉ። ድርጅቱን ለቆ ለመውጣት ቢፈልግ መጀመሪያ የተጣለበትን መቀጫ መክፈል የሚጠበቅበት መሆኑን ይጠቁማሉ። በድርጅቱ ውስጥ ያሉት ሽማግሌዎች የጉልበት ሥራ የማይሳተፉ መሆኑን፤ ሆኖም በበሩ ዙሪያ ያለው ሥራ ብልሃትና ልምድ የማይጠይቅ ስለሆነ ያንን የሚሠሩት ሽማግሌዎች መሆናቸውን ያስረዳሉ። ከዚህም ሌላ ሽማግሌዎች የማስተባበር፣ የማስማማት፤ የመምከር ኃላፊነት ያላቸው በመሆኑ ለቤት ሥራው ስኬት የሚጫወቱት ሚና ቀላል አለመሆኑን አስገንዝበዋል።
እንደ አቶ ከቤታና ገለፃ፤ በሲዳማ ባህል መሠረት ሽማግሌዎች ትልቅ ክብርና ተሰሚነት ስለአላቸው ‹‹ለሙርቻ›› (መሪዎች) ጭምር የሥራ አመራር ስልትና ምክር ይሰጣሉ። በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ሽማግሌዎች ‹‹ጭሜሳ›› የሚባሉ በዕድሜ ወይም በ‹‹ሉዋ›› ታላቅ የሆኑ ሰዎች ናቸው። ‹‹ሙርቻ›› ግን የሥራ ችሎታና ጠባዩን አይተው አባላት የሚመርጡት ሰው ነው።አንድ ቤት ሠርቶ ለመጨረስ ከሦስት ሳምንት እስከ ሁለት ወር ይወሰዳል። በዚህ ረዥም ጊዜ ውስጥ ምግብና ቡና ለሠራተኞቹ የሚያቀርበው ባለቤቱ ራሱ ነው።ሆኖም ጓደኞቹ ይረዱታል።በተለይም የሚስቱ ጓደኞች የሆኑ ሴቶች በዚህ ዕለት ‹‹እኔ ስለምረዳሽ ምግብ አታሰናጂ›› ብለዋት ለሴትየዋ ይነግሯታል። በተባለው ቀን እነርሱ ያቀርባሉ። በዚህ ዓይነት የሚቀርበው ምግብ ‹‹ካአጡ›› ይባላል። እንዲህ ላደረጉ ሰዎች (ሴቶች) ቤት በሚሠራበት ጊዜ ውለታ ይመለስላቸዋል። ቤት ተሠርቶ በሚያልቅበት ጊዜ ከብት ታርዶ ግብዣ ይደረጋል፡፡
ስለሆነም ወንዶቹ የቤቱን ሥራ በሚጀምሩበት ጊዜ ሴቶቹ ደግሞ በበኩላቸው ሴቷን ለመርዳት በአንድ ላይ ተሰባስበው ምግብ ማዘጋጀት ይጀምራሉ።የአካባቢው ዋና ምግብ የሆነውና ከእንሰት የሚሰራው ‹‹‹ዋሳ›› (ቆጮ) ብዙ ሥራ የሚጠይቅ በመሆኑ ሴቶች በተቻላቸው መጠን ሥራውን ቀደም ብለው ይጀምራሉ።አሮጊቶቹም በቦታው ተገኝተው ቀለል ያለ ሥራ የሚያከናውኑ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሆኖም የአሮጊቶቹ ሥራ ከሽማ ግሌዎቹ ጋር ሲነፃፀር የሽማግሌዎቹ ከባድ ነው። ይሁንና በሲዳማ ማህበረሰብ ከወንዶቹ መካከል ሽማግሌዎች እንደሚከበሩ ሁሉ ከሴቶች በኩልም አሮጊቶቹ የሚከበሩ ናቸው። በሲዳምኛ ቋንቋ ሽማግሌዎች ‹‹ጭሜሳ›› አሮጊቶቹ ደግሞ ‹‹ቃርቾ›› የሚል መጠሪያ አላቸው።
‹‹ቤት በሚሠራበት ጊዜ ሴቶቹ ‹‹ሐኖ›› የተባለውን ዘፈን ይዘፍናሉ። ወንዶቹ ደግሞ ‹‹ዌዶ›› የተባለውን ጨዋታ ይጫወታሉ››። ቤቱ ተሠርቶ ሲያልቅ ደግሞ ትልቅ ግብዣ የሚደረግ ሲሆን፤ የዚያኑ ዕለት ማታ ወጣቶቹ ተሰብስበው ‹‹ፋኖ›› የተባለውን ዘፈን እየዘፈኑ ሌሊቱን በሙሉ ያነጋሉ።ለግብዣው ከታረደው ሥጋ መካከል ወርችና ጎድን (ሃዬና ሜጣቄ) ለሴቶች የሚሰጥ ሲሆን፤ የቤቱ ሥራ ከተፈፀመ በኋላ የሚደረገው ግብዣ ደግሞ ‹‹ኢማኔ›› እየተባለ ይጠራል።ቤት ሥራ ለመጀመር ማለትም መሠረት (ጋታ) ለመጣልም ሆነ ‹‹ኢማኔ›› (የቤት ምርቃት) ለማድረግ ወደ ከዋክብት ቆጣሪዎች ዘንድ በመሄድ መልካም ቀን ይመረጣል፤ ‹‹አያንቶ›› በሚነግሩት ቀን ድርጊቱ የሚፈፀም ይሆናል።
ኦላ
እንደ አቶ ከቤታና ገለጻ፤ ከሦስት እስከ ሰባት ያሉ ጭናንቾች (ጎጦች) በመሰብሰብ አላ የተባለውን ድርጅት ያቋቁማሉ። ለዚህ ድርጅትም ሙርቻዎች ይኖሩታል። የአመራረጡ ሁኔታ ከጭናንቶች ጋር አንድ ነው። ዋናውና ምክትል (ላይንክ) ‹‹ሙርቻ›› የሚመረጡት በመላው ‹‹ኦላ›› ሲሆን ለየ‹‹ጭኛኝቶች››ም አንድ ተጠሪ ይኖራል። የዚህ ድርጅት ዋና አገልግሎት ለቀብር ለለቅሶ፣ ጥል በማስወገድ ሰላም መፍጠር፣ መስዋት ማቅረብ፤ ሸንጎ መሰብሰብ እና የመሳሰሉት ናቸው። ኦላም ለአባላት ቤት ይሠራል። ሆኖም ለግብዣ ብዙ ወጪ ስለሚጠይቅ በኦላ ቤት ለመሥራት የሚደፍሩ ሰዎች በጣም ጥቂት (ሀብታሞች) ናቸው። አንድ ሰው ከፍተኛ ጉዳት ቢኖረውም ኦላ እንዲሰበሰብለት ለሙርቻ (መሪዎች) ሄዶ ይነግራል። ሙርቻም ለየጭናንቾ ተጠሪዎች ይነግራል። ተጠሪዎቹም ለየአባላቱ ትዕዛዝ ያስተላልፋሉ፤ አባሎቹም በተባለው ቀንና ሰዓት ወደተጠሩበት ቦታ በመሄድ የተነገራቸውን ጉዳይ ያከናውናሉ።በ ‹‹ኦላ›› ውስጥ ያለው ድርጅታዊም ሆነ አስተዳደራዊ ሁኔታ ከጭናንቾ ጋር አንድ ዓይነት ነው።
ቤት ለመሥራት ሕዝብ የሚገለገልባቸው ዕቃዎች በአካባቢው ከሚገኙ ሀብቶች (ደን) መሆኑን ጸሐፊው ያመለክታሉ። በዚህ መሠረት የደጋው ቤት የሚሠራው በአካባቢው ከሚገኙ እንጨቶች መሆኑን ጠቅሰው፤ በመሆኑም ቤት ለመሥራት የሚያስፈልጉ ዕቃዎች በመጀመሪያ ከተሰበሰቡ በኋላ ጥሩ ቀን ከ‹‹አያንቶ›› (ኮከብ ቆጣሪዎች ወይም ቀን ተንባዮች) የሚጠየቁበት ሂደት መኖሩን ጸሐፊው ያብራራሉ። ‹‹በዚያች ‹‹አያንቶ›› በሚነግሩት ቀን ቤት የሚሠሩ ሰዎች በቦታው ይገኛሉ፤ ሰውዬው አካባቢውን ከአሳየ በኋላ ትክክለኛ ቦታ (ሳይት) በሰዎቹ ይመረጣል›› ይላሉ። የቤቱን መሠረት የሚጥለው ባለቤቱ ወይንም የአካባቢው ‹‹ጭሜሳ›› ሊሆን እንደሚችልና ከዚያም በተመረጠው ሥፍራ በመሀከሉ ላይ አንድ ‹‹ሂልቾ›› ቀጭን አጠና ወይንም ዱላ የሚተከል መሆኑን ያስረዳሉ።
እንደእርሳቸው ማብራሪያ፤ ቤቱ ሲሠራ ‹‹ሂሊቾ›› (ምሰሶ) የሚቆምበት ሲሆን በዚህ ዱላ ላይ በክንድ (ጭጊሌ) ወይንም በጫማ ‹‹ሃርኡማ›› የተለካ ‹‹ጡሾ›› (ገመድ) ያስሩና ርቀቱ በርሱ እየተለካ ዙሪያው ‹‹ጋታ›› ይቆፈራል። በዚህ ዓይነት መሠረት ሲቆፈር፣ ከምሰሶ እስከ ግድግዳ ያለው ርቀት ሲለካ በሁሉም አቅጣጫ እኩል ይሆናል። ስለሆነም ቤቱ ሲሠራ ፍጹም የሆነ ክብ ቅርጽ ይኖረዋል። በዚህ ዓይነት መሠረቱ ከተቆፈረ በኋላ ቁመታቸው እኩል የሆነ ጠርብ ‹‹ጣራ›› ወይንም ‹‹ኩሩሜ›› የሚባል ይተካል። ይህም እንዳይናጋ በትክክል ተይዘው አፈር ይመለሳል። ከዚያም ቀደም ባለጊዜ በሌላ ቦታ ተሠርቶ የቆየውን ለወደፊት የቤቱ ጣሪያ የሚሆነውን ‹‹ቃልቾ›› (ጣሪያው ላይ የሚታሰር ርብራብ) ያመጡና በቤቱ መሃል ያኖሩታል። በ‹‹ቃልቾ›› መሀል ወይም ጫፍ ላይ ጠባብ የሆነ ቀዳዳ አለው። በዚህ ቀዳዳ ነው ቤቱ ተሠርቶ ሲያልቅ የሚገባው የምሰሶው ጫፍ ብቅ የሚለው፡፡
‹‹እንግዲህ በተተከለው ጠርብ ላይ ተደርበው ‹‹ሕሎ›› የተባሉት ቀጫጭን አጠናዎች ይተከላሉ።አሁን በግድግዳው ላይ ከውስጥና ከውጭ አጠናዎችን እያጋደሙ ሁለት ጠንካራ ‹‹ዳጋሌ›› ማገር ይሠራል።ማገሩ የሚታሰረው በጣም ጠንካራ በሆነ ‹‹ዲኪቻ›› በሚባለው ሐረግ ነው›› ይላሉ። ይህም ተሠርቶ ካለቀ በኋላ በመሀል ላይ ያለው ‹‹ቃልቾ›› በጊዜያዊ ምሰሶ ላይ የሚሰቀል መሆኑና በመቀጠልም በቃልቾው ላይ ያለው ‹‹ሄርቾ›› (ጣሪያው ላይ የሚታሰር እንጨት) ላይ እየቀጣጠሉ ተብትበው የሚሠሩበት ሂደት መኖሩን ነው ያስገነዘቡት፡፡
ስለዚህ ከላይ የተሰቀለው ቃልቾ በዚህ ዓይነት ወደታች እያደገ ይመጣና ከጠርቡ ጋር ከተተከለው ሕሎ (አጠናዎች) ጋር የማገናኘት ሥራ እንደሚሠራ አቶ ከቤታና ጠቁመው፤ እነዚህ አጠናዎች እየተሳቡ ከላይ ከመጣው ‹‹ሄርቾ›› ጋር በማሰር ቤቱ በጣም እንዲወጠር የሚደረግ መሆኑን ያስረዳሉ። በዚህ ዓይነት ተሠርቶ ሲጠናቀቅ እንደ አካባቢው ሁኔታ ማለትም ደጋ ከሆነ በሆንጮ (የቀርካሃ አቃፊ) በሌላ አካባቢ ከሆነ ግን ደግሞ በ‹‹ቡዮ›› ለቤት ኪዳን ተብሎ የሚያድግና ከሌላው ለየት ያለ ሣር የሚከደንበት የአሠራር ሂደት መኖሩን ያብራራሉ። በመጨረሻም ቤቱ ተሠርቶ ሲጠናቀቅ ግለሰቡ ከ‹‹አያንቶ›› ጥሩ ቀን ጠይቆ ወደ ቤቱ የሚገባ መሆኑን ነው የጠቆሙት፡፡
እንደፀሐፊው ማብራሪያ፤ ቤቱ ‹‹ኦልእዶ›› እና ‹‹ሃድሮ›› ተብሎ ለሁለት ይከፈላል። አልእዶ የሰው መኖሪያ ሲሆን በስፋት ከ‹‹ሃድሮ›› ይበልጣል። ‹‹ሃድሮ›› ወይም ጋጣ የከብት መኖሪያ ይሆናል።‹‹ኦልእዶ›› እንዲሁም ‹‹ዱኡኮ›› (መጋረጃ) በመባል የሚታወቀው ግድግዳ ለሁለት ይከፈላል። ይህ ግድግዳ በደጋው አካባቢ ቀጭን ሆነው በተሰነጠቀና ጥልፍ በሚመስል ቀርከሃ ስለሚሠራ በጣም ያምራል። በሌላው አካባቢ ግን በአካባቢው በሚገኝ እንጨት ይሠራል።ሆኖም ሀብታሞቹ ከደጋ ቀርከሃ አስመጥተው ነው የሚሠሩት። ምክንያቱም የደጋው ቀርከሃ የተሠራው ትልቅ ክብር የሚሰጠው በመሆኑ ነው። የባልና የሚስት መኝታ እዚያው ውስጥ ይሆናል።በአካባቢው ማህበረሰብ ‹‹ቦሣሎ›› (ሳሎን) እየተባለ የሚጠራው ክፍል ደግሞ የልጆች መኖሪያ ሲሆን፣ ቀላል ዕቃዎችና የምርት መሣሪያዎች ይቀመጣሉ።እንግዳ ሲመጣም ጊዜያዊ መኝታ ተዘጋጅቶለት በዚህ ክፍል ያድራል።
ጸሐፊው ርዕሰ ጉዳያቸውን ሲደመድሙም የሲዳማ ሕዝብ ካሉት ጥንታዊ እሴቶች መካከል ይህ ቤትን በደቦ የመሥራት ባህል ዋነኛው መሆኑን፤ ለዘመናትም ከትውልድ ትውልድ በመሻገር ለማህበረሰቡ ከፍተኛ ጠቀሜታ ሲያበረክት መቆየቱን አስገንዝበዋል። በተለይም በደቦ በመሥራት ሂደት የሕዝቡን ማህበራዊ ትስስር ከማጠናከሩም ባሻገር አቅም የሌላቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች በማገዝ ከስጋትና ችግር በመገላገል ረገድ አወንታዊ ሚና ሲጫወት መቆየቱን አስረድተዋል።
ይህ ከፍተኛ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያለው እሴት ታዲያ አሁን አሁን በተወሰነ ደረጃ እየተሸረሸረ መምጣቱን የአካባቢው ተወላጆች ይናገራሉ። በተለይም ባህላዊ የቤት አሠራር ወደ ዘመናዊ (ቆርቆሮ) ቤት አሠራር እየተተካ በመምጣቱ ሁሉም በተናጠል ቤቱን ከፍሎ እንደሚያሠራ ይጠቁማሉ። ይህ ደግሞ ባህላዊውን ዘዴ እንዲረሳ ከማድረጉም ባሻገር አቅምንም የሚፈታተን፤ ወጪንም የሚጨምር መሆኑን ያስረዳሉ። ከሁሉ በላይ የመረዳዳትና በጋራ ተሳስቦ የመኖር ባህሉን እየሸረሸረ በመሆኑ የሚመለከታቸው አካላት ለዚህ መልካም እሴት ዳግሞ ማበብ የበኩላቸውን ርብርብ ማድረግ ይገባቸዋል።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን መጋቢት 8 ቀን 2015 ዓ.ም